Items filtered by date: Wednesday, 25 April 2018 - Sendek NewsPaper

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወልድያ እና በፋሲል ከነማ ጨዋታ በተከሰተው ረብሻ ጋር ተያይዞ የወልድያ የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የወጣቶች ማዕከል ማናቸውንም ውድድሮች ለአንድ ዓመት እንዳያካሂድ መታገዱ ይታወሳል። ይህም ጉዳይ የስፖርት ቤተሰቡንና ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላትን ሲያወያይ ከርሟል። የወልድያ ስታዲየም ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ግንባታው በይፋ መመረቁና በዕለቱም ሼህ ሙሐመድ ላሳደጋቸውና ለወግ ለማዕረግ ላበቃቸው የወልድያ ሕዝብ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በስጦታ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው። ስታዲየሙ ትልልቅ አገራዊና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ይካሄዱበታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ነገርግን ሰሞኑን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን የወጣው ቅጣት ከክለቦች አልፎ ስታዲየሙ እንዲዘጋ የሚያደርግ ውሳኔ መያዙ ብዙዎችን አሳዝኗል። ይህንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ ከወልድያ ስታዲየም የምህንድስና ጥበብ ጀርባ ስማቸው በጉልህ የሚነሱት ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል። የደብዳቤው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

***          ***          ***

ለክቡር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡    ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየምና

የወጣቶች ማዕከልን ይመለከታል

ተጠቃሽ፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወልድያ ከተማ ስፖርት ክለብ የተጻፈ ደብዳቤ ቁጥር፡ 25/ኢእፌአ9/034 ቀን 08/08/2010 ደብዳቤ

ከሁሉ አስቀድሜ የስፖርቱን ዓለም በማፍቀር በግላቸው፣ በመንግሥት ሥራ ኃላፊነታቸው፣ በቡድን መሪነታቸው፣ በክለብ አስተዳዳሪነታቸው፣ በተለያዩ የፌዴሬሽን ሥራቸው፣ በዜና ዘጋቢነታቸው ተግባር ተሰማርተው ለስፖርት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ለሚደክሙ ሁሉ ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦና መስዋእትነት ከፍ ያለ መስሎ ስለሚታየኝ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው። ይህ ደብዳቤ እንደ አንድ ግለሰብ በተቆርቋሪነት የቀረበ መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እወዳለሁ። የተለያዩ የግል ድርጅቶችና የዩኒቨርስቲ የመምራት ኃላፊነቴ፣ ስፖርት ሥራን በህብረት በማሠራት፣ ደንበኛን በማርካትና ውጤታማ በመሆን ለሥራዬ ዓቢይ አስተዋጽኦ እንዳለው ከልብ አምናለሁ። በምመራቸው 25 የሚድሮክ ቴክናሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ውስጥም የተለያዩ ክለቦች በማቋቋም፣ ዓመታዊ ውድድር ማድረግ ከጀመርን ከ13 ዓመት በላይ ሆኖናል። ስፖርት ህብረት ፈጥሮልናል፣ መልካም ሥነ ምግባርን እንድናበለጽግ ረድቶናል። ቆንጆ ስታዲየም የመገንባት ሙያችንንም አዳብሮልናል።

በአንድ ወቅት ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የተውጣጡ ተጫዋቾች ያሉበት "የመቻሬ" እግር ኳስ ቡድን በአዲስ አበባ አቋቁመን ወደ ብሔራዊ ሊግ ገብቶ እንዲጫወት አድርገን ነበር። ይህ ቡድን በመንግሥትና በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰጡ ህጐችንና መመሪያዎችን እንዲያከብር ከማድረጋችን በላይ የራሳችን የውስጥ መመሪያ አውጥተን ቡድኑ በሥራ ላይ እንዲያውለው በማድረግና በየሜዳው ተገኝተን መከታተል ጀመርን። ከውስጥ የዲሲፕሊን መመሪያችን ውስጥ ጨዋታ ተመልካቹ በኩባንያዎቻችን ውስጥ የምናመርታቸው ምርቶች ገዥ በመሆኑ በደንበኛ (Customer) መልክ በጥንቃቄ በመያዝ ተገቢውን አክብሮት ማድረግ እንዳለብን፣ ተጫዋቾቹን አሳምነን ሥራ ጀመርን። የኩባንያዎቻችን ማልያ ማንነታችንን በአዎንታዊ መልኩ በህዝቡ ዘንድ እንዲያስተዋውቀን በማቀድ በጽኑ አምነን ሥራ ገባን። ሆኖም በየጨዋታው ቦታ ስንገኝ ብዙ በጆሮ ሊሰሙ የማይገቡ ቃላትና አልባሌ ሁናቴዎችን ብንመለከትም በጨዋታው ገፋንበት። ከዚህ በኋላ ተጫዋቾቻችን የውስጥ ደንባችንን መጣስ ጀመሩ። ከእነዚህ የውስጥ ደንቦች ውስጥ የዳኛን ውሳኔ አለማክበርና መጨቃጨቅ፣ በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ቀይ ካርድ ማግኘት ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በደንባችን ውስጥ ስለነበር፣ ይህን በመተላለፍ ስነ-ስርዓት የጐደለው ሥራ በመሥራት፣ ሁለት ቀይ ካርድ ከገንዘብ ቅጣት ጋር ቡድኑ አገኘ። ማኔጅመንቱም ቡድኑ ምናልባትም በዲስፕሊን አቋሙ ከሚጠበቅበት ደረጃ እንዳልደረሰ በመገንዘብ ከፌዴሬሽን እንዲወጣ የራሳችን ውሳኔ ወሰድን። ሠራተኛው ከ"መቻሬ" ቡድን ይልቅ በየኩባንያዎቹ ቡድን አቋቁሞ የሠራተኞቹን የስፖርት ፍላጐት የማርካት ሥራ እንዲሠራ አደረግን። ይህን በማድረጋችን የጠቅላላው የቴክኖሎጂ ግሩፕ ሠራተኞችን የስፖርት ስሜት ሳንጐዳ በተሻለ መልኩ ስፖርቱ እንዲቀጥል አድርገናል። "የመቻሬ" ቡድን አጠፋ ብለን የስፖርቱ እንቅስቃሴ ከኩባንያዎቻችን ውስጥ እንዲጠፋ አላደረግንም። ማንም ጥፋተኛ በመመሪያና በህግ መሠረት ቅጣት ማግኘት እንዳለበት አምናለሁ። ሆኖም ቅጣቱ ፍትሐዊ መሆን ብቻ ሳይሆን ክለቡን፣ ቡድኑን፣ አጠቃላይ የስፖርት አፍቃሪውን የስፖርት ፍቅር በአሉታዊ መንገድ የሚጐዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ ከመሪዎች/ከሀላፊዎች የሚጠበቅ ነው።    

ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሚያዝያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልድያ ከተማ ቡድንና በፋሲል ከተማ ቡድን መካከል የተደረገውን የእግር ኳስ ጨዋታ አስመልክቶ ለተፈጠረው ችግር የሰጠውን ውሳኔ ኮፒ አግኝቼ መመልከት ችያለሁ። በዚህ ውሳኔ ላይ ቅጣት የተጣለባቸው የወልድያ ስፖርት ክለብ አሠልጣኝ፣ አንድ የወልድያ ስፖርት ቡድን ተጫዋች፣ የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን ያካተተ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ላይ የፌዴሬሽኑን የዲስፕሊን መመሪያ አንቀጾች በመጥቀስ የተደረጉ ውሳኔዎች ላይ በጉዳዩ ጥልቅ እውቀት ስለሌለኝ ለባለሙያዎች በመተው ተገቢው ፍትሃዊ ውሳኔ እንደገና የማየት ሁኔታ ይደረግበታል የሚል ተስፋ ጽኑ እምነት አለኝ።

ይህ እንዳለ ሆኖ በውሳኔው ቁጥር 2 ላይ የቀረበውና የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም አጠቃቀምን በሚመለከት የተወሰነው ውሳኔ ግን ፍትሃዊና ትክክለኛ መስሎ ስላልታየኝ ፌዴሬሽኑ በጥሞና እንዲመለከተው ትንሽ ልበል።

በመጀመሪያ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም እና የወጣቶች ማዕከል በለጋሹና በአንድየው የሀገር አጋር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ተሠርቶ የተበረከተው ለወልድያና ለአካባቢው ህብረተሰብ መገልገያ እንዲሆን ታቅዶ ነው። ይህም ማለት ተቋሙ (ስታዲየሙ) የወልድያ የእግር ኳስ ክለብ ወይም ቡድን ሀብት አይደለም። በወልድያና አካባቢዋ፣ ከዚያም አልፎ በሀገር ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ወገኖች ከአንድ ለእናት ሀገሩ ፍቅር ባለው ባለሃብት የተሰጠ መሆኑና በከፍተኛ ደረጃ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ በተገኙበት ተመርቆ ለህዝቡ የተበረከተ ተቋም ነው።

ይህ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለና ፌዴሬሽኑ ይህን ስታዲየም ለሀገርም፣ ለአህጉርም እንዲሁም ለዓለም ልዩ ልዩ ውድድሮች እንዲውል በማድረግ ያስተዋውቀዋል ብለን በምንጠብቅበት ወቅት፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ባለሀብት የሆነው የአካባቢው ህዝብ እንዳይገለገልበት ማድረግ ፍጹም አሳዛኝና ስሜታዊ እርምጃ ነው። የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቁጥር 2 ውሳኔ እንዲህ ይላል፡-

"የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለጨዋታው ያስመዘገበው የወልዲያ ሼህ አላሙዲ ስታዲየም ክለቡ ጥፋት ከፈፀመበት ከሚያዚያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲኘሊን መመሪያ ክፍል 2 ምዕራፍ 5 በአንቀጽ 43 መሰረት በወልዲያ ሼህ አላሙዲ ስታዲየም የሚደረጉ ጨዋታዎች የመጫወት መብት እንዲያጡ እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚካሄዱ ማንኛውም የእግር ኳስ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ተወስኗል።"

ይህ ማለት ስታዲየሙ ባለበት ዝግጁ ሆኖ እንዲገኝ የሚያስፈልገው የገንዘብ ምንጭ ሁሉ ተቋርጦ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ሸረሪት ጠረጋ ውስጥ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ላይ እንዲጠመድ ማድረግ ይሆናል። ወልድያና አካባቢው ብሎም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህን ለሀገር የተበረከተ ስታዲየም በአግባቡ መጠቀም ይፈልጋሉ። ተገቢውን ክልላዊና ፌዴራላዊ ድጋፍ እና አስተዳደር በማመቻቸት የሀገራችን ባለሃብቶች በስፖርቱ ዓለም በሰፊው እንዲሳተፉ ቀስቃሽ (insentive) ይሆናል ብለን ሂደቱን በመጠባበቅ ላይ ባለንበት ወቅት ግራ የሚያጋባና እጅግ ለምናፈቅራት ወልድያና አካባቢዋ የቱሪስት መስህብ በመሆንና የወጣቶቹንም በስፖርቱ ዓለም የመሳተፍ ስሜትና ፍላጐት እንዲያጐለብት የተሠራው ስታዲየም ላይ የተወሰነው እገዳ ፍጹም ፍትሃዊ ስላልሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአንክሮ እንዲመለከተው በአክብሮት ስጠይቅ፣ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም ምን አጠፋ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመሻት ነው። ተቋሙ ብዙ ዓይነት የስፖርት መሥሪያ ያለው በመሆኑ ከተማዋና አካባቢው በስታዲየሙ መገልገል የሚፈልግ መሆኑን አግንዛቤ ማስገባት ለአካባቢው እንደሚጠቅም ፌዴሬሽኑ እንደሚረዳ እርግጠኛ ነኝ። ስለሆነም አስቸኳይ መፍትሄ ቢሰጥበት ሁላችንም ደስ ይለናል።

በተያያዘ መልኩ የምንወዳትን ወልድያ በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በልማት ወዘት ወደፊት እንዳትራመድ አሉታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች የአመራር አካላት፣ ግለሰቦች፣ ወዘተ ሰከን ባለ መልኩ ለአካባቢው እድገትና ብልጽግና ቅድሚያ በመስጠት የተፈጠረውን አንገት የሚያስደፋ አሉታዊ ገጽታ (image) በያገባኛል ስሜት በህብረት ማስወገድ እንዳለብንና ለዚህም ወልድያ-ወዳዶች የሆን ሁሉ እንደምንረባረብ ከወዲሁ እየገለጽኩ፣ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ወልድያ የሰዎች መገናኛ ሆና እድገቷን እንደምታፋጥን ሙሉ እምነትና ተስፋ በመሰነቅ ነው።

           ከአክብሮት ሠላምታ ጋር

አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)

ቺፍ ኤግዝኪዩቲቭ ኦፊሰር/ፕሬዚዳንት

ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ

         (ፊርማና ማሕተም አለው)

ክፍል ስፖርት

 

አዲስ አበባ ስታዲየም ለስድስት ቀናት ሲካሔድ የቆየው 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመከላከያ ክለብ የበላይነት ተጠናቋል።

ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለያዩ የፍጻሜ ውድሮችና የመዝጊያ ስነ ስርአቶች እሁድ እለት በድምቀት ተጠናቋል። አዳዲስ ክብረወሰን ላስመዘገቡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል። አንጋፋ አትሌቶችና አመራሮች በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ሽልማቶችን አበርክተዋል።

ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀው መከላከያ በሴቶች 158 ነጥብ እና በወንዶች 177 ነጥብ በማስመዝገብ ዋንጫ ወስዷል። ኦሮሚያ ክልል በሁለቱም ጾታ ሁለተኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ ሲዳማ ቡና በወንዶች ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፈው ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች በቀጣይ በሚካሔደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማስታወቁ ይታወሳል።

ክፍል ስፖርት

 

(Jurisdiction of Courts or Divisions)

ዳግም አሰፋ (www.abyssinialaw.com)

 

ይህን ለመጻፍ ያስገደዱኝን እና የገጠመኙን ሁኔታዎች በቅድሚያ ላብራራ። ነገሩ እንዲህ ነው። አንድ ሰራተኛ አሰሪው በነበረው ድርጅት ላይ ህገ-ወጥ የስራ ውል መቋረጥ ተፈጽሞብኛል በማለት ላቀረበው ክስ አሰሪው ድርጅት በተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ሰራተኛው የስራ ውሉን ስላቋረጠ ካሳ እንዲከፍለኝ የሚልና ሰራተኛው ስራ ላይ በነበረ ጊዜ ለስራው አገልግሎት የተሰጠውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሳይመልስ በመቅረቱ ንብረቱን እንዲመልስ ወይም የንብረቱን ግምት ብር 23,000 (ሃያ ሶስት ሺ) እንዲከፍለኝ በማለት ክስ አቀረበ። ጉዳዩን ሲያይ የነበረው የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የስራ-ክርክር ችሎትም በድርጅቱ የላፕቶፕ ንብረትን በተመለከተ የቀረበውን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ይህ ችሎት (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የማየት ስልጣን ስለሌለው ጉዳዩን በዚሁ ፍ/ቤት በፍትሐብሄር ችሎት ክስ የማቅረብ መብታቸውን ጠብቄ አቤቱታውን ውድቅ አድርጌዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል።


በተመሳሳይ ሁኔታም ተከራይ አከራዩ ድርጅት ሶስት ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን በተለያየ ጊዜ የተከራየ ሲሆን በቅድሚያ ለተከራያቸው ሁለት ክፍሎች የውል ሰነድ ያለው ሲሆን ለሶስተኛው ክፍል ግን ከቃል ስምምነት ባለፈ በጽሁፍ የተደረገ ውል የለም። ነገር ግን ለሶስተኛው ክፍልም ቢሆን ለአራት ወራት ያህል በየወሩ ከተከራይ የኪራይ ገንዘብ የተቀበለበትን ደረሰኝ በማስረጃ አያይዟል። ይህንንም የኪራይ ውልና የኪራይ ክፍያ ደረሰኝ መሰረት በማድረግ አከራይ ላልተከፈለው እና ተከራይ ለተገለገለበት ጊዜ የኪራዩ ክፍያ ይከፈለኝ በማለት በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ክስ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የፍ/ቤቱ የኪራይ ችሎትም (ልብ በሉ ፍ/ቤቱ አይደለም) የኪራይ ውል ሰነድ ያላቸውን  ክፍሎች አስመልክቶ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለኝ ሲሆን የኪራይ ውል የሌለውን ሶስተኛውን የቢሮ ኪራይ ክፍያ ክስ በተመለከተ ግን ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው በዚሁ ፍ/ቤት የንግድና ልዩ ልዩ ችሎት ስለሆነ በዚህ ችሎት ክስ የማቅረብ መብታችሁን ጠብቄ በሶስተኛው ቢሮ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ ዘግቼዋለሁ በማለት ብይን ሰጥቷል።


ለመሆኑ በአዋጅ የተቋቋሙ ፍ/ቤቶች እንጂ ችሎቶች ይህን መሰሉ ስልጣን አላቸው? የፍትሐብሔር የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማስ ከዚህ አኳያ እንዴት ይመዘናል የሚለውን በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡- የፌደራል ፍ/ቤቶችን ያቋቋመው አዋጅ ቀ. 25/88 በፌደራል ደረጃ የሚኖሩት ፍ/ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ጠቅላይ ፍ/ቤት መሆናቸውን ሲገልጽ የእነዚህ ፍ/ቤቶችም በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣንም ሆነ በይግባኝ ደረጃ ጉዳዮችን ተቀብለው አይተው እና አከራክረው ወሳኔ ሊሰጡ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ደንግጓል።


