ህግ

ህግ (65)

ይዞታና ሁከት

July 22, 2015

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    የይዞታ መብት ምን ማለት ነው?

-    ባለ ይዞታነትን መደበቅ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት ምን ይመስላል?

-    የአንድ ንብረት ይዞታ እንዴት ለሌላ ሰው ይተላለፋል?

-    ይዞታን ለማስከበር በጉልበት መጠቀምን ሕጉ ይፈቅዳል። በምን መልኩ?

-    የሁከት ይወገድልኝ ክስ ምንድንነው? እንዴትስ መቅረብ አለበት? በባህርዛፍ መሬት ይዞታ ከሰሜን ሸዋ ስድስትኪሎ የደረሰው የሁከት ይወገድልኝ ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሠላም ነው? የዛሬው ወጋችን አንድ ሰው የራሱ ንብረት በሆነ ወይም በኪራይ በአደራ ጠባቂነት በይዞታው በሚገኝ ንብረት ላይ ሌሎች ሰዎች በንብረቱ የመጠቀም መብቱን የሚያሰናክሉ ድርጊቶች ሲፈፅሙበት በይዞታው ላይ ያለውን መብት ለማስጠበቅ ያለውን “የሁከት ይወገድልኝ ክስ” የማቅረብ መብት ጋር የተያያዙ ነጥቦችን የሚመለከት ነው። ሕጉን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የሁከት ይወገድልኝ ክስ መነሻዎችን እና የተደረገውን ክርክር የሚያሳይ እስከ ፌሬራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ደርሶ እንደ ክርክር የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜም እናያለ

1.  የባህር ዛፎቹ ጉዳይ፡-

አቶ ሙሳ በሰሜን ሸዋ ዞን አሌልቱ ወረዳ በ1993 ከአቶ ደስታ እና ከወ/ሮ ሸዋዬ በሽያጭ አገኘሁት የሚሉት ይዞታ ላይ ባህር ዛፎች ተክለው ባህር ዛፎቹን እየተንከባከቡና እየጠበቁ ነበር። መስከረም 27 ቀን 2000 ዓ.ም የአቶ ደስታና የወ/ሮ ሸዋዬ ልጅ ጥላሁን ይዞታው ከነባህርዛፎቹ የኔ ነው ብሎ ይዞታዬ ላይ ድርሽ እንዳትል ስላላቸው ሁከት ፈጥሮ በይዞታዬ እንዳልጠቀም አድርጎኛልና ጥላሁን የፈጠረብኝ ሁከት ይወገድልኝ ሲሉ ለአሌልቱ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሰባተኛው ቀን አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ ጥላሁንም ቀርቦ በሰጠው መልስ ይዞታው ከሟች አባቴ ከአቶ ደስታ በውርስ ያገኘሁት ይዞታ በመሁኑ አቶ ሙሳ እንዳይነካብኝ መከላከሌ መብቴን ማስከበሬ እንጂ ሁከት መፍጠር ስላልሆነ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ተከራከረ። ፍ/ቤቱም ጥላሁን በአቶ ሙሳ ባህር ዛፍ የተተከለበት መሬት ይዞታ ላይ ሁከት ፈጥሯልና ሁከቱን ያስወገድ ሲል ወሰነ።

አቶ ጥላሁን በውሳኔው ቅር ተሰኘና ይግባኝ ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረበ። ፍ/ቤቱም አቶ ሙሳ ከተከሳሽ አቶ ጥላሁን አባት ከአቶ ደስታ አያሌው ይዞታውን አግኝቼበታለሁ የሚሉት በ1993 የተደረገው የልዋጭ ውል ላይ የሰፈረው ፊርማ የሟች የአቶ አያሌው መሆኑ ተጣርቶ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥ በማለት ጉዳዩን ለአሌልቱ ወረዳ ፍ/ቤት መለሰለት።

የአሌሊቱ ወረዳ ፍ/ቤትም ፊርማው በፎረንሲክ ተመርምሮ የጥላሁን አባት የአቶ ደስታ ይሁን፣ አይሁን መለየት ስላልተቻለ አቶ ሙሳ በልዋጭ ውል ቦታውን አግኝቼበታለሁ የሚለው ሰነድ በአቶ ደስታ የተፈረመ አይደለም ብሎ በመደምደም ለሙሳ ወስኖት የነበረውን የሁከት ይወገድ ክስ ውድቅ አደረገው።

አሁን ደግሞ ይግባኝ የሙሳ ተራ ሆነ። በየደረጃው ለዞኑ ከ/ፍ/ቤት ቀጥሎም ለዞኑ ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት ስላላገኘ ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ ሲል አመለከተ። የክልሉ ሰበር ሰሚ ሙሳንና ጥላሁንን አከራክሮ ጥላሁን ሁከት ፈጥሮ ይዞታውን መያዝ፣ አለመያዙ በምስክሮች እና ከሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት ተጠይቆ ተገቢው ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ የመሰለውን ውሳኔ ሰጥበት ሲል ለሁለተኛ ጊዜ ለአሌልቱ ወረዳ ፍ/ቤት መለሰለት።

የወረዳ ፍ/ቤት ከወረዳው አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ስለጉዳዩ ጠይቆ ካጣራ በኋላ አቶ ጥላሁን የፈፀመው ተግባር ሁከት አይደለም ሊል የሚችል ባለመሆኑ ሁከቱን አቁሞ ሙሳ በይዞታው ላይ ይጠቀም ሲል ወሰነ።

ጥላሁን በውሳኔው ባለመስማማት ይግባኝ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቢያቀርብም አልተሳካም። የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ጋርም ቢቀርብ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ፀና። በዚህ ሁሉ ያልታከተው ጥላሁን ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግራቀኙን አከራክሮና ማስረጃቸውን ሲመረምር ለክልሉ መነሻ የሆነው ይዞታ በመጀመሪያ የአቶ ጥላሁን አባት የአቶ ደስታ እንደነበረና ከ1993 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ግን በአቶ ሙሳ ስም ግብር እየተከፈለበት ባህር ዛፍ ተክለውበት ከይዞታቸው ስር መቆየቱን አረጋገጠ።

በ1998 አቶ ሙሳ በይዞታው ላይ የባለቤትነት የምስክር ወረቀትም አውጥተውበት ነበር። ይሄን ያወቀው አቶ ጥላሁን በ1999 እናቱን ወ/ሮ ሸዋዬን ከሶ ከአባቱ ከሟች አቶ ደስታ በውርስ የሚያገኘው ይዞታ ነው ተብሎ ተፈርዶበት በፍርድ አፈፃፀም ትዕዛዝ በ2001 ይዞታውን መቀበሉንና ከ2001 ጀምሮ በስሙ ግብር መገበሩን በ2002 የይዞታው ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በስሙ እንደተሰጠው አረጋገጠ። በተጨማሪ ጥላሁን እናቱን ሲከስ አቶ ሙሳ በመቃወሚያ አቅራቢነት ወደ ክርክሩ ገብቶ አቤቱታቸው ውድቅ እንደተደረገበት ስለተገነዘበ አቶ ጥላሁን በፍርድ ውሳኔ ያገኘውንና በእጁ አድርጎ የሚገብርበትን የዞታ ሁከት ፈጥረሃል ሊባልበት አይገባም በሚል የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ሻረው።

አቶ ሙሳ የመጨረሻ እድሉን ለመሞከር ለፌ/ጠ/ፍ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርቦ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠበት። ውሳኔው ይቆየንና አንድ ሌላ ክርክር ልጨምር።

 

2.  ሕጋችን ምን ይላል?

የፍትህ ብሔር ሕጋችን በሶስተኛው መፅሐፍ ስለንብረቶች በጠቅላላውና ስለ ይዞታ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። ስለንብረቶች አከፋፈል ከዘረዘረ በኋላ በሁለተኛው ምዕራፍ ስለይዞታ ምንነት ከቁጥር 1140-1150 የሕግ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። ይህ የህግ ምዕራፍ ስለይዞታ ምንነት ትርጓሜ በመስጠት የሚጀምር ሲሆን ይዞታ ማለት “አንድ ሰው አንድንነገር በእጁ አድርጎ በእውነት የሚያዝበት ሆኖ ሲገኝ ነው” ብሎ ይተረጉመዋል። ይዞታ ከባለቤትነት ያነሰ መብት ሲሆን በቀጥታ ባለቤት በመሆን ወይም በጊዜያዊ ስምምነት በተሰጠ ውክልና ኪራይ፣ አደራ ወይም የመጠቀም መብትም ባለይዞታነት ሊፈጠር እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 1141 ይደነግጋል። ይህ የባለ ይዞታነት መብት ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች መቋረጡ ወይም መገደቡ ብቻ የባለይዞታት መብት አያስቀርም።

አንድ ይዞታ ለሌላ ሰው በውል ተላልፏል የሚባለው ይዞታውን በመረከብ ነው። ይህ በተለይ የተለየ ምዝገባ የሚያስፈልጋቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ለምሳሌ (ሞባይል፣ ላፕቶፕ የመሳሰሉትን በእጅ ማድረግ ወይም በይዞታችን ስር ማድረግ ብቻ በቂ ነው።

በሌላ በኩል አዲስ ባለይዞታ የሆነውን ሰው ባለይዞታነት የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በማስረከብ ለምሳሌ የይዞታ ወይም የባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት የሽያጭ ውል ወይም ደረሰኝ ወይም ስጦታ ሰጪው ለገዥ ወይም ለተቀባይ በመስጠት ይዞታን ማስተላለፍ ይቻላል:: ሆኖም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1144 መሰረት የዚህን ይዞታ የሚያስረዳ ሰነድ ባቀረበ ሰውና ንብረቴን በእጁ ባደረገ ሰው መካከል ክርክር ከተነሳ ንብረቱን በእጁ ሰው ተንኮል ወይም ክፉ ልቦና እንዳለበት ካልተገለፀ በስተቀር የባለ ይዞታነት አብላጫ ግምት የሚሰጠው ሰነድ ብቻ ካለው ይልቅ ንብረቱን በተጨባጭ ይዞ ለተገኘው ሰው ነው። የተለዩ እና የታወቁ እቃዎችን አዲሱ ባለይዞታ በእጅ ባያረገቸውም በእቃዎቹ የማዘዝ መብት ያለው ሰው እቃውን የያዝኩት ወደፊት አዲስ ባለይዞታ ለሚሆነው ሰው ነው ብሎ በሚፀና መልኩ ሲያሳውቅ የእቃው ይዞታ እንደተላለፈ ይቆጠራል።

የይዞታ ባለመብትነት በማያጠራጥር መልኩ በግልጽ መደረግ አለበት በእጅ የሚያገኘውን ንብረት ላይ አንዳችም መብት እንደሌለው ለማስመሰል የደበቀ ሰው በስውር የያዘው ይዞታ ነውና ምንም አይነት መብት በንብረቱ ላይ አይኖረውም። የሚያሻማ ይዞታ የሚባለው ደግሞ ንብረቱን ይዞ የሚጠቀመው ሰው የንብረቱ ባለቤት ነው ለማለት አካባቢው ሁኔታዎች የሚያጠራጥሩ ሲሆን ወይም ንብረቱ ለሌላ ሰው የያዘው ሲሆን ባለመብትነቱ አሻሚ በመሆኑ የባለይዞታነት መብት እንደማይኖረው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1146 ይደነግጋል። ስለሌላ ሰው ንብረቱን የያዘ ሰው ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ እንደ የንብረቱ ጠባቂ ተደርጎ ነው የሚገመተው።

ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን እንዳይጠቀም መሰናክል ወይም ንጥቂያ ሲፈጠርበት ይዞታውን ለማስከበር ሕጉ ሁለት አማራጮችን አስቀምጦለታል። የመጀመሪያው በኃይል ይዞታውን በመንጠቅ ወይም እንዳይጠቀምበት ለማድረግ የሚሞከረውን ሙከራ በኃይል መመለስ ነው። በተለይም በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ ነገሮችን በንጥቂያ ወይም ወስዶ በመደበቅ ይዞታውን ሲቀጣ በግፍ ንብረቱን የሚወስደውን ወይም ይዞ የሚሸሸውን ነጣቂ ወዲያውኑ በጉልበት በማስለቀቅ ማስመለስ ይቻላል። የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ በጉልበት ይዞታውን ነጣቂውን በማስወጣት ማስከበር አንዱ የሁከት ማስወገጃ አማራጭ ሲሆን ይህም ሕጋዊ ነው። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1148(3) ላይ አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ቀላል ህመም የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ድብደባ (ቦክስ ጥፊ ካልቾ ቴስታ የመሳሰሉትን) የእጅ እልፊት የኃይል ተግባር ከመፈፀሙ በፊት ባለይዞታው መታገስ እንዳለበት ተደንግጓል።

ሁለተኛው አማራጭ የሁከት ይወገድልኝ ክስ ማቅረብ ሲሆን ይዞታው ላይ ሁከት የተነሳበት ሰው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1149(1) መሠረት የተወሰደው ነገር እንደመለሰለት ወይም የተፈጠረበት ሁከት እንዲወገድለት በተጨማሪም ይዞታውን እንዳይጠቀም በመከልከሉ ለደረሰበት ጉዳት ኪሳራ እንዲከፈለው ፍ/ቤት ክስ መጠየቅ አማራጭ  ነው።

ይህን የመክሰስ መብት ባለይዞታው ሁከት ከተነሳበት ቀን አንስቶ እስከ ሁለት አመት ክስ ካልጠቀየቀ ይዞታውን የማስመለስ መብቱ በይርጋ ይታገዳል። ሁከት በመፍጠር የተከሰሰው በፍጥነትና በማይስተባበል መልኩ ካላስረዳ ፍ/ቤቱ የተወሰደው ነገር እንደሚመለስ ወይም ይዞታው ላይ የተነሳው ሁከት እንዲወገድ 1149(3) መሰረት ያዛል።

የይዞታው ባለቤት የመሆን መብት ያለው ሰው ንብረቱን ያስተላለፈለትን ሰው የይዞታ ጊዜ ተደርቦ የሚቆጠርበት ንብረቱን ያስተላለፈው ሰው ከላይ በተቀመጠው የይርጋ ገደብ ይዞታውን ለራሱ የማስቀረት መብት ሲኖረው ሲሆን በ1150(2) መሠረት በአንድ ነባር ይዞታ ላይ ወይም በይዞታ የመጠቀም መብት ላይ ለሚነሳ ክርክር ይዞታውን እየተጠቀመበት የሚገኘው ሰው በስሙ የከፈለውን ግብር መከራከሪያ  ሊያደርገው ይችላል።

 

3.  ሰበር ምን አለ?

በመነሻችን ላይ ያነሳነው የአቶ ሙሳ እና የአቶ ጥላሁን ክርክር ላይ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ. በ4869 ሰኔ 19  ቀን 2006 በሰጠው ቅጽ 16 የሰበር ችሎቶች ውሳኔ ላይ ታትሞ በወጣው መጨረሻ ፍርዱ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎ የወሰነውን ውሳኔ በማጽናት አቶ ጥላሁን ይዞታውን ያገኙት በፍርድ ቤት ውሳኔ በመሆኑ ባለይዞታነታቸው ስለተረጋገጠ ሁከት አልፈጠሩም ሲል ወሰኗል።

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    የተሽከርካሪ ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት መደረግ አለበት?

-    የስም ዝውውርን ለማድረግ የመኪና ሻጭ ያለበት ግዴታ እስከምን ድረስ ነው?

-    ተሽጦ ስሙ ያልተዛወረ ተሽከርካሪ አደጋ ቢያደርስ ሻጭ ይጠየቃል?

-    እስከ ሰበር የደረሱ የመኪና ሽያጭና የስም ዝውውር ጉዳዮች በምን ውሳኔ ተቋጩ

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? በዛሬው ጽሁፍ አንድ መኪና በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሌላ ሰው ተላልፏል የሚባለው ምን ነገሮች ተሟልተው ሲገኙ ነው። የመኪና ባለሀብትነት ስም ዝውውር ባልተደረገበት ሁኔታ ተሽከርካሪው ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ቢያደርስ የባለቤቱ የካሳ ኃላፊነት ምን ይመስላል የሚሉትን ጉዳዮችና ተያያዥ ነጥቦች እናነሳለን።

 

 

1.ለወ/ሮ አስናቀች ማን ካሳ ይክፈል?

