ቀረፋ - ከመድሐኒቶች የሚልቅ መድሐኒት

Wednesday, 18 July 2018 16:26

 

ቀረፋ ከጥንት ግብፃዊያን ጊዜ ጀምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲያገለግል ነበር። ለጥንት ንጉሳዊያንም እንደ ውድ ስጦታ ሆኖ ይቀርብ ነበር። አሁን ባለንበት ጊዜ ደግሞ የዕፅዋትን እና የዕፅዋት ውጤቶችን የመድሐኒትነት ባህሪይ የሚያጠኑ የጤና ባለሙያዎች ቀረፋ በዓለማችን ላይ የመድሐኒትነት ባህሪያቸው ከሚያመዝን የዕፅዋት ውጤቶች መካከል እንደሚመደብ እየገለፁ እና እንድንጠቀምም እያበረታቱን ይገኛሉ። በኢሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በማሌዥያ ኬላንታን እና ሴንስ የህክምና ትምህርት ቤት የተደረጉ ጥናቶችም የቀረፋን ባህሪይ እና ያሉትን ጠቀሜታዎች እንደሚከተለው አስቀምጠዋቸዋል።

 

ቀረፋ ለበርካታ የምግብ ማጣፈጫነት እንዲያገለግል የሚያደርገው ያለው ቃና ነው። ሳይንቲስቶች እንደሚገልፁትም ቀረፋ አሁን ያለውን ቃና እንዲይዝ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲሰጥ የሚያደርገው ሲናሚልዲሃይድ የተባለው ውህድ ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቀረፋ የአንቲኦክሲደንትነት ባህሪው ጠንካራ ነው። አንቲ-ኦክሱደንቶች ሰውነትን ከተለያዩ ጐጂ የሆኑ ፍሪራዲካልስ የሚከላከሉ ናቸው። የቀረፋ አንቲኦክሲዳንትነት ባህሪም ነጭ ሽንኩርትን ጨምሮ ከ26 የቅመማ ቅመም አይነቶች በልጦ መገኘቱን በማሌዢያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት አረጋግጧል። የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ማንሴኒ ፊልሆ እንደገለፁት ደግሞ ከቀረፋ የሚገኙት ውጤቶች ከፍተኛ የሆነ የአንቲኦክሲዳንትነት ባህሪይ አላቸው። በተለይ የቀረፋ ጭማቂ እና ከቅጠሉ የሚገኘው ዱቄት በዚህ ባህሪው የበለፀገ በመሆኑ ቀረፋን የበለጠ ጠቃሚ ያደርገዋል። ከቀረፋ የሚገኘው ውሃማ እና አልኮላማ ጭማቂም ፋቲ አሲድ በሰውነታችን ውስጥ ከኦክሱጅን ጋር የሚያደርገውን ውህደት በማስተጓጐል የሚያስከትለውንም ጉዳት ለመከላከል ያግዛል። በሚያስገርም ሁኔታም የቀረፋ ቅጠሉ፣ ግንዱ እና ስሩም ጭምር ናቸው ጠቀሜታ ያላቸው።

 

ሌላው ቀረፋ የሚሰጠን አብይ ጠቀሜታ የሚያያዘው ከቀረፋ የፀረ መመረዝ ባህሪይ ጋር ነው። የሰውነት መመረዝ በተወሰነ መልኩ ለህይወታችን አስፈላጊ ቢሆንም፤ ከመጠን ሲያልፍ ግን ወደ ችግርነት እንደሚቀየር ጥናቶች ያመለክታሉ። በመሆኑም የሰውነት መመረዙ ወደ ችግርነት እንዳይቀየር በተለያየ መልኩ መከላከል ያስፈልጋል። ለዚሁ አገልግሎት ከሚውሉ እፅዋት መካከል ቀረፋ አንዱ ነው። በተለይ ከቀረፋ ቅጠል የሚገኘው ዘይት እና ቅባት የሰውነት መቆጣትን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚሁ ባህሪው የተነሳም በሰውነት ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት እንዲሁም በአንጐል ላይ የሚከሰቱ መቆጣቶችን ይከላከላል። በተጨማሪም በሰውነት ህዋሳት ውስጥ የሚኖረውን የካልሲየም እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በህዋሳት (ሴሎች) ላይ የሚከሰት እብጠት እንዳይኖር በማድረግ በኩል ቀረፋን የሚያክለው የለም። ከተደረጉ ጥናቶች ማረጋገጥ እንደተቻለውም በቀረፋ ውስጥ የሚገኘው ሶዲየም ቤንዞኤት የተባለ ንጥረ ነገር ታው የተባለው ፕሮቲን በአንጐል ውስጥ እንዳይከማች በማድረግ እንደ አልዛይመር እና ፓርኪንሰንስ ያሉ ከአንጐል ጋር የተያያዙ ህመሞችን ለመከላከል ያግዛል። በዚሁ ተግባሩም ለተለያዩ በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት በከፈተኛ መጠን ይቀንሰዋል።

