ውርርዱውርርዱ

Wednesday, 21 May 2014 12:51

አጭር ልብወለድ

ደራሲ አንቷን ናቭሎች ቼሆቭ

ትርጉም ኪዳኔ መካሻ

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ይህ የስመጥሩው ሩሲያዊ ደራሲ የአንቷን ቼሆቭ ልብ ወለድ የሚያጠነጥነው ከሞት ቅጣት እና ከእድሜ ልክ እስራት የትኛው ይበልጣል የሚል መነሻ ላይ ሆኖ የነፃነትንና የገንዘብንም ዋጋ ቁልጭ አድርጎ መዝኖ ያሳየናል።

ዘመን አይሽሬ ከሆኑት የቼሆቭ ስራዎች አንዱ የሆነው ይህ አጭር ልብ ወለድ በተለይም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነፃነታችንን ሊያሳቱ ወደሚችሉ ተግባሮች ለምን መግባት እንደሌለብንየሚጠቁም ነፃነት እና መብታችንን በቼሆቭ የትረካ መነፅር ላሳያችሁ ወደድኩ። ቼሆብ ቀጥል. . .

በአንድ የበልግ ጭለማማ ምሽት ላይ ነበር። ሽማግሌው የባንክ ኃላፊ በጥናት ክፍሉ ውስጥ ከወዲህ ወዲያ እየተመላለሰ ከአስራ አምስት አመታት በፊት በዚሁ በበልግ ወቅት ውስጥ አዘጋጅቶት የነበረውን ግብዣ አያስታወሰ ነበር። በግብዣው ላይ በርካታ ብልህ ሰዎች ታድመውበት የነበረ ሲሆን ሲወያዩባቸው የነበሩ ጉዳዮችም ትኩረትን የሚስቡ ነበሩ። ግብዣው ላይ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የሞት ቅጣት ጉዳይም ተነስቶ ነበር። ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ምሁራንና ጋዜጠኞች የሞት ቅጣትን በአብዛኛው የሚቃወሙ ነበሩ። ለእነሱ የሞት ቅጣት ያረጀ ያፈጀ የቅጣት ዘዴ ነው፤ ለክርስቲያን መንግስት የማይመጥንና ለግብረገብም ተፃራሪ ነበር። አንዳንዶቻቸው በአለም ላይ በጠቅላላ የሞት ቅጣት በእድሜ ልክ እስር መተካት አለበት ብለው የሚያስቡ ነበሩ።

“እኔ በናንተ ሃሳብ አልስማማም” አለ ጋባዡ። “የሞት ቅጣትም ሆነ የእድሜ ልክ አስራት ቅጣት እኔ በራሴ ላይ ደርሶብኝ ባያውቅም አንዱ ዳኛ ከሁለቱ የሚሻልህን ምረጥ ቢለኝ እንደእኔ እንደእኔ ከእስር ይልቅ የሞት ቅጣት በጣም ግብረ ገባዊ እና ሰብዓዊ የሆነ ቅጣት ነው። የሞት ቅጣት በቅፅበት ነው ሚገልህ የእድሜ ልክ እስራት የሚገልህ ግን ደረጃ በደረጃ ነው። ታዲያ የትኛው ነው ሰብዓዊ ገዳይ የሚባለው? በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ የሚገላግለው ነው ወይንስ ያለማቋረጥ ቀስ እያለ ከአመታት ውስጥ ነፍስን የሚነጥቀው ነው?”

