Items filtered by date: Wednesday, 04 July 2018 - Sendek NewsPaper

 

የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳትና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው ዓመታዊው አገር አቀፍ ሻምፒዮና በሀረር ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ በሴቶች ደቡብ ክልል ወንዶች ትግራይ ክልል ሻምፒዮን ሲሆኑ አጠቃላይ ውድድሩ ሰላማዊ ቢሆንም በርካታ የቤት ስራዎች መኖራቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል። የጸባይ ዋንጫውን አዘጋጁ ሀረሪ ክል ወስዶታል።

አገር አቀፍ ደረጃ ክለቦችም ሆነ ቡድኖች አለመኖራቸው፣ የበጀት እጥረት እና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችና መሳሪያዎች በአገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለመኖር ለክብደት ማንሳት ስፖርት ፈተና ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህ ፈተና ግን አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የሚናገሩት የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ አበበ አሽኔ ናቸው። ኃላፊው ሲናገሩም አንድ የክብደት ማንሳት ስፖርት ሙሉ መሳሪያ (ሴት) 80 ሺህ ብር ይፈጃል። ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ወጪው ለስፖርቱ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአገር አቀፉ የታዳጊዎች ፕሮጄክት ሻምፒዮና ስፖርቱ የሚሰጥ በመሆኑ ብሎም በታዳጊዎች ስፖር ማዕከል ከሚታቀፉ ስፖርቶች አንዱ ሆኖ መቅረቡ ለክብደት ማንሳት ስፖርት ተስፋ ፈንጣቂ መሆኑን ተናግረዋል።

ታዳጊዎች በለጋ እድሜያቸው ክብደት ማንሳት ላይ ሲሳተፉ ለእድገታቸውም ሆነ ለአካላዊና አዕምሯዊ ጤንነታቸው ከባድ አይሆንባቸውም ወይ ስንል ጠይቀናቸው ነበር። አቶ አበበ ሲመልሱም ታዳጊዎቹ ስልጠና የሚወስዱት በመሳሪያ ሳይሆን በንድፈ ሃሳብና በተመሳሳይ መሳሪያ እንጂ በክብደት አለመሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም ቻይናዊያን በአስር ዓመታቸው ጀምረው ስፖርቱን እንደሚዘወትሩት ገልጸው ስልጠናውን የሚወስዱት ግን በዲሞንስትሬሽን እንጂ በክብደት መሳሪያ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ክፍል ስፖርት

 

በሩስያው የአለም ዋንጫ ሴኔጋልን ከሩብ ፍጻሜው ያስቀራት የፊፋ አዲስ ህግ አነጋጋሪ ሆኗል።የህጉ ተጠቂ የሆነችው ሴኔጋለን መልሶ እንዲያጤነው ጠየቀች።

በምድብ ከጃፓን፣ ፖላንድ እና ኮሎምቢያ ጋር ተመድባ የነበረችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል በአለም ዋንጫው በአሳዛኝ ሁኔታ ተሰናባች ሆናለች። በምድቡ ፖላንድን 2ለ0 አሸንፋ እና ከጃፓን 2ለ2 በመለያየት፤ እንዲሁም በኮሎምቢያ 1ለ0 ተሸንፋ አራት ነጥብ በመያዝ ከጃፓን ጋር እኩል ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር። በምድቡ ክሮሽያ አንደኛ ሆና ማለፏን በማረጋገጧ፤ ሁለተኛ ሆኖ የሚያልፈውን ቡድን ለማወቅ እኩል ነጥብና እኩል የግብ ክፍያ ያላቸው ሴኔጋልና ጃፓንን መለየት የግድ ነበር።

ፊፋ በ2015 ባወጣው ህግ መሰረት ቡድኖች በተመሳሳይ የውጤት ደረጃ ላይ ሲገኙ አንደኛቸውን ለመለየት በስፖርታዊ ጨዋነት የተሻለ የሆነው ቡድን ቀዳሚ ደረጃ ያገኛል። ማለትም ቡድኖቹ በጥፋት ያስመዘገቡት ቢጫ ካርድ መመዘኛ እንደሚሆን ደንግጎ ነበር። በዚህ መሰረት ከጃፓንና ሴኔጋል አነስተኛ ቢጫ ካርድ የተመዘበበት ቡድን ጃፓን ስለነበር ቡድኑ ወደ ቀጣዩ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ እንዲያልፍ ተደርጓል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ህጉ ተግባራዊ የሆነበት የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድንም ቅሬታውን አሰምቷል። ፊፋ ህጉን መልሶ እንዲያጤንና እንዲያሻሽለው የሴጋኔል እግር ኳስ ፌዴሬሽን መጠየቁ ተዘግቧል። በጨዋታ ወቅት ተጨዋቾች በሰሩት ጥፋት የተመዘገቡ ቢጫ ካርዶች ቡድኑ ውጤት ላይ ወሳኝ መሆን አይገባቸውም ብሏል። ተጨዋቾች በቢጫ ካርድ መቀጣታቸው ብቻ በቂ ስለሆነ ተጨማሪ ቅጣት ሰበቡድናቸው ላይ ሊጣል እንደማይገባ ፌዴሬሽኑ በማሳሰብ፤ ፊፋ ህጉን መልሶ ሊፈትሸው ያስፈልጋል ብሏል።

በቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ የሚሰለጥነው የሴኔጋል ብራዊ ቡድን በሩስያው የአለም ዋንጫ ከምደብ ማጣሪያው አልፎ የተሸለ የውጤት ታሪክ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት የአፍሪካ ቡድን ነበር። በአለም ዋንጫው ከሴኔጋል በተጨማሪ አራቱም ቡድኖች ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ናይጄሪያ ከምድብ ማጣሪያው ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ክፍል ስፖርት

 

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት በመቀሌ እየተካሄደ ያለው 9ኛው የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጨዋታ እንደቀጠለ ነው። በዚህ ስፖርታዊ ጨዋታ ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ 57 ዩኒቨርስቲዎች ተወክለው እየተወዳደሩ ይገኛሉ።

ከተሳታፊ ሀገራት መካከልም ዛምቢያ፣ ዑጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ሴራሊዮን፣ ካሜሮን፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪሸስ እና ዚምባብዌ ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎችን ወክለው ከተገኙት ቡድኖች መካከልም ከአዘጋጁ ዩኒቨርስቲ መቀሌ ዩኒቨርስቲ በተጨማሪ የወሎ እና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ እንደዚሁም የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ እና የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል።

ይህ የመላው አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጨዋታ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በሌሎች ስምንት የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች አዘጋጅነት ተካሂዷል። የመጀመሪያው ስፖርታዊ ጨዋታ በአክራ ጋና የተካሄደ ሲሆን ከዚያም በኋላ በተከታታይ ሁለት ጊዜያት በናይሮቢ ኬኒያ እንደዚሁም፤ በባዋውቺ ናይጄሪያ፣ በትሸዋነ ደቡብ አፍሪካ፣ በካምፓላ ኡጋንዳ፣ በዊንድሆክ ናሚቢያ እና በጆሀስበርግ ደቡብ አፍሪካ ተካሂዷል።

መክፈቻው ባለፈው ዕሁድ ሰኔ 24 ቀን በትግራይ ስታዲየም የተካሄደ ሲሆን በበነጋታው ሰኞ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ከዛንዚባር ዩኒቨርስቲ ያደረጉት የእግር ኳስ ጨዋታ በዛንዚባር ዩኒቨርስቲ 5 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይህ ባለፈው እሁድ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድር ለስድስት ቀናት ቆይታ የሚኖረው ነው። ከተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ጎን ለጎን የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ህብረት በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት የሚያሳይ ውይይትም ተካሂዷል።  

ክፍል ስፖርት

 

በሩስያው የአለም ዋንጫ ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው የአፍሪካ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በጊዜ ከውድድሩ ተሰናብቷል። የሊቨርፑሉን አጥቂ መሀመድ ሳላህን ያካተተው የፈርኦኖቹ ቡድን ውጤታማ ያልሆነበት ምክንያት እግር ኳሳዊ ብቻ ያልመሰላት ሀገሪቱ፤ ችግሩን የሚፈትሽ መርማሪ ኮሚቴ አቋቁማለች። መርማሪ ኮሚቴውም ባለፈው ሰኞ እለት ምርመራ መጀመሩ ታውቋል።

በአለም ዋንጫው ከአስተናጋጇ ሩስያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ኡራጋይ ጋር ተመድቦ የነበረው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ማጣሪያዎቹን ሶስቱን ጨዋታዎች ተሸንፎ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ምንም እንኳ ከ28 አመት በኃላ ወደ አለም ዋንጫ የተመለሰ ቢሆንም ጠንካራ ተፎካካሪ ሳይሆን በጊዜ መሰናበቱ ደጋፊዎቹንና የሀገሪቱን የስፖርት አመራሮች አሳዝኗል። ቡድኑ በሩስያ 3ለ1 እና በኡራጋይ 1ለ0 መረታቱ ይታወሳል። በተለይም ደግሞ በሩስያ 5ለ0 በተሸነፈውና ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቶት በነበረው በሳውዲ አረቢያ ቡድን 2ለ1 መሸነፉ ያልተጠበቀ ነበር።

ግብጽ ከአለም ዋንጫው መልስ የፈርኦኖቹ ስብስብ አሰልጣኙን ወዲያውኑ በማሰናበት ቡድኑ ውጤት ያጣበትን ምክንያት መመርመርን ነው ያስቀደመችው። አንዳንድ ውስጠ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነም ቡድኑ ውጤታማ መሆን ያልቻለው በእግር ኳሳዊ ምክንያት ብቻ አይደለም። በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች የተፈጸመ ዝርክርክ አስተዳደር እና ያልተገባ የገንዘብ አጠቃቀም በቡድኑ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ነው የተወራው።

በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ የብሔራዊ ቡድኑን የአለም ዋንጫ ውጤት አልባ ቆይታና ምክንያቶቹን የሚያጣራ መርማሪ ኮሚቴ ማቋቋሟን አስታውቃለች። ኮሚቴው ሰኞ እለት በይፋ ስራውን እንደጀመረም የሀገሪቱ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል።

በሀኒ አቦ ሪዳ የሚመራው የግብጽ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም መርማሪ ኮሚቴ መቋቋሙን እንማይቃወምና በሚዲያዎች የተሰራጩት ያልተገቡ የገንዘብ አጠቃቀምና ሌሎች አሉታዊ ወሬዎች በሙሉ እንዲያረጋግጡ እንፈልጋለን ብሏል።

በሀገሪቱ ፓርላማ በፋራግ ሰብሳቢነት የሚመራው የወጣቶችና ስፖርት ኮሚቴ ‹‹አሳፋሪ ስንብት›› እና ‹‹የወረደ ተሳትፎ›› ሲል የገለጸው የብራሔዊ ቡድኑ የአለም ዋንጫ ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግ ከጠየቀ በኃላ ነበር መርማሪ ኮሚቴ እንዲዋቀር የተደረገው።

ከወደ ሩስያ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ለመሀመድ ሳላህ ከፍተኛ አድናቆት ያላቸው የቼቺን ግዛት አስተዳዳሪ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በሩስያ ቆይታው የነበረበትን ሙሉ ወጪ ክፍያ ፈጽሟል። የግብጽ መንግስት ደግሞ ለብሔራዊ ቡድኑ የሩስያ ቆይታ 1.8 ሚሊዮን ዶላር መድቦ እንደነበር አስታውቋል።

