Items filtered by date: Wednesday, 05 April 2017 - Sendek NewsPaper

 

“ሀገሬን የማገልገል ፍላጎት ነው ወደዚህ ኃላፊነት ያመጣኝ”

 

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 42ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዳማ ከተማ አካሂዷል። ጉባኤው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ ለቀጣዮቹ አራት አመታትም ኮሚቴውን የሚመሩ ፕሬዝዳትና ስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫን አካሒዷል።

በጠቅላላ ጉባኤው ሲጠበቅ የነበረው የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን የወከሉትንና ብቸኛ እጩ ሆነው የቀረቡት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ተስማምቷል። ሌሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን በቀጥታ ያለ ድምጽ እና በድምጽ ምርጫ በማድረግም መርጧል።

ለአስራ አስፈጻሚነት 11 ግለሰቦች ሲሆኑ፤ አምስቱ ድምጽ ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። ከእነርሱም መካከል የፓራሊምፒክ ኮሚቴ የአካል ጉዳተኞች ስፖርቶችን ለማስፋፋትና ለማሳደግ እንዲሁም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በሚል ምክንያት ድምጽ ምርጫ ፉክክር ውስጥ ሳይገባ በቀጥታ እንዲመረጥ ያቀረበው ጥያቄ ላይ ጉባኤው ቀርቦ ደምጽ ተሰጥቶበት ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም መሰረት ከፓራሊምፒክ ኮሚቴ የቀረቡት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ ተመርጠዋል።

በአመራር ውስጥ ቢያንስ 30 ከመቶ ያህሉ ሴቶች መሆን ይኖርባቸዋል ስለሚል የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለ ድምጽ ምርጫ በቀጥታ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ቦታ መስጠት አስፈልጓል። በዚህም መሰረት ቦውሊንግ ፌዴሬሽን ያቀረባቸው የፌዴ,ሬሽኑ ፕሬዝዳትና የስፖርቱ ተጫዋች የነበሩት ወይዘሮ ሔሮዳዊት ዘለቀ ተመርጠዋል።

ሌሎች ያለ ድምጽ በቀጥታ አመራሩን ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው የተረገው የአለምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ፣ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አቶ ተስፋዬ በቀለ እና ከኦሊምፒክ አትሌቶች ተወካይ ደራርቱ ቱሉ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤው ለስራ አስፈጻሚ አባልነት የስፖርት ፌዴሬሽናቸውን ወክለው በእጩነት በቀረቡት ላይም ድምጽ ሰጥቷል። በተለያዩ የመመዘኛ ነጥቦችም ውጤት በመስጠት ከፍተኛ ነጥብ ያገኙ አምስት ተወዳዳሪዎችን ለይቶ ተቀብሏል።

አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን 75 ነጥብ ብልጫ በማግኘት የተመረጡ ሲሆን፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም ከአትሌቲክስ 73 ነጥብ አግኝቷል። ዶክተር ዳዲ ወዳጆ እና አቶ ዳዊት አስፋው ከወርልድ ቴኳንዶ 60 ነጥብ፤ እንዲሁም አቶ ኪሮስ ሀብቴ ከውሃ ስፖርቶች 43 ነጥብ አግኝተው አመራሩን ተቀላቅለዋል።

አቶ ተክለወይኒ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ወይዘሮ ሔሮዳዊት አቃቤ ነዋይ ሆነው መመደባቸው ተገልጻል።

ዶ/ር አሸብር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት፣ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች ሴካፋን በፕሬዝዳንትነትና በምክትል ፕሬዝዳንትነት በመሩበት ወቅት ያስመዘገቧቸው ውጤቶችን በማስታወስ በአመራርነት ውጤታማ ተሞክሮ እንዳላቸው በማስታወስ አሁንም ለሀገራቸው ስፖርት ጠቃሚ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል ብቸኛ ተመራጭ ሆነው በቆዩባቸው አመታትም በተለያዩ ሀላፊነት ላይ የቆዩት ዶክተር አሸብር፤ ከስፖርቱም ፍጹም እንዳልራቁ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በቀጣይ ሊሰሩ ያሰቡት በዋናነት ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቴሌቭዥን መብት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል። በቀደመው የስራ አስፈጻሚ የተጀመሩ ስራዎችንም በማስቀጠል ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

‹‹እዚህ ቦታ የተለየ የግል የሆነ እቅድ የለኝም። ምናልባት በግልህ ያለህ ምኞት ብባል ሀገራችን በስፖርቱ የቴሌቭዥን መብት ተጠቃሚ እንድትሆን ነው። እንደ ፊፋ ያሉት ተቋማት በገንዘብ የዳበረ አቅም ነው ያላቸው። ይህም በዋናነት በቴሌቭዥን መብት ጋር በተያያዘ በሚያገኘው ገቢ ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያም ማግኘት ያለባትን የቴሌቭዥን መብት ጥቅም እንድታገኝ ከሌሎች የስራ አመራሮች ጋር በመሆን እሰራለሁ።›› ብለዋል

ከዚህ በተጨማሪም ሴቶችን በተለያየ የስራ ኃላፊነት ቦታዎች እንዲመጡ የማብቃት ስራዎች በቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል።

 ‹‹የሴቶች ተሳትፎ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የግድ ነው። እኛም ማብቃት አለብን። እውቀት ያላቸውም አሉ። ትንሽ ድጋፍ እና እድል የሚፈልጉ እነሱን ወደዚህ ማምጣት ይኖርብናል።›› በማለትም ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት አስላጊነቱን ገልጸዋል።

‹‹ወደ ኦሊምፒክ አመራርነት ለመምጣት የፈለኩበት ዋና ምክንያቴ ሀገሬን ለማገልገል መፈለጌ ነው። ለስፖርት ትልቅ ፍቅር አለኝ። በስፖርቱ ሀገሬን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እፈልጋለሁ። ሀገሬን የማገልገል ፍላጎት ነው ወደዚህ ሀላፊነት ያመጣኝ›› በማለትም ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራርነት የመጡበትን ዋነኛ ምክንያት አስታውቀዋል።

ክፍል ስፖርት

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

በአገር አቋራጭ የብስኪሌት ውድድር ላይ የነበሩ የትግራይ፣ የአማራና የድሬደዋ ተወዳዳሪዎች የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው ለማቋረጥ መገደዳቸውን ተናገሩ። የኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየነው ጌታቸው በበኩላቸው አደጋው መከሰቱን አምነው የአካልና የንብረት ካሣ እንዲደረግ ስለመጠየቃቸውም ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት የበዓል አከባበርን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ አበባ እስከ አሶሳ በ56 ተወዳዳሪዎች አማካኝነት የተካሄደ ሲሆን፤ 653 ኪሎ ሜትር የፈጀውን ውድድር ትራንስ ኢትዮጵያ አንደኛ፤ መሰቦ ሲሚንቶ ሁለተኛ እንዲሁም ጉና ንግድ ስራዎች ሦስተኛ በመውጣት በቡድን ማሸነፋቸው ታውቋል።

