“ማን ባስ” በአዲሱ ዓመት ይጀምራል

Wednesday, 10 August 2016 13:29

 

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞችን ጨምሮ በኬኒያ፣ በሱዳንና በጅቡቲ ለህዝብ  የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ተወዳዳሪና ተመራጭ እሆናለሁ ያለው ማን ባስ አክስዮን ማህበር ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀ። በስድስት መስራች ባለአክስዮኖች አማካኝነት ወደስራ የገባው ማን ባስ የጀርመን ሀገር ምርት የሆኑና በህንደ ሀገር የተገጣጠሙ አምስት አውቶብሶችን ለሙከራ አስገብቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ፤ የአክሲዮኑ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኔ ዘሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በ1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር መነሻ  ካፒታል ስራውን የጀመረው ማንባስ አክሲዮን ማህበር በአሁኑ ወቅት ወደሀገር ውስጥ ከገቡት አምስት አውቶቡሶች በተጨማሪ በቅርቡ 30 አውቶብሶች ወደሀገር ውስጥ ገብተው በልዩ የትራንስፖርት አገልግሎትን ላይ ይሰማራሉ ተብሏል። በቅርቡ የአክሲዮን ሽያጭም እንደሚጀምር ያስታወቁት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ የአንዱ አክሲዮን ዋጋ 50ሺህ ብር ሲሆን አንድ ሰው መግዛት የሚችለው በትንሹ 10 አክሲዮኖችን እንደሆነም በመግለጫው ወቅት ተጠቁሟል።

በአገራችን ካሉ ልዩ የትራንስፖት አክሲዮኖች ጋር ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ ለመስራት ሰባተኛ አክሲዮን የሆነው  ማን ባስ፤ በሀገር አቋራጭ ብቻ ሳይሆን በከተማ የትምህርት ቤት ትራንስፖርትና በአስቸኳይ የሌሊት ጉዞ ላይ ለመሰማራት የመንግስትን መመሪያ እየጠበቀ እንደሚገኝ በመግለጫው ወቅት ተነግሯል።

በጀርመን የአውቶሞቢል ኩባንያ ተመርተው እንደሚመጡ የሚጠበቁት 30 አውቶብሶች ተጠቃለው ወደሀገር ውስጥ ሲገቡ፤ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በመላው አገሪቱ ወደስራ ይገባልም ሲሉ የአክሲዮኑ ኃላፊዎች ተናግረዋል። ማን ባስ የተሰኘው ይህ አውቶብስ እስከ 60 የሚደርሱ መንገደኞችን በአንዴ ማስተናገድ የሚችል ቢሆንም፤ ለደንበኞች ምቾትና ደህንነት ሲባል ግን ለ45 ሰዎች ብቻ እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀቱን የአክሲዮን ማህበሩ ፀሐፊ አቶ ገንዘብ አስማማው ያስረዳሉ። አውቶብሱን ወደሀገር የሚያስመጣው ካሌብ ፋርመርስ ሀውስ ነው ተብሏል።

በቂ የገበያ ጥናት አድርገን ወደስራ ገብተናል ያሉት የአክሲዮኑ ኃላፊዎች፤ አሁን ካለው የልዩ ባስ አገር አቋራጭ የክፍያ ዋጋ ቀንሰን ብንሰራም ያዋጣናል ብለዋል። ማን ባስ የደህንነት አቅሙ ከፍ ያለሲሆን በአራቱም አቅጣጫ ማሳየት የሚችል ካሜራ የተገጠመለት መሆኑም ተነግሯል። በአንድ ሌትር በሰዓት ከ3 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል የተባለ ያሉት ኃላፊዎቹ ይህም ከሌሎች ባሶች የተሻለ የነዳጅ አጠቃቀም እንዳለው ያሳያል፤ ዲዛይኑም ቢሆን ወደኢትዮጵያ የመጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ የማን ባስ ቴክኒካል ማኔጀር አቶ ፋሲል ጌጡ አስረድተዋል።

ማን ባስ በሙሉ አቅሙ ስራውን ሲጀምር ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራ የተባለ ሲሆን፤ በአምስቱ አውቶብስ ብቻ ለ30 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯልም ሲሉ ተናግረዋል። በቀጣይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በኬኒያ በጅቡቲና በሱዳን (ካርቱም) የጉዞ እንቅስቃሴ ለመጀመር እንዳቀደ የተናገሩት ኃላፊዎቹ በአሁኑ ወቅት በሚዛን፤ በሃዋሳ፤ በአርባምንጭና በነገሌ ቦረና እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
521 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us