ክፍል ስፖርት

ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባሕርዳር ከተማ የ“መደመር ቀን” በሚል መሪ ቃል በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የከተማውና የአካባቢው ሕዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው በተለያዩ ዝግጅቶች አክበርዋል። አምስት መቶ ሜትር ርዝመት በስድሰት ሜትር ስፋት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንድራ ይዘው በውጣት ዝግጅቱን አድመቀውታል።

የሰለፉ መሰረታዊ ዓላማ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የ“መደመር” ፖለቲካዊ መርህን ለመደገፍና፤ ለመደመር ያለመ መሆኑን ከአዘጋጆቹ ተደምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል በስብሰባው ላይ ባይገኙም “ለባሕርዳር ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን” በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለታዳሚው አስተላልፈዋል።

በባሕርዳር ስታዲየም ዝግጅት ላይ በርካታ ሰዎች ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል። ንግግር ካደረጉት መካከከል አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ገዱ አዳርጋቸው፣ ብርጋዴን ጀነራል አሳምንው ፅጌ፣ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ እና አቶ ሽባባው የእኔአባት ይገኙበታል። በቀረቡት ንግግሮች ላይ ተንተርሰን ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ከማቅርብ፤ የመረጥነው እንዳለ ማቅርብ ነው። ምክንያቱም ንግግር ካቀረቡት ሰዎች አውድ ውጪ፣ ትንታኔ ከማቅረብ ለመቆጠብ ነው።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለየት ያለና ወደፊት ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ሃሳብ የተሰነዘረው ከወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ነው። ይኸውም፤ ወ/ሮ እማዋይሽ ለድጋፍ ሰልፈኛው ያቀረቡት ጥያቄ “የአብረን እንስራ ጥሪ ሲቀርብልን በተቀደደልን ቦይ ለመፍሰስ ነው ወይንስ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም?” የሚል ነው። ይህ ሃሳብ ብዙ ጉዳዮች የታጨቁበት ብዙ ገጽ ወሬ መልዕክት ያለው መሆኑን ብንገነዘብም፤ እሳቸው ካሉት በላይ ብዙ ዕርቀት መሄድ አልፈለግንም።

ሆኖም ግን የድጋፍ ሰልፉ ገዢ ሃሳብ ይሆናሉ በማለት የብአዴን ሊቀመንበር የአቶ ደመቀ መኮንን እና የምክትል ሊቀመንበሩን የአቶ ገዱ አዳርጋቸውን ንግግሮች በተቻለ መጠን ሙሉውን አስፍረነዋል። በሊቀመናብርቱ ሊተላለፉ የተፈለጉትን መልዕክቶች፣ አንባቢዎቻችን በተረዳችሁበት አግባብ እንድትወስዱት ለእናንተው ተውነው። የአውዱን ፍቺ ነፃነት ለመጠበቅ በማሰብ ነው። መልካም ንባብ።

 

 

ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን

ባህርዳር ላይ ያስተላለፉት መልዕክት

 

በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ . . . በአካል በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ላይ ባይታደሙም፤ በመንፈስ ግን አብረውን እንደሆኑ በመግለጽ ለባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን በክብር አስተላልፈዋል።

እነሆ ዛሬ! እንደዚህ በደመቀ አብሮነት እና ባሸበረቀው ህዝባዊ ሰልፍ በመካከላችሁ ተገኝቼ ይሄን ንግግር ሳደርግ የተሰማኝ ልባዊ ደስታ እና የፈጠረብኝን ውስጣዊ ፍሰሃ ምንኛ ትልቅ እንደሆነ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው።

ይህ ታሪካዊ ቀን ቀጣዩን ጊዜ የተሻለ እና ክልላችንን እና ሀገራችንን ተመራጭና ተወዳጅ፣ የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ብሩህ ዕለት የወገገበት ነው። ለዚህ ዕለት ዕውን መሆን በየፈርጁ የታገሉ፣ የደሙና የቆሰሉ፣ ከዚያም አልፎ ክቡር ሕይወታቸውን የሰው በዚህ አደባባይ ክብርና ሞገስ ለእነሱ ይሁን። እናመሰግናለን።

ባህርዳር የክልላችን መናገሻ ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ በለሱ ቀንቷቸው ጎራ ያሉ የሃገራችን እና የሌሎች ዓለም ሰዎች በፍቅር የሚማረኩላት፤ ስለውበቷና ስለምቹነቷ ደጋግመው የሚመሰክሩላት፤ የሃገራችን ከተሞች ፈርጥ ነች።

ባህርዳር - ጣናን ተንተርሳ፣ ጊዮንን እንደመቀነቷ አገልድማ ታላላቅ ጥበቦችን በማህፀኗ ያቀፈች ድንቅ ሃብታችን ነች። አሁን. . .አሁን! በሃገር አቀፍ ደረጃ የዘመናዊነትና የብልፅግና ማሳያ ምልክት ከሆኑ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ባህርዳራችን ነች። እንኳን በዚች ውብ ከተማ በሚካሄደው ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በጋራ ለመታደም አበቃችሁ፤ አበቃን።

ይህ ትዕይንት፣ የለውጥ ጥማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ፍላጐት ብቻ አይደለም። ኃይልም ነው። ጉልበትም ነው። ሁሉንም ዕውን የሚያደርግ አቅም ነው። ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ ቆሜ በአይበገሬነትና በተስፋ የሚደልቀው ልባችን ዓለት ሲያንቀጠቅጥ፣ ድህነትን ሲንጥ ይሠማኛል። ለዓለም ሁሉም ይሰማል።

ይህ አስደማሚ የጥምረታችን ኃይል የትኛውንም መሰናክል ገርስሶ፣ እንቅፋቶችን ሁሉ አፍርሶ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም። ይህ እንዳለላ ሙዳይ፣ እንደ ህብር ሙካሽ የተንቆጠቆጠ ውበታችን የኢትዮጵያዊነት ፈርጥ ሆንነ፤ ሕዝቦቿን በውበት ሠድረንና ደምረን ለሀገራችን ድምቀት እንደምንሆን ይሄው ያየን ሁሉ ይመሰክራል። አብረን ቆመን አንጀታችን እንደክራር፣ ልባችን እንደከበሮ ተዋህዶ እየፈጠረ ያለው ዜማ ልዩ ኀብረ ዝማሬ ነው። ለሁሉም የሚጥም፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ሰሞቶ የሚያበቃው ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚደመርበት የፍቅር ቅኝት ነው። ፍቅራችን ሁሉንም ያሸንፋል።

የዛሬው የምስጋናና የድጋፍ ትዕይንት እያደር በየፈርጁ የሚገለጥ የአደራ ጥራዝ የብርታት ስንቅ ነው። አደራው የሁሉም፤ አቅሙም የጋራ ነው። ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ስንበረታ እንደዛሬው ተመሰጋግነን፣ ስንሰንፍ ተወቃቅሰን፣ ተግሳፃችሁን ሰምተን ልንታረምና ልናገለግላችሁ ቃል የምንገባበት መድረክም ነው።

በዘመን ቅብብሎሽ አያቶቻችን እና አባቶቻችን . . . በአገር ፍቅር የነደደው ነፍስ፤ በነፃነት ጥማት የተሞላው መንፈስ፤ ለችግር የማይንበረከክ ነፃና ኩሩ ህዝብ፤ በፈተናዎች ፊት ፀንታ ሳትበገር የምትቆይ ሃገር አቆይተውናል።

ገና ከጥንቱ! አገርና ህዝብ ሲደፈር "ከራስ በላይ ንፋስ!" የሚል አስተሳሰብን አሽቀንጥረው "ከራስ በላይ ሃገር!" መኖሩን በታላቅ ጀግንነት ወድቀው፤ ተዋድቀው ክብሯን የጠበቀች እና ነፃነቷን ያስጠበቀች ሃገር በአደራ አውርሰውናል።

በቀደሙት የታፈረችውን ሃገር፤ በእኛ ደግሞ . . . የለውጥ ጉዟችን ፈተና ቢበዛውም ሃገራችን ከስኬት ማማ ላይ እንድትታይ በቁጭት እና በስስት ለውጥን በምኞት ሳይሆን በተግባር ለማምጣት የምንታትርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

እነሆ ዛሬ! ያለማንም ቀስቃሽ እና ጎትጓች በገዛ ፍቃዳችን በዚህ ታላቅ ስቴዲየም የተገናኘነው በተጀመረው ሃገራዊ አዲስ የለውጥ ስሜት አጋርነታችንን ለመግለፅና ይኸው ለውጥ በክልላችን ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ባለቤትነታችንን ለማሳየት ነው።

ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃም ሆነ በክልላችን ለለውጥ መነሻ የሆኑ ስራዎች ተመዝግበዋል። ነገር ግን ከሚጠበቀው ለውጥ አኳያ የሰራነው ትንሽ፤ የወቃነው ደግሞ ዕፍኝ እንደማይሞላ እንገነዘባለን።

ዛሬ የሰጣችሁን ድጋፍ እና የለገሳችሁን ምስጋና የከረሙ ችግሮችን በሙሉ ጠራርገን ስላስወገድን እንዳልሆነ በሚገባ እንረዳለን። ዋናው ነገር ጅምር የለውጥ አያያዛችን "የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!" የሚል መነሻ መሆኑን አንዘነጋም።

ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለን መሪዎች ካለፈው ጉድለታችን ተምረን ቃላችንን ለማደስና ህዝባችንን ለመካስ ከፊታችሁ ቆመናል። ንቅናቄው ጥቂቶች የሚዘውሩት፤ ብዙዎች የሚታዘቡት ሳይሆን ሁሉም በባለቤትነት ሊተውንበት የሚገባ ነው።

በዚህ መስተጋብር መሪዎች ስናጠፋ እየተቆነጠጥን፤ በጎ ስንሰራ እየተበረታታን እንድንቀጥል ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ከጎናችን ታስፈልጉናላችሁ።

ህዝቡ ባልተሸበበ አዕምሮ በነፃነትና በሃላፊነት መንፈስ ድጋፍና ተቃውሞውን የመግለፅ ባህሉ መጠናከር አለበት።

ህዝቡ እንደ ንስር ዓይን ችግሮችን ነቅሶ የሚያወጣበት እና እንደ ዶ/ር አዲስ አለማየሁ የተባ ብዕሩ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ እንሻለን።

በፓለቲካ አስተሳሰባችን እዚህ ወይንም እዚያ ልንቆም እንችላለን። የአንደኛው ወይም የሌላኛው አስተሳሰብ አራማጅ ልንሆን አንችላለን። የ”እኔ ሃሳብ የተሻለ ነው፣ የበለጠ ይጠቅማል“ ብለንም ልንፎካከርም እንችላለን። መሠረታዊው ጉዳይ ሁላችንም ለዚህች ሀገር ጥቅምና የተሻለ ነገር ፍለጋ የተሰማራን መሆናችን ነው፤ እርግጠኝነትና ልባዊነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው።

ብዕራችሁ የተባ፣ አዕምሯችሁ የሰላ እንዲሁም ተሳትፏችሁ ደግሞ የነቃ መሆን ዘመኑ ራሱ ይጠይቃል። መንግስት ይሄን ድባብ እንዲፈጠር አቅሙ የፈቀደውን ጠጠር መወርወር እንጂ የዜጎች ባላጋራና የዲሞክራሲ ስርዓት ደግሞ ደንቀራ መሆን አይገባውም። ይሄ ያፈጀበት አካሄድ ነው።

በምንገነባው ስርዓት በዴሞክራሲ ግንባታ እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለፉትን ስርዓቶች መርገምና መውቀሳችን ሳያንስ በዚህ ዘመንም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈፅሟዋል። ብዙ ዋጋም አስከፍለውናል።

