የአፄ ቴዎድሮስ ፍርዶች

Wednesday, 25 June 2014 13:25

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    አፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ፀሐፊያን ፍርድ አዋቂም ፍርድ ገምድልም ነበሩ ይሏቸዋል።

-    ይህን አባባላቸውን የሚያሳዩ አፄ ቴዎድሮስ እንደሰጧቸው በታሪክ ፀሐፊዎች የተፃፈ ፍርዶች

-    የዘመኑን የፍትህ ስርዓትና ህብረተሰቡ ለፍትህ የነበረውን አመለካከትና የፍትህ ባህል የሚያሳዩ ፍርዶች

-    ንጉሱ ራሳቸውን ጥፋተኛ ያሉበትና ተከሳሽ ሆነው የቆሙባቸው ክርክሮች እና ሌሎችም

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ለዛሬ የምናወጋው አፄ ቴዎድሮስ ስለሰጧቸው የተለያዩ ፍርዶች ነው። ካሳ ኃይሉ በ1811 ዓ.ም ጥር 6 ቀን ተወለዱ። በ1845 የካቲት ወር አፄ ቴዎድሮስ ተብለው ነግሰው እስከ 1860 ከእንግሊዝ ጦር ጋር መቅደላ አምባ ላይ በተደረገው ውጊያ ጦራቸው ስለተሸነፈ በገዛ ሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለዋል። አፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ስያሜያቸው ቴዎድሮስ እንዲሆን የመረጡት “ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ሲነግስ ኢትዮጵያን እስከ ባህር ያሰፋታል ፍርድና አስተዳደርንም ያስተካክላል” የሚባል ትንቢት ስለነበር ሕዝቡ “ይህ ትንቢት የእርስዎ ነው” እያሉ አሞካሿቸው። ስሜን ቴዎድሮስ በሉ ብለው አወጁ ይለናል ታሪካቸውን ፅፎ በ1985 ያሳተመው ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ።

ጳውሎስ “ቴዎድሮስ እንዴት ያሉ ሰው ነበሩ?” የሚለውን ጥያቄ በመፅሐፍ አንስቶ “ሁሉንም ጠባይ አሟልተው የያዙ ሰው ነበሩ። ይህም ማለት ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፣ ፍርድ አዋቂ ናቸው፣ ፍርድ ገምድልም ናቸው” ሲል ማስረጃ እያጣቀሰ ይገልፃቸዋል። እኛም ዛሬ ጳውሎስ ኞኞ በመፅሐፍ ላይ ያስፈራቸውን የአፄ ቴዎድሮስን ፍርዶች እንመለከትና በዘመኑ የነበረውን የፍትህ ስርዓት በመጠኑ እንቃኛለን። በሰጧቸው ፍርዶች መነሻነትም በትንቢት ተነግሮላቸዋል። እንደተባለው ፍርድና አስተዳደርን በማስተካከል ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ነበር የሚለውን የራሳችንን ግንዛቤ እንይዛለን። ፍርዶቹ አንዳንዶቹ አስገራሚ፣ አንዳንዶቹ አሳዛኝና አስደንጋጭ አንዳንዶቹም አስተማሪ ናቸው። ለማንኛውም እንቀጥል. . .

1.የጋይንቱ ችሎት

አፄ ቴዎድሮ ጎንደር ጋይንት ላይ ሰፍረው ሰለ ወታደሮቻቸው በአርሶ አደሩ ላይ ተሰሪ አገቡአቸው። ተሰሪ ማግባት ማለት አርሶ አደሩ ወታደሮቹን እንዲቀልብ በየቤቱ መመደብ ማለት ነው። በወቅቱ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና ለጦር ሰራዊቱ የሚመደብ የመንግሥት ባጀት ስላልነበር የነገስታቱ ጦር በየደረሰበት ያለው ህዝብ እንዲቀልበው ይታዘዝ ነበር። ከእነኚህ የጋይንት እና የአካባቢው አርሶ አደር እንዲቀልባቸው ከታዘዘላቸው የቴዎድሮስ ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን አርሶ አደር ገደለው። የሟች ዘመዶች ለአፄ ቴዎድሮስ አመለከቱ። አፄውም ወታደሮቻቸውን አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን እንዲጠቁሙ አዘዙ። ሆኖም ወታደሮቹ በሙሉ በአንድ ላይ አድመው ገዳዩን አናውቅም ብለው በቄስ እየተገዘቱ ስለወጡ ገዳዩ ሊታወቅ አልቻለም።

ቴዎድሮስ ገዳዩን ወታደር ለማወቅ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ተናደው “ወታደር ብላ ባላገር አብላ ያልኩ እኔ ነኝ። ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል” ብለው ተነስተው ለከሳሽ ነገሩት። ከሳሽም ምኑ ሞኝ “እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም” አለ። ቴዎድሮስ እንግዲያውስ ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም ብለው ለሟች ወገኖች የደም ካሳ ገንዘብ ከፍለው አሰናበቷቸው።

