Items filtered by date: Wednesday, 02 May 2018 - Sendek NewsPaper
Wednesday, 02 May 2018 13:10

ጊዜ አልበም ተመረቀ

አርቲስት አበበ አርአያ ከሰሞኑ “ጊዜ” የሚል ርዕስ የሰጠውን አልበሙን አስመርቋል። አርቲስቱ ከዚህ ቀደም እምበር ተጋዳላይ፣ አይርስአከን፣ ዓደይ፣ ቁረፅ በሎ፣ ይአኽለኒ እና ሌሎች የትግል ዘፈኖችን ለአድናቂዎቹ አድርሷል። አዲሱ ግዜ አልበም በአክሱም ሆቴል እንደዚሁም 22 አካባቢ በሚገኘው ፍሪደም ሀውስ በተከታታይ ተመርቋል። ድምፃዊው ሁሉም የጊዜ አልበም ሙዚቃዎቹ በትግርኛ የተሰሩ መሆኑን ገልጾ አልበሙ ከፍቅር ጀምሮ እስከ ሀገር ፍቅር ድረስ ያሉ ሙዚቃዎቹን በአልበሙ ውስጥ ያካተተ መሆኑን አመልክቷል።

 

የደራሲ ፍሰሃ ያዜ ካሴ ስድስተኛ መጽሃፍ የሆነው “የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2” በያዝነው ሳምንት ለንባብ ቀርቧል።

ደራሲ ፍሰሃ ያዜ ካሴ ከዚህ ቀደም “የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ የሰጠው መጽሃፉ በርካታ ሺህ ቅጂዎች የተሸጡ ሲሆን፤ የዚያው መጽሃፍ ቀጣይ ክፍል የሆነው ይህ መጽሃፍ በኢ-ልቦለድ መልክ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። 360 ገጾች ያሉት ይኸው የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2 ትንሿ ስታዲየም ጀርባ በሚገኘው “ሀሁ” መጽሃፍት መደብር በኩል የሚከፋፈል ሲሆን 121 ብር ከ50 ሳንቲም ደግሞ ለገበያ የቀረበበት ዋጋው ነው።

የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2፤ ኢትዮጵያን በሌሎች አገራት ዐይን እንዴት እንደምትገለጽ፣ የሰለጠኑ አገራት በሀብትና በክብራቸው ዓለምን ከሚዘውሩት በተለይም ጂ 20 ከሚባሉት አንጻር ኢትዮጵያ ያላትን ትውፊት እና ባህል ከሀይማኖት እና ከቀዳሚው ገናና ታሪኳ ጋር እያነጻጸረ ያቀርባል።  

 

ሰምና ወርቅ ሚዲያ እና ኢንተርቴይንመንት የሚያዘጋጀው ወርሃዊው የስነ ጽሁፍና የኪነ ጥበብ ምሽት ነገ ሐሙስ መገናኛ አካባቢ (ከገቢዎችና ጉምሩክ ቢሮ ጀርባ ወይም የቦሌ እና ገርጂ ታክሲ መጫኛ ፊት ለፊት) በሚገኘው አፋረንሲስ ሆቴል ይካሄዳል።

የፕሮግራሙ አዘጋጆች ለሰንደቅ ጋዜጣ በላኩት መግለጫ ለማወቅ እንደተቻለው በዕለቱ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ አርቲስት ደበሽ ተመስገን፣ አርቲስት ሰለሞን ዓለሙ እና ጋዜጠኛ እማዋይሽ ዘውዱ ከወጣት ገጣሚያን ጋር ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል። ዝግጅቱን ለመታደም ለይለፍ ካርዱ 50 ብር የሚያስወጣውን ፕሮግራም አርቲስት አዜብ ወርቁ እንደተለመደው የመድረኩ ፈርጥ ሆና ታመሽበታለች። መሶብ የባህል ባንድ ደግሞ የዝግጅቱ አድማቂ ሆነው ያመሻሉ።

 

ላለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሥርዓተ-መንግስቱ፣ ገዢው ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ አስፈሪና ሀገር በታኝ ሥጋቶች ተደቅነውበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው። አሁን ላይ አንፃራዊ ሽግግር የሚመስል መረጋጋት አዝማሚያ ያላቸው አመላካች ነገሮች እየተስተዋሉ ናቸው። ከሁሉም በላይ እነዚህ ሶስት ዓመታት ክቡር የሆነውን የዜጎች ሕይወትን ቀጥፏል። በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የልማት አውታሮች እንደቀላል ነገር በጠራራ ፀሐይ ወድመዋል።

በሀገራችንም ሳያበቃ በምስራቅ አፍሪካና በዓለም ዓቀፉ ሕብርተሰብ ከነበረው ግዙፉ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ችግር አንፃር ኢትዮጵያ የመበተን እድል እንዳላት ሥጋታቸውን ሲያሰሙ ነበር። በተለይ በቀንዱ ሀገሮች ያሉ መንግስታት ጠንካራ የመንግስትነት መሰረት እንደሌላቸው በስፋት ስለሚታመን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው አለመረጋጋት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለመገመት እንኳን አዳጋች ነበር።

ሌላው በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተቀጣጠለው የለውጥ ፍላጎት የተለያየ ትርጉም እየተሰጠው ባለቤቱም በውል ሳይታወቅ ለያዥ ለገናዥ እስከሚያስቸግር ድረስ የተሄደበት ርቀት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን ለመገመት አስቸጋሪ ነበር። በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያው ሁሉም ተንታኛ በታኝ ሆኖ የተሰለፈበት መስመር ለፖለቲካ ጡዘቱ የነበረው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ሌላው የኢሕአዴግ ድርጅቶች ሊቀመናብርት በጋራ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጡት የልዩነትና የአንድነት መግለጫ፤ የገዢው ፓርቲን ውስጣዊ የፖለቲካ ግለትን ልዩነቶች ነፀብራቅ ነበሩ። እንደሕዝብ “ዋስትና” የሚሰጥም መግለጫ አልነበረም። በርግጥም ለግንባሩ ሊቀመንበር ለመምረጥ የነበረውን መተጋገል ለተመለከተ ሰው፣ ውስጣዊ ቀውሳቸው ሕዝቡን እንደረበሸው አውቀው መጠነኛ ማርከሻ ለማስቀመጥ የሰጡት መግለጫ እንደነበር መረዳት ተችሏል።      

የድርጅቱ ሊቀመንበር የተመረጠበትን አግባብ ፕሮፌሰር መድሐኔ ታደሰ እንዳስቀመጡት፣ “የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት መታየት ያለበት፤ እንደከዚህ ቀደሙ በተባበረ ድምፅ፣ በውስጥ ድርጅታዊ ቀመር ወይም በስምምነት ወይም በሹመት ሁሉም ድርጅቶች ያመጡት አመራር አይደለም፤ በውስጥ ትግል የመጡ አመራር ናቸው። በውስጥ ፍልሚያ ላይ የውጭ ተጽዕኖ ተጨምሮበት ነው። ይህም ሲባል ኦሕዴድ የራሱን የኃይል ማዕከልና መሰረት ተጠቅሞ፣ የሕዝቡን ብሶት ተጠቅሞ፣ ግጭቶቹን ተጠቅሞ፣ በድርጅቱ ውስጥ በፖለቲካና በግምገማ የበላይነት ሳይቀዳጅ እንደውም እያቀረቀረ ቆይቶ፤ በምርጫ አሸንፎ ለስልጣን የበቃ ኃይል ነው። ለዚህም ነው በተለየ መንገድ የተገኘ ስልጣን የሚሆነው። የተለያዩ ታክቲኮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጠቅመው ያገኙት ሥልጣን ነው” ብለዋል።

የፕሮፌሰሩ ገለፃ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አሕመድ በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነውም ተሹመዋል። ይህም ሲባል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፓርቲያቸው አብላጫ ድምጽ የተመረጡ እንጂ በሕዝብ በቀጥታ የተመረጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደሉም። ምክንያቱም በፓርላሜንታዊ የመንግስት ቅርጽ-ሥርዓተ መንግስት፣ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ እንጂ፤ ግለሰብ አይደለም። የሚመረጠውም ፓርቲ እንጂ፤ ግለሰብ አይደለም።

ባልተለመደ መልኩም ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ጫና ውስጥ የወደቀበትን ነባራዊ ሁኔታዎችንም ተመልክተናል። ከገዢው ውስጣዊ ሕገ ደንብ በላይ የገዘፈ የህዝብ ግፊት አስተውለናል። የድርጅቱ ሊቀመንበር ምርጫም ባልተለመደ መልኩ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ አግኝቷል። ከሁሉም በላይ ገዢው የነበረው እውነታ ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲያቸውን አጥር ወይም አሰራር ሕዝቡ ተሻግሮ ዳግም በአደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መቀበሉን አረጋግጧል።

ባልተለመደ መልኩም ኦሕዴድ እና ብአዴን ላይ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው የሕዝባዊ መሰረት ውክልና ጥያቄ በከፍተኛ መጠን ሕዝባዊ መሰረት የያዘበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ከዚህ በፊት ከአራቱ እህት ድርጅቶች የማሕበራዊ መሰረት ጥያቄ የማይቀርብበት የነበረ እና ለሌሎቹም ድርጅቶች ዋስትና የነበረው ሕወሓት መሆኑ አሻሚ አይደለም። ዛሬ ላይ ግን ኢሕአዴግ ከመቼውም የበለጠ ማሕበራዊ መሰረት እንዲኖረው ያስቻለ አጋጣሚ አግኝተዋል።

ከላይ ለመነሻ የቀረቡት ሃተታዎች አጠቃላይ ስዕል ባይሰጡም የተወሰነ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ናቸው። በዚህ ጽሁፍም ከፖለቲካ መተጋገል በኋላ ባገኘናቸው ውጤቶች መነሻ፣ በአብላጫ ድምጽ የድርጅቱን ሊቀመንበር የመረጠው ምክር ቤት በተባበረ ድምጽ ወይም ወደቀድሞ የድርጅቱ ባሕሎች በመመለስ ድርጅቱን እና ሊቀመንበሩን ወደ መቀበል እና የተባበረ ድጋፍ ለማቅረብ ያለው እድል ምን ይመስላል? የሚለውን ለመፈተሸ ነው።

አንዱ፤ ምክንያት በልዩነት ውስጥ የሚቀርብ ድጋፍ ወይም ጥርጣሬ ሊያስከትል የሚችለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ በቅጡ ካልተገነዘቡት፤ ወደ አዲስ የፖለቲካ መተጋገልና ትርምስ ውስጥ ይዟቸው እንደሚገባ ለማወቅ የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አይጠይቅም። የሀገሪቷን የመጨረሻ ስልጣን መቆጣጠር፣ በርግጠኝነት የነበረውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ይቀይረዋል። የሚቀየረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ በመተማመንና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ጨዋታው ወደ አዳኝና ታዳኝ መቀየሩ አይቀሬ ነው።

የአዳኝና የታዳኝ ፖለቲካ ጨዋታ ችግሩ በፖለቲካው ፓርቲ ላይ የሚቀር ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ለሕዝብ ዳግም ያለመተማመን እና የመጠራጠር ምንአልባትም፣ እንደሀገር የመቀጠል ስጋት መደቀኑ ሳይታለም የሚፈታ ነው። ገዢው ፓርቲ ወደቀድሞ የተባበረ ድምጽ መመለስ ከቻለና በተለይ የዶክተር አብይ ሕዝባዊ ድጋፍን የልዩነታቸው መፍቻ ቁልፍ አድርገው ከተጠቀሙበት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ቢደረግ ሁሉም ተገቢነቱን በመቀበል ለውጡን የድርጅቱና የአባላቶቹ አድርጎ ይወስደዋል።

ሁለተኛው፤ ከሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙትን የህዝብ ጥያቄዎች ወደ ፖሊሲ ለመቀየር ገዢው ፓርቲ በተባበረ ድምጽ ውስጥ መገኘት ይጠበቅበታል። ግዙፉ የድርጅትና የመንግስት አጀንዳዎችን ለመቅረጽ ሆነ ለማስፈጸም በልዩነት ውስጥ የተቀመጠ ፓርቲ ሊተገብረው አይችልም። ውጤቱም፣ አብላጫ ድምጽ ያለው ገዢ፤ አናሳ ድምፅ ያለው ተገዢ የሚሆንበት የፖለቲካ መድረክና ቅርጽ ያለው ፓርቲ ይሆናል። በተለይ በውስን የፖለቲካ ፕሮግራሞች የተዋቀረው ኢሕአዴግ ለሁለት የሚሰነጠቅበት እድል ሰፊ ነው የሚሆነው።  