ከዚህ በኋላ ፀረ-ዴሞክራሲ በቃ ብለናል፤ እያንዳንዱን ድርጊታችንና ስራችንን በንቃት ተከታታሉ። አካሄዳችንና ሁኔታችን ከዴሞክራሲ ያፈነገጠና የዜጎችን መብት የሚጋፋ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልትታገሉን እና አደብ ልታስገዙን ይገባል።

በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያውያን በነፃ አገራቸው፣ በነፃነት የሚያስቡባት፣ በነፃነት የሚፅፉባት፣ ያለ ገደብ የሚመረጡባትና የሚመርጡባት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ስርዓትን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የጋራ ተቋማት የተገነቡቧት፤ ዴሞክራሲያዊ አገር ባለቤት ይሆናሉ።

ይህ የህዝብ ጎርፍ፣ ሚሊዮኖች ያላንዳች ልዩነት በተባበረና ከፍ ባለ ድምፅ እየዘመሩለት ያለውን ኢትዮጵያን የዳበረና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ባለቤት የሆነች አገር የማድረግ ጉዞ ነው።

ነገር ግን ዕዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ። ዲሞክራሲ እንደፈለግን እንድንሮጥ እንደሚያስችለን፤ ሁሉ ልጓምንም ያበጃል። ልጓሙ የየግል ሩጫችንን በህግ ጥበቃ የተበጀላቸው የሌሎች የዜጎችን መብቶች እንዳይጋፋ ሲባል የተበጀ ነው። እናም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ነፃነትንና ሃላፊነትን በሚዛኑ ያያዘ መሆን ይገባዋል።

ፍቅራችንና አብሮ የመኖር ዕሴታችን ዕንዲሁ በምስጋና ቀንና በሰላሙ ጊዜ ብቻ የምናሳያቸው ሳይሆኑ በችግርና በፈታኝ ወቅትም ቢሆን ፀንተው የሚቆዩ ሃብቶች ናቸው። በዚህ የአብሮነትና የአካታችነት ባህሪያችንን የሚሸረሸሩ አዝማሚያዎችን በጽናት ማውገዝ ይጠይቀናል።

የአማራ ክልል ህዝብ በአገራችን ቀደምት የገናናነት ታሪክ የበኩሉን ወሳኝ ሚና የተጫወተ ባለታሪክና ኩሩ ህዝብ ነው። አለመታደል ሆኖ ያ! የገናናነት አገራዊ ቁመና ተቀይሮ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ቸነፈር ውስጥ ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው። የአማራ ብሄር በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች እሴቶች በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ቦታ ያለው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስርዓቶች ጥቂቶች ከሌሎች አካላት ጋር በጥቅም ተሳስረው በፈፀሙት ስህተት፤ በአማራው ላይ በተካሄደ የተሳሳተ አስተምህሮ ሰፊው የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች በዳይ፣ ዕዳ ከፋይና የተለየ ተጠቃሚ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል። በዚህ ብዙ መፈናቀል፤ ተጠርጣሪ እና ለሌሎች ችግሮች እንዲጋለጥ ሆኗል።

ከዚህ አኳያ የነበሩ ስህተቶችን በማረም የብሄራችንን እና የሃገራችንን ክብር ተመልሶ ገናናነታችንን ለማረጋገጥ መረባረብ ይገባናል። "ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን!" ይለዋል እንዲህ ነው።

ይህን ታላቅ ክልላዊና አገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ መሪ ድርጅቱ ብአዴን/ኢህአዴግ ላስመዘገባቸው ጅምር ስራዎች እንደሚመሰገን ሁሉ ላጠፋውና ላጎደለው ሃላፊነቱን ይወስዳል።

አሁን የተጀመረው የለውጥ ማዕበል ካለፈው ጉድለት ተምሮ በፅናት መጓዝን ይጠይቃል። ይህን የለውጥ ማዕበል በሙሉ ልብ ተቀብሎ ድርሻን መወጣት የግድ ይላል። ከዚህ ውጭ በእኔ አውቅልሃለሁ ፈሊጥ መንታ መንገድ መወጠን አይቻልም። መፍትሄው የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አድምጦ ከእሱ ጋር በመሰለፍ ለውጡን በትክክለኛ አቅጣጫ መምራት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ አንዳንዶቻችን የቅንጦት ህይወት የምንገፋባት እና እንዳሻችን የምንፈነጭባት፤ ሌሎቻችን ደግሞ ባይተዋር የምንሆንባት ሀገር መሆን የለባትም። እናም በእናት አገርና በጋራ ጎጇችን በእኩልንትና በፍቅር እንኖራለን።

አገራችን በተያያዘችው የለውጥ መንፈስ አስቀድመው ለተፈፀሙ እኩይ ታሪኮች ዳግም እንዳይፈፀሙ ትምህርት ወስደንባቸው፤ አዲስ ታሪክ ለመስራት ደግሞ የተለኮሰውን መነሳሳት ሂደቱን በአግባቡ ልንመራውና ልንገራው ይገባል።

በቅርቡ በመዲናችን አዲሳ አበባ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት በአገራችን የሚደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ምንም እንኳን በወሳኝነት በፍጥነት መጓዝ እንደሚቻል ከወዲሁ አፋችን ሞልተን ለመናገር ቢያስችለንም ሂደቱ የአልጋ ባልጋ ጉዞ እንደማይሆን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ክስተት ነው።

በዚህ አጋጣሚ እኔና ባልደረቦቼ ክልላችንና ኢትዮጵያን የተረጋጋና የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤት የማድረግ የቤት ስራን ዳር ለማድረስ ከህዝባችን ጋር በመሆን በፅናት እንደምንዘልቅ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

በታሪካችን አንዳችን በሌላችን ላይ ተነስተናል። ሲከፍም ቃታ ስበን አንዳችን የሌላችንን አካል አቁስለናል። አልያም አጉድለናል። ምንም እንኳ ትናንት የተከሰቱ መጥፎ ታሪኮችን መዘንጋት ሰዋዊው የማስታወስ ችሎታችን የማይፈቅድልን ቢሆንም ለወደፊት የጋራ ጥቅምና ጉዞ ሲባል ሆን ተብሎ እኩይ ትዝታዎችን መቀየር በእጅጉ ያስፈልጋል።

እናም እንደዚህ ዓይነቱን ቅስቀሳና ውትወታ የሚያስተላልፉት ሃይሎች ጆሮ ዳባ ልበስ ልንላቸው ይገባል። አማራ የሚታወቅበት መለያ ባህሪው አካታችነቱና አቃፊነቱ ነው። አማራ የሚታወቅበትን እሴቶችን ጠብቆ መቀጠል የሚገባው ሲሆን፤ ተናጥል ችግሮች እንኳ ቢያጋጥሙ ህዝብን እና ግለሰብን ለይቶ እንዲታረም እና እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ፤ ከዚህ ውጭ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የበቀል እና የጎጠኝነት አረሞችን በማስወገድ ብቻ ሳይሆን ይህው ለትውልድ እንዳይተላለፍ ተግተን መስራት ይኖርብናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከይቅር ባይነት በላይ የምናከብረውና ዋጋ የምንሰጠው ነገር የለም። “ ይቅርታ” በልባችንም በመሐላችንም ትልቅ ቦታ አለው። ዛሬም ይህንን ቦታውን ልናሰፋ መሐላችንም ይቅርታ እርስት እንዲሆን እንውደድ። ይቅር አንባባል። ለየአካባቢው የሚታየውን ግጭትና መቃቃር ከመሠረቱ አክስመን በይቅርታችን እንደይመለስ አድርገን እንጠበው።

ኢትዮጵያውያን ነንና ይሄ አያቅተንም። በትንሹም ሆነ በትልቁ ሆድ መባባስ ቀርቶ አንዳችን ለሌሎችን የፍቅር ማዕድና አውድ እንሁን።

በሚሊዮኖች ተደግፎ የተቀጣጠለው ለውጥ ወደ ኋላ መመለስ ቀርቶ ማዝገምን አይታገስም። መፍትሄው በህዝብ ባለቤትነት እና በወጣቱ መሪነት በፍጥነት መጓዝ ነው። ካሁን በኋላ ሃገራችን ለሁሉም በእኩል የተመቸች፤ ዜጎቿ እኩል የሚደመጡባት፤ እኩል የሚሳተፉባት የጋራ ማዕዳችን ሆና ትቀጥላለች። ለዚህ እውን መሆን በፅናት መታገል ይኖርብናል።

ከዚህ አኳያ የስራ ባልደረቦቼ እና እኔ ቴዎድሮስና ገብርዬ ሆነን ተጋግዘን፤ አለቃ እና ምንዝር ሳንሆን፤ የአንድ አላማ ተሰላፊዎች በመሆን ህዝባችንን የሰላም፤ የዴሞክራሲ እና የልማት ፍላጎት ዳር እናደርሳለን።

በዚህ አጋጣሚ አበክሬ ላነሳ የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ። በኛ በአመራሮቹ በኩል፤ ህዝቡን በሚፈለገው ደረጃ ያለማዳመጥ፤ ያለማቀፍ፤ ያለማቅረብ፤ እና ለያይቶ ማየት ችግር አለ። እንዲሁም በምሁራኑ እና በወጣቱ እንዲሁም ባለሃብቱ የዳር ተመልካች የመሆን እና በራስ አገር ላይ ባይትርነቱ ተስተውሏል።

ክልላችንም ሆነ ሃገራችን ወደ ፊት ሊገሰግሱ የሚችሉት እና በለውጡ ዘልቀው ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡት እኛ አመራሮቹ ችግራችንን ቀርፈን አቃፊና ደጋፊ ስንሆን ወጣቱ፤ ምሁሩ እና ባለሃብቱ ደግሞ ባይተዋርነቱን ትቶ የሃገሬ እና የክልሌ ጉዳይ ያገባኛል ደግሞም አመራሮቹ፤ የኔ ክፋይ ናቸው ብሎ አብሮ ሲሳተፍ እና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገባ ብቻ ነው።

እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ከእንግዲህ እንደማንሳሳት ሳይሆን እንደምናደምጣችሁ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ዘግይተን ሳይሆን ፈጥነን እንደምንመልስላችሁ እና በዚያው ፍጥነት እንደምንስተካከል ነው። ምስጋናችሁን ብቻ ሳይሆን ተግሳፃችሁን ከልብ ሰምተን ፈጥነን ለመታረም ዝግጁ መሆናችንን በልበ ሙሉነት አረጋግጥላችኋለሁ።

በተቻለን መጠን ባለን አቅም ሁሉ በህዝባዊነት እንደምናገለግላችሁ፣ ደከመን ሠለቸን ሳንል ሃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት እንደምናደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

"የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!" በሚል ዕሴት ታንፆ ለቃሉና ለማዕተቡ ታማኝና ሟች ከሆነ የታላቁ ህዝባችን ክፋዮች ነንና ይህንን ቃል እንጠብቃለን።

በዚህ አጋጣሚ ብአዴን በአማራው ስም በውጭ አገር የተደራጁና ለሱ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅች፣የተለያዩ ማህበራዊ የሚዲያ ተቋማት በሰላም ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ ወደ ክልላችን መጥተው እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያስተላለፈ እኛም ከግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ለህዝባችን ጥቅም መከበር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ።¾

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በባህር ዳር በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

 

ከሁሉ በማስቀደም በሚያለያዩንን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንን ማባከኑን ትተን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ለመተሳሰር በመፈለግ ቃል ወደምንገባበት የ“መደመር” ቀን ሁላችንም እንኳን አደረሰን!