2.የንጉሱ ትዕዛዝ

ቴዎድሮስ ለአንድ ታማኝ ወታደራቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈው “በፈርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ” አሉት።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላውን ወታደራቸውን ጠርተው “ፈረስ እያለዋወጥክ ይህን ወረቀት የጁ አድርሰህ በስድስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ ተመለስ” ብለው አዘዙ። መልክተኛው ወታደር መልክቱን ለማድረስ ፈርቃ በር በሚባለው ቦታ ማለፍ ግድ ሆነበት። ፈረሱን እየጋለበ ፈርቃ በር ደረሰ። አስቀድሞ ማንንም እንዳያሳልፍ የታዘዘው የፈርቃ በር ዘበናም የንጉሱን መልዕክት እንዳያልፍ ከለከለው።

መልዕክተናው “ከንጉሡ በስድስት ቀን የጁ ደርሼ እንድመለስ በአስቸኳይ ተልኬ ነው ልለፍ” አለው።

የፈርቃ በር ጠባቂም “ከንጉሥ ከተላክ አትከልክሉት ይለፍ የሚል በማህተም የተደገፈ የይለፍ ደብዳቤ ካለህ አሳየኝ እና አሳልፍሃለሁ ካልሆነ ግን እኔም የንጉሥ ትዕዛዝ ስላለብኝ አታልፈም” ሲል መለሰለት።

መልዕክተኛው ወታደርም የንጉሥ ትዛዝ ሆኖበት በግድ አልፋለሁ ብሎ መንገድ ሲጀምር ጠባቂው ወታደር በጥይት ተኩሶ ገደለው።

የሟቹ መልዕክተኛ ወገኖችም ጉዳዩን ከሰሱና ለፍርድ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀረቡ። በችሎት የተቀመጡት ፈራጆች ሁሉ ገዳይ ላይ ፈረዱ “እምቢ አልፋለሁ ቢልህ ለንጉሥ ማመልከት ሲኖርብህ እንዴት የንጉሥ መልዕክተኛ ትገላለህ ለጥፋትህ ሞት ይገባሃል” ሲሉ ፈረዱበት።

አንድ አስተዋይ ፈራጅ ከተቀመጡበት ተነስተው “መታየት የሚገባው ከንጉሡ የተሰጠው ትዕዛዝ ነው። ንጉሡ የፈርቃ በር ጠባቂን ጠርተው ያለኔ ፈቃድ እርጉዝ ሴት እንኳን እንዳታልፍ ብለው አዘዙ። መልዕክተኛውን ደግሞ በአስቸኳይ የጁ ደርሶ እንዲመጣ በማዘዛቸው በዚያ በፈርቃ በር በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሥ ነገስቱን ነው። ነገር ግን ብርሃን ናቸውና ምን ይደረግ” ብለው ተቀመጡ።

እዚህ ጋር እንግዲህ በዚያ ዘመን የነበረውን ንጉሥ የሚያስተች ዲሞክራሲ ሳናደንቅ አናልፍም። የአስተዋዩ ፈራጅ ንግግር ብቻ ሳይሆን የንጉሡም ምላሽ የሚደንቅ ነው።

አፄው ምን አሉ መሰላችሁ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው “እንዲህ ነው መሸምገል፣ ሁለት ጠጉር ማብቀል” ብለው የአስተዋዩን ፈራጅ ፍርድ ካደነቁ በኋላ “በደለኛው እኔ ነኝ ፍረዱብኝ” ብለው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ። ከዛም ፈራጆች በሰጡት ፍርድ መሰረት ለሟች ወገኖች 500 ብር የደም ካሳ እንዲከፍሉ አፄ ቴዎደሮስ ላይ ፈረዱና ጉዳዩ በዚህ ተቋጨ።

3.በቴዎድሮስ አምላክ!

በወቅቱ ንጉሥ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ሕግም ነበር። በንጉሥ አምላክ' ከተባለ አሁን በሕግ አምላክ ከሚባው በላይ ማንኛውም ድርጊት ይቆም ነበር። ይሄ ታሪክም ከዚሁ ጋር ይያያዛል አንድ ሌባ ከአንድ ሀብታም ሰው ቤት ሌሊት ለስርቆት ገብቶ በረቱን ሲያንጎዳጉድ ባለቤቱ ከእንቅልፍ ነቅቶ መጣበት። ባለቤት ሲያባርር ሌባ እግሬ አውጪኝ ፈረጠጠ እንደማይደርስበት የገባው ባለቤት። “በቴዎድሮስ አምላክ ቁም” ብሎ ሌባውን አወገዘው ሌባውም በቴዎድሮስ አምላክ መባሉን ሲሰማ ቆሞ ጠበቀው። ሀብታሙ ሰውም ሌባውን በያዘው ጦር ደጋግሞ ወግቶት ጥሎት ሄደ።

