ምንጩ ያልታወቀ ሀብት

Wednesday, 28 May 2014 13:27

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


-    ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርቶ መገኘት የሚያስከትለው ወንጀል ኃላፊነት

-    የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ግዴታዎች

-    የጥቅም ግጭትና የሚመለከታቸው የመንግስት ሰራተኞች ግዴታ

-    እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የሚመለከት ክርክር

 

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምናወጋው ምንጩ ስላልታወቀ ሀብትና ስለሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነት ነው። እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰ አንድ የወንጀል ክስን በማሳያነት እናነሳና ሕጎቻችን በጉዳዩ ላይ የሚሉትንም እናጣቅሳለን።

ከየት አመጡት?

ይሄ ጥያቄ መጠየቅ አለበት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል። የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ የፀረ ሙስና ኮሚሽንም መጀመሪያ ከዚህ ጥያቄ በመነሳት ነበር ሶስት ሰዎች ላይ ክስ የመሰረተው። አቶ ታረቀኝ ተክሉና ወ/ሮ እማዋይሽ ገብረመስቀል ባልና ሚስት ሲሆኑ አቶ አብይ ታመነ ደግሞ የወ/ሮ እማዋይሽ ወንድም ናቸው። እነኚህ የቤተሰብ አባላት የሚተዳደሩት በአቶ ታረቀኝ ገቢ ሲሆን አቶ ታረቀኝ ከሰኔ 1/1986 በ182 ብር ወርሃዊ ደምወዝ ተቀጥረው እስከ መጋቢት 2000 ዓ.ም ድረስ በእርከን ጭማሪና በደረጃ እድገት ደምወዛቸው በወር ብር 928 ደርሶ ነበር። የእነኚህን ሶስት ሰዎች ሀብት ለመገመት እና ለማነፃፀር ነው። ሕጋዊ ገቢያቸው የተጠቀሰው አቶ ታረቀኝ በሀዋሳ ዙሪያ የወንዶገነት ወረዳዎች ታክስ አስተዳደር ጽ/ቤት የእለት ገቢ ሰብሳቢ ናቸው። ባለቤታቸው ወ/ሮ እማዋይሽ ቤት እመቤት የእሳቸው ወንድም ደግሞ ሰራም ሆነ ገቢ የሌለው ተማሪ ነው። ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል? ትሉ ይሀናል የሚገርመው አጠቃላይ አቶ ታረቀኝ ከ1986 እስከ 2000 ዓ.ም ያገኙት የነበረው ገቢ ሰባ ሺህ ብር (70,000) ሆኖ ሳለ በስማቸው የተገኘው ንብረት ብር 3,602,00.84 (ሶስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሁለት ሺህ ከሰማንያ አራት ሳቲም መሆኑ ነበር። G+1 መኖሪ ቤት የከተማ ቦታ የተለያዩ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሲኖሯቸው G+1 ቤቱን የተገኘው ከሊዝ ደንብና መመሪያ ውጭ በአቶ አብይ ስም አቶ ታረቀኝ ረጅም እጃቸውን በመጠቀም ቦታውን ተመርተው ከየት መጣ እንዳይባል ሕግ የማያውቀውን የአባቱን ሀብት እንደወረሰ በማስመሰል የሀሰተኛ የባለቤትነት ማረጋገጫ አምጥተዋል። ቤቱ የአቶ ታረቀኝና የወ/ሮ እማዋይሽ ሆኖ ሳለ “ከየት መጣ?” የሚለውን ጠያቂ አፍ ለማስያዝ ምንም በሌለው በሚስትየው ወንድም በአቶ አብይ ስም አስመዘገቡት።

የደቡብ ክልል የፀረ ሙስና ኮሚሽን እነዚህንና ሌሎች እውነታዎችን ካጣራና ተገቢ ማስረጃዎችን ከያዘ በኋላ ነበር ጉዳዩ ከየት አመጡት ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሆኖ ስላላገኘው ግንቦት 24 ቀን 2001 ዓ.ም በግብርአበርነትና በልዩ ተከራይነት ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የማፍራት የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ የቀረበው።

ሶስቱ ተከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ አቶ ታረቀኝ፣ 2ኛ ተከሳሽ ወሮ እማዋይሽ 3ኛ ተከሳሽ አቶ አብይ የቀረባበቸውን ክስ ወንጀሉን አልፈፀምንም ብለው በመካዳቸው ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን አቅርቦ አሰማ። ተከሳሾችም መከላከያ የሚሏቸውን ማስረጃዎች አቀረቡ። ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የሀዋሳ ከተማ ክፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል ብሎ በነፃ አሰናበታቸው። የዐቃቤ ሕግ ከየት አመጡት የሚል ጥያቄ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ባየው ፍ/ቤትምላሽ ሳያገኝ ቀረ።