በውድድሩ አጋማሽ ላይ ነቀምት የደረሱት ግንባር ቀደሞቹ ተወዳዳሪዎች ማለትም የአማራው ሲሳይ፣ የትግራዩ ክብሮምና የድሬዳዋው ጀማል የተባሉ ተወዳዳሪዎች ድንገት ወደመንገድ በገባ ኮድ35 የቤተሰብ መምሪያ ፒካፕ መኪና አደጋ እንደዳረሰባቸው ተናግረዋል። የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው ወደነቀምት መግቢያ “ባኮ” የተባለ አካባቢ ችግሩ መፈጠሩን አስታውሰው፤ አደጋው ግን የመኪና ግጭት ሳይሆን ድንገት ወደመንገድ የገባው መኪና ወደኋላ እንዲመለስ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በመመለስ ላይ ሳለ የተከሰተ መሆኑን አስረድተዋል። በተለይ ጉዳቱ የደረሰበትና በጉባ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ያገኘነው የአማራ ክልሉ ተወዳዳሪ ሲሳይ ባህሩ በግራ እጁ ላይ ያጋጠመውን የመሰበር አደጋ ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ብንመለከትም፤ የፌዴሬሽኑ ኃለፊ ግን ይህ ክስተት በቀጣዩ ቀን ያጋጠመ እንጂ ከመኪና አደጋ ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል። ያጋጠመውን አደጋ ተከትሎ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ወደነቀምት ሆስፒታል ተወስደው ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፤ ሲሳይን ጨምሮ በበነጋታው በቀጠለው የብስክሌት ውድድር ላይ ተሳታፊ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ሲሳይ የብስክሌቱ ጐማ መተንፈስ አጋጥሞት በመውደቁ ህመሙ እንደከፋበትና ስብራቱም ያጋጠመው በዚህ ወቅት እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል።

ብስክሌተኛ ሲሳይ በበኩሉ ለአደጋው መፈጠር የከተማው የፀጥታ ክፍሎችን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብስኪሌት ፌዴሬሽን በበኩሉ ጉዳዩን በነቀምት ወረዳ 7 ፖሊስ ጣቢያ ክስ መመስረታቸውን አስታውሰው ለደረሰባቸው የአካልና የንብረት ውድመትም በዐቃቤ ሕግ በኩል አስረድተው በቀጣይ የነቀምት ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ውክልናውን ወስዶ የካሣ ጥያቄያችንን እንዲመልስ እናደርጋለን ብለዋል።

ከአዲስ አበባ የተነሱት ተወዳዳሪዎች በአምቦ፣ በባኮ፣ በነቀምት፣ በጊምቢና በነጂ አድርጐ አሶሳ ለመድረስ የሰባት ቀን ጊዜን የወሰደ የ653 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ውድድር መሆኑን ሰምተናል።

ክፍል ስፖርት

 

-    ታምራት ቶላ በፕራግ ግማሽ ማራቶን አስደናቂ ውጤት አስመዝግቧል

አትሌት ደጀን ገብረመስቀል በአሜሪካን ምድር በሚካሔደው አመታዊው የካርልስባድ የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን ለአምስተኛ ጊዜ በማሸነፍ ታሪክ ሰርቷል። የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረው ኬንያ አሜሪካዊው ፖል ቼሊሞ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ባለፈው እሁድ የካርልስባድ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የተካሔደ ሲሆን፤ የኦሊምፒክ የብር ሜዳልያ ባለቤት የሆነው የ27 አመቱ ደጀን ርቀቱን በ13፡27 በማጠናቀቅ አሸንፏል። ቼሊሞ ደግሞ አምስት ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ሁለተኛ ሲሆን፤ አሜሪካዊው ሳም ማክኢንቴ ሶስተኛ ሆኗል፡፤ ደጀን ውድድሩን ለአምስተኛ ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን፡ ይህን ታሪክ በማስመዝገቡ መደሰቱን ገልጻል።

‹‹ውድድሩን ለአምስተኛ ጊዜ ማሸነፌ ለኔ በጣም አስደናቂ ነው። በዚህ መድረክ ማንም አትሌት አምስት ጊዜ አላሸነፈም። ይህ ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው። በማለት ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል።

በተመሳሳይ አልት እሁድ ቀን በተካኼደ የፕራግ ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያዊ አትሌት ታምራት ቶላ በአስደናቂ ብቃት ማሸነፉ ተዘግቧል። በውድድሩ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ውድድሩን በ11ኛ ደረጃ ማጠናቀቁ ታውቋል።

የዘንድሮውን የዱባይ ማራቶንን 2፡04፡11 በማጠናቀቅ የውድድሩን አዲስ ክብረወሰን በማስመዝገብ ያሸነፈው ታምራ ቶላ እሁድ እለት የፕራግ ግማሽ ማራቶንን 59፡37 በሆነ ደቂቃ ነው ያጠናቀቀው። ኬንያውያን በተከታታይ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ገብተዋል። 11ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጋለን ሩፕ ከታምራት ከሁለት ደቂቃ በኋላ ውድድሩን ጨርሷል።

የሪዮ ኦሊምፒክ የ10.000 ሜትር የነሐስ ሜዳያ ባለቤት ታምራት፤ በውድድሩ የኬንያውያንን ጠንካራ ፉክክር ተቋቁሞ ያሸነፈበት ብቃት አድናቆትን ያሰጠው ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም በረጅም ርቀት ሩጫዎች ስኬታማ መሆን የቻለ ነው ተብሏል።

ታምራት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ የዱባይ ማራቶንን የቦታውን አዲስ ክብረወሰን በማስመዝገብ ያሸነፈ ሲሆን፤ በሪዮ ኦሊምፒክ በ10.000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ነበር። አሁን ደግሞ የፕራግ ግማሽ ማራቶንን በ59፡37 ማሸነፍ ችሏል። ይህም ውጤቱ የግማሽ ማራቶን ፉክክር ከ60 ደቂቃ በታች መግባት ከቻሉ የአለማችን ጥቂት ሯጮች መካከልም አንዱ አድርጎታል።

ክፍል ስፖርት

 

አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ መመገብ ለውጫዊ የሰውነት ክፍሎችም ሆነ በውስጣዊ የሰውነት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። አትክልትና ፍራፍሬን በመመገብ ብቻ በስርዓተ ልመት፣ የማያስፈልጉ ነገሮችን በማስወገድ እንዲሁም በደም ዝውውር ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሰጣል። አብዛኞቹ አትክልቶችም መርዛማ የሆኑ ነገሮችን ከሰውነት በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። በዚህም ጠቀሜታቸው እንደ ካንሰር፣ የልብ ህመም እንዲሁም ስትሮክ ያሉ በሽታዎችን የመከላከል ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው። አብዛኞቹ አትክልቶችም በበርካታ ቫይታሚኖች የበለፀጉ በመሆናቸው ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በመስጠት የተመጣጠነ የሰውነት ክብደት እንዲኖረን፣ የጤናማ ቆዳ እና ፀጉር ባለቤት እንድንሆን የማድረግ ጠቀሜታ አላቸው።