ሃገራችን ከአመታት የሰላም እጦት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጥታ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት ናህዝቦቿ አንድ መሆን የጀመሩበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የጥይትድምፅና ለቅሶ ያደነቁራቸው የነበሩ ከተሞቻችን ሰላምንና ፍቅርን ከፍ አድርገው መዘመር ጀምረዋል።

ልጀ እንደወጣ ይቀራል ብለው ሰቀቀን ውስጥ ወድቀው የነበሩ የእናት አንጀቶች በሰላም ማረፍ ጀምረዋል። ይህ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን የትናንቱ ገናና ታሪካችንና የነገው ታላቅ ተስፋችን ማስተሳሰሪያና ማረጋገጫ ማህተምነው።

የአማራ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አንድ በመሆን በሀገራችን ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት፣ ታሪክ እንዳይበላሽና ነፃነት እንዳይገፈፍ ጥንትም ጀምሮ የሰራና የታገለ ጀግና እና ባለ ታሪክ ህዝብነው። የእንግሊዝ ወራሪ ኃይልን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ እስከ አድዋ ድል፣ ከኢትዩጵያ አንድነት ምስረታ እሰከ አፍሪካ ዉህደት ጥሪና ገቢር ድርስና ከዚህም በኋላ ሃገራዊና አህጉራዊም ገድል እየፈፀመ የመጣ ህዝብ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክና ትውፊት ከትውልድ ትውልድ ሳይዛባ እንዲተላለፍ ከመፃፍ ከትቶ እስከ ማስቀመጥ የዘለ ቀሃገራዊ ውለታ ያለው ህዝብ፣ ለተራበ ፈትፍቶ አጉራሽ፣ ለተጠማ ቀድቶ የማይበቃው፣ ለወደደው ማርና ለጠላውም ኮሶነው።

ዛሬ በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ተሰፋ ደርዝ ያለው እንዲሆን የአማራ ህዝብ ተደራጅቶም ሆነ በተናጠል የሰራው ታሪክ ዘመን የማይሽረው ነው ብለን ብንናገር መታበይ አይሆንም። ሁላችሁንም የዚህ አንጸባራቂ ታሪክ ባለቤቶች ናችሁና እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን ስላችሁ በኩራት ነው።

ሃገራችን ከወደቀችበት እንደገና መነሳት ጀመረች እንጅ ገና በቅጡ መራመድ አልተቻላትም። አሁን ያሳየነውን አንድነትና ፍቅር በማይናወጥ መሰረት ላይ አንፀንየኔን፣ የእናንተን፣ የልጆቻችንንና የልጅልጆቻችንን እድል ተሰፋ እንዲበቅልበት ማድረግ ካልቻልን በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በአጋጣሚ መገኘታችን ትርጉም የለውም። በስራችን ውጤት ዛሬ እንዲህ አምሮብንና ተውበን ብንታይም ልንሻገራቸው የሚገባ በርካታ ወንዞችና ሰበርባራ መንገዶች ከፊት ለፊታችን ይጠብቁናል። እንደጀመርነው ሁሉንም እናልፋቸዋለን። ግን ስንቅያስፈልገናል። ስንቁም ፍቅር፣ አንድነትና ተሰፋ ነው። አንድስንሆን የማይደፈሩ መስለው ይታዩ የነበሩ ተራሮችን መናድ እንደምንችል ተምረናል። ስንደመር ብረትን ማቅለጥ እንደምንችል አይተናል። ስንፋቀር በሃገራችን የይቅርታና የምህረት ዝናብ እንደሚዘንብ ተገንዝበናል።

ዛሬ ሃገራችን ደስታና ፍቅር ብቻ የሚታይበት ሃገር አይደለችም። የኛ አንድ መሆን የእግር እሳት የሆነባቸው ያልታደሰውና የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከእግር እግራችን ስር እየተከተሉ መንገዳችንን በስጋት ድርሊ ያሰናክሉት ሲሞክሩ እየታዩ ነው። ሰላም የዋለው ሃገር ሰላም እንዳያድር፣ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይጨባበጡ እንዲቆረጡ ስራ ውለቴ ብለው የሚደክሙ ሽንፈትን ያልተቀበሉ ደካሞች ከዙሪያችን አልጠፋም። ድል መንሻው ዘዴ የታወቀና የተለየ ነው። አንድ መሆን፤ መደመር።ተለያይተን ሞክረነዋል አልተሳካልንም። ተነቃቅፈንና ተጠላልፈን አይተነዋል፤ የጅብ እራት ነው የሆን። እናም አንድነትን በጥብቅ እንሻለን። አንድነት የሚጀምረው ከቤት ነው። የአማራ ህዝብ ራሱ አንድ ሳይሆን ኢትዩጵያን ያህል ትልቅ ሃገር አንድ ለማድረግ አይቻለውም።

ከደጃችን ያለውን ቆሻሻ ሳናፀዳ ንፁህና የፀዳ ችሃገር መፍጠር ያዳግተናል። ረጅሙን የፍቅርና የአንድነት ጉዞ ከአጠገባችን ካሉ ቤተሰቦቻችን ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝና በመተሳሰብ እንጀምረው።

ለክልላችን ወጣቶች

የክልላችን ህዝብ አፍላጉልበትን ከእውቀትና ከአስተዋይነት ጋር የተላበሰ ቆፍጣና ወጣት ይፈልጋል። እርምጃችሁ ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ እንዲሆን፣ ሰሜትንትታችሁ ምክንያታዊነትን፣ ጥላቻን ትታችሁ ፍቅርን፣ መገፋፋትን ትታችሁ አንተ ትብስ አንተ ትብስ መባባልን ሂወታችሁ በማድረግ በክልላችሁ የተጀመረው አንድነትና ተሰፋ እንዳይጨናገፍ ትታደጉት ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ። አሁን አንገት የምንደፋበትና ሙሾ እምናዎርድበት ወቅት አይደለም። ያለፈውን ረስተን በአዲስ ተስፋና ጥንካሬ ወደፊት እንራመድ።

ለሀይማኖት አባቶች

በሀገራችን ወንድማማችነትና እህትማማችነት መሰረቱ ሰፍቶ ታላቅ ታናሹን በተለመደው ኢትዩጵያዊ ባህል እንዲያከብርና ሰላም በሀገራችን እንዲበዛ ተግታችሁ ታስተምሩን ዘንድ እንደልጅነቴ በክብር እጠይቃችኃለሁ።

ለጥበብ ሰዎች

ትናንት ለሰላምና ለሰው ልጅ ክብር ያልተመለሰው ብዕራችሁ ዛሬም በምድራችን ፍቅርና መተሳሰብ እንዲሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ፣ የተተባተበው እንዲፍታታ፣ የደበዘዘው እንዲተባ፣ የአማራ ህዝብ ታሪክ እንዳይዛባና እንዳይጠፋ አቅማችሁና የሞያ ደረጃችሁ በሚፈቅደው መጠን ሁሉ ከጐናችን ቁማችሁ እንድንተጋገዝና እንድንደመር ጥሪ አቀርብላችኋለሁ።

ለተፎካካሪ ፖርቲዎች

በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የአማራን ህዝብ በልማትና በዲሞክራሲ ተጠቃሚ እና ደርጋለን የሚል ሀሳብ ይዛችሁ የምትሰሩ ተፎካካሪ ፖርቲዎች እንዳላችሁ እናውቃለን።

አላማችሁና ፍላጐታችሁ የአማራን ህዝብ መጥቀም እስከሆነ ድረስ በፍቅር አይን እንመለከታችኃለን። ከፊታችን ያሉ ትልልቅ ችግሮችን ተራርቀን በመቆምልና ሽንፋቸው እንደማንችል ተገንዝባችሁ ከሀገርውጪ ያላችሁተመልሳችሁ፣ ኢትዩጵያ ውስጥ ያላችሁም ተቀራርበን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ተመስርተን አብረን እንስራ።

አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ሁል ቆመሳፍርት የላቸውምና በሚያለያዩን ጥቃቅን ነገሮች ጊዜ ሳንጨርስ በጊዜ ወደቤታችን እንሰብስብ።

ለአጐራባች ክልል ህዝቦችና ድርጅቶች

ዘመኑ አለም አንድ እየሆነ ያለበት ነው። አንዳችን የጐደለንን ሌላችን ሞልተን፣ የአንዱ ቤት የሌላውም ጭምር ይሆን ዘንድ ማንነታችን ጠብቀንና አክብረን በመካከላችን በማይገባ ያጠርነውን አጥር በጊዜ አፍርሠን በጋራና በመተባበር በመስራት አንዲት ጠንካራ ኢትዩጵያን ለመገንባት እንረባረብ።

ለክልላችንና ለፌዴራል መንግስት የፀጥታ አባላት

ለክልላችንና ለመላ ኢትዩጵያ ሰላምና አንድነት እየከፈላችሁት ያላችሁትን ዋጋ አሳምሬ እገነዘባለሁ። ሀገራችን ሰላሟ የተጠበቀና እኩልነት የተረጋገጠባት ሆና እስክትዘልቅ ክንዳችሁ ሳይዝል፣ ነፃና ገለልተኛ ሆናችሁ የሰላም ምልክትነታችሁን መሰረት እንድታስይዙት አሳስባችኋለሁ። ኢትዩጵያ ንፁህ ደም ሳይሆን ፍቅር የሚፈስባት፣ በስጋት ሳይሆን በራስ መተማመን የተሞሉ ልጆች ያሏት ሃገር ትሆን ዘንድ የጀመራችሁትን ጀግንነት አበርትታችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ ቀርቦላችኋል።

ለሚዲያ ባለሞየወችና ጦማሪያን

በሃገራችን እየታየ ያለው ተስፋ ፍሬ ያፈራ ዘንድ እውነቱን ለህዝቡ አሳዉቁ። ከመላው ህዝባችን የምንደብቀው ጉዳይ የለንም። ስኬታችንም ሆነው ድቀታችን በልክ በልኩ እየተቆጠ ለህዝብ ጀሮ ይደርስ ዘንድ ሙያችሁ የሚጠይቀውን ዲስፕሊን ጠብቃችሁ ስሩ። ማዛባት ሁላችንንም ያጠፋናልና አሁን እንደጀመራችሁት ጣፋጭ ስኬትን ከመራራ እውነት ጋር አጣጥማችሁ ተራመዱ።

መጪው ጊዜ የአማራ ህዝብ የሚሰደድበት፣ የሚሸማቀቅበት፣ አንገት የሚደፋበት ሳይሆን በኩራት ቀና ብሎ የሚሄድበትና ከቁዘማ የሚላቀቅበት ነው። ከእንግዲህ ሆድ ሊብሰን አይገባም። ከእንግዲህ የትናነቱን እያነሳን መብሰልሰል ሳይሆን አንገታችንን ቀና አድረገን በተስፋ ወደፊት መራመድ ነው መለያችን። ሁላችንም ለዚህ እውን መሆን ተቀራርበንና ተደምረን እንስራ።¾

ክፍል ፖለቲካ

በይርጋ አበበ

የኢህአዴግ አስተዳደር በአገሪቱ ለተነሱ ግጭቶችና ብጥብጦች ራሱን ተጠያቂ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ ተናግረዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት አሸባሪ ተብለው በፓርላማ የተፈረጁ ድርጅቶችን በተመለከተም ዶክተር አብይ ሲናገሩ፤ ለስልጣን ማስጠበቂያ ወይም ስልጣን ለማግኘት ሲባል ሰውን መግደል፣ ማሰር እና ማሰቃየት የእኛ ተግባር ነው በማለት ነበር ኢህአዴግ እንጂ ሌላ አሸባሪ ድርጅት እንደሌለ የገለጹት። ይህን ተከትሎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ቅዳሜ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ እና ኦብነግ የተባሉ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት የሚያስፈርጃቸው አዋጅ እንዲነሳ ወስኖ ለፓርላማ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ብዝሃነትን እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበቡ ናቸው የተባሉ የተወሰኑ የህግ ክፍሎችን ለማሻሻል በጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተባባሪነት ኮሚቴ ተዋቅሯል። በሽብርተኝነት ስም በተፈረጁ ድርጅቶች አባልነትና ግንኙነት አላቸው ተብለው የታሰሩ ሰዎች እስካሁን ሲፈቱ ቢቆይም ገና ያልተፈቱ መኖራቸውን ተከትሎ አዋጁ ከተሻሻለ እና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችም ፍረጃው ከተነሳላቸው የታሰሩት የማይፈቱበት ምክንያት የለም ሲሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ይናገራሉ። በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ዙሪያ ከምሁራን እና ፖለቲከኞች ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

…….