“ሁለቱም ቢሆኑ እኩል ግብረገባዊነት የሌላቸው ናቸው” አለ ከእንግዶቹ አንዱ “ምክንያቱም የሁለቱም ፈጣሪ አንድ ነው። ህይወትን መውሰድ መንግስት ፈጣሪ አምላክ አይደለም። ስለዚህ ቢፈለግ እንኳን መልሶ ሊያመጣው የማይችለውን ነገር የመውሰድ መብት የለውም”።

ከተሰበሰቡት ተጋባዦች መካከል እድሜው ሃያ አምስት አመት የሚሆነው ጠበቃ ነበር። በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ሲጠየቅ እንዲህ ነበር ያለው “የሞት ቅጣትም እድሜ ይፍታህ እስርም እኩል ፀረ ግብረገብ ናቸው። እኔ ግን ከሁለቱ መካከል ምረጥ ብባል በርግጠኝነት ሁለተኛውን እመርጣለሁ። ምክንያቱም ከነጭራሹ ካለመኖር በተወሰነ መልኩም ቢሆን መኖሩ የተሻለ ነው።

ይሄኔ ነበር ሞቅ ያለ ክርክር የተነሳው። በወቅቱ ገና ወጣትና ግልፍተኛ የነበረው የባንክ ኃላፊ እራሱን መቆጣጠር ተስኖት ስለነበር ጠረቤዛውን እየደበደበ ወደ ወጣቱ ጠበቃ በመዞር “የምትለው ሁሉ ውሸት ነው። በሁለት ሚሊዮን አስይዛለሁ ለአምስት ዓመት እንኳን ለብቻህ በአንድ ክፍል መታሰር አትችልም” ሲል ነበር ያምባረቀበት።

“ከምርህ ከሆነ” ብሎ ነበር የመለሰለት ጠበቃው። እንግዲያውስ አይደለም አምስት አመት አስራ አምስት አመት እቆያለሁ እንወራረድ”

“አስራ አምስት በአንድ አፍ” ሲል በጩኸት ተናገረና የባንክ ኃላፊው “ክብሩን እኔ ሁለት ሚሊዮን አስይዣለሁ”

“ተስማምቻለሁ አንተ ሁለት ሚሊዮን እኔ ደግሞ ነፃነቴን አስይዣለሁ” ነበር ያለው ጠበቃው።

እናም በዚህ ሁኔታ ነበር ይህ የእብደት ውርርድ የተደረገው በዚያን ጊዜ የባንክ ኃላፊው በርካታ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጥር ተንደላቆና ተሞላቆ የሚኖር እድሉን ለመሞከር የማያወላውልና ከፍተኛ የሀሴት ህይወትን የሚመራ ነበር። በእራት ሰዓት ላይም ለጠበቃው በቀልድ መልክ

“አንተ ጎረምሳ ጊዜው ሳይረፍድብህ ቀልብህን ብትገዛ ጥሩ ነው። ሁለት ሚሊዮን ማለት ለኔ ምንም ነው አንተ ግን ከህይወትህ ምርጡን ጊዜ ሁለት ወይም ሶስት ዓመታትን ማጣትህ ነው። የምልህ ሁለት ሶስት ዓመታትን ነው ምክንያቱም ከዚያ በላይ በፍፁም በውርርድህ ፀንተህ ታስረህ ልትቆይ አትችልም። ይህንንም ቢሆን አትዘንጋው አንተ ደስታ አልባ ሰው በፍቃደኝነት የገቡበት እስር በግድ ከሚገቡበት እስር የበለጠ ከባድ ነው። በማንኛውም ቅፅበት እራስህን በራስህ ነፃ ማውጣት መብት አለህ የሚለው ሁኔታህ ያሳዝነኛል” ብሎት ነበር።

