አድማስ ዩኒቨርስቲ ከሦስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

Wednesday, 10 August 2016 13:29

 

አድማስ ዩኒቨርስቲ አዲስ አበባ በሚገኙ ካምፓሶቹ የዲግሪ እና የቴክኒክ ሙያ የስልጠና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከሶስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ። ባለፈው ቅዳሜ በኤግዚብሽን ማዕከል በተካሄደው በዚሁ የምርቃት ስነስርአት አራት መቶ ሃምሳ ስምንቱ በዲግሪ ፕሮግራም በአካውንቲግ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲግ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመርቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቀሪዎቹ  ምሩቃን ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መርሀ ግብር ዘርፍ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። በምረቃው እለት ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አቶ ሞላ ፀጋይ፤ ዩኒቨርስቲው የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በመሰራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ለመጪው አዲስ አመት ተቋሙ በራሱ ወጪ ባስገነባቸው በመካኒሳ እና መቐለ ካምፓሶች ትምህርት መስጠት እንደሚጀመር አመልክተዋል።

 በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የህፃናት ልብ ፈንድ ኢትዮጵያ የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር በላይ አበጋዝ በበኩላቸው፤ ምሩቃኑ በተማሩበት የሙያ ዘርፍ ህዝባቸውንና አገራቸውን በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንዲያገለግሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

 እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ዩኒቨርስቲው ባለፉት 18 ዓመታት በመደበኛና በርቀት ትምህርት በዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፍ አስመርቋል። ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅትም በዲግሪ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እንደዚሁም በመደበኛውና በርቀት ትምህርት ፕሮግራሙ  ሶማሌ ላንድንና ፑንት ላንድን ጨምሮ ከ 20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ የሚገኝ መሆኑን አቶ ሞላ አመልክተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
487 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us