ስለዓለም አቀፍ ሕግ በጥቂቱ

Wednesday, 11 June 2014 13:35

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


-    የዓለም አቀፍ ሕግ ምንድን ነው?

-    ከሀገራት ሕግ በምን ይለያል?

-    የዓለም አቀፍ ሕግ አይነቶችና ዋና ዋና መገለጫ ባህሪዎቹ ምን ይመስላሉ?

-    ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሕግን የሚመለከቱ መሠረታዊ ነጥቦች


እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬው ትኩረታችን የሀገራችን ሕግ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሕግ ነው። በተለያየ አጋጣሚዎች የዓለም አቀፍ ሕግ ሲሰማ ሰምተናል። ለምሳሌ ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ ለሚነሱ ክርክሮች እኛም ግብፆችም ዓለም አቀፍ ሕግን እናነሳለን። ሌሎችም ከአንድ ሀገር ሕግ የዘለሉ ጉዳዮች ላይ የመገናኛ ብዙሃን ዓለም አቀፍ ሕጎችን ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያነሳሉ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ሕግ ምንድን ነው? ከአንድ ሀገር ሕግ ጋርስ በምን ይለያል? ባህሪውና ተፈፃሚነቱስ ምን ይመስላል የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ዓለም አቀፍ ሕግ ስለሚባለው ነገር መሠረታዊ ግንዛቤ የሚስጨብጡንን ነጥቦች እንመለከታለን።

ማጣቀሻዎቻችን ፒተር ማሊንዙክ በ1997 እ.ኤ.አ እና ማልኩም ኤን ሻው በ2007 በጉዳዩ ላይ የፃፏቸው መፅሐፍት ናቸው።

ዓለም አቀፍ ሕግ ምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ ሕግ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ጃርሚ ቤንታም የተባለው የሕግ ሊቅና ሪላስፍ እ.ኤ.አ በ1780 ዓ.ም ባሳተመው መፅሀፍ ነበር። ከዚያ በኋላ በ1840 ዎቹ ገደማ በእንግሊዝና በሮማውያን ቋንቋዎች የሲሴሮን ቆየት ያለ ሃሳብ በመጠቀም የሀገራት ሕግ በመባልም ይጠራ ነበር።

የሰው ልጅ ከዋሻ ውስጥ ተነስቶ እስካለንበት የኮምፒዩተር ዘመን ባደረገው ረጅም ጉዞ ውስጥ የሕግ ሃሳብ ዋነኛውን ሚና ተጫውቶአል። ይህ የሕግ ሃሳብ የሚያተኩረው ሰላምና ስርዓት አስፈላጊ መሆኑንና አለመግባባትና ግጭት የትክክለኛና የተረጋጋ ኑሮ ጠላቶች መሆናቸው ላይ ነው። የሚመራባቸውና የሚያድግባቸውን የመርህ ማዕቀፎች ፈጥሮአል። ምን ይቻላል? ምን አይቻልም? የተፈቀዱ፣ የተከለከሉ ድርጊቶች የሚባሉትን ነገሮች በማህበረሰቡ ህሊና ውስጥ ፈጥሮአል።

ሕግ ታዲያ የዚያን ማህበረሰብ አባላት በማስገደድ በአንድ ላይ ለተቀመጡት እሴቶችና ወጥ መመሪያዎችን አባላቱ በመደገፍ እውቅና እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል። በሕግ በአንድ በኩል ፈቃጅ በመሆን ግለሰቦች ሕጋዊ ግንኙነቶችን እንዲፈጥሩና መብትና ግዴታን ያካተቱ እንደ ውል መግባት ያሉትን ግንኙነቶች እንዲመሰረቱ የሚያስችላቸው ሲሆን በሌላ ገፅታው ደግሞ አስገዳጅነት ያለውና መመሪያዎቹን የጣሱትን የሚቀጣ ነው። ሕግ ባህሪን የሚቆጣጠሩ ተያያዥነት ያላቸው መመሪያዎችን የያዘ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ተግባራዊ የሚደረግበትን ማህበረሰብ ሃሳብና ተግባር ይገልፃል።