አሁን የባንክ ኃላፊው ወደህ ወዲያ እየተመላለሰ ነበር ይህን ሁሉ ነገር ያስታወሰው። ከዚያ እራሱን እንዲህ ሲል ጠየቀ

“ለምን ብዬ ነው እንዲህ ያለ ወርርድ ውስጥ የገባሁት ምንድን ነው ጥቅሙ? ጠበቃው ከእድሜው ላይ አስራ አምስት ዓመታትን አጣ። እኔም ደግሞ ሁለት ሚሊዮን የትም በተንኩ። ተትኸሐኸኀኁኀኀሐኸ እንዲህ ማድረጋችን የሞት ቅጣት ከእድሜ ልክ እስራት የተሻለ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ህዝቡን ያሳምናል? የለም የለም ሁሉም ነገር ፋይዳ ቢስና የማይረባ ነው። በኔ በኩል የጥጋበኛ የቁማር ጨዋታ ሲሆን በጠበቃው በኩል ደግሞ ከመጠን ያለፈ የገንዘብ መስገብገብ ነበር። ከዚያን ቀን የምሽት ግብዣ በኋላ የተከሰቱትንም ነገሮች ወደኋላ አስታወሰ። ጠበቃው የእስር ጊዜውን በባንክ ኃላፊው መኖሪ ቤት ጎን ያለው የአትክልት ስፍራ ውስጥ ያለ ቤት ውስጥ በጥብቅ ቁጥጥር ስር ሆኖ እንዲያሳልፍ ነበር የተወሰነበት። በእስሩ ወቅት ከተገደበለት ክልል የመውጣት ሰዎችን የማየት፣ ድምፃቸውን የመስማት፣ ደብዳቤና ጋዜጦችንየማግኘት መብቱ እንዲገፈፍ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። የሙዚቃ መሳሪያዎች እንዲኖሩት፣ መፅሀፍት እንዲያነብ፣ ደብዳቤዎች እንዲፅፍ ወይን ጠጅ እንዲጠጣና ትምባሆ እንዲያጬስ ተፈቅዶለት ነበር። በስምምነቱ መሰረት ከውጭው አለም ጋር መገናኘት ይፈቀድለታል ሆኖም ግን በዝምታ እና ሊዘሁ ጉዳይ ተብላ በተሰራች ልዩ መስኮት በኩል ብቻ ነበር። የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ መፅሀፍት፣ ሙዚቃ፣ ወይንጠጅ በፈለገው መጠን በመስኮቷ በኩል ማስታወሻ ፅፎ በመላክ ማግኘት ይችል ነበር። ስምምነቱ እያንዳንዷን ዝርዝር ነገር በፅሁፍ የያዘ መሆኑ እስሩን ጥብቅና የብቸኝነት የሚያደርገው ሲሆን ጠበቃ ወይም እቅጩን ድፍን አስራ አምስት አመታትን ከህዳር 14 1870ከምሽቱ ስድስት ሰዓት እስከ ህዳር 14 1885 ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ከእስር እንዲቆይ የሚያስገድድ ነበር። በጠበቃው በኩል የተሰማማባቸውን ሁኔታዎች ቢጥስ ጊዜው ሊያበቃ ሁለት ደቂቃ ቢቀር እንኳን ቢያመልጥ የባንክ ኃላፊውን ሁለት ሚሊዮን ለመክፈል ከገባው ግዴታ ነፃ ያወጣዋል።

በመጀመሪያው የእስር ዓመት ጠበቃው ከአጫጭር ማስታወሻቹ መገመት እንደሚቻለው በብቸኝነትና በድብርት እጅጉን ተሰቃይቶ ነበር። ከታሰረበት ክፍል ቀን ከሌት የፒያኖ ሙዚቃ ድምፅ ይሰማ ነበር። ወይንጠጅ ትምባሆም አልፈልግም ብሎ ነበር። “ወይን ጠጅ” ሲል ነበር የፃፈው ፍላጎቶችን ያስድስታል ፍላጎቶች ደግሞ የእስረኛ ዋነኛ ጠላቶች ናቸው። በተጨማሪም ደግሞ ጥሩ ወይንን ለብቻ ከመጠጣት በላይ የሚያስጠላ ነገር የለም” ብሎ ነበር። ትምባሆ ደግሞ የእስር ክፍሌን አየር ያበላሽብኛል ብሎ ነበር። በመጀመሪው አመት ጠበቃው የሚጠይቃቸው መፅሀፍት ቀለል ያለ ይዘት ያላቸው ውስብስብ የፍቅር ታሪክ የሚተርኩ ልቦለዶች፣ የወንጀል እና በምናባዊው አለም ብቻ ያሉ ታሪኮች፣ አስቂኝ ፅሁፎችንና የመሳሰሉትን ነበር።