ወ/ሮ አስናቀች ልጃቸው በመኪና ተገጭቶ ሞተ። ልጃቸውን ምናሴ ከበደን ገጭቶ የገደለው የስ.ቁ. 3-03657 የሆነው መኪና የአቶ አለማየሁ አህመድ ነበር። አቶ አለማየሁ ይህን መኪናቸውን ለሌላ ሰው ቢሸጡም፤ ስሙ በገዢው አልተዛወረም። የግጭት አደጋው የደረሰውም ገዢው ቀጥረው ያሰሩት በነበረው ሹፌር መኪናው ሲሽከረከር ነበር። ሹፌሩ በቸልተኝነት ሰው ገጭቶ በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በእስር ተቀጣ።

ወ/ሮ አስናቀች በልጃቸው ሞት ለደረሰባቸው ጉዳት በ1ኛ ተከሳሽነት አቶ አለማየሁን መኪናው በስማቸው ስለሚገኝ፣ በ2ኛ ተከሳሽነት ገዢውን ተሽከርካሪው ገዝተው እየተጠቀሙበት ስለሚገኙ፣ በ3ኛነት አሽከርካሪውን ደግሞ ጉዳቱን ስላደረሰ በአንድነትና በነጠላ ካሳ እንዲከፍሏቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ መሰረቱ።

ፍ/ቤቱም የከሳሽና የ3ቱን ተከሳሾች ክርክር መርምሮ አቶ አለማየሁ መኪናውን ለ2ኛ ተከሳሽ በሽያጭ ስላስተላለፈ ሊጠየቅ አይገባም። የጉዳት ካሳ የመካስ ኃላፊነት ያለባቸው የመኪናው ገዢና ተቀጥሮ መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው ሹፌር ናቸው ሲል ወሰነ።

የወ/ሮ አስናቀች ጠበቃ ኪሩቤል ኃ/ማርያም በውሳኔው ቅር ስለተሰኘ ስም ያላዛወሩት የመኪናው የቀድሞ ባለቤት አቶ አለማየሁም ሊጠየቁ ይገባል ብሎ ይግባኝ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለው ቀረ።

የወ/ሮ አስናቀች ጠበቃ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የተሽከርካሪው የቀድሞ ባለቤት የሆነው አቶ አለማየሁ የተሽከርካሪው ስሙ ሀብት ስላልተዛወረ የካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት፣ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ይታረምልኝ ሲል ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

ሰበር የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ሕጉን በመተርጐም ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት አንድ ክርክር እንጨምር።

2.ዳዊትና ተሻለ

አቶ ተሻለና ወ/ሮ ደብሪቱ የስ.ቁ. 3-07999 ኦሮ የሆነውን መኪና ብር 250 ሺህ ብር ከአቶ ዳዊት ላይ ይገዛሉ። ከሽያጩ ገንዘብ ውስጥ ብር 200 ሺህ ከፍለዋል። ሆኖም ገዢዎቹ አቶ ተሻለ እና ወ/ሮ ደብሪቱ የገዙት ተሽከርካሪያቸው የሽያጭ ውል ውል ክፍል ቀርቦ ባለመመዝገቡ ስሙ ሊዛወርባቸው አልቻለም። በዚህም የተነሳ መኪናወን ማስመርመርና ቦሎ ማሳደስ ባለመቻላቸው በተሽከርካሪው ሰርተው ገቢ ማግኘት አልቻሉም። ለዚህም ሰበቡ የሻጩ የአቶ ዳዊት ላይ ክስ መሰረቱ። በገዥው ምክንያት የመኪናው ስም ስላልተዛወረ ከመጋቢት 2000 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ሰርተን ልናገኝ የምንችለውን ብር 8ሺህ ስላሳጣ በተጨማሪ ብር 20ሺ ጨምሮ ይከፈለን ሲሉ ክስ አቀረቡ።

አቶ ዳዊት ቀርቦ የመኪና ሽያጭ ውሉን በአግባቡ ፈጽሜያለሁ። ይዞታውንም አስተላልፌያለሁ። የመኪናውን ባለቤትነት ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሁሉ ለገዥዎች አስረክቤያለሁ። ስም ማዞር የእኔ የሻጭ ኃላፊነትና ግዴታ አይደለም ሲል ተከራከረ።

ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ አቶ ዳዊት የመኪናው ባለሀብትነት ለማዛወር የሚያስፈልገውን ውል በውል አዋዋይ ፊት ለመፈፀም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ውሉ መፍረስ አለበት።

አቶ ዳዊት ለተከሳሾች ለእያንዳንዳቸው 112 ሺህ 500 ብር ይከፈል። ከሳሾችም መኪናውን ይመልሱለት ሲል ወሰነ።

አቶ ዳዊት ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ ጥቅምት 2001 ዓ.ም አቀረበ። ፍ/ቤቱም ይግባኙን መርምሮ ዳዊት ስም ለማዛወር የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ሁሉ ለገዢዎች አስረክቧል። ስም ማዛወር የሻጭ ግዴታ አይደለም። የመኪና ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት እንዲደረግ የሚያስገድድ ሕግ የለም። ስለዚህ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም በሚል የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሻረው።

አቶ ተሻለ በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረቡ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ደግሞ የከፍተኛ ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሮ የመ/ደ/ፍ/ቤትን ውሳኔ በማፅናት የመኪና ሽያጨ ውሉ መፍረስ አለበት አለ።

አቶ ዳዊት ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመኪና ሽያጭ ውሉን ከ3 ዓመት በፊት ፈጽሜያለሁ። የመኪናውን ባለሀብትነት ወደ ገዥዎች አላዛወርክም በሚል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ስለዚህ ውሳኔው ታይቶ ይታረምልኝ ሲል አመለከተ።

ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶበታል።

3.ሰበር ምን አለ?

ያነሳናቸው በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸው ሁለት ክርክሮች ሁለት መሰረታዊ ጭብጦችን አንስተዋል። አንድ የመኪና ሻጭ ወደ ገዢ ስም ለማዛወር ምን ግዴታዎች አሉበት? ግዴታዎቹን ተወጥቷል የሚባለውስ የትኞቹን ሁኔታዎች ሲያሟላ ነው የሚለው በሁለተኛው ክርክር ላይ የተነሳ ነው። በመጀመሪያ ክርክር ላይ ደግሞ በስጦታ ወይም በሽያጭ ለሌላ ሰው የተላለፈ መኪና ጋር በተያያዘ ሻጭ ወይም ስጦታ ሰጪ ተሽከርካሪው ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር ያለበትን ኃላፊነት ይመለከታል። በመቀጠል ክርክሮቹ ላይ የተሰጡትን አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እንመልከት።

 

 

3.1.   ስም ያላዛወረ የመኪና ሻጭ መኪናው ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊነት አለበት?

ይሄን ነጥብ ወ/ሮ አስናቀች መኪና ሽጠው ስም ባላዛወሩት በአቶ አለማየሁ ላይ ባቀረቡት የጉዳት ካሳ ላይ ነው የተነሳው። ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቅጽ 11 ላይ ታትሞ በወጣው የሰ/መ/ቁ. 24643 ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም ውሳኔ ሰበር ለውሳኔው መሰረት ያደረገው ተሽከርካሪዎች ልዩ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባለሀብት ማስተላለፊያ መንገዶች አንፃር የሕጉን ድንጋጌዎች በማየት ነው።

በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1186 ግዙፍነት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በግዢ ወይም በሌላ አኳሀን ወይም በኑዛዜ የታሰበው ሰው ንብረቱን በእጁ ባደረገ ጊዜ የተላለፈለት ይሆናል ይላል። ማለትም ተንቀሳቃሽ ንብረት ባለቤት ለመሆን ተጨማሪ ሁኔታ ማሟላት ሳያስፈልግ ንብረቱን መግዛት ወይም በስጦታ በኑዛዜ ወይም በሌላ ሁኔታ በእጅ ማድረግ በቂ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌ ልዩ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን እንደሚያካትት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1186(2) ላይ ተደንግጓል።

መኪናና ባለ ሞተር ተሽከርካሪዎች የምዝገባና የባለሀብትነትን ማስተላለፊያ ስርዓትን በመከተል መሆኑን በመንገዶች ላይ ጉዞንና ማመላለሻን ለመቆጣጠርና ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 256/1960 እና በተለያዩ ጊዜዎች የተሻሻለውን ሕግ ክፍል 360/1961 መመልከት ያስፈልጋል።

የፍጥነት ወሰኑ በሰዓት ከ20 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ልዩ ተሽከርካሪ በስተቀር ማንኛውም ባለሞተር ተሽከርካሪን ማስመዝገብ ግዴታ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 256/60 አንቀጽ 6 እና የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር አንቀጽ 21 ያስረዳል።

በዚህም መሰረት ምዝገባ አያስፈልጋቸውም ከተባሉት ተሽከርካሪዎች ውጭ ለአገልግሎት ከተላለፈ ቀን ጀምሮ በ30 ቀን የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር እንዲሰጠው ለሚመለከተው ፍ/ቤት ማመልከት አለበት። ባለቤትነቱ የተላለፈለትን አግባብ የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የቀድሞዋን ባለቤት የመታወቂያ ደብተር እና አስፈላጊ ሰነዶችን አያይዞ ማቅረብ አለበት።

በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት አንድ ተሽከርካሪ ከአንዱ ወደ ሌላ በሽያጭ፣ በስጦታ ወይም በሌላ መንገድ ሲተላለፍ ውል ከመዋዋል በተጨማሪ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተመዝግቦ የባለቤትነት ማስተላለፊያ አስፈላጊው ስርዓት መፈፀም አለበት። ይህም ተሽከርካሪዎች ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር ሊያስከትሉ የሚችሉት የጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሀገራት ልምድም መረዳት የሚቻል ነው።

በመሆኑም የተሽከርካሪ ባለሀብትነት የሚተላለፈው ተገቢው ምዝገባ በሚመለከተው መስሪያ ቤት ተሰጥቶ የተሽከርካሪው ባለቤትነት ስም ሲዛወር ነው።

ከዚህ አንፃር የፍትሐብሔር ሕጉን ከውል ውጭ የሚደርሱ ጉዳቶችን የሚመለከተውን አንቀጽ 2081(1) ስንመለከት አንድ ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት የሆነ ሰው ተሽከርካሪው ተሰርቆ እያለ ላደረሰው አደጋ ከተጠያቂነት ነፃ ከሚሆን በስተቀር መኪናውን ለመንዳት ባልተፈቀደለት ሰው እንኳን ሲሽከረከር ጉዳት ቢያደርስ የካሳ ኃላፊነት አለበት። ይህም የኃላፊነት አይነት ካለጥፋት ኃላፊነት ከሚያስከትሉ ምድቦች ውስጥ የሚመደብ ነው።

በመሆኑም አቶ አለማየሁ መኪናውን ለ2ኛ ተከሳሽ ሸጠው ስሙ ሳይዛወር በስማቸው ስለሚገኝ ተሽከርካሪው ላደረሰው ጉዳት ከ2ኛና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት አለባቸው። ለካሳው ኃላፊ በሆኑበት መጠን ንብረቱን ገዝቶ በእጁ አድርጐ ሲገለገልበት ከነበረው ሰው ላይ ከሶ ገንዘቡን ማስመለስ ግን ይችላል በማለት ስም ያላዛወሩት አቶ አለማየሁ ነፃ ናቸው በሚል የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።

3.2.   የመኪና ሻጭ ስም በማዛወር ግዴታ አለበት?

የአቶ ዳዊትን እና የአቶ ተሻለን ክርክር ላይ በስ/መ/ቁ. 56569 መጋቢት 23 ቀን 2003 ዓ.ም ሰበር በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቶበት በቅጽ 12 ላይ ታትሞ ወጥቷል። የውሳኔው ይዘት አቶ ዳዊት ስም ለማዛወር አስፈላጊውን ሰነዶች ለገዥዎች አስረክቧል። ተሽከርካሪው እዳ እገዳ እንደሌለበት ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ አቅርቧል። የመኪና ሽያጭ ውል በውል አዋዋይ ፊት እንዲደረግ የሚያስገድድ ሕግ የለም።

 

 

በመሆኑም አቶ ተሻለ ሊጠይቁ የሚገባቸው የተሽከርካሪ ምዝገባና ባለቤትነት ማረጋገጫ የሚሰጠውን የመንግስት አካል ነው። በመሆኑም ይህ ተከራካሪዎቹ በሌላ መዝገብ በነበራቸው ክርክር ተረጋግጦ እያለ የስር የመ/ደ/ፍ/ቤትና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሉ ይፍረስ በሚል የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በሚል ውሉን ሽሮ የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባውም ሲል ወስኗል።

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት የሚደርስ ጉዳቶችን የመካስ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?

-    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኤሌክትሪክ አደጋ ኃላፊ የሚሆነው በምን ሁኔታዎች ነው?

-    እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የደረሱ ኢ.ኤ.ኃ.ኮ ተከሳሽ የሆነባቸው ሶስት የኤሌክትሪክ ጉዳት ክርክሮች በምን ውሳኔ ተቋጩ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የኤሌክትሪክ ኃይል የዓለማችንን የስልጣኔ ግስጋሴ ፍጥነት የቀየረ ለማንኛውም የዕለት ተዕለት ህይወታችን የደም ስር ያህል ወሳኝ የሆነ የኃይል ምንጭ ነው። ነገር ግን አንዳንዴ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት መንስኤም ይሆናል። ለመሆኑ በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ንብረትና፣ ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ሲደርስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለጉዳቱ ኃላፊ የሚሆነው በምን አይነት ሁኔታዎች ነው? የሚለውን ነጥብ አግባብነት ያላቸውን ሕጎች እና እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ በመብራት ኃይልና በተጎጂዎች መካከል የተደረጉ ክርክሮችን እናያለን።

 

 

1. የጎረቤት አንቴና. . .

 

ጉዳዩ የተከሰተው በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ውስጥ ነው። ወልደሚካኤል ሻንቆ ጎረቤት ከአቶ ማቴያስ ባህር ዛፍ ላይ ሰቅለውት የነበረው የቴሌቭዥን አንቴና በነበረው ኃይለኛ ንፋስ ተገፍትሮ ከሌሊቱ 9፡45 ላይ በአጠገቡ በሚያልፈው የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ይወድቃል። ይሄኔ የአቶ ማቲያስ ቴሌቭዥን ከፍተኛ ድምፅ አሰምቶ ቤታቸውን በኃይለኛ ብርሃን ሞላው ከእንቅልፋቸው ደንግጠው ሲነሱ ኡኡ ድረሱልን ተቃጠልን የሚል ጩኸት አሰሙ። መምህር ወልደሚካኤልም ጩኸቱን ሰምተው ከእንቅልፋቸው ባነው በመውጣት ወዲያውኑ በመጣላቸው አደጋውን የማስወገድ ሃሳብ በእሳት የተያያዘውን የኤሌክትሪክ መስመሩን ለማላቀቅ ሲሞክሩ ጉዳት ደረሰባቸውና የቀኝ ቀለበት ጣትና ትንሽ ጣታቸው ተቆረጠ። ሌሎች ጣቶቻቸውም ደርቀው የቀኝ እግራቸው 5ኛ ጣትም ተቆረጠ። ከፍተኛ ስቃይና የአካል ጉዳትም ደረሰባቸው።

መምህር ወልደሚካኤልም ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን በዘረጋው መስመር ምክንያት ከፍተኛ የአካል ጉዳት ስለደረሰብኝ ካሳ ይከፈለኝ ሲሉ ከሰሱት። ክሱ የቀረበለት የሃዲያ ዞን ከ/ፍ/ቤት የከሳሹንና የተከሳሽን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ መምህር ወልደሚካኤል ላይ 63 በመቶ ቋሚ የአካል ጉዳት ስለደረሰ ይሰሩ የነበሩትን የመምህርነት ስራ መስራት ስለማይችሉ የሞራል ካሳን ጨምሮ ብር 139ሺህ 228 ብር ከ26 እንዲከፈላቸው መብራት ኃይል ላይ ፈረደ።

መብራት ኃይል በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኝ ቢጠይቅም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ውሳኔውን አፀናበት። ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መምህር ወልደሚካኤል ጉዳት የደረሰባቸው በተነሳው አደጋ የኤሌክትሪክ መስመሩን ሊያላቅቁ ሲሞክሩ በመሆኑ ብቻ መብራት ኃይል ለጉዳቱ ኃላፊ ነው መባሉ ሕጉን ያላገናዘበ ነው ስለዚህ ይታረምልኝ ሲሉ አመለከቱ። ሰበር ግራ ቀኙን አከራክሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን እና እናቆየውና ሌላ ክርክር እንመልከት።

2. ዮድ አቢሲኒያ ላይ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ

 

ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተከራይቶ በሚሰራበት ቤት ላይ አቅራቢያ ያለ የኤሌክትሪክ መስመር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ ተበጥሶ ይወድቅና የእሳት ቃጠሎ ይነሳል። በቃጠሎው የምግብ አዳራሹ አንደ ሚሊዮን ሃያ አራት ሺህ አምስት መቶ ስልሳ ሶስት ብር የሚገመት ንብረት ወደመ።

አቶ ትዕዛዝ ኮሬ የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኤሌክትሪክ መስመሩ መበጠስ ምክንያት በደረሰው ቃጠሎ ለደረሰው ውድመት የንብረቱን ግምት ካሳ እንዲከፍላቸው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቀረቡ።

መብራት ኃይል ለክሱ በሰጠው መልስ የእሳት አደጋው ደርሶ ንብረቱን ከማውደሙ በፊት የተበጠሰ የኤሌክትሪክ መስመር የለም። የቃጠሎው ምክንያት ኤሌክትሪክ ስለመሆኑ የቀረበው ማስረጃ ተቀባይነት የለውም። መስመሩ ሲዘረጋም የከሳሽ ድርጅት አልነበረም። ስለዚህ ክሱ ውድቅ ይደረግ ሲል መልስ ሰጠ።

ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ቃጠሎው የደረሰው በኤሌክትሪክ መስመሩ መውደቅ መሆኑን ከሳሽ ቢያስረዱም ቃጠሎው የደረሰው መብራት ኃይል ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት በፈፀመው ተግባር መሆኑን ስለሚያስረዱ መብራት ኃይል ለጉዳቱ ኃላፊነት የለበትም ሲል ወሰነ።

የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት ይግባኝ ቢጠይቁም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ስላፀናው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። የኤሌክትሪክ መስመሮቹ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። አደጋው ከመድረሱ በፊት ሪፖርት አድርጌ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ያደረገው ጥገና አስተማማኝ ስላልነበር አደጋው እንደደረሰ አስረድቻለሁ። ይህም ቸልተኝነቱን የሚያረጋግጥ ሆኖ እያለ የስር ፍ/ቤቶች ለጉዳቱ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኃላፊነት የለበትም በማለት በመወሰናቸው የህግ ስህተት ፈፅመዋል፤ ስለዚህ ይታረምልኝ ሲሉ ጠየቁ።

መብራት ኃይል በበኩሉ የእሳት ቃጠሎ የተነሳው ከኤሌክትሪክ መስመሩ ሳይሆን ከምግብ አዳራሽ ወጥ ቤት በተነሳ እሳት ምክንያት መሆኑን ማስረጃ ስላቀረብኩ የሰበር አቤቱታው ውድቅ ይደረግ ሲል መልስ ሰጠ። ሰበር የሰጠው ውሳኔ ይቆየንና አንድ ሌላ ክርክር እንድገም።

 

3. ፌሮ ብረቱ ኤሌክትሪኩን፣ ከሳሽ ደግሞ ፌሮውን ነኩና

 

አቶ ወልዱ ግንበኛ ናቸው። አቶ ሳህለ ቀጥረዋቸው የአቶ ታከለን ባለሁለት ፎቅ ህንፃ በመስራት ላይ እያሉ ነበር አደጋው የደረሰባቸው። አደጋው የደረሰው የሚሰሩበት ፎቅ ቁመቱ እየጨመረ ሲሄድ አቶ ወልዱ በስራ ላይ እያሉ በያዙት ፌሮ ብረት ከፍተኛ ኃይል ተሸክሞ የሚያልፈውን የኤሌክትሪክ መስመር በመንካታቸው ሲሆን በዚህም አደጋ ሁለት እጆቻቸው በመቆረጣቸው ሙሉ በሙሉ አቶ ወልዴ የመስራት ችሎታቸውን ማጣታቸው በህክምና ቦርድ ተረጋገጠ።

አቶ ወልዱ በፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት መብራት ኃይል፣ አሰሪያቸውን እና የህንፃውን ባለቤት ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲከፍሏቸው ከሰሱ። ፍ/ቤቱ ከሳሽና ተከሳሾችን አከራክሮ ካሳ መክፈል ያለበት አሰሪውና የቤቱ ባለቤት ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን  ነው ብሎ የአቶ ወልዴን የቀን ገቢ ብር ሃምሳ ለቀሪ የስራ እድሜያቸው በማስላት 91ሺ ብር እንዲከፍል ወሰነ።

በውሳው ላይ መብራት ኃይልም አቶ ወልዴም ይግባኝ ስላቀረቡ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮ መብራት ኃይልና የአቶ ወልዴ አሰሪ አቶ ሳህሌ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ስለሆኑ በጋራ 113ሺህ 500 ብር ለአቶ ወልዴ እንዲከፍሉ ወሰነ።

መብራት ኃይል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረበ። የህንፃው ቁመት ወደ ኤሌክትሪክ መስመሩ ሲጠጋ መስመሩ እስኪነሳ ስራው ማቆም የነበረባቸው የአቶ ወልዴ አሰሪ ናቸው ለጉዳቱ ኃላፊ መሆን ያለባቸውም እሳቸው ሆነው ኃላፊ መባሌ አላግባብ ነው አሉ።

አቶ ወልዱ ከማናቸውም መንገድ ህዝብ በብዛት በሚገኝበት ስፍራ የሚዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር የአደጋ መከለያ ሊኖረው እንደሚገባ የኤሌክትሪክ ደንብ ቁጥር 49/91 ይደነግጋል። መብራት ኃይል ግን ይህን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ አደጋው ስለደረሰ ኃላፊነት አለበት ሲሉ መልስ ሰጡ። ሰበር የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ውሳኔ ሰጠ። ውሳኔዎቹን ከማየታችን በፊት ለካሳ ኃላፊነት መስረት የሚሆኑትን የሕጉን ድንጋጌዎች በአጭሩ እንያቸው።

 

 

4. የካሳ ኃላፊነት

 

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2026 ከውል ውጭ የሆኑ የኃላፊነት ምንጮችን ደንግጓል። የመጀመሪያው ማንኛውም ሰው የውል ግዴታ ባይኖርበትም በፈፀመው ጥፋት በሌላ ሰው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት። ይህ መርህ በጥፋት ላይ የተመሰረተ የካሳ ኃላፊነት ነው። ጥፋት ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የሚደረግ አንድን ነገር የማድረግ ወይም ማድረግ ያለበትን ባለማድረግ ሊከሰት ይችላል።

ሌላው የካሳ ኃላፊነት ደግሞ ማንም ሰው ጥፋት ኖረባቸውም አልኖረባቸውም በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚችል ስራ ከሰራ ወይም በእጁ የያዘው ነገር ንብረቱ የሚጠቀምበት እቃ ወይም የሚሰራው ስራ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ኃላፊ ይሆናል። ለሁለቱም ሁኔታዎች ጉዳቱን ያደረሰው ሌላ ሰው ቢሆንም በሕግ ኃላፊነት ያለበት ሰው (የንብረት ባለቤት፣ አሰሪ፣ ሞግዚት) ኃላፊነት አለባቸው።

በፍ/ብ/ሕ/ቁ/ 2066 አንድ ሰው ጥፋት ባይኖርበትም በራሱ ላይ ፣ በንብረት ወይም በሌላ ሰው ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል እርግጠኛ አደጋን ለመከላከል በሌላ ሰው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ካደረሰ የመካስ ኃላፊነት አለበት። ሆኖም ጉዳቱ የደረሰው በተጎጂው ጥፋትና ምክንያት ከሆነ ጉዳት አድራሹ አይጠየቅም። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2069 ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋትን ጨምሮ የሚፈነዳ መርዝና ነገሮችን በማከማቸት የመሬትን ቅርፅ ወይም መልክ በመለወጥ አደገኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ስራ በማካሄድ ሌላ ሰው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሥራውን የሚሰራው ሰው ኃላፊ ሲሆን ጉዳቱን ያደረሰው መንግስት ወይም ስራውን እንዲሰራ የተፈቀደለት ተቋም ቢሆንም በኃላፊነት ለሚሰራው ስራ ላደረሰው ጉዳት አጠፋም፣ አላጠፋም ኃላፊ ነው። ሆኖም አሰሪው ጥፋት ካልፈጸመ የዋናው ተጎጂ ጎረቤት በሆኑ ንብረቶች ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት የደረሰ መበላሸትን የመካስ ኃላፊነት እንደሌለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2070 ላይ ተደንግጓል። ያነሳነው ጉዳይ መሰረታዊ የካሳ ኃላፊነቶችን የሚደነግጉት እነዚህ አንቀፆች ናቸው፡

5. ሰበር ምን አለ

 

የአቶ ወልደሚካኤል ጉዳይ ሰበር በሰ/መ/ቁ 63231 ግንቦት 6 ቀን 2004 በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። አቶ ወልደሚካኤል ላይ የደረሰው ጉዳት አንቴናው ኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ በመውደቁ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጥፋት ሳይኖርበት ተጠያቂ የሚያደርገውን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለማድረጉን ሳያጣሩ የስር ፍ/ቤቶች ካሳ እንዲከፍል መወሰናቸው አግባብ አይደለም። በመሆኑም የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍቤት የተነሱትን ነጥቦች አጣርቶ ተገቢውን ውሳኔ ይስጥ ብሎ ጉዳዩን መልሶለታል።

በሰ/መ/ቁ 65395 የካቲት 26 ቀን 2004 በዋለው ችሎት የዮድ አቢሲኒያን እና የመብራት ኃይልን ክርክር ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና የአካባቢ ጥበቃን የሚመለከቱ የተለያዩ አዋጆችንና ደንቦችን በመጥቀስ በነዚያ ደምቦች መሰረት ዮድ አቢሲኒያ ላይ ጉዳት ያደረሰው የኤሌክትሪክ መስመር ሲወድቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ወይስ አልተወጣም፣ መስመሩ የኤሌክትሪክ ኤጀንሲ ያወጣውን የጥፋት ደረጃ ያሟላ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ካስፈለገ ሙያዊ ማብራሪያ ኤጀንሲው እንዲያቀርብ አድርጎ እንዲወስን የተሰጠውን የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሽሮ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍቤት መልሶታል። ሁለቱም ውሳኔዎች ቅጽ 13 ላይ ታትመው ወጥተዋል።

በአቶ ወልዱና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መካከል የነበረው ክርክር በሰ/ወ/ቁ 57 904 ታህሳስ 15ቀን 2003 ውሳኔ አግኝቶ በቅጽ 11 ላይ ታትሞ ወጥቷል። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጉዳቱ የደረሰው በአቶ ወልዱ ጥፋት ምክንያት መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ባለማቅረቡ መስመሩ በአደጋ መካላከያ ፕላስቲክ ተሸፍኖ የነበረ ባለመሆኑ በአቶ ወልዱ ከፍተኛ ፍ/ቤቱ የወሰነውን 113 ሺህ 500 ብር ካስ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና አሰሪው እንዲከፍሉ ሲል ውሳኔውን አፅንቷል።

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text67220); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-         ስለ አክሲዮን ማህበር ምንነት መሰረታዊ ነጥቦች፣

-         የአክሲዮን ማህበር የስራ አመራር አባላት ግዴታና ኃላፊነቶች፣

-         የስራ አመራር አባላትን ባለአክስዮኖች ከሰው መጠየቅ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች፣

-         በአንድ አክሲዮን ማህበር አስተዳዳሪዎች ላይ አባላት ያቀረቡት ክስ በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ ከንግድ ማህበራት መሃል አንዱ የሆነው የአክሲዮን ማህበር የአስተዳደር ስራ ላይ ችግሮች ሲፈፀሙ የማህበሩ አባላት ያሉአቸውን መብቶች እና የአክሲዮን ማህበሩ አስተዳዳሪዎች ያሉባቸው ተጠያቂነት እስከምን ድረስ እንደሆነ እናያለን። መነሻችን እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ አስገዳጅ ውሳኔ የተሰጠበት ባነሳነው ጉዳይ ላይ የተደረገ ክርክር ነው።

1.የአማኑኤል ፀጋ አክሲዮን ማህበርና አባላትን አስራ ሁለቱ ስራ አመራሮች

እነ ባህሩ እና ሌሎች የማህበሩ አባላት ያቋቋሙትን በጠቅላላ ጉባኤው ማህበሩን እንዲያስተዳድሩ እነ ባህሩን መረጣቸው። በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የስራ አመራሮች እየመሩት ስራውን ሲያካሂድ የነበረው የአማኑኤል ፀጋ አክሲዮን ማህበር ባሰራው ህንፃ ውስጥ የግንባር ሱቆች (ፊት ለፊት ለንግድ አመቺ የሆኑ ሱቆችን) ላይ ከመተዳደሪ ደንቡ ውጭ ግልፅ ባልሆነ ስብሰባ ተሰብስበው የወሰኑት ውሳኔ የአባላቱን መብት ስለሚጎዳና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጭ ስለሆነ ይፍረስ ብለው አባላት በእነ ባህሩ አብርሃም በአጠቃላይ 12 የስራ አመራሮች ላይ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ አቀረቡ።

የስራ አመራሮቹም ለቀረበባቸው ክስ መልስ እንዲሰጡ መጥሪያ ደርሷቸው በሰጡት መልስ ክሱ አይመለከተንም ብለው ካዱና ያስከስሰናል ቢባልም እንኳን በን/ሕ/ቀ 365(1) መሠረት ክስ መመስረት የሚችለው እራሱን የቻለ ህጋዊ ሰውነት ያለው የአክሲዮኑ ማህበሩ እንጂ አባላት አይደሉም፤ በመሆኑም ክሱ ውድቅ ይደረግ ሲሉ ጠየቁ።

ፍ/ቤቱም ተከሳሾቹ የአክሲዮን ማህበሩ የስራ አመራሮች የጠቀሱትን ንግድ ሕጉን አንቀጽ ጠቅሶ በሕጉ ላይ የተጠቀሰውን ቅድመ ሁኔታ ስላላሟላችሁ ክስ ማቅረብ አትችሉም ብሎ መዝገቡን ዘጋባቸው።

የአክስዮን ማህበሩ አባላት ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ ማቅረብ አትችሉም የሚለው ውሳኔ እንዲሻር ይግባኝ ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ ጭራሽ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ስላፀናው የስር ፍ/ቤቶች “አባላት በአክሲዮን ማህበሩ አመራሮች ላይ ክስ ማቅረብ አይችሉም” በሚል የሰጡት ውሳኔ ላይ መስረታዊ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመ ይታረምልን ሲሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረቡ። ሰበር ሰሚው ችሎት በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት ለውሳኔው መሰረት የሆኑትን የሕግ አንቀፆችን እንመልከት።

2.የአክስዮን ማህበሩ፡-

የአክስዮን ማህበር በንግድ ሕጋችን እውቅና ከተሰጣቸው የንግድ ማህበራት መካከል አንዱ ነው። የአክሲዮን ማህበር አባላቱ ሊሰማሩበት ለሚፈልጉት የንግድ ዓላማ የአክሲዮን ዋጋ በሚል የሚቀመጠውን እኩል መጠን ያለው የድርሻ ክፍልፋይ በመግዛት ወይም በአይነት በማዋጣት የሚያቋቁሙት ማህበር ነው። የአክሲዮን ማህበር ከአባላቱ የተነጠለ ህጋዊ ሰውነት ያለው ሲሆን መክሰስ፣ መከሰስ ንብረት ማፍራት ውል ማዋዋል ሌሎችንም ሕጋዊ ተግባራት በስሙ ማካሄድ ይችላል። የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ቀድሞ እንደሚሰማራበት የስራ ዘርፍ እንደሚጠይቀው ዝቅተኛ የመነሻ ካፒታል የአክሲዮን ዋጋቸው እኩል በሆኑ የአክሲዮን ድርሻዎች ይከፋፈላል። አባላት በሕግ እንደ ባንክ እና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛው መያዝ የሚችሉት የአክሲዮን ድርሻ ካልተወሰነ ከዝቅተኛው በመተዳደሪያ ደንቡ በሌላ መልኩ ካልተወሰነ ከአንድ አክሲዮን አንስቶ የአባላቱ ቁጥር በን/ሕ/ቁ 307 (1) መሠረት ከአምስት እስካላነሰ ድረስ አቅማቸው የቻለውን የአክሲዮን ድርሻ መግዛት ይችላሉ። የአክሲዮን ማህበር በ1952 የወጣው የንግድ ሕግ ቁጥር 306 የማህበሩ ዋና ገንዘብ ቢያንስ ከ50 ሺህ ብር የማያንስ የአንድ የአክሲዮን ዋጋም አስር ብር እንዲሆን ደንግጓል። ሆኖም ግን አሁን ከጊዜው የንግድ እንቅስቃሴ አንጻር እንደ ባንክ እና ኢንሹራንስ ያሉት የአክሲዮን ማህበራት የሚያስፈልጋቸው ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን በሚሊዮኖች እንዲሆን በሕግ ተወስኗል። ሌሎችም የተለያዩ የንግድ ስራ ዘርፎች የሚያስፈልገውን የመነሻ ካፒታል የሚወስኑ ሕጎች የሚኖሩ ሲሆን አክሲዮን ማህበሩ ሕጋዊ እውቅናና ፍቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው ካፒታል ካለ ያን ካፒታል ማሟላት አለበት። ዝቅተኛው የአክሲዮን ዋጋ የነበረው 10 ብርም በአሁኑ የሀገራችን ኢኮኖሚ ገንዘቡ ካለው ዋጋ አንጻር ተግባራዊ አይደለም። አሁን በአብዛኛው አንድ የአክሲዮን ዋጋ አንድ ሺህ ብር ሲሆን አንዳንድ ዝቅተኛ ካፒታል ያላቸው ማህበራት የመቶ ብር የአክሲዮን ዋጋ አላቸው።

የአክሲዮን ማህበር ውስጥ አባላት ማህበሩ ለሚኖርበት ግዴታ ኃላፊነት ያለባቸው ባላቸው ድርሻ ልክ በመሆኑ እና ለስራ የሚያስፍልገውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ከብዙ ሰዎች ማሰባሰብ ስለሚያስችል የአባላቱ ቁጥር ዝቅተኛው እንጂ ከፍተኛው ገደብ ስለሌለው ህዝባዊ ወይም የብዙ ሰዎች ንብረት መሆን የሚችል ማህበር ነው። የማህበሩ ህልውናም በአብዛኛው ከአባላት ህልውና የተነጠለ በመሆኑ አባላት ቢሞቱ፣ ቢከስሩ በሕግ ኃላፊነት ቢወሰንባቸው ለወራሾች ለእዳ ጠያቂዎች ወይም ለሌሎች አባላት ወይም ለውጭ አዲስ ለሚገቡ አባላት ስለሚተላለፉ ቀጣይነት አለው። ማህበሩ የሚተዳደረው በንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች መሰረት በሚያወጣቸው የመመስረቻ ፅሁፎች የመተዳደሪያ ደምብ መሰረት ነው። ይህን ያህል ጠቅለል ባለ መልኩ የአክሲዮን ማህበርን ምንነት ካየን አስተዳዳሪዎችን ኃላፊነት እናንሳ፡-