ከላይ ስለሕግ ከተነሳው ነጥብ አንጻር ስናየው ዓለም አቀፍ ሕግ የሚለለካበት ዋነኛ ነጥብ የሕጉ ተገዢዎች ግለሰቦች ሳይሆኑ ሀገራት በመሆናቸው ነው። በአንድ ሀገር ሕግ እና ከዚያ ውጭ ባሉ በሀገራት በዓለም አቀፍ ተቋማት በተወሰኑ ሁኔታዎች ላይ በግለሰቦችም ላይ ተፈፃሚ በሚሆነው ዓለም አቀፍ ሕግ መካከል በርካታ ልዩነቶች አሉ።

ዓለም አቀፍ ሕግ ማለት በቀላል አገላለፅ በአጠቃላይ በመንግስታትና በሀገራት መካከል በሚኖሩ ግንኙነቶች የሚከበሩና አስገዳጅነት እንዳላቸው ተደርገው ተቀባይነት ያገኙ ሕጎች ናቸው። ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የተረጋጉ እና የተቀናጁ እንዲሆኑ ማዕቀፍ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ዓለም አቀፍ ሕግ ራሱ በሁለት አይነት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል።

  1. የሚጋጩ ሕጎች የሚዳኙበት ሕግ፡- በሌላ አገላለፅ ግላዊ ዓለምአቀፍ ሕግ ተብሎ ይጠራል። ይህ የዓለም አቀፍ ሕግ ክፍል የሚመለከተው በአንድ የሕግ ስርዓት ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጋን ወይም ሕግን የሚመለከት ጉዳይ ተካቶ በሚገኝበት ጊዜ የውጪ ሀገሩ ሕግ ተፈፃሚነት ወይም የውጭ ሀገሩ ፍ/ቤት ጉዳዩን ለመዳኘት ያለውን ስልጣን በተመለከተ የሚነሳውን ግጭት ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሀገራት ወይም የጉዳዩን አይነት የሚመለከተውን ሕግ በመጠቀም የሕግ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚሞክር ነው።

ለምሳሌ ሁለት ኢትዮጵያውያን በጂቡቲ ውስጥ የሚገኝ ንብረታቸውን ለመሻሻጥ እዚያው ጂቡቲ ውስጥ የውል ስምምነት ቢፈፅሙ እና በሀገራችን ፍ/ቤት ይህን ውል በተመለከተ በሀገራችን ፍ/ቤት ቢካሰሱ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ከማየቱ በፊት ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው ውሉ በተደረገበትና ንብረቱ በሚገኝበት ሀገር ፍ/ቤት ነው ወይስ ተከራካሪዎቹ በሚገኙበት ነው? የሚለውን ጥያቄ ከመለሰ በኋላ የመዳኘት ስልጣኑ እንዳለው ካረጋገጠ ጉዳዩ የሚዳኘውስ በኢትዮጵያ ሕግ ነው ወይስ ውሉ በተደረገበትና ንብረቱ በሚገኝበት በጂቡቲ ሕግ መሰረት ነው የሚሉትን ጥያቄዎች ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ውል፣ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ሕጎች አግባብነት ያላቸው አንቀጾችና በጉዳዩ ላይ የሚደነግጉትን በማየት የዳኝነት ስልጣንና የሕግ ግጭት እንዳይፈጠር ማረግ አለበት።

በመሆኑም የህጎች ግጭትን በመፍታት በአንድ ሀገር ፍ/ቤት የሌላ ሀገርን የሚመለከት ጉዳይ ካጋጠመው ይህን የዓለም አቀፍ ሕግ አንድ ክፍል በመጠቀም

-    የየትኛው ሀገር ፍ/ቤት ጉዳዩን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ

-    ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ሲዳኝ የየትኛውን ሀገር ሕግ መጠቀም እንዳለበት ይወስናል

 