በሁለተኛው አመት የፒያኖው ድምፅ መሰማቱ ተቋረጠና ዘመን አይሽሬ መፅሀፍት ብቻ መጠየቅ ጀመረ። በአምስተኛው አመት ላይ ክፍሉ ሙዚቃ ድጋሚ መስማት ጀመረ ወይን ጠጅም እንዲገባለት ጠየቀ። ያዩት ሰዎች እንደሚሉት የዚያን አመት በሙሉ እየበላ እየጠጣ አልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር ያሳለፈው። ደጋግሞ እያዛጋ በብስጭት ከራሱ ጋር ያወራ ነበር። መፅሀፍት አያነብም። አንዳንድ ጊዜ በምሽት ቁጭ ብሎ ይፅፋል። ለረጅም ሰዓት ሲፅፍ ያመሸውን በጠዋት ቀዳዶ ይጥለዋል። በተደጋጋሚም ሲያለቅስ ተሰምቷል።

በስድስተኛው አመት አጋማሽ ላይ እስረኛው ቋንቋ ፍልስፍና እና ታሪክ በትጋት ማጥናት ጀመረ። እነኚህን መፅሀፍት ተስገብግቦ ያነባቸው ስለነበር የባንክ ኃላፊው መፅሀፍቱን ለማግኘት ጊዜ ያጥረው ነበር። በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ስድስትመቶ ጥራዝ መፅሀፍት በጥያቄው መሰረት ተገዝተውለታል። ይህ ፅሁፍ የማንበብ ፍቅሩ ሲሟጠጥ ነበር የባንክ ኃላፊው እንዲህ የሚል ደብዳቤ ከእስረኛው ደረሰው። ውድ አሳሪዬ እነኚህ መፅሀፎች በስድስት ቋንቋዎች ነው የፃፍኳቸው ለባለሙያዎች አሳይልኝና እንዲያነቧቸው አድርግ። አንድም ስህተት ካላገኙ በአትክልት ስፍራው ውስጥ ጥይት እንዲተኩሱ እንድታዝልኝ እለምንሃለሁ። በተኩሱ ድምፅ ጥረቴ በከንቱ እንዳልቀረ እረዳለሁ። የሁሉም ዘመን የሁሉም ሀገር የላቀ አእምሮ ባለቤቶች የተናገሩት በተለያየ ቋንቋ ቢሆንም ሁሉም ውስጥ የምትነደው ግን አንድ ነበልባል ናት። አቤት እነሱን መረዳት ባለመቻሌ የሚሰማኝን ሰማያዊ ደስታ ብታውቀው እንዴት ጥሩ ነበር” የእስረኛው ምኞት ተሟለላት። በባንክ ኃላፊው ትዕዛዝም በአትክልት ስፍራውሁለት ጥይቶች ተተኮሱ።

በኋላ ላይ ከአስር አመት ቆይታው በኋላ ጠበቃው ከተቀመጠበት ሳይነሳ የሚያነበው ሃዲስ ኪዳንን ብቻ ነበር። የባንክ ኋላፊው በአራት አመታት ስድስት መቶ ዳጎስ ያሉ ጥራዞችን እጥብ አድርጎ አንብቦ የጨረሰው ሰው አንድ አመት ያህል አንድ መፅሀፍ ላይ ብቻ ማሳለፍ እንግዳ ነገር ሆኖበት ነበር። መፅሀፍ ደግሞ በቀላሉ የሚገባና ትራዙም ብዙ የሚባል አልነበረም። ከዘያም የሀዲስ ኪዳኑን ከሃይማኖቶች ታሪክና በነገረ መለኮት መፅሀፍት ተክቷቸው ነበር። በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ላይ ደግሞ እስረኛው የሚጠይቃቸው መፅሀፍት እጅግ ከመብዛታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ነበሩ። አሁን ወደተፈጥሮ ሳይንስ አትኩሯል ሲባል የባለቅኔዎቹን የሎርድ ላይረንና የሼክስፔርን ስራዎች ይጠይቃል። በአንድ ማስታወሻ የኬሚስትሪ፣ የህክምና መማሪያ፣ ልቦለድ እና የፍልስፍና ወይም የሃይማኖት የምርምር መፅሀፍት እንዲመጡለት ይጠይቃል አነባበቡ ልክ በሰጠሙ የመርከብ ስብርባሪ መካከል ባህር ውስጥ ሆኖ እየዋጠ እንዳለና ለመኖር ባለው ፍላጎት አንዱን እየለቀቀ ሌላውን በመያዝ እየጣረ እንዳለ ሰው ነበር።

