በክረምት ወቅት የሚጠበቁ ጥንቃቄዎች

Wednesday, 27 June 2018 12:50

 

የክረምት ወራትን ተከትለው በስፋት ከሚስተዋሉ የጤና እክሎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ውሃ ወለድ በሽታዎች እና ከጨጓራ እና ከአንጀት ችግር ጋር የተያያዙ በሽታዎች እንደሆኑ የገለፁት በደቡብ እስያ በሚገኘው በባሃርቲ ሆስፒታል አንደክሪያ ሎጀስቷ ዶክተር ሳንጀይ ካልራ በተጨማሪም የታይፎይድ እና ተቅማጥም በክረምት ወራት በሚፈጠሩ የቫይረስ ጥቃቶች ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እክሎች መሆናቸውን አስቀምጠዋል። በተለይ የክረምት ወቅት መግቢያ እና መውጫ ወራት ሰውነታችን ከአንደኛው የአየር ሁኔታ በፍጥነት ወደሌላኛው የሚሸጋገርባቸው ወራት በመሆናቸው ሰውነታችን እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ይቸገራል። በበጋ እና በፀሃያማ ወቅት ሰውነታችን በሙቀት ሳቢያ የመድከም እና የምግብ ልመት ሂደቱም የመዘግየት ሁኔታ ይፈጠርበታል የሚለው መረጃው፤ በክረምት ወቅት ደግሞ የሰውነታችንን ሚዛናዊ አካላዊ እና ስነልቦናዊ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠረው የሰውነት ክፍል ስለሚደክም የበለጠ በበሽታ እንደምንጠቃ ያትታል።

ከዚህ በተጨማሪም በክረምት ወቅት የምግብ መፈጨትን እና ሌሎች አንጀት የሚያከናውናቸው ተግባራት ደካማ እና ዘገምተኛ ስለሚሆኑ ሰውነታችን በቀላሉ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ይጋልጣል። እነዚህን የክረምት ወራትን ተከትለው የሚከሰቱ የጤና መታወኮችን ለመቋቋምም ማንኛውም ሰው ሊወስዳቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች የሚከተሉት ናቸው ሲሉ ባለሞያዋ ያስቀምጣሉ።

የመጀመሪያ ጥንቃቄ የሚሆነው ለወቅቱ ተስማሚ እና ትክክለኛ የሆነ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል ነው። በዚህ ወቅት የሚፈጠረውን የምግብ መፈጨት ችግር ለማስወገድ የሚያግዙ የምግብ አይነቶችን መመገብ ያስፈልጋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚያግዙ የምግብ አይነቶች መካከልም እንደ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ቢቻል የስጋ ውጤቶች እና የአትክልት ውጤቶች ናቸው። በተጨማሪም እንደማር እና ሌሎች ሀይል ሰጪ የምግብ አይነቶችን መመገብ ችግሩን ለመቅረፍ ያግዛል ይላል መረጃው። በተጨማሪም በማቀዝቀዣ ውስጥ ያልተቀመጡ እና በመደበኛ የሙቀት መጠን ላይ ያሉ ንፅኅናው የተጠበቀ ውሃን በመጠጣት የምግብ መፈጨት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። አየሩ ቀዝቃዛ እና ብርዳማ በሆነ ጊዜም ከጣፋጭ ነገሮች ይልቅ ወደ መራራ እና ጎምዛዛነት የሚያደላ ጣዕም ያላቸው እንዲሁም ከመጠን በላይ ያልሆነ የጨው እና የቅባት ይዘት ያላቸውን ምግቦች በመመገብ ሙቀት ማግኘት ይቻላል።

ሌላው በክረምት ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የእግር ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅት እግራችን ከምን ጊዜውም በላይ ለእርጥበት የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ስለሚሆን በቀላሉ በፈንገስ እና በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ይጠቃል። በዚህም ሳቢያ ለመጥፎ የእግር ጠረን እንዲሁም ለእግር ማሳከክ እና መቅላት እንጋለጣለን። በተለይ የስኳር ህመምተኞች ከሌሎች ሰዎች በበለጠ በዚህ ወቅት ለእግራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ይላሉ ባለሞያዎቹ።

