ከፍተኛ የደም ግፊት - ድምፅ አልባው ገዳይ

Wednesday, 23 May 2018 14:25

 

በአለማችን ላይ ካሉ አስር ሰዎች ውስጥ ሶስቱ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት (hypertension) ያለባቸው ሰዎች ናቸው ይላል በበላንሴት ላይ የሰፈረው የግሎባል አልዝ መረጃ። ይህ እውነታ ወደ አሀዝ ሲቀየርም ከአለማት ህዝብ መካከል 34 ነጥብ 5 በመቶው ወይም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የሚሆኑት በዚህ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። መረጃውን እጅግ አስገራሚ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ችግሩ ካለባቸው ሰዎች መካከል ግማሾቹ ከፍተኛ የደም ግፊትን ሊያመጡ ስለሚችሉ አጋላጭ ነገሮች እና ስለሁኔታው እውቀቱ ያላቸው መሆናቸው ነው። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የደም ግፊታቸውን ወደ መደበኛው ደረጃ ለማምጣት እና ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ረገድ እጅግ ዘገምተኞች ሆነው ተገኝተዋል።

የዓለም ከፍተኛ የደም ግፊት ቀን (World hypertension Day) በየዓመቱ ሜይ 27 ቀን (ግንቦት 9) ተከብሮ ይውላል። ይህ ቀን እ.ኤ.አ. ከ2005 አንስቶ መከበር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮም “ቁጥርዎን ይወቁ (know your number) በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። የቀኑ መከበር ዋና አላማም ህብረተሰቡ በየእለት ህይወቱ ውስጥ ስለከፍተኛ የደም ግፊት በቂ የሆነ ግንዛቤ ኖሮት ራሱን አስቀድሞ መከላከል እንዲችል መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት እና የአለም ከፍተኛ ደም ግፊት ሊግ መረጃዎች ገልጸዋል።

ከፍተኛ የደም ግፊት ማለት በሰውነት ውስጥ የሚኖረው ደም የመረጨት አቅም ከፍተኛ መሆን ነው። ከመረጃዎቹ እንደምንገነዘበው የደም ግፊት ከፍተኛ የሚሆነው የሚረጨው ደም ብዙ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ደሙ የሚረጭበት ኃይል ከፍተኛ መሆን ነው። ከፍተኛ የደም ግፊት አጠቃላይ የሰውነት ጤንነትን በማወክ ሰዎች የእለት ተግባራቸውን በአግበቡ እንዳያከናውኑ ያደርጋቸዋል ይላሉ መረጃዎቹ። ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ስራቸው በማድርግ ስራቸውን በአግበቡ ከማከናወን ይልቅ በራስ መተማመናቸውን እንዲያጡ እንዲሁም በሚሰሩት ስራ ላይ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እንዲፈፅሙ ያደርጋቸዋል። በአጠቃላይ ሲታይም ከፍተኛ የደም ግፊት በቀላሉ ሊቆጣጠሩት የሚችል ነገር ግን ድምጽ ሳያሰማ ህይወትን የሚነጥቅ በሽታ ነው።

ከፍተኛ የደም ግፊት ከሌሎች በሽታዎች የሚለዩት የራሱ የሆኑ ምልክቶችን ያሳያል። ከእነዚህ መካከልም ዋና ዋናዎቹ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የእይታ ብዥ ማለት እና መደናገር፣ በጆሮ ውስጥ የደወል የሚመስል ድምፅ መስማት፣ ከመደበኛው የተለየ እና ፈጣን የልብ ምት እንዲሁም ለመተንፈስ መቸገር ተጠቃሾች ናቸው።

ከፍተኛ የደም ግፊት በሁለት ዋና ዋና አይነቶች የሚከፈል ሲሆን፣ እነሱም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ናቸው። የመጀመሪያ (primary) የሚባለው ከፍተኛ የደም ግፊት በብዛት የተለመደው እና 95 በመቶ በሚሆኑት የከፍተኛ ደም ግፊት ችግር ተጠቂዎች ላይ የሚከሰት ችግር ነው። ይህ የከፍተኛ ደም ግፊት አይነት ግልፅ የሆኑ መንስኤዎች የሉትም። ነገር ግን በዘር የሚሄድ እና ከከባቢ አየር ጋር የሚያያዝ መሆኑ ይገለፃል። በተጨማሪም ከመጠን በላይ የሰውነተ ክብደት፣ ብዙ ጨው (ሶዲየም) መጠቀም፣ አልኮልን አዘውትሮ እና በብዛት መጠጣት፣ የስኳር ህመም፣ ሲጋራ ማጨስ እና የቫይታሚን ዲ እጥረት መንስኤ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል። ለዚህ አይነቱ የከፍተኛ ደም ግፊት ያለው ተጋላጭነትም እድሜ እየገፋ ሲሄድ የመጨመር ባህሪይ አለው። ከፍተኛ የደም ግፊት እና ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደትን በተመለከተ ያላቸው ግንኙነት እጅግ ከፍተኛ ነው። መደበኛ እና የተስተካከለ የሰውነት ክብደት ካላቸው ጋር ሲነፃፀር ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎች በአምስት እጥፍ ለመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጮች ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጨውን በብዛት በመጠቀም ወደሰውነት ውስጥ የሚገባው ሶዲየም መጠን በኩላሊት በኩል መወገድ ከሚችለው መጠን በላይ ሲሆን ፈሳሽ ለማዘዋወር ሃይል ስለሚያስፈልግ የደም ግፊቱ ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል።