ይህ አዋጅ ይህንንም ሲገልጽ እነዚህ የፌደራል ፍ/ቤቶች ጉዳየን ለማየት እንዳለቸው ስልጣን የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት እንዲያስችል እያንዳንዱ ፍ/ቤት ቢያንሰ ሶስት ችሎቶች እነዚህም የፍትሐብሄር፣ የወንጀል እና የስራ-ክርክር ችሎቶች ሊኖሩት እንደሚገባ (በፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ 25/88 አ.ቁ 20(1)፣ 23(1)) ሲደነግግ እንደሚቀርቡለት የጉዳዮች ብዛትና ዓይነት በስሩ እንደ ነገሩ ሁኔታ ሊይዛቸው የሚችሉ ችሎቶችን ፍ/ቤቱ በራሱ አስተዳደራዊ ውሳኔ የማብዛት መብት አለው (በተሻሻለው ፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ 454/97 አ.ቁ 23(1))።


በመሆኑም ፍ/ቤቶች በአዋጅ የተቋቋሙና በስራቸው በአዎጁ ከተጠቀሱት ውጪ ያሉትን ችሎቶች  የሚያዋቅሩት ደግሞ በአስተዳደራዊ ውሳኔ እና የዚህም ዓይነተኛ እና ዋና ዓላማ ደግሞ የፍትሐብሄር ሥነ-ሥርዓት ሕጉን ዋና ዓላማ ለማስፈጸም ሲሆን ይህም የተፈጠነ ፍትህ ለማግኘት እና የተከራካሪዎችንና የፍ/ቤት ጊዜና ወጪን መቆጠብ ነው። ከዚህ ባለፈ ከፌዴራል እና የክልል ሰበር ሰሚ ችሎቶች ውጪ  (የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አ.ቁ 80፣ የፌ/ፍ/ቤ/አ 25/88 እና የተሻሻለው 454/97) በማንኛውም ፍ/ቤት ውስጥ ያሉ ችሎቶች ከተቋቋሙበት ፍ/ቤት ውጪ ያራሳቸው የሆነ የስረ-ነገርም (material jurisdiction) ሆነ የግዛትም ሥልጣን (local jurisdiction) የላቸውም። ነገር ግን በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ስር ያለው ሰበር ሰሚ ችሎት ከፌ/ጠ/ፍ/ቤቱ በሕግም ሆነ በፍሬ ነገር ስህተት ላይ በስር ፍ/ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ በይግባኝ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ውጪ በሀገሪቷ ላይ በሚገኙ ፍ/ቤቶች በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የተፈጸመ የሕግ ትርጉም ስህተትን ብቻ የማረም እና የሚሰጠውም የሕግ ትርጉም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ፍ/ቤቶች እና ውሳኔ ለመስጠት የተቋቋሙ ተቋማትን የሚያስገድድ ሲሆን በክልል ጠ/ፍ/ቤቶች የሚገኙ ሰበር ሰሚ ችሎቶች ደግሞ በየክልሎቻቸው በሚገኙ ፍ/ቤቶች በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተትን የማረም ስልጣን ሲኖራቸው ይህ ግን ክልሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አ.ቁ 80 መሰረት በውክልና በሚያዩት የፌደራል ጉዳይ ላይ በተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዋች ላይ ግን ጉዳዩን የማየት ስልጣን አይኖራቸውም። ብሔራዊ የዳኝነት ስልጣን (Judicial Jurisdiction) ያልገለጽኩት ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር የሚመዘን ወይም የአንድ ሀገር ፍ/ቤት የቀረበለትን ጉዳይ ከማየት እና ከማስፈጸም አኳያ የሚታይ እና የስልጣኑ ምንጭም ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ እና በሀገራት መካከል የሚደረግ የሁለትዮች ወይም የሶስትዮሽ ውል (ለምሳሌ የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 461(1)(ሀ) principles of reciprocity ይመለከቷል) በመሆኑ ሲሆን የተቀሩት የግዛትና የስረ-ነገር ስልጣን ምንጭ ግን በሀገራት በራሳቸው ሕግ (domestic or national laws) የሚወሰን በመሆኑ ነው።


በዚህም ምክንያት በአሰሪና ሰራተኛ በነበረው ክርክር አሰሪው ያነሳው የንብረት ይመለስልኝ ክርክር በፍትሐብሄር ክስ ለማቅረብ ቢፈልግ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለው እራሱ የስራ-ክርከሩ ችሎት የሚገኝበት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሆኖ ሳለ እና ተከራካሪዎቹ ተመሳሳይ ሆነው ሳለ፤ እንደዚሁም በአከራይና በተከራይ በነበረው ጉዳይ እንዲያው የጽሁፍ የኪራይ ውል የሌለውን ቢሮ የኪራይ ክፍያ አስመልክቶ ያለውን ጉዳይ ለመዳኘት ስልጣን ያለው እራሱ ጉዳዩ የቀረበለት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሆኖ ሳለና ተከራካሪዎቹ ተመሳሳይ ሆነው ሳለ፤ በተጨማሪም ማንኛውም ወገን ክስ በሚያቀርብበት ጊዜ ጉዳዩ በየትኛው ፍ/ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ የመለየትና የትኛው ችሎት ጉዳዩን ማየት እንዳለበት መመደብ ያለበት ሬጅስትራሉ ሆኖ ሳለ (ምክንያቱም የችሎት ምደባ ስራ አስተዳደራዊ በመሆኑ አቤቱታ አቅራቢ ሊያውቀው ይገባ ነበር የማይባልበት ጉዳይ ነው) ጉዳዩን የተመለከቱት የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ችሎቶች እራሳቸውን በፍ/ቤት ደረጃ የተቋቋሙ አድርገው በመቁጠር የቀረበላቸውን ጉዳይ ለማየት ስልጣን የለንም በማለት ብይን መስጠታቸው አግባብ አይደለም።


ፍ/ቤቶች የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት ባላቸው አቅም በሚጥሩበት ሁኔታ አንዱ ችሎት ሊያየው የሚገባን ጉዳይ ለአስተዳደራዊ ስራ ምቹነትና የተፋጠነ ፍትህን ለመስጠት በውስጥ ደንብ የተደራጁት ችሎቶች እራሳቸውን በአዋጅ እንደተቋቋመ ፍ/ቤት በማየት ችሎቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም በማለት በፍ/ቤቶች ላይ የስራ ጫና ማብዛት በተከራካሪዎች ላይ የጊዜና የገንዘብ ኪሳራ ማብዛት ሕግን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ በቶሎ ሊስተካከል የሚገባው እይታ ነው።

ክፍል ምልከታ

 

· ተቀባይነትን ያስገኘላቸውና ተደናቂነትን ያተረፈላቸው፣ ከበዓለ ሢመታቸው ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ የሚገልጹባቸው ውብና ወርቃማ ቃላት በመኾናቸው፣ ስለ ተግባራዊነታቸው ዘወትር ሊያስቡበት ይገባል፤


· ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ በመኾኑ፣ በአስተዳደር ዘመናቸው፣ የአንዲት እናት ሀገር ልጆች፣ የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከለን ዐይንህ ላፈር የምንባባልበት የጎጣጎጥ ጉዳይ ሊያበቃና ትውልዱ አንድ በሚኾንበት ጉዳይ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤


· የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ የኢትዮጵያ ባለአደራ፣ ጥንታዊት፣ አንጋፋና እናት ቤተ ክርስቲያን መኾኗ የማይካድ ሐቅ ቢኾንም፣ ውለታዋ ተዘንግቶ፣ በሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት ስም እንርገጥሽ የተባለችበት ዘመን ኾኗል።


· ዛሬም የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በምሥራቁና በደቡቡ፣ መንግሥታዊ አደራን ረግጠው ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ ባደረጉ ባለሥልጣናት ጣጣው እየበዛባት፣ ፈተናው እየከበዳት ነው፤


· እባክዎ ክቡርነትዎ፣ በአስተዳደር ዘመንዎ፡-እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል በቃል ሳይኾን በተግባር ሰፍኖ፤ አልይህ፣ አልይህ መባባል ቀርቶ፣ በትምህርት እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊነት እንዲሰፋና እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ፤


· አባቶቻችን፥ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ፤ ይላሉ፤ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው ይምሩን፤


· እንዲህ እስከመሩን ድረስ፣ ሹመትዎ ከእግዚአብሔር ነውና፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን፤ እንደ ጥንቱ።  


· ኢትዮጵያዊነት ሲሸረሸር እንደቆየና እየተካደም እንዳለ ለባሕር ዳርና አካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ መጠገንና መታከም እንዳለበት አሳስበው፣ ለዚህም ቀና ቀናውን ማሰብ፣ ያሰብነውን መናገር፣ የተናገርነውንም ተደምረን መተግበር እንዳለብን አስገንዝበዋል፤


· መደመር በአንድ ጀንበር እንደማይመጣና ጊዜና መደጋገፍ እንደሚፈልግ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ፣ ቂምን ከመቁጠር ይልቅ በይቅርታ ልብ ተደጋግፈን፣ ከትላንቱ ተምረን መልካሙን በመያዝ፣ ክፋቱ አይበጅም፤ አይደገምም ተባብለን ኢትዮጵያን ማስቀጠል እንዳለብን መክረዋል፤


· “በኦሮሞ ኮታ አታስቡኝ፤ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ፤ እኩል ነው የማገለግላችሁ፤” በማለት አስታውቀው፣ “የሃይማኖት አባቶች፥ በጸሎትና በምክርም እንድታግዙኝ እጠይቃለሁ፤” ብለዋል።


· የሃይማኖት አባቶችም፥ትሕትናን፣ አክብሮተ ሰብእን፣ ግብረ ገብነትን፣ ክፉ ሥር የኾነውን ሌብነትን መጸየፍን ለትውልዱ በማስተማር ድርሻቸውን እንዲወጡና እንዲደግፉ ጠይቀዋል፤


· አገራዊ ዕውቀት እንዲያብብ ጥንታውያኑ ጣና ቂርቆስ፣ ደብረ ኤልያስ እና ዲማ ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት፤ ከእነርሱም የተገኙ ሊቃውንትና አይተኬ አስተምህሮዎች፣ በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሐሳቦችን በማመንጨትና ትውልድን በመቅረጽ መሠረታቸውን ያኖሩ ባለውለታዎች እንደኾኑ ጠቅሰዋል፤


· አራት ዐይና ጎሹና መምህር አካለ ወልድ፣ ከሊቅነታቸው ባሻገር በማኅበራዊ የሽምግልና ሚናቸውና ምክራቸው እንደሚታወቁ፤ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፣ ወለጋ ቢወለዱም ጎጃም-ደብረ ኤልያስ ተምረው በጎንደርም እንዳስተማሩ አንሥተዋል፤


· ዘመናዊ ትምህርት ባልተጀመረበት የአገራችን ታሪክ፣ የአስተዳደሩ መዋቅር ይሸፈን የነበረው ከአብነት ት/ቤት ተመርቀው በሚወጡ ምሁራን እንደነበር አውስተው፤ ዛሬም የባህል፣ የጥበብና የዕውቀት ገድሉን በማስቀጠልና የላቀ ትውልድ ለማፍራት ብዙ መጣር ይጠበቅብናል፤ ብለዋል፤

 

የብፁዕነታቸው ንግግር ሙሉ ቃል፡-


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን


· ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር


· ክቡር ፕሬዝዳንት


· ክቡር ከንቲባ


· ክቡራን ሚኒስትሮችና በዚህ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤

 

ብፁዕ አቡነ አብርሃም: የባሕር ዳር እና ምዕራብ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ


ከሁሉ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ኾኖ በዚህ ዕለት ከልዩ ልዩ ነገር፣ እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው ፈተና ሰውሮ ከመሪያችን ጋራ በአንድነት ስለ ሀገራችን እንድንወያይ፣ እንድንመካከር፤ ከአዲሱ መሪያችንም መመሪያ እንድንቀበል፣ ጊዜውን ፈቅዶና ወዶ በዕድሜያችንም ላይ ተጨማሪ አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ምንም እንኳ እንግዳ ባይኾኑም ወደሚመሩት ሕዝብዎ በመምጣትዎ ቤት ለእንግዳ  የምትለው ሀገር እንኳን ደኅና መጡ፤ ትላለች። ዘመንዎ ኹሉ፥ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመግባባት፣ የብልጽግና ይኾን ዘንድ  ምኞትዋንም ትገልጻለች።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እኔ ልናገር የምፈልገው ክቡርነትዎን በተመለከተ ነው የሚኾነው። በድፍረት ሳይኾን በታላቅ ትሕትና።
ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ማንም ማን አይሾምም። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርታችን፣ ማንኛውም ሰው በታላቅም ደረጃ ይኹን በቤተሰብ አስተዳደር ከታች ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቀደለት ይሾማል። እግዚአብሔር ፈቅዶልዎትም በመራጮችዎ አድሮ ሹሞታል። ያከበርዎትና የሾሞት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን።


እግዚአብሔር ሲሾም ግን፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኹለት ዐይነት አሿሿሞች አሉ። የክቡርነትዎ የትኛው ነው? በጎው እንደሚኾን ሙሉ ተስፋ አለኝ፤ አኹን ከሚታየው። እግዚአብሔር፥ አንዱን ለጅራፍነት፣ ለአለጋነት ይሾማል። ሕዝብ ሲበድል፣ ሕዝብ ሲያምፅ፣ እግዚአብሔርነቱን ሲረሳ፣ አልታዘዝም ባይነት ሲገን፤ የሚገርፍበትን፥ ጨንገሩን፣ አለጋውን፣ ጅራፉን፣ እሾሁን ይሾማል። በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ሕዝብ ሰላማዊ ሲኾን፣ በአምልኮቱ ሲጸና፣ ፍቅርና መከባበር ሲኖረው ደግሞ የሚያከብረውን፣ የሚያለማለትን፣ የሚቆረቆርለትን፣ አለሁ የሚለውን ይሾማል።


በእኔ እምነት እስከ አሁን ድረስ፣ ከበዓለ ሢመትዎ ጀምሮ በሚያስተላልፏቸው ወርቃማ ቃላት፣ ኅብረ ቀለማትን የተላበሱ፣ ሰንሰለት በሰንሰለት ተሳስረው እንደ ሐረግ እየተመዘዙ በሚወርዱ ውብ ዐረፍተ ነገሮች፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው እጅግ ደስ በሚያሰኝ መልኩ እናትነትን የመሳሰሉትን ዝርዝር ሳልገባ ሲገልጹ ሰንብተዋል። በእኒህ የአጭር ጊዜ የሹመት ሳምንታትም፣ ዳር እስከ ዳር፣ ካህን ነኝና “ወጥን ማን ያውቃል ቢሉ ቀለዋጭ” እንዲሉ እንደ ካህንነቴ ብዙ ስለምሰማ፣ ተደናቂነትን አትርፈዋል። በዚህ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን።


ክቡርነትዎን ግን አደራ የምለው፣ መናገር ቀላል ነው፤ ማድረግ ግን ከባድ ነው። ማውራት ይቻላል፤ በአንድ ቀን ሀገርን መገንባት፣ ማልማት ይቻላል - በወሬ ደረጃ፤ መሥራት ግን ፈታኝ ነው። ፈታኝ የሚያደርገው፣ ውስብስብ እየኾነ በተለያየ መልኩ የሚቀርበው ጣጣ ነው። ስለዚህ ከተለያየ አቅጣጫ የሚቀርበው ውስብስብ ነገር፣ የተናሯቸውን ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ የጋራነትን፤ አሁንኮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ትልቁ ችግር፣ እኔነት የሚል ራስ ወዳድነት ሠልጥኖ እኮ ነው። ለእኔ ከሚል ይልቅ ለወንድሜ፣ ለእኅቴ፣ ለጎረቤቴ፣ ለሀገሬ፣ ለወገኔ የሚለው ስሜትኮ በእያንዳንዳችን ቢሠርጽ ሌላ ችግር አይኖርም፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ አእምሮ የሠረጸው የእኔነት ጠባይዕ ነው፤ ራስ ወዳድነት ነው። እንደ እንስሳዊ አባባል፣ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል”  የሚል አስተሳሰብ በመፈጠሩ ነው።


ስለዚህ፣ ይህን ችግር ለመናድ፣ ይህን ችግር ለማስወገድ በተዋቡ ዐረፍተ ነገሮች የሚያስተላልፏቸው ቃላት እንደው ዘወትር እንደ መስተዋት ልበል፣ እንደ ግል ማስታወሻ ከፊትዎ ሰቅለው፥ ምን ተናግሬ ነበረ፤ የቱን ሠራሁት፤ የትኛው ይቀረኛል የሚል የዘወትር ተግባር እንዲኖርዎ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ትሕትና እገልጽልዎታለሁ። ምክንያቱም ይህን ዕድል ያገኘሁት ዛሬ ስለኾነ፣ ነገ ብቻዎን ስለማላገኘዎት አሁኑኑ ልናገር ብዬ ነው።


