በኮንደሚኒየም ዙሪያ ቁጥሮች ይናገራሉ

Wednesday, 03 August 2016 14:20

 

11ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ በመጪው ቅዳሜ የሚወጣ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቤት ፕሮግራሙን በተመለከተ እስከዛሬ በነበረው ሂደት አሃዞች ምን እንደሚናገሩ ለማሳየት ያህል የሚከተሉትን አጠር አጠር ያሉ መረጃዎች አቅርበናል። አሀዛዊ መረጃው በቀጣይ ቅዳሜ የሚወጡ ቤቶችንም አብሮ ዳሷል።

 

 ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም 39 ሺህ 126 ቤቶች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

- እነዚህ ቤቶች በ10/90 እና በ20/80/ የቤት ፕሮግራም ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

- በቤቶቹ ላይ እጣ ይወጣል የሚል የጊዜ ሰሌዳ የነበረው ሰኔ 2008 ዓ.ም ነበር።

- የቤቶች ልማት ፕሮግራም የተጀመረው በ1996 /97 ዓ.ም በ20/80 የኮንደሚኒየም ቤቶች ፕሮግራም ነበር።

- በጊዜው  የቤት ፕሮግራም ምዝገባው  ተመዝጋቢዎች ምንም አይነት  የቁጠባ  ሂሳብ መክፈት አይጠበቅባቸው ነበር።

- በዚሁ የ1996/97 የቤቶች ምዝገባ ከ450 ሺ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች  በቤት ፈላጊነት ተመዝግዋል።

- ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተሞክሮ ታሳቢ በማድረግ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ግንባታን በማካሄድ ለቤት ፈላጊዎች ለማስተላላፍ ቢሞከርም የክልል ከተሞች ነዋሪዎች ብዙም ፍላጎት ባለማሳየታቸው ሂደቱ በተፈለገው መጠን ሊቀጥል ሳይችል ቀርቷል።

- በ1996/97 ዓም በ20/80 የቤቶች ፕሮግራም ከ450 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪ በቤት ፈላጊነት በተመዘገበበት ወቅት በመንግስት በኩል ቃል የተገባው ለተመዝጋቢዎች ቤቶቹን በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንደሚያስረክብ ነበር።

- ቁጠባን መሰረት ያደረገው የጋራ መኖሪያ የቤቶች ምዝገባ በድጋሚ በ2005 ሲካሄድ ከ20/80 ባለፈ 10/90 እና40/ 60 አዳዲስ የግንባታ ፕሮግራሞች ይፋ ሆኑ።

- በጊዜው የቤቶቹ ፕሮግራም ይፋ ሲሆን በ1996/97 ዓ.ም ተመዝግበው ቤት ያላገኙ ነዋሪዎች “ነባር ተመዝጋቢ” በሚል በድጋሚ እንዲመዘገቡ ተደረገ።

- በዚህ ዳግም ምዝገባ ወቅት ቀደም ሲል የድጋሚ ምዝገባው ከመካሄዱ በፊት በ1996/97 ከተመዘገቡት ከ450 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለባለእድለኞች በእጣ ማከፋፈል የተቻለው ከመቶ ሺህ በታች ነበር።

- ነባር ተመዝጋቢዎች በነባርነት ተመዝግበው በቅድሚያ የሚስተናገዱት የፍላጎት ለውጥ ካላሳዩ ብቻ መሆኑ በጊዜው ለህዝብ የተላለፈው የመንግስት መመሪያ ያመለክታል።

- በ1996/97 ዓም ከተመዘገቡት ከ450 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ውስጥ መንግስት በዘጠኝ ዓመት ጊዜ ውስጥ  ሰርቶ ማስረከብ የቻለው የጋራ መኖሪያ ቤት ከመቶ ሺህ በታች ቢሆንም በድጋሚ በተካሄደው የቤቶች ምዝገባ በነባርነት መመዝገብ የቻለው 137 ሺ ነዋሪ ብቻ ነበር።

- ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከምክንያቶቹ መካከልም በርካታ ነባር ቤት ፈላጊዎች የፍላጎት ለውጥ በማሳየት በአዲስ ቤት ፈላጊዎች ፕሮግራም ውስጥ መካተታቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ጊዜው ከመርዘሙ ጋር በተያያዘ በሞት የተለዩና አገር ጥለው የሄዱም  ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል።

- በቅርቡ ይወጣል ተብሎ በሚጠበቀው በ11ኛው ዙር 39 ሺህ 249 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እጣ ውስጥ 14 ሺህ 516ቱ 20/80 ሲሆኑ 23 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ 10/90 ቤቶች ናቸው።

- በ11ኛው ዙር በሚወጣው እጣ 2 ሺህ 449 ስቱድዮ ቤቶች፣ 6 ሺህ 2 መቶ 62 ባለአንድ መኝታ ቤት፣ 3 ሺህ 3 መቶ 16 ባለሁለት መኝታ እንደዚሁም 2 ሺህ 489 ባለሶስት መኝታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

- ቤቶቹ እስከ 95 በመቶ የተጠናቀቁ ናቸው ተብሏል።

- 11ኛው ዙር የቤቶች የማስተላለፊያ ዋጋ ከአስረኛው ዙር የቤቶች ዋጋ የተለየ አይደለም። በዚህም መሰረት ስቱዲዮ በካሬ 2 ሺህ 483 ብር፣ ባለአንድ መኝታ ቤት በካሬ 3 ሺህ 438 ብር፣ ባለሁለት መኝታ ቤት በካሬ 4 ሺህ 3 መቶ 94 ብር፣ ባለሶስት መኝታ ቤት በካሬ 4 ሺህ 776 ብር ነው።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
1182 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us