ሌባው አልሞተምና በአቅራቢያው ወዳለው የአርዋ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ገብቶ እስኪያገግም ቆየ። አፄ ቴዎድሮስ እንፍራንዝ መጥተው መስፈራቸውን ሲሰማም እያዘገመ ሄዶ ታሪኩን ነገራቸው። ቴዎድሮስም በጥሞና ካዳመጡት በኋላ “አንተ የሌሊት ጅብ ከሰው በረት ምን ልታደርግ ገባህ? አበጀ ደግ አረገህ ብለው ሌባውን አስደነገጡትና ሀብታሙ ሰው ተይዞ እንዲመጣ አዘዙ።

ሀብታሙ ሰው እንደመጣ አፄው በፈገግታ “እህሳ አንተ ጎበዝ ይህን ሌባ እንዴት ወጋኸው?” ብለው እየሳቁ ጠየቁት። ሰውዬውም በደስታ “በረቴን ከፍቶ ገብቶ ከብቶቼን ሊነዳ ሲል ነቃሁና ምዝራጤን (አንካሳዬን) ይዤ ልወጋውስል ኮቴዬን ሰምቶ አብላክ አለ (ሮጠ) እኔም ተከትዬው እንደማልደርስበት ሳውቅ በቴዎድሮስ አምላክ ብለው መሮጡን ትቶ ቀጥ ብሎ ቆመልኝ እንደደረስኩም በያዝኩት አንካሴ ወደወድኩት (ወጋሁት) ብሎ ነገራቸው።

ቴዎድሮስ የሰውየውን ንግግር ሰምተው እንደጨረሱ “ወንጀለኛ ነህ እንዴት በስሜ ቆሞልህ ትገድለዋለህ። መሞት ይገባህ ነበር። ግን ምሬሃለሁና ያለህን ሀብትና ንብረት በሙሉ ለወጋኸው ትለቃለህ” ብለው ፈረዱበት።

4.ባለ ወይፈኗ

አንዲት አንድ ወይፈን ብቻ ትቶለት በበሬ ባሏ የሞተባት ሴት ነበረች። ያላት ብቸኛ ንብረት ወይፈኑ ነበርና ቤቷን የምታስተዳድረው በዚሁ ወይፈን በምታርሰው መሬት ነበር። ሆኖም ግን ወይፈኑ ሴት ከብት ፍለጋ እየዞረ አላርስ ብሎ አስቸገራት። የመንደሩን ሰዎች እንዲኮላሹላት ብትለምናቸውም ወይፈኑ ጥሩ ቁመና የነበረው ምርጥ ዝርያ ያለው ስለነበር ከብቶቻቸውን እያጠቃ ጥሩ ዝርያ ያለው ጥጃ ስለሚያስወልዳቸው ለጥቅማቸው ሲሉ እምቢ አሏት። ወይፈኑም እርሻ እምቢ ብሎ ለግሞ እየዞረ የመንደሩን ሰዎች ከብቶች ሲያስወልድ ከረመ። አንድ ቀን ወይፈኑ ከአንድ በሬ ጋር ሲዋጋ ጉልበተኛ ነበርና በሬውን ገፍቶ ገደል ከተተውና በሬው ተሰባብሮ ሞተ። ይሄኔ የሞተው የበሬ ባለቤት ባለወይፈኗን “ተዋጊ በሬህን ተናካሽ ውሻህን ያዝ ያላልና ሕጉ የበሬውን ዋጋ ክፈይኝ” ሲል ከሰሳት።

ባለወይፈኗ በየደረጃው በሽማግሌም ሆነ በዳኞች የበሬውን ዋጋ እንድትከፍል ፈረዱባት። ኢትዮጵያውያን በጥንትም ታሪካችን በፍትህ እናምናለን ከፈጣሪ በታች የመጨረሻው የዳኝነት ሰጪ እስከሆነው እስከ ንጉሡ ችሎት ድረስ ፍትህን ለማግኘት ከታች ከአጥቢያ ዳኛ ተነስተው ከብቶችና መሬታቸውን ሸጠው ጥሪታቸውን አሟጠው የንጉሡ መናገሻ ድረስ ይግባኛቸውን ይዘው የክርክሩ መነሻ ትንሽም ይሁን ትልቅ ለዓመታት ተስፋ ሳይቆርጡ እንደሚሟገቱ የህጎቻችንን ታሪኮች የፃፉ ምሁራን ከትበውታል። እንዲያውም “ያለ ፍትህ ከተወሰደች አንዲት ዶሮ እና በፍትህ በመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ከተወሰደች አንዲት በቅሎ ያለፍትህ የሄደችው ዶሮ ታስቆጫለች” የሚለው ነበር። ብሒል የበለጠ ለፍትህ ያለንን ቀናኢነት እና የፍትህ ባህላችንን የሚያሳይ ነው። ይህ ከሚያኮሩን በርካታ ባህሎችና አመለካቶች አንዱ ሆኖ መጠቀስ አለበት።