ብዙ ታሪክ አሳልፈናል። ስለኢትዮጵያዊነት መቼም፣ አሰብ ስለነበርኩ በአካል የማውቃቸው የአፋሩ ታላቅ አዛውንት መሪ የነበሩት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ “ኢትዮጵያን እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል[ከነባንዴራዋ]” ነው ያሉት አይደል። ግመሎች ያውቋታል፤ ነው ያሉት፤ አስታውሳለሁ። አሁን ግን ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ክቡርነትዎ ተደናቂነትን እያተረፉ ያሉት፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹባቸው ቋንቋዎች፣ እጅግ የተዋቡ በመኾናቸው ነው።


ሰሞኑን ኢየሩሳሌም ነበርኩ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ። ከተለያየ አቅጣጫ ያልመጣ አልነበረም፤ ብዙ ሰው የሚያወራው ግን ትልቅ የምሥራች ነው፤ “እግዚአብሔር በርግጥም ይህችን ሀገር ከጥፋት ሊታደጋት ይኾን?” የሚል ጥያቄ ነው ያለው። አዎ፣ ያንዣበበው ፈተና፣ የደፈረሰውና የታጣው ሰላም አስጊ ነበር። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት አስተላላፊነት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ጮኻለች ወደ እግዚአብሔር። የሰላም አምላክ ሆይ፣ ሰላምህን ስጣት፤ አንድነትን ስጥ ለልጆችህ፤ እያለች። ቤተ ክርስቲያን ወሰን ስለሌላት፤ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ልጆቿ ስለኾኑ፣ ከልጆቿ አንዱም ማንም ማን እንዳይጎዳ ስለምትፈልግ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለሀገራችን ሰላምን ስጣት፤ እያለች ጸሎቷን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አሰምታለች። ወደፊትም ታሰማለች።


ስለዚህ ክቡርነትዎ፣ ይኼን የጎጣጎጡን ጉዳይ፣ የዚያ ማዶ የዚህ ማዶ የመባባሉን ጉዳይ ወደ ጎን ይተዉትና አልጀመሩትም፤ ይጀምሩታልም ብዬ አላስብም፤ ትውልዱ አንድ የሚኾንበትን ጉዳይ፣ ላለመደፈር፤ አባቶቻችንኮ ያልተደፈሩት አንድ ስለኾኑ ነው። ልዩነት ስለሌላቸው ነው፤ ከዚህ ቀደምም ተናግሬዋለሁ፤ በላይ በበራሪ በምድር በተሽከርካሪ የመጣውንኮ በኋላ ቀር መሣሪያ ያሸነፉትና ያንበረከኩት፣ በየትኛውም ዓለም ብንሔድ፣ ኢትዮጵያዊ አትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በሙሉ ወኔ በየትኛውም ቦታ ገብቶ የመናገር፣ የመቀመጥ ዕድሉን ያገኙት በአንድነታቸው ነው። የእገሌ ወእገሌ መባባል ስለሌለባቸው።


አሁን ግን ወዳጆቻችን በሰጡን የቤት ሥራ፣ እዚሁ ተቀምጠን እንኳ በአሁን ሰዓት የእገሌ የቤት ሥራ፣ የእገሌ፣ የእገሌ እየተባባልን ነው። መቼ ነው ከዚህ ሸክም የምንላቀቀው ወገኖቼ? መቼ ነው ከጎጠኝነት የምንላቀቀው? መቼ ነው፣ በኢትዮጵያዊነት አምነን፣ አንች ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለን እግዚአብሔር በሰጠን የነፃነት ምድር፣ አባቶቻችን የደም ዋጋ በከፈሉባት ምድር፣ አባቶቻችን አጥንታቸውን በከሠከሱባት ምድር፣ አባቶቻችን ዕንቁ የኾነውን ታሪካቸውን ለእኛ አሻራ አድርገው ትተውባት በሔዱት ምድር በእፎይታ የማንኖረው እስከ መቼ ነው? የአንድ እናት ልጆች፣ የአንዲት ሀገር ልጆች የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከላለን ዐይንህ ላፈር የምንባባለው እስከ መቼ ነው? ስለዚህ በክቡርነትዎ ዘመን ይኼ እንዲበቃ ምኞቴም ነው፤ ጸሎቴም ነው። የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን እላለሁ።


ሌላው ሳልጠቁም የማላልፈው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት፣ የታሪክም ሰው እንደመኾንዎ፣ ቅድምም ሲናገሩ ዐይናማ የኾኑትን አራት ዐይናማ ሊቃውንት፣ ከየአቅጣጫው ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹትን በሙሉ እየጠቃቀሱ እንዳስረዱን ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ፣ አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች። ይኼ የማይካድ ሐቅ ነው። ርግጠኛ ነኝ፣ ሼኹም ይመስክሩ ሌላውም ይመስክር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እገሌ ወእገሌ ሳትል ሁሉንም በየእምነቱ ፊደል ያስቆጠረች፣ ያስነበበች፤ ለሀገር መሪነት ያበቃች አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች። የእኔ ስለኾነች አይደለም የምመሰክረው። ስለዚህ ቢያንስ የእምነቱ ተከታዮች አይኾኑ፤ እናከብራቸዋለን፤ እንዲያከብሩን እንፈልጋለን። ግን ለባለውለታ፣ ሀገርን ዛሬም በሰንሰለቶቿ አስራ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በሃይማኖት እኩልነት፣ በሃይማኖት ነፃነት እንርገጥሽ እየተባለች ያለችበት ዘመን ቢኖር ግን ዛሬ ነው።


ቤተ ክርስቲያንኮ ባለአደራ ናት። ክቡርነትዎ ጊዜ ቢኖርዎት፣ ክቡር ፕሬዝዳንት ጊዜ ኖሯቸው ቢያስጎበኙልኝ እስኪ እነዳጋ እስጢፋኖስን ይጎብኟቸው፤ የነገሥታቱን የእነዐፄ ሱስንዮስን የእነዐፄ ዳዊትን የእነዐፄ ፋሲለደስን የእነዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን አዕፅምት ይዛ የምትገኝ፣ ባለአደራ ጥንታዊት እናት ቤተ ክርስቲያን ናት። ዛሬ ዛሬ በምሥራቁ ስንሔድ፣ በደቡቡ ስንሔድ፤ እዚህ አካባቢ ያው ጎላ በርከት ብሎ የኦርቶዶክሱ ተከታይ ስላለ ተቻችለን እንኖራለን፤ ወደ ሌላው ስንሔድ ግን ጣጣው እየበዛባት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ ፈተናው እየከበዳት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ መጀመሪያዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች ፊተኞች ይኾናሉ፤ የተባለው ቃል እየተፈጸመባት ነው።


በሥልጣን ክፍፍልም ኾነ በአካባቢው ያሉ ሥልጣን ላይ ይቀመጣሉ፣ የመንግሥት ሓላፊነታቸውን ትተው፣ የተሰጣቸውን አደራ ረስተውና ረግጠው፣ ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ እያደረጉ ይህችን እናት አንጋፋ ቤተ ክርስቲያን በዋለችበት እንዳታድር፤ ባደረችበት እንዳትውል እንደ ጥንቱ እንደ ሮማውያን ዘመን እየኾነ ያለበትም ቦታ አለና እባክዎ ክቡርነትዎ በአስተዳደር ዘመንዎ፡- እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል ሰፍኖ፤ ይኼ በቃል፣ በቋንቋ የምንናገረው ሳይኾን ተግባራዊ በኾነ መልኩ አንተን አልይህ፣ አንተን አልይህ መባባል ቀርቶ እምነትም ከኾነ በትምህርት ላይ የተመሠረተ እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊ የኾነ ነገር እንዲሰፋ እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ


ከዚህ በተረፈ፣ ዘመንዎ ሁሉ፣ አጀማመርዎ ጥሩ ነው፤ አካሔዱን አይቶ ስንቁን ይቀሙታል፤ ይላሉ አባቶቻችን፤ በዚህ አካሔድዎ፣ እጅግ ደስ የሚልና በእያንዳንዱ አእምሮ ተቀባይነትን እያገኙ እንደሚቀጥሉ።


አባቶቻችን የሚሉት አንድ ነገር አለ፤ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ፤ ይላሉ፤ እንደ ዛሬ አየር አይቀድመውም፤ እንደ ጥንቱ ግን ፈረሰኛ አይቀድመውም፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በክፉ ከወጣ አለቀ፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በበጎ ከወጣ ደግሞ አለቀ፤ ስለዚህ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ የእርስዎና የእርስዎ የቤት ሥራ ኹኖ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋራ ኹኖ፣ የትላንትናዋ ምልዕት ኢትዮጵያ፣ ቅድስት ኢትዮጵያ፣ አንድነት የሰፈነባት፣ መለያየት የሌለባት፣ ሁሉም በሔደበት ቤት ለእንግዳ ተብሎ የሚያልፍባት፤ አንተ እገሌ ነህ፣ አንተ እገሌ ነህ የማይባባልባት አገር ትኾን ዘንድ እግዚአብሔርን በመለመን፣ አማካሪዎችዎንም በማማከር፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ምክረ ኵይሲ እንለዋለን…ይኼ አላስፈላጊ ምክር የሚመክሩ እንደ ምክረ አሦር አሉ፤ ስለዚህ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው እስከመሩ ድረስ፣ አዎ ርግጠኛ ነኝ፤ የተናገሩላት፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን ማለት ነው፤ እንደ ጥንቱ። እግዚአብሔር ይስጥልን፤ እግዚአብሔር ይባርክልን።


ከዚህ በተረፈ፣ በመጨረሻ መቸም አንዳንድ ጊዜ የእኛ ልማድ፣ ከይቅርታ ጋራ ነው የምናገረው፣ አዲስ ባለሥልጣን መጣ ሲባል፣ እንግዳ መጣ ሲባል፣ ስሜታችንን መናገር የተለመደ ጠባያችን ስለኾነ ይቅርታ እየጠየቅሁኝ፣ እንደ እኛ እንደ እኛ እንደ ባሕር ዳር፣ ያለአድልዎ፣ በሚገባ፣ እኔም በማውቀው እኔም አንድ ጠያቂና ተመላላሽ ስለኾንኩ፣ የሚያስተናግዱንን ክቡር ከንቲባችንንም ኾነ ክቡር ፕሬዝዳንቱን፣ አጠቃላይ መሥሪያ ቤቱን ሳላመሰግን ባልፍ ኅሊናዬ ስለሚወቅሰኝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እላለሁ፤ በጣም አመሰግናለሁ።
ምንጭ፡- ሀራ ተዋህዶ¾

ክፍል የኔ ሃሳብ

“የኢህአዴግ የፖለቲካ ማዕከል ህወሓት መሆኑ

ከቀረ ቆይቷል”

ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት

የቀድሞ አየር ኃይል አዛዥ

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቀድሞ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለኃይማኖት በ1993 ዓ.ም ከመንግስት የስራ ኃላፊነት ከተለዩ በኋላ በመምህርነት አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። እኒህ የቀድሞ ታጋይ በተለያዩ ጊዜያት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው ማብራሪያ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን ሃሳባቸውን ወደ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በህትመት ሚዲያው በኩል ለህዝብ በማድረስ ተጠቃሽ ናቸው። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመመረቂያ ጥናታዊ ጽሁፍ የባህር በር ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗ ከሚያስቆጫቸው ኢትጵያዊያን መካከል አንዱ ናቸው። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ሊኖር ስለሚችለው ግንኙነት፣ ስለ ዶክተር አብይ አሕመድ ካቢኔ፣ ስለ ህወሓት እና የተለያዩ ጉዳዮች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል እነሆ!!

ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳይ እንጀምረው። በኢትዮጵያ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ከሂደቱ ጀምሮ እስከ ርክክቡ እንዴት አዩት?

ጄኔራል አበበ፡- ኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋት ነበር። አጠቃላይ የነበረው የሰላም ማጣት ሁኔታ ለውጥ፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን እና የህግ የበላይነት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው። ተፈጥሮ የነበረው ሁኔታ ጸረ ዴሞክራሲ የተስፋፋበት፣ የህግ የበላይነት የማይከበርበት፣ ፍትህ የታጣበት ስለነበር ለውጥ ያስፈልግ ነበር። ለውጡ ከየት ይምጣ እና በማን ይነሳ የሚለው ነገር የአገሪቱ ሁኔታ እና ታሪካዊ ሁኔታ ይወስነዋል። በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ አንመራም እያሉ ቢሆንም በዋናነት የተነሳው ግን ኦሮሚያ አካባቢ ነው። በመሰረታዊነት የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የኦሮሞ ወጣት አጠቃላይ ያደረገው እንቅስቃሴ አልገዛም ባይነት ያሳየበት ሁኔታ ነበር፤ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ። በእርግጥ እዚህ ላይ አንዳንድ ወንጀለኞች ከለውጡ ጋር ተደባልቀው ብሔር ተኮር ጥቃት የታየበት፣ ንብረት የወደመበትና በአጠቃላይ ብዙ ጥፋት የተፈጸመበት ቢሆንም በዋናነት ግን የኦሮሞ ወጣት እንቅስቃሴ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ለውጥ ያስፈልግ ስለነበርና የለውጡ ማዕከል ደግሞ ኦሮሚያ በመሆኑ የለውጥ መሪ ከየት ይመጣል የሚለውን ብዙ ጥያቄ እናነሳ ለነበረው ጥያቄ መሪዎች ከኦሮሚያ እየመጡ መሆኑን ማየት ጀመርን። የለማ ቡድን የምንለው መምጣት ጀመረ። ከዚያም ምናልባት ኢትዮጵያን የሚያድናት እና መምራት የሚችል ከዚህ ይመጣል ብዬ ማሰብ ስለጀመርኩ መከታተል ጀመርኩ። ስለዚህ በአንድ በኩል ከነበረው የኢህአዴግ ጸረ ዴሞክራሲ ስርዓት ብዙ ንክኪ ያልነበራቸው፣ በአንጻራዊነት ጎልማሳ የምንላቸው እና የተማሩም ናቸው። ስለዚህ አሁን የሚመጣው ለውጥ ዋናዎቹ መሪዎች ከኦህዴድ ይመጣል ብዬ ሳነሳ ነበር። አሁን ሲታይም የለውጡ መሪዎች እነሱ ናቸው የሆኑት።

ህወሓት እና ብአዴን በነበሩበት ላይ ነው የቆሙት። እነሱ ግን (ኦህዴድ) ተቀይረው ፌዴራሊዝምን እና ኢትጵያዊነትን አንድ ላይ አድርገው የኢትዮጵያ አንድነትን አጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስለዚህ በተለይ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ሲጀመር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያየ መንገድ የምርጫ ቅስቀሳውን ስራ (Campaign) በደንብ ሰርተውታል። ይህ ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዛ መሆን አለበት። እኔም ጓደኞቼም በእነሱ ላይ (የለማ ቡድን) ተስፋ ስናደርግ ነበር። እሳቸው በመመረጣቸውም በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ተገቢም ነው ብዬ አምናለሁ። በእሳቸው መመረጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረናል። በኢትዮጵያ ሁኔታ የሰላም አየር ከለውጥ ውጭ ሊሆን አይችልም።

ሁለተኛ በፓርቲያቸው ግምገማ የነበራቸው ጥንካሬ ለወጣቱም ትልቅ አርአያ ነው የሚሆኑት። ከሁሉም በላይ የኢህአዴግ ዋና በሽታ የሆነውን አግላይነት ሁሉን አቀፍ በሆነ አስተሳሰብ እየቀየሩት ነው። በተለይ ከተመረጡ በኋላ ያደረጓቸው ንግግሮች (ጎንደር እና ባህር ዳር ላይ ተገኝተው ንግግር ከማድረጋቸው በፊት የተደረገ ቃለ ምልልስ ነው) ድሃውን፣ ሴቶችን፣ ወጣቱን ማዕከል የሚደርግ እና የለውጥ አቅጣጫ የሚያሳይ ንግግር ነበር ሲያደርጉ የነበሩት። እንዳጋጣሚ ይህ መጽሐፍ የእሳቸው ነው (ለሁለተኛ ጊዜ እያነበቡት የነበረውን እርካብና መንበር መጽሐፍ እያመለከቱ) አሁን በቴሌቪዥን የሚናገሩት እዚህ መጽሃፋ ላይ ያለውን ነው። ስለዚህ የሚናገሩት ድንገት የመጣላቸውን ሳይሆን ያሰቡበትን እና የራሳቸውን አስተያየት ይዘው ይህችን አገር ለመለወጥ የመጡ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይም ሆኑ አጠቃላይ የለማ ቡድንሚባለው ቡድን እናንተ አዲስ አበባን ስትይዙ ገና ታዳጊ የነበሩ ልጆች ናቸው። እድገታቸው በኢህአዴግ ቤት ውስጥ በመሆኑና የኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና የውስጥ ግምገማ አልፈው ሂስና ግለሂስ እያወረዱ የመጡ ስለሆነ ከእነዚህ ሰዎች ለውጥ መጠበቅ የዋህነት ነው ሲሉ የሚናገሩ አሉ። እርሰዎ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- ጥያቄው ተገቢ ነው። ኢህአዴግን የምንቃወምበት ምክንያት ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ስላላዳረገ እና ጸረ ዴሞክራሲያዊ አየር በመፍጠሩ ነው። የለማ ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ ህገ መንግስቱን የማክበር፣ ፌዴራሊዝሙን የማክበር ነገር እና ኢትየጵያዊነትን የማክበር ነገር ነበራቸው። ስለዚህ ከኢህአዴግ ውስጥ አዲስ ኃይል እየተፈጠረ ነው፤ ሊፈጠርም ይችላል። በሌሎች አገሮችም የሚታዩት እንኳን እንደ ኢህአዴግ ከፊል ዴሞክራሲያዊ የሆነ ድርጅት ጭፍን የሆነ ጸረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ገዥ መደቦች ውስጥም ቢሆን ከእነሱ የሚወጣ ለውጥ ፈላጊ ሊኖር ይችላል። የኢህአዴግ ፕሮግራም ከሞላ ጎደል ዴሞክራሲያዊ ነው። እነሱም ህገ መንግስቱን አክብረው ፌዴራሊዝሙ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ አለበት ብለው ነው የተነሱት። በዚህ ሌሎቹም የኢህአዴግ ድርጅቶች ለውጥ ያስፈልጋል የሚለውን የተሟላ ነገር ሳይዙ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ነው የመጡት። የምርጫ ሂደቱን ስታየው ራሱ የኢህአዴግን ኋላቀር የሆነ ነገር በጣጥሰው ነው የመጡት። ለምሳሌ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለያየ መንገድ ብዙ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ራሳቸውም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ሌሎች ሊያደርጉት ይችላሉ ዶክተር አብይ እንዲመረጡ በተለይ ሶሻል ሚዲያውን ተጠቅመውበታል።