ሶስተኛው፤ ተራማጅ እና በእድሜ የገፉ ኃይሎች የሚመስል በአንዳንድ መድረኮች ሲንፀባረቁ ተሰምተዋል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም በሃምሳዎቹ እድሜ ስልጣን መልቀቅ ሲወደስ፣ የእድሜ ባለጸጎቹ አሁንም በፓርቲው ውስጥ “አልወጣም” ብለዋል በሚል የመድረክ ሽንቆጣ ተደቁሰዋል። ይህ አቀራረብ ከሕዝባዊ ውይይቱ ድጋፍና ሳቅ ተችሮታል። በውስጠ ፓርቲ መተጋገል ውስጥ ሊያስከትል የሚችለው የፖለቲካ ዋጋ በቅጡ ተጢኖ መድረኩ ላይ የተሰነዘረ አይመስልም። ወይም በቀላል አማርኛ ውስጣዊ የፖለቲካ መተጋገሉ “በተራማጅ” እና “በተቸነከሩ” ኃይሎች መካከል አድርጎ የማቅረብ የመድረክ ፖለቲካ ይመስላል። ይህ በራሱ ገዢው ፓርቲ የቀድሞ የፖለቲካ አመራሮችን ከፖለቲካው ውስጣዊ መተጋገል ጋር ብቻ አያይዞ ለማቅረብ መሞከሩ፣ ትርጉሙ ከባድ ነው። ምናልባትም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያምን አስተዋፅዖ ለመግለጽ የነባሩን አመራር አስተዋፅዖ ለማሳነስ መሞከር አደገኛ አካሄድ ነው። አቶ ኃ/ማሪያም በፍላጎታቸው ስልጣናቸውን ስለመልቀቃቸውም ከሚናገሩት ግለሰቦች ውጪ፤ መረጃ የለም። እንዴት እንደለቀቁም “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ።

አራተኛው፤ የፕሮፌሰር መድሃኔን ገልፃ ማቅረቡ ተመራጭ ነው። ይህም ሲባል ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ “የድሮዎቹ አቶ መለስ የነደፏቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አቋሞች በርግጠኝነት እንደነበሩት ይቀጥላሉ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱም በመለስ ውርስና በኢሕአዴግ የሃሳብ አንድነት ላይ ልዩነቶች አሉ። ይኸውም፣ ከብሔር ጥያቄ ይነሳል፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይመጣል፣ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት ሥርዓተ መንግስት ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት የውጭ ዝምድና ሊመጣ ነው? ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊመጣ ነው? የሚሉትን ስንመለከታቸው፤ አንድ አይነት የሃሳብ አንድነትና ስምምነት እንደድሮ ይቀጥላል ማለት አይቻልም። የዶ/ር አብይ ተስፈንጥሮ መውጣት ኢህአዴግን ለድርጅት ማንነት ቀውስ ዳርጐታል። የግድ ማንነቱን ማስተካከል ሊኖርበት ነው።” ብለዋል።

እነዚህ ሥርነቀል የፓርቲ ይዘትና ቅርጽ የሚቀይሩ ጥያቄዎችን በአብላጫ ድምጽ በማግኘት ብቻ የሚታለፉ ተደርገው የሚወሰዱ አይደለም። ምክንያቱም፣ የአፈፃጸም ጥያቄዎች ሳይሆኑ የአራቱም ፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍና ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። የመንግስት ቅርጽን ጭምር የሚቀይሩ ናቸው። ከግንባሩ የመውጣት ውሳኔዎችም ሊያስመዝዙ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው። በምንም መመዘኛ በተባበረ ድምጽ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸው። ስለዚህም፣ አደጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ማግኘት የሚገባው ነው።

ስለዚህም “በአጠቃላይ ሲታይ አዲስ ያልረጋ ጅማሮ ነው የሚመስለኝ። አሁንም የሃሳብ አንድነት፣ የድጋፍ አንድነት ስለሌለ ሁሉም ነገር በቀላሉ ይራመዳል ማለት አይደለም። የተለያዩ የኃይልና የአስተሳሰብ ማዕከላት መኖራቸው አይቀርም። የኃይል ማዕከላት ብዝሃነት እየተፈጠረ ነው። በመንግስት ስልጣን ውስጥም የአመለካከትና የኃይል አሰላለፉ ማዕከሎች መኖራቸው አይቀርም። አሁን ያለው ሽግግር ጅማሮ ነው እንጂ በደንብ ድጋፍ ያገኘ መሰረቱ የጠነከረ ለውጥ ነውም ማለት አይቻልም። በመገዳደር የመጣ የለውጥ ጅማሮ ነው ካልን፣ ለውጡ ሊዘልቅ የሚችለው በትግል (Political Contestation) ነው ማለት ነው። ለውጡን ተከትሎ ያለው የኃይል ዝምድና የተለያዩ የኃይል ማዕከላት እርስ በእርሳቸው የሚገዳደሩበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። እንደቀድሞ ከላይ እስከታች በቁጥጥር ስርዓትና አመለካከት ጥራት፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ ድርጅቱን ቀጥ አድርገህ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እያየህ የሚጓዙበት ሁኔታ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አይኖርም” ሲሉ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በፖለቲካ ትንተናቸው አስቀምጠውታል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤቱ፣ ለድርጅታቸውና ለመንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ሕዝቡ ከሰጣቸው ቅቡልነት አንፃር ቀጣይ ጉዟቸውን ፈጥነው ወደ ተባበረ ድምጽ ገብተው ፓርቲውን ለማዳን ካልሰሩ፣ ከሆነው ያልሆነው ይበልጣል ብለው የሚሰጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጣም ብዙ ናቸው። አበው እንደሚሉት፣ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ…።¾

ክፍል ፖለቲካ

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህር ዳር ሲገቡ በመከላከያ እና በፖሊስ ኃይሎች አጥረው አስቀመጡን”

አቶ አበባው ጌትነት

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ

የአማራ ተወላጆች ተወካይ

 

በይርጋ አበበ

 

527 አባውራዎች ከእነ ሙሉ ቤተሰባቸው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ያቀኑ ሲሆን አሁንም ድረስ ጉዳያቸውን መፍትሔ የሚሰጥ እንዳላገኙ ይናገራሉ። በቅርቡ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ከአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የተቀበሉት ዶክተር አብይ አህመድ በሹመታቸው ዕለት ለኢትዮጵያ ህዝብ የገቡት ቃል ኪዳን፣ “ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በመረጡት የአገራችን ክፍል ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው ሊከበር ይገባል፤ ከዚህ በኋላ መፈናቀል አይኖርም” የሚል ነበር። በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በተፈጠረ “የአመራሮች ግጭት” ከመቶዎች በላይ ህዝብ የተፈናቀለ ሲሆን ዶክተር አብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ ወደ ሶማሌ ክልል መቀመጫ አቅንተው ከክልሉ ባለስልጣናትና “የተመረጡ ታዳሚዎች”ጋር ባካሄዱት ውይይት እንገለፁት “የተፈናቀሉትን የኦሮሚያ ተወላጆች በክልላችን ለማስፈር ሞክረን ነበር። ነገር ግን የሚቻል አልሆነም ምክንያቱም የሰዎቹ ፍላትና ስነ ልቦና ከሶማሌ ክልል ወንድም እና እህቶቹ ጋር በጣም የተዋሀደ በመሆኑ ነው” በማለት የተፈናቀሉት ወደነበሩበት ቀዬ እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መፈናቀል ይቅር የተፈናቀሉትም በአስቸኳይ ወደ ቀደመ ቀያቸው ይመለሱ” ብለው ማሳሰባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ተመሳሳይ ችግሮች አሉብን ያሉ ከአማራ ክልል ሌላ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ለሰንደቅ ጋዜጣ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ከኖሩበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መሰደዳቸውን ይናገራሉ። ሆኖም በዚያ አካባቢ ለመቆየት የሚያስችል ምንም ነገር ስላነበረ ወደ ባህር ዳር ማቅናታቸውንና በባህር ዳርም በተለምዶ “አባይ ማዶ” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን (ቅዱስ ገብርኤል) ተጠልለው እንደሚኖሩ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ “ጉዳያችንን መንግስት እንዲያይልን ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአካልም በደብዳቤም አቅርበን ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ይናገራሉ። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉትን ወገኖች ቅሬታን በመወከል ለሰንደቅ ጋዜጣ ያቀረቡት አቶ አበባው ጌትነት የተባሉ የተፈናቃዮች ተወካይ ናቸው። ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ቃለ-ምልልሱን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅላችሁ እንደመጣችሁ ገልጸውልናል። ለመሆኑ ስንት ሰዎች ናችሁ የተፈናቀላችሁት? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛላችሁ?

አቶ አበባው፡- ህጻናትንና ሙሉ የቤተሰብ አባላትን ሳይጨምር አባውራዎች ብቻ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለን የመጣነው ሰዎች ቁጥራችን 527 ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። የንብረት ባለቤት የነበርን ትጉህ አርሶ አደሮች ዛሬ የዕለት ምግብ ለማግኘት የሰው እጅ እያየን ነው የምናድረው። በአንድ ግቢ ውስጥ ተሰብስበን ውለን የምናድር ሲሆን በታጣቂ ነው የምንጠበቀው። ከአካባቢው ውጡ ተብለን ብዙ ጊዜ ወከባ ሲደርስብን ቆይቷል። አሁን አንተን ከማናገሬ በፊትም እኔን ጨምሮ ስምንት የተፈናቃዮች ተወካይ አስተባባሪዎችን ባህር ዳር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረውን አድረው ነው የተፈታነው። ለጊዜው የምንገኘው ባህር ዳር አባይ ማዶ ከሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እያደርን ያለነው። ከዚያ እንዳናድርም የባህር ዳር ኮማንድ ፖስት የቤተክርሰቲያኑን አስተዳዳሪዎች ሳይቀር ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ቤተክርስቲያኗ ግን እስካሁን ፊቷን አላጠቆረችብንም።

ሰንደቅ፡- ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሄዳችሁ ሰዎች ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ችግር ይደርስባችሁ እንደነበረ እና ተመሳሳይ መፈናቀል ደርሶባችሁ ነበር ይባላል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ አበባው፡- የተባለው ትክክል ነው። እኔ ለምሳሌ እኖርበት በነበረው ከማሺ ዞን ጅጋፎ ወረዳ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰትና በእኩልነት አለመዳኘት ችግር ይደርስብን ነበር። ለምሳሌ ፍርድ ቤት ሄደህ ርትዕ ፍርድ ማግኘት አይታሰብም፤ በአመራሮች የመበደል እና ሌሎች የመብት ጥሰቶችም ይደርሱብናል። ከዚህ በፊትም በ1995 እና 2003 ዓ.ም ተፈናቅለን ነበር። በ1995 ዓ.ም ስንፈናቀል በኦሮሚያ ክልል ተጠግተን ከቆየን በኋላ ተመልሰን ወደ መኖሪያ ቀያችን ገባን። እንደገና በ2003 ዓ.ም በተፈጠረ ግጭት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደን ተጠግተን ከቆየን በኋላ ተመለስን። በሁለቱም ጊዜ በደረሰብን መፈናቀል ንብረቶቻችን ሙሉ በሙሉ ወድመውብናል ከውድመት የተረፈውንም ተዘርፈናል። በተለይ በ2003 ዓ.ም በአንድ ወረዳ ይኖር የነበረ 8 ሺህ ህዝብ ነበር የተፈናቀለውና ንብረቱም ቤቱም የወደመበት።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ መፈናቀል ከተፈጠረ በኋላ በሁለቱ ክልል አመራች መካከል ውይይት በማካሄድ መፍትሔ አልተቀመጠም ነበር?

