You are here:መነሻ ገፅ»ኢኮኖሚ

በሀገራችን ብሎም በአፍሪካ አሳሳቢ የሆነውንና አሜሪካ መጤ ተምች ተብሎ የሚጠራውን ፀረ ሰብል ተምች ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ሲሆኑ በዚሁ ዙሪያ አንድ የተቀናጀ መፍትሄን ለመፈለግ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሰፊው ሲመክሩ ሰንብተዋል። ይህ በአማርኛ “አሜሪካ መጤ ተምች” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፀረ ሰብል ተባይ፤ በእንግሊዘኛ ፎል አርሚዎርም (Fall Army worm) በሚል ይጠሩታል። በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ከሰሞኑ በተካሄደው የሁለት ቀናት ውይይት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተገኙ ተመራማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮችና የመንግስት ሀላፊዎች ተገኝተዋል። መድረኩን ያዘጋጀው የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት እና ሥነ ምህዳር ማዕከል (International Center of Insects Physiology and Ecology) ሲሆን ይህ ተቋም “የተቀናጀ ተባይ መከላከል ድርጅትም” የጋር ሥራን ሰርቷል።

በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት እና ሥነ ምህዳር ማዕከል የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ታደሰ፤ ተባዩን በመከላከሉ ረገድ ውይይቱ በዋነኝነት ሀገራት እንደዚሁም የምርምር ባለሙያዎችና ለጋሽ ድርጅቶች ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ መሆኑን ገልፀውልናል። ተባዩ ከተከሰተባቸው ተወክለው የመጡ የተለያዩ ባለሙያዎች የየሀገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ በሰፊው በማብራራት መፍትሄ በማፈላለጉ ረገድ እየወሰዷቸው ያሏቸውን የመከላከል እርምጃዎች በመድረኩ ላይ በማቅረብ የልምድ ልውውጥን አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ  የተገኙት ልምዶች ተቀምረው በምክረ ሀሳብ ደረጃ ለቀጣይ መፍትሄም እንዲያገለግሉ ይደረጋል ተብሏል። አቶ ደሳለኝ ተባዩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን፤ ብዙ ያልተጠኑ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ስላሉትና ፈጣን የሆነ ውድመትም ስለሚያስከትል የአጭር ጊዜ መፍትሄ ከማፈላለጉ አንፃር ሀገራት ተቀናጅተው መስራታቸው የግድ መሆኑን ይገልፃሉ። የጋራ መከላከሉም ሂደት በተለይ ግንዛቤ ማስጨበጡ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው ጨምረው ገልፀውልናል።

በዚሁ መድረክ ላይ ከተሰራጨው መረጃ መረዳት እንደቻልነው ይሄው አሜሪካ መጤ ተምች በመባል የሚታወቀው የተባይ አይነት መነሻው ተደርጎ የሚገመተው ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ነው። የዚህ ተምች እጩ (ትልም) ከ80 በላይ የሚሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን ዋነኛ የጥቃቱ ዒላማ ተደርገው የሚወሰዱት ግን በቆሎና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ናቸው። በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የበቆሎ ምርት ተመጋቢ የህብረተሰብ ክፍል ያለ ሲሆን የዚህንም አደገኛ ተባይ  ስርጭት በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ የአህጉሪቱ ህዝብ ራሱን በምግብ የመቻል ጥረቱ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

 በዚሁ መድረክ ላይ ከቀረበው ጥናት መረዳት እንደተቻለው በቆሎ ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት በሄክታር የሚሸፍነው እስከ 35 ነጥብ 8 ሚሊዮን ይደርሳል። ጥናታቸውን ያቀረቡት ከዓለም አቀፉ የሥነ ነፍሳት እና ሥነ ምህዳር ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ተባዩ መነሻው ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ እንደሆነ ይነገር እንጂ በአፍሪካ አህጉር መታየት በምዕራባዊው የአህጉሪቱ ክፍል  እ.ኤ.አ በ2016 ነው።

ተባዩ በፍጥነት በመሰራጨት በአሁኑ ሰዓት ከሃያ በላይ የአፍሪካ ሀገራትን ያዳረሰ መሆኑ ታውቋል። በኢትዮጵያም ተባዩ ለመጀሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2017 በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተከሰተ መሆኑን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቀላል የማይባለውን የሀገሪቱን ሰፊ ቆዳ ሽፋን በማካለል ጉዳት አድርሷል። በመድረኩ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የዓለም አቀፉ የሥነ ነፍሳት እና ሥነ ምህዳር ማዕከል (icipe) ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ተፈራ መድረኩ ሁለት መሰረታዊ አላማዎችን ለማሳካት ታሳቢ  አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀውልናል።