የኢህአዴግ አመራረጥ ግን ፊውዳል አትለው ምን አትለው በጣም ኋላ ቀር ሲሆን እሳቸው ግን ይህን እየበጣጠሱ ነው እዚህ የደረሱት። ከተመረጡም በኋላ ቢሆን የተለየ ራዕይ እና አስተሳሰብ ያላቸው መሆናቸውን ነው ያሳዩት። በእርግጥ በተግባር ብዙ የሚታይ ነገር ይኖረዋል። እስካሁን ያለው አቅጣጫ ግን የሚያስደስትና እኛም ሁላችንም ደግፈን ለውጡን ማቀላጠፍ ያለብን ይመስለኛል።  

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ህወሓት በነበረበት ቆሟል ብለዋል። ፓርቲውም ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሰዎች ታጋዮች ናቸው። ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ከዚህ በተለየ መንገድ ነው የሚጓዙት። ይህን በማንሳትም ፖለቲከኞች ህወሓት መውለድ አይችልም (ተተኪ አያፈራም) ሲሉ ይናገራሉ። ህወሓት ለውጥ ያላመጣበት ችግሩ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

ጄኔራል አበበ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው ህወሓት በ1993 ዓ.ም ቆስሎ ነበር። አሁን ያ ቁስል አመርቅዞ የማይድን ቁስል (ጋንግሪን) ሆኗል። ህወሓት ድሮ መማር የሚወድና በመማር የሚያምን ድርጅት ነበር፤ አሁን ግን እንደዛ አይደለም። ስልጣን የተጠሙ ሰዎች የተሰባሰቡበት ስለሆነ የተማረውን ወጣት ክፍል እንዳይቀላቀላቸው የመከልከልና የማራቅ ስራ ይሰራሉ። ምክንያቱም የተማረው ወጣት ወደእነሱ ከገባ ይገዳደርና የእነሱንም ቦታ ይነጥቃል። የህወሓትን ስራ አስፈጻሚ ስትመለከት ከሁለት አባላት በስተቀር ሁሉም ታጋዮች መሆናቸው ይህን ይነግርሃል።

አሁን በአንድ በኩል የእነ ዶክተር ደብረጽዮን የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድንን ከእነ ለማ ቡድን ጋር ታነጻጽራለህ። እነ ለማ አሸንፈው ሲወጡ እነዚህ (ህወሓቶችን) መስራች ነን በሚሉ ሰዎች ታፍነዋል አልወጡም። ስለዚህ ህወሓት ጋንግሪን ያለው ነገር ነው። ጋንግሪን ደግሞ ወይ ተቆርጦ ይወጣና የለውጥ ሀይል ይሆናል አለዚያ ደግሞ ጋንግሪኑ ሌላውን እየበላ የሚሞት ድርጅት ነው ህወሓት።

ሰንደቅ፡- ህወሓት 17 ዓመት በትግል እና 27 ዓመት በስልጣን ላይ ተቀምጦ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት የሚለውን ስሙን አለመቀየሩን በተመለከተ አሁንም ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ድርጅት ነው። እናንተስ ከድርጅቱ የለቀቃችሁ የቀድሞ ታጋዮች በዚህ ዙሪያ የታዘባችሁት ነገር አለ? የስያሜውን ተገቢነት በተመለከተ እርስዎን ጨምሮ አንጋፋ ምሁራንና ታጋዮች ምን ትላላችሁ?

ጄኔራል አበበ፡- ነጻነት ማለት መገንጠል ማለት አይደለም (Liberation is not Independent)። ከብዙ ጭቆና እና ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ነጻ መውጣት ማለት ነው። ስለዚህ ስሙን መቀየሩም ሆነ በስሙ መቀጠሉ የሚለው ጉዳይ ብዙም ለውጥ የለውም። በእርግጥ እስካሁን በዚህ ዙሪያ ውይይትም ሆነ ጥያቄ ገጥሞኝ አያወቅም። ነጻ አውጭ ማለት መገንጠል ሊመስል ይችላል እንጂ ዋናው ፍሬ ነገር (Essence) ግን ገና ሲጀመር ለመገንጠል ሳይሆን እንደነገርኩህ ከሁሉም ጭቆና እና ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ትግራይንም ኢትዮጵያንም ነጻ ለማውጣት ነው።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዙ በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ካደረጉት ንግግር መካከል ‹‹በርካታ የለውጥ አጋጣሚዎችን አግኝተን በወጉ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል›› ብለው ነበር። ብዙ ሰዎች በተለይ በኢህአዴግ ጊዜ ከተፈጠሩ አጋጣሚዎች መካከል የ1983 ዓ.ም ለውጥ፣ የ1993፣ የ1997 ምርጫ ወዘተ… እያሉ ይቀጥላሉ። በእርስዎ እይታ እነዛ መልካም አጋጣሚዎች የተባሉት የትኞቹ ናቸው?

ጄኔራል አበበ፡- ከኤርትራ ጦርነት በኋላ አንድ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ለጦርነት ተንቀሳቅሷል። ለጦርነት እየተንቀሳቀሰን ህዝብ ለዴሞክራሲ እና ለልማት አስተባብሮ ለማነሳሳት በጣም የተመቻቸ ነበር። ስለዚህ ለአገሩ ፍቅር መስዋዕት በመክፈል ያረጋገጠን ህዝብ እንደነገርኩህ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት የተዘጋጀ ህዝብ ነበር። ነገር ግን ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የውስጥ ቀውስ ይህን ሁኔታ በሚገባ ሳንጠቀምበት ቀርተናል። ያ አንድ ዕድል ነበር። በ1993 ዓ.ም የተፈጠረው የፖለቲካ ቅራኔ በሰላማዊ መንገድ ቢፈታ ኖሮ አንድ እርምጃ ወደፊት ይወስደን ነበር።

1997 ዓ.ም ምርጫን እኔ የምገልጸው ወርቃማ (Golden Period) ጊዜ ነበር በማለት ነው። ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ድል ቢቀበል እና ተቃዋሚዎችም ያገኙትን ድል ተቀብለው ፓርላማ ቢገቡ ኖሮ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴያችን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ይሸጋገር ነበር። ከምርጫው በፊት ይካሄዱ የነበሩ ክርክሮች ዴሞክራሲያችንን ወዴት ሊያመራ እንደሚችል እና ሊያብብ እንደሚችል ያሳየ ነበር። ነገር ግን መንግስትም ተደናገጠ ኢህአዴግ ተደናገጠ። ኢህአዴግ ያስብ የነበረው ለፖለቲካ ፍጆታው ያለምንም እንከን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ አደረኩ ለማለት ነበር። ስላልተዘጋጀበት አላወቀበትም። ያ ዕድልም አመለጠን።

ከአስር ዓመት በኋላ ደግሞ ሌላ ምርጫ መጣ። መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል አደገኛ መሆኑን መረዳት ያልቻለ ድርጅት ነው። ግን ደግሞ መቶ በመቶ መረጠኝ የሚለው ህዝብ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ተነሳበት። ስለዚህ 1993፣ 1997 እና 2007 የነበሩ እድሎች አመለጡን ብዬ ነው የማምነው። ግን አሁንም ይህችን አገር ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ዕድል ከፊታችን አለ። ይህን ዕድል እንጠቀምበታለን ወይስ አሁንም እንደ ቀደሙት ሁሉ እናበላሸዋለን? የሚለው ነገር ነው ዋናው ቁም ነገር። አጀማመሩ ጥሩ ነው ተስፋ አለው። እስከምን ድረስ ይሄዳል የሚለውን ግን እያየን መሄድ አለብን። ግን የማይካደው ነገር አንድ ጥሩ ነገር ተፈጥሯል እሱም ዴሞክራሲያዊ አካባቢ መፍጠር የሚያስችል ነገር ነው የተፈጠረው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጸረ ዴሞክራያዊ በሆነ አገዛዝ አንገዛም ብሏል። ስለዚህ አመራሩ ጥሩ ከመራ ወደፊት እንራመዳለን። ያ ከሆነ ከልማቱም ከጸጥታውም ከሰላሙም ተጠቃሚ እንሆናለን።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ሌላው ትኩረት ሳቢ ንግግር ያደረጉት አገራዊ እርቅ እና መግባባት ያስፈልገናል የሚለው ነው። ኢትዮጵያ ሰፊ ምድር እና ብዙ ብሔር ብሔረሰብ ያላት አገር ስትሆን በመካከላችን ግጭቶች መስፈናቸው ታይቷል። የአንድ ብሔር በተለይም የትግራይ የበላይነት አለ ሌሎቹ ተጨቁነዋልም ይባላል። ለመሆኑ ይህ አስተያየት እውነት ከሆነ እና ግጭቶቹም ወደከፋ ደረጃ ሳይሸጋገሩ ተቀርፈው አገሪቱ ወደነበረችበት ሰላም የምትመለሰው እንዴት ነው?

ጄኔራል አበበ፡- ለዚህ ጥያቄ ወደኋላ ተመልሰን ከ2007 ዓ.ም በፊት የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ከ1983 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት 24 ዓመታት ምንም እንኳን አንዳንድ ቦታዎች መጠነኛ ግጭቶች ቢኖርም አገሪቱ ውስጥ ግን ሰላም ነበረ። ይህ ሰላም እንዴት መጣ ብለን ስንጠይቅ በጣም ዘመናዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገ መንግስት ስላለን እና ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ማድረግ ስለጀመርን ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቋሙ፣ ሁሉም በቋንቋው መማር ጀመረ፣ በምርጫ አስተዳዳሪውን መምረጥ ጀመረ፣ ፌዴራል መንግስት እና የክልል መንግስታት ተቋቋሙ፣ እንዲሁም ፕሬሱ ተስፋፋ። እነዚህ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ከባቢ አየር መፍጠር ጀመረ። ስለዚህ ሰው ተስፋ ማድረግ ቻለ።

ከዚያ በኋላ ግን ይህ ዴሞክራሲያ ምህዳሩ እየሰፋ መሄድ ሲኖርበት እየቀጨጨ የሄደበት ሁኔታ ተፈጠረ። ስለዚህ ለሰላሙ መጥፋት እና በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፈጠር ምክንያት የሆነው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ባለመኖሩ ነው። የተሻለ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ህገ መንግስት መያዝ ስንጀምር የተሻለ ሰላም ተገኘ፤ ያ ህገ መንግስት ሲጣስ ደግሞ ችግሩ ተፈጠረ። ያን ህገ መንግስት ጥሰት የፈጠረው ደግሞ ኢህአዴግ ነው። ህዝቡ መሬቱን ሲነጠቅና ያለምንም ካሳ ሲቀማ፣ ማዳበሪያም በግድ ውሰድ የሚባልበት ሁኔታ ነበረ፣ በአጠቃላይ ብዙ ግፍ ነው ህዝቡ ውስጥ የደረሰው። ይህ በመሆኑ ደግሞ በህዝቦች መካከል ግጨትን ፈጠረ። ከዚያ በፊት እኮ አንዳንድ አካባቢ የአማራ ተወላጆችን የማፈናቀል ነገር ነበረ እንጂ በሶማሌ እና በኦሮሚያ መካከል እንደተደረገው አይነት ግጭት አልነበረም።

ለምሳሌ የትግራይ የበላይነት አለ ይባላል። ይህ ውይይት አይደረግበትም። በሚዲያ ውይይት ቢደረግበት ችግሩ ካለ ይስተካከላል ችግሩ ከሌለ ደግሞ የለም ይባላል። በእኔ እምነት የትግራይ የበላይነት የሚባል ነገር አልነበረም በዚህ ስርዓት ሊኖርም አይችልም። በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያዊነት እንዳሁኑ አድጎ አያውቅም። በደርግ ጊዜ ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ነጻ አውጭ ድርጅት ነበር። ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ቢነግርም ህዝቡ ግን ይገደል ነበር። ህዝቡ እየተገደለ ኢትዮጵያዊነትን ማሳደግ አይቻልም። አሁን ለምሳሌ ጋምቤላው ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለት የሱን ማንነት የሚያውቅ የራሱ አስተዳዳሪ አለው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት በጣም ነው ያደገው። ነገር ግን ዴሞክራሲው እየቀጨጨ ሲሄድ ኢትዮጵያዊነትን እየተፈታተነው መጣ። ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ከባቢ አየር ቢኖር ብሔር ብሔረሰቦች በመካከላቸው ልዩነት ቢኖር እንኳን ችግሩ ለዚህ ሳይደርስ በውይይት መፍታት ይቻል ነበር። እስከ 2007 ዓ.ም ያልነበረ ነገር ነው እኮ አሁን የተፈጠረው ነገር።

ሰንደቅ፡- እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ሰላም ከነበረ በአንድ ጀምበር ተነስቶ እዚህ ደረጃ ደርሶ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል እና ለበርካች ሞት እንዴት ሊበቃ ቻለ? የዞረ ድር ውጤት ነው ብለን መውሰድ አንችልም?

ጄኔራል አበበ፡- እሱ እኮ ነው ያልኩህ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየቀጨጨ ሲሄድ ህዝቡ መብቶቹ እየተረገጡ ሄዱ። ይህ የመብት ጥሰት ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ነው የበደለው ተለይቶ ተጠቃሚ የሆነ ብሔር የለም። ለምሳሌ በትግራይ ክልል ያለው አፈና እና የመብት ጥሰት ከሌላው ብሔር ይልቅ የከፋ ነው። ከሞላ ጎደል በትግራይ ክልል ያለው አገዛዝ የኤርትራ አይነት ነው ማለት ይቻላል። እኔ ያልኩት ችግሩ 2007 ዓ.ም መጣ ሳይሆን የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ ሲሄድ ሰው ስጋት ውስጥ ገባ እና በ2007 ዓ.ም ችግሩ ፈነዳ። አሁን ያለው ችግር እየመጣ መሆኑን የገዥው ፓርቲ ሰዎች እየተነገራቸው ቀለል አድርገው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ብለው ሊያልፉት ፈለጉ። በ2009 ዓ.ም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ አዋጁን ሊሰሩበት ሲገባ ተደበቁበት።

ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ መሰረታዊ ችግሩ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እጥረት ስላለ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከብዙ ሺህ እና መቶ ዓመታት አብሮ የኖረ ህዝብ ችግሮች እንኳን ቢኖሩበት በውይይት ችግሮቹን በመፍታት እንደቀደመው አብሮ ይኖር ነበር። ለምሳሌ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል የተፈጠረው ችግር እዛ አካባቢ ያሉ መሪዎች በሙስና የተዘፈቁ ስለሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉት ሰላም እንዳይኖር ነው የሚፈልጉት። ምክንያቱም ሰላም ካለ የእነሱ ሙስና እና ወንጀል ይጋለጥባቸዋል። ይህ ደግሞ የመንግስት ችግር በተለይ ህገ መንግስቱ ላይ ኢህአዴግ ስላመጸ ህገ መንግሰቱን ስላላስከበረው እንጂ ህዝቡ በሰላም አብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊትም ሆነ ከዚያ በፊት የአማራ ተወላጆች ከኦሮሚያ እና ሌሎች አካባቢዎች ሲፈናቀሉ ምንም አልተደረገም። ችግሩን ማነው ያጠፋው ለምን አጠፋው? ተብሎ በህገ መንስቱ መሰረት ማጣራትና ምርመራ አልተደረገም። ዝም ብሎ እነዚህ ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ ናቸው ወዘተ ተብሎ በዝምታ ታለፈ፡ ያ ችግር ዝም ሲባል አሁን ከደረሰበት ደረጃ ደረሰ።

ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ጥሩ መስመር እንዲመጣ ለኤርትራው መንግስት ዶክተር አብይ በአደባባይ ጥሪ አቅርበዋል። በኤርትራ በኩል ደግሞ የሚነሳው ቅሬታ ‹‹መጀመሪያ ኢትዮጵያ በወረራ የያዘችብንን ባድሜን ትመልስልን›› የሚል ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ከሁለት ወራት በፊት ተናግረው ነበር። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንደተሳተፈ የጦር አዛዥ በባድሜ እና በአሰብ ጉዳይ ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ይስጡን እስቲ፤

ጄኔራል አበበ፡- ፕሬዝደንት ኢሳያስ እንኳን የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝቦች ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግ ቀርቶ ኤርትራዊያንንም ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ ነው በጭቆና ስር እና ሙሉ በሙሉ በፖሊስ አስተዳደር ነው እየገዟት ያለው። ስለዚህ ለሁለቱ ህዝቦች መገናኘት የሰላም አምባሳደር ሊሆኑ አይችሉም። ነገር ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ዘንባባ ይዘው መምጣታቸው ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ኢሳያስን ብቻ አይደለም የምናየው፤ የኤርትራ ህዝብን ነው። ስለዚህ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በሰላም ከመጡ ጥሩ ካልመጡ ደግሞ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ጥሩ ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ ጥሩ ይመስለኛል።

የባድመም ሆነ የአሰብ ጉዳዮች ቁጭ ብሎ በውይይት መፈታት ይኖርበታል። ቀደም ብሎ የተፈረደው ፍርድ አለ ያን ፍርድ የሚተገበርበትን መንገድ በራሱ መወያየት ያስፈልጋል። ነገሩ ግን ከዚያ በላይ ነው። በተለይ ትግራይ እና አፋር አካባቢ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሰላምም ጦርነትም የሌለበት መሆን ህዝቡን ብዙ ጎድቷል። ምክንያቱም በአካባቢው ኢንቨስትመንት ማካሄድ ያስቸግራል፤ ገበሬዎቹም በየቀኑ ዘብ መውጣት አለባቸው፤ ስለዚህ ያ ነገር መፈታት አለበት። ችግሩ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰዷ ጥሩ ነው። ነገር ግን እዛ በሰላም የማይኖር ህዝብ አለ። ስለዚህ በአጭር ጊዜ ከኤርትራ መንግስት የምንጠብቀው ምላሽ ‹እምቢ›› ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ዶክተር ያዕቆብ ኃለማሪያም “አሰብ የማናት?” በሚለው መጽሃፋቸው ዓለም አቀፍ ህጎችን ተጠቅመን የባህር በር ሊኖረን የሚያስችል መብት አለን ሲሉ ጽፈው ነበር። በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ግንኙነት ሲፈጠር ወደቡን የመጠቀም እድል ለኢትዮጵያ መብት ይሰጣል ወይስ ቀድሞም ወደቡ ለኢትዮጵያ ይገባት ነበር ብለው ነው የሚያምኑት?

ጄኔራል አበበ፡- የማስትሬት ዲግሪ መመረቂያ የጥናት ጽሁፍ የሰራሁት “Ethiopian Soveriegn Right Access to the Sea” በሚል ርዕስ ነበር። መጀመሪያ በዚህ ርዕስ ለማጥናት ከመጀመሬ በፊት በፖለቲካ የማምንበት የነበረው አሰብ የኤርትራ ነው ስለዚህ እኛ ኤርትራን መውረር የለብንም የሚል እምነት ነበረ፣ ስልጣን ላይ እያለሁ። የማስትሬት ትምህርቴን ስጀምር ግን “የባህር በር አልባ ሆነን ምንድን ነው መብታችን?” የሚለውን ለማወቅ ነበር ጥናቱን የጀመርኩት። ምክንያቱም በጦርነቱ ጊዜ ከአሰብ ወደ ጅቡቲ ስንዞር ብዙ ንብረት ነበር የወሰዱብን። እንዲሁም ብዙ ውጣ ውረድ ስለነበረ በጣም ነበር የተናደድኩት። የባህር በር ባይኖረንም መብት አይኖረንም ወይ የሚል ነበር ህግ ትምህርት ቤት ያጠናሁት።

መጀመሪያ የባህር በር ባይኖረንም የምናገኘው መብት ምንድን ነው? የሚለውን ርዕስ እየቆየሁ በሂደት ርዕሱን ቀየርኩትና የባህር በር የማግኘት መብት (Access to the Sea) ቀየርኩት። ዓለም አቀፉ ህግም ይፈቅድልናል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፌዴሬሽን በነበሩበት ወቅት የነበረው ውሳኔ (ያ ውሳኔ) ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ስትቀላቀል አንደኛውና ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዲኖራት የሚያደርግ ነው። ኤርትራ ስትገነጠልም ያ መብት ለኢትዮጵያ ይቀርላታል ማለት ነው። ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መብቷ የማይገረሰስ (Sovereign Right) ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ህግ ሳናጠና እና እውቀቱ ያለው ሰውም ሳናማክር አስቀድመን በነበረው ፖለቲካ ነው የወሰነው።

ሰንደቅ፡- እዚህ ላይ ግን ዓለም አቀፍ ህጉን ሳናጠና ወይም ባለሙያ እንዲያማክረን ሳናደርግ በፖለቲካ አቋም ብቻ ነው የወሰነው ይበሉን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ምሁራን (ዶክተር ያዕቆብን ጨምሮ) በወቅቱ ለአቶ መለስም ሆነ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ለነበሩት ኮፊ አናን ውሳኔው ኢትዮጵያን ተጎጂ እንዳያደርጋት ደብዳቤ በመጻፍ ጭምር ጠይቀው ነበር። በወቅቱ አቶ መለስም የአሰብን ወደብ የሻዕቢያ መንግስት ‹‹ግመል ያጠጣበት›› ብለው እስከመመለስ ደርሰው ነበር በፓርላማ። አሁን ደግሞ እርስዎ ባለማወቅ የተወሰነ መሆኑን እየነገሩን ነው። በትክክል ግን ባለማወቅ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ጄኔራል አበበ፡- በጥናቴ ላይ የተረዳሁት ሁለት ነገሮች ድንቁርና ወይም አለማወቅ እና እብሪት (Ignorance and arrogance) መደባለቃቸውን ነው። አሸናፊ ስትሆን ሁሉንም ነገር የምታውቅ ይመስልሃል ሳታውቀው። አቶ መለስም ቢሆን የኢትዮጵያን መብት አሳልፈው ለመስጠት ፈልገው አይደለም እኔም አመለካከቴ እንደዛ ነው። የኤርትራ ከሆነ እና ኤርትራ የምትባል አገር ካለች የሌላ አገር መሬት መውሰድ የለብንም የሚል አቋም ነው የነበረኝ። ግን ዓለም አቀፍ ህግ ሁላችንም አናውቅም። እስኪ አጥኑ እና የጥናታችሁን ውጤት አምጡ የሚል የለም። ‹‹አሰብ የእኛ ናት›› የሚሉ በሙሉ የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ጦርነት ናፋቂ ናቸው ብለን ከመጀመሪያው ነው የደመደምነው። እብሪት ያልኩህ እሱ ነው። ጥናቴ ላይ የጻፍኩትም ድንቁርና እና እብሪት ተደባልቋል የሚል ነው።

ሰንደቅ፡- ከኤርትራ መገንጠል ጋር ተያይዞ የአሰብ ወደብን ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠ ውሳኔ በመወሰኑ ወደቡን ለኢትዮጵያ በጎ የማያስቡ አገራት በቁጥጥር ስር አውለውታል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አደጋ አለው ሲሉ ፖለቲከኞች ይናገራሉ። እውን አደጋው ምን ያህል ያሰጋል? መፍትሔውስ ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- አሁን አደጋው የባህር በር አልባ (Land locked) መሆናችን ብቻ አይደለም፤ ችግሩ ከዚያ በላይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ አንድ ያጠናሁት ጥናት ነበረ። ብሔራዊ የደህንነት ፖሊሲ ላይ የሚጠና አንድም ተቋም የለንም። መከላከያ የራሱን ያጠናል ያም የራሱን ያጠናል። አጠቃላይ አገሪቱን የሚመለከት የደህንነት ፖሊሲ አጥንቶ ስትራቴጂ ተቀርጾ በእሱ የምንሄድበት ሁኔታ የለም። ተቋም አለመኖሩ ነው ትልቁ ስጋት። ኤርትራ ውስጥ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ቡድን ማስቀመጥ አልነበረብንም። እኔ በኤርትራ ነጻነት አምናለሁ፤ ምክንያቱም ህዝቡ ፈልጎታል፤ መብታቸውን ማክበር አለብን። ግን የእኛ መብት ደግሞ መረጋገጥ አለበት። በኤርትራ ያለው ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ነው። እኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦታ ብሆን በኤርትራ ያለው ነገር እንዲቀጥል አልፈቅድለትም፤ የራሳቸውን ስራ ይስሩ በእኛ ጉዳይ ግን ጣልቃ እንዲገቡ አልፈልግም፤ በየጊዜው ሰው እየላኩ የማተራመስ ስራ አልፈቅድላቸውም። አሁን ችግሩ በኤርትራ ያለው በተግባር ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ኃይል ዝም ብለነዋል። በዚህ ደግሞ ዋናው ስጋት ኤርትራ ሳትሆን የባህር በር የሌለን መሆኑን ተከትሎ ኤርትራ ውስጥ የጦር እንቅስቃሴ ይታያል፤ የግብጽም የገልፍ አገራትም። ኤርትራ የምትባለው አገር ሰላማዊ ሆና እስከቀጠለች ድረስ የባህር በር የማግኘት መብታችንን እንጠይቃለን። በህጋዊ መንገድ ማግኘት ይኖርብናል። ግን ህግ ደግሞ ሁልጊዜ ከኃይል ውጭ በህግ የሚባል ነገር የለም። በዓለም አቀፍ ህግ ኃይል እና ህግ ተሳስረው ነው የሚታዩት። ስለዚህ ያን መብታችንን ማረጋገጥ አለብን።

የአትዮጵያ መንግስት ደግሞ በኤርትራ በኩልም ሆነ በደቡብ ሱዳን የተቀናጀ ስትራቴጂ እና ፖሊሲ ያለው አይመስለኝም። አካባቢያችንን በደንብ አውቀን ደህንነታችንን የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማውጣት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የሚችል ተቋም የሌለን መሆኑ ደግሞ ትልቁ ፈተና ነው።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተ ፖሊሲ እየቀረጸ መሆኑን ከዓመታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር። እስካሁን ግን የፖሊሲው ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተገለጸ ነገር የለም። እርስዎን ጨምሮ በርካታ ምሁራን እና ፖለቲከኞች የኤርትራ ጉዳይ ለኢትዮጵያ በጣም አሳሳቢ እና አስጊ መሆኑን እየገለጻችሁ ነው። በዚህ ሁኔታ የፖሊሲው ጉዳይ መዘግየቱን እንዴት ያዩታል?

ጄኔራል አበበ፡- በ1994 ዓ.ም የወጣ የውጭ ጉዳይ እና ግንኙነት ፖሊሲ አለ። ያ ፖሊሲ ከሞላ ጎደል ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉት። ግን ደግሞ ብዙ ችግሮችም አሉበት። አሁን ያለነው 2010 ዓ.ም ነው፤ ፖሊሲው ከወጣ 16 ዓመቱ ነው፤ እስካሁንም አልተሻሻለም። ሌላው ፖሊሲው ሲቀረጽ ባለሙያዎች የሰሩት ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ እና በአካባቢው ያሉ የተወሰኑ ሰዎችን ሰብስቦ ያደረገውን ጨዋታ ነው ፖሊሲ አወጣን የሚሉት። በመጀመሪያ ደረጃ የአገር ፖሊሲ ሲወጣ በመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ፓርላማው ቢሆንም ሁሉን አሳታፊ የሆነ ለምሳሌ ምሁራንን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና ራሱ ኢህአዴግ ያሉበት ሆኖ የሁሉም ድምጽ ሊሰማ ይገባዋል። ያም ሆኖ እየተቀረጸ ነው የተባለውም አጀማመሩ ጥሩ ስላልሆነ አሁን የት እንደገባም አይታወቅም።

ሰንደቅ፡- ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖሊሲ ረቂቅ መዘጋጀት አለበት የሚለውን በርካቶች የሚስማሙበት ነጥብ ነው። ነገር ግን ‹‹ኢህአዴግ በተለይም የኢህአዴግ አስኳል የሆነው ህወሓት በባህሪው አግላይነት የተጠናወተው ስለሆነ አብሮ መስራት አይታሰብም›› ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

ጄኔራል አበበ፡- በመሰረታዊነት አግላይ ባህሪ የህወሓት ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ባህሪ ነው። አሁን ግን አዲስ አመራር ከኦህዴድ እየመጣ ነው፤ ተስፋ እየጣልንበትም ነው። ይህ አመራር ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች እያነጋገረ እና ቃል የሚገቡትን ነገሮች እየፈጸመ ከሄደ ህወሓት የግድ ይቀየራል። ህወሓት የኢህአዴግ አስኳል መሆኑን ካቋረጠ ቆየ እኮ። ተቃዋሚውም ሆነ ራሱ ህወሓት አልገባቸውም እንጂ የኢህአዴግ የፖለቲካ ማዕከል ህወሓት መሆኑ ከቀረ ቆይቷል። ህወሓት እንደ ድርጅት ጠንካራ መሆኑን ካጣ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ደጋግሜ በትግርኛ የምጽፈውም ህወሓት እየሞተ መሆኑን ነው።

ሰንደቅ፡- የህወሓት መዳከምም ሆነ እየሞተ መሄድ የጀመረው እናንተ ከወጣችሁ በኋላ ነው ወይስ አቶ መለስ ካለፉ በኋላ?

ጄኔራል አበበ፡- እኛ ስንወጣም ትንሽ ችግር ነበረው። በእርግጥ እኛ ከዛ ፖለቲካ ውስጥ አልነበርንም (እሳቸውና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ በጡረታ የተገለሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ነበሩ)። ዋናው ግን እሱ ሳይሆን ከዛ በኋላ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ከባቢ እና ተቋማት እየተፈጠሩ አለመሆኑ ነው። አቶ መለስ ይህችን አገር ለመቀየር የተቻላቸውን ነገር አድርገዋል፤ በተለይ ከልማትና ከድህነት ቅነሳ አኳያ። ዴሞክራሲን በመገንባት በኩል ግን እየታፈነ እየታፈነ ነው የሄደው። ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ እኮ ህወሓት ጽሁፍ የሚጽፍ አንድም ሰው እንኳን የላቸውም። ህወሓት በእሳቸው ቃል ብቻ የምትኖር ድርጅት ነበረች የሚል ነገር ነበር። በእርግጥ አገሪቱም ወደዛ የመሄድ ነገር ነበረ። ስለዚህ የ1993 ዓ.ም ክፍፍሉ አንድ አስደንጋጭ ተሞክሮ (trauma) ነበር። ግን ሊታረም የሚችል ነገር ነበር። ከዛ በኋላ የተማረውን ወጣት በሙሉ አገሪቱን በመገንባቱ ሂደት ቢሳተፍ ኖሮ ተቋማት ስራቸውን ቢሰሩ ለምሳሌ አቶ መለስ በገመገሙት 1992 ዓ.ም ፓርላማው አቅመ ቢስ (Rubber Stamp) ሆኗል የሚል ነበር። በዚያ ጊዜ የነበረው ፓርላማ ጥቂትም ቢሆን ተቃዋሚዎች የነበሩበት ስለነበረ ይሻል ነበር። ከዚያ በኋላ ያሉት የፓርላማው እንቅስቃሴ (2002 እና 2007 በተደረጉ ምርጫዎች የተመሠረተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) በ1992 ዓ.ም ከነበረው የባሰበት ሆነ። ፓርቲዎችም ተቋማትም እየተዳከሙ ነው የሄዱት።

ህወሓት ብቻ ሳይሆን ብአዴንም የአማራውን የተማረ ወጣት በማደራጀት አልተጠናከረም እየተዳከመ ነው የሄደው። ኦህዴድም እንዲሁ በአንጻራዊነት ደኢህዴን ይሻሻላል። ህወሓትም ሆነ ብአዴን የተዳከሙት ከእነሱ ውስጥ ያሉት ሰዎች መጥፎ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም መተካካት አለመኖር ነው።

ሰንደቅ፡- ውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አድርገን እንጨርስ። ዶክተር አብይ ትናንት ያዋቀሩትን ካቢኔ (ቃለ ምልልሱ የተካሄደው ዐርብ ዕለት ነበር) እንዴት አዩት?