 

የጸረ ሽብር አዋጁ እና የምሁራን እይታ

 

የህግ ባለሙያውና በሽብርተኝነት ወንጄል የተከሰሱ ፖለቲከኞችን ጉዳይ ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት አቶ ተማም አባቡልጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት ብለው ያምናሉ። የህግ ባለሙያው ሃሳባቸውን ሲያቀርቡም ‹‹በሁለት መንገድ አዋጁ መወገድ አለበት። የመጀመሪያው ነገር ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት የተጋላጭነት ደረጃዋ ዝቅተኛ ቦታ ላይ የምትቀመጥና የሽብር ስጋት የማያሰጋት ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ አዋጁ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ክፍሎች በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይም የተካተቱ ናቸው›› ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አዋጁን የስልጣን ማስጠበቂያው አድርጎታል ብለው የሚናገሩት አቶ ተማም ‹‹በጸረ ሽብር አዋጁ እኮ የማያስከስስ ነገር የለም። አሁን አንተ ጋዜጠኛ በመሆንህ ብቻ ልትከሰስና ልትታሰርም ትችላለህ። እስካሁን በዚህ አዋጅ የተቀጡትም ሆነ የተከሰሱት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ብቻ እንጂ አሸባሪ ሲቀጣ አላየንም። ይህ ደግሞ የሚያሳይህ በፖለቲካ ልዩነት የሚመጣበትን ሀይል አፍኖ ለመያዝ ገዥው ፓርቲ ያወጣው እንደሆነ ነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ስራ አስፈጻሚ አባል እና የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን በበኩላቸው ‹‹አዋጁ ሲወጣ አገራችን በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የምትገኝ ከመሆኑ አንጻር ለሽብር የተጋለጠች ስለሆነች ህዝቧንና አገሪቱንም ከሽብር ለመጠበቅ በሚል ነው መግቢያው ላይ የተቀመጠው። ሆኖም በተግባር እንደምናየው ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር በተያየዘ የተከሰሱ ሰዎችን ጥብቅና በመቆም እንዳየሁት ሙሉ በሙሉ ዓላማውን የሳተ እና አዋጁ በሚወጣበት ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ምሁራን አዋጁ አስፈላጊ አይደለም፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጋርጦባታል የተባለውን የሽብር ስጋትም በነበረው መደበኛ ህግ ማስተካከል ይቻላል ብለው ይከራከሩ ነበር። አሁን ያየሁትም የምሁራኑና የፖለቲከኞቹ ስጋት ትክክል እንደነበረ ነው። በእኔ ግምት በአዋጁ ከተከሰሱት ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት እውነትም ሁላችንም በምንስማማበት ሽብርተኛ ተብለው ሊቀጡና ሊወገዙ የሚገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ ይልቁንም ለህዝብ መብት የሚታገሉ፣ የመንግስት አስተዳደር ይስተካከል እና የተለየ የፖለቲካ አስተዳደር ያስፈልጋል ብለው የታገሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ናቸው። መከሰሳቸውም ብቻ ሳይሆን በማረሚያ ቤት እጅግ አሰቃቂ አያያዝ ይፈጸምባቸው ነበር። አዋጁ ባለፉት ዓመታት መንግስት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች ለመጨፍለቅ፣ ለማሳደድ፣ ለማፈን እና ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ ካዋላቸው ህጎች አንደኛውና በጣም አደገኛው ነው ብዬ ነው የማየው›› ሲሉ አዋጁ ለምን ዓላማ እንደዋለ ተናግረዋል።

አቶ አመሃ አክለውም ‹‹አዋጁ ሲወጣ አንዳንዶቻችን በቅንነት አይተነው ነበር። አገራችንን ከሽብርተኝነት ለመጠበቅና ለመከላከል ያስፈልጋል ብለን ነበር።›› ሲሉ በወቅቱ የነበራቸውን ስሜት ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም አዋጁ ለዜጎች አፋኝና አሸማቃቂ በመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊስተካከል ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ሊሻሻል ዝግጅት መኖሩንም አድንቀዋል።

‹‹የጸረ ሽብር አዋጁ የፍርሃት ፕሮጄክት ነው›› የሚሉት የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት አስፋው፤ ከአቶ ተማም አባቡልጉ አስተያየት ጋር ይስማማሉ። ዶክተር ንጋት ሃሳባቸውን ሲስብራሩም ‹‹አዋጁ ህዝብን አፍኖ ለመግዛት የታለመ ፕሮጄክት ነው። በአንድ አገር ምንም አይነት የዴሞክራሲዊ መብቶች በሌሉበት ውስጥ አፋኝ አዋጆች ይወጣሉ ከአፋኝ አዋጆች አንዱ ደግሞ ይህ የጸረ ሽብር አዋጅ ነው›› ብለዋል። ምሁሩ አያይዘውም አዋጁን ከመመልከታችን በፊት አዋጁን ያጸደቀውን አካል መመልከት ይበጃል ይላሉ። ‹‹የአገራችንን አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደቱን እንመልከት። በእኔ እምነት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ አልተወከለም ብዬ ነው የማምነው። ምክር ቤቱ የኢህአዴግ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መባል የለበትም። አስፈጻሚዎቹም ሆኑ ህግ ተርጓሚው በሙሉ በኢህአዴግ ሰዎች ተይዞና የኢትዮጵያ ህዝብ ከፖለቲካ ውክልና ተገልሎ የሚወሰን ውሳኔ የህዝብን ጥቅም ያስከብራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ይህ አዋጅም ይህን ህዝብ ረግጦ ለመግዛትና እንደፈለጉት ለማገላበጥ እንዲመቻቸው ካወጧቸው አፋኝ አዋጆች አንዱ ነው›› በማለት አዋጁ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

 

 

ጸረ ሽብር አዋጁ ማዕከል ያደረገው ክፍል

የህግ ባለሙያዎቹ አቶ ተማም አባቡልጉም እና አቶ አመሃ መኮንንም ሆኑ ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት አስፋው በጋራ የሚስማሙበት ነጥብ ‹‹ጸረ ሽብር ህጉ የተወሰነ የህዝብ ክፍልን ማዕከል አድርጎ ለማጥቃት ተግባር ላይ ውሏል›› ይላሉ። ከአረና ሊቀመንበሩ አቶ አብርሃ ደስታ እስከ ሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ድረስ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎችን ጥብቅና የቆሙት አቶ ተማም አባቡልጉ ሲናገሩ በዚህ አዋጅ ዋጋ የከፈለችው ኢትዮጵያ ናት። በርካታ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ንቁ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ለማሰር የወጣ አዋጅ በመሆኑ በእነዚህ ዜጎች መታሰር ደግሞ አንደኛ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በመታሰራቸው ቤተሰብ ዋጋ ከፍሏል፤ አገር እንደ አገር መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልግ ምሁርና ንቁ ተሳታፊው ክፍል ሲሸማቀቅ ዋጋ ከፍላለች›› ሲሉ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ትኩረት የተደረገባቸውን አካላትና አገር የከፈለችውን ዋጋ ጭምር ገልጸዋል።

ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት በጸረ ሽብር አዋጁ ምክንያት ‹‹ኢትዮጵያ በተለይም የአዲስ አስተሳሰብ ፈላጊው ትውልድ ዋጋ ከፍሏል‹‹ ይላሉ። ‹‹ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለምን የታሰረ ይመስልሃል? አንዷለም አራጌስ ለምን ታሰረ? እነዚህንና መሰል የዚህ ዘመን ለውጥ አራማጅ ወጣቶች ለእስር የተዳረጉት በኢህአዴግ የተቀነባበረ የስልጣን ማስጠበቂያ አፋኝ አዋጅ የተነሳ ነው›› ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ይላሉ ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት፤ ‹‹ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ አፋኝ፣ ገራፊና አሳሪ ሆኖ ህዝቡንና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ፖለቲከኞችን ባሸበረበት ተግባሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል እኮ። ይህ ሁሉ የሆነው ለስልጣን ሲባል የታሰበ እና ዓላማ አድርጎ ሊያጠቃ የተነሳውም ለስርዓቱ አስተዳደር የማይመቹ ሰዎችን ለማጥፋ ነው›› ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

 

 

ቀጣይ ጉዞ

በዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ኦነግና ኦብነግ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ በህግ ስርዓቱ መሰረት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በእነዚህ ድርጅቶች ስም የታሰሩ ፖለቲከኞችና የአገሪቱ ዜጎች አሁንም እስር ቤት መኖራቸው ይነገራል። ጸረ ሽብር አዋጁ ከመነሳቱም ሆነ ከመሻሻሉ በፊት በሽብርተኝነት የታሰሩ ሰዎች ከእስር የተፈቱም ነበሩ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ያሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር በዶክተር አብይ አህመድ ግብዣ ቤተመንግስት ገብተው የተነጋገሩ ሲሆን ከእስር ለመፈታታቸውም ዶክተር አብይ ስልጣናቸውን ለድርድር አቅርበው እንዳስፈቷቸው ራሳቸው አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል። ሆኖም አሁንም ድረስ እስር ቤት ውስጥ ያሉ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ስንል ሶስቱንም ምሁራን ጠይቀናቸው ነበር። የታሰሩት በሙሉ መፈታት እንዳለባቸው ተናግረው በዚህ ህግ ምክንያት ዋጋ ለከፈሉ ዜጎች መንግስት የህሊና እና የሞራል ካሳ እንዲከፍል ጠይቀዋል። በስራ ላይ የነበሩ ደግሞ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በተጨማሪም ህጉ ለዜጎች ጥቅም እንጂ ለስልጣን መጠበቂያ እንዳይሆን ተማጽነዋል።

 

 

በምሁራኑ የተነቀፉ የአዋጁ ክፍሎች

ዶክተር ንጋት አስፋው እና አቶ ተማም አባቡልጉ አዋጁ ሙሉ በሙሉ አያስፈልግም ሲሉ አቶ አመሃ መኮንን ግን የአዋጁን መሻሻል የሚደግፉ ምሁር ናቸው፡ ሶስቱም ምሁራን ታዲያ ከአዋጁ ክፍል ውስጥ በተለየ መልኩ ለዜጎች ተስማሚ አለመሆናቸውን የሚናገሩባቸው ክፍሎች በርከት ያሉ ናቸው። በሽብርተኝነት ስለመሰየም እና ሽብርተኛ ተብሎ በተጠረጠረ ሰው ላይ ስለሚወሰድ ናሙና፣ ለፖሊስ መረጃ የመስጠት ግዴታና ፖሊስ ከተጠርጣሪው መረጃ ለመውሰድ የሚጠቀመው ሀይል፣ የምርመራ ጊዜ እና በሽብር ተግባር ስለመሳተፍ የሚሉ አንቀጾች ይገኙበታል።

