ከመንደሪን መኮምጠጥ በስተጀርባ

Wednesday, 11 July 2018 13:17

 

መንደሪን ምንም እንኳን የብርቱካን ዝርያ ቢሆንም ከመጣፈጥ ይልቅ የመኮምጠጥ ባህሪው ስለሚያይል ብዙዎቻችን አንደፍረውም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ስናገኘው እንመገበው ይሆናል እንጂ ልክ እንደብርቱካን ጥቅም ይሰጠናል ብለን አዘውትረን እና አስበንበት አንመገበውም። ጥናቶች የሚጠቁሙት ግን መንደሪን በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሰወ ልጅ የጤና ጠንቅ የሆኑ ህመሞችን ለመከላከል ያግዛል። መንደሪን በፋብሪካ ደረጃም ከረሜላዎችን፣ ማስቲካዎችን እና አይስክሬሞችን ለማጣፈጥ እና ቃና ለመስጠት ያገለግላል።

መንደሪን እንደብርቱካን ዝርያነቱ ያለው የቫይታሚን ሲ ይዘት ከፍተኛ ነው። በውስጡ ያለው የቫይታሚን ሲ ይዘት አንድ ሰው በቀን ሊያገኝ የሚገባውን 80 በመቶ የያዘ ነው ይላል በክዮቶ ህክምና ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት። ቫይታን ሲ ደግሞ ለሰውነታችን መጠነ ሰፊ ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ የቫይታሚን አይነት ነው። ከእነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም በአንቲኦክሲደንትነት ባህሪው የሚሰጠው ጠቀሜታ አንዱ ነው። በዚህ ባህሪውም ፍሪራዲካልስ ተብለው የሚጠሩ እና ቋሚ ያልሆኑ ሞሎኪዮሎችን የመበታተን ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። እነዚህ ፍሪ ራዲክሎች ቋሚ የሆኑትን ሞሎኪዮሎች ቋሚ ወዳልሆነ ሞሎኪዩል በመቀየር በሽታ የመቋቋም አቅምን የማዳከም እንዲሁም በሰውነት ውስጥ ያለን ፕሮቲን እና ዘረመል የማዳከም እና የመግደል ጉዳት ያደርሳሉ። ይሄን ሂደት በማስተጓጎል እና የህዋሳትን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ መንደሪን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በመንደሪን ውስጥ ከቫይታሚን ሲ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የቫይታን ኤ እና ቢ ክምችትም ይገኛል።

የመንደሪን አንቲኦክሲደንት ባህሪይ ሌላው የሚሰጠው ጠቀሜታ ጥሩ የሆነው ኮሌስትሮል በበቂ ሁኔታ እንዲመረት ማድረግ ነው። ይህን የሚያደርገውም መጥፎው ኮሌስትሮል በደም ስሮች ግድግዳ ላይ ተጣብቀው የደም ዝውውሩን ዘገምተኛ የሚያደርጉና ፍሪራዲካሎች በማጥቃት ነው። መጥፎው ኮሌስትሮል በደም ስር ግድግዳዎች ላይ በሚጣበቅበት ወቅት የደም ዝውውሩ ዘገምተኛ ስለሚሆን ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ ህመም፣ ለስትሮክ እና ለጉበት በሽታ ያጋልጣል። ነገር ግን መንደሪንን በምንመገብበት ወቅት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ እነዚህን ችግሮች ማስወገድ እንደሚቻል መረጃው ጠቁሟል። በተጨማሪም መንደሪን ከፍተኛ የሆነ የሚሟሟ እና የማይሟሟ የአሰር ይዘት ስላለው መጥፎው ኮሌስትሮል በሰውነት በቀላሉ እንዳይመጠጥ የማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ሌላው የመንደሪን የጤና ጠቀሜታ የጉበት ካንሰርን መከላከል ነው። በኦሪዞና ካንሰር ማዕከል በ2014 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በመንደሪን ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የቫይታሚን ኤ ይዘት ደግሞ ለዚህ ጠቀሜታው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በመንደሪን ውስጥ የሚገኘው ቤታ ክራይፕሮክሳንቲን የተባለው ንጥረ ነገር ሔፒታይተስ ሲ የተባለውን የጉበት በሽታ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በመንደሪን ውስጥ የሚገኘው ላይሞኒን የተባለው ንጥረ ነገር ከፍተኛ የሆነ የፀረ ካንሰር ባህሪይ ያለው ሲሆን፣ በተለይም የጉበት ካንሰር እና የጡት ካንሰርን ለመከላከል ይጠቅማል።