II

የባንክ ኃላፊው ይህንሁሉ አስታወሶ ሲጨርስ እንዲህ አሰበ “ነገ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ነፃነቱን ያገኛል። በስምምነቱ ሁለት ሚሊዮን መክፈል እገደዳለሁ። ከከፈልኩ ደግሞ የኔ ነገር አበቃልኝ። እስከ መጨረሻው ያልቅልኛል. . .”

ከ15 ዓመታት በፊት በርካታ ሚሊዮኖቸ ነበሩኝ አሁን ግን ካለው ገንዘብና ካለበት እዳ የቱ እንደሚበልጥ እንኳን ለመጠየቅ ይፈራል። የአክስዮን ገቢያው ቁማር፣ በድፍረት አስቦ የገባባቸው ስራዎችና በስተርጅና እንኳን ያለቀቀው አባካኝነት ቀስ በቀስ የንግድ ስራውን አንኮታኩተውታል። በመሆኑም ፍርሃት አልባውን ልበ ሙሉውን ኩሩውን የንግድ ሰው ገበያው በወጣ በወረደ ቁጥር የሚበር ተራ የባንክ ባለሙያ አድርገውታል።

“ያ የተረገመ ውድድር” ሽማግሌው የጭንቁን እራሱን በመዳፉ እየደበደበ ያጉተመትማል “ለምንድንነው ሰውዬው የማይሞተው? ገና አርባ አመቱ ነው። የቀረችኝን ጥሪት አሟጦ ይወስዳል፣ ያገባል በገበያው ላይ እየቆመረ በደስታ ህይወቱን ሲያጣጥም እኔ ደግሞ እንደሚቀላውጥ ለማኝ ህይወቴን ደስተኛ ለማድረግ ስል ስላንተ ግዴታ አለብኝ ስለዚህ ልርዳህ” የሚሉትን ተመሳሳይ ቃሎች በየቀኑ ከአንድበቱ ስሰማ መኖሬ ነው። የለም ይህማ ይበዛብኛል አልችለውም ከኪሳራና ከውርደት ለመዳን ብቸኛው አማራጭ የሰውየው የግድ መሞት አለበት።

ሰዓቱ ገና ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ነበር። የባንክ ኃላፊው በትኩረት እያዳመጠ ነው። በቤቱ ውስጥ ያሉት ሁሉ ስለተኙ የሚሰማው በመስኮቱ የሚገባው የቀዘቀዙት ዛፎች የንፋስ እንቅስቃሴ ድምፅ ብቻ ነበር። አንዳችም ድምፅ ላለመስማት እየሞከረ ለ15 ዓታት ያልተከፈተውን በር የመክፈቻ ቁልፍ ከካዝናው ውስጥ አወጣ፣ ካፖርቱን ደረበና ከቤቱ ወጣ። የአትክልት ስፍራው ጨለማና ቀዝቃዛ ነበር። ዝናቡ እየጣለ ነበር። እርጥቡና የሚያፏጨው ንፋስ የአፅዱን ዛፎች እረፍት ነስቷቸዋል። ወደአትክልት ስፍራው ቅጥር ተጠግቶ ሁለት ጊዜ ዘበኛውን ተጣራ። መልስ አልነበረም። በርግጠኝነት ዘበኛው ከመጥፎው አየር ለመጠለል ኩሽናው ውስጥ ወይም የችግረኝ ማፊያው ቤት ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ተኝቷል።