ዐቃቤ ሕግ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረበ ጠ/ፍ/ቤቱም ዐቃቤ ሕግንም ሆነ ተከሳሾችን አከራክሮ ጉዳዩን ከሰማ በኋላ “የለም የሰር ፍ/ቤት ውሳኔ ስህተት ነውመሻር አለበት” ብሎ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር ተከሳሾችን ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው 1ኛ ተከሳሽ አቶ ታረቀኝ በሌላ ወንጀል እድሜ ልክ እስራት ስለተቀጡ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት 2ኛና 3ኛ ተከሳሶች ደግሞ እያንዳንዳቸው በአንድ አመት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ምንጩ ያልታወቀው ሀብታቸውም በመንግስት እንዲወረስ ወሰነ።

ተከሳሾች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ስላላገኙ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ ሲሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረቡ። የአቤቱታቸው ዋነኛ ፍሬ ሃሳብ የሀብት ምዝገባና ማሳወቂያ ስርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተዋል በሚል መቀጣታችንና ንብረታችን እንዲወረስ በመወሰኑ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የሚል ነበር።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተከሳሾችን የሰበር አቤቱታ ተቀብሎ ከዐቃቤ ሕግ ጋር አከራክሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ሕጉ ምን እንደሚል እንይ

ምንጩ ያልታወቀ ሀብት

በ1996 የወጣው የወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 419 ላይ ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ወይም የመንግስት ሰራተኛ የነበረ ሰው የሚኖረው ሀብት ንብረት የኑሮ ደረጃው አሁን ካለበት ወይም ቀድሞ ከነበረበት የመንግስት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ወይም ሲያገኝ ከነበረው ሕጋዊ ገቢ የበለጠ ከሆነ ከየት አመጣኸው ተብሎ እንደሚጠየቅ ይደነግጋል። ይህን ጥያቄ በአግባቡ እና በአሳማኝ ማስረጃ በመመለስ ለፍ/ቤት ካላስረዳ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ የሕጋዊ ገቢውና ያለው ሀብት ልዩነት በጣም በከባዱ ከሰፋ ደግሞ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም መቀጮ ይቀጣል።

ይህን ተጠያቂነት ለማምለጥ ክሱ ተጀምሮ በፍ/ቤት እየታየ ባለበት ጊዜ አንድ ሰው ከተከሳሹ ጋር ካለው ቅርበት ወይም ሌሎች ሁኔታዎች የተነሳ ለተከሳሹ ባለትዳር በመሆን አንድን ንብረት ወይም የገንዘብ ምንጭ እንዳያዝ ወይም ከተከሳሹ ከስጦታ እንዳገኘ ፍ/ቤቱ ካመነበት ጉዳዩን ለሌላ ማስረጃ ካላፈረሰ በስተቀር ንብረቱ ወይም የገንዘብ ምንጩ በተከሳሹ ይዞታ ስር እንደሆነ እንደሚቆጠር በአንቀፅ 419(2) ላይ ደንግጓል። ይህ ንዑስ አንቀፅ ምንጬ ያልታወቀውን ሀብት ለመሰወር በተለያዩ ዘመድ አዝማዶችና የቅርብ ሰዎች ስም ንብረቱን የማዛወር ማስተላለፍ ድርጊትን ውጤታማ እንዳይሆን ለማድረግ ያለመ ነው።

ይህ ድንጋጌ ብቻውን ግን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድና ምንጩ የማይታወቅ ወፍ ዘራሽ ሀብትን ለማድረቅ በቂ ባለመሆኑ ሚያዝያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም በሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት ተሿሚዎችና ኃላፊዎች ላይ ሀብትን የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታን የሚጥለው አዋጅ ቁጥር 668/2002 ወጥቷል።

በዚህ አዋጅ ላይ ሀብት የሚባለው ማንኛውንም የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ግዙፍነት ያለው ወይም የሌለው ንብረት ሲሆን የመሬት ይዞታነትም እዳንም ይጨምራል። አዋጁ ተፈፃሚነት በፌዴራሉ መንግስት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ተሿሚዎች ተመራጮችና የመንግስት ሰራተኞን የሚመለከቱ ሲሆኑ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ጭምር በኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ እና ተመጣጣኝ የስራ ደረጃ ያላቸው ፈቃድ የመስጠት የመቆጣጠር ግብር የመሰብሰብ ሥራ የሚያከናውኑ ሰራተኞች ዐቃቤ ሕጎች መርማሪዎችን እና የትራፊክ ፖሊስ እና ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው መመሪያዎች የሚወስኑ መስሪያ ቤት ሰራተኞችም ላይ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታዎችን ይጥላል።