አቶ አበባው፡- በ2003 ዓ.ም በነበረው መፈናቀል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዙ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ነብሳቸውን ይማርና አቶ አህመድ ናስር ሁለቱ ኃላፊዎች ተናበቡና ‹‹የተፈናቀሉት ሰዎች በሙሉ ከእኔ ክልል ከሆነ የተፈናቀሉት ማረጋገጫ ካላቸው እንደገና ወደነበሩበት ቀየ ተመልሰው እንዲሰፍሩ አደርጋለሁ›› ሲሉ አቶ አህመድ ናስር ቃል መግባታቸው የሚታወቅ ነው። በዛን ጊዜ የነበሩት አስመላሽ ኮሚቴ አሁን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰማ ጥሩነህ አስተባባሪነት ወደ ቦታው እንድንመለስ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን የአማራ ክልል መንግስት ተመልሰን የሰፈርነውን ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳለን ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልነበረም። ይህን ባለማድረጉ ደግሞ ሁልጊዜም በእኛ ላይ የመብትና የነጻነት ጥቃት የሚፈጽሙብን የአካባቢው ባለስልጣናት ጫና ይበልጥ በረታብን። ያላግባብ እና ያለ ደረሰኝ የመሬት ግብር ክፈሉ እንባላለን፤ እኛም ለመኖር ስንል እንከፍላለን። በአጠቃላይ በአገራችን እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረን ነው ስንኖር የቆየነው።

ሰንደቅ፡- በዚህ ዓመት ደግሞ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው ከአካባቢው የተፈናቀላችሁት። የአሁኑ ችግር መነሻ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ አበባው፡- በሁለት ወጣቶች መካከል ግጭት ተፈጠረ። ግጭቱ የተፈጠረው ከአንድ የክልሉ ተወላጅ እና ከአማራ ክልል በሄደ ወጣት መካከል ነበር። በግጭቱም የቤኒሻንጉል ጉሙዙ ተወላጅ ይሞታል። ግጭቱ የተነሳው በተራ ውንብድና ቢሆንም ወደ ጎሰኝነት ቀይረው ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ቀኑን ሙሉ ግጭቱ እና ማሳደዱ በረታ። በዚህ ሂደት ውስጥም 14 ሰዎች ሲሞቱ የዘጠኙ ስርዓተ ቀብር ተፈጽሞላቸዋል፤ የአራቱ ግን አስከሬናቸው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ስለገባ ሊገኙ አልቻሉም ነበር። እኔ ባለኝ መረጃ 139 ቤቶች ሲቃጠሉ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

እንደምታውቀው ጥቅምት ወር አዝመራ የሚደርስበት ወቅት ቢሆንም ዓመቱን ሙሉ የደከምንበት ሰብል (አኩሪ አትር፣ ሰሊጥ፣ ቦቆሎ…..) ሳይሰበሰብ ሜዳ ላይ ቀርቷል። የነገርኩህ 527 አባውራዎች ከነሙሉ ቤተሰባቸው ምንም ንብረትና ሀብት ሳይዙ ህይወቱን ለማትረፍ ሊፈናቀሉ ችሏል።

ሰንደቅ፡- መፈናቀሉ ከደረሰ በኋላ ወደ አማራ ክልል አምርታችሁ ምን አደረጋችሁ?

አቶ አበባው፡- እንደነገርኩህ ነብሳችንን ለማረፍ ማቄን ጨርቄን ሳንል ከመኖሪያ ቀያችን የተፈናቀልን ሰዎች ወደ አማራ ክልል ሄድን። በአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ሜካናይዜሽን ጎንደር ቅርንጫፍ በመሰባሰብ ከመንግስት ተገቢውን እርዳታ እና የሰፈራ ፕሮግራም እንድናገኝ ጠይቀን ነበር። በዋናነት እኛ አስተባባሪዎች የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለምን እና ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ያነጋገርናቸው። አቶ ገዱን ስናነጋግራቸው “የእናንተ ጉዳይ የሚፈታውም ሆነ መኖር የምትችሉት ክልል ስድስት (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል) ስለሆነ በድጋሚ ሄዳችሁ እንድትሰፍሩ ነው የሚደረገው” ሲሉ መልስ ሰጡን። እኛም በበኩላችን ወደነበርንበት ክልል ተመልሰን እንደማንሄድ አጥብቀን ተከራከርን። ምክያቱም በተደጋጋሚ መፈናቀልና ግጭት ሲደርስብን ስለቆየ አሁንም ዋስትና በሌለው መልኩ ልንመለስ አይገባም” ብለን ስንነግራቸው እሳቸውም መልሰው፤ “ወደ ነበራችሁበት ክልል የማትሄዱ ከሆነ ወደተወለዳችሁበት ቀየ መሄድ ትችላላችሁ እንጂ ከመንግስት ምንም አይነት እርዳታ ልታገኙ አትችሉም። ምክንያቱም ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይገኛል፡ ይህን ሁሉ ህዝብ ተፈናቅሎ በመጣ ቁጥር አስፍረን ማኖር አንችልም። ስለዚህ ሊሆን የሚገባው ወደነበራችሁበት ክልል ተመልሳችሁ እንድትኖሩ እንጂ እርዳታ ማቅረብም ሆነ ማስፈር አንችልም። ልትጠይቁ የምትችሉትም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን እንጂ እኔን አይደለም ምክንያቱም እናንተን አላውቃችሁም›› አሉን።

በዚህ ንግግራቸው በጣም ነው የተከፋነው። ምክንያቱም ኑሯችን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይሁን እንጂ ባለንበት ክልል ሰርተን ከምናፈራው ሀብት ላይ በተቋቋመ ኮሚቴና ጽ/ቤት በኩል ለአልማ (አማራ አቀፍ ልማት ማህበር) እና ለብአዴን (ለብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) በየዓመቱ ገንዘብ ስናዋጣ የኖርን ሰዎች ነን። ይህ ለእኛ የደህንነት ዋስትና ሊሆን አይገባም ወይ? ብለን ጥያቄም አቅርበንላቸው የነበረ ቢሆንም መልስም ሳይሰጡንና ንግግራችንንም በወጉ ሳያዳምጡን ‹‹ስብሰባ አለብኝ›› ብለውን ትተውን ገቡ።

ሰንደቅ፡- በእሳቸው ንግግር መሰረት ወደ ወላጆቻችሁ ቀየ ሄዳችሁ ለመኖር አልሞከራችሁም? ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንመለስም ያላችሁበት ምክንያትስ ምንድን ነው?

አቶ አበባው፡- አቶ ገዱ መልስ በኋላ ወደ ነበርንበት ሰፈር ሄደን ከባህር ዳር ህዝብ ጋር ተቀላቅለን በተቀመጥንበት በኮማንድ ፖስት የታገዘ ሀይል ወዳለንበት ቦታ በመምጣት ‹‹ከአቶ ገዱ መልስ ተሰጥቷችኋል፤ ስለዚህ ወይ ወደነበራችሁበት ክልል ሂዱ ወይም ደግሞ ወደ ወላጆቻችሁ ቀየ ተበተኑ›› ነበር ያሉን። ለምሳሌ እኔ ትውልድ ቀየዬን ለቅቄ ከወጣሁ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖኛል። ሌሎቹም ከእኔ በላይ ለሆነ ጊዜ ከትውልድ ቀያቸው ተለይተው የኖሩ ናቸው። ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ወደማናውቀው የወላጆቻችን አገር ሄደን የምንሰፍረው? የአካባቢው አስተዳዳሪዎች አያውቁን፤ ለመኖሪያ የሚሆን መሬት በሌለበት ሁኔታ ምን ሰርተን ልንኖር ነው የምንሄደው? ብለን መልስ ሰጠናቸው። በነገራችን ላይ አንዳንዶቻችን ቤተሰቦቻችን እንኳን አያውቁንም።

የኮማንድ ፖስቱ እና የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች በሰጠናቸው ምላሽ ተበሳጭተው “በፈቃዳችሁ የማትሄዱ ከሆነ ተገዳችሁ እንድትሄዱ ትደረጋላችሁ” ብለው ለማስፈራራት ሞከሩ። እኛም የፈለጋችሁትን አምጡ እንጂ ለጥያቄያችን መልስ ሳናገኝ ከዚህ ወደየትም አንሄድም ብለን በአቋማችን ጸናን። በዚህ ጊዜ የተፈናቃዮቹን ስምንት አስተባባሪዎች ጠርተው “የምግብ ዋስትና ኃላፊ በምግብ ጉዳይ ሊያነጋግራችሁ ይፈልጋል” ብለው ጠሩንና አፍነው ወስደው ባህር ዳር ከተማ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አሰሩን። ለአንድ ቀን ካሰሩን በኋላ አስፈራርተውና አስፈርመው ፈቱን። ነገር ግን ከተፈታን በኋላ የባህር ዳር አካባቢ ኮማንድ ፖስት አዛዥ አቶ ገደፋው መጥተው ከሰፈርንበት አካባቢ (ምግብ ዋስትና ጎንደር ቅርንጫፍ ግቢ) እንድንነሳ አደረጉን። ከዚያም ማደሪያ ስናጣ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሄደን የደብሩን አስተዳዳሪ ጠይቀን እዚያ እንድናድር ፈቅደውልን አደርን። ነገር ግን አሁንም ቤተ የክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እኛን ከደብሩ ለተጨማሪ ጊዜ እንዳያሳድሩ ጫና እና ትዕዛዝ ሰጥተዋቸው ስለነበር ለተጨማሪ ቀን እንዳናድር ተደረገ። ከዚያም ወደ ምግብ ዋስትና ግቢ ሄደን ስንሰፍር በፓትሮል መኪና የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እያመጡ ሲያስፈራሩን ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ግቢው ውስጥ እንድናድር እንዲፈቅዱልን ልመና አቅርበን ፈቃደኛ ስለሆኑልን እዛው ነው ያለነው።

ወደ ሁለተኛው ጥያቄህ ልምጣልህና ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመመለስ የማንፈልግበት ምክንያት አንደኛ ነጻነታችን ሁልጊዜም እየተረገጠ ነው የምንኖረው፤ ከዚያም አልፎ የንብረት ውድመት ስለደረሰብን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በሞት ያጣን ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ። እንደዚህ እየሆንን በዚያ ቦታ መኖር አንችልም ምክንያቱም የክልላችን መንግስት (የአማራ ክልል ማለታቸው ነው) ለእኛ ደህንነት ሊከራከርልንና መብታችንን ሊያስጠብቅልን አልቻለም። ለዚህ ነው ወደዛ አንሄድም ብለን አቋም የወሰድነው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት በእናንተ ላይ ‹‹ደን ይመነጥራሉ፣ ጦረኛ ናቸው እና በአካባቢው ተወላጅ ላይ ስድብ ይሰነዝራሉ›› የሚል የሚቀርብባችሁ ውንጀላ ነበር። ለመሆኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስትኖሩ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ያላችሁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ አበባው፡- አንተ ያልከውን ውንጀላ አውቀዋለሁ፣ እንዳልከው ከዚህ በፊት የተነገረ ነው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ሀሰትና በሬ ወለደ ወሬ ነው። ይህን የሚሉት ለክስ እና ለአንዳንድ ነገር ማጭበርበሪያ እንዲመቻቸው ነው። በእርግጥ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ስንኖር በተለያየ መንገድ ተከባብረን የምንኖር ሰዎች ነበርን። ጫና የሚደረግብን ከአመራሩ ነው። አሁንም ይህ ችግር የደረሰብን የወረዳው አመራር እስከ ታች ድረስ ያለው ካቢኔ ህዝቡን በመቀስቀስ ነው እርምጃ እንዲወሰድብን ያደረጉት። ስለዚህ እኛ እንኳን ስድብ ልንሳደብ ይቅርና ከመጥረቢያ፣ ማጭድና የመሳሰሉት የእርሻ መሳሪያዎች በስተቀር ማንኛውንም ነገር (ዱላም ሆነ የጦር መሳሪያ) ይዘን መንቀሳቀስ አንችልም። በመንግስት የስራ ኃላፊነት በኩልም ካየን ከእኛ ከአማራውም ሆነ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች እና ከሌሎቹ ብሔረሰብ የተወለደ ሰው ስልጣን ላይ የለም። ሁሉንም የመንግስት ኃላፊነት የያዙት የክልሉ ተወላጆች ብቻ ናቸው።

ደን ጨፈጨፉ ለሚለው ጥያቄህ ስመልስልህ፤ ደኑን የሚጨፈጭፉት የዚያው የክልሉ ተወላጆች ናቸው። መሬቱ በእነሱ እጅ እንጂ እኛ የምናርሰውን መሬት ሙሉ በሙሉ የምናገኘው ከእነሱ በኪራይ እና በአበል እየተኮናተርን ነው። ስለዚህ የመሬት ባለቤት ባለመሆናችን በዚህ ጉዳይ ልንወቀስ አይገባንም።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትነት ስልጣን ሲወጡ “ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው በመረጡት አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመስራትና የመኖር መብታቸው ሊከበር ይገባል፤ መፈናቀልም ይቁም” ሲሉ ተናግረው ነበር። እናንተ አሁን ካላችሁበት ሁኔታ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለችግራችሁ መፍትሔ አመላካች አይሆንም ይላሉ? ንግግሩንስ እንዴት አዩት?

