የሕግ ተፈጥሮ ፍልስፍናዎች

Wednesday, 04 June 2014 12:21

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ሕገ-ተፈጥሮ ምንድን ነው

-    የተለያዩ የዓለማችን ፈላስፎች ስለ ሕግ እና ስለ ተፈጥሮ ምን አሉ

             

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምናወራው የሕጐች ሁሉ ምንጭ ነው ስለሚባለው ስለ ሕገ ተፈጥሮ ነው። የተለያዩ የዓለማችን ሊቃውንት በየዘመናቱ የሰነዘሯቸውን ፍልስፍናዎች እያነሳን ሕግ ምንድን ነው? ከየት መጣ? ለምን እንገዛለታለን? እያልን እንፈላሰፋለን።

የሆነ ድርጊት ወይም ነገር አይታችሁ ምን ያህል ጊዜ “ይኼማ ትክክል አይደለም?”፣ “ይሄማ ተፈጥሮአዊ አይደለም” ብላችሁ ታውቃላችሁ? ውርጃ ሕገወጥ ነው፣ የተመሳሳይ ጾታ ጾታዊ ግንኙነት ክልክል ነው የሚባልበት መሠረቱ ምንድን ነው? አንድን ነገር ትክክል ነው የሚባልበት መሠረቱ ምንድን ነው? አንድን ነገር ትክክል ወይስ ስህተት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን የምንመዝንበት ወጥ የሆነ መስፈሪያስ ይኖር ይሆን? ካለስ እንዴት ብለን ነው የምንደርስበት?

እነኚህ ግብረገባዊ ጥያቄዎች ከአሪስቶትል ጀምሮ የነበሩ የግብረገብ ፈላስፋዎችን ሲያከራክሩ የኖሩ ናቸው። አንድን ነገር ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ብለን የምንመዝንባቸው ግብረገባዊ ጥያቄዎች የእለት ተእለት ህይወታችን የሚነሱ ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካዊም ሆነ የሕጋዊም ክርክሮች አካል ናቸው። ከተባበሩት መንግስታት ምስረታ በኋላ ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶችና ስምምነቶች ውስጥ ተካተዋል። አብዛኞቹ መነሻቸው ሕገ ተፈጥሮ ሲሆን፤ በውስጣቸውም ያለው ግብረገባዊ እውነታ መሆኑን አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ለመከተል እንደርስበታለን።

“ሕገ ተፈጥሮን ደህና አድርጐ ለመግለፅ” ይላል ጆን ፊን የተባለው የሕገ ተፈጥሮ አቀንቃኝ የሕግ ባለሙያ “በሕግ እና በግብረገብ መካከል ያለው የጋራ ነጥብ ስያሜ ነው” ይለዋል። አባባሉን በቀላል አነጋገር ለመግለፅ “ተፈጥሮአዊ የሆነው ነገር እሱ መሆን ያለበት ነው ማለት ነው። ‘ሕገ ተፈጥሮና ተፈጥሮአዊ መብቶች’ በተሰኘው ሰፊ ተቀባይነት ያገኘበት መፅሐፈ ጃንፈን የሕግን ምንነት ለመግለፅ ስንሞክር በዚያም አለ በዚህ “መልካም ነገር” ምንድን ነው የሚለውን ነው የምንገልፀው” ሲል ያሰምርበታል።

ሕግን እንደ ማኅበረሰባዊ ተቋም ለመገምገም በዘመናዊ የሕግ ፍልስፍና እንደሚጠቀሰውና ማንኛውም የማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናት እንደሚያረጋግጠው አንድን ማኅበራዊ እውነታ የሚያጠና ተመራማሪ እራሱ በግምገማው ሂደት ውስጥ ተሳትፎ ለማኅበረሰቡ ወይም በአጠቃላይ ለሰብአዊ ፍጡር መልካም ወይም ጥሩ የሚሆነው ምንድን ነው የሚለውን ቅድሚያ ካልመዘገበ በቀር ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