2. የሀገራት ሕግ፡- ይህ ሁለተኛው የዓለም አቀፍ ሕግ አካል በተለምዶ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባለው ወይም ደግሞ በግርድፍ የአማርኛ ትርጉሙ የህዝብ ዓለም አቀፍ ሕግ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የአንድን ሀገር ሕግ የሚያጣቅስ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እራሱን የቻለ ሕገ ነው። ይህ የዓለም አቀፍ ሕግ ክፍል መንግስታት በተለያዩ ዘርፍ ብዙ ግንኙነቶቻቸው ከጦርነት አንስቶ በጠፈር ያሉ ሳተላይቶችን ሳይቀር የሚሸፍንና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ሕግ ነው። ይህ ሕግ በበኩሉ ሁለት አይነት ነው። ሁሉን አቀፍ ዓለም አቀፍ ሕግ ወይም አካባቢያዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው ሁሉንም ሀገራት የሚመለከቱ እና የሚያስገድድ ሕጎች ወይም በተግባር ሁሉም የዚያ ሕግ አካል የሚሆኑበት ሕግ ነው። ለምሳሌ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃልኪዳን ሰነድ እና ሌሎችም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አባል ሀገራት የሚመለከቱ ስምምነቶች በዚህ ጎራ ውስጥ ይወድቃሉ። ሁለተኛው ደግሞ አካባቢያዊ ሲሆን የተወሰኑ በመልከአምድራዊ አቀማመጥ ወይም በርእዮተ ዓለም የሚዛመዱ ሀገሮች እነሱን ብቻ የሚመለከቱ ሕጎችን አውጥተው ተግባራዊ የሚያደርጉበት ነው። ለምሳሌ የተወሰኑ የዲፕሎማሲያዊ ጥገኝነት ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕጎችን በደቡብ አሜሪካ ሀገራት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆኑ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ በአባል ሀገራት መካከል ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚያወጧቸው ሕጎች ይጠቀሳሉ።

ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ ምንነቱና አይነቶች ከላይ የተጠቀሱትን ይመስላል። እዚህ ጋር ዓለም አቀፍ ሕግን ከዓለም አቀፍ የወዳጅነት ግንኙነቶች (International comity) መለየት አለብን። ዓለማቀፍ የወዳጅነት ወይም የመከባበር መገለጫ የሆነ ድርጊቶች የሚባሉት ለምሳሌ በባህር ላይ ለሌላ ሀገር የጦር መርከብ የአክብሮት ሰላምታ መስጠትን የመሰሉት ድርጊቶች የሚደረጉት መከባበርን ለመግለፅ ያህል ብቻ እንጂ በሕግ አስገዳጅነት ስላላቸው አይደለም። በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ሕግን እና ዓለም አቀፍ ግብረገባዊነትም የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው። በርግጥ ሁለቱ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ የሚጋሩት ነገር ቢኖም ዓለም አቀፍ ሕግ በይዘቱም ሆነ በቅርፁ የሕግ ሙያ አንድ ዘርፍ ሲሆን ዓለም አቀፍ ግብረገባዊነት ግን የስነ ምግባር አንዱ ቅርንጫፍ ነው። ይህ ማለት ግን ዓለም አቀፍ ሕግም ቢሆን ከራሱ የስነምግባር እሴቶች የተነጠለ ነው ወይም የስነ ምግባር እሴቶች የሉትም ማለት አይደለም።