እንደሳቸው ገለፃ መድረኩ የተዘጋጀው በአንድ መልኩ ግንዛቤ ለመፍጠር ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በሀገራትና በባለድርሻ አካላት መካከል የልምድ ለውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ነው። የተለያዩ ሀገራት ተወካዮችና ተመራማሪዎች ተምቹን ለመቆጣጠር እየወሰዱት ስላለው እርምጃ በመድረኩ ላይ ያቀረቡ ሲሆን እንደ ዶክተር ታደለ ገለፃ ኢትዮጵያም በመድረኩ የቀረቡትን ልምዶችና ምክረ ሀሳቦች በመውሰድ ቀምራ የምትጠቀምበት መሆኗን ገልፀውልናል። እንደ ዶክተር ታደለ ተፈራ ገለፃ  የተምቹ ተስፋፊነት እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በ 6 ወራት ጊዚያት ውስጥ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ተባዩ የተከሰተ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል። በኢትዮጵያም ቢሆን ተምቹ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከታየ ብዙም ሩቅ ባይሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን ከስድስት ያላነሱ ክልሎች የተምቹን መከሰት ሪፖርት ያደረጉ መሆኑን ዶክተር ታደለ ተፈራ ገልፀውልናል።

ተምቹ በእጭ ወይንም በትል ደረጃ የሰብሎችን በተለይም የለጋ በቆሎ ቅጠልና ማቀፊያ ውስጥ ፈልፍሎ በመግባት የሚመገበው ሲሆን ጉዳቱ በስፋት የሚታየው ሰብሉ ገና በእንጭጭነት የእድገት ወቅቱ መሆኑን ዶክተር ታደለ ተፈራ ገልፀውልናል። እንደ ዶክተር ታደለ ተፈራ ገለፃ ሰብሉ የእንጭነት ጊዜውን ካለፈ በኋላ ግን ራሱን የመከላከል አዝማሚያ ስለሚታይበት በመከላከሉ በኩል ሰፊ ትኩረት ሊደረግ የሚገባው በሰብሉ በሰብሉ የመጀመሪያ የእድገት ደረጃ ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት ተምቹን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ያለው በእጅ በመልቀምና በመግደል ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ተምቹ በእሳት ራት ደረጃ እያለም በመያዣ ወጥመዶች በመጠቀም በሄክታር ከ 4 እስከ 6 የሚሆን ተምችን በመያዝ ማስወገድ የሚቻልበት ሁኔታም ያለ መሆኑ ታውቋል። የኬሚካል ርጭት አንዱ የመከላከል መፍትሄ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በተጨማሪም ተባዩን ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም ሌላኛው መፍትሄ ተደርጎ ተወስዷል። ነፍሳትን የሚያጠቁ ረቂቅ ፍጥረታትን መጠቀም፣ ከዕፀዋት የሚቀመሙ መርዛማ የተፈጥሮ ኬሚካሎችን ጥቅም ላይ መዋሉም አንዱ የመከላከል ዘዴ ተደርጎ በምክረ ሀሳብነት የተቀመጠ ነው።

ተምቹ ካደረሰው ጉዳት አንፃር በቀጣዩ ዓመት ምርታማነት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ሀገር አቀፍ አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ ይህ ነው ሊባል የሚችል መረጃ ያልወጣ መሆኑን ዶክተር ተፈራ ጨምረው ገልፀውልናል።

ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከነበሩት የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ ቀደም ሲል ሲጠቀምበት የነበረውን አርማ በአዲስ አርማ (ሎጎ) የቀየረ መሆኑን ባለፈው ሀሙስ ሀምሌ 6 ቀን 2009 ቀን አስታውቋል። በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው በዚሁ ፕሮግራም ላይ የቀደመውን አርማ ለምን በአዲስ አርማ መቀየር እንዳስፈለገ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አርአያ ገብረ እግዘአብሄር ባንኩ ከ2 ዓመት  በፊት በአፍሪካ ካሉት አስር ስመጥር ባንኮች አንዱ ለመሆን ራዕይ ቀርፆ የነበረ መሆኑን አስታውሰው አርማውም ከዚሁ ራዕይ ጋር ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ በአዲስ መልክ የተቀረፀ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪቀደም ሲል የነበረው ዓርማ ለአንዳንድ የህትመት ሥራዎች ተስማሚ እንዳልነበርና በአዲስ መልኩ ለመቀየሩ ስራም አንዱ ምክንያት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል።

 በቅርቡም አርማው በባንኩ ቅርንጫፍ መስሪያቤቶች ስራ ላይ እንዲውል የመቀየር ሥራው ይሰራል ተብሏል። ባንኩ ላላፉት 20 ዓመታት ባንኩ ሲጠቀምበት የነበረውን አርማ ሲቀይር ያለፈውን ጊዜ ስኬት፣ የወደፊቱን ብሩህ ተስፋና  ዛሬ ላይ የደረሰበትን ፅኑ መሰረት እንዲያንፀባርቅና  የመጪውን ትውልድ ስሜትና ዝንባሌ ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል።

 አርማው ላለፉት 12 ወራት ያህል ሲዘጋጅ የቆየው መሆኑ ታውቋል። አዲሱ አርማ ከቀረቡት የተለያዩ አመራጮች መካከል ከመመረጡ በፊት በተለያዩ የግምገማ ሂደቶች አልፎና የተለያዩ ሙያዊ አስተያየቶች ሲሰጡበት ከቆየ በኋላ በመጨረሻ በባንኩ በማኔጅመንትና ዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ተቀባይነት አግኝቶ የፀደቀ መሆኑን ሀላዎቹ አመለክተዋል። ባንኩ አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ያስገነባውን ዋና መስሪያ ቤት በቀርቡ በማስመረቅ በዋና መስሪያቤትነት የሚጠቀምበት መሆኑን በዕለቱ ከተደረገው ገለፃ መረዳት ችለናል።

