ኦቲዝምና ተያያዥ ችግሮቹ

Wednesday, 16 May 2018 13:28

ሚያዝያ ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦቲዝም ግንዛቤ ወር ተብሎ ይከበራል። ዘንድሮም ወሩ በተለያዩ መንገዶች በተካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች ተከብሯል። የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን አስመልክቶ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎችን የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ግልፅ እና ሰፋፊ ስለኦቲዝም የሚያወሱ ጥናቶችንና መረጃዎችን ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ከእነዚህ ተቋማት መካከልም ኦቲዝም ስፒክስ የተባለው ኦቲዝም ትሪትመንት ኔትዎርክ ኦቲዝም ያለባቸውን ሰዎች በተጓዳኝነት ሊያጠቋቸው የሚችሉ የጤና እክሎችን ጥናት አጣቅሶ አስነብቧል። የኔትዎርኩ መረጃ እንደሚለው እነዚህ ተያያዥ የጤና እክሎች ኦቲዝም ያለባቸውን ሰዎች ህይወት የባሰ ፈታኝ የማድረግ እና የማክበድ ባህሪይ አላቸው። በመሆኑም ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች፣ ወላጆች፣ ቤተሰቦች እና ተንከባካቢዎች እነዚህ ተጓዳኝ ችግሮች መኖራቸውን ተረድተው በየእለት ተግባራቸው ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ያስፈልጋል።

 

ኦቲዝም ያለባቸውን ሰዎች ከማህበረሰቡ ጋር አቀላቅሎ ለማኖር በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ብዙም ድፍረቱ የሌላቸው ሲሆን፤ ችግሩን እንደፈጣሪ ቁጣ በመቁጠር ከማህበረሰቡ ያገሏቸዋል። በዚህም ሳቢያ ቀደም ብለው ችግሩን ተገንዝበው መፍትሔ አያፈላልጉም። ነገር ግን ቀደም ብሎ ቢታወቅ ህፃናቱ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችና አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን እንዲለማመዱ መርዳት ይቻላል።


ኦቲዝም ዘር ቀለም እና ሌሎች ልዩነቶችን መሠረት ሳያደርግ ህፃናትን የሚያጠቃ የአእምሮ እድገት መዛባት ነው። ይህ ችግር ከሴቶች ይልቅ ወንድ ህጻናትን የማጥቃት እድሉ በአራት እጥፍ የጨመረ ነው። ብዙውን ጊዜ የኦቲዝም ችግር መኖር አለመኖሩ ከሁለት ዓመት እድሜ ጀምሮ የሚታወቅ ቢሆንም በአንዳንድ ህጻናት ላይ ግን ከዚህ እድሜ ቀደም ብሎ የሚታይበት ጊዜም አለ። ይህን የአእምሮ እድገት መዛባት የሚያመጡት ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ከመላ ምት የዘለለ ማስረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ነው ባለሞያዎች የሚገልፁት። በመላ ምት ከተቀመጡት ምክንያቶች መካከል የዘር ግንድ፣ አእምሮ በለጋነት እድሜው የሚኖረው ብልፅግና መጠን እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖ ተጠቃሾች ናቸው። የችግሩ ምክንያቶች አለመታወቃቸውም ችግሩን አክሞ ለማዳን የሚደረገውን ጥረት ከባድ አድርጎታል። ነገር ግን ችግሩን ቀደም ብሎ በመለየት በተለያዩ መንገዶች ህፃናቱን መርዳት እና ቀሪው ህይወታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።


ኦቲዝም ያለባቸው ህፃናት መገለጫ ከሆኑት ባህሪያት ዋና ዋናዎቹ በንግግር ለመግባባት አለመቻል፣ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ መኖር አለመቻል እና ብቸኝነትን መምረጥ በአንድ ነገር ላይ ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ፍላጎትን ማሳየት ናቸው። እነዚህ ምልክቶች የአብዛኞቹ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ህጻናት መገለጫዎች ሲሆኑ፣ የተወሰኑት ህፃናትም ከእነዚህ ምልክቶች በተጨማሪ አንድ ልጅ ለነገሮች አለመጓጓት፣ ቀና ብሎ ሰውን ለማየት አለመድፈር እና አንድ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር የመሳሰሉ ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ። ከዚህ በተቃራኒው ግን ኦቲዝም ያለባቸው አንዳንድ ህፃናት ከሌሎች ሰዎች የበለጠ የላቀ አእምሮ እና ክህሎት ያላቸው ናቸው።


ሌላው ከዚህ ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ አሳሳቢው ነገር ከኦቲዝም ጋር ተያያዥ የሆኑ የአእምሮ እና የሌላ ሰውነት ክፍል ጤና መዛባቶች ናቸው። ኦቲዝም ስፒክስ ይሄንን ጉዳይ በተመለከተም በኦቲዝም የተጠቁ ህጻናት ወላጆችና ተንከባካቢዎች መርሳት የሌለባቸው ተያያዥ ችግሮች በዝርዝር አስቀምጧል።