በመንደሪን ውስጥ በርካታ ተፈጥሯዊ ማዕድናት የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም አንዱ ፖታሲየም ነው። ይህ ማእድን በሰውነት ውስጥ የሚከናወነው የደም ዝውውር የተረጋጋ እና መደበኛ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም በደም ስሮች ውስጥ ያለው የደም ዝውውር የተረጋጋ እና ያልተረበሸ እንዲሆን በማድረግ ለከፍተኛ የደም ግፊት ያለንን ተጋላጭነት በእጅጉ ይቀንሰዋል።

ቫይታሚን ሲ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ በሽታ የመከላከል አቅምን ማዳበር ነው። መንደሪንም የቫይታሚን ሲ ይዘቱ ከፍተኛ እንደመሆኑ የሰውነትን በሽታ የመቋቋም አቅም ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም መንደሪን በተፈጥሮው ባክቴሪያ እንዳይራባ እና እንዳያድግ የማድረግ ባህሪይ ስላለው ሰውነት በቀላሉ በጀርሞች በተለይም በባክቴሪያ እንዳይጠቃ በማድረግ እንደ ሳንባ በሽታ ያሉ ህመሞችን ለመከላከል ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም መንደሪን በተፈጥሮ የታደላቸው የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ከምግብ መፈጨት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል እንዲሁም መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ለማስወገድ ቀዳሚው የፍራፍሬ ዝርያ ያደርገዋል።

ሌላው ከመንደሪን የምናገኘው ጠቀሜታ ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ የሚሰጠው ጠቀሜታ ነው። ይሄንን ጠቀሜታ እንዲሰጥ የሚያደርገው ደግሞ በውስጡ ያለው ከፍተኛ የሆነ የሚሟሟ እና የማይሟሟ አሰር ይዘቱ ነው። የመንደሪን የአሰር ይዘትን ስንመለከት በአንድ መቶ ግራም መንደሪን ውስጥ 3 ግራሙ አሰር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በምግብ ውስጥ የሚገኙ አሰርን ስንመገብም በቀላሉ የመጥገብ ስሜት እንዲሰማን እንዲሁም ለረጅም ሰዓት ምግብ ባንመገብም የረሃብ ስሜት ሳይሰማን መቆየት እንድንችል ያግዘናል። በዚህም ብዙ ምግብ ከመመገብ እና ቶሎ ቶሎ ከመራብ ስለሚታደግ ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠር ያግዛል። ላልተፈለገ የሰውነት ክብደት የተዳረጉ እና ይሄንን ክብደታቸውን መቀነስ የሚፈልጉ ሴቶች በቀን ውስጥ 25 ግራም አሰር መመገብ እንዳለባቸው የሚመክር ሲሆን፤ ወንዶች ደግሞ 38 ግራም ያህል አሰር ቢመገቡ የተፈለገውን ውጤት ያገኛሉ ይላሉ ባለሞያዎች። በዘር ምርምር ያደረጉ ባለሞያዎች እንደሚገልጹትም መንደሪን በደም ውስጥ የሚገኘው ኢንሱሊን መጠን እንዲቀንስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በዚህ ባህሪውም በሰውነት ውስጥ የሚከማች ስኳር እንዳይኖር እና የተከማቸው ስብም እንዲፈጭ በማድረግ ያልተፈለገ የሰውነት ክብደት የመቀነስ ጥረቱ ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል።

የመንደሪን አንቲኦክሲደንትነት ባህሪይ የቆዳ ጤንነትን ለመጠበቅም መጠነ ሰፊ ጠቀሜታ አለው። ይህ ባህሪው ጎጂ የሆነ የፀሐይ ጨረርን የመከላከል እና ጉዳት እንዳያደርስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም ከዚህ ከጎጂ የጸሐይ ጨረር ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የቆዳ መሸብሸብ እና መኮማተር እንዲሁም መስመር መስራት እና መጨማደድን ለመከላከል ይጠቅማል። በተጨማሪም በመንደሪን ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የቫይታሚን ሲ ይዘት ቆዳ ጤናማ እንዲሆን እና ጉዳት ከደረሰበትም በቀላሉ እንዲያገግም ያግዘዋል። መንደሪንን አዘውትረው የሚመገቡ ነፍሰ ጡር ሴቶች ጽንሱ በቂ ቫይታን ሲ እንዲያገኝ ስለሚረዳው የተስተካከለ እና ፈጣን እድገት እንዲኖው ያደርግላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በፅንሱ እና በእናትየዋ ማህጸን መካከል ያሉት ህዋሳት እና ደም ስሮች ግንኙነታቸው ጠንካራ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው።    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
306 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1010 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us