ከሰሞኑ የወጣ አንድ የጥናት ውጤት ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዘውትረን መመገብ ያስፈለገበትን ሌላ ምክንያት ይዞ ብቅ ብሏል። ጥናቱ የተካሄደው በአውስትራሊያ ሲድኒ ዩኒቨርስቲ ነው። ጥናቱ የተካሄደው እድሜያቸው 45 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ 60ሺህ 404 የሀገሪቱ ዜጎች ላይ ነው። በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለውም በየዕለት ምግባቸው ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትረው የሚያካትቱ ሴቶች እና ወንዶች በአጠቃላይ ለጭንቀት ያላቸው ተጋላጭነት አነስተኛ መሆኑን ነው። በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ወንድና ሴት አውስትራሊያዊያን ለሶስት ዓመታት ያህል የአመጋገብ ስርዓታቸው ሲፈተሽ እና የስነ ልቦናና የጭንቀት እንዲሁም የድብርት መጠናቸው ሲጠና ቆይቷል።

የጥናቱ ማብቂያን ተከትሎ በተሳታፊዎች ላይ የተመዘገበው ለውጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢነትን የሚያበረታታ ሆኖ ተገኝቷል። እንደ ጥናቱ ውጤት በየእለት ምግባቸው ውስጥ ከሶስት እስከ አራት የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶችን የሚያካትቱ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከማይመገቡት ጋር ሲነፃፀሩ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው በ12 በመቶ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል። በቀን የሚመገቡት የአትክልት መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥርም ለጭንቀት እና ለድብርት የሚኖራቸው ተጋላጭነት እየቀነሰ መጥቷል። በዚህም መሠረት በየቀኑ ከአምስት እስከ ሰባት አይነት አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚመገቡት ይሄንኑ ያህል ከማይመገቡት ጋር ሲነፃፀሩ ለድብርትና ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው በ14 በመቶ የቀነሰ ሆኗል።

ሌላው በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለው ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ እና የሴቶች ጭንቀት ያላቸውን ግንኙነት ነው። በተደረገው ጥናትም አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትረው የሚመገቡ ሴቶች በተመሳሳይ ደረጃ ከሚመገቡት ወንዶች በተሻለ ሁኔታ ለጭንቀት፣ ለድብርት እና ለሌሎች የስነ ልቦና ጫናዎች የመጋለጥ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። በመሆኑም በቀን ምግባቸው ውስጥ እስከ ሰባት አይነት አትክልትና ፍራፍሬን አካተው የሚመገቡ ሴቶች በቀን ውስጥ አንድ አይነት አትክልት ወይም ፍራፍሬን አካተው ከሚመገቡት ጋር ሲነፃፀሩ የፊተኞቹ ለእነዚህ የስነልቦና ጫናዎች የመጋለጥ እድላቸው በ23 በመቶ ቀንሶ ተገኝቷል። ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ሴቶችም በቀን የሚመገቧቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች መጠናቸው እየቀነሰ ሲመጣ ለችግሮቹ የመጋለጥ እድላቸው እየጨመረ እንደሚሄድ በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የህብረተሰብ ጤና ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ሜሎዲ ዲንግ አስረድተዋል። በዚህም መሠረት በቀን ሁለት አይነት አትክልትና ፍራፍሬ የሚመገቡት በ16 በመቶ እንዲሁም በቀን ሶስትና አራት አይነት የሚመገቡት በ18 በመቶ ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው እንደሚቀንስ ተረጋግጧል። ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት ያላቸው በትምህርታቸው እና በእውቀታቸው ብዙም ያልገፉ፣ ብዙም እንቅስቃሴ የማያደርጉ እንዲሁም የኒኮቲን ጥገኛ የሆኑ ሴቶች በአብዛኛው ለጭንቀትና መሰል ስነልቦናዊ ጫናዎች ተጋላጭ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር ዲንግ፣ የጥናቱ ውጤት በእንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ላሉ ሴቶች መፍትሄ እንደሚሆንም ያለውን ተስፋ ገልፀዋል።

ስር የሰደደ ጭንቀት ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን፣ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊትን እንዲሁም ድንገተኛ የልብ ድካምን እና የስኳር ህመምን እንደሚያስከትል የሚገልጸው የአሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሲዬሽን በበኩሉ፣ ይሄን መጠነ ሰፊ ችግር የሚያመጣውን ጭንቀት በአትክልትና ፍራፍሬ መቆጣጠር ይቻላል ብሏል። በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ለጭንቀት እና ለድብርት የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች እንደመሆናቸው አዘውትረው አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመመገብ ከመሰል ችግሮች ራሳቸውን መታደግ እንዲችሉም አሳስቧል።

ሴቶች ምንም እንኳን ከወንዶች ያነሰ ካሎሪ ቢያስፈልጋቸውም በተፈጥሯቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይታሚን እና ማዕድናት ያስፈልጋቸዋል ይላል ጥናቱ። ከወር አበባ፣ ከእርግዝና እና ወሊድ እንዲሁም ከማረጥ ጋር በተያያዘ ሴቶች ለደም ማነስ፣ እንዲሁም ለአጥነት መድከም እና መሳሳት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑም እንደ ብረት፣ ካልሲየም፣ ማግኒዚየም፣ ቫይታሚንዲ እና ቫይታሚን ቢ9 የመሳሰሉትን ንጥረ ነገሮች በብዛት ማግኘት ይኖርባቸዋል። እነዚህን ንጥረ ነገሮች ማግኘት የሚቻለው ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አብዝቶ በመመገብ ነው እንደጥናቱ ግኝት። በተለይ የካልሲየም ማዕድን እጥረት በሰውነት ውስጥ ከተፈጠረ፤ ለተለያዩ የስሜት መለወጦች (ድብርት፣ንዴት እንዲሁም ድባቴ እና የእንቅልፍ መዛባት) የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው። በምንመገበው ምግብ ውስጥ በቂ የሆነ የካልሲየም ማዕድን ሳናካትት ስንቀር ሰውነታችን መደበኛ ስራውን ለማከናወን የካልሲየም ማዕድን እጥረት ስለሚገጥመው ካልሲየምን ከአጥንት ይወስዳል። በዚህ ጊዜ አጥንት ለካልሲየም ማዕድን እጥረት በመጋለጥ መድከም እና መሳሳት ይከሰትበታል። በዚህም የተነሳ ሴቶች በብዛት ለአጥንት መድከም እና መሳሳት የተጋለጡ ይሆናሉ።