ለእግር ከሚደረጉት ጥንቃቄዎች ቀዳሚው የሚሆነው እግራችን በቂ የሆነ የአየር ዝውውር እንዲያገኝ ለተወሰነ ሰዓት ያለምንም መሸፈኛ መቆየት አለበት። ከዚህ በተጨማሪም እግራችን በተቻለ መጠን ንፁህ እና ደረቅ እንዲሆን ማድረግ ቢቻል በተለይ በጣቶቻችን መካከል የፈንገስ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር ያደርጋል። ወደቤታችን ስንገባ አሊያም እረፍት በምናደርግበት ቦታ ላይ ስንደርስ እግራችንን በንፁህ ውሃ እና በሳሙና ወይም ተዋሲያንን ሊገድሉ የሚችሉ ኬሚካሎን ከተቻለ ከጥቂት ጨው ጋር አድርጎ መታጠብ ያስፈልጋል። መታጠቡ ብቻ ፈንገሱን ለማስወገድ እና ኢንፌክሽኑን ለመከላከልም ዋስትና ላይሆን ይችላል የሚሉት ባለሞያዋ፣ በተጨማሪም እግራችንን እና የጣቶቻችንን መካከል በሚገባ ማድረቅ ይኖርብናል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ለእግር የሚደረግ ጥንቃቄን በተመለከተ ሌላው መደረግ የሚገባው ጥንቃቄ እርጥበት ያላቸውን ካልሲዎች እና ጫማዎች ማስወገድ ነው። የካልሲው እና የጫማው እርጥበት ፈንገስ በእግራችን ላይ ኢንፌክሽን እንዲፈጥር ከማድረግ በተጨማሪም ለመራባት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርለት እርጥበት ያላቸው ጫማዎችን እና ካልሲዎችን ወይም ሌሎች እግራችንን የምንጠቀልልባቸውን ነገሮች ማስወገድ ያኖርብናል። በአጋጣሚ ሆኖ እነዚህን ነገሮች በእርጥቡ ለመጠቀም ከተገደድንም በምናወልቅበት ቅጽበት እግራችንን በሚገባ ማድረቅ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የምንጠቀማቸው ካልሲዎች ከእግራችን መጠን ጋር የተስተካከሉ መሆን አለባቸው። በዚህ ወቅት በእግር ላይ የሚከማቸውን ጀርም መጠን ለመቀነስ ሲባልም እግርን በተለይም ጣቶችን የማይሸፍኑ እና ውሃን የማይቋጥሩ ክፍት ጫማዎችን መጫማት ይመከራል።

በእግር ላይ የሚገኝ ማንኛውም ቁስል በክረምት ወይም በእርጥበት ወቅት በጀርሞች ለመመረዝ እጅግ የተጋለጠ በመሆኑ በእግር ላይ የሚገኘው ቁስል እርጥበት እንዳያገኘው አድርጎ መሸፈን ያስፈልጋል። የስኳር ህመምተኛ የሆነ ሰውም በእግሩ ላይ ቁስለቶች ካሉ ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ ይገባዋል። በእግሮቹ ላይ ቀደም ብሎ ልብ ያላላቸው ቁስሎች ሊኖሩ ስለሚችሉም እግሩን በሚያደርቅበት ወቅት ጉዳት እንዳይደርስበት ከፍተኛ ሀይልን መጠቀም የለበትም። ከዚህ በተጨማሪም በሳምንት ውስጥ ለሁለት ጊዜ ያህል እግርን በማሸት በቆዳው ላይ የሚገኙ የሞቱ ሴሎችን ማስወገድ ለጤናማ እግር ከሚመከሩ ጥንቃቄዎች አንዱ ነው።

ጥፍርም ሌላው በቀዝቃዛ እና እርጥባማ ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ነገር ነው። ጥፍራችን እንደ ጭቃ ያሉ ቆሻሻ ነገሮች በብዛት የሚከማቹበት እና ጀርሞች የሚሰባሰቡበት የሰውነት ክፍል ነው። እነዚህ ቆሻሻዎች እና ጀርሞች በመከማቸታቸውም ጥፍራቸን ለኢንፌክሽን እንዲሁም ቀለሙን ወደ ጥቁርነት የመቀየር እና የሞቱ የጥፍር ሴሎች የተከማቸበት ያደርገዋል። እነዚህን ችግሮች ለመከላከልም ጥፍርን በአጭሩ መቁረጥ፣ የምንቀባቸውን ጥፍር ቀለሞች በጥፍር ላይ ለረጅም ጊዜ አለማቆየት እንዲሁም የጥፍርን ዳርና ዳር በአግባቡ ማጽዳት ያስፈልጋል።

ልክ እንደ እግራችን ሁሉ ለቆዳችንም በክረምት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። እንደ ባለሞያዋ ማብራሪያ ምንም እንኳን በዚህ ወቅት እንደ አባሯ ያሉ ቆሻሻዎች ያሉ ባይመስለንም በአይናችን የማናያቸው በርካታ ቆሻሻዎች በቆዳችን ላይ ሊያርፉ ስለሚችሉ ወደ መኝታችን ከመሄዳችን በፊት በሚገባ መታጠብ ፤ ማድረቅ እና ማለስለሻዎችን መቀባት ያስፈልጋል። ጉዳት የሚያደርሱ የፀሀይ ጨረር በዚህ ወቅትም ስላሉ የፀሐይ መከላከያዎችን በአግባቡ በመጠቀም በተለይ ለጸሀይ ተጋላጭ የሆኑ የሰውነት ክፍሎቻችንን ከጉዳት መጠበቅ እንዳለብንም ባለሞያዋ ተናግረዋል። የቆዳ ማስዋቢያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎችም በክረምት መጠኑ ከበጋው ወቅት ያነሰ መዋቢያን መጠቀም የሚገባቸው ሲሆን፤ በቂ እና ለሰውነት አስፈላጊ መጠን ያለው ውሃንም መጠጣት ያስፈልጋል ሲሉ ባለሞያዋ ይመክራሉ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
352 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1036 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us