የሀገር ውስጥ ፊልሞችንና የሙዚቃ ክሊፖችን  ውጪ ሄዶ ማስቀረፅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ ነው ያለው የናይጄሪያ የኢንፎርሜሽንና የባህል ሚኒስቴር በቀጣይ በዚህ አካሄድ ላይ እገዳ የሚጥል መሆኑን አስታውቋል። የሀገሪቱ የኢንፎርሜሽንና ባህል ሚኒስትር ላኢ ሞሀመድ እንደገለፁት በመንግስት በኩል የተደረጉት ጥናቶች የሚያሳዩት በናይጄሪያዊያን ለናይጀሪያዊያን የሚሰሩት የጥበብ ውጤቶች በዚያው በሀገረ ናይጄሪያ ምድር መሰራት ያለባቸው መሆኑን ነው።

በናይጄሪያ ፊልሞችን እና የሙዚቃ ክሊፖችን በእንግሊዝ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በዱባይ፣ በሲሸልስ፣ በደቡብና ሰሜን አሜሪካ እንደዚሁም በካረቢያን ሀገራት መቅረፅ የተለመደ ሲሆን ይህም ልምድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ይገልፃል። በዚሁ ዙሪያ በሚኒስትሩ የተሰጠውን መግለጫ ተከትሎ በርካታ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። የናይጄሪያ መንግስት ከመነሻው ለጥበቡ ኢንዱስትሪ ተገቢውን ድጋፍ ያደረገበት ሁኔታ ያለመኖሩን ያመለከቱት ባለሙያዎቹ፤ መንግስት በኢኮኖሚ ስም የራሱን የቁጥጥር መረብ ለመዘርጋት በማሰብ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ባቀረቡት መከራከሪያ ሀሳብ ናይጀሪያዊያን አርቲስቶችና ባለሙያዎች ለዜጎቻቸው የሚቀርብን የጥበብ ስራ ውጭ አቀነባብሮ መልሶ ለናይጀሪያዊያን ማቅረብ አንድን የናይጀሪያ ጥሬ እቃ ወስዶ በሌላ ሀገር አምርቶ መልሶ ለራሳቸው ለናይጀሪያዊያን ከማቅረብ ጋር አንድ አይነት ነው የሚል ነው። “ይህም ናይጀሪያን በጥበብ ስም የሸቀጥ ማራገፊያ ማድረግ ነው” ያሉት ሚስተር  ሞሃመድ፤ በጊዜ እልባት ያገኝ ዘንድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን አመልክተዋል። ይህ የመንግስት ሀሳብ መቼ ወደ መሬት እንደሚወርድ ባይታወቅም ትግበራው ግን ከባድ ፈተና የሚገጥመው መሆኑን በርካቶች እየገለፁ ነው። ሰሞኑን በርካታ አለም ዓቀፍ የናይጀሪያ ሚዲያዎች ጉዳዩን እየተቀባበሉ በስፋት መነጋገሪያ አድርገውት ሰንብተዋል።

በኢትዮጵያ ከመንግስት ንብረት ግዢ ጋር በተያያዘ ቀላል የማይባል የሀብት ብክነት መኖሩን በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመንግስት የግዢ ስርዓት ለመለወጥ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ከለውጦቹ መካከልም የማዕቀፍ ግዢ በሚል የሚጠራ አሰራርን እውን ማድረግ ነው።

 የመንግስትን የማዕቀፍ ግዢ አፈፃፀም እና ንብረት ማስወገድን በተመለከተ ጥናት ሲያደርግ የቆየው የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት ከሰሞኑ ለባለድርሻ አካላት ባቀረበው ሪፖርት የግዢ ብሎም ንብረትን የማስወገድ ሥርዓቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን አመልክቷል። ይሄው ጥናት  በአዲስ አበባ የሚገኙ 55 የፌደራል የመንግስት መስሪያቤቶችንና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችን እንደዚሁም ስምንት አቅራቢ ድርጅቶችን በመዳሰስ መረጃዎችን የሰበሰበ መሆኑ ተመልክቷል።

 ከዚህ ቀደም የመንግስት ግዢዎች ሲፈፀሙ በየጊዜው ጨረታዎች የሚወጡበት ሁኔታ ስለሚኖርና አቅራቢዎችም ብዙም ሳይቆዩ በየጊዜው የሚቀያየሩበት ሁኔታ ስለነበር በርካታ ዝርክርክ አሰራሮች ሲከሰቱ የቆየ መሆኑ በዚህ ጥናት ተመልክቷል። ይሄው የማዕቀፍ ግዢ በሚባል የሚታወቀው የግዢ አይነት  በየጊዜው ጨረታ በማውጣት በርካታ አቅራቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚቀያየሩበት ወቅት የሚፈጠረውን ውጣ ውረድና የጊዜ ብክነት በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም አሰራር ጨረታዎች በአጭር ጊዜና በተደጋጋሚ በሚወጡበት ወቅት ሊኖር የሚችለውን ሙስና እና የብልሹ አሰራር ክፍተት ለመከላከል የሚረዳ መሆኑንም ጥናቱ ጨምሮ ያመለክታል።