3.የአክሲዮን ማህበሩ አስተዳዳሪዎች፡-

በን/ሕ/ቁ 347 መሠረት የአክሲዮን ማህበርን የአስተዳደር ስራ የሚያካሂዱት ከአባላት መካከል በሚመረጡ ከ3-12 የሚደርሱ አባላት ባሉት የአስተዳደር ምክር ቤት ወይም የዳይሬክተሮች ቦርድ ነው። እነዚህ የስራ አመራር ቦርድ አባላት የሚመረጡት በአክሲዮን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ወይም ወኪሎቻቸው በሚሰጡት ድምፅ ወይም የመስራቾች ጉባኤ ስልጣቸውን ሲያፀድቀው ነው። ጠቅላላ ጉባኤውም በማናቸውም ጊዜ አስተዳዳሪዎቹን የመሻር ስልጣንም በንግድ ሕጉ ቁጥር 354 ላይ ተሰጥቶታል። የአስተዳደር ቦርዱ ውሳኔዎችን የሚያሳልፈው በአብላጫ ድምፅ ሲሆን ይህም በቃለ ጉባኤ ተይዞ ተፈርሞበት በዋናው መስሪያ ቤት ለማህበርተኞች ወይም ለሌላ ሰው ክፍት መሆን አለበት።

አስተዳዳሪዎች በን/ሕ/ቁ 362 ላይ ግዴታዎቻቸው ተቀምጠዋል በዚህም መሰረት የአስተዳደርና የጉባኤዎችን ቃለ ጉባኤ፣ ሂሳብና የሂሳብ መዝገብ በአግባቡ በጥንቃቄ የመያዝ ግዴታቸው ቀዳሚ ነው። ሂሳቦችን ለተቆጣጣሪዎች ማቅረብ፣ የስራ አካሄድና ማህበሩን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት ማቅረብ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ጠቅላላ አስቸኳይ ወይም ልዩ ጉባኤዎችን መጥራት በሕግ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት የመጠባበቂያ ገንዘብ መያዝ እና ማህበሩ እዳውን ካልከፈለ ከባለገንዘቦች ጋር የመጠባበቂያ ገንዘብ ስምምነት ማድረግ ወይም የማህበሩ መክሰር በፍ/ቤት እንዲታወጅ የሚቀርብ ግዴታ አለባቸው።

ስልጣቸው የሚመነጨው ለሕግ ከማህበሩ የመመስረቻ ወይም የመተዳደሪያ ደንብ ወይም ጉባኤዎች ውሳኔ ሲሆን ስራውን ለመስራት የሚያስፈልገውን የስልጣን ከውክልናም በነዚሁ ውሳኔዎች የሚያገኙት ነው።

የስራ አመራር አባላቱ ከላይ በስልጣን ምንጮቻቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነቶችና ውሳኔዎች ወኪል እንደሚያደርገው በጥንቃቄ መፈፀም ያለባቸው ሲሆን ግዴታቸውን ካልተወጡ በን/ሕ/ቁ 364 (2) መሠረት ሳይከፋፈል ኃላፊት አለባቸው። አባል የሆነ ሰው በውሳኔው ላይ አለመስማማቱን በቃለ ጉባኤው ላይ ካሰፈረና በተቆጣጣሪ ካመለከተ ነው፤ በአንድ ላይ ተጠያቂ ከመሆን የሚድነው። እነዚህን ኃላፊነቶች ካልተወጡ በኃላፊነት ስለሚጠየቁበት ሁኔታና እነማን መክሰስ እንደሚችሉ በንግድ ሕጉ ላይ ተቀምጧል።

የአክሲዮን ማህበሩ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአጀንዳ ባይያዝም አስተዳዳሪዎቹ ላይ ክስ እንዲቀርብ መወሰን ይችላል። በን/ሕ/ቁ 365 መሠረት ይህ ክስ የሚቀርበው ወይም ጉዳዩ በግልግል እንዲያልቅ የሚወሰነው ከማህበሩ ዋና ገንዘብ 20 ከመቶ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች የድጋፍ ድምፅ ሲሰጡት ሲሆን ይህም የአስተዳዳሪዎችን መሻርና አዲስ የመሾምን ውጤት ያስከትላል። ክስ ወይም ጉዳዩን በግልግል የመፍታት ውሳኔ ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆኑት የአክሲዮን ማህበሩ ባለድርሻዎች ያልተቃወሙት መሆን አለበት። ክስ እንዲቀርብ ከተወሰነ በኋላ በሶስት ወር ጊዜ ማህበሩ ካልከሰሰ ክሱ እንዲቀርብ የደገፉት አባላት የማህበሩን ክስ በራሳቸው ማቅረብ ይችላሉ።

አስተዳዳሪዎች የማህበሩን ሙሉ ገንዘብ የመጡበት ግዴታዎችን ካልተወጡ በን/ሕ/ቁ 366መሰረት ከአክሲዮን ማህበሩ ላይ ገንዘብ ጠያቂዎች አስተዳዳሪዎችን በኃላፊነት መክሰስ የሚችሉ ሲሆን የማህበሩ ንብረት እና ለመከፈል የማይበቃ ከሆነም በገንዘብ ጠያቂዎች ሊከሷቸው ይችላሉ።

አክሲዮኖችና ሶስተኛ ወገኖች በአስተዳዳሪዎች ጥፋት ወይም ማጭበርበር ለደረሰባቸው ጉዳት ኪሳራ እንዲከፍሏቸው አስተዳዳሪዎችን የመጠየቅ መብታቸውም በን/ሕ/ቁ 367 ላይ ተጠብቋል።

4.ሰበር ምን አለ?

የአማኑኤል ፀጋ አክሲዮን ማህበር ላይ አባላት ያቀረቡትን ክስ በሰ/መ/ቁ 23384 ሐምሌ 10 ቀን 1999 በዋናው ችሎት ውሳኔ ሰጥቶበታል። በዚህም ውሳኔ በን/ሕ/ቁ 363 ላይ ቅድመ ሁኔታዎች የተቀመጡት ማህበሩ በአስተዳዳሪዎች ላይ ለሚያቀርበው ክስ ነው። አባላት ግን አስተዳዳሪዎች በወሰኑት ውሳኔ የተነሳ ተጎጂ መሆናቸውን ለን/ሕ/ቁ 367 መሠረት ማረጋገጥ ከቻሉ የኃላፊነት ክሱን ማቅረብ ስለሚችሉ የስር ፍ/ቤት ተገቢ ያልሆነውን አንቀፅ በመጥቀስ የባለአክሲዮኖች ክስ መዝጋቱ የሕግ ስህተት በመፈፀሙ ውሳኔውን ሽሮ ጉዳዩን ወደ መጀመሪያው ደረጃ ፍ/ቤት በመመለስ የአስተዳዳሪዎች ውሳኔ በከሳሽ የአክሲዮን ማህበሩ አባላት ላይ የደረሰው ጉዳት መኖር አለመኖሩን አጣርቶ እንዲወስን መልሶለታል።

ከውርስ መነቀል

June 10, 2015

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-         ተናዛዥ ሕጋዊ ወራሾቹን ከውርስ ሊከለክል የሚችልበት ሁኔታና ገደቦቹ፣

-         ከውርስ መነቀልና አይነቶቹ፣

-         በልጅና በሟች የእህት ልጅ ልጅ መካከል የተደረገው ከውርስ የመነቀል ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምናወጋው አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሀብቱን በኑዛዜ ሲያወርስ በሕግ ወራሾቹ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆቹን ሀብቱን እንዳይወርስ ማድረግ ይቻላል? በሕግ ወራሽ የሟችን ሀብት እንዳይወርስ ማድረግ የማይችሉት የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው። በኑዛዜ የወራሽነት መብቱን እንዲያጣ የተደረገ ወራሽስ ምን መከራከሪያዎችን ማንሳት ይችላል? የሚሉትን እና ሌሎችንም ተያያዥ ነጥቦች እናነሳለን።

1.የወ/ሮ በላይነሽ ኑዛዜ፡-

ወ/ሮ በላይነሽ ሚያዝያ 1996 ተናዘዙ። ከተናዘዙ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ኑዛዜው ተከፍቶ ታየ። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ቤቴን ለእህቴ ልጅ ልጅ ለኤርምያስ አውርሼዋለሁ። ለልጄ ለፍቃዱ ደግሞ አንድ አንድ መቶ ብር ብቻ ስጡልኝ የሚል ነበር። ፈቃዱ እናቱ ያለውን አንድ ቤት ለአክስቱ የልጅ ልጅ ለኤርሚያስ ብቻ ሰጥተው እሱን ልጃቸውን በአንድ መቶ ብር ማሰናበታቸው አስከፋው።

ፍቃዱ ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ኑዛዜውን አቅርቦ የወ/ሮ በላይነሽ የኑዛዜ ወራሽ መሆኑን አረጋግጦ መጣ። በዚህ ውሳኔ መሰረት የእናቱ ብቸኛ ቤት ለአክስቱ የልጅ ልጅ ሊሰጥበት በመሆኑ ፍቃዱ በሌለሁበት የተሰጠው ውሳኔ መብቴን ይነካል ልጅ እንደመሆኑ በሕግ አገኝ የነበረውን የውርስ ድርሻ በማሳጣት በ100 ብር ብቻ ስለተሰጠኝ አላግባብ ከኑዛዜ ተነቅያለሁ። ስለዚህ ኤርምያስ የኑዛዜ ወራሽ መሆኑን የሚያረጋግጠው ውሳኔ ይሻርልኝ ሲል አመለከተ።

ፍ/ቤቱም የኤርሚያስና የአያቱ የህግ ልጅ የሆነው የፍቃዱን ክርክር መርምሮ ኑዛዜው በሕግ የተቀመጡትን መስፈርቶች ስለሚያሟላና ሟች ለፍቃዱ አንድ መቶ ብር በማውረሳቸው ነቅለውታል። (በውርስ ሀብታቸውን እንዳያገኝ) አድርገዋል ሊባል የሚችል ባለመሆኑ የሰጠሁት የኑዛዜ ወራሽነት ውሳኔ ሊሽር አይገባም ብሎ ወሰነ።

አቶ ፍቃዱ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅር ስለተሰኙ ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት እና ለሰበር ችሎቱ አቤቱታ ቢያቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ ስለቀረ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመ ውሳኔው ይሻርልኝ ሲል ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ሰበር አቤቱታ አቀረበ። ሰበር ሰሚው ችሎት የፍቃዱንና የኤርሚያስን ክርክር እና የወ/ሮ በላይነሽን ኑዛዜ መርምሮ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ለክርክሩ መነሻ የሆኑትን የሕግ አንቀፆች ምን እንደሚሉ እንጥቀስ።

2.ከውርስ መነቀል

አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ አብረውት የማይሞቱ ቀሪ መብቶቹና ግዴታዎቹን ለወራሾቹ ይተላለፋሉ። ይህ የውርስ መተላለፍ በሁለት መንገዶች የሚደረግ ነው። አንደኛው የሚፀና ኑዛዜ ሳያስቀር የሞተ ሰውን ውርስ የሚመለከት ሲሆን በሕግ መሰረት ከሟች ልጆች፣ እነሱ ከሌለ ወላጆች እያለ በቅደም ተከተል የወራሽነት መብታቸውንና ከውርሱ የሚደርሳቸውን ድርሻ በፍ/ብሔር ሕጉ የሕግ የወራሽነት መብት ድንጋጌዎች መሰረት ወራሾች መብታቸውን የሚያገኙበት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ሟች በሕግ ፊት ተቀባይነት ያለው የፀና ኑዛዜ ትቶ ሲያልፍ በኑዛዜው መሰረት ኑዛዜው ሟች የሚፈልገውን ሃሳብ ይዟል ተብሎ ስለሚገመት ከሞተ በኋላ በሚቀረው ኑዛዜ መሰረት የኑዛዜ ወራሾች እና የኑዛዜ ተጠቃሚዎች እና ከሟች ሀብት የሚደርሳቸው የውርስ ድርሻ የሚለይበት ነው። በተጨማሪ ሞግዚትነትን እንዲሁም ደግሞ ከንብረቱ ላይ ስጦታ፣ ቀለብ ወይም መጦሪያ ማግኘት ያለባቸውንም ሰዎች ሊጠቀስም ይችላል።

ኑዛዜ ሟች ከሞተ በኋላ በሕግ ተፈፃሚነቱ የሚያገኝ ሰነድ በመሆኑ ኑዛዜው ባይኖር በሕግ ከሟች የውርስ ሀብት ላይ ድርሻ ያላቸውን አንድ ወይም ብዙ ወራሾቹን ከውርስ መብታቸው መንቀል (መከልከልም) ይቻላል። በሕጉ አግባብ የተደረገ ኑዛዜ የሚፀና ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ የሟች ስለ ውርስ ሀብቱ በህይወት እያለ የነበረው ሃሳብ ከሞተ በኋላ ተፈፃሚ የሚሆንበት ሰነድ በመሆኑ በሕግ ተቀባይነት ያለው ከውርስ መነቀልም እንዲሁ በሕግ ከተቀመጠው የወራሽነት መብት በላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል። ሟች በኑዛዜ በሁለት መንገድ ወራሾቹን ከውርስ ሊነቀል ይችላል።

2.1     በግልጽ ከውርስ መንቀል፡- ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ ያለ ኑዛዜ ሊወርሱት የሚችሉትን ወራሾቹን በሙሉ ወይም አንደኛቸውን በግልፅ በስም ወይም በዝምድና ደረጃቸው በመጥቀስ የወራሽነት መብት እንዳይኖራቸው መከልከል (መንቀል) እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 937(1) ሆኖም ተናዛዡ በግልፅ ወራሾቹን ከኑዛዜ በሚነቅልበት ጊዜ ሁለተኛና ከዚያ በላይ ያሉ የሕግ የወራሽነት ደረጃ ያላቸው ወራሾችን (የሟች እናት አባት፣ አያቶች፣ እህት ወንድም፣ አክስት ፣ አጎት) የመሳሰሉትን የውርስ ሀብቱን ማግኘት እንደሌለባች ብቻ በግልጽ በመጥቀስ ማስቀመጥ ብቻ ከውርስ መነቀሉን በሕግ ፊት የፀና የሚያደርገው ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 937 (1) መሠረት እነኚህ በግልጽ የተነቀሉ ወራሾች ከተናዛዡ በፊት እንደሞቱ ይቆጠራል፡ (በሕግም እራሳቸው የመውረስ መብቱን ሳያገኙ የሞቱ ተተኪዎች (ልጆች ካላቸው) መውረስ የሚችሉበት የምትክነት ሕግ አለ) በመሆኑም የተነቀሉት የሟች ዘመዶች ለመውረስ የሚያስፈልገው ሟች በሚሞትበት ጊዜ በሕይወት የመኖር መስፈርትን እናዳላሟሉ ይዘለሉና መብቱ ለሌሎች የሕግ ወራሾች ወይም በኑዛዜ ልዩ ወይም ጠቅላላ ስጦታ ለተደረገላቸው ሰዎች ይተላለፋል።

ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆችን (የሟች ልጅ፣ የልጅ ልጅ) በግልፅ ኑዛዜ ከውርስ ለመንቀል ግን በፍ/ብ/ሕ/ቁ938 (1) መሠረት ተናዛዡ ከውርስ ለመንቀል የደረሰበትን ምክንያት መግለፅ አለበት። ምክንያቱ ሳይገልፅ ልጁን ወይም የልጅ ልጁን ከውርስ ከነቀለ ኑዛዜው በሕግ ፊት አይፀናም።

የሚሞት ሰው ትክክለኛውን ይናገራል በሚል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 938(2) ከውርስ የመንቀያ ምክንያት ትክክል (እውነት) አድርገው መቁጠር እንዳለባቸውና እውነት ነው አይደለም የሚለውን የመመርመር ስልጣን እንደሌላቸው ይደነግጋል። ሆኖም ግን ዳኞቹ ተናዛዥ ለወሰደው እርምጃ አደረሰብኝ ብሎ የጠቀሰው ምክንያት በቂ ነው ወይም የሚለውን ይመረምራሉ። ምክንያቱ በቂና በምክንያታዊ አስተሳሰብ ከውርስ ለመንቀል የሚያበቃ ሆኖ ካገኙት ከውርስ መነቀሉ በሕግ ፊት ውጤት የሚያስከትል ይሆናል።

2.2     በዝምታ ከውርስ መንቀል፡- ተናዛዡ ከ2ኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ያላቸው ዘመዶቹን (ከወላጆች እስከ ቅድመ አያት) ያሉትን በዝምታ መንቀሉን ወይም እንዳይወርሱ መከልከሉን ሳይገልጽ ለአንደኛው ያለኑዛዜ ወራሽ ወይም ለሌላ ሰው ሀብቱን ጠቅላላ በመናዘዝ በዝምታ ከውርስ መንቀል እንደሚችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 939 (3) ይደነግጋል።

ሟች ልጆቹን ወይም የልጅ ልጆቹንም በዝምታ ማለፍ የሚችል ሲሆን ይህ የሚያስከትለው ግን ከውርስ መነቀልን ሳይሆን የኑዛዜ ጠቅላላ ስጦታ የተደረገለትን ሰው ከሟች የህግ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች (ልጆች) እንደ አንዱ ተቆጥሮ እኩል የወርሱ ድርሻ ተካፋይ እንዲሆን ማድረግን ነው እንጂ የተነቀለውን ወራሽ ሙሉ በሙሉ የውርስ መብት ወይም ድርሻ ማሳጣት አለበት።

በዝምታ በሚደረግ የውርስ መነቀል ውስጥ ሟች ካለው ጠቅላላ ሀብት እጅግ አነስተኛ የሆነውን ሰጥቶ ብቻ ካለፈውና ይህ ተራ የኑዛዜ ክፍያ እንጂ እንደኑዛዜ ስጦታ እንደማይቆጠር ይደነግጋል። ወራሹ የተደረገለት ስጦታ በሕግ ከሚያገኘው የውርስ ድርሻ መጠን ከአንድ አራተኛ እጅ በላይ የሚያሰጠው ከሆነ ከውርስ እንደመነቀል እንደሚቆጠርና ኑዛዜና ቀሪ እንዲሆን መጠየቅ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 ላይ ተደንግጓል።

ሰበር ምን አለ?