ሌላው ሴቶች አትክልትና ፍራፍሬን እንዲያዘወትሩ የሚያስገድዳቸው ነገር ከፍተኛ የሆነ እና ከወንዶች የበለጠ የብረት ማዕድን ስለሚያስፈልጋቸው ነው። የብረት ማእድን በደማችን ውስጥ ኦክሲጅንን ተሸክሞ የሚያዘዋውረውን ሄሞግሎቢንን ለመፍጠር የሚያግዝ ማዕድን ነው። ሴቶች ደግሞ በተለይ በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ደም ከሰውነታቸው ስለሚወጣ ይሄንን ለመተካት ከወንዶች የበለጠ የብረት ማዕድን ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በእርግዝና እና በጡት ማጥባት ወቅት ብዙ የብረት ማእድን ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ከፍተኛ የብረት ማእድን ምንጭ የሆኑትን አትክልትና ፍራፍሬዎች በመመገብ ለሰውነት የሚያስፈልገውን የብረት ማእድን ማግኘት ካልተቻለ ከፍተኛ ለሆነ ደም ማነስ ያጋልጣል። በሰውነት ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን መኖር ከሚገባው መጠን ያነሰ ሲሆን ደግሞ ኃይል ከማሳጣት በተጨማሪም እንደ ድብርት፣ ብስጭትና ትኩረትን ለመሰብሰብ መቸገር ለመሰሉ የስነ ልቦና ችግሮች ያጋልጣል። በተመሳሳይም ቫይታሚን ቢ9 ወይም ፎሌት አሲድ በሴቶች ላይ የሚከሰቱ እንደ ካንሰር እና ድንገተኛ የልብ ድካምን የመከላከል ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም የሴቷ እድሜ እየገፋ ሲሄድ እና የማረጥ እድሜ ላይ ስትደርስ ሰውነቷ በቂ የሆነ ስትሮጂን የተባለውን ሆርሞን እንዲያመርት ፎሌት አሲድ ያግዘዋል። ይሄን አይነት ጠቀሜታ ያለውን ቫይታሚን ቢ9 በበቂ ሁኔታ ማግኘት ያልቻለች ሴትም እንደ ግልፍተኝነት፣ ድብርት፣ ንዴት፣ ለነገሮች ትኩረት ለመስጠት መቸገር እና ለራስ ምታት ችግሮች ተጋላጭ ናት። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በቂ የሆነ አትክልትና ፍራፍሬን በመመገብ ማስተካከል እንደሚቻል ጥናቱ ተስፋ ሰጥቷል።     

ክፍል ጤና

 

በአቡ ቪዲዮ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበው “ፈልጌ አስፈልጌ” የተሰኘው ልብ አንጠልጣይ ዘውግ ያለው የቤተሰብ ድራማ ፊልም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በበርካታ ሲኒማ ቤቶች ተመርቆ ለዕይታ ይቀርባል። በደራሲ መላኩ ደምሰው የተደረሰው ይህ ፊልም ዳይሬክት የተደረገው በአቦወርቅ ሃብቴ ሲሆን፤ በአቡ ቪዲዮ ፊልም ፕሮዳክሽን እና በአሰፋ ገረመው ፕሮዲዩስ መደረጉም ታውቋል። የፊልሙ ርዝመት 1 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ነው ተብሏል። በፊልሙ ላይ ዝናህ ብዙ ፀጋዬ፣ ፍፁም ፀጋዬ፣ ተዘራ ለማ፣ ያየህይራድ ማሞ፣ እየሩሳሌም ደረጀ፣ ሃረግ መኳንንት፣ ዳንኤል አበበና ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል። አቡ ቪዲዮ ፊልም ፕሮዳክሽን ላለፉት 20 ዓመታት የተለያዩ የቪዲዮ ክሊፖችን፣ የሙዚቃ ህትመትና ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት ይታወቃል።  

 

ሚዮዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመፅሐፍት ንባብና ውይይት ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በመጪው እሁድ ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት የአንጋፋው ገጣሚና መምህር ደበቡ ሰይፉ ስራ በሆነው “ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር)” በተሰኘው የግጥም መድብል ላይ ውይይት ያካሂዳል። በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) በሚካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ለውይይት የሚሆን የመነሻ ሃሳብ የሚያቀርበው ደራሲ ዳንኤል ወርቁ ነው። የመድረኩ አጋፋሪ ደግሞ የቋንቋ መምህሩና የታሪክ ተመራማሪው ሰለሞን ተሰማ ጂ. እንደሆነ ዝግጅት ክፍሉ ያደረሰን መረጃ ይመለከታል። በውይይተ መድረኩ ላይ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪያን ሁሉ ተጋብዘዋል።

 

ከዚህ ቀደም በስራቸው “አያስቅም”፣ “ቀዮ” እና “የማታ” በተሰኙ ፊልሞቹ የሚታወቀው ደራሲና ዳይሬክተሩ ሰዓሊ ኤሊያስ ሙሉአለም እነሆ “ያልተሾፈው” የተሰኘ አዲስ ፊልም ይዞ መጣ። መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በአቤል ሲኒማ የተመረቀው ይህ ፊልም በአሜን ፊልምስ ፕሮዳክሽን የተሰራው ፊልሙ፤ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ አንድ ዓመት ሲሆን፤ የፊልሙ ርዝመትም 1 ሰዓት ከ39 ደቂቃ መሆኑ ታውቋል። ፊልሙ ብዛት ያላቸውን ዘውጎች ማለትም የድራማ፣ የፍቅር፣ የባልታዊ፣ የኮሜዲና የልብ አንጠልጣይነት ባህሪይ አለው ተብሏል። በፊልሙ ላይ ሜላት ነብዩ፣ ዮሴፍ ገብሬ፣ ናሆም ጌታቸው፣ ሃይሉ አስመላሽ፣ ቴዎድሮስ ክፍሌ፣ ዘነቡ ገሰሰ እና ሌሎችም ከ30 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል። 

-    የፕሮጀክቱ 57 በመቶ ተከናውኗል

 

በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድ ኢትዮጵያ በረሃብና በድርቅ ስሟ ሲነሳ የነበረበት ታሪክ ጨርሶ ጠፍቷል ባይባልም፤ ቢያንስ ሀገሪቷን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነ ረሃብ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት አልተከሠተም። በድርቅ እና የሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግሮች ግን ሀገሪቷን ከመፈታተን እስከአሁን አልተገቱም።

 

 

ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧን እያመሰገነ፤ በሌላ በኩል፣ ድርቅ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እጁን እየዘረጋ በነበረበት ወቅት ነው፤ አዲስ የልማት አጀንዳን ያነገበና ፖለቲካዊ አንድምታው የገዘፈ ዜና በዐበይት የብዙኃን መገናኛዎች ያዳመጠው።

 

 

መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ኢትዮጵያ፣ በናይል ወንዝ ላይ 6ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ “የሚሌኒየም ግድብ” ለመስራት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ አበሰሩ። በሁለት አሃዝ እድገት እና በድርቅ መካከል ስሟ ሲነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ትልቁን የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ማቀዷ፣ በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ የነበራትን የረሃብ ብሔራዊ መለዮ በአረንግዴ ልማታዊ አጀንዳ በመቀየር ተስፋ ያላት ሃገር የሚል አዲስ ብሔራዊ መለዮ (Nation branding) ለመያዝ በቅታለች።

 

 

አዲሱን የብሔራዊ መለዮ ስያሜ ከሚያጸኑት ዐበይት ክንዋኔዎች መካከል አንዱ፣ ይኽው የታላቁ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ነው፤ ግንባታው ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል። የመሰረት ድንጋዩ በተጣለበት ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተን፣ ከግንባታው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው አካላት ስለግንባታው ዋና ዋና ክፍሎች እና ወቅታዊ ሒደቱና ደረጃውን የሚያሳዩ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

 

 

የግንባታው ዋና ዋና ክፍሎች

የዋናው ግድብ መጠኑ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በRCC ኮንክሪት ሙሌት ቴክኖሎጂ የሚገነባ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊቤ-III የኃይል ማመንጫ ቀጥሎ የሚገነባበት ዝቅተኛ ሲሚንቶ የሚጠቀምና ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ነው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታና 1 ነጥብ 8 ኪ.ሜ. ርዝመት ይኖረዋል።