 በአንድ ሀገር የመንግስት ግዢ ከፍተኛውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ድርሻ ይይዛል። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙም የግሉ ዘርፍ ባልዳበረበት ሀገር ደግሞ የመንግስት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሰፊውን ድርሻ ስለሚይዝ የግዢ መጠኑም በዚያው መጠን ሰፊ መሆኑ ይታወቃል። በዚሁ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ሀገራት ከአጠቃላይ ዓመታዊ በጀታቸው ውስጥ ከ 60 እስከ 64 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ የሚውለው ለግዢ (Public procurment) ነው። ይሄው ጥናት የሀገራችንንም የመንግስት በጀት ግዢ መጠንንም ጭምር የዳሰሰ ሲሆን ከአጠቃላይ የመንግስት በጀት ውስጥም 62 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑን አመልክቷል። ይህም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ውስጥ እስከ 15 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል።

ይህንንም አሰራር ለመቀየር የማዕቀፍ ግዢ በሚል የሚጠራ አሰራር መተግበር የጀመረ መሆኑን ይሄው ጥናት ያመለክታል። በጥናቱ መሰረት የማዕቀፍ ግዢ ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር  ወደ ፊት የሚገዙትን እቃዎች ወይም አገልግሎቶች በማደራጀት የውል ስምምነት ላይ መድረስና የውል ስምምነት ጊዜው እስኪጠናቀቅ ድረስም ሌላ ጨረታ ማውጣት አይጠበቅም። ይህም ሆኖ ግን በፌደራል የመንግስት ግዢዎች ያሉትን ችግሮች በተገቢው ሁኔታ መቅረፍ አልተቻለም።

የቀረበውን ጥናት ተከትሎ ሰፋ ያለ ውይይትም ተካሂዷል። በግዢ በኩል ያለውን ችግር በተመለከተ በተለይ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው በጥናቱ መድረክ ላይ የተገኙት ባለሙያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ተሳታፊ አስተያየት ሰጪዎቹ ከአቅራቢዎች ጋር ውል ከፈፀሙ በኋላ ንብረቱ በጊዜ አለመድረስ፣ ንብረቱ ቢደርስም እንኳን በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ መሆኑ፣የሚቀርበው እቃ የጥራት ጉድለት እንደዚሁም ንብረቱን ከአቅራቢው መጋዘን በገዢው ትራንስፖርት እንዲጓጓዝ የመፈለግና የማድረግ ችግሮችም በዋነኝነት ተነስተዋል። በተለይ የዕቃዎቹ በጊዜ አለማቅረብ በበጀት በሚተዳደሩ መስሪያቤቶች ላይ የበጀት አጠቃቀም ቀውስን እየፈጠረ መሆኑን ጭምር ይሄው ጥናት አመልክቷል። ዕቃዎቹ በጊዜ አለመቅረባቸው በበጀት አጠቃቀም ላይ ችግር ከመፍጠር ባሻገር በአሰራር ላይም ሳይቀር ተጨማሪ ችግር እንቅፋት እየሆነ መሄዱ ተገልጿል።

 እንኳን ሌላ የፅህፈት መሳሪያ አቅራቢ ድርጅቶች ሳይቀሩ ወረቀትን ጨምሮ፣ ወረቀትን፣ ቶነርንና የመሳሰሉትን የፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ግብዓቶች በተገቢው ጊዜ የማያቀርቡበት ሁኔታ በመኖሩ ተማሪዎች በተቀመጠው የትምህርትና የፈተና የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፈተናዎችን እንዳይወስዱ ምክንያት እየሆነ መሄዱም በዚሁ ጥናት ተዳሷል። ይህም ተማሪዎች ከትምህርት ፕሮግራሙ ውጪ ተጨማሪ ጊዜያትን በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እንዲያሳልፉ በማድረግ ተጨማሪ የምገባ በጀት እንዲወጣ እያደረገም ነው ተብሏል። አንዳንድ ጊዜ ዕቃዎቹ በተፈለገው ጊዜ ሳይቀርቡ ቀርተው የበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ በሚደርስበት ወቅትም የበጀት መመለስ ችግሮች የሚፈጠሩበት ሁኔታ መኖሩንም ይሄው ጥናት አመልክቷል። በአቅራቢዎች በኩል የመንግስትን ንብረት አሰራር፣ህግና መመሪያ በሚገባ አለማወቅ  ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ተደርጎ ተጠቅሷል። ይህንንም ችግር ለመፍታት ተቋማቱ ለሰራተኞቻቸው የመንግስት ግዢና ስርዓትን በተመለከተ ተገቢው እውቀት እንዲኖራቸው ስልጠናዎች ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑ ተመልክቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ሆነ በአቅራቢዎች በኩል ያሉ ክፍሎችን ወይንም ዲፓርትመንቶችን በተገቢው ባለሙያ ማዋቀር የሚገባ መሆኑንም ይህ ጥናት በምክረ ሀሳቡ ያስቀምጣል።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የሚቀርቡ ንብረቶችን አጠቃቀም በተመለከተ ከአምራቹ ወይንም ከአስመጪው ውጪ ገዢው አካል የማያውቃቸው መሆኑና አቅራቢው ንብረቱን ከማቅረብ ባለፈ የንብረቶቹን አጠቃቀም በተመለከተ የባለሙያ ድጋፍ ጭምር አካቶ የማይሰጥበት ሁኔታ መኖሩ እንደ አንድ ችግር ተነስቷል። አንዳንዶቹ ንብረቶች ከሽያጭ በኋላ የሚኖረውን ጥገና በተመለከተ ንብረቱ አገልግሎት በሚሰጥበት አቅራቢያ የጥገና አገልግሎት ስለማይኖር ሁልጊዜም ንብረቶቹን አዲስ አበባ ድረስ በማጓጓዝ የጥገና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩም እንደ አንድ ችግር ተመልክቷል። በአቅራቢዎች በኩል አንድ አቅራቢ በገባው ውል መሰረት ንብረቱን ካቀረበ በኋላ በገዢው በኩል ንብረቱን በተረከበ በአምስት ቀናት ውስጥ ክፍያ መፈፀም የሚጠበቅበት ቢሆንም በተግባር ግን ይህ እንደማይሆን  ንብረቱ ለገዢዎች ካቀረበ በኋላም ክፍያን ለመውሰድ ከፍተኛ የሆነ መጉላላት የሚገጥማቸው መሆኑን ገልፀዋል።