አቶ አበባው፡- እኔ ይህንን ንግግር የተመለከትኩት ለመድረክ የፕሮፓጋዳ ፍጆታ እንጂ ይፈጸማል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ዶክተር አብይ ባህር ዳር በመጡ ሰዓት እኛ እዚያው ነበርን። ከእሳቸው ጋር እንዳንነጋገር ሆን ተብሎ ገና ሊመጡ አንድ ቀን ሲቀራቸው ጀምሮ የምንኖርበት አካባቢ በፖሊስና በመከላከያ ታጥሮ ከእሳቸው ጋር እንዳንገናኝ መብታችን ተነፍጎ ነበር። ከባህር ዳሩ ጉዞ ውጭም እኔ የተፈናቃዮቹን ጉዳይ ይዤ ጽ/ቤታቸው ድረስ በመሄድ በዝርዝር ጽፌ አስገብቼ ነበር። ስደውል የሚሰጠኝ ምላሽ ግን እስካሁን አልታየም ሲያዩት መልሱን ደውለን እናሰውቅሃለን የሚል ነው። እና እሳቸው የተናገሩት ነገር ተግባራዊ የሚሆን ቢሆን ኖሮ ይህ የእኛ ጉዳይ እስካሁን ሳይዘገይ ታይቶ መልስ ይሰጠን ነበር። ለዚህ ነው ተግባራዊ ይሆናል ብዬ እምነት ያልጣልኩበት።

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እኔ አላውቃችሁም ብለውናል ሲሉ ነግረውናል። እናንተ ደግሞ ከክልላችን ውጭ ብንኖርም የአማራ ክልልን መንግስት ልማት በመደገፍ በኩል የድርሻችንን ስንወጣ ቆይተናል ብላችኋል። ስለዚህ እናንተ ከስርዓቱ ጋር ችግር የለባችሁም ማለት ይቻላል?

አቶ ጌትነት፡- ከመንግስት ጋር የፖለቲካ ችግርም ሆነ ልዩነት የለንም። እኛ ትግላችን ከድህነት እና ከርሃብ ጋር እንጂ ከመንግስት ጋር በፖለቲካ ጉዳይ አንነካካም። ምክንያቱም የኢህአዴግ መንግስት ደጋፊ እና የብአዴን አባል ነን። ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በላይ ለብአዴን የገበርንበት ደረሰኝ አለን። ለአልማ ገንዘብ እናዋጣለን። ብአዴን ለሚሰራቸው የክልሉ ልማቶች የማናዋጣው ገንዘብ የለም። ስለዚህ ይህን ሁሉ ስራ የምንሰራው ከብአዴን ጋር ሆኖ ሳለ የፖለቲካ ልዩነትና ችግር አለባችሁ የሚለውን አልቀበለውም። የመብት ጥሰትና ችግራችንን አድምጦ መፍትሔ የሚሰጠን አጣን ነው እያልን ያለነው። ይህን ችግራችንን ደግሞ ብአዴንም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አይተው መፍትሔ እንዲሰጡን ነው የምንጠይቀው። የባህር ዳር እና አካባቢው ህዝብም ለዕለት ችግራችን የሚችለውን እንዲያደርግልን በአጽኦት እጠይቃሁ።

ክፍል ፖለቲካ

 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን የ2006 - 2008 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ሚያዚያ 10 ቀን 2010 ዓ.ም አካሄደ። ተቋሙ በኦዲት በተሰጡ አስተያቶች መሰረት መሠረታዊ የሚባል የማሻሻያ እርምጃ እንዳልወሰደ በስብሰባው ላይ ተጠቁሟል።


በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ በተሠጠው ሥልጣን መሠረት የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ደንብና መመሪያውን አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው ደንብና መመሪያው በረቂቅ ደረጃ ከማዘጋጀት ያለፈ አፀድቆ ተግባራዊ አለመደረጉ፤ የኢነርጂ ብቃት መፈተሻ ሥርዓት እንዳልተዘረጋ፤ የኢነርጂ ብቃት መፈተሻ ላብራቶሪዎችም እንዳልተቋቋሙ መረጋገጡንና በዚህም ምክንያት ብቃት ያላቸውና የሌላቸውን የኢነርጂ መጠቀሚያ መሣሪያዎች እና የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ተለይተው እንዳይታወቁ ከማድረጉም በላይ ወጭ ቆጣቢና ኃይል ቆጣቢ የሆኑትን ለይቶ ሥራ ላይ እንዳላዋለ ተገልጿል።


ባለሥልጣን መ/ቤቱ ለኢነርጂ መጠቀሚያና ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች የአጠቃቀም ደረጃ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው በጅምር ደረጃ እንጂ በተጨባጭ አስገዳጅ የአጠቃቀም ደረጃ ባለመውጣቱ በገበያ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ምርትና የቴክኖሎጂዎች የአጠቃቀም ደረጃቸው እንዳይታወቅ ማድረጉን፣ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና የሌላቸውን ለይቶ ለማወቅ እና ኢነርጂ ቆጣቢ የሆኑ መሣሪያዎችን ለማበረታታትና ድጋፍ ለማደረግ እንዳልተቻለ ተመልክቷል።


በአገሪቱ ውስጥ ኤሌክትሪክ በማመንጨት፣ በማስተላለፍ በማከፋፈል እና በመሸጥ ሥራ ላይ ለተሰማሩ የፈቃድ አሰጣጥ የአሠራር ሥርዓት በሚገባው ደረጃ አለመሠራቱ በዘርፉ ለመሠማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶችና ባለሙያዎች ችግር የሚፈጥርና የኢነርጂ ዘርፍ እንዳያድግ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረጉ፤ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች የቁጥጥርና ክትትል ሥራ በመሥራት የኢነርጂ አጠቃቀማቸው የተሻለ እንዲሆንና ብቃት ያላቸውን የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ያለመሠራቱ እንዲሁም የኢነርጂ ተጠቃሚዎች ኃይል ቆጣቢ ያልሆኑና ብቃት የሌላቸው ማሽነሪዎች፣ መሣሪያዎች፣ ጀነሬተሮች እንዲሁም አምፑሎች እንዲጠቀሙ እና ኢነርጂው እንዲባክን መደረጉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል።


ባለሥልጣን መ/ቤቱ የሀገሪቱ የኢነርጂ ፍላጎት፣ የተመረተ፣ ጥቅም ላይ የዋለ፣ እና ያልዋለ የኢነርጂ መጠን ለይቶ ማወቁን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ተግባራዊ አለመሆኑንና በዚህም ምክንያት መቆጠብ የሚገባን የኢነርጂ መጠን እንዳይቆጥብ እንቅፋት መሆኑ እና ጥቅም ላይ የዋለና ያልዋለ የኢነርጂ መጠን መረጃዎችንም በመተንተን ውጤቱን ለስትራቴጂክ እና ፖሊሲ ውሳኔ ግብዓት እንዲሆን አለመደረጉ እና ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚ አካላት የኢነርጂ አጠቃቀም ዕቅድና መርሀ-ግብር እንዲያወጡና አፈፃፀማቸውንም ሪፖርት እንዲያደርጉለት ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ አለማድረጉ፤ የሚቀርብለትን የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከመርሃ-ግብር አንፃር ገምግሞ ውጤቱን ለሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ አካላት ማሳወቅ ቢገባውም ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች የፈቃደኝነት ስምምነቱን ያልፈረሙ በመሆኑ የኢነርጂ አጠቃቀም ዕቅድና መርሃ ግብር እንደማያዘጋጅና በዕቅዱ መሠረት ግምገማ ውጤታቸውንም ለሚመለከተው አካል እንደማያሳውቅ ተገልጿል።


በናሙና ተመርጠው ከታዩ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚ ፋብሪካዎች፣ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች እና ሆስፒታሎች የተደረገላቸው የቴክኒክና ፋይናንስ ድጋፍ እንደሌለ እንዲሁም ኃይል አባካኝ የሆኑ የኢነርጂ መጠቀሚያ ቴክኖሎጂዎች በኃይል ቆጣቢ ለመተካት የመግዛት አቅም የሌላቸው ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ እንዳይኖራቸው ክፍተት ከመፈጠሩም በላይ ለአላስፈላጊ ወጪ እንዲዳረጉና ተቋሞቹ መቆጠብ የሚገባቸውን የኢነርጂ መጠን እንዳይቆጥቡ እንዳደረጋቸው እንዲሁም የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባን በሚመለከትም የሚነሱ ቅሬታዎች አፈታት ሥርዓት ያልዘረጋ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተገልፆ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ የተሠጠውን ተግባርና ኃላፊነት እንዳይወጣ ያደረገውን ምክንያት እንዲያስረዳ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄውን አቅርቧል።


አቶ ጌታሁን ሞገስ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ደንብና መመሪያ ያልወጣው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ የማመንጨት ፍላጎት በግል ባለሃብቱ በመነሳቱና ተያይዞም የፈቃድ አሠጣጥ ጥያቄዎች በመምጣቸው የአዋጅ ማሻሻያ ጥያቄ ቀርቦ ለምክርቤቱ መላኩንና አወጁ ሲፀድቅ ደንቡም ተያይዞ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ ደንቡ በሚፈለገው ጊዜ አለመፅደቅ በርካታ ጉዳዮችን በወቅቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንዳላስቻላቸው፤ ላብራቶሪዎችን በተመለከተ የ2006 አዋጅን ተከትሎ ተፈፃሚ ለማድረግ መዋቅራዊ ማስተካከያ የሚፈልጉ በመሆኑ ለመተግበር መቸገራቸውን ነገር ግን የተለያዩ የላብራቶሪ እቃዎች ግዥዎችን የመፈፀም ሂደት ላይ እንደሚገኙ፤ አስገዳጅ የአጠቃቀም ደረጃን በተመለከተም በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ፕሮግራም ውስጥ ሁሉንም እቃ ማስገባት እንደማይችሉ ገልፀው በዋናነት የእንጀራ ምጣድ፣ ምድጃ እና ኢንዱስቲሪያል ሞተሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ለማውጣት የምርት ማኑዋል ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።


የፈቃድ አሠጣጥ በተመለከተም በአዲሱ አዋጅ ውስጥ ያለና ደንቡ ያልፀደቀ በመሆኑ ተግባራዊ አለመደረጉን፤ ከፍተኛ የኢነርጂ ተጠቃሚዎች ብቃት ያለቸውን ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ከማድረግ አኳያ የ2006 አዋጅ ቅጣትንም የሚደነግግ ቢሆንም በቀጥታ ተግባራዊ ለማደረግ ደንቡ ባለመፅደቁ ተፈፃሚ ለማድረግ እንደተቸገሩና በዋናነትም ከቅጣት ይልቅ በማግባባትና በስምምነት ሊሠሩ የሚችሉ እንደዝርዝር እና ዎክሥሩ /walkthrough/ ኦዲት ያሉ መንገዶችን በመጠቀም የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ፤ በቁጠባ በኩልም ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ቢጠቀሙ ኢንዱስትሪው አዋጭ መሆኑን የማስተማር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ፤ የኢነርጂ አጠቃቀም የፈቃደኝነት ስምምነትን በተመለከተም ሥልጠና መሰጠቱን፣ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱንና በሰነዱ ላይ አንድ ዙር ምክክር ካደረጉ በኋላ ወደመፈራረም ሥርዓት እንደሚገቡ፤ በኢነርጂ ፈንድ በኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ለሚሣተፉ የኢነርጂ ተጠቃሚ ተቋማት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር አሠራር ለመዘርጋት መመሪያና ሌሎች ስታንዳርዶች መጽደቅ ጋር ምላሽ የሚያገኙ መሆናቸውን እና የቅሬታ አፈታት ሥርዓትም ደንብና መመሪያን ተከትሎ ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን አቶ ጌታሁን አስረድተዋል።


የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተሰጡት ምላሾች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችንና ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሰጡ ሲሆን በዋናነት በተቋሙ ላይ ኦዲቱ የተደረገው ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም ተቋሙ አስካሁም ምንም እርምጃ አለመውሰዱ ለኦዲት ግኝቱ ትኩረት አለመስጠቱን እንደሚያሳይ፤ ደንብና መመሪያ የማያስፈልጋቸው ሥራዎችም ደንብ አልወጣም በሚል ምክንያት አለመሰራታቸውን፤ ከፍተሻ ላብራቶሪ ጋር በተያያዘም ተቋሙ አጥጋቢ ምላሽ አለመሠጠቱን ገልፀው ደንብና መመሪያ ለማፀደቅ ረጅም ጊዜ ተቋሙ የወሰደበትን ምክንያት ለተከበረው ምክር ቤት ማብራሪያ እንዲሠጡ ተጠይቀዋል።


በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት ወልደሃና (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ በተቋሙ የአቅም ውስንነት መኖሩን እና ያለውን የአቅም ውስንነት ለመቅረፍ አቅም የማጎልበት ከፍተኛ ሥራ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቀጣይ እንደሚሠራ ገልፀዋል።


ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ተቋሙ የኢነርጂ ብቃት መፈተሸ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ፤ የኢነርጂ ብቃት ማረጋገጫ ኮዶች ተግባረዊ ማድረግ እንዳለበት፤ ከፍተኛ ኢነርጂ በሚጠቀሙ ተቋማት ላይ ኢነርጂ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ፤ የኢነርጂ ውጤታማነት ጋር በተያያዘ የቁጥጥርና የክትትል ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፤ መ/ቤቱ በአገሪቱ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውንና የሌለውን ኢነርጂ ሊያውቅ እንደሚገባ እና የኢነርጂ መጠቀሚያ ቴክኖሎጂዎች ገበያ ላይ ከመዋላቸው በፊት ፍተሻ ሊደረግልቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።


አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ደንቡን መ/ቤቱ በወቅቱ አለማዘጋጀቱንና የውሃ፣ መስኖና ኤሊክትሪክ ሚኒስቴርም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ 2006 ዓ.ም የወጣው አዋጅ እንደገና የሚሻሻል ከሆነ ደንቡም ጎን ለጎን ተሻሽሎ የማቅረቡ ሥራ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ፤ የመፈተሻ ለብራቶሪ ግንባታ ደንቡ ባይወጣም ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባረዊ ሊደረግ እንደሚገባ፤ የአስገዳጅ ደረጃን ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችለውን መመሪያም ደንቡ ፀድቆ እንደወጣ በቶሎ ወደተግባር መግባት በሚያስችል ደረጃ ተዘጋጅቶ ሊቀመጥ እንደሚያስፈልግ እና የኢነርጂ ፈቃድ ቁጠባ የሚነሱ ቅሬታዎች መቅረፍ የሚያስችል የቅሬታ አፈታት ሥርዓትም ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል።


ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት በኦዲት አስተያየት ላይ መሠረታዊ የሚባል የማሻሻያ እርምጃ አለመውሰዱን፤ ደንብ የማያስፈልጋቸውና ደንብ ባይወጣም ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች በአግባቡ ተለይተው አገልግሎት ሊሰጥና የኢነርጂ ብቃት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው ሊሠሩ እንደሚገባ፤ ቅንጅታዊ አሠራር ከምርምርና ቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና የቅሬታ አፈታት ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ሊዘረጋ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ያገኘነው ዘገባ ያስረዳል። 

 


ክፍል ወቅታዊ
Wednesday, 02 May 2018 12:54

ከዳቦ አቅም ፈተና ሆኗል

 

የዳቦ ዋጋ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። በዚያ ላይ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ዳቦ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። እንደ እድል ሆኖ ዳቦውን ማግኘት ከተቻለም ትንሹ የአንድ ዳቦ ዋጋ ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሆኗል። ቀድሞ በ1 ብር ከ30 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ባለመቶ ግራም ዳቦ አሁን በ2 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ ነው። ዋጋው በዚህ መልኩ በአንድ ጊዜ ሊንር የቻለበትን ምክንያት ስንጠይቃቸው ነጋዴዎቹ የሚሰጡት ምላሽ ዱቄት ጠፍቷል የሚል ነው። አማራጭ ስለሌለን በተባለው ዋጋ ለመግዛት ተገደናል። ነጋዴው የሚለውን መቀበል እንጂ ሌላ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው። ሰሞኑን ደግሞ መንግስት የዳቦ ዋጋው ሊጨምር የቻለው ከውጭ የሚገባው ስንዴ በተፈጠረ ችግር ምክንያት በተባለው ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ባለመቻሉ ነው የሚል መረጃን እየለቀቀ ይገኛል። መረጃው ከመዘግየቱም በላይ ለነጋዴው ማበረታቻ እየሆነው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለአንድ ሀገር ህዝብ መሠረታዊ ፍጆታ የሆነው ዳቦ ጉዳይ ምንም አይነት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። አንዱ አማራጭ ባይሳካ ሌላ ብዙ አማራጭን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። የዳቦ ችግር ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥበት እንዲሁም ዋጋው አሁን ባለበት እንዳይቀጥል አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርግ ይገባዋል።

 

                             አቶ ደምስ - ከአስኮ      

 

ክፍል መልዕክቶች
Wednesday, 02 May 2018 12:53

ቁጥሮች

 

2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር             የቀንትቻ ታንታለም ፋብሪካ ለአራት ወራት ስራ በማቆሙ የታጣው ገቢ ፤

 

40 ቶን                                  ፋብሪካው ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ማምረት የነበረበት ታንታለም መጠን፤

 

18 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር       ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው የውጭ ምንዛሪ፤

 

14 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር       ከታቀደው እቅድ ውስጥ ማሳካት የተቻለው፤

 

   ምንጭ ፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በየዓመቱ ሜይ 3 ቀን ይከበራል። በዚህ መሠረት በሀገራችንም በነገው ዕለት (ሚያዚያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም) የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ታስቦ ይውላል። ይህ ቀን የነጻነት ቀን ነው። ይህ ቀን “keeping power in check: Media, justice & The rule of Law” (ሚዲያ ለፍትሕና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው) በሚል መርህ ተከብሮ ይውላል። በዓሉ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሬሱን ለመደገፍ፣ የሐሳብ ብዝሃነት እንዲስፋፋ ለመስራት ቃል በገባበት በዚህ ወቅት መከበሩ ለየት ያደርገዋል። የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች በምህረት በተለቀቁበት ወቅት መከበሩ የተለየ ድባብ ያላብሰዋል።

ፕሬስ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እንዲያድግ፣ እንዲፋፋ በመረጃ መበልጸግ አለበት። ፕሬስ ተልዕኮውን በፍጥነትና በጥራት እንዲወጣ በመረጃ መታገዝ የግድና ወሳኝ ነው። የመረጃ ነጻነት ጉዳይ በሕገመንግሥቱ የተደነገገ ነው። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 የመረጃ ነጻነትን በሕግ ደንግጓል። በተግባር ግን መረጃ የማግኘት ነጻነት በኢትዮጵያ የተረጋገጠ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። በሕገመንግሥት ጭምር የተረጋገጠን ነጻነት አስፈጻሚው አካል እያከበረ አይደለም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ የፕሬስ መግለጫዎች ላይ የግል ጋዜጦችን የማሳተፍ በጎ ጅምር እያሳዩ መሆናቸው በጥሩ ጎኑ የሚወሰድ ቢሆንም በአንጻሩ ጥቂት የማይባሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሁን ድረስ የግል ጋዜጦችን የሚሸሹ፣ ለግል ጋዜጦችም በር የሚዘጉ፣ የግሉን ፕሬስ በመርገምና በመኮነን የሚረኩ መሆናቸው አነጋጋሪ ነው። በተዋረድም ወደታች ሲመጣ ተመሳሳይ ችግሮች የሚታዩ መሆኑ የፕሬስ ሥራን አዳጋች አድርጎታል። በተለይ በመንግሥታዊ ተቋማት መረጃ ማግኘት መብት፣ መስጠት ደግሞ ግዴታ መሆኑ ጭራሽኑ ተዘንግቶ ልመና ሆኗል። በዚህ ረገድ አስፈጻሚው አካል በጥልቀት ራሱን ፈትሾ ተገቢውን ቁርጠኛ እርምጃ ሊወስድና ፕሬሱን ሊያግዘው ይገባል።

ሌላው ፕሬሱ በሰው ኃይልና በፋይናንስ እንዲጠናከር መንግስታዊ ማስታወቂያዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኝ መደረግ አለበት። ይህ መሆኑ ፕሬሱ በፋይናንስ ተጠናክሮ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲያፈራና መረጃ የመስጠት ስራውን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። በዚህም ረገድ በመንግሥት የተያዙ ዕቅዶች በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርዱና እንዲተገበሩ የአብዛኛው ፕሬስ ፍላጎት ነው።

ፕሬሱም በራሱ ውስጥ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ይታወቃል። ወደውስጡ ተመልክቶ ጉድለቱን ማረም ተገቢ ይሆናል።

እናም የዓለም አቀፉን የፕሬስ ነጻነት ቀን ስናስብ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በፕሬሱ ላይ የተጋረጡ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ፣ የችግሩም ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካል ለመሆን ቃል በመግባት ጭምር ሊሆን ይገባል።¾

 

 

ግርማ ጌታኹን (ዶ/ር)

 

ደራሲ፤ አስማማው ኃይሉ
ርእስ፤ ከደንቢያ-ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ
አሳታሚ፤ ደራሲው
ጊዜ እና ቦታ፤ ሂዩስተን፣ ቴክሳስ፣ 2002 ዓ.ም
ገጽ ብዛት፤ 211
ጥራዝ፤ ለስላሳ ልባስ

 

ቀዳሚ ቃል


ይህ ሒሳዊ ዳሰሳ በሚያዝያ 2002 ዓ.ም ለደራሲው በቀረበ ሒሳዊ ተማግቦ (critical feedback) ላይ የተመሠረተ ነው። ተማግቦው የተጻፈው “ከደንቢያ - ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” ለንባብ በበቃ በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር። እንዲያ በመኾኑም በዚያ ጊዜ ኹነቶች ላይ የቀረቡ አንዳንድ ትዝብቶችን ያካትታል። አስማማው ኃይሉ (ነፍስ ኄር) ዛሬ በሕይወት የሉም። ይህ ሥራቸው ግን ስማቸውን ሲያስጠራ ይኖራል፤ የርሱ ተከታይ የኾነው ቍጥር 2 እና ሌሎች የግጥም እና የታሪክ ድርሰቶቻቸውም እንዲሁ። ተማግቦው ያኔ ለደራሲው ሲቀርብ ልቦለዱ ሕጸጾቹን በሚያስወግድ ኹለተኛ ዝግጅት ይታተም ይኾናል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ያ ተስፋ ከአስማማው ኅልፈት ጋር ያለፈ ይመስላል። የተማግቦው ነጥቦች እና አስተያየቶች ግን ልቦለዱን ባነበቡ ሰዎች እና በሌሎችም የዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ አፍቃሪዎች ዘንድ ሐሳብ ቀስቃሽ ይኾናሉ በማለት በሚከተለው ዳሰሳ ቀርበዋል።


አጠቃላይ
ይህ መራ መውጫ (debut) ታሪካዊ ልቦለድ እጅግ አማላይ እና ደርዘኛ ሥራ ኾኖ አግኝቼዋለኹ። ልቦለዱን ደርዘኛ ሥራ ካደረጉልኝ ነጥቦች ውስጥ የታሪኩ አማላይነት እና ርባና፣ የዋናው ገጸ-ባሕርይ (የባለገድሉ) ግዝፈት እና ተአማኒነት እንዲሁም የትረካው ቅልለት እና ቅልጥፍና ተለባሚ (noteworthy) ናቸው።

 

የታሪኩ አማላይነት እና ርባና
“ከደንቢያ-ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” (ከዚህ በኋላ “ደ/ጎ/ዋ” እለዋለኹ) በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል ተሳትፎ ለስደት እና ለግዞት ኑሮ በተዳረገ የአንድ ትውልድ ታሪክ ላይ እያተኰረ፣ የትውልዱን የተናጠል እና የወል የሕይወት ውጣ-ውረዶች ያሥሣል። ታሪኩን በሚጋሩ የትውልዱ አባላት ዘንድ ጐልተው የሚታዩ የአኗኗር፣ የሥነ-ልቦና፣ የወቅታዊ ፖለቲካ አተናተን፣ ወዘተ. ዝንባሌዎች ስለሚታሠሡም መጽሐፉ በኔ-ብጤው አንባቢ ዘንድ የግል እና የማኅበራዊ ሕይወቱ ነጸብራቅ እንደሚኾን ዐስባለኹ። የተጠቀሱት የትውልዱ ዝንባሌዎች በቀሪው የባሕርማዶ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ልባሜ እና ዐዘኔታ (understanding and sympathy) የሚያገኙ አይመስሉም። ይህ ታሪካዊ ልቦለድ በደራሲው የራስ ተመክሮዎች እና አስተውሎዎች የጎለበቱ ስሜታዊ፣ ሥነ-አእምሯዊ እና ባሕሪያዊ አርእስተ-ነገርን በታሪኩ ውስጥ ስለሚቃኝ ስለዚያ ትውልድ ጠለቅ እና ሰፋ ያሉ ግንዛቤዎችን ለአንባቢ ያስጨብጣል ብዬ ዐስባለኹ። ዐሠሣው ምጥን እና ሚዛናዊ በመኾኑም ተአማኒ ነው።