የመጀመሪያው ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአእምሮ ጤና መዛባት የሚጥል በሽታ ነው። ኦቲዝም ካለባቸው ህጻናት መካከል 30 በመቶዎቹ የሚጥል በሽታ አለባቸው። የሚጥል በሽታን በመከታተል እና በመቆጣጠር የሚያደርሰውን አደጋ ማስቀረት ካልተቻለ ሲደጋገም አእምሮን የመጉዳት እና ከጥቅም ውጪ የማድረግ ባህሪይ ስላለው የህፃኑን ህይወት የበለጠ በፈተና የተሞላ ያደርገዋል። ኦቲዝም ያለበት ህፃን በተጨማሪም የሚጥል በሽታ ካለበት ያልተለመደ እና ያለፈቃዱ ፊቱን ወይም ከንፈሮቹን ማንቀሳቀስ፣ ለመግለፅ የሚከብድ ግራ መጋባት ማሳየት፣ ከባድ የራስ ምታት እንዲሁም ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ መተኛት አሊያም የእንቅልፍ መዛባት እና ቅፅበታዊ የስሜት መለወጥ ሊያሳይ ይችላል።


ሌላው ከኦቲዝም ጋር ተያያዥ የሆነው የአእምሮ ጤና እክል ስጋት ወይም ፍራቻ ነው። ኦቲዝም ካለባቸው ህፃናት መካከል ቢያንስ አንድ ሶስተኛዎቹ የዚህ ችግር ተጠቂዎች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህን ህፃናት ከሚያጠቋቸው ስጋቶች መካከልም የማህበራዊ ህይወት ስጋት፣ የመለየት ስጋት እንዲሁም ምክንያታዊ ያልሆነ እና የተጋነነ ስጋት እና ሌሎችም ናቸው። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች በሆነ ምክንያት አንድ ጊዜ ስጋት ከገባቸው ያንን ስጋታቸውን ለመቆጣጠር በጣም ይቸገራሉ። ይሄ የስጋት ስሜት በአብዛኞቹ ላይ በመደበኛነት የሚከሰት ሲሆን፤ ደረጃውም ቀላል፣ መካከለኛ እና ከባድ ሊሆን ይችላል።


ድብርት ሌላው ኦቲዝም ያለባቸውን ሰዎች በተደራቢነት የሚያጠቃ የተለመደ የአእምሮ ጤና መዛባት ነው። የድብርትን ምልክቶች ከኦቲዝም ምልክቶች ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ ድብርት የሚከሰትበት ምክንያትም ከሌላው ሰው ጋር መግባባት ካለመቻላቸው የተነሳ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ይህን የድብርት ስሜት ለመገንዘብም ሆነ ለመግለፅ ይቸገራሉ። ነገር ግን ችግሮቹ ተደራርበው መኖራቸውን ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል ለሚወዱት እንቅስቃሴ እና ተግባር የሚኖራቸው ፍላጎት መጥፋት እና ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም የራሳቸውን ንጽህና ለመጠበቅ እና ለራሳቸው ማድረግ ያለባቸውን ነገር መዘንጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።


አብዛኞቹ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል ሌላው የእንቅልፍ መዛባት ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች በእቅልፍ ለመያዝ በጣም የሚቸገሩ ሲሆን፤ እንቅልፍ ከያዛቸው በኋላም መተኛት ያለባቸውን ሰዓት ያህል ተኝተው ለመቆየት በጣም ይቸገራሉ። በዚህ ሳቢያ የተዛባ እና ከሚፈለገው በታች የሆነ እንቅልፍን ስለሚተኙ ቀን ላይ የሚኖራቸው ባህሪይ እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆን እንዲሁም የሚማሩ ከሆነ በተገቢው መንገድ መማር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።
ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች በአአምሯቸው ላይ ከሚከሰቱ ተያያዥ የጤና እክሎች በተጨማሪም በተለይ ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው የሚያጋጥሟቸው እክሎች አሉ። አንዱ (Gastrointestinal (GI) disorders) የተባለው እና ከሆድ እና ከአንጀት ጋር የተያያዘው ችግር ነው። ጥናቶች እንደጠቆሙት ኦቲዝም ካለባቸው ህጻናት መካል ከግማሽ በላዮቹ ከምግብ ጋር የተያያዘ ችግር አለባቸው። እነዚህ ህፃናት የሚመገቡትን ምግብ እጅግ የሚመርጡ እና ከለመዱት ውጪ አዲስ የምግብ አይነቶችንም ለመሞከር የማይፈልጉ ናቸው። በተጨማሪም አንዳንዶቹ ከመጠን በላይ የመመገብ ፍላጎት ያላቸው ይሆናሉ። በወጣትነት እና በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኙ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ሁልጊዜም የለመዱት ጣዕም ያለውን ምግብ ብቻ የመመገብ ፍላጎት አላቸው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያትም ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ስር የሰደደ የሆድ ድርቀት፣ ተቅማጥ እንዲሁም ከመጠን በላይ ለሆነ የጨጓራ አሲድ መመንጨት እና ቃር እንዲሁም ለአንጀት መመርቀዝ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች የተካተተባቸውን ምግቦች መመገብ ስለማይችሉ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ከመጠን በላይ ለሆነ የሰውነት ክብደት ይዳረጋሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
433 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us