 

በቀረፋ ውስጥ የሚገኙት ሲናሚክ አልዲሃይድ እና ሲናሚክ አሲድ የተባሉት ንጥረ ነገሮች የልብ ህመም እና ከልብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የጤና እክሎች ለመከላከል ብሎም ህመሞቹን ለማከም እንደሚያገለግሉ በኢሊኒዩስ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት አመልክቷል። ጥናቱ እንዳስቀመጠውም እነዚህ ንጥረ ነገሮች መጥፎውን ኮሌስትሮል በመቀነስ እና ጠቃሚ የሆነውን ኮሌስትሮል መመንጨት በማበረታታት ለልብ ህመም እና ሌሎች ተያያዥ ህመሞች ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል። ከዚህ በተጨማሪም ለልብ ህመም መንስኤ የሆኑትን ከፍተኛ የደም ግፊት፣ መጠኑ ከፍ ያለ መጥፎ ኮሌስትሮል መመንጨት እና ሌሎች ምክንያቶችንም የመከላከል ጠቀሜታው የጐላ ነው።

 

ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የተመገብነው ምግብ ወደ ኃይል የሚቀየርበትን ሥርዓት እና ያ ኃይልም አገልግሎት ላይ የሚውልበትን ሂደት መቆጣጠር እንዲሁም በደም ውስጥ የሚገኝ ስኳርን ከደምስሮች ተቀብሎ ወደ ሰውነት ህዋሳት ማጓጓዣ ነው። በአንዳንድ ሰዎች ላይ ግን ኢንሱሊን በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ሲያቅተው አይነት 2 የተባለው የስኳር ህመም ይከሰታል። ነገር ግን ይህን ችግር ለመቀነስ ቀረፋ አይነተኛው መድሐኒት ነው። በቀረፋ ውስጥ የሚገኙት ተፈጥሯዊ ኢንዛይሞች ምግብ ከተመገብን በኋላ ከምግቡ የምናገኘው ካርቦሃይድሬት የሚሰባበርበት ፍጥነት ዝግ ያለ እንዲሆን በማድረግ ወደ ደምስራችን የሚገባው ግሉኮስ መጠን አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል። እግረመንገዱንም ኢንሱሊን ለሰውነታችን በቂ በሆነ መጠን እንዲመነጭ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

 

በአውስትራሊያ ስዊንቦርን የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተደርጐ ሰሞኑን ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ ቀረፋ በሰውነት ላይ የሚደርሰውን የመመረዝ (Infection) ችግር ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የጥናት ቡድኑ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሳንዲጂ ቶፓ እንደገለፁትም፣ በቀረፋ ውስጥ የሚገኙት ተፈጥሮአዊ ንጥረነገሮች ከፀረ ባክቴሪያ መድሐኒቶች በተሻለ መልኩ የሰውነት መመረዝን የመከላከል አቅም አላቸው። በተለይ ሲናማልዲሃይድ የተባለው እና በቀረፋ ውስጥ በብዛት የሚገኘው ውህድ የተለያዩ ኢንፌክሽኖችን ለመቋቋም ያግዛል። ከቀረፋ የሚገኘው ዘይትም በፈንገስ ሳቢያ የሚከሰቱ የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ህመሞችን ለመከላከል፤ ተከስተው ሲገኙም አክሞ ለማዳን እንደሚያገለግሉ ዶክተር ቶፓ ገልፀዋል። በዚህ ብቻ ሳያበቃም ይህ ንጥረ ነገር ሊስቴሪያ እና ሳልሞኔሊ የሚባሉትን ባክቴሪያዎች ጨምሮ የተወሰነ የባክቴሪያ አይነቶችን እድገት የመግታት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም የጥርስ መበስበስ እና መሰባበርን እንዲሁም መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

 

ከላይ የተቀመጡት የቀረፋ ጠቀሜታዎች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቀረፋ ኤች አይቪ እና ካንሰርን ጨምሮ በርካታ የጤና እክሎችን የመከላከል ጠቀሜታ አለው። በደቡብ ቬይና ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ዲፓርትመንት ተመራማሪው ዶክተር ፓሱፑሌቲ ቪስዌስዋራ ራኦ እንደሚገልፁትም፤ ቀረፋ ከቅጠሉ ጀምሮ እስከ ስሩ ድረስ ያለው ክፍሉ በአጠቃላይ ለተለያዩ ህመሞች መድሐኒት ነው። ቀረፋ በተፈጥሮው እጅግ ብዙ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እና ውህዶችን የያዘ በመሆኑ በምርምር ከሚፈጠሩ መድሐኑቶች በተሻለ መልኩ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጥ ተመራማሪው አረጋግጠዋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
220 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 65 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us