 ከዚህም በተጨማሪ ለአንድ የመንግስት መስሪያቤት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ጨረታ አሸንፈው ውል ከገቡ በኋላ በሀገሪቱ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ንብረቶቹን ከውጭ በማስመጣት በተገቢው ጊዜ እንዳያቀርቡ እያደረጋቸው መሆኑንም አቅራቢዎቹ ገልፀዋል።  ከዚህም በተጨማሪ በወደብ አካባቢ የሚታየው ውጣ ውረድና ያልተቀናጀ የሎጂስቲክ ሁኔታም እቃዎች ሀገር ውስጥ ገብተው በጊዜ ወደ ተፈለገው ቦታ እንዳይሰራጩ አንዱ እንቅፋት መሆኑም በአቅራቢዎች በኩል የተነሳ ሌላኛው ቅሬታ ነው።

የንብረት አወጋገድ ችግሮች

 አንድ ንብረት ተገቢውን አገልግሎት ከሰጠ በኋላ  ወይንም የመጠቀሚያ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ በልዩ ልዩ ዘዴዎች እንዲወገድ ይደረጋል። እንደ ተሸከርካሪና ልዩ ልዩ የቢሮ መገልገያን የመሳሰሉ ንብረቶች በጨረታ የሚወገዱበት አሰራር አለ። ሆኖም በጥናቱ እንደተመለከተው በዚህ በኩልም በርካታ ችግሮች መኖራቸው ተመልክቷል። ንብረቶች በሽያጭ ሲወገዱ ከዋጋ በታች እንዲሸጡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩም ታውቋል። በሽያጭ መወገድ የሚገባቸው ንብረቶች በጊዜና በአግባቡ እንዲወገዱ ከማድረግ ይልቅ ንብረቶቹ በየጓሮው ተጥለው አፈር የሚበላቸው መሆኑንም ይሄው ጥናት ይገልፃል። አሮጌ ንብረቶችን በማስወገድ ስም አዳዲስ ንብረቶችን ለራስ ጥቅም የማዋል ሁኔታም መኖሩ ተጠቁሟል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በሶሪያ በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ሀገሪቱ በአጠቃላይ 226 ቢሊዮን ዶላር የከሰረች መሆኑን የዓለም ባንክ ጥናትን ዋቢ በማድረግ አዣንሽስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስታውቋል። ይሄው ጥናት ሶርያ በጦርነቱ 320 ሺህ ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች መሆኗን እንደዚሁም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝቧ ደግሞ በስደት ቀየውን ጥሎ የተበታተነ መሆኑን ያመለክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም 538 ሺህ የስራ እድልም ከኢኮኖሚው የቀነ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ይገልፃል።

ደቡብ ሱዳን ከገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ የነፃነት በአሏን በድግስ የማታከብር መሆኗን በማስታወቅ በዓሉ ታስቦ እንዲውል አድርጋለች። ሀገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት፣በድርቅና በረሃብ ውስጥ ስትሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿም በጎረቤት ሀገራትና በዚያው በደቡብ ሱዳን በስደት ይገኛሉ። ሀገሪቱ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መሆኗን ያመለከቱት ፕሬዝዳንት ሳልቫኪየር “በዚህ ወቅት ለነፃነት በዓል ወጪ ማውጣት አላስፈላጊ ነው” በማለት በዜጎች ላይ እየታየ ያለውን ችግርን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ በስፋት አትተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የነፃነት በዓሉ በወታደራዊ ሰልፍ፣ በአደባባይ ትርዒቶች፣ በሙዚቃ ዝግጅቶችና በመሳሰሉት ፈንጠዝያዎች የማይከበር መሆኑን ቀደም ብለው አመልክተው ነበር። ደቡብ ሱዳን በህዝበ ውሳኔ ከሱዳን በይፋ ተገንጥላ እንደ ሀገር የቆመችበትን ዕለት በየዓመቱ ጁላይ 9 ቀን በነፃነት በዓልነት ታከብራለች። አሁን ታስቦ የዋለውም የሀገሪቱ ስድስተኛ ዓመት የነፃነት በዓል ነው።