 

 የግድቡ ግንባታ ሁለት ዋና የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር ኩነቶች እና ተጓዳኝ ግንባታ ሂደቶች አለው። ይኸውም፣ በግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ.ም የተከናወነው የወንዙን አቅጣጫ በጊዜያዊነት በግድቡ ቀኝ በኩል የማስቀየር ሂደት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በግድቡ ግራ በኩል በአራት የውሃ ማስኬጃ ትቦዎች አማካኝነት በታህሳስ 2008 ዓ.ም እንዲያልፍ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ ውሃው ይሄድበት በነበረበት (ኤፕን ቻናል) ግንባታው እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ከግድቡ በስተኋላ የተጠራቀመውን ወደ እያንዳንዱ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ውሃ የሚያደርሱ 16 የብረት አሸንዳዎችና የታችኞችን ሀገራት የውሃ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሁለት የቦተም አውትሌቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

 

የኃይል ማመንጫ ቤቶች

ከዋናው ግድብ ግርጌ በቀኝና በግራ በኩል ሁለት የኃይል ማመንጫ ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን፤ በስተቀኝ የሚገኘው የኃይል ማመንጫ ቤት 10 እንዲሁም በስተግራ በኩል በሚገኘው ደግሞ 6 የኃየል ማመንጫ ዩኒቶች ይኖሩታል። እያንዳንዱ ዩኒትም ከ375 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ያላቸው ጄኔሬተሮች ያሉት ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከጠቅላላው 16 ዩኒቶች የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ6,000 ሜጋ ዋት በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

 

 እንዲሁም ቀደም ብለው ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብለው የሚታሰቡት ዩኒት ሁለት ዩኒቶች (ዩኒት 9 እና 10) ሲጠናቀቁ በሚኖረው የውሃ መጠን በመጀመሪያ ወደ 216 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ኃይል እንደሚያመነጩ የሚገመት ሲሆን፤ በሙሉ የውሃ የመያዝ ከፍታ ሲደርስ ደግሞ 750 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ መሆናቸው ተገልጸል።

 

ውሃ ማስተንፈሻዎች (Spillways)

በፕሮጀክቱ የሚፈጠረው ሰው-ሰራሽ ሐይቅ (Reservoir) የማጠራቀም ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜ (Full Supply Level) ነው። ይህንንም ተጨማሪ የውሃ መጠን ተቀብለው ከግድቡ በታች ለመልቀቅ የሚያስችሉ ከዋናው ግድብ ግራ በኩል መዝጊያ ያለው የውሃ ማስተንፈሻ (Gated Spillway)፤ በዋናው ግድብ መካከለኛ ክፍል (Low Block Emergency Spillway) እና በሳድል ግድብ በስተቀኝ በኩል የሚገኝ ውሃ ማስተንፈሻ (Emergency Spillway) እየተገነቡ ይገኛሉ።

 

የኮርቻ ቅርፅ ያለው ግድብ (Saddle Dam)

ይህ ግድብ 50 ሜትር ከፍታ እና 5 ነጥብ 2 ኪ. ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሲሆን፤ የግድቡ አካል ውሃ በማያሳልፍና በማያሰርግ መልኩ የሚገነባ ሆኖ የድንጋይ ሙሌቱም መጠን ወደ 15 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሆነ በግድቡ አቅራቢያ በሚገኝ የድንጋይ ግብዓት እየተገነባ ያለው ግድብ ነው።

 

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ

ከዋናው ግድብ በ1 ነጥብ 4 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለ 500 ኪ.ቮ. ባለ ሁለት ባዝባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ይገኛል። የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው  ወደ ትራንስፎርመሮች የሚገባውን የመነጨ ኃይልና ወደ ማስተላለፊያ መስመሮች የሚወጣውን ገቢና ወጪ ቤዮችን ያካትታል፤ ይህ ባለ 500 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ በኢትዮጵያ የቮልቴጅ መጠን ታሪክ አንጻር ከፍተኛው መሆኑ ከባለሙያዎች ማብራሪ መረዳት ችለናል። 

 

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር

ከኃይል ማመንጫው የመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ትስስር ለማገናኘት የሚያስችል ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በደዴሳ - ሆለታ - አዲስ አበባ የሚደርስ 725 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ባለ 500 ኪ.ቮ. ባለ ሁለት ሰርኩዩት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተጠናቋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ 240 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ባለ 400 ኪ.ቮ. ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እስከ በለስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ድረስ ተገንብቶ አገለግሎት እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል ከብሔራዊ የኃይል ስርጭት መረብ ማቅረብ ያስቻለ ሲሆን፤ ይኸው መስመር ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምርም ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የኃይል ማስተላለፊያ በመሆን ያገለግላል።

 

በአሁን ሰዓት በመከናወን ላይ ያሉ ሥራዎች ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራዎች

የፕሮጀክቱ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራ የሚያካትታቸው ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤ የዋናው ግድብ ግንባታ፤ የኮረቻ ቅርፅ ያለው ግድብ ግንባታ፤ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ፤ የማስተንፈሰ በሮች ግንባታ የ500 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ከግድቡ በታች ድልድይ ግንባታ፤ የሰራተኞች መኖሪያ ካምፕ ግንባታ ናቸው።

 

ዋናው ግድብ በተመለከተ ያሉ ክንውኖች

በግድቡ ግንባታ ሂደት የቁፋሮ፤ የማጽዳት፣ የደንታል ኮንክሪት እንዲሁም የRCC (ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት) ሙሌት ሥራዎችን በቅደም ተከተል እየተከናወኑ ናቸው። እስካሁን ድረስ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያላነሰ የRCC አርማታ ሙሌት ሥራ ተከናውኗል። በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ውስጥም የቁፋሮ መጠን 21 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል እንደሚደርስ ተነግሯል።

 

ኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ

በግራና ቀኝ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ማለትም (በሁሉም 16 ዩኒቶች) እንዲሁም በLow block እና Tailrace አካባቢ የቁፋሮ ሥራ ተጠናቆ የግንባታ ሥራው እየተካሄደ ይገኛል። እንዲሁም ቀደም ብለው ኃይል በሚያመነጩት ዩኒቶች፤ በኢፌክሽን ቤይ እንዲሁም በሌሎቹ በቀኝም በግራም ባሉ ዩኒቶች የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና ኃይድሮ ሜካኒካል መሳሪያዎች ተቀባሪ አካላት ተከላና የአርማታ ሙሌት ሥራዎችም በቅንጅት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

የወንዙን አቅጣጫ ለማስቀየር የሚከናወኑ ሥራዎች

የወንዙ አቅጣጫ ለሁለተኛ ጊዜ በሚቀየርበት በግድቡ ግራ በኩል አስፈላጊ ሥራዎች ተከናወኑው ወንዙ በታህሳስ 2008 ዓ.ም በዳይቨርሽን ቦክስ ከልቨርት በኩል እንዲያልፍ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ ውሃው ይሄድበት የነበረውን ቻናል ለRCC የማዘጋጀትና የመሙላት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲገኙ በአሁኑ ሰዓትም ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 514 ሜትር ከፍታ ድረስ ተሞልቷል። እንዲሁም የዳይቨርሽን ከልቨርት የላይኛውና የታችኛው በሮች ምርት ተጠናቀው ወደ ሳይቱ በመድረሳቸው ከተከላው ጋር የተያያዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