መልካም ወይም ጥሩ ምንድነው የሚለውን ለመለየት ነባራዊውን ሁኔታ ከምንመለከትበት በተለየ መልኩ የህሊናችንን ሚዛን መጠቀም አለብን። በሌላ አባባል ተፈጥሮንና የሕገተፈጥሮን ተፅዕኖ መረዳት ከፈለግን የሚያስገኘው ውጤት የተለየ አመክንዮ እንደሚሆን ማወቅ ግድ ይለናል።

የጥንታዊት ሮማ የሕግ ሊቅ ሲሲሮ ማንኛውም የሕገ ተፈጥሮ ፍልስፍና የሚኖሩትን ሦስት ነገሮች ለይቷል፡-

“እውነተኛ ሕግ ምክንያቱ ትክክለኛና ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ ነው። ተግባራዊነቱም ዓለም አቀፋዊ የማይለወጥ እና ዘላቂ ነው…. ይህን ሕግ ለመለወጥ መሞከር ሐጢያት ነው። አንዱን ክፍሉን እንኳን ለመሻር መሞከር አይፈቀድም። ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረግማ አይቻልም …. ፈጣሪ አምላክ ነውና የዚህ ሕግ ፀሐፊ፣ ሕጉን የሰጠንም የሚያስፈፅመውም ዳኛ እሱ ብቻ ነው።”

ሲሴሮ ሕገተፈጠሮ ዓለም አቀፋዊ የማይሞትና ከሕጐች ሁሉ በላይ መሆኑን የሚታወቀውም በምክንያታዊ አስተሳሰብ መሆኑን ነው ያሰመረበት። ዘመን አይሽሬው ሕገተፈጥሮ እሳቤ አብዮትን እና ለአብዮተኞች የሚሰጠውን ምላሽ ተገቢነት ማሳያ ሲሆን ኖሯል። በ6ኛው ክ/ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ግሪካውያን የሰዎች ሕጐች ሁሉንም ነገር ለሚቆጣጠረው የእጣ ፈንታ ኃይል ያላቸውን ጥቅሞች ይገልፁ ነበር። ይህ ወግ አጥባቂ አመለካከት በቀላሉ የመደብ ወይም የደረጃ ልዩነትንም ለማጉላት ጥቅም ላይ ውሏል። በ5ኛው ዓመተ ዓለም ላይ ግን በሰዎች ሕግና በተፈጥሮ ሕግ መካከል ቅራኔ መሞት እውቅና ተሰጥቶት ነበር።

አሪስቶትል ለሕገ ተፈጥሮ ብዙም ትኩረት ባይሰጥም በተፈጥሮ ፍትሕና በሰዎች ስርዓት በሚሰጥ ፍትህ መካከል ያለውን ልዩነት ቢያስቀምጥም፤ በሕገተፈጥሮ ፅንሰ ኀሳብ የተሰሙት ግን እና የሰው ልጅ እራሱን የመቆጣጠር ኃይሉ ትልቁ ፀጋው ነው የሚለውን አስተምህሮት የሚያላምዱ የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፎች ነበሩ። ለነሱ ተፈጥሮ ማለት በምክንያታዊነት ማሰብ ነው። የዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች ከሲሴሮ ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ ቢያንስ በንድፈ ኀሳብ ደረጃ ከምክንያታዊነት ጋር የማይጣጣሙ ሕጐች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስተምረዋል።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሕገተፈጥሮ ፍልስፍና ጐልቶ እንዲወጣና የዛሬውን ቅርፅ እንዲይዝ ሁነኛ ሚና ተጫውታለች። “አስቀድሞ በ5ኛው ክ/ዘመን ቅዱስ አውግስቶስ አገር ካለ ፍትህ ግዙፍ የዘራፊዎች ቡድን እንጂ ሌላ ምንድን ነች?” ሲል ጥያቄ ቢያነሳም ዋናውን የሕገተፈጥሮን ነጥብ ያስቀመጠው ግን ከ1225 እስከ 1274 የኖረው ቅዱስ ቶማስ አኩያንስ ነበር።