ባለወይፈኗም በዚሁ የፍትህ ባህላችን መሰረት ከአፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ በበታች ዳኞች በተወሰነባት ፍርድ የተሰማትን ቅሬታ አሰማች። አፄ ቴዎድሮስም ጉዳይዋን በጥሞና ከሰሙ በኋላ “ሕጉ ያዛልና ወይፈንሽ የገደለውን ዛሬ ዋጋ መክፈሉንስ ትከፍያለሽ” ሲሉ ፈረዱ። ነገር ግን አንድ ጥያቄ ጠየቋት፡፤

“ለመሆኑ ለዚህ ወይፈንሽ የተወለዱትን ከብቶች ታውቂያቸዋለሽ?” አሏት

“አዎን ንጉሥ ሆይ አውቃቸዋለሁ” ስትል መለሰች ባለወይፈኗ አፄ ቴዎድሮስም አጋፋሪያቸውን ጠርተው “ንሳማ እሷ የምታሳይህን ከብቶች ሁሉ እየያዝክ አንድ ለሷ አንድ ለባለ ላም እየደረክ አካፍላቸው” ብለው አዘዙ። አፄ ቴዎድሮስ ወይፈኗ ያደረሰውን ጉዳት እንድትከፍል ብቻ ሳይሆን ካስገኘው ጥምም እንድትጋራ ስለፈረዱላት ሴትዬዋ በተከፈለቻቸው ከወይፈኗ የተወለዱ ከብቶች በአንድ ጊዜ ሀብታም ሆነች።

5.አርባ ክንድ መቀነት

አንዲት ሴት አርባ ክንድ ያለው መቀነት አሰርታ ለአፄ ቴዎድስሮ ስጦታ ሰጠች። አፄውም ስጦታውን ተቀብለው “እንዴት በአርባ ክንድ መቀነት ወሰንሽኝ እንደተራሰው ቆጥረሺኝ ነው?” ቢሏት።

ሴትየዋም “አይደለም ጃንሆይ ድሃ ብሆን ነው እንጂ ለእርስዎስ መቶ ክንድም አይበቃም” ስትል መለሰች። በመልሷ የተደሰቱት ንጉሥም ሴትየዋን ሸልመው አሰናበቷት፡፤

ይህን የሴትየዋን ታሪክ የሰማች ሌላ ሴት ለዚያች ለመልከ ጥፉ ያን ያህል የሸለሙ የኔንማ ቁንጅና ሲያዩ የበለጠ ይሸልሙኛል ብላ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ እጅ ነሳች።

አፄ ቴዎድሮስም “ሙያሽ ምንድን ነው እቱ?” ብለው ጠየቋት።

ሴትየዋም “የከተማ ቅሬ (ሴተኛ አዳሪ) ነኝ እንጂ ሌላ ስራ የለኝም ብላ መለሰችላቸው።

አፄ ቴዎድሮስም ሴትዬዋ ስራፈትነትን የምታበረታታ ሙያ የሌላት ስርታ የላቧን ከማግኘት ይልቅ በአስነዋሪ የዝሙት አዳሪነት ተግባር ላይ መስማራቷንና አስባ የአቅሟን የመቀነት ስጦታ ያቀረበችውን ታታሪ ሴት ለፍታ ያገኘችውን እሷ በከንቱ ለማግኘት መምጧን ሰለተረዱ እንዲህ ፈረዱባት።

“እግዚአብሔር ሁለት እጆች የፈጠረልሽ እንድትሰሪባቸው ነበር። ለመብል ብቻ ከሆነ ግን አንድ እጅ ይበቃሻል” ብለው ለመሰሎችዋ መቀጣጫ እንድትሆን አንድ እጇን አስቆርጠው ቀጧት።

የዘመኑ አዝማሪዎች በዚህች ሴት ላይ የደረሰውን ቅጣት ታዝበው የዘፈኑትን ግጥም ለአፄ ቴዎድሮስ ፍርዶች መቋጫ አርገን እንድሰነባበት። የዘመኑ አዝማሪዎች እንዲህ ሲሉ ዘፈኑ

“ማረስ ይሻላል መገበር

እጅ እግርን ይዞ ለመኖር

አላርስም ያሉ አልነግድ

      ተመለመሉ እንደ ግንድ”

ይምረጡ
(39 ሰዎች መርጠዋል)
13183 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1007 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us