የዓለም አቀፍ ሕግ መገለጫ ባህሪያት

ዓለም አቀፍ ሕግ ከጥንታዊ መሠረቱን ከጣሉለት ሊቃውንት ከነቶማስ ሆብስ ፐፈንድሮፍ አንቶ በአውስቴን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃሳብ ጭራሽም ሕግ የሚያስብል ቁመና የለውም ተብሎ ሲታማ እንደኖረ አንደኛው ማጣቀሻችን የፒተር ማላክቲክ መፅሐፍ ጠቀሷል። በዚህም መነሻው ደግሞ ዓለም አቀፍ ሕግ ሲጣስ እንደ አንድ ሀገር ሕግ የጣሰውን የሚቀጣ ሕጉን እንዲፈፅም የሚያስገድድ ሕግ አስፈፃሚ ባለስልጣን ባለመኖሩና አፈፃፀም ላይ ውጤታማ ባለመሆኑ ነው። ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንፃር ይህን የዓለም አቀፍ ሕግን የሚያንኳስስ እይታ አሁንም ተቀባይነት ያለው ሲሆን በተጨባጭ የሀገራት ሁኔታ ላይ የሚያተኩሩ እሳቤዎችን የሚያቀነቅኑ ምሁራን ትኩረት መስጠት ያለበት የአንድ ሀገር የዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ላለው አቅም እና ሀገራዊ ጥቅም ነው እንጂ ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው ዓለም አቀፍ ሕግ አይደለም የሚለውን ያሰምሩበታል።

የአንድ ሀገር ሕግ ብንመለከት ሕግ አውጭው ሕጉን ያወጣል ሕግ ተርጓሚው (የስልጣን ተዋረድ ያለው የዳኝነት አለ) ሕጉን ተርጉሞ ውሳኔ ይሰጣል። ሕግ አስፈፃሚው ደግሞ ሕጉ መፈፀሙን የሚረጋገጥበትን ስርዓት ይዘረጋል። እነኚህ ሶስት አካላት የሌሉት ዓለም አቀፍ ሕግን በለመድነው የሀገራት ሕግ መስፈርት ከመዘንነው ይጎልብናል። የሁሉንም አባል ሀገራት ወኪሎች ያቀፈው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የውሳኔ ሃሳብ ያሳልፋል። ሆኖም የውሳኔ ሃሳቡ የተወሰኑ ተቋማቱንና ጉዳዮችን በሚመለከት ካልሆነ ሕጋዊ አስገዳጅነት የለውም። የፍርድ ቤቶች ስርዓትም የለውም። ዘሄግ ሲውዝርላንድ የሚቀመጠው ዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት ቢኖርም ጉዳዮችን አከራክሮ መወሰን የሚችለው ተፈፃሚነቱንም የሚያረጋግጥበት አቅም የለውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ አስፈፃሚ ወይም መሪ አካል የለውም ለዚህ ታስቦ የነበረው የፀጥታው ምክር ቤት አምስቱ ድምፅን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ሀገራት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና ታላቋ ብሪታንያ እንቅፋት እየሆኑበት ይገኛሉ።

የተጠቀሱት ድክመቶች ቢኖሩም ሕገ ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት ፀሀፊዎቹ ሁሉም ሀገራት ሉአላዊ እና እንደሕግ የበላይ ተቆጣጣሪ የሌለበት የሁሉ እኩል ቤት የሕግ ስርዓት በመሆኑ አስገዳጅነት ያንሰዋል። ሆኖም ግን ከአንድ ሀገር ሕግ ጋር ዓለም አቀፍ ሕግ ማነፃፀር እና ሀገራዊ ስርዓትን ከዓለም አቀፍ ስርዓት ጋር በምስስሎሽ የንፅፅር ዘይቤ ማየቱ ዓለም አቀፍ ሕግ አይደለም ለሚለው ክርክር መነሻ ነው ይሉታል። የእንግሊዛዊው ፈላስፋ የጆን አውስቴን ሕግ ሁሉ የሚያስፈፅመው ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት ያለውና ሕጉን የሚጥሱትን የሚቀጣ፣ የሚያስገድድ መሆን አለበት የሚለው ንድፈ ሃሳቡ ለዚህ ክርክር የጀርባ አጥንት ቢሆንም ሁሉም ሕግ የግድ አስገዳጅ ካልሆነ የሚለው ሃሳብ ግን ሕግ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ባህሪ የሚያቃልልና የቅጣትንም ዓላማ ከሁሉም ሕግ ጋር በማያያዝ የሚያሳንስ እሳቤ በመሆኑ ይተቻል። ሆኖም ግን አስገዳጅነት የኣለም አቀፍ ሕግም አንድ አካል ሆኖ የራሱን ሚና የሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

