“የትኬት ማጭበርበርን ለመከላከል መፍትሄው የኤሌክትሮኒክ ትኬት በመሆኑ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል”

Wednesday, 10 August 2016 13:32

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን

የኮሙኑኬሽን አገልግሎት ኃላፊ

አቶ ደረጀ ተፈራ

 

ከሶስት ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ወደ ስራ ገብቷል። የባቡር አገልግሎቱ ወደ ስራ ቢገባም የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር በታሰበው ደረጃ ሊቃለል አልቻለም። ባቡሩ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት ተሳፋሪን በማንሳቱ ረገድ ብዙ ሲጠበቅ ቢቆይም አሁንም ቢሆን አገልግሎቱና ፍላጎቱ ሊጣጣም አልቻለም። ከዚህና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደረጀ ተፈራን አነጋግረናል። የሰጡንንም ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- የአዲስ አበባ የከተማ የባቡር አገልግሎት ብዙውን ጊዜ ቀላል ባቡር ሲባል ይሰማል “ቀላል ባቡር” ሲባል ምን ማለት ነው?

 

 አቶ ደረጀ፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 34 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ነው። ግንባታው ሶስት አመታትን ፈጅቶ በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ይገኛል። ቀላል ባቡር የምንልባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ከምክንያቶቹ መካከልም ባቡሩ ረዥም ርቀት የማይጓዝ መሆኑ አንዱ ነው። ከጭነት አንፃር ከተመለከትነው ለጭነት አገልግሎት የሚውል አለመሆኑም ቀላል ባቡር ያስብለዋል። መንገደኞች አጭር ርቀት የሚጓዙ በመሆኑ ተሳፋሪዎች መቀመጥ አይጠበቅባቸውም። አገልግሎቱንም እየሰጠ ያለው በሁለት አቅጣጫ ብቻ ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ቀላል ባቡር የሚለውን ስያሜ ይዟል።

 

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል የባቡር ትራንስፖርት ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ሰዎች ወደ ቻይና እና ሩስያ ይላኩ ነበር። አሁን ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል?

 

አቶ ደረጀ፡- ቀደም ሲል ሰዎች ወደተለያዩ ሀገራት ሄደው ስልጠና እንዲያገኙ ሲደረግ ቆይቷል። አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው። ስልጠናው በአገር ውስጥ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው። ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል ስለሚጠይቅ ሁሉንም ሰው ውጭ እየላኩ ማሰለጥን ከውጪ ምንዛሪ አንፃር አዋጪ ሆኖ አይታይም። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የራሱ ኢኒስቲትዩት አለው። ከአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል። የሲቪል እና የኤሌክትሪካል መሀንዲሶቻችን እንደዚሁም መካኒካል መሀንዲሶቻችን የመጀመሪያ ዲግሪ የያዙትን ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ነው። ከዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ አጫጭር ስልጠናዎች የሚሰጡበት አሰራርም አለ።

 

ሰንደቅ፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ወደ ስራ ከመግባቱ ቀደም ብሎ ሲገለፅ የነበረው አንድ ተሳፋሪ አንድ ባቡር ካመለጠው ሁለተኛውን ባቡር ለመያዝ ስድስት ደቂቃ ብቻ የሚጠብቅ መሆኑን ነበር። ወደ ስራ ከገባ በኋላ ግን የሚታየው እንደተባለው አይደለም። ተሳፋሪ የማንሳት አቅሙም ቢሆን በተለይ በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት በእጅጉ የተጨናነቀ ነው። ምልልሱም ቢሆን የተባለውን ያህል ያልሆነው ለምንድን ነው?