በምሁራኑ ከተጠቀሱት የአዋጁ ክፍሎች መካከል በተለይ ‹‹መረጃ የመስጠት ግዴታ እና ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ›› የሚሉትን ክፍሎች በትኩረት ተናግረውባቸዋል። አንቀጽ 21 እና 22 ሲሆኑ ከአዋጁ የተጠቀሱትን ቃል በቃል አስፍረናቸዋል።

 

 

ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ (አንቀጽ 21)

ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሑፉን፣ የጣት አሻራውን ፣ ፎቶግራፉን፣ የፀጉሩን፣ የድምፁን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል። በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዝ ይችላል። ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል።

 

መረጃ የመስጠት ግዴታ (አንቀጽ 22)

የሽብርተኝነት ወንጀል ለመከላከል ወይም ምርመራ ለማከናወን ፖሊስ ለምርመራው የሚረዳው መሆኑን በሚገባ የሚያምንበትን መረጃ ወይም ማስረጃ ከማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ባለሥልጣን፣ ባንክ፣ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል። መረጃ ወይም ማስረጃ የተጠየቀው ወገን መረጃውን ወይም ማስረጃውን የመስጠት ግዴታ አለበት።

ክፍል ፖለቲካ
Wednesday, 04 July 2018 13:05

ቀስ በቀስ ገዳዮቹ ምግቦች

“አያት ቅድመ አያቶቻችሁ ምግብ ነው ብለው የማያስቡትን ነገር በፍፁም አትመገቡ ይላሉ የስነ-ምግብ ተመራማሪው እና የተለያዩ መፅሐፍት ደራሲው ማይከል ፖላን። ባለሞያው እንደሚገልፁት የአሁን ዘመን ሰዎች “ዘመናዊ” የምንላቸው ምግቦች ከምግብነታቸው ይልቅ ይዘውብን የሚመጡት ጉዳት ህይወትን እስከ ማሳጣት የሚደርሱ ናቸው። በዘመናችን በየእለት ምግባችን የምንጠቀማቸው ዘመን አመጣሽ ምግቦች ከተፈጥሯዊ የስነ ምግብ ይዘት ይልቅ የተለያዩ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች እና ማጣፈቻዎች የተጨመሩባቸው ናቸው። እነዚህ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች እና ማጣፈጫዎች ታዲያ ሰውነትን ከመንባት ይልቅ ቀስ በቀስ እና በሂደት ለተለያዩ ስር የሰደዱ እና ለሞት ለሚያበቁ በሽታዎች የሚያጋልጡ ናቸው። የዶክተረ ፖላንን ጥናት ጨምሮ በርካታ በዘርፉ በቂ ጥናት ያደረጉ ተቋማትም የሰውን ልጅ ቀስ በቀስ ለሞት የሚያበቁት የዘመናችን ምግቦች የሚከተሉት ናቸው ይላሉ።

የተዘጋጀ ስጋ

ስጋ ለሰውነታችን ከሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች መካካል የተወሰኑት ይገኙበታል በመሆኑም ስጋን መመገብ ሁልጊዜ ጎጂ ብቻ አይደለም። በተለይ ሳር እና እፅዋቶችን የሚመገቡ እንስሳትን በመመገብ ለሰው ልጅ ጤንነት ጠቃሚ ነገሮችን ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን በተለያየ መልኩ ተዘጋጅተው በየመደብሩ የሚሸጡ የስጋ አይነቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘነ ነው። እነዚህን የስጋ አይነቶች ለማከም እና የባክቴሪያን እድገት ለመግታት በማሰብ አምራቾች ሶዲየም ናይትሪት የተባለውን ኬሚካል እንደሚጨምሩበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ንጥረ ነገር በስጋው ውስጥ ካለው ኬሚካል ጋር ሲገናኝም ሰውን ለተለያዩ አደጋዎች የማጋለጥ ሁኔታ አለው። በተጨማሪም በእነዚህ የተዘጋጁ የስጋ አይነቶች ውስጥ ያለው የሶዲየም ይዘት ከፍተኛ በመሆኑ ለልብ ህመም፣ ለስኳር ህመም እና ለካንሰር ያለንን ተጋላጭነት ከፍ ያደርጉታል። በተጨማሪም ከልጅነታቸው ጀምረው ይሄን ስጋ የተመገቡ ህጻናት በትምህርት አቀባበል ላይ ችግር እንዲገጥማቸው ያደርጋል ይላል መረጃው።

ለስላሳ መጠጦች

የካርቦን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ የለስላሳ መጠጦች ሌላው ቀስ በቀስ የሰውን ልጅ ከሚገድሉ የዘመናችን መጠጦች ይመደባሉ። እነዚሁ መጠጦች ከፍተኛ የሆነ የስኳር፣ ሰው ሰራሽ ማጣፈጫዎች እና እንዳይበላሹ ለማድረግ የሚጨመር ማቆያ ኬሚካል ይዘት አላቸው።

እነዚህ መጠጦች ያላቸውን ቃና እና ቀለም እንዲይዙ የተለያዩ ሰው ሰራሽ ኬሚካሎች የሚጨመርባቸው ሲሆን፤ ስኳር የለባቸውም የሚባሉትም ቢሆኑ ያላቸው የሰው ሰራሽ ማጣፈጫቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ዶክተር ፖላን የገለፁት። እነዚህ በለስላሳ መጠጦች ውስጥ የሚጨመሩ ሰው ሰራሽ ኬሚካሎችም ቀስ በቀስ ለልብ ህመም፣ ለስኳር ህመም፣ ለኩላሊት መዳከም እንዲሁም ለአስም እና ለጥርስ ህመም ይዳርጋሉ። በተጨማሪም እነዚህ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ የሚኖረውን የሆርሞን ስርዓት በማዛባትና የስሜት ሁኔታን በማለዋወጥ ላልተፈለገ ችግር ይቻርጋሉ።

ቅባታቸው የተወገደ የወተት ተዋፅኦዎች

በአሁኑ ጊዜ ያሉ የጥናት ውጤቶች እየጠቆሙ ያሉት የተፈጥሯዊ ቅባት ይዘታቸው ከፍተኛ ከሆነ የወተት ተዋፅኦዎች ይልቅ ቅባታቸው የተወገደው ለጤና አደገኛ መሆናቸውን ነው። በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተውም እነዚህ ቅባታቸው የተወገደ የወተት ተዋፅኦዎችን ተፈጥሯዊ ለማስመሰል እና ጣዕም ለመስጠት የተለያዩ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች ይጨመርባቸዋል። እነዚህ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮችም ሰውነታችን የምግብ ንጥረ ነገሮችን የሚቀበልበትን ሂደት የማዘግየት እንዲሁም ለአጥንት መሳሳት፣ ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች፣ ለአለርጂ እና ለአስም በሽታ ያጋልጣል። በተጨማሪም እነዚህ ንጥረ ነገሮች በተለይ በሴቶች ላይ የመራባት ችግር እድላቸውን በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምሩት የዩነቨርስቲው ጥናት አመልክቷል።

ነጭ ዱቄትና ነጭ ዳቦ

ስንዴ ለጤንነት ከሚመከር የጥራጥሬ አይነቶች አንዱ ቢሆንም፤ የተጣራ የስንዴ ዱቄትን መመገብ ግን ቀስ በቀስ በራስ ላይ ሞትን መጋበዝ እንደሆነ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። በተለይ ፍርኖ ዱቄት እየተባለ የሚጠራው ነጭ ዱቄት ሲዘጋጅ ነጭ ቀለም እንዲኖረው ለማድረግ በስንዴው ውስጥ የሚገኙት የምግብ ይዘቶች፣ ማዕድናት፣ ቫይታሚኖች እና አሰር እንዲወገዱ ይደረጋል። በምትኩም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጨመር ነጭ እንዲሆን ይደረጋል። ይህ ነጭ ዱቄትና ከነጭ ዱቄት የሚዘጋጅ ዳቦም የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮችን ካለመያዙ በተጨማሪም በሚጨመሩበት ኬሚካሎች ሳቢያ ላልተፈለገ የሰውነት ክብደት እና ከእርሱ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የጤና እክሎች፣ እንዲሁም ለስኳር ህመም፣ ለታይሮይድ እጢ መዳከም እና ለሌሎች የሰውነት ህዋሳት መዛል ያጋልጣሉ። በተጨማሪም ሰውነት በቀላሉ እንዲመረቅዝ እና የምግብ ልመት ስርዓትም እንዲስተጓጎል የማድረግ ጉዳት አላቸው።

የታሸጉ ጭማቂዎች

የፍራፍሬዎች የጤና ጠቀሜታ የሚያጠያይቅ አይደለም። ነገር ግን ጠቀሜታዎቹን ማግኘት የሚቻለው ፍራፍሬዎቹ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ጥቅም ላይ ሲውሉ ነው። ተዘጋጅተው የታሸጉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ግን ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ ይዘታቸው የተወገዱ ናቸው ይላሉ ዶክተረ ፖላን በፅሁፋቸው። ፍራፍሬዎቹ ተፈጥሯዊ ይዘታቸው ከመወገዱ በተጨማሪም ለጣዕም እና ለቀለም ማሳመሪያ እንዲሁም ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች እና ስኳር ይጨመርባቸዋል። ጭማቂዎቹን ከተዋህሲያን ለማፅዳት በሚያልፍበት ሂደት ወቅትም ፍራፍሬዎቹ የምግብ ይዘታቸውን ያጣሉ። በስተመጨረሻ የሚቀረው ውሃ እና ስኳር ነው የሚሉት ባለሞያው፤ ይሄ ስኳር እና ውሃ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የበረታ መሆኑን አስቀምጠዋል። በተለይ እንደ ስኳር ህመም፣ የልብ ህመም እና ከመጠን ያለፈ ውፍረትን የመሳሰሉ የጤና እክሎች እነዚህ የታሸጉ የጭማቂ አይነቶችን ቀስ በቀስ የሚያስከትሏቸው መሆናቸውን ባለሞያው ገልጸዋል።

ፈጣን ምግቦች

ፈጣን ምግቦች ጊዜ ካፈራቸው እና የሰውን ልጅ ህይወት ቀለል ካደረጉት ነገሮች አንዱ ናቸው። እነዚህ ፈጣን ምግቦች ከፍጥነታቸው በተጨማሪም ለመመገብ ቀላል እና ጣዕማቸው የሚስብ በመሆኑ ብዙዎች ያዘወትሯቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ቀላል የምንላቸው የዘመናችን ፈጣን ምግቦች የሚያስከትሉት የጤና መዘዝ ቀላል እንዳልሆነ መረጃዎቹ አሰቀምጠዋል። እንደ በርገር፣ ድንች ጥብስ እና የመሳሰሉት ፈጣን ምግቦች በአብዛኛው ይዘታቸው ስኳር፣ ትራንስ ፋቶች እንዲሁም ጨው እና ሌሎች ቃና ሰጪ ኬሚካሎች ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ምግቦች መመገብ በሂደት ለስኳር ህመም፣ ለልብ እና ከልብ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ህመሞች እንዲሁም ላልተፈለገ የሰውነት ክብደትና እርሱን ተከትለው ለሚመጡ የጤና እክሎች፣ ለስሜት መለዋወጥ እና ምግብ ወደ ሀይል የሚለወጥበትን ሂደት ለሚያዛባ የጤና እክሎች ይዳርጋል ይላሉ መረጃዎቹ። በተጨማሪም በእነዚህ ምግቦች ውስጥ የሚገኘው ሞኖሶዲየም ግሉታሜን የተባለው ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገር በአንጎል ላይ ችግር በመፍጠር፣ ትምህርት የመቀበል አቅምን በማዳከም እንዲሁም ለአልዛይመርስ በሽታ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።    