ጄኔራል አበበ፡- በጣም አስበው እና አቅደውበት እንዳደረጉት ይገባኛል። ለውጥ ለማካሄድ እንቅፋት ይሆኑብኛል ያሏቸውን አካባቢዎች ለይተው አስበው እንደሰሩት ያሳያል። በአቶ ኃይለማሪያም ጊዜ የጠፋ አንድ አደረጃጀት ነበር። የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኦፊስ የሚባል አቶ አባዱላ የተመደቡበት። እሱ መደራጀቱ ራሱ በጣም ጠቃሚ ነው። ግን ደግሞ ከጠበኩት በታች ሆኖ ነው ያገኘሁት። በተለይ ተፎካካሪነትን በሚመለከት ወደ ፖለቲካ ታማኝነትና የፖለቲካ አጋርነት ያዘነበለ ምደባ ነው ያካሄዱት። ስለዚህ እዛ ላይ ትንሽ ቅሬታ አለኝ። ሰዎቹን ስለማውቃቸው ሳይሆን ከዚህም እዚያም የነበሩ ሰዎች ናቸው አሁንም ወደ ሌላ ስራ የተመደቡት። ለምሳሌ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ወደ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መመደብ አልገባኝም። አጠቃላይ ሲታይ ጥሩ ቢመስልም ከተፎካካሪነት አኳያ ሲታይ ክፍተት አለበት።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት ወቅት የተናገሩት “የችሎታ ክፍተት ቢኖር ለመማር ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ በመማማር መሙላት ስለሚቻል እሱን እናደርጋለን” የሚል ሀረግ ተጠቅመዋል። የአቅም ችግር እንዳለ እያመኑ ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ግለሰቡን መመደብ አሁንም ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለንም የሚሉ ምሁራን አሉ። እርስዎ ይህን እንዴት ገመገሙት?

ጄኔራል አበበ፡- የአቅም ችግር ያለበትን ሰው ከመጀመሪያው ለምን ወደ ስልጣን ማምጣት አስፈለገ? የኔ የመጀመሪያው ጥያቄም ይህ ነው። አቅም ያለው ሲባልም መቶ በመቶ ብቁ የሆነ ሰው የለም፤ ስለዚህ መደጋገፉ አይከፋም። ነገር ግን የአቅም ጉድለት ቢኖርም ብለው ሲናገሩ ግን መጀመሪያ አቅም አለው ብለው ያቀረቡት በመሆኑ ነው ጥያቄዬ። ሁሉንም ባይሆን አንዳንዶቹ አቅም እንደሌላቸው እኛም እናውቃቸዋለን። ለምሳሌ መከላከያ ሚኒስትር የተመደቡት ስለ ሴኩሪቲ ምን ያህል ያውቃሉ? ብለን እናነሳለን። ግን መማር የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በነገራችን ላይ እየተናገርኩ ያለሁት ስለ አንድ ግለሰብ አይደለም። አጠቃላይ ግን ብቃትን ማዕከል ያደረገ ሰው ይመጣል ብዬ ነበር ስጠብቅ የነበረው። በአንድ በኩል ጊዜው አጭር በመሆኑ አሁን የተዋቀረው ካቢኔ የእሳቸው ካቢኔ ሳይሆን የሽግግር ካቢኔ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ፖለቲካውን ለማረጋጋት የፖለቲካ አጋርነትን (political alliance) ፈልገው ይሆናል እንጂ ከብቃት (Compitenecy) አንጻር የዶክተር አብይ ካቢኔ ይህ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም።

ክፍል ፖለቲካ

 

ዳሸን ባንክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ላስገኙለት ደንበኞቹ ሚያዚያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው መርሃ - ግብር ዕውቅና ሰጠ።

በሥነሥርዓቱ ላይ 168 የንግድ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ለባንኩ ባስገኙት የላቀ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ዕውቅና ተችሯቸዋል።

ለባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላኪዎች፣ ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ተቀባዮች፣ በውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ ሂሳብ አንቀሳቃሾች፣ ክፍያን በዓለም አቀፍ ካርዶች የሚቀበሉ አጋር የንግድ ተቋማት ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል ይገኙበታል።

ዝግጅቱ ባንኩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳሰቡበት ሆኗል።

የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለሆኑ የባንኩ ደንበኞች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ብሎም ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቁርኝቱን ለማጎልበት ባንኩ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን የዳሸን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ነዋይ በየነ እንዲሁም የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ በወቅቱ አስታውቀዋል።

በዕውቅና መስጫ ስነ -ስርዓቱ ወቅት የውጪ ምንዛሬ የሚያስገኙ የዳሸን ባንክ ደንበኞችን ተጠቃሚ ስለሚያደርጉ የብድር አቅርቦቶች በባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ገለፃ ተደርጓል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የባንክ ኃላፊዎች፣ ኤክስፖርተሮች፣ በሆቴልና ሱፐርማርኬት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች እንዲሁም የንግድ ዘርፍ አመራሮች በመርሃ - ግብሩ ታድመዋል።

እ.ኤ.አ. በ2016/17 የበጀት ዓለም ዳሸን ባንክ ከ530 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ሊያገኝ ችሏል። ባንኩ በ70 ሀገራት ውስጥ በሚገኙ ከ170 በላይ ከተሞች ከሚገኙ 461 ባንኮች ጋር ትስስር ፈጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል።

ክፍል ወቅታዊ

ጌታቸው አስፋው

 

(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

 

በገበያ የቀረበው የገንዘብ መጠን በገበያ ዋጋ ካልተለካው ምርት ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ በዋጋ ግሽበት የሰደድ እሳት ተቃጠልን፣ በሸቀጥ ዋጋ ጭቅጭቅና ንትርክ ውስጥ ገባን፣ ዋጋዎች በቀናትና በሳምንታት ተለዋወጡብን። ገቢ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ስለሆነ ገንዘቡ ዋጋ አጣ። ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት ተተክቶ ምርታማነትን ቀነሰ። በጥቃቅን የተደራጁት ወጣቶች በሙሉ አቅማቸው ሳይሰሩ በነርሱ ላይ ሌሎች ማደራጀት የቀድሞዎቹንም አዲሶቹንም በሙሉ አቅማቸው ሠርተው ምርታማ እንዳይሆኑ አደረጋቸው።


ሥራ ፈጠራ በብሎኬት ምርት፣ መስኮትና በር መግጠም፣ አልባሳት፣ ቦርሳና ቀበቶን የመሳሰሉ የግል መጠቀሚያዎችን ማምረት ጀምሮ አሁን ወደ ጀበና ቡና፣ ቦርዴ (ሻሜታ) ጠመቃ፣ የዐረብ ሱቅ፣ በቆርቆሮ ግድግዳ ደሳሳ ጎጆ የሆቴል ኪዎስክ ወርዷል። ከዚህ በታች ወዴት እንደሚወርድ አይታወቅም። በየመንገድ ዳሩ ጠላ ጠምቆ መሸጥ ይሆናል። አምርቶ ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ አጭበርብሮም ቀምቶም ሰርቆም የሰው አካልን ደልሎም ገንዘብ ለማግኘት ይሞከራል። በውድድር ሳይሆን በሽሚያ ገንዘብ ለማግኘት ለመክበር መስገብገብ መሻማት መሻሻጥ መታወቂያችን ሆኗል። በሦስት ሺሕ ብር ሥራ ጀምሮ በዓመቱ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ፣ መቶ ሺሕ ብር ለደላላ ከፍሎ ወደሞት ለመሄድ መደራደር፣ ለደቂቃዎች መዝናኛ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት፣ ቅጥ ላጣ የውጭ አገር ጉዞ የቅንጦት ወጪ ማድረግ፣ ጥሬ ገንዘብ ከጓሮ የሚሸመጠጥ ቅጠል አስመስሏል። በየቴሌቪዥኑ መዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢዎች ለእንግዶቻቸው የሃያ ሺሕ ብር ሐምሳ ሺሕ ብር የቀን ውሎ ጉርሻ ሲሰጡ ታይቷል። በ1960ዎቹ ቦሌ አስፋልት ዳር የነበረ ዘመናዊ ቪላ ቤት በአምስት ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር የሚያውቅ ሰው ይኽን ሁሉ ጉድ ሲያይ ምን ይል ይሆን?


አምና በመቶ ብር መነሻ ካፒታል የከተማ ሥራ ጀምሬ ዘንድሮ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ በግማሽ ሔክታር መሬት የግብርና ሥራ ዐሥር ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የወጣቱን ሥነ ልቦና ሰለበ፤ የሥራ ባህል ጠፋ፤ ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ ሳይሆን ከሜዳ የሚታፈስ፣ ጓሮ ከበቀለ ዛፍ የሚሸመጠጥ መሰለ፤ መቶ ሺሕ በትኖ ሚልዮን ለማፈስ የተሰናዳ ትውልድ ተፈጠረ፤ ከሠርቶ በሌው አውርቶ በሌውና ዘሎ በሌው በዛ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አቋርጦ ጊታር ማንሳት ተለመደ።


ግማሽ ያህሉን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በያዘው የአገልግሎት ምርት መሰማራት የሕዝቡን ገቢ ከምርታማነቱ በላይ በፍጥነት አሳደገ፣ ሎሚና እምቧይ ተቀላቅለው እየተቆጠሩ የአገር ውስጥ ምርት አብጦ ያደገ መሰለ። በአንዳንድ ሥራዎች ምርታማነት ሊጨምር ቢችልም በአገር ደረጃ ግን ምርታማነት ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል። የተናጠል ምርታማነት የአገር ምርታማነት ሊሆን አልቻለም።


በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ የሕዝቡን ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ ለውጦችና መሻሻያዎች ቢታዩም ሰውን ማልማት ባለዲግሪ መቁጠር መስሎን ቁጥር አምላኪዎች ሆነናል፣ በዚህም ላይ የምናፈራቸው ወጣቶች ፌርማታ ለባዕድ አገር ሎሌነት ሥራ መሆኑ ከቀጠለ አገራዊ ምርታማነት ሊያድግ አይችልም። በመሠረተልማት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ስራዎች የህዝቡ የተጠቃሚነት ደረጃ እንደ የሀብት መደቡ፣ የሚኖርበት አካባቢ፣ የዕድሜው ክልል፣ ቢለያይም በጥቅሉ ለሁሉም ሰው ለኢኮኖሚ ዕድገትም ለልማትም ስለሚጠቅም መልካም ነው። በዚህ ምንም ተቃውሞና ትችት የለኝም።


ሆኖም ለግለሰብ ሊሸጥ የሚችልና በግለሰብ ሊለማና የገበያ ዋጋ ሊኖረውም ይገባ የነበረን የገበያ ሸቀጥ የጋራ ልማት ሥራ አድርጎ በመንግሥት እጅ አፍኖ ይዞ የገበያ ዋጋ እንዳይኖረው ማድረግ፣ ምርቱን ትክክለኛ ዋጋ እንዳሳጣው ሳልገልጽ ግን አላልፍም።


የጋራ በሆነ መሬት ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ መሥራት የሚቻለው በጋራ ብቻ ነው። የጋራ የሆነም የግል አይደለም፤ የግል ያልሆነም ገበያ አይወጣም፤ ገበያ ያልወጣም የገበያ ዋጋ የለውም፤ የገበያ ዋጋ የሌለውም፤ በገበያ ዋጋ በገንዘብ አይተመንም። ስለዚህም በሪፖርት ከምናየውና ከሚነገረን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ገሚሱ የገበያ ዋጋ የሌለው ምናባዊ ስሌት ነው። የኑሮ መሐንዲሱ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኑሮን ወደ ምናባዊ ስሌት ከወሰደው የህዝብ ገቢ መጠንና ኑሮም በገበያ ተለክቶ እውነቱ የሚታወቅ ሳይሆን ምናባዊ ይሆናል። አመለካከቱና አስተሳሰቡም የኑሮው ነጸብራቅ ነውና ኑሮውን ተከትሎ ምናባዊ ይሆናል። ሲያገኝም ሲያወጣም በምናባዊ ስሌት ነው።


ሳይበላ የበላ መስሎ፣ ሳይጠጣ የጠጣ መስሎ፣ ሳይደላው የደላው መስሎ፣ ያላመነውን ያመነ መስሎ፣ ያልተቀበለውን የተቀበለ መስሎ፣ የናቀውን ያከበረ መስሎ፣ የጠላውን የወደደ መስሎ፣ በመታየት በምናባዊ ዓለም ውስጥ ይኖራል። ከኢሕአዴገ አባላት ውስጥ ጥቂቶቹ የጥቅም ተካፋይ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን በዚህ ምናባዊ ቀፎ ውስጥ እንደ ንብ የሰፈሩ ናቸው። ሕዝቡም በምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው፣ የምክር ቤት ምርጫ ሊያደርጉ የወጡ ሰዎች በነጠላ ተሸፋፍነው የሆነ ያልሆነውን በትዝብት ተከታትለው የአስመራጮቹ ዓይን አስፈርቷቸው፣ ኢሕአዴግን መርጠው ቤታቸው ሲገቡ፣ የሚያውቋቸውን ታቦቶች ሁሉ እየጠሩ ኢሕአዴግን ንቀልልኝ ብለው የእርግማን መዓት ያወርዳሉ።


ከመቶ ሚልዮን ሕዝብ ውስጥ ሁለት መቶ ሺሕ ሰው ሕንጻ ቢገነባ ከመቶ ሚልዮን ውስጥ ሦስት መቶ ሺሕ ሰው መኪና ቢገዛ አገር አደገች ማለት አይደለም። ብሔራዊ ሀብት በጥቂቶች በግል ይዞታ እየተሰረቀም ብሔራዊ ሀብት ሊሆን አልቻለም ተቆንጥሮ ተቆንጥሮ አልቋል፤ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ስሜትም ይሰረቃል። የኢትዮጵያውያን አገራዊ ስሜት ተሠርቆ አልቋል። ከገንዘብ ስርቆቱም በላይ ይኽ ስርቆት አገር እያጠፋ ነው።


ሕዝቡ ከምናባዊ ዓለም ወጥቶ ገሃዱን ዓለም እንዲቀላቀል የኢኮኖሚ ባለሟል አለ ብሎ በወረቀት ላይ የሚጽፈውን ምርት ለሽያጭ ወደ ገበያ አውጥቶ፣ በገበያ ዋጋ አስተምኖ፣ እውነተኛውን በገበያ ዋጋ የተለካ የምርት መጠን አሳይቶ አለ ያለው መኖሩን ሊያረጋግጥ ይገባዋል። ገብረማርያምን የኃይለማርያምን አይተህ ተጽናና ማለት አይቻልም። አንጀት ላይ ጠብ የሚለው ሺዎች ለሚልዮኖች አስበው ሲሰሩ ሳይሆን ሚልዮኖች ለራሳቸው አስበው በገበያ ውስጥ ተወዳድረው እንዲሠሩ በተሟላ የመንግስት ቁጥጥር ድጋፍና አመራር የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ነው። “ጧት ጧት ደቧችንን ጠረጴዛችን ላይ የምናገኘው በዳቦ ጋጋሪው ጽድቅ ሥራ ሳይሆን ለራሱ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በሚሠራው ሥራ ነው፤” ሲል የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ስውር እጅ አሠራር አዳም ስሚዝ አረጋግጧል። ከርሱ በኋላም ሌሎች ኢኮኖሚስቶች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር የገበያውን ጉድለት እንዴት እንደሚቀርፍ አመልክተዋል። “ልማት ማለት አንድ ሰው ሊሆንና ሊያደርግ የሚፈልገውን ሕጋዊ ነገሮች የመሆንና የማድረግ ነጻነትና አቅም ሲያገኝ ነው፤” ሲሉ በ1998 በልማት ኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት አማርተያ ሴን ነግረውናል።


ይኽን አይቶ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንደገና ካልመረመረ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹን ችሎታ ካልተጠራጠረ፣ የወረቀት ላይ ቁጥርን ብቻ ሳይሆን ገበያዎችን ተንትናችሁ ተርጉሙልኝ ካላላቸው ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው። በፖለቲካው የተፈለገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓይነት ማዕከላዊ ዕቅድን እና ነጻ ገበያውን ማቀላቀል ቢሆንም የቅልቅሉን ዓይነት በብልሃት መምረጥ፣ ምናባዊ ዕቅድና ክንውኑን ብቻ ሳይሆን በገሃድ በዓይን የሚታየውን የገበያውን ሁኔታ መከታተል፣ ተነጣጥለው ለየራስ እየሄዱ ያሉትን ማዕከላዊ እቅድና ገበያውን ማቀናጀት ያስፈልጋል።


የገበያውን ምልክትና ቋንቋ ያልተረዱ፣ ይኽ ከዚያ ይበልጣል ያ ከዚህ ያንሳል እያሉ ምናባዊ ቁጥር ገጣጥመው ማማለል የለመዱ፣ በምናባቸው አቅደው በምናባቸው የፈፀሙትን ማነጻጸር ብቻ የሚችሉ፣ ወደ ገበያ ወረድ ብለው ተጨባጭ ሁኔታን ያላዩ ቁጥር አምላኪ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ገበያው በሽሚያ እርሾ እየቦካ መሆኑን ማየት ተስኗቸዋል። ሙያቸው ሰው እያስራበ፣ አያስኮበለለና እያስገደለ እንደሆነ አልተሰማቸውም፤ ልባቸው ደንድኗል።


በምርጫ 2002 ፋሲካ ሰሞን አርባ ብር የነበረ የዶሮ ዋጋ በምርጫ 2007 ፋሲካ ሰሞን አራት መቶ ብር ከገባ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል፣ በምርጫ 2007 ሚልዮኖች ከተሰደዱ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሰደዱ እንደሚችሉ መገመት ያስቸግራል። ያሰቃየን ካይዘንን፣ ውጤት ተኮርን፣ ቢ.ፒ.አርን፣ ቢ.ኤስ.ሲ.ን አለማወቅ አይደለም፣ ያሰቃየን ደላላው አይደለም። ነጋዴውም አይደለም። ያሰቃየን የእነኚህ ሁሉ ገዢ ቃል የሆነው ገበያው ነው። እኛው ከውድድር ወደ ሽሚያ የለወጥነው ገበያው ነው።