ከክርስትና አስተምህሮቶች አንፃር ስለሕገተፈጥሮ በፃፈው መፅሐፍ ቅዱስ ቶማስ አኩያን አራት አይነት ሕጐችን ለይቶ አስቀምጧል። የመጀመሪያው ዘላለማዊ ሕግ ሲሆን፤ በፈጣሪ ብቻ የሚታወቅ መለኰታዊ ምክንያት ያለው ነው። ሁለተኛው ሕገተፈጥሮ ሲሆን ይህ ሕግ ደግሞ ማሰብ የሚችሉ ፍጡራን በዘላለማዊ ሕግ ውስጥ ምክንያታዊ አስተሳሰባቸውን በመጠቀም ተሳትፈው የሚደርሱበት ነው። ሌላኛው መለኰታዊ ሕግ ሲሆን በቅዱሳት መፅሐፍት የተገለፀው ሲሆን፤ አራተኛው ደግሞ የሰዎች ሕግ ሲሆን በምክንያታዊነት ተደግፎ ለማኅበረሰቡ የጋራ ጥቅም ሲባል የተደነገገ ነው።

እነኚህ የአኩያንስ ንድፈ ኀሳቦች ትኩረትን መሳባቸው አልቀረም። ከሕገተፈጥሮ ጋር ወይም ከመለኰታዊ ሕግ፣ ጋር የማይጣጣም ሕግ ከነጭራሹ ሕግ አይደለም። ወይም ትክክል ያልሆነ ሕግ ሕግ አይደለም ብሎ ያስቀምጠዋል። ይህ ማለትም ከሕገተፈጥሮን መስፈርት ጋር የሚቃረን ሕግ ግብረገባዊ የማስገደድ አቅም ያንሰዋል። መንግስት ትክክል ያልሆኑ ምክንያታዊነት የሚጐላቸው ሕጐችን በማወጅ ስልጣኑን አለአግባብ ከተጠቀመ የግብረገባዊ የበላይነት ስለሚያንሰው ሕዝቡን የመግዛት መብቱን አሳልፎ ሰጥቷል። እንዲህ አይነት ሕግጋትን አኩያንስ “የሕጐች ንቅዘት” ብሎ ቢጠራቸውም ሁሌም ግን ትክክል ያልሆኑ ሕጐችን አለመገዛትን የሚደግፍ አይመስልም። ምክንያቱም መሪዎች ትክክለኛ ያልሆኑ ሕጐችን ሲያወጁ ሕዝቡ በነኛ ሕጐች የመገዛት ግዴታ እንደሌለበት ቢገልፅም “እምቢታው መሆን ያለበት በተወሰኑ የስልጣን ቅሌትን ለማስወገድ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ማለትም ለሌሎችም ምሳሌ በሚሆኑ የስነ-ምግባር ዝቅጠቶችን እና ሌሎች የህዝብን ሰላም በሚያደፈርሱ ልዩ ጉዳዮች ላይ በቻ ነው” ሲል ያሰምርበታል።

በ17ኛው ክ/ዘመን በአውሮፓ ያቆጠቆጠው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚገቡ ሕጐች መሰረታቸው ይኸው ሕገተፈጥሮ ነው። ሁጐ ደግሮትስ (1583-1645) ይነሳል። ፈጣሪ አምላክ እንኳን ባይኖር የሕገተፈጥሮ ይዘት ያው እንደነበረው ነው የሚለው ገሮትየስ ሕገ ተፈጥሮ ለዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት መሠረት እንዲሆን የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በግሮትየስ አባባል የተወሰኑ ነገሮች ከመሠረታቸው ስህተት ናቸው። ፈጣሪ አምላክ ቢደነግጋቸውም ባይደነግጋቸውም፣ ምክንያቱም እራሱ ፈጣሪ እንኳን የማይሆነውን ሁለት ሲደመር ሁለት አራት እንዳይመጣ ማድረግ ስለማይችል ነው በሚለው አገላለፁ።