“ሀሳቤን የማሳካበት ወኔው ካለኝ” ሲል አሰበ ሸማግሌው “ጥርጣሬው የሚያርፈው በመጀመሪያ ዘበኛው ላይ ነው”

“በጭለማ ውስጥ በዳበሳ ደረጃውን ወጣና ወደ አትክልት ስፍራው አዳራሽ ገባ ከዚያም ወደ ቀጭኗ መተላፊያ ሲገባ ክብሪት አውጥቶ ለኮሰ አንድም ዝር የሚል ሰው አልነበረም። ብርድ ልብሱ የሌለበት የአንድ ሰው አልጋ ጥግ ይዞ ቆሟል። እስሩ ደግሞ የብረት ተወሽቋል። ወደ እስረኛ ክፍል የሚያስገባው በር ላይ ያለው የማሸጊያ ማህተም አልተገኘም የለኮሰው ክብሪት ሲጠፋ ሽማግሌው በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ በጠባቧ መስኮት አጮልቆ ተመለከተ።

በእስረኛው ክፍል ውስጥ ያለችው ሻማ ጭልጭል እያለች እየበራች ነበር። እስረኛው እራሱም ጠረጴዛውን ደገፍ ብሎ ተቀምጧል። ጀርባውን ሰጥቶ ነበር የተቀመጠውና የጭንቅላቱ ፀጉርና እጆቹ ብቻ ነበር የሚታዩት የተገለጠ መፅሀፍ ጠረጴዛው ላይ ተዘርግቷል። ሁለት ወንበሮች ላይ እና ጠረጴዛው አጠገብ ያለ ምንጣፍ ላይም መፅሀፍ ነበር። አምስት ደቂቃዎች ቢያልፍም እስረኛው ለአንዴ እንኳን አልተንቀሳቀሰም። የ15 ዓመታት እስር ቆይታው በድን ሆኖ ሳይንቀሳቀስ መቀመጥን አስተምሮታል የባንክ ኋላፊው በጣቶቹ መስኮቱን ቆረቆረ እስረኛው ግን በምላሹ ምንም እንቅስቃሴ አላሳየም። ከዚያም የባንክ ኃላፊው በጥንቃቄ በማህተም የታሸገበትን ወረቀት ቀዳዳና መክፈቻውን መቆለፊያው ውስጥ ከተተ። የዛገው ቁልፍ ጮሆ ተንቋቋና በሩ እየተንሳጠጠ ተከፈተ። የባንክ ኃላፊው በመደነቅ የመጮኽ ድምፅና የኮቴ ድምፅ ለመስማት ጠብቆ ነበር። ሶስት ደቂቃዎች ቢያፍም ክፍሉ እንደነበረ ፀጥ እንዳለ ነበር። ወደውስጥ ለመግባት ወሰነ።

ከጠረጴዛው ፊት ሰው ተቀምጧል። እንደተራ ሰው ግን አይደለም። ከዚያም ለጋ የለበሰ ቆዳው አጥንቱ ላይ የተጣበቀ አፅም ነበር ፀጉሩ እንደ ሴት ፀጉር እረጅም ሆኖ የተንጨባረረ ጢሙም አድጎ ተፈተልትሏል የፊቱ ቀለም ቢጫ ሆኖ መድራዊ ጥላ አጥለቶበታል። የጉንጩ ከአጥንተ ጋር ተጣብቆ ወደ ውስጥ ሰምጧል። ጀርባው ረጅም እና ጠባብ ነው። የተንጨባረረ ፀጉሩን ያስደገፈባቸው እጆቹ ቀጭንና ቆዳቸው የተጣበቀባቸው ከመሆናቸው የተነሳ እነሱን ማየት ያሳምማል። ፀጉሩ እየሸበተ ወደ ግራጫማ ቀለም ተቀይሯል። ምንም የጃጀ የሚመስለውን ፊቱን ያየሰው ገና አርባ አመቱ ነው ቢባል አያምንም። ጠረጴዛው ላይ ካቀረቀረ ጭንቅላቱ ፊት በቀጭኑ እጁ የሆነ ነገር የተጻፈበት ወረቀት ተቀምጧል