የበላን የበረሀ አሸዋ አይደለም፣ ባህርም አይደለም፣ ያረደንም ሰው አይደለም። የበላን ያረደን፣ ለስደት፣ ለስቃይ፣ ለሞት፣ ለዋይታ፣ የዳረገን ገበያው ነው። ሰው አገር ሞልቶና ተርፎ እኛ አገር የጠበበውና የተኮማተረው መኮማተሩንም ራሱን ሳይደብቅ የሚነግረን በመንግስት አስተዳደር ሳጥን ውስጥ ታስሮ ያለው የሥራና የእንጀራ ገበያ ነው። በአዋጅና በሕግ ስለተደነገገው ገበያ እንደ ካይዘኑ፣ እንደ ውጤት ተኮሩ፣ እንደ ‹ቢ.ፒ. አሩ›፣ እንደ ‹በ.ኤስ.ሲው› ልናውቅ ልናጠና ባለመፈለጋችን በኑሮ ተቀጣን እየተቀጣንም ነው። ገበያው ሰማይ ይሰቅለናል፤ መቀመቅ ያወርደናል፤ ገበያው ያሰድደናል፤ ያስገድለናል፤ ጥቂቶችንም ገበያው ያንቀባርራል፤ ያንደላቅቃል፤ ያመጻድቃል።


የሚጻፉትን ቁጥሮች እና የገበያውን ምልክት በማያገናዝቡ፣ የኛን የምርትና የሸመታ ምርጫ ሥነልቦና በማያውቁ፣ እኛ በገበያዎቻችን ውስጥ ልናገኛቸው የምንፈልጋቸውን የሸቀጦች ዓይነት በማይረዱ ባዕዳን አማካሪዎች እገዛ ምክርና ትዕዛዝ ገበያውን ማየትና የገበያውን ቋንቋ መስማት በተሳናቸው የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጓዳ ውስጥ በማዕከል ታቅዶ የሚተገበር ፖሊሲ ጎደሎ ነው። የውጭውን አገር ጽንሰ-ሐሳብና ልምድ ብቻ ይዞ ምድሩ ሳይታወቅ ሰማይ መቧጠጥ ነው። በሰው አገር ዕድገት ሞዴል ጉጉት ናፍቆትና ምኞት ራስን መደለል የልማትን ትርጉም ሳያውቁ ልማታዊ ነኝ ማለት የሕዝብ ሕይወትና ኑሮን የሙከራ ጊዜ ማድረግ ነው። ለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና ለህዝቡ ሥነልቦና በቂ ትኩረት አለመስጠት ነው።


ቁጥር ብቻ እየታየ የሸማቹን አቅም ለመገንባት የሚረጨው የጥሬ ገንዘብ መጠን ወደኋላ ተኩሶ ዋጋን በማናር ጀርባችንን አቁስሎታል። የአምራቹን አቅም ለማሳደግ ለጥቂቶች የሚሰጥ ያዝ ለቀቅ ድጋፍ ግብታዊ እርምጃም ነቀዝ ፈልፍሏል። ከቁጥር ቁማር ወጥተን ከፈጠርነው አርተፊሻል የሽሚያ ገበያ ተላቀን የገበያ ኢኮኖሚውን እና የልማት ኢኮኖሚውን ካላመጣጠን ላንነሳ ተሰናክለን እስከምንወድቅ ኑሯችን የአቦ ሰጥ እንደሆነ ይቀጥላል። በአቦ ሰጥ ይገኛል በአቦ ሰጥ ይታጣል።


የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አካሄድ በውስጣዊ ኃይላት እቅስቃሴ የሚመራ ሥርዓት ነው። ላለመሰቃየት፣ ላለመሰደድ ላለመሞት ላለማልቀስ በአቦሰጥ ላለመኖር ከሽሚያ ገበያና ኑሯችንን ቤተሙከራ ከማድረግ ወጥተን ትክክለኛውን የነጻ ገበያ ሥርዓት መዘርጋትና የሥርዓቱን ውስጣዊ ኃይላት እንቅስቃሴ ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል።

 

በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት እጥፍ ያደገ ኢኮኖሚ


ከላይ በእንቆቅልሽ መልክ በተመለከተው የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ፋይዳ ቢስ መሆኑን በገበያ መገለጫ ያረጋገጥን ቢሆንም በስታቲስቲካዊ መረጃውም የተሳሳተ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። ብዙ ኢትዮጵያውን ስለ ኢኮኖሚው የመንግስትን መረጃ ፈጽሞ እንዳያምኑ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ተብሎ የሚጠራው ነው። ገበያ ውስጥ ምርት ጠፍቶ ዋጋው በየጊዜው ከሚገባው በላይ ወደላይ እየተሰቀለ ምርቱና አቅርቦቱ በየዓመቱ በዐሥራ አንድ በመቶ አደገ ሲሉ ሕዝቡ ታዲያ እንዴት ይመናቸው?


ይኽ በፍጥነት አደገ የሚባል ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የሕዝቡን ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን ከልክ በላይ አሳድጎ፣ በድህነት ቅነሳ መለኪያ አመልካች የሕዝቡ ኑሮ ደረጃ የተለወጠ በማስመሰል ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ሆኖበታል። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በዓመት በአገር ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በፀጥታ አስከባሪው፣ በመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በዳኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በመምህሩ፣ በሐኪሙ፣ በቢሮ ሠራተኞች፣ በነጋዴው፣ በሙዚቀኛው፣ በፀጉር አስተካካዩ፣ በቤት ሠራተኛው፣ በሾፌሩ፣ በዘበኛው በጫማ አሳማሪው በዳንስ አስተማሪው በጭፈራ ቤት ሥርዓት አስከባሪው ወዘተ. ተመርቶ በሸቀጥ መልክ ለገበያ የቀረበ ወይም ለገበያ እንደቀረበ ተቆጥሮ ዋጋው የተተመነ ቁሳዊ ዕቃና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ነው።


ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ ዋጋ በኹለት መልክ ይለካል። አንዱ ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ መለካት ሲሆን፣ ኹለተኛው የዋጋ ንረትን በምርቱ ልኬት ውስጥ ላለማስገባት በአንድ በተመረጠ ዓመት ቋሚ ዋጋ አማካኝነት የተከታታይ በርካታ ዓመታት ምርት መጠንን መለካት ነው። ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የየዓመቱን የዋጋ ንረቶች ስለሚጨምር እርግጠኛው የምርት መጠን አይደለም የዋጋ ንረቱ አሳብጦታል። ይኽ በዋጋ ንረት ያበጠ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ምስለ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ይባላል።


በሌላ በኩል እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) በተመረጠ ዓመት ቋሚ የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ሲሆን በየዓመቱ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ስለማይጨምር በዋጋ ንረት ሳይበከል የተተመነ ምርት መጠን ነው። አንድ ገበሬ አምና ስምንት ኩንታል ስንዴ አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በአንድ ሺሕ ብር ቢሸጥ የስምንት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ማለት ነው። ዘንድሮ ዐሥር ኩንታል ምርት አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በሺሕ ኹለት መቶ ብር ቢሸጥ የዐሥራ ሁለት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ይባላል።


የአምናው ኩንታል ምርት በአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ተለክቶ የዘንድሮው ኩንታል ምርት በሺሕ ሁለት መቶ ብር ዋጋ መለካቱ የዘንድሮውን ምርት የዋጋው ንረት አሳብጦታል።


የአምናው ስምንት ኩንታል ምርትና የዘንድሮው ዐሥር ኩንታል ምርት በተመሳሳይ የአምና ቋሚ ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ቢለኩ ገበሬው ዘንድሮ ያመረተው ምርት መጠን ዐሥራ ኹለት ሺሕ ብር ሳይሆን ዐሥር ሺሕ ብር ነው። በአምናው ቋሚ ዋጋ የተለካው የዘንድሮ ምርት መጠን በዋጋ ንረት አልተበከለም። እርግጠኛውን የምርት መጠን ለመለካት የአገር ውስጥ ምርት መጠን በአንድ በተወሰነ የቀድሞ ዋጋ መሠረት ይለካል። የቀድሞዎቹን ዓመታት ትተን የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ብቻ ብንወስድ፣ በኢትዮጵያ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የየዓመቱ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በ1992 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ሲለካ ቆይቷል። ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ተከልሷል።


ይኽ የሚሆንበት ምክንያትም ዋጋ ሳይከለስ ለረጅም ጊዜ ቢቆይ ትክክለኛውን የምርት መጠን ስለማይለካ ነው። ስለሆነም ሁሉም አገራት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የምርት መለኪያ ዋጋ ዓመታቸውን ይከልሳሉ። ኢትዮጵያ ኬንና ናይጄሪያ መከለሳቸውን ከዚህ ቀደም አይተናል ኢትዮጵያ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት ዓመታትም እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እየተለካ ያለው የ1992ቱን ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ በ2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ አማካኝነት በመከለስ ነው። የዚህ እንድምታ ምን እንደሆነ ቀጥለን እንመልከት።


በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 ዓ.ም. መከለስ ምክንያት የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ከ1992 እስከ 2003 በነበሩት የየዓመታቱ ዋጋ ንረቶች ተበክሎ አብጧል። ስለሆነም በዋጋ ንረት ተበክሎ በማበጥ አራት መቶ ሰባ ቢልዮን ብር የሆነው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካውን አንድ መቶ ሐምሳ ስምንት ቢልዮን ብር የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሦስት ነጥብ ሦስት እጥፍ ሆኗል። ነፍስ ወከፍ ገቢም ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ብር ወደ ስድስት ሺሕ ኹለት መቶ ስልሳ ሰባት ብር አብጧል።


የግብርናው የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዕድገቶችም አብጠዋል። በዚህም መሠረት ስልሳ አምስት ቢልዮን ብር የነበረው የግብርና ምርት ወደ ኹለት መቶ ዐሥራ ሦስት ቢልዮን ብር፣ ሃያ አንድ ቢልዮን ብር የነበረው የኢንዱስትሪ ምርት ወደ ሐምሳ ቢልዮን ብር፣ ሰባ ሦስት ቢልዮን ብር የነበረው የአገልግሎት ምርት ወደ ኹለት መቶ ሰባት ቢልዮን ብር አብጠዋል። የሕዝቡ ኑሮ የአዲሱን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ያህል ሦስት እጥፍ አደገ ማለት ነው ወይስ ለቆጠራ ያህል ብቻ የሚያገለግል የወረቀት ላይ ዳማ ጨዋታ ነው? ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው።


የአገር ውስጥ ምርቱ መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 በመቀየሩ ምክንያት በወረቀት ላይ በሚጻፉ ቁጥሮች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅጽበታዊ ሦስት እጥፍ ጭማሪ ነፍስ ወከፍ ገቢን ማሳደግና ድህነትን መቀነሰ ይቻላል ማለት ነውን። ይኽ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መጠን ሳያድግ በዋጋ ንረት አማካኝነት ያደገ መምሰል ብዙ እንድምታዎች አሉት። የአገር ውስጥ ምርት ዕድገቱን መሠረት አድርገው የሚለኩ ሌሎች የሰውና ኢኮኖሚ ልማት መረጃዎች የተዛቡ ይሆናሉ። የዋጋ ንረትም በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሲሆን መንግሥትም በዋጋ ንረቱ ምክንያት ለመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ ለማድረግ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር በውጭ መንዛሪ እያስገባ ማከፋፈል የጀመረው በዚሁ ዓመት ነው።


ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሁሉም አገሮች በተወሰኑ ዓመታት እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዓመተ ምሕረቱን ይከልሳሉ። በተባበሩት መንግሥታት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ልኬት መርህም ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠኑን ያሳበጠው የቋሚ መለኪያ ዓመቱ መከለሱ በራሱ ሳይሆን ከክለሳው በፊት የነበሩት እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረቶች በክለሳው ውስጥ በመካተታቸው ነው። የዋጋ ንረት በኹለትና በሶስት በመቶ ብቻ በሚቆጠር መጠነኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ የመለኪያ ቋሚ ዓመቱ መከለስ ብዙ ለውጥ አያስከትልም። የዋጋ ንረት ከፍተኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ግን የመለኪያ ቋሚ ዓመት ክለሳው የአገር ውስጥ ምርት መጠንን ከልክ በላይ ያሳብጠዋል።


በቋሚ መለኪያ ዓ.ም. ክለሳው ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ በወረቀት ላይ በሚታይ ቁጥር ደረጃ ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ በፍጥነት እየተጠጉ ነው። ድህነትም በፍጥነት እየቀነሰ ነው። አብዛኛው ሕዝብ ግን በዋጋ ንረት ምክንያት ኑሮው በማዘቅዘቁ ከመካከለኛ ኑሮ ደረጃ እየራቀ እየደኸየም ነው። ወረቀቱ ነው ስለኑሯችን የሚመሰክረው ወይስ የገሃዱ እውነታ ነው? የየዓመቱ ገደብ የለሽ ዋጋ ንረቶች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭንቀቶችና ስቃዮች ናቸው። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን በፍጥነት አሳድገው በፍጥነት መካከለኛ ገቢ ውስጥ ለማስገባት ድህነትንም ለመቀነስ ሩቅ ዓልመው ሩቅ ለማደር ለሚተጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለሙያዎች በደስታ ጮቤ የሚያስረግጡ ናቸው። የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ዓ.ም. በየዐሥር ዓመቱ ስለሚከልሱት በ2013 እንደገና ተከልሶ የምርት መጠኑና ነፍስ ወከፍ ገቢው ሦስት እጥፍ አድገው እንደታለመው በቅርብ ዓመታት ድህነትን ለማጥፋት ወደ መካከለኛ ገቢ መጠን መቃረብም ይቻላል።


በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዐሥር ቢልዮን ብር ገደማ ነበር። የ2003 ዓ.ም. አራት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢልዮን ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ዐሥር ቢልዮን ብር አካባቢ ጋር ሲነጻጸር ሐምሳ እጥፍ ግድም እንደሆነ ይታያል። በ2008ም ሰባት መቶ አርባ ሰባት ቢልዮን ብር ስለደረሰ ሰባ እጥፍ ደርሷል። ይኸ ዕድገት በእርግጠኛ የአገር ውስጥ ምርት ስሌት ሲሆን በምስለ የአገር ውስጥ ምርት ስሌትም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከሃያ ቢልዮን ብር በታች የነበረው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ወደ ኹለት ተሪልየን ብር እየተቃረበ ስለሆነ ከመቶ እጥፍ በላይ አድጓል።


እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ስልሳ ዓመታት ፈጅቶባታል። አሜሪካ በ19ኛው ክፍ ለዘመን መጨረሻ ገደማ ኢኮኖሚዋ መመንጠቅ ሲጀምር ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ሐምሳ ዓመታት ፈጅቶባታል። በፍጥነት ያደጉት የምሥራቅና ደቡብ ምስራቅ እስያ አገራትም ኢኮኖሚያቸውን እጥፍ ለማድረግ እስከ ዐሥር ዓመታት ፈጅቶባቸዋል። የእኛን አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከነዚህ አገራት እድገት ታሪክ ጋር ስናነጻጽር የኤሊና የጥንቸል ሩጫ ውድድር ይመስላል። እነርሱ ኤሊዎቹ እኛ ጥንቸሏ ነን። ይህ የሚታመን መረጃ ነውን በኢኮኖሚ ጥናት ሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን።


እንደ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሳሰሉ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሁኔታውን ያውቃሉ ወይስ አያውቁም? አውቀውስ ተቀበሉት ወይስ አልተቀበሉትም? አሳምረው ያውቃሉ። ከማወቅም አልፎ አምነው ተቀብለው መዝግበውታልም። የአገራትን መረጃዎች አጣጥለው በዚህ ሳቢያ በትውውቅና በሹመት የተገኘ ሥራቸውንና ወፍራም ደመወዛቸውን ከሚያጡ አዎን ብለው አጨብጭበው መቀበሉን ይመርጣሉ። ማን ለማን መስዋዕት ይሆናል? የተከበሩት ፈረንጆች የሙስና ተማሪዎች ሳይሆኑ አስተማሪዎች እየሆኑ ነው።


አገራትም አንዱ የሌላውን መረጃ ለማጣጣልና ላለመቀበል ወኔው የላቸውም። ከሶቭየት ኅብረት መውደቅና ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ የመጣ ተቻችሎና ተግባብቶ የመኖር የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ዘይቤ ነው። ይኽ የድርጅቶችና የመንግሥታት መቻቻል የታዳጊ አገራት ሕዝቦች ድህነት ይብቃን የሚያጠግቡን ይምሩን እንዳይሉ አደረጋቸው። መገናኛ ብዙሃን በእጃቸው በሆነ ባለሥልጣናትና የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሹማምንት የታዳጊ አገራት ድሃ ድምጻቸው ተቀማ። ከምዕራባውያን ጋር ተስማምተው እስከኖሩ ድረስ ሕዝባቸውን ቢያስርቡም ባያስርቡም ጉዳዬ ነው የሚል ጠፋ። ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶቹ እንደውም ለውጭ ኢንቬስተሮች ሁኔታዎች ይመቻቹ እንጂ የማያውቁትን ለመመስከር መጽሐፍ ቅዱስ ይዘውም ቢሆን ይምላሉ።