የሕገ ተፈጥሮ ፅንሰ ኀሳብ ወደ እንግሊዝ ብቅ ያለው በ18ኛው ክ/ዘመን በሰር ዊልያም ብላክስቶን ስራ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ሕጐች ምንጫቸው ሕገ ተፈጥሮ መሆኑን ይገልፃል። ምንም እንኳን አኩያንስ ከሕገተፈጥሮ ወግ አጥባቂ እይታው ጋር ተያይዞ ቢነሳም የሕገተፈጥሮ መርሆዎች ግን የአሜሪካንና የፈረንሳይ አብዮቶችን ተቀባይነት እንዲኖራቸው ጥቅም ላይ ውሏል። ነባሩን ሕግ የጣሱ አብዮተኞች ተፈጥሮአዊ መብታቸውን ለመጠቀም ነው በሚል በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ላይ የተቀሰቀሰው የአሜሪካ አብዮት በ1776 በታወጀው የነፃነት አዋጅ ላይ “ህይወት፣ ነፃነትና ደስታን መፈለግ ሁሉም ሰዎች እኩል በመሆናቸው ከፈጣሪያቸው እነኚህን የማይገፈፉ መብቶች ተጐናፅፈዋል። ይህም በራሱ ማረጋገጫ የማይፈልግ እውነት ነው” ሲል የወጣው አዋጅ የተወሰኑ ተፈጥሮአዊ መብቶችን የሚያጣቅስ ነበር።

ሕገ ተፈጥሮ በተለያዩ የፖለቲካ መብቶችንና ግዴታዎችን እንደ ማኅበራዊ ውል በሚያዩ አቀንቃኞችም ዘንድ ጥቅም ላይ ውሏል። በትክክለኛው የሕግ ውል ነው ባይባልም አንድ ሰው በሌላው ሰው የፖለቲካ ኃይል ስር ሊገባ የሚችለው ፈቃዱን ሲሰጥ ብቻ ነው የሚለውን ኀሳብ ያንፀባርቃል።  

ተፈጥሮአዊ መብቶች

ቶማስ ሆብስ (1588 - 1674) የሚታወሰው ህይወትን “ለብቻ የተገለለች፣ ደሀ፣ የማታስደስት በጭካኔ የተሞላተና አጭር” ናት ብሎ በመግለፁ ቢሆንም፤ ይህን ባለበት ሌቪታን በተሰኘው ዝነኛ መፅሐፍ ውስጥ ይህ የህይወት ገፅታ ከማኅበራዊ ውለ በፊት የነበረ መሆኑን ገልጿል። ሕገ ተፈጥሮ ራስን መጠበቅን ያስተምረናል ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ደግሞ ሕግ እና መንግሰት ያስፈልገናል። በማኅበራዊ ውል ውስጥ ደግሞ ስርዓት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲባል ተፈጥሮአዊ መብቶቻችንን አሳልፈን እንሰጣለን በማለት ከማኅበራዊ ውል መንግስትና ሕግ ከተፈጠረ በኋላ ቀድሞ የነበረው አስቀያሚ የህይወት ገፅታ እንደማይኖር ያሰምርበታል። የሆብስ ፍልስፍና በተወሰነ መልኩ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን የሚደግፍ ነው። ምክንያቱም ከፍትህ በላይ ሰላምና ፀጥታን ያስቀድማል። በተለይ ደግሞ እሱም እራሱም እንደሚያምነው በንድፈ ኀሳቡ ውስጥ የአብዮት አመፅን ጨቋኝ መንግስታት ላይ እንኳን ቢሆን አግባብነት የለውም በሚል ያጣጥለዋል።