ባለፈው ሀሙስ ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የምረቃ ሥነ-ስርዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን የካርጎ ጭነት ተርሚናል አስመርቋል። አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ተርሚናል አንድ ተብሎ የሚጠራውን የካርጎ ተርሚናል ገንብቶ በማጠናቀቅ በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን ይህ ከሰሞኑ የተመረቀው ተርሚናል ሁለተኛው የካርጎ ተርሚናል መሆኑን በዕለቱ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አመልክተዋል።

  የመጀመሪያው ተርሚናል እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ  በመግባት እስከ ዛሬ ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን ጭነት የመያዝ አቅሙም 3 መቶ ሺ ቶን እንደነበር አቶ ተወልደ አመልክተዋል። የአሁኑ ሁለተኛው የማስፋፊያ የካርጎ ተርሚናል በዓመት 6 መቶ ሺ ቶን ጭነትን የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑ ተመልክቷል። አጠቃላይ ወጪው 150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን በግንባታውም የውጭ እና ሀገር በቀል ኩባንያዎች የተሳተፉበት መሆኑን አቶ ተወልደ አመልክተዋል። የፕሮጀክት ሲኒየር ማናጀር አቶ ሳሙኤል አበበ እንደገለፁልን በዚሁ ካርጎ ግንባታ ዩኒቴክ የተባለ የጀርመን ኩባንያና ቫርኔሮ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች ናቸው። 

 የጀርመን ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክና የፈረንሳይ የልማት ባንክ እንደዚሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የግንባታው የፋይናስ ምንጭ ናቸው። ይህ ካርጎ ተርሚናል የመጀመሪያውን እና አሁን ተገንብቶ የተመረቀውን አጠቃሎ እስከ አንድ ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ጭነትን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን እ.ኤ.አ እስከ 2025 ሌላ ተጨማሪ ማስፋፊያን ሳይጠይቅ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ተደርጎ የተገነባ ነው።

 ካርጎ ተርሚናሉ የሚይዛቸው ወጪና ገቢ እቃዎች በቀላሉ ሊበላሹ ከሚችሉ እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የሥጋ ምርቶች፣ እና የመድሃኒት ምርቶችን ጨምሮ ከዚህ ውጪ ሆነው በቀላሉ ለብልሽት ሊጋለጡ የማይችሉ የተለያዩ የምርት ዓይነቶችንም የሚያጠቃልል መሆኑን ከኃላፊዎቹ ገለፃ መረዳት ችለናል። እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ የካርጎ ተርሚናሉ በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በቀላሉ ለሚበላሹ ወጪና ገቢ ምርቶች የተዘጋጀው ቀዝቃዛ ክፍል (Cold room) 17 ሺህ ካሬ ሜትር አካባቢ ነው። ተርሚናሉ ያለማቋረጥ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በተለይ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተያያዘ የኃይል  መቆራረጥ ተፈጥሮ የእቃዎች ብልሽት እንዳይፈጠር በመፍትሄነት ተካተው የተሰሩ ሥራዎችም አሉ። የመጀመሪያው ተርሚናሉ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  የኃይል  አቅርቦት እንዲያገኝ የተደረገው በሁለት መስመሮች ነው።

ይህም ከአንዱ መስመር የኃይል መቋረጥ ቢያጋጥም በአፋጣኝ ሌላኛውን መስመር መጠቀም እንዲቻል በማሰብ ነው። ከዚህ ባለፈም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል የኃይል  መቋረጥ ሊያጋጥም የሚችል ከሆነ እንኳን ተርሚናሉን በሙሉ አቅም ሊያንቀሳቅስ የሚችል ጄኔሬተር ተዘጋጅቷል። ተርሚናሉ ከሶስት ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልፀውልናል። በግንባታው ሂደት በተለይ የጣሊያኑ ቫርኔሮ ኩባንያ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን በስፋት ያሳተፈ መሆኑ ታውቋል።

 ይህም በአፍሪካ ግዙፉ ተርሚናል መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ካርጎ ተርሚናሉ አደገኛ ጨረር ሊለቁ የሚችሉ ሬዲዮ አክቲቭ ቁሶችንና የተለያዩ የምርት አይነቶችን በየአይነታቸው ለይቶ መያዝ የሚያስችሉ ክፍሎችን በየደረጃቸው አካቶ እንዲይዝ ተደርጓል። ካርጎ ተርሚናሉ ያለ ሰው ንክኪ እቃዎችን ላይቶ ኮምፒተራይዝድ በሆነ መልኩ በተዘጋጁ መደርደሪያ እቃዎች ቦታ መርጦ የሚያስቀምጥ ብሎም ዕቃው ሲፈለግ ከቦታው አንሰቶ ማቅረብ የሚችል ቴክኖሎጂን አካቶ እንዲይዝ የተደረገ ነው። ይህም በባለሙያዎቹ አጠራር “Elevating Transport Vehicle” ተብሎ የሚጠራ ነው። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አሁን የተገነባው ካርጎ ተርሚናልን ለማስፋፋት ባለው እቅድ የተጨማሪ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ለመተግበር የዲዛይን ሥራው የተጠናቀቀ መሆኑ ታውቋል።