“ምስኪን ዲያብሎስ” አለና የባንክ ኃላፊው “ይሄኔ በተኛበት ሚሊዮኖችን እያለመ ይሆናል ይሄኔ በክፍል የሞተ ሰው በቀላሉ አንስቼ አልጋው ላይ ጥዬ በደቂቃ ውስጥ በትራስ አፍኜ እገላግለዋለሁ። የፈለገውን ይህል ጠንቃቃ ምርመራ ቢካሄድም ከተፈጥሮአዊ ሞት ውጭ ሌላ ፍንጭ አይገኝብኝም ከዛ በፊት ግን እስቲ እዚህ የተፃፈውን እናንብበው።

የባንክ ኃላፊው ወረቀቱን ከጠረጴዛው ላይ አንስቶ አነበበው “ነገ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ነፃነቴንና ከሰዎች የመቀላቀል መብቴን አገኛለሁ። ሆኖም ግን ይህ ክፍል ከመልቀቄና ፀሀይን ከመመልከቴ በፊት ጥቂት ቃላቶችን ማለት እፈልጋለሁ። በንፁህ ህልናዬና በፈጣሪ አምላክ ፊት መፅሀፍቶቻችሁ የአለማችን በረከቶች የሚሏቸውን ነፃነትን፣ ህይወትን፣ ጤናን መናቄን በግልፅ ማወጅ እፈልጋለሁ።

ለ15 ዓመታት በትጋት ምድራዊ ህይወትን አጠናሁ። እውነት ነው በርግጥ ምድራችሁንም ሰዎንም አላየሁም ሆኖም ከመፅሀፍቶቻችሁ ምርጥ ወይኖቻችሁን ጠጣሁ፣ ሙዚቃችሁን ዘፈንኩ፣ በጫካዎቻችሁ አጋዘንና አውሬዎችን አደንኩ፣ ሴቶችን አፈቀርኩ ቆንጆ ሴቶን የባለቅኔዎቻችሁ ድንቅ ስራዎች እንዳደምጥ ተንሳፈው መጥተው ድንቅ ወጎችን በጀሮዬ ሲያንቆረቁሩልኝ በስካር ጢምብራዬ ይዞራል። በመፅሀፍቶቻችሁ የአርቤዝ እና የሞንት ብላንክ ተራራ ጫፎች ላይ ወጣሁ ከዚያ ላይ ሆኜም የማለዳ አበቦችን በምሽት የጀምበር መጥለቅን ውቅያኖሱን እና የተዘረጉ የተራራ ሰንሰለቶችን ወርቅማ ሪዝ ብርሃን ደምቀው አየሁ። እዚያው ላይ ሆኜ እንደምን ከበላዬ የመብረቁ ብልጭታ ደመናውን እየገመሰ እንደሚወረወር ተመለከትኩ። አረንጓዴ ዳኖችን፣ መስኮቶች፣ ወንዞችን ሃይቆች ከተሞችን ተመለከትኩ የመንፈሳዊ አባቶቻችሁን የማንቂያ ደወል ድምጻቸውን ሰምቻለሁ፣ ስለእግዚአብሔር ሊነግሩኝ የሚወጡትን የተዋቡ ዲያቢሎሶች ዳሰስኩ በመፅሀፍቶቻችሁ ውስጥ እራሴን መጨረሻ የሌለው ጥልቅ ውስጥ ከትቻለሁ፣ ተአምራትን አድረጌያሁ ከተሞችን አጋይቼ አውድሜያለሁ አዲስ ሃይማኖት ሰብኬያለሁ ሀገራትን ሁሉ ገዝቻለሁ. . .