ሊሆብስ ማንኛውም የምናደርገው ነገር መልካምነቱ ወይም ከራስ ወዳድነት የፀዳ መሆኑ ቢደበቅም እንኳን የምናደርገው ለእራሳችን ብለን ነው። በመሆኑም በልግስና የምሰጠው ስጦታ በረግጥም ማድረግ በመቻሌ መደሰቻ ዘዴ ነው። ትክክለኛ የሰዎች ድርጊት ግብረገባዊነትም ጭምር የማይቀር እራስ ወዳድነታችን እንዳለባቸው መታወቅ አለበት ሲልም ይሞግታል። ሌቪታን በተሰኘው መፅሐፍ ከመንግስት ምስረታ በፊት በተፈጥሮአዊ ሁኔታችን ባህሪያችን እንዴት እንደነበር ይጠይቃል። በመሰረታዊ ነገሮች በአእምሮና በአካል እኩል ነበርን ደካማው እንኳን የሚስማማውን መሳሪያ ለመጠቀም ጠንካራውን የመግደል አቅም ያገኛል። ይህ በእኩልነት የመገዳደር አቅም ደግሞ የአለመግባባት ፀብን ያመነጫል። ለፀብ የምናዘነብለው በሦስት ዋነኛ ምክንያቶች ነው ነው የሚለው ሆብስ፤ ምክንያቶቹን ውስን የሆነውን ቁሳዊ ሀብት ባለቤት ለመሆን የሚደረግ ፉክክር የመጀመሪያው ሲሆን፤ አለመተማመንና የክብር ጉዳይ ደግሞ ተከታዮቹ ናቸው። የነበረንን የኃይል ተሰሚነት ጠብቀን በማቆየት በጥላቻ እንጠመዳለን በማለት ያብራራቸዋል። በዚህ ያለመግባባት ዝንባሌያችን የተነሳም ሁላችንም በማያባራ ጦርነት ውስጥ ካለ ግብረገብ በፍርሃት ስለምንኖር ጦርነቱ እስኪያበቃ ሁላችንም የሌላውን ህይወት ላይ ሳይቀር ሁሉም ነገር ላይ መብት ይኖረናል ሲል ይደመድማል። ሆብስ ለሰው ልጅና ጥቅም እና በማኅበራዊ ስምምነት ሲባል የሕገ ተፈጥሮ ሊቃውንት የማይሞተው ሕገ ተፈጥሮ የሚሉትን ዓይነት ተመሳሳይ ሕግ ማውጣት ይቻላል። በመሆኑም ከአስፈሪው ተፈጥሮአዊ ሁኔታችን ለማምለጥ ሕገ ተፈጥሮ ያስፈልገናል። የመጀመሪያው ሕገ ተፈጥሮ ደግሞ ሰላም ነው ሲል ይደመድማል።

ሁለተኛው የተፈጥሮ ሕግ ደግሞ ለጋራ ጥቅም የተወሰኑ መብቶቻችን አለመጠቀም አሳልፈን መስጠት ሲሆን ይህም ሰላምን ለማግኘት ሲባል የሚከፈል ነው። ይህ ለጋራ ጥቅም መብቶችን ማስተላለፍ የግብረገባዊ ግዴታ መሰረት የሆነው ማኅበራዊ ውል ነው። ታዲያ ይህ ውል መገባቱ ብቻ ሰላምን አያረጋግጥም እንዲህ ያሉ ውሎች መከበርም አለባቸው።

ሦስተኛው የሆብስ የተፈጥሮ ሕግ ደግሞ ይህን ማኅበራዊ ውል ማስከበርን የሚመለከት ሲሆን፤ እኛ ሰዎች እራስ ወዳድ በመሆናችን ለግል ጥቅማችን ስንል ውሉን ልናፈርስ እንችላለን። ከአንተ ለመስረቅ የገባሁትን ውል ልጥስ የምችለው እንደማልያዝ እርግጠኛ ስሆን ነው። አንተም ይህን ታውቃለህ። ብቸኛው ይህን የእርስ በርስ ግዴታችንን እንዳንጥስ የሚከላከለው ደግሞ ለፖለቲካዊ የስልጣን ባለቤት ለሆነ አካል ውሉን የሚጥስን ሰው የመቅጣት ገደብ የለሽ ስልጣን ስንሰጠው ነው ሲል ይሞግታል። ይህም ቢሆን ራሱ የራስ ወዳድነታችን ተፈጥሮ ያመነጨው ነው እኛን የመቅጣት ስልጣን ያለው አካል እንድንፈጥር ያነሳሳን። ሆኖም እንዲህ አይነት የስልጣን ባለቤት ሉአላዊ አካል ሲኖር ብቻ ነው። ወጥ በሆነ መልኩ ነገሮችን ይህ ትክክል ነው ይህ ደግሞ ስህተት ነው ብለን መደምደም የሚያስችለን።

    የሰው ልጅ ተፈጥሮ ምክንያታዊነቱና ሕገ ተፈጥሮ ከሕጐች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚፈትሹትን የተወሰኑ ፈላስፎችን ሀሳብ ነው፤ በጥቂቱ የዳሰስነው። ሌሎቹን ደግሞ ሌላ ጊዜ እናነሳቸዋለን። ለዛሬ በዚህ ይብቃን።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
8067 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 997 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us