ኢትዮጵያ በራሷ እምነትና መንገድ ኢኮኖሚዋን በዚህን ያህል መጠን አሳድጌአለሁ ብላ ብትል፣ ይኽ አለካክ ትክክል አይደለም የሚልና የሚያጣጥለው የትኛው የሕዝብን ጉዳይ ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ወይም አገር ነው? በጥቂቱም ቢሆን ወኔው ያላቸውና መጻፍ ካስፈለጋቸው የሚጽፉትና በሳይንሳዊ መንገድ የሚተነትኑት አንዳንድ ታዋቂ የኢኮኖሚክስ ጥናት ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲዎች እና የአንድ አገር ኢኮኖሚ ተመራማሪ ግለሰቦች ናቸው።


(www.facebook.com/TheBlackLionAfrica)

ክፍል የኔ ሃሳብ

 

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ድርጅት የሆነው ዩናይትድ የአውቶሞቢል ጥገና አገልግሎት ኃ/የተ/የግል ኩባንያ የመጀመሪያው የሆነውን የነዳጅ ማደያ እና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ በቀራኒዮ አካባቢ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም አስመረቀ።

ማደያው የተገነባው በኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ይዞታ ላይ ሲሆን ዩናይትድ አውቶሞቢል ለአገልግሎቱ ኪራይ እንደሚከፍልበት ታውቋል።

የነዳጅ ማደያው በልዩ ዲዛይን የተገነባ መሆኑን አቶ ታደሰ ጥላሁን የኖክ ሲኢኦ ተናግረዋል። ኖክ ከዚህ ቀደም የገነባቸው ማደያዎች እያንዳንዱ 150 ሺ ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም አላቸው ያሉት አቶ ታደሰ የቀራኒዮ አዲሱ ማደያ ግን 250 ሺ ሊትር የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ መገንባቱን በመጥቀስ ሁልጊዜም በዚህ ማደያ ነዳጅ ሊጠፋ እንደማይችል ተናግረዋል። የነዳጅ ማደያው ዲዛይን ልዩና ሳቢ መሆኑን በመጥቀስ ወደሌሎች የኖክ ማደያዎች ለማስፋፋት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር አረጋ ይርዳው በበኩላቸው የነዳጅ ማደያው የተገነባበት ቦታ በንጉሱ ዘመን ልዕልት ተናኜ ወርቅ የወተት ላሞች ርቢ የሚያካሂዱበት ቦታ እንደነበርና በወቅቱ ተተክሎ የነበረ አንድ የነዳጅ መቅጃ ማሽን እና የላሞች ማርቢያ ቤቶች በቅርስነት እንዲጠበቁ መደረጉን አስታውሰዋል። በወቅቱ በዚህ ቦታ ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞች የያዙት ይዞታ በተመለከተ ከሼክ ሙሐመድ ጋር በመነጋገር በነጻ እንዲዛወርላቸው ተወስኗል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ማደያው ግንባታ ወቅት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ኩባንያዎች እንዲሳተፉ መደረጉንና በራስ አቅም ለየት ባለ ዲዛይን እንዲሰራ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አቶ መሠረት ሻረው የዩናይትድ የአውቶሞቢል ጥገና አገልግሎት ኃ/የተ/የግል ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የነዳጅ ማደያ እና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ከነዳጅ ማደያ አገልግሎት በተጨማሪ የተለያዩ የተሽከርካሪ አይነቶች፣ ቅባቶች እና ግራሶዎች፣ መኪና መጠበቂያ ምርቶች፣ የመኪና ኦይል ትሪትመንት እና የነዳጅ ፓምፕ እና ኖዝሎች፣ ችግር የሚፈቱ ኬሚካሎችና ኦዲቲቮች ሽያጭ ያከናውናል። በተጨማሪም ዘመናዊ የተሽከርካሪ እጥበት፣ ፈጣን የጥገና አገልግሎት እና የካፌ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የቀራንዮ የነዳጅ ማደያ እና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጪያ በቀጣይ ለ27 ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

 

 

 

 

ክፍል ወቅታዊ

 

ከሃያት ጎሮ እና ከሃያት ቦሌ አራብሳ እንዲሁም በፍጥነት መንገዶች መግቢያ መስመሮች የመንገድ መብራት መስመሮች በአግባቡ ተዘርግተው ሙከራም ተደርጎባቸው ነበር። ነገር ግን እነዚህ መስመሮች መብራት እስከ አሁን ድረስ አልተለቀቁላቸውም። ኮንዶሚኒየሞቹ አዲስ እንደመሆናቸው መጠን የተወሰኑ ነዋሪዎች ከመግባታቸው ውጪ አብዛኞቹ ባዶ ናቸው። በእነዚህ መስመሮች የመብራት ኃይል አለመዘርጋቱ አካባቢውን የወንጀለኞች መፈልፈያ አድርጎታል። በተለይ መሸት ሲል በዚያ መስመር የሚያልፉ ሰዎች በዝርፊያ እና ለድብደባ እየተጋለጡ ይገኛሉ። ጨለማን ተገን በማድረግ በርካታ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ይገኛሉ። በአካባቢው ያለው ህዝብ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ እና እንቅስቃሴውም ውስን በመሆኑ ማንም ለማንም ሊደርስ እና ከአደጋ ሊታደገው አይችልም። ከዚህ በተጨማሪም የመብራት አለመኖሩ በአካባቢ የመኪና አደጋዎች እንዲፈጠሩ አንዱ ምክንያት እየሆነ ነው።

 

የመንገድ መብራት ዝርጋታው በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅንጅት እንደሚሰራ ነው የሚታወቀው። አሁን ባለው መረጃ ማዘጋጃ ቤት ክፍያውን ባለመክፈሉ የኤሌክትሪክ ሃይሉ እንዳልተለቀቀ ነው። መሰራት ያለበት አብዛኛው ነገር ተሰርቶ ጥቂት ነገሮች ሲቀሩ ስራው ችላ በመባሉ በርካታ ችግሮች እየተፈጠሩ ስለሆነ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን እና ከእነዚህ ችግሮች ሊታደገን ይገባል።

                             

መምህር ሲሳይ አለሙ - ከቦሌ አራብሳ        

ክፍል መልዕክቶች

ምንም እንኳን ወቅቱን ጠብቆ የሚገኝ ቢሆንም ተፈጥሮ ያለ ማንም ተቆጣጣሪነት ለሰው ልጅ ከሰጠቻቸው ነገሮች አንዱ የዝናብ ውሃ ነው። በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል እንዲሉ የዝናብ ውሃን ከሌሎች የውሃ አማራጮች እኩል የመጠቀም ሁኔታ ብዙም አይስተዋልም። በተለይ የውሃ አቅርቦቱ የተስተካከለ በሆነባቸው የከተማ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን በችግር ጊዜ ከመጠቀም በዘለለ እንደመደበኛ ውሃ አገልግሎት ላይ ሲውል አይታይም። ነገር ግን የዝናብ ውሃ ከሌሎች በጸረ ጀርም እና በማዕድናት ከበለፀጉት የውሃ አይነቶች በበለጠ የራሱ የሆነ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በያል ዩኒቨርስቲ እና አውስትራሊያ ዩኒቨርስቲ የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ይፋ የተደረጉ የጥናት ውጤቶች አመልክተዋል። የዝናብ ውሃ በተፈጥሮው ያለው ጤናማ የሆነ ይዘት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የጤና ጠቀሜታዎች እንዲሰጥ አድርገውታል ይላሉ ጥናቶቹ።

ከጠቀሜታው በተጓዳኝም የዝናብ ውሃን በተመለከተ ሊወሰዱ የሚገባቸው ሁለት ጥንቃቄዎች እንዳሉም ጥናቶቹ አመልክተዋል። የመጀመሪያው የዝናብ ውሃ ከአፈር ወደ ውሃ የሚገቡ እንደ ሶዲየም፣ ፖታሲየም፣ ካልሲየም እና ፍሎራይድ ማዕድናት ስለሌሉት ከዚህ ውሃ የማናገኛቸውን ጠቃሚ የማዕድን አይነቶች በሌሎች መጠጦች እና ምግቦች አማካይነት መጠቀም እና መተካት ይኖርብናል። ሁለተኛው ጥንቃቄ ደግሞ ውሃው ከላይ በሚወርድበት ወቅት እንደጀርም ላሉ በካይ ነገሮች ያለውን ተጋላጭነት በሚያስቀር መልኩ መጠራቀም ይኖርበታል። ውሃው መሬት ደርሶ አልያም በተለያዩ ቁሳቁሶች ተጠራቅሞ አገልግሎት ላይ መዋል ግዴታው ከሆነም ከእነዚህ በካይ ነገሮች ሊፀዳ በሚችልባቸው የማጣራት ወይም የማፍላት ሂደቶች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል።

ለስርዓተ ልመት እና ሰውነት ማጥራት ያግዛል

የአልካላይን ይዘቱ ከፍተኛ የሆነ የውሃ አይነት በሰውነት ውስጥ የሚከናወኑ የምግብ ስርዓተ ልመቶች የተስተካከሉ እና ጤናማ እንዲሆኑ ያግዛል። በተጨማሪም ሰውነት አላስፈላጊ እና መርዛማ የሆኑ ነገሮችን የሚያስወግድበት ስርዓት (detoxification system) የተመቻቸ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም የዝናብ ውሃ በደም ውስጥ ያለው (የውሃን አሲዳማነት መሳቢያው) የፒ ኤች (PH) መጠን ለሰውነት ተስማሚ በሆነ ደረጃ እንዲገኝ የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በሰውነት ውስጥ የሚገኙ መርዛማ ነገሮች እና ፍሪ ራዲካልስ በደም ውስጥ ያለው የፒ ኤች መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የአሲድነት ባህሪው እንዲጎላ የማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚፈጥሩ ሲሆን፤ የዝናብ ውሃን በምንጠጣበት ጊዜ ይሄን የተዛባ ስርዓት በማስተካከል ሰውነት በተቀላጠፈ መንገድ ስራዎቹን እንዲያከናውን ያግዘዋል ይላል መረጃው። በዚህ ሳቢያ ተግባራቸው ከሚቀላጠፍ ስርዓቶች መካከልም ዋና ዋናዎቹ የምግብ ልመት ስርዓት እና መርዛማ ነገሮችን የማስወገድ ስርአት ናቸው።

የጨጓራ ህመም፣ ራስ ምታት እና የህዋሳት ጉዳትን ይከላከላል

የዝናብ ውሃ ከክሎሪን እና ከፍሎራይድ ኬሚካሎች የፀዳ ነው። የቧንቧ ውሃ አሊያም የታሸጉ የውሃ አይነቶችን ከተለያዩ ጀርሞች ለመከላከል ሲባል ክሎሪን እና ፍሎራይድ እንዲገባባቸው ይደረጋል። እነዚህ ኬሚካሎች መጠናቸው ከሚገባው በላይ ሆኖ ሲገኝም እንደ ራስ ምታት፣ የጨጓራ ህመም እንዲሁም በአንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ላይ የመጎዳት ሁኔታን ይፈጥራሉ። የዝናብ ውሃን በምንጠቀምበት ወቅት ግን ንፁህ የሆነ ውሃን ከማግኘታችንም በላይ ከእነዚህ ተያያዥ የጤና እክሎች ነፃ እንሆናለን።

ፀረ -ካንሰር ጠቀሜታ አለው

በዝናብ ውሃ ውስጥ የሚገኘው የውሃ አሲድነት ባህሪይ (ፒ ኤች) የካንሰር ሴሎችን በፍጥነት ማደግ እና መሰራጨት የመግታት ባህሪይ አለው። ይህ የዝናብ ውሃ ለእነዚህ የካንሰር ህዋሳት እንደ አንቲኦክሲደንት ስለሚሆንባቸው ህዋሳቱ እና እጢዎቹ በፍጥነት እንዳያድጉ ያደርጋቸዋል። ተፈጥረው የነበሩ የካንሰር አምጪ ህዋሳት ካሉም ስርጭታቸውን በመግታት ወደ በሽታነት የመቀየሪያ ጊዜያቸውን በማሳጠር ለህመሙ ያለውን ተጋላጭነት ይቀንሱታል።

በሆድ ውስጥ የሚከሰቱ ህመሞችን ይፈውሳል

በህንድ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጠዋት ላይ በባዶ ሆዳቸው ከሁለት እስከ ሶስት የሻይ ማንኪያ የዝናብ ውሃ የሚጠጡ ሰዎች በሆዳቸው ውስጥ የሚሰማቸውን የህመም ስሜት በእጅጉ መቀነስ ችለዋል። በዝናብ ውሃ ውስጥ የሚገኘው ጤናማ እና የተስተካከለ የፒ ኤች መጠን በሆድ ውስጥ የሚገኘው አሲድ ተስማሚ እንዲሆን በማድረግ በአሲዱ ሳቢያ የሚከሰተውን መቆጣት ያስቀራል። በዚህ ባህሪው የተነሳም እንደ ቃር፣ የጨጓራ ህመም እና የጨጓራ ቁስለት ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ለማስታገስ ያግዛል።

የቆዳ ጤንነትን ይጠብቃል

የዝናብ ውሃ ባህሪያት ከሆኑት አንዱ ከሳሙና ጋር ሲገናኝ በቀላሉ አረፋ መፍጠር መቻሉ ነው። በዚህም ሳቢያ በዝናብ ውሃ በምንታጠብበት ወቅት በሰውነታችን ላይ የሚያርፈው ሳሙና መጠን እንዲቀንስ እና በቀላሉ አረፋ እንድናገኝ ያግዘናል። ይኸውም ሰውነታችን (ቆዳችን) በሳሙና ውስጥ ላሉ ኬሚካሎች ያለውን ተጋላጭነት በመቀነስ ተፈጥሯዊ ይዘቱ እንዲጠበቅ ያግዛል። በተጨማሪም የዝናብ ውሃ ቀላል የሚባል የውሃ አይነት በመሆኑ ቆዳችን ተፈጥሯዊ እርጥበቱን እና የመሳሳብ ባህሪውን እንደያዘ እንዲቆይም ያግዘዋል። በመሆኑም አዘውትሮ በዝናብ ውሃ መታጠብ ቆዳችን ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ እና ብሩህ ቀለም ያለው እንዲሆን ያግዘዋል።

ሌላው የዝናብ ውሃ ለቆዳ የሚሰጠው ጠቀሜታ እንደ ብጉር ያሉ የቆዳ ህመሞችን ማስወገድ ነው። የዝናብ ውሃ በቀላሉ ቆዳን አጥርቶ ለመታጠብ እና ህመም ፈጣሪ የሆኑ ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ ያግዛል። በተለይ በፊት ላይ እና በአንገት አካባቢ ብጉር እና መሰል ችግሮችን የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎችን ከቆዳ ላይ በማስወገድ እነዚህ ብጉሮች እብጠታቸው እንዲቀንስ እንዲሁም የሚፈጥሩት የህመም ስሜት እንዲቀንስ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

የፀጉር ጤንነት ይጠብቃል

የዝናብ ውሃ ከሌሎች የውሃ አይነቶች ይልቅ ከአፈር ከሚገኙ የተለያዩ ማዕድናት የፀዳ ነው። እነዚህ ከአፈር የሚገኙ ማዕድናት ፀጉርን በተለያየ መንገድ የመጉዳት ባህሪይ ስላላቸው በዝናብ ውሃ መታጠብ ከእነዚህ ማዕድናት ለመራቅ ያግዛል። በተጨማሪም ፀጉራችንን የምንታጠብበት ውሃ የአሲድነት ይዘት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ኬራቲን እና ፎሊክል የተባሉ ፀጉር የተሰራባቸው ንጥረ ነገሮች እየተጎዱ ይሄዳሉ። የዝናብ ውሃ ግን ያለው የአሲድነት ባህሪይ የተመጣጠነ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ያገለግላል። በተጨማሪም በዚህ ውሃ ውስጥ የሚገኘው አልካላይን ፒ ኤች ፀጉር በፍጥነት እንዲያድግ እና ስሮቹም ጠንካራ እንዲሆኑ የማድረግ ጠቀሜታ አለው።

የዝናብ ውሃ ቀላል ውሃ በመሆኑ ከከባድ ውሃ በበለጠ ፍጥት የኤሌክትሪክ ሃይል ያለው ኦቶም የመፍጠር (ionised) ባህሪይ አለው። በዚህ ባህሪውም በቀላሉ ወደ ደም በመግባት የመዋሃድ እና በሰውነት ውስጥ የሚኖረው የኦክሲጅን ዝውውር የተሳለጠ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተጨማሪም ፍሪ ራዲካልስ የተባሉት እና ለሰውነት አላስፈላጊ የሆኑ ቁጡ የኦክሲጅን አይነቶችን ወደ ጤናማነት በመቀየር በሰውነት ህዋሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ያግዛል።

ከዚህ በተጨማሪም የዝናብ ውሃ ከሳሙና ጋር ሲገናኝ በቀላሉ አረፋ የመፍጠር ባህሪይ ስላለው ለማንኛውም አይነት እጥበት የሚያገለግል ሲሆን፤ በዚህ ባህሪውም የሚታጠቡት ነገሮች (ልብስን ጨምሮ) ተፈጥሯዊ ቀለማቸውን ይዘው ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።

ክፍል ጤና
Page 1 of 3

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1045 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us