ሌላው የከፍተኛ ደም ግፊት አይነት ሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት (secondary hypertension) ነው። ይሄንኛው የከፍተኛ ደም ግፊት አይነት የራሱ የሆነ ግልጽ ምክንያቶች ያሉት ነው። ዋና ዋዎቹ ምክንያቶችም ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዘ የእንቅልፍ ችግር፤ የተለያዩ እፆች፣ የታይሮይድ እጢ ስራውን በአግባቡ መስራት አለመቻል፣ ለጤና ጠቃሚ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብ፣ የአልኮል መጠጥን ማዘውተር እንዲሁም የተሳሳተ መድሐኒትን (አግባብነት የሌለው መድሐኒትን) መጠቀም እና ከመጠን በላይ የሆነ መድሐኒትን መጠቀም ለዚህ ለሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት ያለውን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ምክንያቶች ናቸው።

ከፍተኛ የደም ግፊት ከወላጆች ወደ ልጆች የሚተላለፍ በሽታ ነው። ችግሩን ከራሳቸው አልፈው ወደ ልጆቻቸው የሚያሸጋግሩ ወላጆችም ሲጋራ የሚያጨሱ እና ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል የሚጠቀሙ፤ በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን የሚወስዱ እንዲሁም ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት ያላቸውና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉ ወላጆች ናቸው።

ከፍተኛ የደም ግፊት በራሱ የጤና እክል ከመሆኑ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ የጤና መታወኮችን የሚያስከትል ውስብስብ የጤና እክል ነው። ከፍተኛ የደም ግፊት ያለው ሰው ለተለያዩ የልብ እና የልብ ነክ ጤንነት መታወክ፣ የእምሮ እና አንጎልን የማገናዘብ አቅም የማዳከም እና የመግደል እንዲሁም ኩላሊትን በማጥቃት ከሽንት አወገጋድ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የጤና መታወኮች የመጋለጥ እድሉ ከሌሎች ይልቅ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም የአይን ጤንነትን በማዛባት እና እይታን እስከማወክ የደረሱ ተያያዥ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከፍተኛ የደም ግፊት ችግር በአሁኑ ጊዜ ከምን ጊዜውም በላይ በመላው ዓለም ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው መንስኤ ኩባንያዎች የሚሰጧቸው እጅግ ውስብስብ እና ሰፊ ሥራዎች ናቸው። በርካታ ኩባንያዎች ዋና ትኩረታቸውን ትርፍ ላይ ብቻ በማድረግ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ስራዎችን እንዲሰሩ ስለሚያደርጓቸው ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለዚህ ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍ እንዳደረጉት መረጃው ያትታል። እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ሰዎችም በዚህ ስቃይ ውስጥ ሆነው እነዚህን ኩባንያዎች ለማገልገል እየተገደዱ ናቸው ይላል መረጃው።

ከፍተኛ የደም ግፊትን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰው በቂ የሆነ ግንዛቤን በመያዝ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት እለቱን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች አሳስበዋል። ሊወሰዱ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች አንዱ ጭንቀትን እና ውጥረትን ማስወገድ ነው። ጫና በሚፈጥሩ ስራዎች መካከል ለተወሰኑ ደቂቃዎች እረፍት በማድረግ እና አእምሯቸውን ከውጥረት በማላቀቅ ለችግሩ ያላቸውን ተጋላጭነት መቀነስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ስብ እና ቅባት ያላቸውን ምግቦች ባለመመገብ፣ ቅመም የበዛባቸውን እና የተጠበሱ ምግቦችን በማስወገድ እንዲሁም የሰውነት ክብደትን በማስተካከል፣ የአልኮል ተጠቃሚነትን በማስወገድ እና ሲጋራ ባለማጨስ ለችግሩ ያለውን ተጋላጭነት ማስወገድ ይቻላል። በተቻለ አቅም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የደም ግፊት ያለበትን ሁኔታ ማወቅ ችግሩን እና ከእርሱ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለማከም ይረዳናልና ቢለመድ መልካም ነው ይላሉ መረጃዎቹ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
435 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 116 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us