የሃይል እርምጃ፡- ወጥ የሆነ የቅጣት ወይም የሃይል እርምጃ ስርዓት በዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ ባይኖም ተቀባይነት የሚያገኝባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የፀጥታው ምክር ቤት ሰላምንም የሚያደፈርሱ ድርጊቶች እና የወረራ የጦርነት አጫሪነት ድርጊቶች መሆናቸውን ሲያምን ማዕቀብ እንዲጣል ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በ1950ዎቹ በኮሪያ ጦርነት የተወሰደውን እርምጃ ወይም በ1990ዎቹ ኢራቅ ላይ የተወሰደውን መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም ግን አስገዳጅ እርምጃዎች አልፎ አልፎ የሚወሰዱ ናቸው። ምክንያቱም እንዲህ አይነት እርምጃዎች አምስቱን ቋሚ መቀመጫ ያላቸውን የፀጥታው ምክርቤትን አባላት ትብብርና የልእለ ሃያላኑን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ካልሆነ ነው ስምነት ላይ መድረስ የሚቻለው።

ከተቋማዊው የቅጣት እርምጃ በተለየ ሀገራትም የራስን መብት ማስጠበቅ የሚባለው የሃይል እርምጃ የመውሰድ መብት አላቸው። ይህ አካሄድ ኋላ ቀርና ደም አፋሳሽ ቢሆን በሀገራት ሕጎች ውስጥ ይህን አይነቱን እርምጃ መጠቀምን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት አካላት ይቆጣጠሩታል። ሀገራት ሀይል መጠቀም ራሳቸውን መከላከል የሚችሉት ወረራ ከተፈፀመባቸውና በሌላ ሀገር ለተካሄደባቸው ሕገ ወጥ ድርጊት ምላሽ ነው። ይህም ቢሆን ተገቢነቱ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር የሚታይበት ራሱን የቻሉ ሕግጋቶች አሉት።

በርግጥ ሀገራት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚገደዱት ስምምነታቸውን ሲገልፁ ብቻ ነው። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባለው ሁሉንም ሀገራት የሚገዛ ሕግ የለም የሚለው ክርክር ቢኖርም ታሪክን ስናጣቅስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩ ወደ መቶ የሚጠጉ ሀገራት ሁሉ ከመመስረታቸው በፊት ወጥተው የነበሩ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን መቀበላቸው ሲታይ አገራት በሕጉ ለመገዛት ፍቃደኛ ካልሆኑስ የሚለውን ክርክር ተጨባጭ መሠረት የሌለው ያደርገዋል።

በተጨማሪም ሀገራት በየዕለቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶቻቸው በርካታ ስምምነቶችን የሚፈርሙ በርካታ ግንኙነትን የዓለም አቀፍ ሕግጋትን ተከትለው የሚያካሂዱ ከመሆኑ አንጻር አስገዳጅ ባይሆንም እንኳን ዓለም አቀፍ ሕግ ሀገራት አክብረው እንዲመሩበት የማድረግ ሃይል ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም የሕግ የበላይነት እሳቤ በበርካታ የዓለማችን ሀገራት እየዳበረና ባህል እየሆነ እንደመምጣቱ በሀገራትም መካከል ለዓለም አቀፍ ሕግጋት የመገዛት ባህል እየተለመደ መጥቷል። የአ/ሕግን ድክመትና ጥንካሬዎች አውቆ መጠቀሙን ነው ፀሀፊዎቹ ለሁሉም ሀገራት የመከሩት። ሰው ስርዓት፣ ሰላም፣ ደህንነትና ፍትህን በሚኖርበት ሀገር ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው ሀገሩ በምትኖርበት ዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥም ጭምር ነው።  

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
7094 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1047 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us