ክፍል ጤና

 

በ48 ኪሎ ግራም ሴቶች ምድብ አዲስ አበባ፣ ትግራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከእነደኛ እስከ ሶስተኛ ሲወጡ፤ በ53 ኪሎ ግራም ደግሞ ደቡብ፣ አማራ እና ትግራይ ተከታትለው ወጥተዋል። በ58 ኪሎ ግራም የተካሄደውን ውድድር ደቡብ፣ ትግራይና አዲስ አበባ ከወርቅ እስከ ነሃስ ያለውን ሜዳሊያ ወስደዋል። በ63 ኪሎ ግራም ምድብ ደግሞ ደቡብ፣ አማራ እና ትግራይ ወርቅ፣ ብር እና ነሃስ ሜዳሊያ ወስደዋል።

በወንዶች በኩል ከ56 ኪሎ ግራም ጀምሮ ውድድሩ የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ምድብ፤ የትግራይ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የአዲስ አበባ ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ሆነዋል። በ62 ኪሎ ግራም አሁንም ትግራይ ወርቅ ሲወስድ፣ አዲስ አበባ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በንር እና ነሃስ ወስደዋል። የ69 ኪሎ ግራሙን ውድድር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት አሸንፈዋል። በ85 ኪሎ ግራ የተካሄደውን የደቡብ ክልሉ እምነቱ ደጉ 192 ኪሎ ግራም በማንሳት ወርቁን ሲያነሳ፤ አመዲን ጀማል 176 ኪሎ በማሳት ብር እንዲሁም የአማራ ክልሉ ውብእድል አናጋው 174 ኪሎ አንስቶ ነሃስ ወስዷል። ከፍተኛ ፉክክር የታየበትን የ92 ኪሎ ግራም ምድብ ደግሞ የደቡብ ክልሉ ምህረተአብ በቀለ 214 ኪሎ ግራም በማንሳት አሸናፊ ሆኗል። የድሬዳዋ ተወዳደሪው ሀይልነት አወቀ 191 ኪሎ ሲያነሳ፤ ሶስተኛ የወጣው የሀረሪ ክልሉ ዮሴፍ ኩማ ደግሞ 135 ኪሎ ግራም አንስቷል።

ክፍል ስፖርት

 

ጃዋር መሀመድ

ጃዋር መሀመድ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በኦሮሚያ የተካሄዱ አመጾችን ከጀርባም ከፊትም ሆኖ በማስተባበር ይታወቃል። የሚወዱትም ሆነ የሚጠሉት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስል ውስጥ ሊፍቁት አይቻላቸውም።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለታየው ፖለቲካዊ ለውጥ የእርሱን የትግል ስልት በዋነኝነት የሚያነሱም በርካታ ናቸው። ናይሮቢ ለስራ በመጣበት ወቅት ሶስት ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሰንዝረንለታል።

ቢቢሲ (አማርኛ)፡-በዚህ ወቅት ሀገር ቤት ለመግባት ምክንያትህ ምንድን ነው?

ጃዋር፡- መጀመሪያም እኤአ በ2003 በ 17 አመቴ ከሀገር የወጣሁት ለትምህርት ነው። ከዛ በኋላም እየተመላለስኩ በየዓመቱ ጥናቴን የምሰራው እዛው ነበር። ነገሮች ከመንግስት ጋር እየተካረሩ ሲመጡ እንዲሁም ደግሞ ውጭ ቆይቼ ትግሉን መርዳት የምችልበት መንገድ ስለተገኘ ባለፉት ዓመታት ትግሉን በማህበራዊ ሚዲያም፣ በሚዲያም፣ በአካዳሚውም ትግሉን ስረዳ ነበረ። ያ ትግል ባይቋጭም በአብዛኛው ውጤት አምጥቷል። የነደፍነው ስልት ውጤት አምጥቶ በስርዓት ውስጥ ለውጥ አምጥቷል። የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ ነው ያለው። ወደ ዲሞክራሲ የምናደርገው ሽግግር በፍጥነት እየተካሄደ ነው። ከዚህ አንፃር ውጭ ከመቆየት ሀገር ውስጥ ገብቶ መስራት ይረዳል። በተለይ ደግሞ እየተደረገ ላለው ሽግግር ምሁራዊ እርዳታ፣ በሚዲያውም፣ ህዝብን በማስተባበር እርዳታ ማድረግ ያስፈልጋል። ገዢው ፓርቲ ላይም ጫና በመፍጠር ሽግግሩ በፍጥነት እንዲሄድና የተቃውሞ ኃይሉም በፍጥነት እየተዘጋጀ ለሽግግሩ አቅሙ እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ በትምህርትም በልምድም ያለኝን ለማካፈል ሚዲያውንም ደግሞ ለመምራትና ለማጠናከር አስፈላጊ ነው ብዬ ስላመንኩ በዚህ ወቅት ለመሄድ ወስኛለሁ።

ቢቢሲ (አማርኛ)፡- አንተ የምትታወቅበት የትግል ስልት አለ። ከዚህ በኋላ ያ የትግል ስልት ነው የሚቀጥለው ወይስ ሌላ የትግል መንገድ ይኖርሃል?

ጃዋር፡- የምትለው የሰላማዊ ትግሉን መሰለኝ። ሰላማዊ ትግል በተለያየ መልኩ ልትጠቀመው ትችላለህ። አንደኛው አምባገነናዊ ስርአትን ለመጣል ልትጠቀመው ትችላለህ። ከጦር የተሻለ ውጤት አለው። በዚህ የዛሬ አስራ ምናምን ዓመት ስከራከር ሰዎች ይስቁ ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጣው ለውጥ ትልቅ መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ ግን በጦር ቢሆን ኖሮ መስዋዕትነቱ እጥፍ ድርብ ነበር። የሚመጣውም ለውጥ ከፍተኛ ውድመትን ሊያስከትል ይችል የነበረ ሲሆን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገርም ብዙ እድል አይኖርም ነበር። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል በህዝባችን ውስጥ እንዲተዋወቅና ህዝባችን ከውጭ ያሉ ወይም ደግሞ በጫካ ያሉ አማፅያንን ከመጠበቅ ይልቅ በየቦታው በየሰፈሩ እንዲታገል ማድረጉ ጠቃሚ ነው። እና ሰላማዊ ትግል አምባገነን ስርዓትን ለመጣል ይረዳል። በሁለተኛነት ደግሞ አምባገነናዊ ስርዓትን ከገለበጥክ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ይረዳል። አሁን እያየህ ያለኸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደረገው ድጋፍ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን ለውጥን ለማበረታታትና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲፋጠን ሽግግሩን የሚያደናቅፉ ኃይሎችን ተስፋ ለማስቆረጥም ነው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል አምባገነናዊ ስርዓትን ለመገልበጥም ከዛ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትም ይረዳሃል ማለት ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኃይል ሁለት ነው። አንድ የመንግስት ኃይል፤ ሁለተኛው የህዝብ ኃይል አለ። የመንግስት ኃይል አሁንም በአብዛኛው ለውጥ በማይፈልጉት እጅ ነው ያለው። እነሱ ናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠልፈው ሊጥሉ የነበሩት። ግን ህዝባችን በሰላማዊ ትግል በደንብ ስለታነፀ በቀላሉ ሊያከሽፍባቸው ቻለ።

ወደ ዲሞክራሲ ከተሸጋገርን በኋላም ይህ ስልት ይረዳል። ፀረ ሙስና ላይ መስራት ትችላለህ። የሚዲያ ኃላፊነትን የማጠናከር ስራ ላይ ማተኮር ትችላለህ። በህዝቦች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የምትከላከልበት ብዙ ስልቶች አሉ። እነዚህን ነገሮች ማስተማር እፈልጋለሁ። ሀገር ቤት ስገባ አንዱ ማድረግ የምፈልገው ከሚዲያው አንፃር ‘ቲንክ ታንክ' ማቋቋም እፈልጋለሁ። ከዛው ጋር በተያያዘ ደግሞ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአመራር ስልጠና ተቋም በተለይም ከስር የሚወጣውን ወጣት ብቁ አመራር እንዲወጣው ለማድረግ። ሀገራችን ብዙ ስጦታ አላት፤ ብዙ ልጆች ይወለዳሉ፤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የአመራር ክህሎትን በተፈጥሮ እንዲሁም በትምህርት ታገኘዋለህ። የተፈጥሮ ክህሎት ያላቸውን ልጆች በማሰልጠንና በማጠንከር እንዲተዋወቁ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ ይቻላል፤ እዚህ ላይ እንግዲህ እኔም የተማርኩት አለ፤ ከኔም ጋር የሚሰሩ ባልደረቦች አሉ፤ በዚህ ላይ መስራት እንፈልጋለን ወደፊት።

ቢቢሲ (አማርኛ)፡- ብዙ ጊዜ ለነፃነትና ለለውጥ ሲታገሉ የሚቆዩ ሰዎች እድሉን ካገኙ በኋላ ጭልጥ ካለ ተቃዋሚነት ወደ ጭልጥ ያለ አመስጋኝነት የሚዘዋወሩበት አጋጣሚ ይኖራል። አንተን የምናውቅህ ስርአቱን በመንቀፍ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ጋር ያለህ መልካም ግንኙነት ወትሮ የምትታወቅበትን የትግል መልክ ምን ያህል ይለውጠዋል?

ጃዋር፡- እኔ እንደውም የምፈራው ቋሚ ተቃዋሚ እንዳልሆን ነው። ምክንያቱም እኔ አንደኛ የመንግስት ስልጣን የመያዝ ፍላጎት የለኝም። መንግስት ሲባል ደግሞ ሁሌም መግፋት አለብህ። የኛ ወጣቶች ማወቅ ያለባቸው መንግስት ሁሌም ካልገፋኸው አስቸጋሪ ነው። መደገፍ ጥሩ ነው። ግን ከደገፍከው ውስጥ ገብተህ ባለህ እውቀትና ባለህ ችሎታ መርዳት መቻል አለብህ። ከኦህዴድ ልጆች ጋር ስንከራከር የነበረውም፤ ይኸው ነው። ኦህዴድን የሚደግፉ ልጆች ቁጭ ብሎ ለኦህዴድ ማጨብጨብ ዋጋ የለውም። ለአብይ ሰልፍ መውጣት ማጨብጨብ የአንድ ቀን ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በመለስ ዜናዊ እና በኢህአዴግ ጊዜ እውቀት ያለው ችሎታ ያለው ተገፍቶ ወጥቷል። አሁን ያን ችሎታና እውቀት ወደ ሀገር በመመለስ የሀገሪቷን ቢሮክራሲ ውስጥ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች አቅምን መጨመር ያስፈልጋል።