በቅርቡ ዐሥርታት ውስጥ በየካቲቱ አብዮት ዘመን የነበረውን ወጣት ትውልድ በድፍን፣ በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል የተሳተፈውን ደግሞ በተለይ፣ ሀገር አፍራሽ እና ታሪክ አርካሽ አድርጎ የመውቀስ አንዳንዴም የመኰነን አዝማሚያ ጐልቶ ይታያል። ወቀሳ እና ኵነናው የሚቀነቀነው አብዛኛውን ጊዜ ወይ በዐፄው ሥርዐት ደጋፊዎች፣ አሊያም በደርግ ሥርዐት ተጠቃሚዎች ይመስላል። በርግጥ ከነዚህ ሥርዐቶች ጋር ትውውቅ ባልነበረው፣ የዛሬው ወጣት ትውልድም ውስጥ ዐልፎ ዐልፎ ይኸው ወቀሳ እና ምሬት እንደሚደመጥ ዐስባለኹ። ታዲያ ተወቃሹ ትውልድ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የኖረባቸውን ማኅበራዊ ሥርዐቶች ግፍ እና ፍትሕ-አልባነት፣ ከንቱ እምነት እና ኋላቀርነት የሚያሳይ ታሪካዊ የፈጠራ ሥራ ከትልሂት (entertainment) የላቀ ፋይዳ አለው፤ በሥርዐቶቹ ላይ ማመፅ ለምን አማራጭ-የለሽ ተልእኮ እንደነበር ያስገነዝባልና። በዚህ ረገድ ይህ ተአማኒ የውስጥ-ዐወቅ ትረካ ሰፋ እና ጠለቅ ያለ ዐሠሣ ባያደርግም በ“ስለሺ” የልጅነት ባህላዊ ከባቢ እና ከንቱ እምነቶች ላይ ብርሃን በመፈንጠቅ የኵነናውን ከንቱነት በተምሳሌት ያሳየ ይመስለኛል።


የገጸ-ባሕርዩ ግዝፈት
ዋናው ገጸ-ባሕርይ በተለምዶው የዐማርኛ ልቦለድ ውስጥ የሚታይ የመልክ እና የቁመና ገለጻ አልቀረበለትም። መልከ-መልካም ይኹን መልከ-ጥፉ፣ ረዥም ይኹን ዐጭር፣ ኮሳሳ ይኹን ደንዳና፣ ደንሴ ይኹን ተናጣቢ ለአንባቢ በመጀመሪያው ገጾች ላይ በቃል አልተሳለለትም። ስሙ እንኳ አልተሰጠም - የአያቱ ስም እንጂ። ይህ ግን ገጸ-ባሕሪውን ማንነት እና ምንነት አልነፈገውም፤ አንባቢ በፍናፅንስ (preconceived) ሐሳብ ምናቡ እንዳይሸበብ ረዳ እንጂ። የርሱን ምስል እና ሰብእና አንባቢው ከታሪኩ፣ ከገጠመኞቹ እና ለኹነቶች ከሚያያደርገው ዐጸፋ ቀስ-በ-ቀስ እንዲገነባ ዕድል በመስጠቱ ገጸ-ባሕርዩ ግዝፈት እና ውስብስብነት ሊጎናጸፍ የቻለ ይመስለኛል።


“ስለሺ” ከአስተሳሰቡም ኾነ ከምኞቱ ጋር በሚቃረኑ ኹኔታዎች ውስጥ ራሱን ማግኘቱ ለገጸ-ባሕሪው ግዝፈት መልካም መቼት ኾኗል። ይህ ከማርክሳዊ እና ግራ-ዘመም እምነት በፍጹም ያልተላቀቀ ወጣት ቀንደኛ ጠላቱ አድርጎ የታገለው ሀገር እና ሥርዐተ-ማኅበር ተገን ሰጥቶት መኖሩ ምቾት ይነሣዋል፤ ግን የግርመት ምንጭም ይኾነዋል። ብጤዎቹ እና የትግል ጓዶቹ ራሳቸውን ከነጩ ማኅበረሰብ በተቻላቸው መጠን አርቀው እና አግልለው ሲኖሩ፣ እርሱ ግን ስፖንሰር ኾኖ ባመጣው ነጭ ቤተሰብ ውስጥ ፍቅር እና ክብካቤ ሳይጓደልበት ለዓመታት መኖሩን እንታዘባለን። ደግሞም በርእዮትም ኾነ በአኗኗር ምርጫ ከማትጣጣመው ወጣት ሴት ጋር ሲኖር እናየዋለን። እነዚህ ትድረቶቹ (ways of life) ዘለቄታ ባይኖራቸውም፣ እጅግ ብዙ ተመክሮዎች የገበየባቸው ይኾናሉ። በነዚህ መቼቶች ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ሕይወት በወጣትነቱ ዘመን እንዳሰበው ግልጽ እና ቀላል ምርጫዎችን የያዘ አይኾንለትም፤ በውስብስብ፣ ጠመዝማዛ እና ተዛናቂ (overlapping) ምርጫዎች የተሞላ እንጂ። በመቼቶቹ ውስጥ የነበረው መስተጋብር የራሱን ከንቱ እምነቶች (prejudices) እና አጕል ግንዛቤዎች (misconceptions) ከላዩ እየቀረፈ እንዲጥል፣ የሌሎችንም እንዲቃወም የሚያስችሉ ልዩ አስተውሎዎችን ያቀርቡለታል።


የፓርከር ቤተሰብ ድፍን ነጭ ነው፤ “ስለሺ” እስከሚዘነቅበት ድረስ (ደንቢያኛ/ጐንደርኛ ዘዬ መዋሴን ልብ ይሏል)። በዚያ ቤተሰብ ውስጥ ግን ባለቤት እና ባልተቤት የኹለቱ ዐበይት የአሜሪካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ኾነው ከትዳራቸው ጐን የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። የአደንዛዥ ዕፅ ሰለባ ኾና በለጋ ዕድሜዋ ከምትሞተው ልጃቸው ይልቅ ኹለቱ ከ“ስለሺ” ጋር ትርጕም ያለው የልጅ እና የወላጅ ዝምድና ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ እነርሱም ኾነ እርሱ በዕቅድ የፈጠሩት ዝምድና አይኾንም፤ በኺደት የሚገኝ እንጂ። ይህን የመካከለኛ መደብ ዐይነተኛ ነጭ ቤተሰብ - እነዳንኤል እና ሁሴን ከውጭ ዐይተው በዘረኛነት እና በጨቋኝነት የሚፈርጁት ነጭ ቤተሰብ - በአባላቱ ቍጥር ግለወጥ ባሕርያት ያቀፈ፣ የፖለቲካ እና የእምነት ልዩነቶችን አቻችሎ የያዘ ቤተሰባዊ አሐድ (family unit) ኾኖ እናገኘዋለን። ሐዘን እና ደስታ የተፈራረቁበት፣ ውድቀት እና ስኬት የጐበኙት፣ እርጅና እና አደንዛዥ ዕፅ ቀጣይነት የነሡት ቤተሰብ በመኾኑ፣ በቀለም መለያው ብቻ ዘረኛ እና ጨቋኝ አድርጎ ለመፈረጅ አይመችም። ታዲያ ደ/ጎ/ዋ “ስለሺ”ን በዚያ ነጭ ቤተሰብ ውስጥ “ዘንቆ” በማሳየት ነጭ ባልኾ ነው የአሜሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉትን ከንቱ እምነት፣ አሉታዊ አዝማሚያ እና ግልብጥ ዘረኛነት ያጋልጣል።


ሕይወት እና እውነታ እንዲህ ናቸው። ስለዚህም ነው በአሜሪካ ማኅበረሰባዊ ውስብስብ ውስጥ “ስለሺ” እና ብጤዎቹ ያላቸውን ትድረት በአማላይ ትረካ እየገለጸ እውናዊ ሥዕል የሚያቀርብልንን ደ/ጎ/ዋ ደርዘኛ ሥራ የምለው።

 

አተራረክ
ታሪኩ በጊዜ ቅደም-ተከተል አልቀረበም፤ ወደፊት እና ወደኋላ እየተመላለሰ እንጂ። ይህም አተራረኩን ዘመናዊ እና አማላይ ያደርገዋል። ታሪካዊው ልቦለድ በአንደኛ ሰው (በራስ) ትረካ መቅረቡም ግላዊ እና ውስጣዊ ስሜትን ጠለቅ ባለ ደረጃ ለመዳሰስ ይበልጥ አመችቷል እላለኹ። የ“ስለሺ” ታሪክ በኻያኛዎቹ የዕድሜ ቅጥብ ውስጥ ኾኖ በፍልሰት አሜሪካ ሲደርስ ይጀምራ ል። ስለ ልጅነቱ፣ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለ ንሕሰት ዘመኑ ቅጥ- ሰጪዎች (moulders of his formative years) የምናውቀው በምልሰት (flashback) ነው፤ ገጠመኞቹ ዐልፎ ዐልፎ በሚቀሰቅሷቸው ያለፉ ዘመናት ትውስቶቹ ውስጥ። ለስደት እና ፍልሰት ስላበቃውም ምክንያት ለአንባቢ የሚገለጸው ቀስ-በ-ቀስ ነው።


የአተራረኩ ሌላ ዐቢይ አማላይ ታሳቢ በደንቢያ (በጐንደር) ዘዬ እና ፈሊጥ የቀረቡ የእልፍነሽ (የእናቱ) እና ሌሎች “ደንብያውያን” ምልልሶች ወይም ግላዊ መነባንቦች (monologues) ናቸው። የእኒህ ለዛ እና ጥፍጥና አንባቢን (በተለይም ከጐንደር ዐማርኛ ጋር የማይተዋወቅ ከተሜ አንባቢን) አፍነክናኪ ናቸው። የዐማርኛ አፋዊ ቋንቋ ውበት እና ሕብራምነት (colourfulness) በየአካባቢው በሚነገሩ ልይዩ (diverse) ዘዬዎች እና ፈሊጦች ይከሠታሉ። እኒህ ቀበልኛ ዘዬዎች እና ፈሊጦች በጥልቀት እና በምልአት ያልተጠኑ፣ በሥነ-ጽሑፍም ውስጥ እምብዛ ያልተወከሉ በመኾናቸው (1) በዚህ መራ መውጫ ሥራ ውስጥ ተቈጥበው እና በሥሡ ተፈንጥቀው ለሚገኙት ልዩ እኳቴ (appreciation) ይገባቸዋል እላለኹ።


ብዙ ጊዜ ችግር የሚያስከትለው ብሂል-መር (pronunciation-led) አጻጻፍ አግባብ እና ፋይዳ የሚኖረው እኒህን መሰል ቀበልኛ አገላለጾች ሲወክል ነው።
በዘዬ እና ፈሊጥ አጻጻፍ ረገድ የሚታይ ይዘት-ለቀቅነት (inconsistency) እንደ “ኈ” እና “ኰ” ያሉ ፍንጽቅ ቀለማትን (diphthongs) ይመለከታል። በሀገረሰብኛ አባባል ውስጥ ፍንጽቅ ቀለማት እጅግ ገንነው ይደመጣሉ፤ (በጐንደርም ልክ እንደ ሸዋ፣ ወሎ እና ጐጃም)። ለምሳሌ “ጐጃም”፣ “ጐንደር”፣ “ጕልበት”፣ “ጕብል” የሚሉትን ስሞች እንውሰድ። በስሞቹ ውስጥ ያሉት “ጐ” እና “ጕ” በኹሉም ሀገረሰባዊ ዐማርኛ ውስጥ ፍንጽቅ ኾነው ይደመጣሉ። በዚህ ልቦለድ ውስጥ ግን “ጎ” እና “ጉ” ተብለው ተጽፈዋል፣ የዘዬ እና ፈሊጥ አባባል ወካይ ተደርገው በተጻፉበት ቦታዎች ሳይቀር። በተመሳሳይ “ቈዳ”፣ “ቍልፍ”፣ … በከተሜኛ አጻጻፋቸው “ቆዳ”፣ “ቁልፍ”፣ … ተብለው ተሰጥተዋል። በዚህ የተነሣ የፈሊጦች እና ዘዬዎች ጽሑፋዊ ውክልና የተሟላ ሳይኾን ቀርቷል።

 

ጥቂት ስም እና ባሕርይ-ነክ ችግሮች
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ዋናው ገጸ-ባሕርይ ስም አልተሰጠውም። ይህ ደግሞ ታስቦበት የተደረገ አይመስልም፤ በዝንጋታ እንጂ። ባለገድሉ ስም-የለሽ መኾኑ (የቤተሰቡ እና የጓዶቹ ስሞች እየተጠቀሱ) ለግዝፈቱ ስሓ ከመኾን የዘለለ ፋይዳ ይኖረው ይኾን? በበኩሌ እጠራጠራለኹ። ወዲህም ስለ ባለገድሉ ለሚደረግ ሥነ-ጽሑፋዊ ተዋሥኦ (literary discourse) ቢያንስ ቅልጥፍናን ይነሣል። በዋሽንግተን ዲሲ እንደከተሙ ጓደኞቹ “ጓዱ” ወይም እንደ ፓርከር ቤተሰብ በአያቱ ስም “ስለሺ” ማለትም አግባብ አይኾንም (በዚህ ተማግቦ ውስጥ የኋለኛውን አጠራር እንዲመቸኝ ብዬ ብጠቀምም)።