 

 

አቶ ደረጀ፡- አቅርቦትና ፍላጎት በማይጣጣሙበት ወቅት እንደዚህ አይነት አስተያየቶች ይመጣሉ። ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት ያለን 41 ባቡሮች ናቸው። ማኔጅመንት ኮንትራቱን የሚሰራው የውጭ ኩባንያ ነው። የስምሪት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ በመሆን በየትኛውም አቅጣጫ ከፍተኛ የመንገደኞች ፍላጎት እንዳለ ይታያል። ከዚያ ይህንን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ባቡሮች እንዲሰማሩ ይደረጋል ማለት ነው። ሆኖም በከተማዋ ካለው ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍላጎት አንፃር በተለይም በስራ መውጪያና መግቢያ ሰዓት የትራንስፖርት ፍላጎቱን ይመልሳል ብሎ መናገር አይቻልም። አንደኛ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት የሚሸፍነው 34 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን የመስመር አቅጣጫውም ቢሆን ሁለት ብቻ ነው። ይህም በመሆኑ ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ለማጣጣም የሁለተኛው እቅድ የባቡር መስመር ግንባታ መጠበቅ ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ አሁን ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በስራ ላይ ካሉት ባቡሮች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ባቡሮች ከውጭ ለማስገባት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። ይህ ለጊዜው አሁን ባለው መስመር ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ያቃልለዋል ተብሎ ይታሰባል።

 

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ለዓመታት ተጠራቅሞ የቆየ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ሊፈታ የሚችል አይደለም። ችግሩ የሚፈታው የትራንስፖርት አይነቱን፣ የአገልግሎት ጥራቱንና ብዛቱንም ጭምር በማስፋት ነው። ይህ ማለት በባቡር፣ በሌሎች አገሮች ላይ እንደሚታየው የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት፣ ተጨማሪ ታክሲዎችና ሌሎች የትራንስፖርት አይነቶች በስፋት መስፋፋት መቻል አለባቸው።

 

ሰንደቅ፡- በከተማው የባቡር ትራንስፖርት ላይ የትኬት ቁጥጥር በስፋት አይታይም። አልፎ አልፎ በሚደረጉ ቁጥጥሮች ሰዎች ባለፈ ትኬት ሳይቀር ሲጓዙ የሚገኝበት ሁኔታ አለ። የቁጥጥር መላላት ከምን የመነጨ ነው?

 

አቶ ደረጀ፡- የከተማ የባቡር ትራንስፖርት ላይ በአንድ ባቡር ውስጥ የሚገለገለው የተሳፋሪ ቁጥር ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ከፍተኛው 118 የተሳፋሪ ቁጥር ነው። ሁሉም የሚጓዙት በመቀመጫ ነው። በመሆኑም ለቁጥጥር ቀላል ነው። ወደ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ስንመጣ አንድ ባቡር እስከ 317 ሰው ይይዛል።

 

የጉዞ መስመሩ አጭር ስለሆነ፤ ተሳፋሪው ቆሞ ነው የሚጓዘው። በጣም የተጨናነቀ ነው። 317 ተሳፋሪን ሰው በሰው ትኬት እየፈተሹ ለመቆጣጠር ከባድ ነው። ለዚህ አዋጪው የቁጥጥር ዘዴ የኤሌክትሮኒክስ የትኬት ዘዴን መጠቀም  ነው። ኤሌክትሮኒክ ትኬቱ በቂ ገንዘብ በውስጡ ከሌለው ተሳፋሪውን ወደ ባቡር ጣቢያው አያሳልፈውም። ይህ ዘዴ በቀላሉ ተሳፋሪዎች በነፃ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርግ ዘዴ ነው። ይህ የሰለጠነው አለም የሚጠቀምበት ዘዴ ነው። እንደዚህ አይነት የማጭበርበር ስራን በተመለከተ ጥቂት አጥፊዎች ቢኖሩም የሁሉም ተሳፋሪ ችግር ነው ብሎ ግን መውሰድ አይቻልም።

 

ሰንደቅ፡- የአሌክትሮኒክ ካርድ ትኬቶቹ ቻይና በህትመት ላይ እንዳሉ ቀደም ሲል ሲገለፅ ቆይቷል። አሁን ያሉበት ደረጃ ምን ይመስላል?