“መፅሀፍቶቻችሁ ጥበብን ሰጡኝ። ያ ሁሉ ተዝቆ የማያልቅ የማያረጁ ክፍለ ዘመናት የተፈጠሩ የሰው ልጆች ሃሳቦችን ሁሉ እዚህ የራስ ቅሌ ውስጥ ባለ ትንሽ ልፍጭ ውስጥ ታጭቀዋል። ከሁላችሁም የተሻልኩ ብልህና ጠቢብ እንደሆንኩ አውቄዋለሁ።

“ስለዚህ መፅሀፍቶቻችሁን ናቅኳቸው፣ የአለም በረከቶችንና ጥበቦችን በሙሉ ንቄያቸዋለሁ። ሁሉም ነገር ቀሪ፣ ተሰባሪ የማይጨበጥ ህልምና እንደማዕራዥ ምናባዊ ነው። ምንም ኩሩ ጠቢብ እና ቆንጆ ብትሆኑ ሞት እንደ ምድር አይጠመጎጥ ከምድረገፅታላይ ጠርጎ ያጠፋችኋል፣ መጪው ትውልዳችሁ ታሪካችሁ የማይሞተው የጠቢባኖቻችሁ ምጡቅ ስራ የልጦ እንዲረጋ ዝቃጭ ሆኖ ከምድራዊው አለማችሁ ጋር ተቃጥሎ ይጠፋል።

“አብዳችሁ በተሳሳተ መንገድ ሄዳችኋል ውሸትን እንደ እውነት መልክ ጭፍንነት እንደ ቁንጅና ወስዳጅሁታል። እናንተ በድነገት የበለስና የብርቱካን ዛፎች እንቁራሪትና እንሽላሊት በፍራፍሬዎቸው ፈንታ ቢያፈሩ ታደንቋቸዋላችሁ ፅጌሬዳ አበባ ያላበው ፈረስ ብቻ ብታመነጭ ትደመጣላችሁ። እኔም በናንተ ገነትን በምድር ለውጣችሁ በሸጣችሁ እንዲሁ ነው ምደመምላችሁ እናንተን ማወቅም አልፈልግም።

ያልኩትንም ንቀቴን አሳያችኋለሁ እናንተ የምትኖሩለትን እኔም በአንድ ወቅት ገነትን መውረስ የሚመስለኝን አሁን የናቅኩትን ሁለት ሚሊዮኑን ትቼላችኋለሁ። ገንዘቡ ላይ ያለኝን መብት ለማጣት ስል ከተስማማንበት ጊዜ አምስት ደቂቃ በፊት እወጣለሁ በዚህም የተስማማሁበትን ግዴታዬን አፈርሳለሁ።

ይህን እንዳነበበ የባንኩ ኃላፊ ወረቀቱን መልሶ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠና የእንግዳውን ሰው ጭንቅላት ስሞ ማንባት ጀመረ። ከክፍሉም ወጥቶ ሄደ። መቼም ቢሆን በአክስዮን ገብያው ላይ ከባድ ኪሳራ ሲደርስበት እንኳን እንዲህ እንዳሁኑ እራሱን የመናቅ ስሜት ተሰምቶት አያውቅም። ቤቱ እንዲገባ አልጋውላይ ቢንጋለለልም የሚተናነቀው እንባ ለረጅም ጊዜ ከመተኛት ከለከለው. . .

     በንጋታው ጠዋት ምስኪኑ ዘበኛ እየሮጠ በመምጣት ክፍሉ ውስጥ ተዘግቶበት ይኖር የነበረው ሰው ተንጠላጥሎ በመስኮት ሾልኮ ወደ አትክልቱ ክፍል መግባቱን ማየታቸውን ነገረው። ወደበሩ ወጥቶ ጠፋ አለው። የባንክ ኃላፊው በፍጥነት ከአሸክሩ ጋር ወደ እስር ክፍሉ በመሄድ የእስረኛውን ማምለጥ አረጋገጠ።የሚያስፈልግ ሃሜትን በማስወገድ እስረኛው መብቱን የተወበትን ወረቀት ከጠረጴዛው ላይ አንስቶ ወሰደና ወደ ቤቱ ተመልሶ ካዝናው ውስጥ ቆለፈበት።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
9377 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1076 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us