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 54 ጥር 27 ቀን 2003 በዋለው ችሎት ፍቃዱ ሟች እናታቸው ወ/ሮ በላይነሽ በኑዛዜ ለሱ መቶ ብር ለእህታቸው የልጅ ልጅ ለኤርሚያስ ብቸኛ ሐብታቸው የሆነውን ቤታቸውን በማውረሳቸው ከሕግ አግባብ ውጭ በኑዛዜ ተነቅያለሁ በሚል ያቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።

    በውሳኔውም ሟች ለልጃቸው ለአቶ ፍቃዱ 100 ብር ብቻ እንዲሰጠው ተናዘው ቤታቸውን ለእህታቸው የልጅ ልጅ በማውረሳቸው በተዘዋዋሪ አቶ ፍቃዱን ከውርስ ነቅለዋል። ሆኖም በሕግ የተቀመጠ በቂ የሚባል ያስቀመጡት ምክንያት ባለመኖሩ ፍቃዱ የተዘዋዋሪ በዝምታ ከውርስ ነቅለውታል። በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 939(3) መሰረት ኑዛዜውን ሙሉ በሙሉ ወራሽ ባይሆንም ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ የተደረገበት የሟች የእህት ልጅ ልጅ እንደ ሕጋዊ ወራሽ ተቆጥሮ የውርስ ሀብቱን የሚካፈል በመሆኑ ኑዛዜው ተሻሽሎ አቶ ፍቃዱና ኤርሚያስ የሟችን ሀብት እኩል መካፈል አለባቸው በሚል የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አሻሽሎታል።

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

- በስራ ላይ የሚደርሱ የጉዳት አይነቶች ምን ምን ናቸው?

- ለየጉዳቶቹ መጠን የሚከፈሉ የካሳ ክፍያዎች፣

- በሥራ ላይ ለደረሱ ጉዳት የሞተ ሰራተኞች ክፍያ የሚያገኙ ጥገኞች እነማን ናቸው?

- አሰሪ ያለበት የጉዳት የካሳ እና የህክምና ወጪ የመሸፈን ኃላፊነቶች፣

እንዴት ናችሁ? ባለፈው ሳምንት ሰራተኞች ላይ በስራ ምክንያት ስለሚደርስ ጉዳቶች ጉዳቶቹን ለመከላከል በአሰሪውም ሆነ በሰራተኞች በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ላይ የተቀመጡ ግዴታዎችን ተመልክተዋል። የሙያ ደህንነት ጤንነትና የስራ አካባቢን ለመጠበቅ መሟላት ያለባቸውን ነገሮችም አይተናል። በስራ ላይ ጉዳቶች የሚባሉት በስራ ላይ የደረሱ አደጋዎችን እና በስራ የሚመጡ በሽታዎችም የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁ አሰሪው ያለበትን ኃላፊነትና ሰራተኛው በስራ ላይ ለደረሰ ጉዳት ካሳ የማግኘት መብቱን ሊያጣ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አንስተናል። ዛሬስ? በይደር ያቆየነውን የጉዳት አይነቶች የሚሰጡ የካሳ ክፍያዎን ተያያዥ ጉዳዮችን እናወጋለን።

የሥራ ላይ የጉዳት ዓይነቶች

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀፅ 99 መሠረት ሰራተኛው ጉዳትን ወይም ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው የአካል ጉዳት ማለት የሰራተኛውን የመስራት ችሎታ መቀነስን ወይም ማጣትን በሚያስከትል ሁኔታ በስራው ላይ የሚደርስበት ጉዳት ሲሆን ሶስት የአካል ጉዳት አይነቶች አሉ። እነሱም 

ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፣

ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት፣

ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ተብለው ይመደባሉ።

በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት በሰራተኛው ላይ የሞት ጉዳትም ሊያስከትል ስለሚችል አራተኛው የጉዳት አይነት ሆኖ ተቀምጧል።

ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፡- የሚባለው ሰራተኛው ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከናወን የማያስችል የጉዳት የአካል ጉዳት አይነት ነው። ይህ የጉዳት አይነት በባህሪው በስራ ላይ በደረሰው አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የመጣ በሽታ ሰራተኛው ላይ የሚከሰትና ጉዳቱ ለጊዜው በህክምና እስኪድን ድረስ የሰራተኛውን የመስራት አቅም የሚገድብ ነው።

ሰራተኛው ጊዜያዊ የስራ ላይ ጉዳት ሲደርስበት በአዋጅ አንቀጽ 107(1) መሰረት ጊዜያዊ የአካል ጉዳቱ እስከሚወገድ ድረስ በአሰሪው በየጊዜው የሚደረጉ ክፍያዎችን ያገኛል።

በየጊዜው የሚገኙ ክፍያዎች፡- ሰራተኛው ጊዜያዊ የአካል ጉዳት ከደረሰበት በአዋጁ አንቀጽ 108 መሰረት ከሚያገኘው ህክምና በተጨማሪ በጉዳቱ ምክንያት ሰራተኛው ስራ ባይሰራም አሰሪው ከአንድ ዓመት ለበለጠ ጊዜ የሚከፍላቸው በሰራተኛው አማካይ ደመወዝና የጉዳቱ ማገገሚያ ጊዜ ቆይታ ላይ ተመስርተው የሚሰሉ ክፍያዎች ናቸው።

የመጀመሪያው ዙር የጊዜያዊ የአካል ጉዳት ክፍያ ጉዳት ከደረሰበት እለት ጀምሮ የሚከፈል ነው። ይህ የመጀመሪያው የጊዜያዊ የአካል ጉዳት ክፍያ ለ3 ወራት የሚቆይ ሲሆን ሰራተኛው ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ያገኝ የነበረው የአንድ ዓመት አማካይ የወር ደምወዙን በሙሉ በየወሩ ሳይሰራ የሚያገኝነበት ነው። ይህ ክፍያ ጉዳቱ መወገድ በሀኪም እስካልተረጋገጠ ወይም የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት እስካገኘበት ቀን ድረስ ከጉዳቱ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ላሉት ቀጣይ ሰዓት ወራት አሰሪው ከሰራተኛው የሚከፍለው ክፍያ ነው።

ሁለተኛው ዙር ክፍያ የሚቀጥለው በሶስቱ ወራት ውስጥ ጊዜያዊ ጉዳቱ ካልተወገደ ወይም ሰራተኛው የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት ካላገኘ ለቀጣዮቹ ሰዓት ወራት የሚቀጥል ሲሆን መጠኑም የሰራተኛው የአመቱ አማካይ ወርሃዊ ደምወዙ 75 በመቶ ነው። ለምሳሌ ጊዜያዊ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት በነበረው ዓመት 1000 ብር በወር ያገኝ የነበረ ሰራተኛ 6ኛው ወር ላይ ደመወዙ በጭማሪ በወር 1500 ብር ቢሆን እና 12ኛው ወር ላይ ጊዜያዊ ጉዳቱ ቢደርስበት ጊዜያዊ ክፍያው የሚሰላው በሰራተኛው ከጉዳቱ ቀን በፊት በነበረው የአመቱ አማካይ የወር ደምወዝ በመሆኑ የ6 ወራቱ 1000 ሺ ብር ከደመወዙ ጭማሪው በኋላ እስከ ጉዳቱ ቀን በወር ያገኘው የነበረው 1500 ብር በ6 ተባዝቶ አንድ ላይ ሲደመሩ የአመቱን ደመወዝ ብር 15000 ይመጣል። የዓመቱን አማካይ የወር ደምወዝ ለማግኘት ከ12 ወራት ስናካፍለው 1250 ብር ይመጣል። ይህ ሰራተኛው ከጉዳቱ በፊት ያገኝ የነበረው የአመቱ አማካይ ደመወዝ በመሆኑ ጉዳቱ ከደረሰበት ቀን ለቀጣዩ 3 ወር በወር ብር 1250 ጊዜያዊ የጉዳት ክፍያ ይከፈለዋል።

በሁለተኛው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ደግሞ ለቀጣዩ 3 ወር ጊዜ አማካይ የወር ደመወዙ የ1250 ወደ 75 በመቶ ይከፈለዋል።

ጉዳቱ ከመጀመሪያውና በሁለተኛው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ካልተወገደ ደግሞ ሶስተኛውና የመጨረሻው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ለቀጣዮቹ 6 ወራት የሚቀጥል ሲሆን መጠኑም የአማካይ የወር ደምወዙ 50 በመቶ ነው።

አሰሪው ሰራተኛው በጊዜያዊ ጉዳት ምክንያት ስራ መስራት ካቀመበት እለት ጀምሮ አስራ ሁለት ወራት ከሞላው ሰራተኛው ያገኝ የነበረው የጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ ይቋረጣል። ለጊዜያዊ ጉዳት ክፍያ የሚቀበል ወይም የጠየቀ ሰራተኛ ለህክምና ምርመራ ለመቅረብ እምቢተኛ ወይም ቸልተኛ ከሆነ፣ በማናቸውም ሁኔታ ሆን ብሎ ምርመራውን ካደናቀፈ ወይም ያለበቂ ምክንያት ካንጓተተ፡-

- ጉዳቱ የሚድንበትን ጊዜ ለማዘግየት አስቦ ያልተገባ ፀባይ ካሳየ

- አግባብ ባለው ካሳስልጣን ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰራተኞች የመጣውን መመሪያ ከተላለፈ በየጊዜው የሚደረገው ጉዳት ሊታገድ ይችላል። ለእገዳው ምክንያት የሆነው ሁኔታ ሲወገድ ክፍያው እንደገና የሚቀጥል ሲሆን በእገዳው ጊዜ ያልተከፈለውን ክፍያ ግን ሰራተኛው የማግኘት መብት የለውም።

ዘላቂ የአካል ጉዳት፡- ሰራተኛው የደረሰበት ጉዳት ሙሉ ወይም ከፊል ዘላቂ የአካል ጉዳት ከሆነ የጉዳት ጡረታ ወይም የዳረጎት ወይም ካሳ እንደሚያገኝ በአዋጁ አንቀጽ 107(ለ) ይደነግጋል። ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት የሚባለው በአንቀጽ 101 (1) መሠረት ጉዳት የደረሰበትን ሠራተኛ የመስራት ችሎታ የሚቀንስ የማይድን በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው። ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ደግሞ ሠራተኛውን ማናቸውንም ደምወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመስራት የመከላከል የማይድን በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው።

ከነዚህ ጉዳቶች በተጨማሪ ከባድ የአካል ወይም የመልክ መበላሸትን ያስከተለ ጉዳት የመስራት ችሎታ ማጣትን ቢያስከትልም ለጉዳት ካሳ አከፋፈልና ሌሎች ጥቅሞች ሲባል እንደ ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት ይቆጠራል።

የዘላቂ ጉዳት መጠን ደረጃው የሚወሰነው የሰራተኛውና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያወጣው ሰንጠረዥ መሰረት ሲሆን የጉዳት መጠኑ የሚወሰነው ሥልጣን ባለው የህክምና ቦርድ ሲሆን ምርመራው ትክክል ካልሆነ ሰራተኛው ወይም አሰሪው ሲጠይቁ ድጋሚ ይደረጋል።

የጉዳት ካሳው መጠን በጡረታ ሕግ ለሚሸፈኑ ሰራተኞች በመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ሕግ መሰረት የሚፈፀም ሲሆን፤ በጡረታ ሕጉ ለማይሸፈኑ ሰራተኞች ደግሞ

ሀ. ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት፡- በአዋጁ አንቀፅ 104 (3) መሰረት የሰራተኛው የአመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው ክፍያ ሲሆን በአንድ ጊዜ ነው የሚከፈለው፣

ለ. ዘላቂ ክፍል የአካል ጉዳት፡- የማይድን ሆኖም የሰራተኛውን የመስራት ችሎታ የቀነሰ ክፍል የአካል ጉዳት የካሳ ክፍያው የአምስት ዓመት ደመወዙ በመቶኛ ጉዳቱ ሰራተኛው አካል ላይ ላስከተለው ጉዳት ከተሰጠው ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ ነው።

ጉዳቱ ለማጅ ሠራተኞች ላይ የደረሰ ከሆነ ደግሞ ለማጁ ልምምዱን ሲጨርስ ሊያገኝ ይችል በነበረው ደመወዙ የሚሰራ ነው።

ለጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2005 አንቀጽ 23 መሰረት ቢያስ 10 ዓት ያገለገለ ሰራተኛ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ከስራ ሲሰናበት ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እድሜ ልኩን የጡረታ አካል ያገኛል። አገልግሎቱ አስር ዓመት ያልሞላ ሰረተኛ ደግሞ በጤና ጉድለቱ ምክንያት ከስራ ሲሰናበት አማካይ የወር ደምወዙ ከፖሊስና ከመከላከያ ውጭ ያለ ሰራተኛ 1ነጥብ 25 በመቶ ያገለገለበት ዓመት ብዛት ተባዝቶ ይከፈለዋል።

እነዚህን ክፍያዎች ሠራተኞች በሰራተኛ ማህበራቸው ከአሰሪው ጋር በሚያደረጉት ድርድር ከሕጉ የተሻለ ለሰራተኛው በሚጠቅም መልኩ ሊያሻሽሉት ይችላሉ።

የሞት ጉዳት፡- ሠራተኛው ወይም ተለማማጅ ሰራተኛው በስራ ላይ በደረሰ ጉዳት ከሞተ በአዋጅ አንቀፅ 110 መሠረት ለጥገኞች ክፍያ እና ለቀብር ማስፈፀሚያ ከሁለት ወር ደምወዝ ያላነሰ ክፍያ ይከፍላል። በጡረታ ሕግ የሚሸፈኑ ሰራተኞች የሚያገኙት የጡረታ አበል ሲሆን በጡረታ ሕጉ ለማይሸፈን ሰራተኛ ደግሞ የዓመት ደመወዙ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው።

የሟች ሰራተኛ ጥገኞች የሚባሉት

የሟች ሕጋዊ ባል ወይም ሚስት የጥገኞች ካሳ ክፍያውን 50 በመቶ

እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች ለእያንዳንዳቸው 10 በመቶ

በሟች ድጋፍ ይረዱ የነበሩ የሟች ወላጆ እያንዳንዳቸው 10 በመቶ ያገኛሉ።

የክፍፍሉ መጠን ሙሉ የካሳውን መጠን እስኪሸፈን ድረስ እንደ ጥገኞቹ ቁጥር ብዛት ማነስ ወይም መብዛት እየተቀነሰ ወይም እየተጨመረ ይደለደላል።

የአሰሪ ግዴታዎች፡- በአዋጁ አንቀጽ 104 ላይ አሰሪው ላይ ሰራተኞች ላይ ከሚደርስ ጉዳት አንጻር ልዩ ግዴታዎች ተጥለዋል እነሱም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ጉዳት ለደረሰበት ሰራተኛ ወዲያውኑ መስጠትና ተስማሚ በሆነ መጓጓዣ ወደ ህክምና ጣቢያ ማድረስና ጉዳቱን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ናቸው። ሰራተኛው ከሞተ የቀብር ወጪ መሸፈንም ልዩ የአሰሪው ግዴታ ነው። ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ በአሰሪው የህክምና ወጪዎችን የመሸፈን ግዴታ የተጣለበት ሲሆን ጠቅላላና ልዩ ህክምና እንዲሁም የቀዶ ህክምና ወጪ፣ የሆስፒታልና የመድሃት ወጪ፣ የማንኛውንም አስፈላጊ ጥገና ወጪዎችንም የመሸፈን ግዴታ አለበት። ሰራተኛው የሚደረግለት ህክምና የሚቋረጠውም የህክምና ቦርድ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ነው። 

  

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    አሰሪዎችም ሰራተኞውም የሙያ ደህንነትን የሰራተኞን ጤንነት ለማስጠበቅ ማክበር ያለባቸው ግዱታዎች፣

-    በስራ ላይ የደረሱ ጉዳቶች የሚሉት የትኞቹ የጉዳት አይነቶች ናቸው፣

-    በአሰሪዎች ኃላፊነት ምንድነው?