በነገራችን ላይ ክልሎች የየራሳቸውን የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ አዋጆችን የሚያወጡ ሲሆን እያየነው ያለው ሕግ የሚመለከተው የፌዴራል መንግስቱ ስር ያሉትን እና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድርን ነው።

የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታው በአዋጁ ላይ በዝርዝር የተመለከቱት ተሿሚ ወይም ተመራጭ ወይም የመንግስት ሰራተኛ በአንቀፅ 4 መሰረት

-    በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ስር የሚገኝ ሀብትን እና

-    የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጮች የማሳወቅና የማስመዝገብን የሚያጠቃልል ነው።

በግል በአስመዝጋቢው ስም ብቻ ያለውን ሀብት ሳይሆን ግዴታው የቤተሰብንም ስለሚመለከት አዋጁ ለአንቀፅ 2(7) ላይ ቤተሰብ የሚባው የአስመዝጋቢው የትዳር ጓደኛ ወይም በሥሩ የሚተዳደር እድሜው 18 ዓመት ያልሞላው ልጁን እንደሚያካትትና ጋብቻ ሳይፈፅም ከአስመዝጋቢው ጋር እንደባልና ሚስት አብሮ የሚኖር ሰው እና የጉዲፈቻ ልጁም በቤተሰብ ስር ይካተታሉ። ስለዚህ የማስመዝገብና የማሳወቅ ግዴታው በነዚህ የቤተሰብ አባላት ስም የሚገኘውንም ሀብት ንብረት ያመለክታል።

በሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ግዴታው ውስጥ የማይካተቱ ንብረቶች በአዋጁ አንቀፅ 5 መሰረት

-    በውርስ ተገኝቶ በጋራ የተያዘና ለወራሾች የግል አገልግሎት የሚውል ንብረት

-    የቤት እቃዎችና የግል መገልገያዎች

-    ከጡረታ የሚገኝ ገቢ

ሲሆኑ በውርስ የተገኘ ገቢን በተመለከተ በጋራ ተይዞ የነበረ ከሆነ የውርስ ክፍፍል ለወራሾች መካከል ሲደረግ ክፍፍሉ እንደተደረገ አስመዝጋቢው በውርስ የሚያገኘው ድርሻ ተለይቶ ታውቋልና በውርስ ያገኘሁት ብሎ ማስመዝገብ አለበት።

አዋጁ ከወጣበት ከሚያዝያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ያለው የ6 ወር ጊዜ ካለፈ በኋላ ባለው 6 ወር ማስመዝገብ ግዴታ ያለበት ሰው ግዴታውን መወጣት እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፤ አዲስ ተሿም፣ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሠራተኛ ደግሞ ከተሾመበት፣ ከተመረጠበት ወይም ከተቀጠረበት ቀን ጀምሮ ባለው አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ ማስመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ አንቀፅ 7(2) ላይ ተደንግጓል።

አንዴ ሀብቱን ያስመዘገበ አስመዝጋቢ ደግሞ ሀብቱን የሚያስመዘግበው በየሁለት አመቱ ሲሆን የበጀት አመቱ በተጠናቀቀ በ30 ቀናት ውስጥ የድጋሚ ምዝገባውን ወይም የምዝገባ እድሳቶችን ግዴታውን መወጣት አለበት። ምናልባት በተለያዩ ሁኔታዎች ለመመዝገቢያ የተቀመጠው ጊዜ ያልበቃው ሰው ጊዜው ለተወሰኑ ቀናት እንዲራዘምለት የምዝገባውን በኃላፊነት ለሚያከናውነው ለፌዴራል የስነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። በተቀመጠው ጊዜ ያላስመዘገበ ሀብት አስመዝጋቢ በአንቀፅ 9 መሰረት ብር 1000 መቀጫ ከፍሎ ማስመዝገብ ይችላል።

የምዝገባ ግዴታው የሚመለከተው በሥራ ላይ ያለውን የሀብት አስመዝግቢ ብቻ ሳይሆን በጡረታም ሆነ በማንኛውም ምክንያት አገልግሎቱን የሚያቋርጥ ሰራተኛም አገልግሎቱ በተቋረጠ በ30ቀናት ውስጥ ለሚመለከተው የስነ-ምግባር መከታተያ ሀብቱን ማሳወቅ ያለበት ሲሆን ይህ ከስራ ከተሰናበተም በኋላ ያለበት ሀብቱን የማሳወቅ ግዴታ የመጨረሻ የሚሆነው ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ ለኮሚሽኑ ከስራው የተሰናበተው አስመዝጋቢ ሀብቱን ሲያሳውቅ ነው።