መንግስትን የሚወዱ፣ አብይን የሚወዱ የተለወጠውን ኢህአዴግን እንወዳለን የሚሉ ሰዎች ማጨብጨብ አይደለም የሚያስፈልጋቸው። ገብተው በችሎታቸው መርዳት መቻል አለባቸው። ብዙዎች ደግሞ እየገቡ እየረዱ ነው። በፖለቲካ መንግስት ውስጥ መግባት የማንፈልግ ነገር ግን በሲቪክ ማህበረሰቡ ውስጥ መቆየት የምንፈልግ ሰዎች ወደድንም ጠላንም ተቃዋሚ ሆነን ነው የምንቀጥለው። ተቃዋሚ እንደተቃዋሚ ፓርቲ ሳይሆን የመንግስት ተቺዎች ሆነን ነው የምንቀጥለው። ምክንያቱም አክቲቪስት ከሆንክ ልትረካ አትችልም። ምንም ቢያደርግ መንግስት ሊያስድስትህ አይችልም። ምክንያቱም አንድ ነገር ከሟላልህ አሁንም ሌላ የሚጎድል ነገር አለ። አይደለም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፍትህ እጦት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ብዙ ነገሮች ያሉበትን ሀገር ተውና እኔ በምኖርበት አሜሪካ ወይንም ደግሞ ገነት በምትላት እንደ ስዊድንና ኖርዌይ ራሱ አክቲቪዝም መሰረታዊ ፍላጎት ነው።

ሙስናን ለመታገል መንግስት ብቃቱ እንዲጨምር አቃቂር እያወጣህ መግፋት መቻል አለብህ። እናም ወደፊት በማደርገው ሂደት እርግጥ ነው ከዚህ በፊት እንደማደርገው ጭልጥ ያለ ተቃውሞ ውስጥ መቀጠል አልችልም። ይሄንን አፍርሱ ይሄንን ናዱ ማለት አልችልም። ምክንያቱም እኔና ሌሎች ያለብን አንዱ ችግር ባለፉት አራት ዓመታት ወጣቱ መንግስት እንዲያፈርስ (ወጣቱ መንግስት የማፍረስና የማሽመድመድ) አሰልጥንነዋል። በአሁኑ ወቅት እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር መንግስት አለ ማለት አይቻልም። ከታች ያለውን መዋቅር አሽመድምደነዋል። ይህን ወጣት እንደገና ዲሞክራሲን የመገንባት፤ ሀገርን መልሶ የመገንባት ክህሎት ማስተማር መቻል አለብን። እና ያንን ከመንግስት ጋር እየተረዳዳን የምንሰራው ብዙ ነገር አለ።

በተለይ ደግሞ አሁን ባለው ሽግግር ላይ መንግስትን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እደግፋለሁ። ምክንያቱም ሀገሪቱ ወደ ገደል እየሄደች ሳለች ነው ትንሽ ያስቀየሳት እርሱ። ወደ ገደል ሊመሯት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር መሆን አንችልም። አሁን ያለን እድል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመቆም የሚያጠፋቸውን ነገሮች እየተቸን ግን በተለይ ይህንን ለውጥ ሊያኮላሹና ሊያከሽፉ የሚፈልጉ ኃይሎች ባለን ተሰሚነትና ባለን እውቀት ባለን ስልት እያዳከምን ሀገሪቷን ወደፊት ማሻገር አለብን።

ሀገሪቷ ወደ ብጥብጥ እንዳትሄድ እንደገና ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም አምባገነን ሊያደርጉት ይችላሉ። እየነካኩ ከሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይል ወደ መጠቀም ወደ አምባገነንነት የሚሄድበት እድል ሊኖር ይችላል። ፈልገው ሳይሆን ሳያውቁ አምባገነን የሆኑ ብዙ አምባገነኖች አሉ። ሁኔታዎች ወደዛ ይገፏቸዋል።

አለበለዚያ ደግሞ እርሱን ገልብጠው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያስገቡን ለምሳሌ አሁን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ቢገሉት ኖሮ ለውጥን የሚደግፈው የኛ ወገንም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድበት ሁኔታ ነበረ። ያ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይከተናል። እና እዛ ውስጥ እንዳንገባ ከመንግስት ሰዎች ጋር እንወያያለን።

በበለጠ ደግሞ የተቃውሞውን አቅም ማጠናከር እፈልጋለሁ። እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም። ግን ክህሎቶች አሉኝ የተማርኳቸው ስልቶች አሉ። እድሜ ልኬን ይሄንን ነው የሰራሁት። በዚህ የተቃውሞ ኃይል ወደ አንድ እንዲመጣ እንዲጠናከር የሚሰራውን ስራ በስትራቴጂ እየደገፈ እንዲሄድ እፈልጋለው። ጠንካራ ተቃዋሚ የሌለበት ሀገር ውስጥ ዲሞክራሲን መገንባት አትችልም፤ የአማራጭ ፖሊሲዎች ብፌም ሊኖረው ይገባል የኛ ህዝብ። ዝም ብሎ ዶሮ ወጥ ቢበላ የኛ ህዝብ ይደብረዋል ሽሮ መኖር አለበት። እና ይሄ የተወዳዳሪ እድል ምርጫ ሊኖረው ይገባል የኛ ህዝብ።

እኛና ሌሎች ባለፉት ዓመታት ስርዓቱን የማዳከም ስራ ስርተናል። በጣም በተዋጣ መልኩ። በ2020 እዚህ እንደርሳለን እንል ነበር። ነገር ግን ፍጥነቱ በጣም ስለሄደ አሁን እዚህ ደርሰናል። እርሱ ራሱ ችግር አለው። አሁን ደግሞ በተቀሩት አመታት አትሊስት በ2020 ወደ ሙሉ ዲሞክራሲ እንድንሸጋገር ከዛ በኋላ ደግሞ የተሸጋገርንበት ዲሞክራሲ እየተጠናከረ እንዲሄድ የሚመጣው መንግስት በተለይ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን እየፈታ እንዲሄድ እናስባለን። አሁን እዚህ የመጣሁት (ናይሮቢ) አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩት ያሉት ሁኔታ አለ። ለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደት በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ እምቅ ኃይል አላት ትልቅ የሆነ ሃብትም አላት። ይህንን ሃብት ከአካባቢው ህዝቦች ጋር የኢኮኖሚ ቁርኝት በማድረግ ማሳደግ መቻል አለባት። ከኤርትራ ጋር እየተደረገ ያለው ነገር በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ሰዎች ከኤርትራ ጋር ያለውን ጉዳይ ከፖለቲካ አንፃር ብቻ ነው እያዩ ያሉት። ፖለቲካውን ለጊዜው ገሸሽ አድርገነው ኢኮኖሚው ላይ እያተኮርን መሄድ መቻል አለብን። ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ መሄድ መቻል አለበት። ከኬኒያ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ መሄድ መቻል አለበት።

ይሄንን መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ይሰራል። እኛ ደግሞ ያንን መንግስት የሚያመጣውን ፖሊሲ አስቀድመን ጥናት በማድረግ በተለያዩ ኮንፍረንሶች በተለያዩ የጥናት ወረቀቶች በተለያዩ ሚዲያዎች ህዝቡን ማዘጋጀት መቻል አለብን። እና እንግዲህ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ነው መስራት የምፈልገው።¾

ክፍል ምልከታ

 

የክልላችን ሕዝብ ህጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይፈታ!!

የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ብሔር ብሔረሰቦች) ላለፉት በርካታ ዓመታትና ተከታታይ መንግስታት ዘመን ከግፍ-ወደ ግፍ፣ ከበደል ወደ በደል፣ ከጭቆና ወደ ጭቆና አገዛዝ በመሸጋገር የስቃይና የመከራ ቀንበር ተሸክመው ዛሬ ላሉበት ደረጃ ደርሷል። በዛሬ ላይ ሆነውም ከግፍ፣ ከበደልና ከጭቆና አገዛዝ መውጣት ስላልቻሉ ከዚህ ለመላቀቅና ከስቃይና መከራ ህይወት ለመውጣት በሚችሉት መንገድና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመታገል ላይ ይገኛሉ።

ይህ በኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሔር- ብሔረሰቦች) ላይ ሲደርስ የቆየውና አሁንም እየደረሰ ያለው ግፍ፣ በደልና ጭቆና አገዛዝ ቀንበር የበለጠ የተጫነው እና የሲቃይና መከራ ህይወት ሸክሙ እጅግ የከበደው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚኖሩ ብሔር-ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ ነው። በመሆኑም ይህ ሰሞኑን በክልሉ የተከሰተው ፀብ፣ ግጭት፣ ዝርፊያ፣ ሞትና እንግልት በአጋጣሚና በድንገት የመጣና የተፈጠረ ሳይሆን ላለፉት 27 ዓመታት የነበረው የግፍ፣ የበደልና የጭቆና አገዛዝ የፈጠረውና የወለደው የእምቢተኝነት ውጤት ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሔር- ብሔረሰቦች) ላለፉት 27 ዓመታት ሌላው ይቅርና በአካባቢያቸውና በአቅራቢያቸው አስተዳደርና የፍትህ አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርገውና አጥተው ኖረዋል። ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ የክልሉን ሕዝብ (ብሔር- ብሔረሰቦችን) ብሶትና ምሬት በመጨመርና በማባባስ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጓል። ይህ የሕዝቡ ተስፋ መቁረጥ አሁን በክልሉ ውስጥ በየቦታው እየተከሰተው ያለው ፀብ፣ ግጭትና አደጋ እንዲፈጠር አድርጓል።

የአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ በቀደሙት መንግስታት ዘመን በተለያየ ክፍለ-ሀገሮችና የአስተዳደር ክልሎች ተዋቅሮ ይኖርና ይተዳደር የነበረ ሕዝብ ነው። ህዝቡ በተለያየ ክፍለ ሀገሮችና የአስተዳደር ክልሎች ተዋቅሮ ሲተዳደርም ሆነ ሲኖር እርስ በርሱ ተባብሮ፣ ተቻችሎና ተግባብቶ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት የኖረ ሕዝብ ነው። ነገር ግን ይህ የህዝቡ ተባብሮ፣ ተግባብቶና ተቻችሎ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት የመኖር ልምድና ባህል በክልሉ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በደልና ጭቆና ምክንያት እና የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት የተነሳ በአደጋ ላይ ወድቋል። በመሆኑም በክልሉ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ዋስትና አጥቷል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ሕዝብ (ብሔር- ብሔረሰቦች) በኢትዮጵያ አንድነት ስር ሆነው ራሴን በራሴ የማስተዳድርበት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ክልል ይሰጠኝ የሚል ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ። ይህ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ዛሬ ላይ በስፋት ይስተጋባ እንጂ ላለፉት 27 ዓመታት ሲነሳና ሲወድቅ የመጣ ጥያቄ ነው። ስለዚህ፡-

$11.  የክልሉ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄን በኃይልና በጉልበት ለማፈንና በልዩ ልዩ መንገድ ለመቀልበስ የሚደረገው ሩጫ እንዲቆምና ለሚነሳው ሕዝባዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ፣

$12.  በክልሉ ለመልካምና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና፣ ለፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ለፍትሃዊ የልማትና የኢኮኖሚ ስርጭት ተደራሽነት አመቺ የሆነ፣ ተቀራራቢ የሕዝብ አሰፋፈር፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትና የህዝብን ማህበራዊ ትስስርን ማዕከል ያደረገ ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር እንዲፈጠር፣

$13.  መንግስት በክልሉ ያሉ ዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲያከብር፣ የህዝቡን (የብሔር - ብሐየረሰቦችን) ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄ እንዲያዳምጥ፣ በክልሉ የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ የመኖር፣ ዋስትና እንዲረጋገጥ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኮንግረስ (የደቡብ ኮንግረስ)

            ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

            24/10/2010 ዓ.ም

                  ሀዋሳ

ክፍል የኔ ሃሳብ
Page 1 of 3

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 666 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us