-    በስራ ላይ ጉዳቶች አሰሪው በኃላፊነት እንዳይጠየቅ የሚያደርጉ የሰራተኛው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ስራ እንዴት ነው? የዛሬው ወጋችን ከስራ ጋር በተያያዘ ሰራተኞች አካልና ህይወት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በሚመለከት አሰሪዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? የሰራተኞስ መብትና ግዴታ ምን ይመስላል የሚሉትን ነጥቦች እናነሳለን።

1.ቅድሚያ ደህንነት

“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል የስራው ብሂል አለ። እያወራን ያለነው ሰራተኞች በስራ ላይ እያሉ የሚደርስባቸው ጉዳት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ነው። የግልና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የአሰሪዎች እና የሰራተኞች የስራ ግንኙነት የሚገባው አዋጅ ቁጥር 377/96 ሰራተኞች ላይ ጉዳት ሲደርስ አሰሪው ያለበትን ኃላፊነት ከማስቀመጥ በፊት ለአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ቅድሚያ ለአሰሪውም ከሰራተኛውም ሆነ በአሰሪው መወሰድ ያለባቸውን የመከላከያ እርምጃዎች ነው። ምክንያቱም በዚህ ሆነ በሌሎ ሕጎች ጉዳት ያደረሰው ሰው ጉዳት የደረሰበትን ሰው የመካስ ግዴታ አለበት። ይህን ግዴታ ለመወጣት አሰሪው ያለበትን ኃላፊነት ለሰራተኞች የመድህን ዋስትና ሽፋን በመግባት ወይም በራሱ ኃላፊነት በመውሰድ ሊወጣው ይችላል። ከዚያ በፊት ግን መቅደም ያበት ለስጋት ተጋላጭነት (Risk) በማስወገድ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ነው። ለዚህም ነው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 92 ስር አሰሪው የሠራተኞችን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ እርምጃዎን የመውሰድ ኃላፊነት የተጣለበት

የአሰሪ ግዴታዎች፡-

የመጀመሪያው ግዴታው ሰራተኞች የሚሰሩት ስራ ሊያስከትልባቸው ስለሚችለው አደጋና የጤንነት ጉዳት ለማስወገድ ስለሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ተገቢውን ስልጠና መስጠት ነው። ሁለተኛው ግዴታ ደግሞ ሰራተኞችን የአደጋ ማስወገጃ ስልጠና ብቻውን በቂ አይደለም። አንድ ሰራተኛ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ስላወቀ ብቻ ሙሉ በሙሉ አደጋ አይደርስም ማለት ስለማይቻል አሰሪው የአደጋ ተከላካይ ሠራተኛ የመመደብ ግዴታ አለበት። ይህ በውስጣዊ አደረጃጀቱና በራሱ ወጪ አደጋዎች ቢከሰቱ ለመከላከል እንዲያስችል የተጣለበት ግዴታ ነው። በተጨማሪ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ተከታታይ ኮሚቴዎች የማቋቋም ግዴታ አለበት።

ሌላውና ዋነኛው ደግሞ እንደ ስራው ባህሪ የአደጋ መከላከያ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማቅረብ ሲሆን፤ ስለአጠቃቀሙም ለሰራተኞቹ በማሳወቁ ተገቢውን የአጠቃቀም መመሪያ መስጠት አለበት። ከዚህ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ የሥራ ቦታ እና ግቢ በሰራተኞች ደህንነትና ጤንነት ላይ አደጋ የማያስከትል መሆኑን በማረጋገጥ ምቹ እና ለደህንነት አስተማማኝ የስራ ቦታ የማቅረብ ግዴታ አለበት። ከተለያዩ የስራው ሂደቶች ጋር በተያያዘ ቁሳዊ፣ ኬሚካላዊ፣ ስነህይወታዊ፣ ከስራው ግብአቶች ንድፍ እና ስነልቦናዊ ምንጮች በሰራተኛና ደህንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

አዲስ የሚቀጠሩ ሰራተኞችን እንደየስራው ባህሪ የጤና ምርመራ ማድረግ እና በአደገኛ ስራ ላይ የሚመደቡ ሰራተኞችም እንደየአስፈላጊነቱ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግም አለበት። በአዋጁ የተቀመጡትን የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤናማነት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዲሁም በሚመለከተው የመንግስት አካል የሚሰጡ ትዕዛዞችን ማክበርም የአሰሪው ግዴታ ነው። ጥንቃቄው ከሁለቱም ወገኖች ከአሰሪውም ከሰራተኛውም የሚፈለግ ነውና ሰራተኞችም ግዴታዎች ተጥለውባቸዋል።

የሠራተኛው ግዴታዎች፡-

በስራ ላይ ደህንነትን እና ጤንነትን ለማስጠበቅ ማንኛውም ሰራተኛ ለዚሁ ዓላማ የሚወጡትን የሥራ ደንቦች በማዘጋጀት መተባበር እንዲሁም ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለበት። በድርጅቱ ወይም በመሳሪዎች ላይ የሠራተኛውን ደህንነትና ጤንነት የሚጎዳ ጉድለት ሲያገኝ እና ጉድለቱ ሊያደርሰው የሚችለውን አደጋ ወዲያውኑ ለአሰሪው የማሳወቅ ግዴታ አለበት። አይቶ እንዳላየ ማለፍ አይቻልም።

ሰራተኛው አደጋ ሊያደርስ ይችላል ብሎ ለማመን ምክንያት ያለው ሁኔታ ሲያጋጥመው በቅድሚያ በራሱ ሊያስወግደው የሚችለው ከሆነ ማስወገድ አለበት። ሊያስወግደው የማይችለው ከሆነ ደግሞ ለአሰሪው ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት። በተጨማሪ ከስራ ጋር ግንኑነት ባለው ሁኔታ በጤንነት የደረሰ ጉዳት እራሱም ላይ ሆነ ሌላ ሰራተኛ ላይ ካለም ለአሰሪው ማሳወቅ የሰራተኛው ግዴታ ነው። ምክንያቱም አደጋዎችና ጉዳቶች ሳይባባሱ አሰሪው ያለውን ክፍተት በመሙላት ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት መረጃ ስለሚያስፈልገው ነው።

የአደጋ መከላከያዎች ወይም የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን አሰሪው የማሟላት ግዴታ አለበት። ውጤታማ የሚሆኑት ግን ሰራተኛው በትክክል ሲጠቀምባቸው በመሆኑ እነዚህን የመከላከያ መሳሪያዎና ሌሎች መሳሪያዎችን በትክክል ጥቅም ላይ የማዋል ግዴታ አለበት። አሰሪው ወይም ኃላፊነት የተሰጠው አካል የሚያመጣቸውን የደህንነትና የጤንነት መጠበቂያ መመሪዎም ማክበር አለበት።

በአዋጁ አንቀጽ 94 ላይ ማንኛውም ሰራተኛ ለራሱ ወይም ለሌሎች ደህንነት ሲባል የተቀመጡ የደህንነት መጠበቂያ እቃዎች ወይም ሌሎች መሳሪያዎችን መነካካት ማንሳት ያለቦታቸው ማስቀመጥ፣ ማበላሸት ወይም ማጥፋት በስራ ላይ የሚደርስ አደጋን ለመቀነስ ሲባል የሚሰራበትን ማንኛውንም ዘዴ ወይም አሰራር ማሰናከል የተከለከለና በወንጀልም ጭምር ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር ነው።

የሥራ ላይ ጉዳቶች

የስጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በአሰሪውና በሰራተኛው ላይ በአዋጅ የተጣሉ ግዴታዎን ተመልክተናል። ዋና አላቸውም ሰራተኞች በስራ ላይ በሚደርስባቸው ጉዳት የሚታጣውን ምርታማነት፣ የሰው ሃይል፣ ገቢ እንዲሁም አሰሪው የሚደርስበትን ኃላፊነት በመቀነስ ጉዳቶ የሚያስከትሉትን አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ መቀነስ ነው። ሆኖም አደጋን መቀነስ እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ስለማይቻል በስራ ላይ የሚመጡ ጉዳቶች የትኞቹ እንደሆኑ ተቀምጠዋል። በአንቀፅ 95 መሰረት በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት የሚባለው በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። እስቲ ሁለቱን የሥራ ላይ የጉዳት አይነቶች እንመልከት፡-

በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ፡- በአዋጅ አንቀጽ 97 መሰረት ማንኛውም ሰራተኛ ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባው ሁኔታ ከሰራተኛው ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ስራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ወይም በማንኛውም የአካል ክፍሉ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት ሲሆን የሚከተሉትን የጉዳት አይነቶችም ያካትታል፣

-    በስራ ቦታው ወይም ከመደበኛ የስራ ሰዓትው የአሰሪውን ትዕዛዝ ሲተሰገብር በነበረ ጊዜ የደረሰበት ጉዳት፣

-    ከስራው ጋር በተያያዘ ግዴታ ከስራው በፊት ለጊዜው ስራው በተቋረጠበት ወይም ለስራው በኋላ (ከመደበኛ የስራ ሰዓት) በስራው ቦታ ወይም በድርጅቱ ግቢ ውስጥ እያለ የደረሰበት ማንኛውም ጉዳት፣

-    ወደስራ ወይም ከስራ ቦታ ድርጅቱ ለሰራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው መጓጓዣ ወይም ለዚሁ ተግባር በተከራየውና በግልፅ ከሰራተኞች መጓጓዣ አገልግሎት ለመደበው መጓጓዣ ሲጓዝ እያለ የደረሰበት አደጋ፤ እዚህ ጋር በግል መጓጓዣ ወይም በህዝብ ማመላለሻ ወይም በሌሎች አማራጭ ወደ ስራ ቦታ ወይም ከስራ ቦታ የሚጓጓዙ ሰራተኞች በጉዞ ላይ የሚደርስባቸው አደጋ እንደ ስራ ላይ አደጋ እንደማይታይ ልብ ሊባል ይገባል።

-    ሰራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ እያለ በአሰሪው ወይም ከሰራተኛ ወገን ድርጊት የደረሰበት ጉዳት በአዋጁ መሠረት በስራ ላይ የደረሱ አደጋዎች ናቸው።

በሥራምክንያትሚመጣ በሽታ፡- በአዋጅ አንቀፅ 98 መሠረት ሠራተኛው ከሚሰራው የስራ አይነት ወይም ከሚያከናውነው ሥራ አካባቢ ከበሽታው መከሰት በፊት በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በቁሳዊ፣ ኬሚካላዊ ወይም ስነህይወታዊ ነገሮች አማካኝነት በሰራተኛው ላይ የሚደርስ የጤና መታወክ ነው።

በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ስራው በሚሰራበት አካባቢ የሚዛመቱና የሚይዙ ነባር ተላላፊ በሽታዎች የሚያካትቱ ሲሆን እነኚህ ነባር ተላላፊ በሽታዎች እንደ ስራ በሽታ የሚቆጠሩት ስራቸው በሽታውን ማጣራት ለሆኑ ባለሙያዎች ብቻ ነው።

እነዚህ በስራ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችና በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች በስራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ሲሆኑ አሰሪው ለነዚህ ጉዳቶች ካሳ የመክፈልና የህክምና ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት አለበት።

የአሰሪው ኃላፊነት፡- በአዋጁ አንቀጽ 96 መሰረት በስራ ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች አሰሪው የፈፀመው ጥፋት ባይኖርም አሰሪ በመሆኑ ብቻ ኃላፊነት አለበት። ይሄ በአሰሪና ሰራተኛ ሕጉ የተደነገገ የአሰሪዎች ኃላፊነት ሲሆን አሰሪው ለጉዳቱ መንስኤ የሆነውን ጥፋትም ሲፈፀም እንደተጠበቀ ነው። ሆኖም አሰሪው ተጠያቂ የማይሆንባቸው የተወሰኑ ሁኔታዎች አሉ እነሱም፡-

-    ሆን ብሎ ሰራተኛው በራሱ ላይ ለደረሰው ማንኛውም ጉዳት ምክንያቱም ማንም ሰው ከጥፋቱ ተጠቃሚ መሆን የለበትም፡-

-    አሰሪው አስቀድሞ በግል የተሰጡትን የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በመጣስ ወይም የመከላከያ ደንቦችን በመተላለፍ ወይም

-    አካሉን ወይም አእምሮውን በሚገባ ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ እፅ ሰክሮ ስራ ላይ በመገኘቱ ሰራተኛው የሚደርስበትን ጉዳት ሆን ብሎ በራሱ ላይ እንደደርሰው ይቆጠራል።

ከላይ ያነሳናቸው የሥራ ላይ አደጋን የማስወገጃ አስገዳጅ የመከላከል ግዴታዎችና የስራ ላይ ጉዳቶች አሰሪው ላይ የሚያስከትሉትን የኃላፊነት አይነቶች እንዲሁም የጉዳቶቹን አይነቶ ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት ልመለስበት።

                                                                                  መልካም ስራ


ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   '; document.write(''); document.write(addy_text82091); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ንግድ ላይ ለመሰማራት የሚያስፈልጉ የምዝገባና የንግድ ፈቃድ ግዴታዎች፣

-    የምዝገባና የፈቃድ እድሳት፣

-    የፀና ንግድ ፈቃድ ሳይኖር መነገድ የሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነት፣

-    የታደሰ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሁለት ማዳበሪያ ቆዳ ሲሸጡ የተገኙት ግለሰብ ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ በምን ተቋጨ፣

 

 

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን የንግድ ስራ እና የንግድ ፈቃድን ይመለከታል። ለመሆኑ የንግድ ፈቃድ ሳይኖ ወይም ፈቃዱ በተገቢው ጊዜ ሳይታደስ መነገድ የሚያስከትለውን የወንጀል ኃላፊነት እንመለከታለን። በቅድሚያ የአቶ ባዘዘውን ክስ እንመልከት፡-

1.አቶ ባዘዘው ለምን ተከሰሱ?

ሚያዝያ 22 ቀን 2003 ዓ.ም በአማራ ክልል የአዊ ዞን ኖዊ ወረዳ ፈንደቀ ከተማ አንድ ግለሰብ ከሌሊቱ 11፡30 ላይ ተያዙ። የተያዙት ሁለት ማዳበሪያ የበግና የፍየል ቆዳ በህዝ ማመላለሻ መኪና ኪስ ውስጥ ከተው ሊጓዙ ሲሉ ነው። “የንግድ ፈቃድ አለህ?” ተጠየቁ “አለኝ” አሉ። ግለሰቡ ንግድ ፈቃዱን አወጡና አሳዩ። “ይሄማ የታደሰ ንግድ ፈቃድ አይደለም። ስለዚህ የፀና ንግድ ፈቃድ ሳይኖርህ የንግድ ስራ ስትሰራ ስለተያዝክ ክስ ይቀርብብሃል” ተባሉ ግለሰቡ አቶ ባዘዘው ነበሩ።

እንደተባለውም የክልሉ ዐቃቤ ሕግ የንግድ ምዝገባ አዋጅ 686/2007 አንቀፅ 60(1) በመተላለፉ የዘመኑ የታደሰ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው የቆዳ ንግድ ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል በሚል ተከሰሱ።

አቶ ባዘዘው ቦኞዊ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ተነበበላቸው። በርግጥ ሁለት ማዳበሪያ ቆዳ ይዤ በእለቱ ሳጓጉዝ ተገኝቻለሁ ነገር ግን ሕጋዊ ፈቃዱ ስላለኝ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ አቶ ባዘዘው የቀረበባቸውን ክስ ካዱ።

ዐቃቤ ሕግ የሰው ማስረጃ አቅርቦ አቶ ባዘዘው የበግና የፍየል ቆዳ ሲነግዱ እንዲነበር ሆኖም ግን ንግድ ፈቃድ የነበራቸው ቢሆኑም በወቅቱ ስላልታደሰ የማያገለግል መሆኑን መሰከሩና ፍ/ቤቱ አቶ ባዘዘው ዐቃቤ ሕግ ክሱን በበቂ ማስረጃ ስላስረዳ ይከላከሉ ሲል ብይን ሰጠ።

የአቶ ባዘዘው የመከላከያ ምስክሮችም አቶ ባዘዘው ንግድ ፈቃድ እንዳላቸው እንጂ በወቅቱ የታደሰ ይሆን ያልታደሰ እንደማውቁ ገለፁ።

ፍ/ቤቱም የከሳሽ ዐቃቤ ሕግን እና የአቶ ባዘዘውን ማስረጃዎ መርምሮ አቶ ባዘዘው ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው በተከሰሱበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ናቸው ብሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ሰምቶ አቶ ባዘዘው ሁለት ማዳበሪያ ቆዳ ያለንግድ ፈቃድ በመነገዳቸው በሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እና በብር አንድ መቶ ሃምሳ ሺ የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ያስወነጀላቸው ቆዳ ተሸጦ የተገኘው ብር 2,432 ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተወሰነ።

አቶ ባዘዘው በዚህ ከባድ ቅጣት ብቻ ሳይሆን ጥፋተኛ የተባልኩትም አላግባብ ነው በሚል ለአዊ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።

ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤቶች የህግ ስህተት ፈፅመዋል በሚል የሰበር አቤቱታ በአቶ ባዘዘው ቀረበለት። የሰበር ሰሚ ችሎቱ ግራቀኙን አስቀርቦ አከራከረና የጥፋተኝነት ውሳኔውን ቢያፀናም አቶ ባዘዘው ላይ የተጣለው ቅጣት ግን በዝቶ ስላገኘው በ3 ዓመት ተኩል ፅኑ እስራትና በ5 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ይሁን ሲል ቅጣቱን ቀንሶ ወሰነላቸው።

