የዓይን ጤናን በምግብ

Wednesday, 09 May 2018 13:21

 

ጤናማ አይን ነገሮችን አጣርቶ ከማየትም ያለፈ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። አይን የሰውነትን ሚዛን ለመጠበቅ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ጀምሮ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ምንም እንኳን ለአይናችን ያለን ግምት ከፍተኛ ቢሆንም የምናደርግለት እንክብካቤ ግን እስከዚህም ነው። በተለይ የምንመገባቸው ምግቦች የአይናችንን ጤንነት ያገናዘቡ አይደሉም። በዚህም የተነሳ በቀላሉ መከላከል ሲቻል ለተለያዩ ችግሮች ስንጋለጥ ይታያል። በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ዊልመር አይ ኢንስቲቲዩት በዶክተር በማርክ ቲሶ እንዲሁም በኤሊኖይስ ዩኒቨርስቲ የአይን ባንክ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የምግብ አይነቶች የአይንን ጤንነት ለመጠበቅ የሚመከሩ ናቸው። በተለይ እንደ ስኳር ህመም እና ሌሎች ተያያዥ ለአይን ችግር አጋላጭ የሆኑ ችግሮች ያሉባቸው ሰዎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገቡ ጥናቶቹ ጠቁመዋል።

ቲማቲም

ቲማቲም ያለውን ቀለም እንዲኖረው የሚያደርግ እና ላይኮፒን የተባለ ማቅለሚያ አለው። ይህ ማቅለሚያም አይናችንን ከጎጂ ጨረሮች የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ከጸሐይ የሚለቀቁ እና እንደ አልትራ ቫዬት ካሉ ጨረሮች አይናችንን በመጠበቅ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የአይን ጡንቻዎች መጎዳት እና ማርጀት ለመከላከል ይጠቅማል። ሌላው በቲማቲም ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ደግሞ ቫይታሚን ኤ ነው። ይህ ቫይታሚን ኤ የአይናችን እይታ ጠንካራ እንዲሆን እንዲሁም ኮርኒያ የተባለው የአይናችን የውጪኛው ክፍል ጤናማ እንዲሆን ያደርጋል። በቲማቲም ውስጥ በብዛት የሚገኘው ከፍተኛ የቫይታን ሲ መጠንም ሌላው ለአይን ጤንነት ጠቃሚ ንጥረ ነገር ነው። ይህን ንጥረ ነገር በብዛት የተመገቡ ሰዎች እንደ ሞራ ግርዶሽ ላሉ የአይን ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ነው።

ለውዝ

ለውዝ አጠቃላይ ጤንነትን ለመጠበቅ ከሚያግዙ ተፈጥሯዊ ምግቦች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ምግብ በቫይታሚን ኢ የበለፀገ በመሆኑ፣ ይህ ንጥረ ነገርም አደገኛ የሆኑ አንቲኦክሲደንቶችን የመከላከል ጠቀሜታ አለው። በዚህ ጠቀሜታውም የአይናችንን የተወሰኑ ክፍሎ ከተለያዩ ጨረሮች የመከላከል ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለውዝ ኦሜጋ 3 የተባለ ፋቲ አሲድ ይዘቱ ከፍተኛ ነው። ይህ ፋቲ አሲድ ደግሞ እይታ ጤናማ እንዲሆን እንዲሁም በአይናችን ላይ የሚኖረው ግፊት የተስተካከለ እንዲሆን ያግዘዋል። በዚህም በአይናችን ላይ የሚኖረው ግፊት ሃይለኛ ሲሆን የሚከሰተውን እንደግላኮማ ያለ አይነስውርነትን ለመከላከል ያግዛል። በተጨማሪም ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የአይን ጡንቻዎች መዛል በማስቀረት ለአይነ ስውርነት ያለንን ተጋላጭነት ያስቀራል።

እንቁላል

በእንቁላል ውስጥ ሉቴን እና ዚያንቲን የተባሉ ሁለት ወሳኝ አንቲኦክሲደንቶች ይገኛሉ። እነዚህ ሁለት አንቲኦክሲደንቶችም ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የአይን ጡንቻ መዛል እና የአይን ሞራ ግርዶሽን በመከላከል ረገድ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ በበኩሉ ግላኮማ የተባው የአይንት እይታ መዛባትን ይከላከላል። ይህ ግለኮማ የሚባለው የአይን እይታ መዛባት የአይን ነርቮችን የመጉዳት ችግር የሚፈጥር ሲሆን፣ በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ግን በአይን ብሌን ላይ የሚኖረውን ግፊት በማስተካከል ችግሩን ለመከላከል ያግዛል።

ሌላው በእንቁላል ውስጥ በብዛት የሚገኘው ዚንክ ማዕድን ነው። ይህ ማዕድንም በሰውነት ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ኤ፤ ሜላኒን የተባለውን ማቅለሚያ እንዲያመርት ያደርገዋል። ይህ ማቅለሚያም የአይናችን እይታ የተስተካከለ እንዲሆን እንዲሁም የአይን ግፊት ከመጠን በላይ እንዳይሆን ያግዘዋል። በተጨማሪም እድሜ እየገፋ በሄደ ጊዜ የሚከሰተውን የእይታ መደብዘዝ ለማስቀረት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