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ቤት ላሉ ዘመድ ወዳጆቻቸው የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈፀም የሚችሉበት አገልግሎት ተጀመረ። ባለፈው ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ሥነስርዓት ፋይናሺያል ቴክኖሎጂና ማስተር ካርድ ባደረጉት ስምምነት አገልግሎቱን ለመስጠት ውል ተፈራርመዋል።

 በዚህም ቴክኖሎጂ በኮምፒዩተር እንደዚሁም በሞባይል ስልኮች ላይ አፕልኬሽን በመጫን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ሰው እንደ ውሃ፣ መብራትና ስልክን የመሳሰሉ ወጪዎች በውጪ ሀገር ባሉ ዘመድ አዝማዶቹ እንዲሸፈን ማድረግ የሚችል መሆኑ ታውቋል። የአገልግሎቱ መጀመር በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገር ቤት ካሉ ዘመድ አዝማዶቻቸው ጋር ይበልጥ እንዲተሳሰሩ ያደርጋል ተብሏል። በዚሁ አዲስ በተጀመረው የዲጂታል ክፍያ ዲያስፖራዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው በዴቢት ካርድ፣ በክሬዲት ካርድ፣ በመኒ ሞባይልና በልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶች ለዘመድ አዝማዶቻቸውና ወዳጆቻቸው የቤት ወጪን መሸፈን የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ የክፍያ ሥርዓትም አንድ በውጪ ሀገር የሚኖር ሰው በሀገር ቤት ላለው ሰው የመድህን ኢንሹራንስ ክፍያን፣ የትምህርትና የህክምና ወጪን፣ እንደዚሁም የስልክ፣ የመብራትና የውሃ ወጪን መሸፈን ያስችላል ተብሏል። ከክፍያ ፋይናሺያል ቴክኖሎጂ ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው ማስተር ካርድ ኩባንያ አሁን ያደረገው ሥምምነት እ.ኤ.አ በ2020 በአፍሪካ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በዲጂታል ክፍያ ለማስተሳሰር  የያዘው አንድ እቅድ አንድ አካል መሆኑ ታውቋል።

 ይሄው መረጃ በአሁኑ ሰዓት ከሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ መሆኑን ያመለክታል። ይህ አይነቱ የቴክኖሎጂ ክፍያ ሥርዓትም  ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚካሄደውን የገንዘብ ማስተላለፍ ሂደት ወደ ህጋዊውን መስመር እንዲከተል ለማድረግ የተሻለ እድል ሆኖ የሚታይ መሆኑን የክፍያ ፋይናሺያል  ቴክኖሎጂ የሥራ ዓመራር ሀለፊ የሆኑት አቶ ሙኒር ዱሪ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከሚመረትበት ማዕከል ጀምሮ ተጠቃሚው ቤት እስከሚደርስበት ድረስ በብዙ የብክነት ሂደቶች ውስጥ ያልፋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ቢሊዮን ብሮች የምትገነባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች የሚያመርቱት የኤሌክትሪክ  ኃይል  መጠን በኃይል  ቆጣቢ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች እንደዚሁም በሌሎች ታዳሽ  ኃይል  ድጋፍ ሰጪ ቴክኖሎጂዎች መደገፍ ባለመቻሉ ሁሉም ነገር ብሄራዊ የኃይል  ቋቱ (National Grid) ጥገኛ ሆኖ ይታያል።

 በዚህ ረገድ በበርካታ ሀገራት የፀሀይ ኃይልን በኤሌክትሪክ የኃይል  ምንጭነት መጠቀም የሚችሉ ልዩ ልዩ ታዳሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። በሀገራችን መሰል ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ከማስገባት ባለፈ ያን ያህል በስፋት አምርቶ የመጠቀሙ ጉዳይ እውን መሆን ሳይችል ቆይቷል።

 በዚህ ዘርፍ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ፋብሪካ በሰንዳፋ ተመልክተናል። ኢንዱስትሪው አፍሮአምክ ሶላርቴክ በሚል ስያሜ የሚጠራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን በፀሀይ  ኃይል  ውሃ የሚያሞቁ መሳሪያዎችን በማምረት ላይ ይገኛል።

  ይሄው በሰንዳፋ ኢንዱስትሪ ዞን  በሶስት ሺህ  ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ አርፎ በታዳሽ  ኃይል  በኩል በፀሀይ  ኃይል  አማካኝነት የሚሰሩ የውሃ ማሞቂያዎችንና የፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያ ፓኔሎችን በማምረት ላይ ያለው ኩባንያ በማምረቱ ረገድ ኢትዮጵያ በአካባቢው ባሉ ሀገራት ብቸኛዋ የሚያደርጋት መሆኑን የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ መንገሻ ገልፀውልናል።