 

አቶ ደረጀ፡- የኤሌክትሮኒክ ትኬቶቹን በተመለከተ የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ይሄ ስራ የሚሰራው የማኔጅመንት ኮንትራቱን በወሰደው አካል በኩል ነው። ህትመቶቹ እየተጠናቀቁ ስለሆነ ትኬቶቹ በቅርቡ አገር ውስጥ እንደገቡ ስራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም የትኬት ማጭበርበርን ለመከላከል መፍትሄው የኤሌክትሮኒክ ትኬት በመሆኑ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል።

 

ሰንደቅ፡- ሌላው የባቡር ድልድይ ተሸካሚ ምሶሶዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ማስታወቂያ እየተለጠፈ በመሆኑ የከተማዋን ገፅታ እያበላሸ ነው። የምድር ባቡር ከርፖሬሽን ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ በመሆን ቁጥጥር የማያደርግበት ምክንያት ምንድን ነው?

 

አቶ ደረጀ፡- የባቡር መሰረተ ልማቶች መጠበቅን በተመለከተ የወጣ የባቡር አዋጅ አለ። በዚህ ህግ መሰረት የሚያስጠይቁ ሁኔታዎች አሉ። ከዚህ ውጪም የአዲስ አበባ ከተማ  ፅዳትና ውበት መናፈሻ ኤጀንሲም ይሄንን ጉዳይ የመቆጣጠር አንዱ ኃላፊነቱ ነው። ማስታወቂያዎች መለጠፍ ያለባቸው በተፈቀዱ ቦታዎች ብቻ ነው። እስከዛሬ ባለው አሰራር እየተለጠፉ ያሉት ህገ ወጥ ማስታወቂያዎች በአፋጣኝ ከስር ከስር እንዲነሱ እየተደረገ ነው። ሆኖም በዚህ መቀጠል አይቻልም።

 

 እነዚህን ሰዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ፤ ከዚህም ባለፈ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኃላፊነት ነው። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ለትርፍ የተቋቋመ ሳይሆን የከተማዋን ትራንስፖርት ለመደገፍ የተቋቋመ ተቋም በመሆኑ ራሱን ለመደጎም ከትኬት ሽያጭ ባሻገር አንዳንድ የገቢ ምንጮችን መፈጠር መቻል አለበት። ከእነዚህ የገቢ ምንጮች መካከል አንዱ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢ ነው።

 

በባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ላይ የተመረጡ ቦታዎች ላይ ደረጃቸውን በጠበቁ መልኩ የተለያዩ ማስታወቂያዎች መትከያና መለጠፊያ ቦታዎች እንዲለዩ ተደርጓል። እነዚህ ቦታዎች ተለይተው ለጨረታ ወጥተዋል። ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ጨረታውን ያሸነፉት ድርጅቶች እንዲይዙት ይደረጋል። እዚህ ቦታ ላይ ማስታወቀያ መለጠፍ የሚችለው ሰው በህግና በውል አግባባዊነቱ የታወቀ ሰው ብቻ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ያለውል፣ ከህግ ውጪ የከተማዋን ገፅታ በሚያበላሽ መልኩ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ማስታወቂያዎችን በባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ መለጠፍ በህግ የሚያስጠይቅ ይሆናል። አሁን ያለው አካሄድ በዚህ የሚቀጥል አይሆንም። ግንዛቤ የማስጨበጡ ላይ የሚሰራ ስራ ይኖራል። ከዚህ ውጪ ግን ህጋዊ እርምጃዎች ይከተላሉ።

 

ሰንደቅ፡- ሊፍቶቹና የኤሌክትሮኒክ ደረጃዎቹ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?

 

 

አቶ ደረጀ፡- አገልግሎቱ የዘገየው እነዚህ መሰረተ ልማቶች ስራ ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ የሰው ኃይልን በማዘጋጀቱ ረገድ በቂ የሰው ኃይል ስለጠየቀን ነው። ባቡሩ ወደ ስራ በገባባቸው ጊዜያት አገልግሎት ሲሰጡ ነበር።  አገልግሎታቸውንም በዋነኝነት ለአካል ጉዳተኞች ነው።  ይሁንና ወደ ስራ በገቡበት ወቅት ዝም ብለው መጫወቻ ነው የሆኑት። አስፈላጊው የሰው ኃይል እንደተሟላ ግን ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
531 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us