የኮርቻ ቅርፅ ያለው ግድብ (Saddle Dam)

ይህ ግድብ 50 ሜትር ከፍታ እና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ሲኖረው የግድቡ አካል መጠን 15 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ሲሆን ለዚሁም የሚያገለግል ግብዓት በግድቡ አቅራቢያ ካለ የድንጋይ ኳሪ የሚገኝ ነው።

 

የከርሰምድር ፍተሻ ሥራዎች ተጠናቀው የቁፋሮ ሥራውም አልቋል። የግድቡ አካል ግንባታ ሥራ (Embankment Construction) 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል ደርሷል። ከዚሁ የግንባታ ሂደት ጎን ለጎን የግራውቲንግ፣ ፕላስቲክ ዳያፍራም ዎል ካስቲንግ ያሉ የውሃ ስርገትንና ማሳለፍን የሚከላከሉ ሥራዎች እንዲሁም የኢንስፔክሽን ጋለሪ ግንባታ ሥራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

 

ጊዜያዊ የመዳረሻ እና የቋሚ መንገዶች ግንባታ

አዲሱን የአሶሳ - ጉባ መንገድ እንዲሁም ቋሚ መንገዶችና ጊዜያዊ መዳረሻ መንገዶችን ጨምሮ የ124 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፤ አፈፃፀሙም 99 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

 

ሞቢላይዜሽንና ሎጂስቲክ

የተቋራጩ ሠራተኞች የመኖሪያ ካምፕና የቢሮዎች ግንባታ

የተለያዩ 10,500 የሥራ ተቋራጩ ሠራተኞችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው የመኖሪያ ካምፕ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በጊዜያዊና ቋሚ ካምፖች ውስጥ ለአማካሪ መሐንዲሱና ፕሮጀክት ቢሮው ሰራተኞች የሚያገለግል የመኖሪያ ካምፕ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

 

የተቋራጩ ሎጂስቲክ ኢንስታሌሽን ኮንስትራክሽን

ጊዜያዊና የተለያዩ የግንባታና ተከላ ሥራዎች በሳይቱ የተከናወነበት ነው፤ ከነዚህም መካከል ወርክሾፕ፣ ነዳጅ ማደያ፣ ላቦራቶሪ፣ ክሊኒክ፣ ቢሮዎች፣ የብረት ማከማቻ (Steel Yard)፣ የደማሚት ማከማቻ (Explosive Store) እና እንዲሁም ዋናው RCC ኮንክሪት ማምረቻ መሳሪያዎችና ተያያዥ ፕላንቶች ተከላ ያጠቃልላል። እነዚህም ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

 

የኮንክሪት ማምረቻ መሣሪያ የመገጣጠም ሥራ

በዋናው ግድብ ቀኝ እና ግራ በኩል የRCC ፕላንት ተከላው ተጠናቆ የRCC ምርት በማከናወን ላይ ይገኛል።

 

የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራዎች

የፕሮጀክቱ የኃይል ማመንጫ፤ የ500 ኪሎ ቮልት ስዊችያርድ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የሃይድሮ ሜካኒካል ዲዛይን፤ ምርት፤ አቅርቦት ተከላና ፍተሻ ሥራዎች በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብ.ኢ.ኮ) እየተከናወኑ ይገኛሉ፤ በዚህም በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ የኤሌክትሮሜካኒካል እና የሃይድሮሜካኒካል ምርትና ተከላ እየተከናወኑ ይገኛል።

 

ከዚህም ጋር በተገናኘ ቀድመው ኃይል ማመንጨት ለሚጀምሩት ዩኒቶች (ዩኒት 9 እና ድኒት 10) የተርባይንና ጀነሬተር ምርት ተጠናቆ ወደ ሳይት ተጓጉዞ የተከላ ሥራው በመከናወን ላይ ነው። ቀድመው ኃይል ማመንጨት ከሚጀምሩት ዩኒቶች ውጭ ያሉት 14 ዩኒቶችና የተዛማጅ መሳሪያዎች ወይም ዕቃዎች የምርትና የተከላ ሂደትም እንደቀጠለ መሆኑ ተገልጸል።

 

ከዚህም በተጨማሪ ቀድመው ኃይል ማመንጨት ለሚጀምሩት ዩኒቶች ፓወር ትራንስፎርመሮችና ሻንት ሪአክተር ምርት ተጠናቆ ለተከላ ዝግጁ ሆኗል። ከኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ሥራዎች ጋር በተገናኘ የቦተም አውትሌትና ቀደም ብለው ለሚገቡት ዩኒቶች የትራንዚሽንና እንዲሁመ የላይኛውና የታችኛው በሮች ምርትና በተጓዳኝም የተከላ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

500 ኪ.ቮ. የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርና

የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተነስቶ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ አልፎ እስከ ሆለታ የሚደርሰውና 725 ኪሎ ሜትር ግንባታው ተጠናቆ የዋናውን ኃይል ማመንጨት በጉጉት እየተጠባበቀ የሚገኘው ከህዳሴ-ደዴሳ-ሆለታ የተዘረጋው ጥምር ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።  

 

ተጨማሪ መረጃ

የሚገኝበት ቦታ፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከጉባ ከተማ 20 ኪ.ሜ. ርቀት አካባቢ ላይ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ ወደ ፕሮጀክቱ የሚወስዱ አማራጭ መንገዶች

አማራጭ 1፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ ደብረ-ማርቆስ፣ እንጅባራ እና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ በ730 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል።

አማራጭ 2፡ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ በ830 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል።

የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል፡ ከ6,450 ሜጋ ዋት

አማካይ የውሃ ፍሰት መጠን፡ 1,547 ኪዩቢክ ሜትር በሰከንድ

የውሃው መጠን ከፍታ፡ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜ. ከፍተኛ እና ከባህር ጠለል በላይ 590 ሜ. ዝቅተኛ፤

የዋናው ግድብ ከፍታ እና ርዝመት፡ 145 ሜ. ከፍታ፣ 1 ነጥብ 8 ኪ.ሜ. ርዝመት

የኮርቻ ቅርፅ ግድብ (Saddle Dam) ከፈታ እና ርዝመት፣ 50 ሜ. ከፍታ፣ 5 ነጥብ 2 ሜ. ርዝመት

ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጠር ኃይል ስፋት፡ 1,874 ስኩየር ኪ.ሜ.¾

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 6ኛ ዓመት በዓል አከባበር ከፊል ገፅታዎች

ክፍል ፖለቲካ

 