ከላይ በተመለከትነው መልኩ አዋጁ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምዝገባው የሚመለከታቸው አስመዝጋቢዎችና መመዝገብ ያለበት ሀብት ሳይመዘገብ ከቀረ ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር በአዋጁ አንቀጽ 13 መሰረት በወንጀል ሕግ አንቀፅ 419(2) ላይ እንደተቀመጠው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ተደርጎ ይቆጠራል። የወንጀል ኃላፊነትም ያስከትላል።

በዚህ አዋጁ ላይ ከሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ በተጨማሪ የጥቅም ግጭትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ተካተዋል። በአዋጁ አንቀፅ 14 መሰረት ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሰራተኛ የተሰጠውን ኃላፊነት ማዋል ያለበት የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሆን በስራው አጋጣሚ ያገኘውን ህዝብ እንደያውቀው ያልተደረገ መረጃንም በግል ጥቅሙ ማዋል የለበትም።

በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 15 ላይ ማንኛውም ተሿሚ ተመራጭ ወይም የመንግስት ሰራተኛ የመወሰን ሥልጣኑን የሚፈታተን ወይም የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ስጦታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ መቀበል የለበትም። ሆኖም ግብዣውን ወይም ስጦታውን ያለመቀበሉ በስራ ግንኙነት ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ ካገኘው መቀበል ይችላል። ሆኖም የተቀበለውን ስጦታ አግባብ ባለው የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም መንግስት የልማት ድርጅት ገቢ ማድረግ ወይም ግብዣውን ለኮሚሽኑ ለሚመለከተው ክፍል የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበታል።

ሌላው ደግሞ ይህ የማስመዝገብ ግዴታ የተጣለባቸው ሰራተኞች በራሳቸው ወይም በቅርብ ዘመድ የግል ጥቅም መሀከል ግጭት ሊያስከትል የሚችል ጉዳይ ሲገጥማቸው በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ወይም አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ከኃላፊነቱ ጋር የማይጣጣምወይም ታማኝነቱን ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ማንኛውንም ድርጊት ከመፈፀም መቆጠብ እና ሁኔታውን ለሚመለከተው የበላይ ኃላፊ ማሳወቅ እንዳለበት በአዋጁ አንቀፅ 16 ላይ ተደንግጓል።

የጥቅም ግጭትን በተመለከተ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በበላይ ኃላፊው ሲጠየቅ ጥፋተኛ መሆኑን ባይፋ አምኖ ይቅርታ የመጠየቅ ወይም እራሱን ከኃላፊነት የማግለል ግዴታ እንዳለበት በአንቀፅ 17 ላይ ተቀምጧል። በተጨማሪ አስመዝጋቢው ሥራ ከለቀቀ እስከ ሁለት አመት ድረስ ሲቆጣጠራቸው ከነበረው ሰዎች ጋር ጥቅም የሚያስገኙ ሥራዎችን መስራት የለበትም። የአስመዝጋቢው የቅርብ ዘመዶች የሚባሉት በአዋጁ አንቀፅ 2(8) መሰረት ወላጆች፣ ተወላጆች፣ እህት ወንድሞችና ሌሎች እስከ ሶስተኛ ደረጃ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያላቸውን ዘመዶች ናቸው። እነኚህን የጥቅም ግጭትን የሚመለከቱ ግዴታዎችን አለመወጣት ሰራተኛው ላይ በአንቀፅ 19 መሰረት ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ ሊያስወስዱበት ይችላሉ።

በነገራችን ላይ ይህን አዋጅ መጣሱን ጥቆማ በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን በጥቆማው መሰረት መረጃው በወ/ሕ/አ 419(2) መሰረት የሀብት መወረስ ውሳኔ ካስገኘ ከተወረሰው ሀብት ላይ 25 በመቶ ለጠቋሚው ይሰጣል።

ሰበር ምን አለ

በመግቢያችን ላይ ያነሳነውን እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰውን ክርክር የመረመረው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ.ቁ 67411 ታህሳስ 30 ቀን 2004 በዋለው ችሎት የሀብት ማሳቅና ንብረት ማስመዝገብ ሥርዓት አለመዘርጋቱ ምንጩ ያታወቀ ሀብት ይዞ መገኘትን በሚመለከተው በወ/ሕ/አ 419 ተጠያቂ ከመሆን አያድንም በማለት ሶስቱ ተከሳሾች አቶ ታረቀኝ፣ ወ.ሮ እማዋይሽ፣ አቶ አብይ ላይ የተሰጠው የእስራት ውሳኔ እና ያካበቱት ንምጩ ያልታወቀ ሶስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሁለት ሺህብር የሚያወጣ ንብረት ተወርሶ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን በመወሰኑ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም ብለው ውሳኔውን አፅንቶታል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
7824 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1060 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us