አቶ ባዘዘው ግን አሁንም በውሳኔው ስላልረኩ ለጥፋቴ እስካሁን የታሰርኩት ከበቂ በላይ ነውና በነፃ ልሰናበት የስር ፍ/ቤቶች የፈፀሙት የሕግ ስህተት ይታረምልኝ ሲሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

የመጨረሻ ስልጣኑ ያለው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለአቶ ባዘዘው ጉዳይ ምን ውሳኔ ሰጠ? በነፃ አሰናበታቸው ወይስ የ7 ዓመቱን ወይስ የ3 ዓመቱን እስር ቅጣት አፀና ከውሳኔው በፊት ሕጉ ምን እንደሚል እንይ።

2.ንግድ እና የንግድ ፈቃድ፡-

በስራ ላይ ያለው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ በቁ 686/2007 የታወጀ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 731/2004 እና በቁ 813/2006 የተወሰኑ ድንጋጌዎቹ ተሻሽለው አሁንም በስራ ላይ ይገኛል። ነጋዴ የሚባለው እንግዲህ በንግድ ሕግ ቁጥር 5 ስር የተዘረዘሩትን የንግድ ስራዎች ሙያዬ ብለው ይዘው ጥቅም ወይም ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ ሰዎች ናቸው። ነጋዴ የማይባሉት በእርሻ፣ በከብት እርባታ በግል ወይም ከቤተሰብ በእደ ጥበብ እና በአሳ ማጥመድ ያመረቱትን የሚሸጡ ሰዎች ግን ነጋዴ አይባሉም። እንግዲህ እነኚህ ሕጉ ነጋዴ የሚላቸው በሙሉ በአዋጅ ቀጥር 686/2002 አንቀፅ 6 መመዝገብና የንግድ ፈቃድ ማውጣት አለበት። የንግድ ምዝገባ የሚያካሂደው አንዴ ብቻ ሲሆን ቀድመው ተመዝግበው የነበሩ ነጋዴዎች በአዋጁ መሰረት ለሐምሌ 17 ቀን 2002 ዓ.ም ባለው 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ድጋሚ መመዝገብ አለባቸው።

ነጋዴው ከተመዘገበ በኋላ በአዋጁ 686/2002 አንቀጽ 30 መሰረት አንድ ንግድ ስራው መስክ ከሚመለከታቸው ፈቃጅና ተቆጣጣሪ አካላት ከሚሰጡ የሙያ ስራ ፈቃዶች በስተቀር ሌሎች የንግድ ስራ ፈቃዶች የሚሰጡት በንግደ ሚኒስቴር በክልሉ የንግድ ቢሮዎች ወይም በኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ነው።

ከነዚህ አካላት የፀና (የታደሰ) የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖው የንግድ ስራ ላይ መሰማራት እንደማይችል በአንቀጽ 31 ላይ ተደንግጓል። የ ፀና ንግድ ፈቃድ ሳይኖር መነገድ የሚያስከትላቸው የወንጀል ኃላፊነቶች እንዳሉ ሆነው በተጨማሪ የፀና ፈቃድ ሳይኖረው ንግድ ሲሰራ የተገኘ ሰው ላይ አግባብ ያለው ባለስልጣን የንግድ ድርጅቱን የመዝጋት እርምጃ መውሰድ ይችላል።

የንግድ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ የሚቀርበው አግባብ ላለው ፈቃድ ሰጪ አካል ሲሆን ከማመልከቻው ጋር አዲስ ወይም የታደሰ የንግድ ምዝገባ ወረቀት የነጋዴውን ወይም የስራ አስኪያጁን የ6 ወር ፎቶ ግራፍ፣ የውጭ ባለሀብት ከሆነ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማመልከቻው በወኪል ካቀረበ የውክልና ሰነድ እና የተወካዩ የቀበሌ መታወቂያ ወይም የፓስፖርት ከፒ፣ በንግድ ስራው የመደበውን ካፒታል የሚያሳይ ማስረጃ እናንግዱ የሚከናወንበት ቤት ሊሰራው ተስማሚ መሆኑን ከሚመለከተው የመንግስት አካል የተሰጠ ማረጋገጫ ነጋዴው ለንግዱ የሚጠቀምበት ቤት የራሱ ከሆነ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ካርታ፣ ኪራይ ከሆነ በውል አረጋጋጭ የተረጋገጠ የኪራይ ውል ይህን ማቅረብ ካልቻለ ስለቤቱ አድራሻ ለአካባቢው መስተዳድር የተሰጠ የፅሁፍ ማስረጃ ማቅረብ አለበት።

እንግዲህ በዚህ አዋጅ መሰረት በሕግ አግባብነት ያላቸው መስፈርቶች መሟላታቸውንና ስራው በሕግ ያልተከለከለ መሆኑን አረጋግጦ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ አስከፍሎ በአንቀጽ 33 መሰረት ነጋዴው የንግድ ስራ ፈቃድ ይሰጠዋል። ጥያቄው ተቀባይነት ከሌለው ደግሞ ምክንያቱን በፅሁፍ ይገልፁለታል።

የንግድ ስራ ፈቃዱ የተሰጠው ሰው የንግድ ስራው በሚፈቀድበት መልኩ አግባብ ያላቸው ተቆጣጣሪ አካላት የሚያመጡትን መመሪያዎች ተከትሎ ቤቱ ውስጥ በግልፅ በሚታይበት ማስቀመጥ ለሌላ ለማንኛውም ሰው እንዲጠቀምበት ወይም በመያዣነት እንዲይዘው እንዲከራየው አሳልፎ ያለመስጠት ግዴታ አለበት። ንግድ ስራውን ማሻሻል ወይም ማስፋፋት ከፈለገም አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች አቀርቦ ፈቃዱን ማሻሻል አለበት።

በአዋጅ አንቀፅ 36 መሰረት የተሰጠው የንግድ ስራ ፈቃድ ካልተሰረዘ የንግድ ፈቃድ የተሰጠበት የበጀት አመት ወይም የታደሰበት የበጀት ዓመት ካበቃ በኋላ ባሉት አራት ወራት ተገቢውን ክፍያ ፈፅሞ እስከታደሰ ድረስ ፀንቶ የሚቆይ ነው።

በተጠቀሰው አራት ወር ከሰኔ 30 እስከ ጥቅምት 30 ባሉት አራት ወራት ያለቅጣት ያላሳደሰ ነጋዴ በህዳርና በታህሳ ያለቅጣት ማሳደስ ይችላል። ፍቃዱ በአራት ወራቱ ካልታደሰ ግን የንግድ ስራ ሊሰራበት አይችልም። ከጥር 1 እስከ ሰኔ ሰላሳ ቀን በቅጣት ማሳደስ የሚችል ሲሆን በቅጣት በማሳደሻ ወቅት ቀርቦ ያልታደሰ የንግድ ፈቃድ በአዋጁ አንቀጽ 36(6) መሰረት ይሰረዛል። ፈቃድ ለማሳደስ ነጋዴው ሲቀርብ የግብር ግዴታውንና ሌሎች ያገልግሎት ክፍያዎችን መፈፀሙን ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት።

በአዋጁ አንጽ 60 (1) ላይ የፀና የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖረው በንግድ ስራ ተሰማርቶ የተገኘ ሰው ከ7-15 ዓመት ፅኑ እስር እና ከብር 150,000 - 300 ሺ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል። ለንግድ ስራው የሚጠቀምባቸው እቃዎችና መሳሪዎችም ይወረሳሉ።

በሀሰት መረጃ ንግደ መመዝገብ ፈቃድ ማውጣተ ማሳደስ ደግሞ ከ7-12 ዓመት ፅኑ እስር እና ከብር 60ሺ እስከ 120 ሺ የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል። የንግድ ምዝገባ አዋጁንና ደንቦችን የህዝብ ማስታወቂያዎችን መጣስ ደግሞ ማንኛውንም ሰው ከ3 - 5 ዓመት ፅኑ እስርና ከ30ሺ እስከ 60ሺ ብር ያስቀጣል

3.ሰበር ምን አለ?

የአቶ ባዘዘውን የሰበር አቤቱታ መርምሮ ቅ 215 ላይ ታትሞ በመጣው በሰ/መ/ዙ 86388 ሰኔ 17 ቀን 2005 በዋለው ችሎት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን አቶ ባዘዘው የታደሰ ወይም የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ቆዳ ሲነግዱ መገኘታቸው በአዋጅ ቁጥር 688/2002 አንቀፅ 60 (1) መሰረት ጥፋተኛ የሚያሰኛቸው ሲሆን በስር ፍ/ቤት የተወሰነባቸውን የ7 ዓመት ፅኑ እስርና የ150ሺ ብር ቅጣት የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ የወንጀሉን አፈፃፀምና ክብደት በማስላት በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት በ3ዓመት ተኩል ፅኑ እስርና በ5ሺብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑ አግባብ ስለመሆነ የህግ ስህተት አልተፈፀመበትም ብሎ ውሳኔውን አንፅንቷል።

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ከማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነት ጋር የሚነሱ የምዝገባ ጉዳዮች

-    ስም ማዛወር የሻጭ ወይስ የገዥ ግዴታ

-    የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነትን መዝገብ ግዴታ ያለበትን የአስተዳደር አካል ስም እንዲያዛውር ማስገደድ ይቻላል።

-    ከማይንቀሳቀስ ንብረት (ከቤት) ሽያጭ ስም ዝውውር ጋር እስከ ሰበር የደረሱ ክርክሮች በምን ተቋጩ

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬው ወጋችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭን ተከትሎ የሚነሳ የስም ዝውውርን ጉዳይ ይመለከታል። ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሁለት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሱ ክርክሮችን እና የተሰጠባቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እናነሳለን። መልካም ንባብ።

1.ሻጭ ስም እንዲያዛወር የቀረበበት ክስ

አቶ ደግፌ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06 የነበራቸውን ሕዳር 20 ቀን 1980 በተፃፈ የብድርና የዋስትና ውል ቤቱን መያዣ አድርገው ከአቶ ሳልህ ሀሴን አስራ ሁለት ሺህ ብር ይበደራሉ። በወቅቱ ቤት መሸጥ መለወጥ አስቸጋሪ ስለነበር እስከ ሕዳር 20 ቀን 1990 ብድሩን ከፍለው ለማጠናቀቅ ይስማማሉ። ቤት መሸጥ ሲፈቀድ አቶ ሳልህ ለአቶ ደግፌ ብር 5 ሺህ ጨምረው በድምሩ በብር 17 ሺህ ቤቱን ለመሸጥ ይስማሙና ከቤቱ የእድሳት ወጪ ጋር በአጠቃላይ 18,787.90 ቤቱን ለመሸጥ ይስማማሉ። ቤት መሸጥ በመንግስት የተፈቀደው በ1982 ዓ.ም ነበር።

ሆኖም አቶ ደግፌ የተበደሩትን ብድር ካለመመለሳቸውም ሌላ በአማራጭ የቤቱን ባለቤትነት በስማቸው እንዲያዛውሩላቸው አቶ ሳልህ ቢጠይቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።

በመሆኑም አቶ ሳልህ አቶ ደግፌ ላይ ክስ አቀረቡ። በውላችን መሰረት አቶ ደግፌ ግዴታውን ስላልተወጣ ብር 5ሺ ጨምሬለት የቤቱ ባለቤትነት በስሜ እንዲዛወር ይወሰንልኝ ሲሉ ከሰሷቸው። አቶ ደግፌ ክሱ ቢደርሳቸውም ቀርበው መልስ ባለመስጠታቸው በሌሉበት ጉዳዩ ታየ። ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ በአቶ ደግፌና በአቶ ሳልህ መሀል የተደረገው የመያዣ ውል ሳይሆን የወለድ አገድ ውል ነው። ውሉ በተደረገበት ወቅት ተፈፃሚ የነበረው አዋጅ ቁጥር 47/67 ወለድ አገድ ውልን የሚከላከል በመሆኑ ውሉ ሕገወጥና ፈራሽ ነው። ተከራካሪዎቹ ወደነበሩበት ይመለሱ አቶ ሳልህ ቤቱን ይመልሱላቸው አቶ ደግፌ ደግሞ ገንዘቡን ይመልስ ሲል ወሰነ።

አቶ ሳልህ በጉዳዩ ቅር ተሰኝተው ይግባኝ ቢጠይቁም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን አፀናው። አቶ ሳልህ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመ ይታረምልኝ ብለው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ ደግፌ ቀርቦ ባልተከራከረበት እና ዳኝነት ባልጠየቀበት ቤቱን ይረከብ ተብሎ መወሰኑ ያለአግባብ በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ በውል ያገኙት መብት እንዲጠበቅላቸው ጠየቁ።

አቶ ደግፌ በሰበር አቤቱታው ላይ መልስ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቦላቸው እንደ ስር ፍርድ ቤት ሳይቀሩ ቀርበው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሊፀና ይገባል ሲሉ መልስ ሰጡ። ሰበር ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት ከጐንደር የተነሳውን ሌላ ክርክር እንመልከት።

2.ማዘጋጃ ቤቱ ስም እንዲያዛውር ተከሰሰ

አቶ ፀዳሉ የጐንደር ከተማ ውስጥ ከወ/ሮ ከበቡሽ ጥር 9 ቀን 1989 በተደረገ የሽያጭ ውል ቤት ይገዛሉ። ከዚያም ቤቱን ከባለቤቷ ላይ ስለገዛሁት የባለቤትነት ስሙን በስሜ አዛውሩልኝ ካርታም በስሜ ተሰርቶ ይሰጠኝ ብሎ የጐንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤትን ቢጠይቅም ማዘጋጃ ቤቱ ፍቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም በፍርድ ቤት ታገደ የገዛሁትን ቤት በስሜ ያዙርልኝ ካርታም በስሜ አዘጋጅቶ ይሰጠኝ ሲል ከሰሰ።

ክሱ የቀረበለት የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤትም የጐንደር ከተማ አቶ ፀዳሉ የጠየቁትን አስተዳደራዊ ተግባሩን እንዲያከናውንና የቤቱን ስም በስማቸው አዙሮ የባለቤትነት ማረጋገጫ በስማቸው እንዲያዘጋጅላቸው ወሰነ። ቤቱን ለአቶ ፀዳሉ የሸጡት ወ/ሮ ከበቡሽ እና ወ/ሮ መና ውሳኔው መብትና ጥቅማችንን ይጐዳል በሚል መቃወሚያ ቢያቀርቡበትም ፍ/ቤቱ መቃወሚያቸውን ባለመቀበል የሰጠውን ውሳኔ አፀናው። እነ ወ/ሮ ከበቡሽ ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም ሆነ ለአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ቢያቀርቡም፤ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በሚል ውሳኔው ፀና።

ከዚያም እነ ወ/ሮ ከበቡሽ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ብለው የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። የሰበር ሰሚው ችሎት የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ወይ? አቶ ፀዳሉ ለማዘጋጃ ቤቱ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የተረጋገጠ የሽያጭ ውልን አቀርበው ስም ይዛወርኝ፣ ካርታ ይሰራልኝ ብለው የመጠየቅ መብት አላቸው የሚሉትን ነጥቦች ለመመርመር ጉዳዩ ያስቀርባል ብሎ አቶ ፀዳሉን መልስ እንዲሰጡ አዘዘ። አቶ ፀዳሉም ያቀረብኩት ክስ በይርጋ አልታገደም የጠየኩት ዳኘነትም ውልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ለክልሉ ሕግ መሰረት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ሲሉ መልስ ሰጡ።

ሰበር የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ የሰጠውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት ጉዳዩን የሚመለከቱ ሕጐችን እንመልከት።

3.የማይንቀሳቀስ ንብረት ማስተላለፍ

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚባሉት ቤት እና ህንፃ እንዲሁም ያረፈበት የመሬት ይዞታ ነው። የዚህ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ባለሀብትነትን በሕግ ወይም ባለጉዳዮቹ በሚያደርጉት ሕጋውያን ተግባራት (የሽያጭ ውል፣ የስጦታ ውል ወይም ኑዛዜ) እንደሚተላለፉ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1184 ይደነግጋል። የእነኚህ ንብረቶች ባለሀብትነት በውል ወይም በኑዛዜ ሲተላለፍም በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ማስመዝገብ አስፈላጊ መሆኑን በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1185 ላይ ተቀምጧል። የተለየ አንዳንድ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባለቤትነትም ለምሳሌ ተሽከርካሪዎች ግዙፍ ማሽኖች እና የመሳሰሉትም ልክ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነታቸው ሲተላለፍ መመዝገብ አለበት።

ይሄ የማስመዝገቡ አስፈላጊነት የሚመነጨው እነኚህ ንብረቶች ካላቸው ከፍተኛ ኢኰኖሚያዊ ዋጋ አንፃር የባለሀብቶቹን ፍላጐት የገዥና የሻጭን መብት እንዲሁም በእነዚህ ንብረቶች ላይ አስቀድመው የተደረጉ የተለያዩ መብቶተና ግዴታዎች ካሉ ሦስተኛ ወገኖች እንዲያውቁት በማድረግ ነው ግዙፍ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ግን በእጁ ይዞ የሚገኝ ሰው የራሱ እንደሆኑ ሕግ የሚገምት ሲሆን፤ አይደለም የሚል ሰው ስላለመሆኑ ማስረጃ አቅርቦ ማስረዳት አለበት።

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ባለሀብትነት ምስክር ወረቀት የሚሰጠው ንብረቱ በሚገኝበት ቦታ ያለው የሚመለከተው የመንግስት የአስተዳደር አካል ሲሆን፤ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1195 መሰረት ይህ ምስክር ወረቀት የተሰጠው ሰው የንብረቱ ባለቤት እንደሆነ ይቆጠራል። በአስተደደር ደንብ የሚወሰን የአስተደደሩ ወጪ እና ለሚደርስበት ኃላፊነት ዋስትና የምስክር ወረቀቱን ሲሰጥ የሚከፈል ክፍያ እንዳለም ሕጉ ደንግጓል። የአስተዳደር መስሪያ ቤቱ የባለሀብትነቱን ምስክር ወረቀት ለሌላ ሰው ከመስጠቱ በፊት ቀድሞ ሰጥቶት የነበረው ምስክር ወረቀት እንዲመለስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1196 መሰረት ማስገደድ ይችላል።

በዚህ መልኩ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብት ያገኘ ሰው የባለቤትነት መብቱ እንዲመዘገብለት ንብረቱ በሚገኝበት የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝጋቢ አካል ማስረጃዎቹን በማያያዝ ባለሀብትነቱ እንዲመዘገብለትና የባለቤትነት ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቅ ይቻላል።

በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2876 መሰረት በጽሁፍ እና ከሁለት ምስክሮች በላይ ባሉበት የተደረገ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በውል አዋዋይ ፊት መደረግ አለበት። በተጨማሪ ለ3ኛ ወገኖች ከሽያጩ በኋላ ለሚያነሱት የመብት ጥያቄ መቃወሚያ ሊሆን የሚችለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2878 መሠረት ንብረቱ ባለበት ቦታ ባለው የማይንቀሳቀስ መዝገብ ሲመዘገብ ነው።

ሻጭ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1879 መሠረት ያለበት ግዴታ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በገዥ ስም ለማስመዝገብና የስም ዝውውር ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ማንኛቸውንም ሰነዶች መስጠት ሲሆን፤ ይህ ግዴታም የሽያጭ ውሉ ዋና አካል ተደርጐ ይገመታል።

4.ሰበር ምን አለ?