“ሃሳብን በሃሳብ መፈተን” በሚል መሪ ቃል በየወሩ በትራኮን ታወር በሚካሄደው የመፅሐፍት አውደ-ርዕይና የውይይት መድረክ ላይ ቅዳሜ (ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም) በዶክተር ምህረት ደበበ በተፃፈው “ የተቆለፈበት ቁልፍ” መጽሐፍ ላይ ውይይት ይካሄድበታል። የመፅሐፍትን ዋጋና ክብር ለመጨመር፤ ፀሐፊያንን ለማበረታታትና አንባቢያንም ስለሚያነቡት መፅሐፍ ጥቆማ ለመስጠት ታስቦ በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ ስለ“ተቆለፈበት ቁልፍ” መፅሐፍ ለውይይት የሚሆን የመነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት ከዚህ ቀደም ለየት ባለ መልኩ በ “ፍቅር እስከመቃብር” ላይ ትንታኔና ሀሳብ በማቅረብ “ምናብና ገሃድ” የተሰኘ መፅሐፍ ያዘጋጁት ዶክተር ዘካሪያስ አምደብርሃን ናቸው። ክብሩ መፅሐፍት፣ ለትማን ቡክስና እነሆ መጽሐፍት መደብሮች ፕሮግራሙን በጋራ አዘጋጅተውታል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፕሮግራም ላይ ከ25-50 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸው በርካታ መፅሐፍት በአውደ-ርዕይው እንደሚቀርብም አስተባባሪው አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልጸዋል።

በይርጋ አበበ

ከ2008 ዓም ህዳር ወር ጀምሮ ለተከታታይ የሰላም መደፍረስ የገጠመው የኢትዮጵያ ምድር ለበርካታ ዜጎች ህልፈት እና በቃፍ ላይ ላለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ መድቀቅም ምክንያት ሲሆን ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተሳትፎ ባላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ራስ ምታት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ችግር ተባብሶም አገሪቱ ወደከፋ እልቂት ሳታመራ ችግሩ በጊዜ መፍትሔ እንዲያገኝ የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ ለ21 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ድርድርና ውይይት እንዲያደርጉ ጥያቄ አቀረበ። ጥር 3 ቀን 2009 ዓም ለፖለቲካ ፓርቲዎች በተጻፈ ደብዳቤ የተገለጸውም ይኸው ጉዳይ እንደሆነ ደብዳቤው ይገልጻል።

በኢህአዴግ ጥሪ የቀረበላቸው ፓርቲዎቹም ሊካሄድ ስለታሰበው ድርድር የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት መርሆች ላይ ለሰባት ጊዜያት (መድረክ እና መአሕድ ለስድስት ጊዜ ብቻ ነው የተሳተፉት) ውይይት ካደረጉ በኋላ በተለይ “ድርድሩን ሶስተኛ ወገን ይምራው” በሚለው ነጥብ መስማማት ባለመቻላቸው ከመድረክና ከመአሕድ በተጨማሪ ስድስት ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ገዥው ፓርቲ በበኩሉ “ድርድሩ በዙር እየተመራ ቢካሄድ ጉዳቱ ምን ላይ ነው?” ሲል ይጠይቅና “አደራዳሪ የምትሉትን ቅድመ ዝግጅት ርሱት ይህን ማድረግ ካልቻላችሁ ግን ጉዟችን እዚህ ላይ ሊቆም ይገባል” ሲል አቋሙን በግልጽ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ድርድር አንዳች ለውጥ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በሁለቱ ወገኖች አለመግባባት ድርድሩ ሳንካ ተፈጥሮበታል። ለመሆኑ ሁለቱ ወገኖች በዚህ አቋማቸው ከቀጠሉ በአገሪቱ የተፈጠረው ችግር ወዴት ሊያመራ ይችላል ስንል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወጧቸውን መግለጫዎችና አመራሮችን ጠይቀን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረከ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓም ባወጣው መግለጫ “የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ ህጎችም የተደነገጉትን እና በተለያዩ ወቅቶች ቃል የገባቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበርና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ፤ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር በርካታና እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውናል። ለእነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሰላማዊ አግባብ ወቅታዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰላማዊ አግባብ ሲጠይቁና ሲታገሉ የቆዩ ቢሆንም፤ ከኢህአዴግ ሰሚ ጆሮ ስለተነፈጉ ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተው፤ ሀገራችንን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከተዋት ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ስር በኮማንድ ፖስት አማካይነት ሁኔታዎችን ሃይል በመጠቀም ለማረጋጋት በሚሞከርበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ላይ እንገኛለን” በማለት በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ምክንያት ነው ብሎ ያመነበትን አስቀምጧል።

 መድረክ በመግለጫው አያይዞም “የኢህአዴግ አገዛዝ ለሕዝባችን ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎች በሕጋዊ አግባብ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ፈንታ በኃይል ለማፈን መንቀሳቀሱና መድረክና ሌሎችም ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን በመዝጋት ኢህአዴግ የፈጠራቸውን ችግሮች በትክክል ነቅሶ በማውጣት ተጨባጭ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚያስችል ድርድር ለማካሄድ ለብዙ ዓመታት ሲያቀርቡ ለቆዩት ጥያቄዎች ኢህአዴግ አዎንታዊ ምላሽ ነፍጎ በመቆየቱ ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል” ሲል ይገልጻል። መድረክ ሀቀኛ ተቃዋሚ ሲል የሚገልጸው በምን መመዘኛ ነው ተብለው የተጠየቁት የመድረኩ ኃላፊዎች “በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል በመሆኑን ከኢህአዴግ ጋር የጥቅም ተጋሪ ያልሆኑትን ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር በቅድመ ሁኔታ ባለመስማማት ራሱን ያገለለው ሌላው ፓርቲ ሰማያዊ ነው። ፓርቲው “በነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ ያልተመራ ድርድር ለህዝብ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ አያመጣም” ሲል ያወጣውና ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ “ኢህአዴግ በግንቦት 2007 ዓም በተካሄደው ምርጫ መቶ በመቶ ድል ተጎናጽፌያለሁ ብሎ አውጆ መስከረም 2008 ዓም መንግስት ቢመሰርትም ጥቂት ወራትን እንኳን በሰላም ማስተዳደር አቅቶት ሀገሪቱ በተቃውሞ መታመስ ጀመረች” ሲል የችግሩን መነሻ ይገልጻል። ሰማያዊ ፓርቲ ከድርድሩ መውጣቱን በገለጸበት መግለጫው “አንድ ገዥ ፓርቲ ነጻ አደራዳሪ የምትለውን ትንሽ ጥያቄ መልሶ መደራደር ካልቻለ ለሌሎች ትልልቅ ህዝባዊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል ብሎ ፓርቲያችን አያምንም። በመሆኑም ፓርቲያችን ከዚህ በኋላ ነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ በማይመራው ቅድመ ድርድር ሂደቶች ላይ እንደማይሳተፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናሳውቃለን” ብሏል። “ሆኖም ገዥው ፓርቲ ኢትዮጵያ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ የአቋም ለውጥ ካመጣ ፓርቲያችን ሁሌም ለውጥ ለሚያመጣ ድርድር ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል። ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ “እዚህ ውሳኔ ላይ (ከቅድመ ድርድሩ መውጣትን) የደረስነው በስራ አስፈጻሚው ሙሉ ድምጽ ነው” ብለዋል።