  ፕሮጀክቱ ሲጀመር በ16 ሚሊዮን ብር ግንባታውን ለማከናወን ታቅዶ የነበረ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ይሁንና ወደ ስራ ሲገባ የነበሩት ነባራዊ ሁኔታዎችና ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታ ቀድሞ በዕቅድ ተይዞ የነበረውን የካፒታል ወጪ መጠን ወደ 30 ሚሊዮን ብር ያናረው መሆኑን አመልክተዋል።

 ለፕሮጀክቱ ፋይናንስ በማፈላለጉ ረገድም ቴክኖሎጂው በሀገር ውስጥ ብዙም የማይታወቅ በመሆኑ በባንኮች በኩል የተወሰኑ ተግዳሮቶች ገጥሟቸው የነበረ መሆኑንም አቶ አሰፋ ጨምረው ገልፀውልናል። ከዚህም ባለፈ ወደስራ በመግባቱ ረገድ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማግኘቱም በኩል ቀላል የማይባል ተግዳሮቶች ገጥሟቸውም ነበር።

 ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት ባለ 80፣ ባለ 150 እና ባለ 2 መቶ ሊትር የውሃ ማሞቂያ ጋኖችን እስከነ ፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያ ፓኔሎቻቸው በማምረት ላይ ይገኛል።  አቶ አሰፋ አንድ ሰው የእሳቸውን ምርት ሲጠቀም አስተማማኝና ዋስትና ያለው ምርት መሆኑን ገልፀውልናል። ምርቱም በዘርፉ ታዋቂ ከሆነችው እስራኤል አገር ምርቶች ጋር በጥራትም ሆነ በጥንካሬ እኩል መሆኑን አቶ አሰፋ አመልክተዋል። ፋብሪካው በአፍሪካ ደረጃ በአካባቢው ብቸኛ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አሰፋ፤ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ  ወደ ወጪ በመላክ ለሀገራቸው የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት እቅድም አላቸው። ፋብሪካው አሁን ባለበት ደረጃም በወር ሶስት ሺህ ፓኔሎችንና የውሃ ማሞቂያ በርሚሎችን የማምረት አቅም ያለው መሆኑ ተመልክቷል። የውሃ ማሞቂያዎቹ በፀሀይ ኃይል ከመስራት ባሻገር በክረምት ወራት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መሆናቸውንም አቶ አሰፋ አመልክተዋል።

 ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት እስከ 23 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። የስራው ሁኔታ እየሰፋ ሲመጣም በቀጣይ የሰራተኛው መጠን እየጨመረ የሚሄድ መሆኑም ተመልክቷል። ሰራተኞች በፋብሪካው ውስጥ ከመስራት ባሻገር  ማሞቂያዎቹ በሚገጠሙባቸው አካባቢዎች የገጠማ ስራን በማከናወን ከተቀጣሪነት ወደ ራሳቸው ሲራ የሚገቡበት ሁኔታ የሚመቻች መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገልፀውልናል።

 በዚህም ሙያዊ ስልጠና ወስደው በየቦታው የገጠማ ስራ የሚያከናውኑ በርካታ ዜጎችንም በስፋት ለማሳተፍና የስራ እድልን ለመፍጠር በአቶ አሰፋ በኩል በእቅድ ተይዟል። አሁን ባለው ገበያም አንድ ሰው በቀን እስከ 3 ቦይለር የሚገጥም ከሆነ እስከ 2 ሺህ 1 ብር የሚያገኝ መሆኑን አቶ አሰፋ ነግረውናል። ኩባንያው ምርቶቹን እያቀረበ ያለው ለግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ ለሆቴሎች፣ ለሆስፒታሎችና ለመሳሰሉት ተቋማት ነው።

  በግብርና ግብዓት አቅርቦቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ያለው ኤፍ. ኤስ. ሲ. ፒ- ጂ. አይ. ሲ ኢትዮጵያ- በአርሲ ዞን ከሚገኙና በዘርፉ ከተሰማሩ የግብርና ምርት አቅራቢዎች ጋር የስምምነት ውል አደረገ። በስምምነቱ መሰረት  ድርጅቱ ለእያንዳንዳቸው ግብዓት አቅራቢ ግለሰቦቹ 30 ሺህ ዩሮ የገንዘብ መጠን በካሽና በአይነት እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ በአንፃሩ የራሳቸውንም የፋይናስ አቅም ጭምር በመጠቀም የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ የሚያቀርቡ ይሆናል።

አገልግሎቱን ለማቅረብ የተካሄደውን ውድድር ያሸነፉት ግብዓት አቅራቢዎች ወይዘሮ ፅጌረዳ ሰለሞን እና አቶ አብርሃም እንድርያስ የተባሉ የአርሲ ዞን ነዋሪዎች ናቸው። የግብርና ምርት አቅርቦቱን በዚህ መልኩ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ አርሶ አደሩ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በቅርበትና በጥራት እንዲያገኝ በከፍተኛ ሁኔታ ያግዘዋል ተብሏል።

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Page 1 of 31

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us