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቶ ሳልህ እና የአቶ ደግፌ ጉዳይ የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ 8 ላይ ታትሞ በወጣው በሰ/መ/ቁ. 33945 ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። የስር ፍ/ቤት አቶ ደግፌ ቀርበው ያለልጠየቁትን አቶ ሳልህም በግልጽ ባላመለከቱትና ያልጠየቁትን ዳኝነት በመሆኑ በአቶ ደግፌና አቶ ሳልህ መሀል የነበረው የወለድ አገድ ውል ነው። ውሉ በሚደረግበት ጊዜ በነበረው ሕግ ወለድ አገድ ስለተከለከለ ውሉ ፈራሽ ነው። አቶ ሳልህ ቤቱን አቶ ደግፌ ደግሞ ገንዘቡን ይመላለሱ ብሎ መወሰኑን ተችቶ ከሻረው በኋላ አቶ ደግፌ ስም አዛውር ተብለው ሊከሰሱ መቻል አለመቻላቸውን በተመለከተ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነት ማስተላለፉን መዝግቦ የስም ዝውውር የሚፈፀመው የመንግስት አካል እንጂ ሻጭ ነው የሚል ከሕግም ሆነ ከውል የሚመነጭ ግዴታ የለም። ቤቱን የሚመለከቱ ማስረጃዎችንም አቶ ደግፌ እንዳላስረከቡ አቶ ሳልህ አልጠቀሱም። በመሆኑም ስም ዝውውር ይፈጽምልኝ ብለው አቶ ደግፌን የሚከሱበት የሕግ ምክንያት ስለሌለ አቶ ሳልህ ቤቱን የሸጡላቸውን አቶ ደግፌን ስም አዛውር ብለው መክሰስ አይችሉም ሲል ወስኗል።

የወ/ሮ ከበቡሽን እና የአቶ ፀዳሉን ክርክር ደግሞ ቅጽ 11 ላይ በታተመው በሰ/መ/ቁ.     49428 ሕዳር 28 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ የሰጠበት ሲሆን፤ የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ካለ በኋላ የጐንደር ማዘጋጃ ቤት በሕግ የተጣለበተን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን የመመዝገብ ግዴታውን ስላልተወጣ የቤቱ ገዥ አቶ ፀዳሉ መብታቸውን ለማስከበር ማዘጋጃ ቤቱ ላይ ክስ መመስረታቸውና ፍ/ቤቱም አስተዳደራዊ ተግባሩን ማዘጋጃ ቤቱ እንዲወጣ መወሰኑ አግባብ ነው በሚል በስር ፍ/ቤት ውሳኔውን አጽንቷል።

ጣልቃ ገብነት

April 24, 2015

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በሌሎች ሰዎች ክርክር ሶስተኛ ወገኖች ጣልቃ የሚገቡበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

-    ጣልቃ የመግባት መብት ከምን ይገኛል?

-    እስከ ሰበር የደረሰው የጣልቃ ገብነት ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? አንዳንዴ በሆነ ጉዳይ ላይ “አያገባችሁም” ተብላችሁ አታውቁም። ለምሳሌ የሁለት ሰዎች ክርክር ፀብ ወይም ስምምነት ሊሆን ይችላል። ምን ብላችሁ መለሳችሁ? “በዚህ በዚህ ምክንያት ያገባኛል!” ነው እንዴ ሌላ ምን ይባላል። “ጣልቃ መግባት” ብዙም አዎንታዊ ስሜት የሚሰጥ አይደለም። ነገር ግን አንዳንዴ የራስን መብት ወይም ጥቅም ለማስጠበቅ በሌሎች ጉዳይ መካከል መግባት ግድ ይላል። ለመሆኑ በፍ/ብሔር ክርክሮች ላይ በስነስርዓት ሕጉ መሰረት ጣልቃ እንዴት ይገባል? ጣልቃ የመግባት መብትስ ያለው ማነው የሚለው የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ነው። እስከ ሰበር የደረሰ የጣልቃ ገብነት ክርክር እናነሳለን። በጉዳዩ ላይ ሕጉ ያስቀመጣቸውን አንቀጾችም እናነሳና ስለ ጣልቃ ገብነት መሠረታዊ የሕግ እውቀት ይኖረናል ማለት ነው። መልካም ንባብ፡-

1.ሻጭ ተከሳሽ ገዥ ጣልቃ መግባት ይችላሉ

ወ/ሮ እየሩሳሌም አቶ መከተ ላይ ክስ ያቀርባሉ። ክሱ አቶ መከተ የቤት ቁጥር 3936 የሆነው ቤት ላይ ያለኝን መብት ከልክለውኛል ቤቱ የኔ ነው ያስረከቡኝ የሚል ነበር። ቤቱን ደግሞ አቶ መከተ ለአቶ አስፋው ሸጠውታል። አቶ አስፋውም ቤቱን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የይዞታ ማረጋገጫም አውጥተውበታል። በተጨማሪ ተከሳሽ አቶ መከተ በሰጧቸው ውክልና ጠበቃ ቀጥረው የወይዘሮ እየሩሳሌምን ክስ እየተከራከሩ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወ/ሮ እየሩስን እና የወኪል ተደራጊያቸው የአቶ መከተን ክስ እያየ ለነበረው ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አቶ አስፋው እና ወ/ሮ ፀሐይ ቸከሩ የተባሉ ግለሰብ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንግባ ብለው ያመለክታሉ።

ፍ/ቤቱም የጣልቃ ገብነት ማመልከቻቸው ለዋናዎቹ ከሳሽና ተከሳሽ ለወ/ሮ እየሩሳሌም እና ለአቶ መከተ ምን ትላላችሁ ወደ ክርክራቸው ይግቡ ወይስ አይግቡ አስተያየታችሁን አቅርቡልኝ ሲል ጠየቃቸው።

ወ/ሮ እየሩስ በሰጡት አስተያየት አቶ አስፋው እኔ የከሰስኩት የአቶ መከተ ወኪል ሆኖ ጠበቃ ቀጥሮ እየተከራከረኝ ከቆየ በኋላ በክርክሩ የኔም ጥቅም ነካህ ብሎ ጣልቃ ልግባ የሚልበት የሕግ አግባብ የለም። ወ/ሮ ፀሐይም ጣልቃ ልግባ ያለበት ምክንያት በማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ ውድቅ መደረግ አለበት ሲሉ ለፍ/ቤቱ አስተያየታቸውን አቀረቡ።

ተከሳሹ አቶ መከተ በበኩላቸው አቶ አስፋውም ሆነ ወ/ሮ ፀሐይ ጣልቃ ቢገቡ አልተወውም ሲሉ ገለፁ።

ፍ/ቤቱም የጣልቃ አስገቡኝ ጥያቄውንና ዋናዎቹ ተከራካሪዎች የሰጡትን አስተያየት ከሕጉ ጋር አገናዝቦ መረመረ። ጣልቃ አስገቡኝ ያሉት አቶ አስፋው የተከሳሹ ወኪል ሆነው በቀጠሯቸው ጠበቃ በኩል ክርክር የተነሳበት የቤት ቁጥር 3936 የሆነው ቤት የአቶ መከተ የግል ቤት ባልሆኑ ለአቶ አስፋው ሸጠውላቸው በእጃቸው እንደሚገኝና አቶ አስፋው (ጣልቃ ልግባ ባዩ) በስማቸው ስለተመዘገበ የወ/ሮ እየሩስ ክስ ውድቅ ይደረግ ብለው በመከራከራቸው ጣልቃ ልግባበት የሚሉት ክርክር መብትና ጥቅማቸውን የሚነካበትን የሕግ አግባብ አያሳይም። በተጨማሪ በተከሳሽነትም በጣልቃ ገብነትም የሚከራከሩበት አግባብ የለም በሚል የጣልቃ ልግባ አቤቱታቸውን ውድቅ አደረገው። ወ/ሮ ፀሐይም ጣልቃ መግባት የሚያስችል ማስረጃ አላቀረቡም በሚል ሳይቀበለው ቀረ።

አቶ አስፋው ጣልቃ እንዳልገባ መከልከሌ አላግባብ ነው ሲሉ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ስላልተቀበላቸው የሕግ ስህተት ተፈፅሟል፣ ጣልቃ አትገባም የተባልኩት ከሕግ ውጭ በመሆኑ ይታረምልኝ ሲሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። ፍ/ቤቱም የሰበር አቤቱታው ላይ የከሳሽ የወ/ሮ እየሩስ አቶ አስፋው በወከላቸውና በራሳቸው ስም በአንድ ጊዜ መከራከር አይችሉም አለኝ የሚሉት የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርም በሚመለከተው አካል መክኗል። ስለዚህ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሊፀና ይገባል ሲሉ አቶ መከተ (ተከሳሹ) ደግሞ አቶ አስፋው ጣልቃ ሊገቡ ይገባል ሲሉ መልስ ሰጡ። የሰበር ፍ/ቤቱ አቤቱታውን ከሕጉ አንጻር መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ጉዳዩን የሚመለከተው ሕግ ምን ይላል የሚለውን እናንሳ።

2.ሶስተኛ ወገኖች እንዴት ወደ ክርክር ይገባሉ

በሌሎች ተከራካሪዎች በሚደረግ ክርክር መካከል ተከራካሪ ወገን ያልሆኑ 3ኛ ወገኖች ጣልቃ የሚገቡት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41-43 በተደነገጉት ሶስት መንገዶች ነው።

2.1.    ጠይቀው የሚገቡ ሰዎች፡- እነኚህ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41 መሠረት ክርክሩ እኔንም ያገባኛል የሚለውን ምክንያት ለፍ/ቤቱ አቅርበው ጣልቃ ለመግባት ፈቃድ መጠየቅ የሚችሉ ናቸው።

2.2.    የዐ/ሕግ ጣልቃ ገብነት፡- በተወሰኑ ፍ/ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሕጉ ዐ/ሕግ መንግሥትን በመወከል ተከራካሪ መሆን እንደሚችል ይፈቅዳል። በመሆኑም ይህ ሕግ በፈቀዳቸው የሰዎች መብት፣ ችሎታ ማጣት፣ ጋብቻ እና ስለኪሳራ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዐ/ሕግ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 42 መሠረት ጣልቃ ገብቶ የመከራከር ስልጣን ተሰጥቶታል።

2.3.    በፍ/ቤት ታዞ ጣልቃ መግባት፡- አንድ ሰው ለቀረበበት ክስ ሌላ ያልተከሰሰ ሰው እኔ የተከሰስኩበትን የክሱ ኃላፊነት ላይ ይህን ያህል ድርሻ አለው፤ ስለዚህ በተከሳሽ ጣልቃ ገብነት ወደ ክርክሩ እንዲገባ ይታዘዝልኝ ብሎ ፍ/ቤቱን ሲጠይቅ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለው በወሰነው ቀጠሮ ቀርቦ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ ያዛል። ጣልቃ ግባ ተብሎ የታዘዘው ሰው በቀጠሮው ቀን ካልቀረበ ፍ/ቤቱ ክሱ እንዲቀርብበትና በክሱ ውስጥ እንዳለ አድርጎ በመቁጠር ውሳኔ ይሰጣል።

እንግዲህ በስነስርዓት ሕጉ በሌሎች ሰዎች ክርክር ጣልቃ የሚገባባቸው ከላይ ያነሳናቸው ሶስቱ አግባቦች ሲሆኑ ጣልቃ መግባት ዓላማው በክርክሩ ተካፋይ መሆኑ ጥያቄው ሊቀርብ የሚችለው በሂደት ላይ ባለ ክርክር ሲሆን ክርክሩ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ጣልቃ ልግባ ማለት አይቻልም።

በተጨማሪ ክርክሩ የሌሎች ነውና ጣልቃ ይግባ ባዩ በጉዳዩ ላይ ይገባኛል የሚል መሆን አለበት። በስነስርዓት ሕጉ ቁ 41(2) መሰረትም ያገባኛል የሚልበትን ምክንያት በተለይም በክርክሩ ላይ ያለውን መብት ወይም ጥቅም የሚገልጽ ማመልከቻ ለፍ/ቤቱ ማቅረብ አለበት። ሰው ሳይሆን በሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት ክርክር ላይ ለሚያገባቸውና ለምን ጉዳዩ እንደሚያገባቸው ማስረዳት ለሚችሉ ሰዎች የተቀመጠ መብት ነው።

ይህን መብት ለመጠቀም ግን ለፍ/ቤቱ ጥያቄ መቅረብና በሥነሥርዓት ሕጉ ቁጥር 41(3) መሠረት ጣልቃ ገቡ በክርክሩ እንዲገቡ ያቀረብ ምክንያትና ማስረጃ መዝኖ ፍ/ቤቱ መፍቀድ አለበት። ብዙ ጊዜ ፍ/ቤቶች ዋናዎቹ ተከራካሪዎች እንዲሰጡ ያደርጋሉ። ሕጉ ግን የመፍቀድ ያለመፍቀዱን ጉዳይ ለፍ/ቤቶች ስልጣን የተተወ ይመስላል።

የጣልቃ ገብነቱ ጥያቄ ከተፈቀደ ፍ/ቤቱ ጣልቃ ገቡ የሚያቀርበው መከራከሪያ ለዋናዎቹ ተከራካሪዎች እስኪደርሳቸው ክርክሩን ለጊዜው አግዶ ያቆየዋል።

ጣልቃ ገቡ ከተፈቀደለት በኋላ ክርክሩን ለዋናዎቹ ተከራካሪዎች በራሱ ምክንያት ሳያደርሳቸው ከቀረ በራሱ ፍላጎት ጣልቃ መግባቱን እንደተወው ተቆጥሮ መብቱ እንደሚሰረዝ የሥነሥርዓት ሕጉ በቁ 41(4) ላይ ደንግጓል።

ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታና ስርዓት ከላይ የጠቀስኩት ሲሆን በመግቢያችን ላይ ባነሳሁት ክርክር ሰበር ወደ ሰጠው ውሳኔ ልመለስ።

3.ሰበር ምን አለ?

አቶ አስፋው በከሳሽ ወ/ሮ እየሩሳሌም በተከሳሽ አቶ መከተ ጉዳይ ጣልቃ ልግባ በሚል ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ በሰ/መ/ቁ 95934 ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቶበት በቅፅ 16 የሰበር ውሳኔዎች ላይ ታትሟል።

    ውሳኔው አቶ አስፋው አቶ መከተ በሰጧቸው ውክልና ጠበቃ ቀጥረው ስለአቶ መከተ ተከራክረዋል። ክርክሩ የአቶ መከተን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ቢወሰን የአቶ አስፋውን መብት የሚነካበት ሁኔታ የለም። የራሳቸውንም መብት እና ጥቅም አንፃር የገዙትን ቤት በራሳቸው ስም ጣልቃ መግባታቸው ክርክሩን ከማጓተት ውጭ ሌላ ጥቅም የለውም። ስለዚህ በስር ፍ/ቤቶች አቶ አስፋው ጣልቃ ሊገቡ አይገባም በሚል የተሰጠው ውሳኔ አግባብ ነው ብሎ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አፅንቶታል።

Page 1 of 5

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 137 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us