 “ለሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ ለማስገኘት ኢህአዴግ ከሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውጤታማ የሆነ ድርድር ሊያካሂድ ይገባል” በሚል ርዕሰ መግለጫ ያወጣም መድረክ “መድረክ ከነሐሴ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ከሁሉ አስቀድሞ የሀገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውጤታማ ድርድር በማካሄድ ተጨባጭ መፍትሄዎችን ለማስገኘት ሲጠይቅ ቢቆይም፤ ኢህአዴግ ግን በሀገራችን ወቅታዊና ነባራዊ ተጨባጭ የፖለቲካ ችግሮች ላይ በማያተኩሩና ተጨባጭ መፍትሄም በማያስገኙ ጉዳዮች ላይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያህል ከአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በፈጠረው “የጋራ ም/ቤት እየተወያየሁ ነኝ” እያለ ካላአንዳች ተጨባጭ ውጤት እስከ አሁን ቆይቷል። በእነዚህ በከንቱ በባከኑት ጊዜያት የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከድጡ ወደ ማጡ እየወረደ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አድርሶን ይገኛል” ብሏል። ፓርቲው አያይዞም “ኢህአዴግ በጠራው የድርድር ቅድመ ዝግጅት ላይ የመተማመኛ እርምጃዎች ኢህአዴግ መውሰድ እንዳለበት” አስታውቆ እንደነበር ገልጿል። መድረክ ያስቀመጠው የመተማመኛ እርምጃ “በዚሁ ድርድር ላይ በግምባር ቀደምትነት ሊሳተፉ የሚገባቸው የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ፤ በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ላይ እያሉ የታሰሩብን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ይገኙባቸዋል” የሚሉ እንደነበር ገልጾ “ሆኖም ግን ከኢህአዴግ ጋር ስብሰባ ከተጀመረ ወዲህ ከሁለት ወራት በላይ የቆየን ቢሆንም፤ የጠየቅናቸው የመተማመኛ እርምጃዎች እስከ አሁንም ተግባራዊ አለመደረጋቸው በግንኙነቱ ላይ ተስፋ እንዳይኖረን አድርጓል” ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለቀጣዮቹ አራት ወራት መራዘሙን የተቃወመው መድረክ ምክንያቱን ሲያስቀምጥም “መላውን ህዝባችንን በከፍተኛ የታጠቀ ሰራዊት ተፅዕኖ ስር ተሸማቅቆ እንዲኖር ያስገደደው አዋጅ አሁንም ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ፤ የመብት ጥያቄ አንስቶ ከፍተኛ መስዋዕት የከፈለውን ህዝብ ቁጣና ምሬት የሚያባብስ እርምጃ እንጂ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ አይሆንም!” በማለት ነው። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በበኩላቸው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም በአገሪቱ ያሉ ቸግሮች ከኢህአዴግ አቅም በላይ መሆናቸውን ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

ድርድሩን የገጠመው ሌላ ፈተና

ኢህአዴግ የጠራው የድርድር ሀሳብ ተቃውሞ የገጠመው ከአደራዳሪ ነጻና ገለልተኛ መሆን ብቻ አይደለም። መድረክ ድርድሩ የ22 ፓርቲዎች ስብሰባ ሳይሆን የሁለትዮሽ ወይም ሀሳባቸው ተቀራራቢ የሆኑ ፓርቲዎች በመሪ ተደራዳሪ እንዲደራደሩ የሚል ነው። እንደ መድረክ አቋም የፖለቲካ ድርድር በ22 ፓርቲዎች መካሄዱ “ጉንጭ አልፋ ክርክር” ከመሆን አይዘልም። ይህን አቋሙን በመግለጫ ሲያስታወቅም “መድረክ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ እንደመሆኑ እና በፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋት ምክንያት ከፍተኛ በደል በራሱ፤ በመሪዎቹና በአባላቱ ላይ እየደረሰ እንደመሆኑ፤ ከሌሎች መሰል ፓርቲዎች ጋር ወይም ለብቻው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎቹና ኢህአዴግ በጋራ በሚስማሙባቸው አጀንዳዎች ላይ ከቀሩት ፓርቲዎች ጋርም በጋራ ስብሰባ ላይ እየተወያየ፤ ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ድርድር የማካሄድ መሪ ወይም ተቀዳሚ ሚና እንዲኖረው ባቀረብነው አካሄድ ላይም ኢህአዴግ መስማመት አልፈለገም። በዚህ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ከቀረ በኋላም መድረክ በርካታ ራሱ በቀጥታ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ያለባቸው አስቸኳይና አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደመኖራቸው በሁለትዮሽ ለመደራደር ያቀረበው አማራጭ ሃሳብም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም። ይህ የኢህአዴግ አቋም ድርድሩ በሁለትዮሽ በአስቸኳይ ተካሂዶ ችግሮችን በተጨባጭ ለመፍታት ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርግ ስለሆነ ሲጀምርም ኢህአዴግ የድርድር አጀንዳ እንዳልነበረው ዳግመኛ ማረጋገጫ ነው” በማለት አሰታውቋል።

መድረክ በመግለጫው አክሎም “በዚህ ትክክለኛ የድርድር ባህሪይ በሌለውና ቀደም ሲል ኢህአዴግና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስርተው ከቆዩት “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት” ከሚባው አካል ውይይት ጋር በሚመሳሰልና ውጤታማ ሊሆን በማይችል የ22 ፓርቲዎች ውይይት ሂደት ውስጥ መቀጠል ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው ከላይ የተጠቀሰውን የሁለትዮሽ የድርድር አማራጭ ለኢህአዴግ አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በመሆኑም መድረክ ባቀረባቸውና ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶችን ሊያስገኝ የሚችለው የሁለትዮሽ ድርድር በኢህአዴግና በመድረክ መካከል በአስቸኳይ እንዲጀመር በኢህአዴግ በኩል ፈቃደኛነቱ በአስቸኳይ እንዲገልፅ አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል።

 

ሌሎች ፓርቲዎችስ ምን አሉ?

ኢህአዴግ ድርድሩ ሊካሄድ የሚገባው በነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ ሳይሆን ራሳችን ተደራዳረዎቹ በዙር እናደራድር ሲል በድርድሩ ኢህአዴግን ወክለው የቀረቡት አቶ አሰመላሽ ወልደስላሴ እና አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናግረዋል።

መድረክና ሰማያዊ ቀደም ብለው አቋማቸውን ያሳወቁ ሲሆን የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአሕድ)ም የሁለቱን ፓርቲዎች ዱካ ተከትሎ ያለ አደራዳሪ መደራደር አልፈልግም ሲል አቋሙን ገልጿል። ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ኢብአፓ፣ ኢራፓ እና መኢዴፓ “ያለ አደራዳሪ መደራደር አንፈልግም ሆኖም ከድርድሩ መውጣታቸንንም ሆነ በድርድሩ መቀላችንን የምናሳውቀው በፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።   

በአቶ አየለ ጫሜሶ የሚመራው ቅንጅት፣ አንድነት፣ መኢብን፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ እና ሌሎች ፓርቲዎች ድርድሩን በዙር እየተመሩ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።  

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ቅድመ ዝግጅት ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓም የሚቀጥል ይሆናል። በዚያ እለትም ሰማያዊ መድረክ እና መአሕድ የማይሳተፉ መሆኑን ከአሁኑ አሰታውቀዋል። ድርድሩ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችልም ወደፊት የምናየው ይሆናል።  

ክፍል ፖለቲካ
Page 1 of 3

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 93 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us