ሌላው ስም-ነክ ችግር ባለገድሉ እና የፓርከር ቤተሰብ እርስበርስ የሚጠራሩበት ስሞች ናቸው። ስፖንሰሮቹ እርሱን ከአውሮፕላን ማረፊያ ሲቀበሉ ጀምሮ እስከ ዕለታተ-ሞታቸው ድረስ “ሚስተር ስለሺ” ወይም “ስለሺ” ሲሉት፣ እርሱም ከመጀመሪያ ግንኙነታቸው እስከ መጨረሻው “ሚስተር ፓርከር” እና “ሚሲስ ፓርከር” ይላቸዋል። ይህ ግን ከመቀራረባቸው እና እንደ ወላጅ እና ልጅ ከመዛመዳቸው ጋር ስሙም አይደለም። በተለይ በአሜሪካኖች ወግ-ለቀቅ (informal) ባህል “ልጄ” የሚሉትን እና የቤት ገበናቸውን ያለምንም ገደብ የሚያዋዩትን ወጣት ሲኾን በቅጽል ወይም በቍልምጫ ስም፣ ሳይኾን ደግሞ በተጸውኦ ስም መጥራት ልማድ ይመስለኛል። በዚያው ልክም አሜሪካኖቹ የተወዳጁት/የተዛመዱት ሰው ከቤተሰብ ስም ይልቅ በመጀመሪያ ስማቸው ወይም በሚወድዱት የስማቸው ምኅጻር እንዲጠራቸው ይፈልጋሉ። ታዲያ በመጀመሪያው የግንኙነት ዕለት እንኳ ባይኾን ውሎ ዐድሮ በነዚህ የቤተሰብ አባላት መካከል እንዲህ ያለው ወግ-ለቀቅ አጠራር አለመከሠቱ የአስተውሎ ሕጸጽ ነው።


ሦስተኛ ስም-ነክ ችግር የተምታታ የስም አጠቀቀም ነው። “ስለሺ” ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የሚያገኛቸው የጓደኛው የዳዊት እናት “የከበደ እናት” ተብለዋል፤(ገ. 194)።
ሌላው ምቾት ነሺ ችግር በአሳዛኙ ቤተሰብ ፍጻሜ ላይ የሚከሠት የ“ስለሺ” ድርጊት ነው። የሚስተር ፓርከርን የጣት ቀለበት እና የፓርከሮችን ቤት መክፈቻዎች እወንዝ ውስጥ መጣል፣ አስደንጋጭ እና ግራ አጋቢ ድርጊት ኾኖብኛል። ይህ በብዙ ረገድ ጨዋ እና ቅን ቤተሰብ ባለመታደል የአስከፊ ዕጣ-ፈንታ ሰለባ መኾኑ በገዛ ራሱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ታዲያ የቤተሰቡ መሪር ፍጻሜ በቂ እንዳልኾ ነ ኹሉ በ“ስለሺ” ገቢር የመታወስ እና በባለውለታነት የመታሰብ ዕድሉን ማጣት ያለበት አይመስለኝም። አንባቢም ስለ ቤተሰቡ የሚለብመውን የሥርየት ገጽታዎች (redeeming features) አላስፈለጊ በሚያስመስል ድርጊት መቋጨት ፋይዳው አይታየኝም። የዚህ ገቢር እምራ ዊ ጕልኽ ነት (symbolic significance) ምንድነው? የቤተሰቡን አሳዛኝ ፍጻሜ ማግነን? የቤተሰቡ እጅ ዐመድ-አፋሽ መኾኑን ማጕላት? “ስለሺ” ለቁሳዊ ቅርስ ግድ-የለሽ መኾኑን ማሳየት? “ስለሺ” ከነጩ ማኅበረሰብ ጋር የነበረውን ግንኙነቶች ቈርጦ ከሐበሻ ወይም ከጥቍር ብጤዎቹ ጋር መወገኑን ማሳየት? በበኩሌ የትኛውም የእምራዊው ገቢር ማጠየቂያ አሳማኝ የሚኾን አይመስለኝም፤ ከ“ስለሺ” ባሕሪ ያፈነገጠ፣ ኢምክንያታዊ ድርጊት መኾኑን የሚሸፍን አይኾንምና።


ከላይ የተሰጡት አስተያየቶች በባለሙያ ዕውቀት እና ልምድ ላይ የተመረኰዙ፣ ወይም በሥነ-ጽሑፍ ምሁራዊ መመዘኛዎች ተገምግመው በተያዙ ጭብጦች ላይ የቀረቡ ትንታኔዎች አይደሉም፤ እንደ ተራ አንባቢ የተሰቡኝን፣ ትዝብት እና ጥያቄ የቀሰቀሱብኝን የታሪኩ አላባዎች ከብዙ በጥቂቱ ያኰትኩባቸው ነጥቦች እንጂ።

 

ቋንቋ-ነክ ሐተታ
ለዚህ ዳሰሳ መሠረት የኾነው ተማግቦ በቋንቋ-ነክ አብነቶች እና ችግሮች ላይ በማትኰር ዐይነተኛ ተዋፅኦ ያደርጋል። በእላዴ-ቃላት (lexicography) ሙያ የተሰማራኹ ሰው በመኾኔ አብዛኛውን ጊዜ ትኵረቴን የሚስቡ የሥነ-ጽሑፍ አርእስተ-ነገር በቃላት እና አገባብ ዙሪያ የሚነሡ ጕዳዮች ናቸው። እንዲያ በመኾኑም ከዚህ በታች የተሰጡት አጠቃላይ የሐተታ ነጥቦች ስለ ቃላት ፍቺ እና ርባታ፣ ስለአጠቃቀማቸው እና አጻጻፋቸው በመጽሐፉ ውስጥ የታዩ ችግሮችን እና አብነቶችን ይመለከታሉ።


ለፈጠራ ሥነ-ጽሑፍ ኪነታዊ ዕሴት ዐበይት መመዘኛ ከኾኑ ቁምነገሮች ኹለቱ የጽሑፉ ቋንቋ ውበት እና ስብቅልና በመኾናቸው ይህ ዳሰሳ በነርሱ ላይ ተጨማሪ ትኵረት ያደርጋል። በቋንቋ-ነክ ጕዳዮች ዙሪያ የማነሣቸው ነጥቦች እጅግ አብዛኞቹ በዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ጐልተው እና ተደጋግመው የሚታዩ ናቸው።

 

ተለባሚ ቃላት
በመጀመሪያ ግን ደ/ጎ/ዋ ብዙ ተለባሚ ቃላት እና ብሂሎች ያዘለ በመኾኑ ለኔ-ብጤው አላዲ-ቃላት እና የቋንቋው ተመራማሪ አማላይ ሥራ መኾኑን መግለጽ እወድዳለኹ። የተማግቦው ዐባሪ ሰነድ እኒህን ከመጽሐፉ ውስጥ ለቅሞ በኹለት ንኡሳን አርእስት አስቀምጧቸዋል። ፋይዳቸውን ለዚህ ዳሰሳ አንባቢ ለማሳየት ከቃላቱ እኒህን ልጠቍም - ህ(ሕ)ሉፍ፣ ቅራቦት እና ጥቃሞት።


ህሉፍ (ገ.12) ወይም ሕሉፍ (186) ዐዲስ ቃል ባይኾንም፣ በከተሜ ዐማርኛ እና በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የተለመደ አይደለም። በትግርኛ የዘወትር ቃል የመኾኑን ያኽል በጐንደርም የሚደመጥ ይኾንን? የተሰማ ሀብተ- ሚካኤል እና የደስታ ተክለ-ወልድ መዛግብተ-ቃላት አያካትቱትም። በግእዝ የቃሉ ዐምድ/ኅ-ል-ፍ/ ነውና በሥርውቃላዊ አጻጻፍ “ኅሉፍ” ቢባል ሆሄ ይጠነቅቃል። በዐማርኛ የተለመደ የቃሉ አቻ ማለፊያ ነው። ለማለፊያ መልካም ተማራጭ ይኾናል፤ በተለይ ለሥነ-ግጥም አኹኖ (poetic effect)።


በሌላ በኩል በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት “ቅራቦት” (ገ. 188) እና “ጥቃሞት” (ገገ. 95፣ 127) ዐዳዲስ ወይም እምብዛ የማይታወቁ ቃላት ይመስላሉ። በደንቢያ እና በሌሎች የጐንደር አውራጆች የሚነገሩ ቀበልኛዎች ይኹኑ ወይም ደራሲው የፈጠሯቸው ቃላት ግልጽ አይደለም። ከዐውደ-አገባባቸው “ቅራቦት” ለአቅርቦት “ጥቃሞት” ደግሞ ለአገልግሎት እና ጠቀሜታ ተማራጭ/ተዋራሽ (alternative/synonym) መኾናቸውን መገመት ይቻላል። ቃላቱ ከ‹ቀረበ› እና ‹ጠቀመ› በቀጥታ የተመሠረቱ ናቸውና ቀልብ ይስባሉ። ‹ፍላጎት› ከ‹ፈለገ› እንደተመሠረተ ደንብ ጠብቀው ቢመሠረቱም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸው ይኾን?


የደ/ጎ/ዋ ሌላው አማላይ ገጽታ በገጠር ዘዬ እና ለዛ የተከሸኑ ግልጸቶች (expressions) ናቸው። ለቅምሻ ያኽል ጥቂት ላቅርብ። የገድለኛው አባት ልጃቸው በእናቱ ተሞላቅቆ ማደጉን ለመግለጽ እንዲህ ይላሉ፤ “የመጨረሻ ልጀ ነው፤ እናቱ እስከዛሬ አልወለደችውም አርግዛው ነው የምትኖረው። …” (ገ. 25)። ገድለኛው በበኩሉ ልጅ ሳለ የታቦት አገልጋይ እንዲኾን አባቱ ያደረጉትን ጥረት ሲያስታውስ “ከቸንከሩ ተክለሃይማኖት ካህን የተበደሩ ይመስል እኔን ለመክፈል ሲዘጋጁ” (ገ. 95) ይላል ወቀሳ በሚደመጥበት ፍሬ ቃል። እርሱ ብዙ ዓመታት እባሕር ማዶ አሳልፎም የትውልድ አካባቢውን ለዛኛ ንግግር አይዘነጋም። “ፈረንጅም በቅባት ሳያርስ የሰውን ቆዳ እንደሚልጥ...” (ገ. 130) ይለናል፤ ነጮች ሐሜት አያውቁም የሚል የቀድሞ እምነቱን ከንቱነት በመገንዘብ።

 

የከተባ እና የሥርዐተ-ጽሕፈት ችግሮች
አማላዩ የፈጠራ ሥራ እጅግ ብዙ የከተባ ስሕተቶች ይታዩበታል። እንዲያ በመኾኑም ሥራው ታትሞ ከመውጣቱ በፊት የናሙና ዕትም አራሚ (proofreader) ያላየው ያስመስለዋል። በተማግቦው ዐባሪ ውስጥ የተሰጠው ዝርዝር ረዥም ነው። ከዝርዝሩ ርዝማኔ በየገጹ በአማካይ አንድ የከተባ ስሕተት እንደሚገኝ መገመት ያስችላል።


ሌላው ዐቢይ ችግር ከሥርዐተ-ጽሕፈት ይዘት-ለቀቅነት (inconsistency) ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ብዙ ቦታዎች ላይ ይህ አጠቃላይ እና መሠረታዊ ችግር በብሂል-መር አጻጻፍ ይከሠታል። ለምሳሌ ሕወኀት (ወይም በዘመናዊ ትግርኛ አጻጻፍ ሕወሓት) የሚባለውን ስመ-ስም (acronym) እንመልከት። ስሙ ሥርዐት ባልተከተለ መንገድ ተጽፎ እናየዋለን (ህወሀት - 131፤ ሕወኅት 107፣ 110፣ 185፤ ኅወሓት -182፣ 183)። ይህ የንባብ እና የትርጕም ውዥንብር እስካላመጣ ችግር የለውም በሚል ማጠየቂያ (justification) ችላ ሊባል አይገባውም። በዘፈቀደ የመጻፍ ባህል ዐማርኛ መደበኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት እንዳይኖረው ከማድረግ በቀር ምን ፋይዳ ይኖረዋል?