ካሮት

ካሮት ቤታ ካሮቲን በተባለ ማቅለሚያ የበለፀገ የስር ምግብ አይነት ነው። በካሮት ውስጥ በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የቫይታሚን ኤ ክምችት ይገኛል። ይህ ማቅለሚያ እና ቫይታሚን ኤ ኮርኒያ የተባለው የአይናችን ክፍል ጤናማ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ሌላው በካሮት ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ሉቴን ሲሆን፤ ይህ ንጥረ ነገርም ልክ እንደ ቫይታሚን ኤ ሁሉ በአይን ላይ የሚደርሰን የእይታ መዛባት ለመከላከል ያግዛል። በተጨማሪም የአይን መድረቅን እና ከፍተኛ ግፊትን በመከላከል በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚከሰተውን አይነስውርነት ለመከላከል ያግዛል።

አረንጓዴ አትክልቶች

አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ቅጠላማ አትክልቶች በዋናነት የሉቴን እና ዚያንቲን አንቲኦክሲደንቶች ምንጭ ናቸው። እነዚህ ንጥረ ነገሮችም ከብርሀን የሚመነጩ ጨረሮች ሬቲና በተባለው የአይን ክፍል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ይጠቅማል። በተጨማሪም በእነዚህ አትክልቶች ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች የአይናችን የመኮማተር እና የመላላት ሂደት ተፈጥሯዊ እና ጤናማ እንዲሆን ያግዘዋል።

ጠቆር ያለ ቀለም ያላቸው የአትክልት ዝርያዎች ቤታ ኬሮቲን የተባለው ማቅለሚያ ይዘታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በሰውነታችን ውስጥ ሲገቡም ወደ ቫይታሚን ኤ ይቀይረዋል። ይሄ ቫይታሚን ኤ የአይናችን እይታው ጤናማ እንዲሆን፣ እና እንዳይደርቅ ይከላከልለታል። የአይን ድርቀት በሚከሰትበት ወቅት ኢንፌክሽን በመፈጠር የእይታ ብዥታ እንዲፈጠር ያደርጋል። ሌላው በአረንጓዴ አትክልቶች ውስጥ የሚገኘው የቫይታሚን አይነት ቫይታሚን ኢ ነው። ይህ ቫይታን አይን የፕሮቲን ክምችቱ በመብዛት በተለምዶ የሞራ ግርዶሽ ለተባለው ችግር እንዳይጋለጥ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም በእነዚህ ቅጠላማ አትክልቶች ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የሆነ የዚንክ ማዕድን ክምችት ሜላኒን የተባለው ማቀለሚያ በብዛት እንዲመረት በማድረግ ከእድሜ ቀደም ብሎ የሚከሰተውን የአይን ጡንቻ መጎዳት ለማስቀረት ያግዛል።

አሳ

በዓሳ ውስጥ በብዛት ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱና ከፍተኛ መጠን ያለው ኦሜጋ 3 የተባለው ፋቲ አሲድ ነው። ይህ ፋቲ አሲድ አይናችን እንዳይደርቅ እና በቂ እምባ እና ማለስለሻ እንዲያመነጭ ያግዘዋል። በተጨማሪም ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአይን ጡንቻ መድከምን ለመከላከል ያግዛል። በአሳ ውስጥ የሚገኘው የቫይታሚን ዲ መጠንም ከፍተኛ ነው። ይህ የቫይታሚን አይነትም ሬቲና በተባለው የአይን ክፍል ላይ የሚደርሰውን ኢንፍላሜሽን በመከላከል እና የጠራ እይታ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

እንጆሪ

የተለያየ ቀለም ያላቸው የእንጆሪ ዝርያዎች ጥሩ የሆነ አንቲኦክሲደንት እና ቫይታሚን ሲ ምንጮች ናቸው። እነዚህ ኢንቲኦክሲደንቶችም አይንን ከጉዳት አምጪ ፍሪራዲካልስ የመከላከል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ቫይታሚን ሲ ደግሞ እንደ ግላኮማ፣ የአይን ሞራ ግርዶሽ እንዲሁም የአይን ጡንቻ ያለጊዜው መጎዳትን ለመከላከል ያግዛል። ሰሚያዊ ቀለም ያላቸው እና ጠቆር ያሉ የእንጆሪ ዝርያዎችም ሰማያዊ ቀለሞችን የማጣራት ተግባርን ስለሚያከናውኑ ሬቲና በተባለው የአይን ክፍል ላይ በብርሃን ሳቢያ የሚደርስ ጉዳትን የማስቀረት ጠቀሜታ አላቸው። በተጨማሪም በእንጆሪ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በአይናችን አካባቢ ያለው የደም ዝውውር የተስተካከለ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም በምሽት ወቅት የሚፈጠረውን የእይታ ብዥታ ለመከላከል እንዲሁም ቫይታሚን ኤ ከተለያዩ ኢንፍላሜሽኖች (መቆጣት) ለመከላከል ያግዛል።

በአጠቃላይ በቫይታሚን ኤ፣ ኢ እና ዲ የበለፀጉ የእህል ዝርያዎች፣ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው የአትክልት ዝርያዎች እንዲሁም የአሳ ዘሮች የአይንን ጤንነት በመጠበቅ ረገድ ወደር የማይገኝላቸው ናቸው። እነዚህ የተፈጥሮ ምግቦችም አይናችን የጠራ እይታ እንዲኖረው በማድረግ፣ ከእድሜ ቀድሞ የሚከሰትን የአይን ጡንቻ መዛል ለመከላከል እንዲሁም በንጥረ ነገሮች እጥረት ሳቢያ ለሚከሰቱ የእይታ ብዥታ፣ የእይታ መስተጓጎል እንዲሁም የግላኮማ ችግረ ለመከላከል ያግዛል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች እድሜ እየጨመረ ሲሄድ ለአይነ ስውርነት የማጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ በእነዚህ ነገሮች መከላከል ይቻላል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
581 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1022 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us