ብሂል-መር አጻጻፍ የትርጕም አሻሚነት አያስከትልም ማለትም አይቻልም። ሊያስከትል እንደሚችል ከደ/ጎ/ዋ ጥቂት ምሳሌዎችን ማየት ይበቃል። ከድምፀ-ሞክሼ ቃላት “ምሑር”ን፣ ድርብ ቀለም ካላቸው ቃላት ደግሞ “ለቀቀ”ን በአስረጅነት እንመልከት። የመጀመሪያው በቍጥር ርባታው “ምሑራን” ተብሎ ተጽፏል (ገ. 185)፤ የተማሩ የተመራመሩ ሰዎችን ለመግለጽ። “ምሑራን” ግን በቁሙ “ምሕረት ወይም ይቅርታ የተደረገላቸው” ሰዎችን የሚገልጽ ቃል ነው። የተማሩ የተመራመሩ ሰዎችን ለመግልጽ ቃሉ “ምሁራን” ተብሎ መጻፍ ነበረበት። የኹለቱ ቃላት ዐምዶች /ም-ህ-ር/ እና /ም-ሕ-ር/ የፍቺ ልዩነቶችን ያዘሉ በመኾናቸው ሥርው-ቃላዊ አጻጻፍ ሆሄዎቻቸውን ለመጠንቀቅ፣ እንዲያም ሲል እቅጭ ሐሳብን ለማስተላለፍ ያስችላል። ኹለተኛው አስረጅ (“ለቀቀ”) በቦዝ አንቀጽ ሲነገር “ለቅቀን” መኾን ሲገባው “ለቀን” ተብሎ ተጽፏል፤ (ገገ. 7፣ 169)። “ለቀን” ግን በቁሙ ከለቀቀ ይልቅ የቀን (የዕለት) ፍቺ እንዳለው ልብ ይሏል።


ለሥርዐተ-ጽሕፈት መደበኛነት ነፋጊ የምለው ብሂል-መር አጻጻፍ በሥነ-ቃል እና በሥነ-ጽሑፍ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በቅጡ ካለመረዳት፣ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት የሚያዝሏቸውንም የፍቺ ጕልኽ ነቶች (phonemic significance) ካለመገንዘብ የተከተለ ባህል ነው። ከላይ በተሰጠው ምሳሌ ውስጥ በ<ህ> እና ‹ሕ› መካከል ያሉ ታሪካዊ እና ፍቺ-ዐዘል ልዩነቶችን ያለመረዳት ችግር ነው “ምሁር” እና “ምሑር” አንዱ በሌላው ተለዋጭ ቃላት ተደርገው እንዲታዩ የሚያደፋፍረው። ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያትን እንገደፍ ማለትም ከዚህ የግንዛቤ ሕጸጽ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው።

 

አጕል እና ዝንኵር አጠቃቀሞች
ደ/ጎ/ዋ በርካታ አጕል እና ዝንኵር አጠቃቀሞች (misuses and abuses) ይታዩበታል። በተማግቦው ዐባሪ ከተዘረዘሩት አላባት ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላት እና ሐረጎች የሚከተሉትን እንመልከት።


በገጽ 78 ላይ “ሕብረ ብሔራዊ ጥንቅር” የሚል ሐረግ እናነባለን። ቃል-በ-ቃል ሲተረጐም ሐረጉ “ብሔር-ነክ የቀለሞች ስብጥር” ማለት ነው። እንዲያ በመኾኑም ሐረጉ እምብዛ ስሜት-ሰጭ አይደለም። ደራሲው “ከተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች (ethnic communities) የመጡ አባላትን ያካተተ” ለማለት ግልጸቱን እንደተጠቀሙበት ከዐውደ-አገባቡ መገመት ይቻላል። ግምቱ ትክክል ከኾነ ከ“ሕብረ ብሔራዊ ጥንቅር” ይልቅ “ዘውገይር ስብጥር” (= multiethnic composition) የተሻለ ተማራጭ ይመስለኛል። “ዘውገይር” ከ“ዘውግ” እና “ዕይር” የተበጀ ዐዲስ ስያሜ ነው፤ በዘውግ (ethnicity) ቅይጥ መኾንን፣ (በሌላ አነጋገር የተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች አባላት አሳታፊነትን) በቅጡ የሚገልጽ ቃል ይመስለኛል።


በገጽ 161 ላይ ደግሞ እንደ ረመጥ የሚፋጅ ስሜት ለማለት “ስሜተ-ረመጥን” ጥቅም ላይ ውሎ እናያለን። “ስሜተ-ረመጥ” ግን ቃል-በ-ቃል “የረመጥ ስሜት” ማለት ነው። ረመጥ የራሱ ስሜት የለውምና የጥምር ቃሉ አበጃጀት እንከናም ነው። እንደ ረመጥ የሚፋጅ ስሜትን ዐጠር አድርጎ ለመግለጽ “ረመጣዊ/ረመጥማ ስሜት” ማለት ተገቢ ይኾናል።


በገጽ 120 ላይ የባለገድሉ ሙታን ጓዶች አንጸባራቂ ታሪክ እንደነበራቸው ለመግለጽ “በወርቅ የተኮላ ታሪካቸውን” የሚል ሐረግ እናነባለን። በሐረጉ ውስጥ ያለው “የተኮላ” ግን ተዘንኵሯል። ተኰላ (ከተሜኛውን “ኮ” አለመምረጤን ልብ ይሏል) በቁሙ “ተሰነገለ፤ ተወለወለ፤ እንዲያብረቅረቅ ኾነ” ማለት ነው። እንግዲያስ “በወርቅ የተጻፈ አንጸባራቂ ታሪካቸውን” ማለት ሐሳቡን በእቅጩ ሊገልጽ በቻለ ነበር። ወርቅን ይኰሉታል እንጂ፤ በወርቅ አይኰሉም።


ከነዚህ በተጨማሪ እና በተለይ ሊቀ መጡ የሚገባቸው ደግሞ በአገባብ እና አሰካክ ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ብዛታቸው በዚህ ዳሰሳ ውስጥ በጥቂቱም ቢኾን መካተታቸውን ግድ ይላል። በዚህ ርእሰ-ነገር ላይ ከሚያተኵረው ከዐባሪው ሰነድ አንድ ንኡስ ክፍል የሚከተሉትን በአስረጅነት እንመልከት።


1. ጠጅ፣ አረቄና ጠላ እየጠመቅን … ተለምዶን አስፋፍተናል። (ገ.7)
  1ሀ. ጠጅ እየጣልን፣ አረቄ እያወጣን፣ ጠላ እየጠመቅን … ሱሰኛነትን አስፋፍተናል።
2. ፊቷ ወደ ሳንባነት ይቀየርና (ገ.22)
  2ሀ. የፊቷ ቀለም በለዲ ይኾንና

  2ለ. የፊቷ ቀለም የሳንባ ይመስልና
3. ገላውን ሰዶና ዘና ብሎ የሚዝናናው ተዝናኚ ብዛት (ገ. 83)
  3ሀ. ገላውን ሰድዶ የሚዝናና ታዳሚ ብዛት
4. የቡና ተርቲም … ያንድ ሰሞን ዜና ሆኖ ይባጃል። (ገ. 157)
  4ሀ. በየቡናው ተርቲም … ያንድ ሰሞን ርእሰ-ነገር ይኾናል።

ከላይ ከአንድ እስከ አራት የተሰጡት ዐረፍተ-ነገሮች እና ሐረጎች ከመጽሐፉ የተቀዱ ናቸው፤ ከገጽ ማጣቀሻዎቻቸው ጋር ቀርበዋል። የአገባብ እና የቃላት ምርጫ ችግሮቻቸውን ከግርጌዎቻቸው ከተሰጡት ተማራጮች (1ሀ - 4ሀ) ጋር በማነጻጸር መገንዘብ አያዳግትም። ሦስተኛውን ምሳሌ ቀረብ አድርገን ብናየው የአሰካክ ብቻ ሳይኾን የድግግሞሽ ችግሮቹን እንታዘባለን። ንኡስ ሐረጎችን በያዘው በዚህ ሐረግ ውስጥ “ሰባት ቃላት” ሲኖሩ፣ ሦስቱ የ“ተዝናና” ርባታዎች ናቸው። በዚህ ላይ “ገላውን ሰዶ” የሚለው ቦዛዊ ሐረግ ሲጨመር የድግግሞሹን አለቅጥ መብዛት እንረዳለን፤ እርሱም የመዝናናት ፍቺን ያዘለ ነውና። የአራተኛው ምሳሌ ክፍል የኾነው “ያንድ ሰሞን ዜና ሆኖ ይባጃል” ደግሞ ውስጣዊ አለመመጣጠን ወይም አለመደጋገፍ የሚታይበት ንኡስ ዐረፍተ-ነገር ነው። የተሰጠው ጊዜ “አንድ ሰሞን” ነው። ታዲያ ለሰሞን ቈይታ የሚመጥን ቃል “ሰነበተ” እንጂ “ባጀ” አይደለም። መባጀት የበጋን ቈይታ የሚገልጽ ቃል ነው። በጋን ይባጇል፤ ክረምትን ይከርሟል፤ ሰሞንን ይሰነብቷል። በቃላት ምርጫም ረገድ ከ“ዜና” ይልቅ ርእሰ-ነገር (topic) ለዐውደ-አገባቡ የተሻለ ምርጫ ይመስላል። ዜናን እንደ ትኵስ ወሬ ብንወስደው፣ ብርቅነቱ/ትኵስነቱ የሚሰነባብት አይደለምና።


እኒህን መሰል ችግሮች በአፋዊ ዐማርኛ ውስጥ ዘወትር ይደመጣሉ። በአፋዊ ቋንቋ የሚደመጡትን ያለምንም ማረቂያ በጽሑፍ ቋንቋ ውስጥ መጠቀም ግን ተገቢ አይደለም፤ (ለኪናዊ ፋይዳ ካልኾ ነ በቀር)። ኹለተኛውን ምሳሌ በንግግር መልክ ብናዳምጥ፣ የሰው ፊት ወደ ሳንባ እንደማይቀየር በማወቅ ደራሲው “የፊቷ ቀለም የሳንባ ቀለም እንደመሰለ” ለመግለጽ መፈለጉን እንገምታለን። ግን ደራሲው የኋለኛውን ግልጸት ለመጠቀም ምን የሚያግደው ነገር ነበር? ሐሳብ በንግግር ሲገለጽ ለቃላት ምርጫ፣ ለአገባብ ስኬት ወይም ለሰዋስው ርታታ ፋታ አይገኝ ይኾናል። ያንኑ ሐሳብ በጽሑፍ ለመግለጽ ግን እንዴት ፋታ ይታጣል፣ ያውም ሥነ-ጥበባዊ ዕሴትን ቀዳማው (objective) ለሚያደርግ ሥራ?

 

መደምደሚያ
ደ/ጎ/ዋ በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል ተሳትፎ ወደ ሰሜን አሜሪካ ስለፈለሰ አንድ ትውልድ ማለፊያ ሥዕል የሚያቀርብ ደርዘኛ ልቦለድ ነው። በ80ኛዎቹ እና በ90ኛዎቹ ጎርጎሮሳዊ ዐሥርታት የዚህ ፈልሶ-መጤ ወገን ትድረት ምን ይመስል እንደነበር ለማሳየት አንድ ሓብሮት (painting) ያቀርብልናል። ፈልሶ-መጤው ከባዕድ ሀገር እና ከዐዲስ ማኅበረሰብ ጋር ለመጣወር ያደረገውን (ወይም ሳያደርግ የቀረውን) ጥረት፣ በትግል ታሪኩ ላይ የተከሠቱ የአተያይ ልዩነቶችን ለማስተናገድ የተጠቀመበትን ዘዴ፣ በልምድ እና በባህል ዳራ ከማይመስሉት ሌሎች የትውልድ ሀገሩ ሰዎች ጋር ለመተሳሰር ያደረገውን ሙከራ፣ ወዘተ. የሚያሳይ ሓብሮት ነው። ባለመታደል ምስሉ እንከን-የለሽ አይደለም፤ በብሩሹ ጥራት ማነስ የተነሣ መስመሮች ደብዝዘው፣ ቀለሞች ተዛልቀው ፍጽምና ነሥተውታልና።


-አበቃ-
22 ግንቦት 2009 ዓ.ም

ዶ/ር ግርማ ጌታኹን በብሪቲሽ አካዳሚ የታተመውን ‹The Gojjam Chronicles› የሚለውን ሥራቸውን ጨምሮ፣ “የጐጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ”፣ “የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት” እና ሌሎች በርካታ የምርምር ሥራዎችን የጻፉ [እና ያሰናኙ] ባለሙያ ናቸው።
(www.facebook.com/TheBlackLionAfrica)¾

ክፍል ኪነ-ጥበብ
Page 1 of 3

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 221 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us