የቆዳ ኢንዱስትሪ በጨው አቅርቦት ተቸግሯል

Wednesday, 17 August 2016 12:20

 

በይርጋ አበበ

ለውጭ ገበያ ምርቶቹን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ይገኝበታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የቆየውና ከእቅዱ በታች ያስመዘገበው የቆዳው ኢንዱስትሪ የጨው አቅርቦት ፈተና እንደሆነበት አስታወቀ።

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ያለፈውን ዓመት እቅድ አፈፃፀም በተመለከተ በተዘጋጀ የጋራ የውይይት መድረክ ላይ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አብዲሳ አዱኛ የማህበራቸውን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ዘርፉ በርካታ ፈተናዎች እንደተጋረጡበት ገልጸዋል። አቶ አብዲሳ የቆዳው ኢንዱስትሪ ስኬታማ እንዳይሆን የገጠመውን ፈተና ሲገልጹም “ቀደም ሲል ከአፍዴራ ስናገኝ የነበረው ጨው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጨው ማምረቻው በግለሰቦች ስለተያዘ ዋጋው ውድ ሆኖብናል። በዚህ ከቀጠለም ማህበሩ ጨውን ከውጭ ለማስመጣት (Import) ይገደዳል” ብለዋል።

አቶ አብዲሳ በሪፖርታቸው አክለውም የቆዳ ኢንዱስትሪውን ጉዞ ወደኋላ እየጎተቱ ያስቸገሩት የመንግስት አዳዲስ አሰራሮች እና የገቢዎችና ጉምሩክ ቀልጣፋ ያልሆነ አሰራር ነው። አቶ አብዲሳ የዘርፉ ጎታች ናቸው ካሏቸው ምክንያቶች መካከል ቀደም ሲል የነበረው የሲኤዲ (CAD) እና ቮውቸር አሰራር በአዲስ መልኩ መቀየሩ ኢንቨስተሩን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑን ገልጸዋል። የቫት ተመላሽን በተመለከተም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከአንድ ዓመት በላይ ስለሚያዘገይ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ተናግረዋል።

የቆሻሻ ማስወገጃ ችግር ሌላው ገፊ ምክንያት መሆኑን ያስታወቁት የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ዋና ፀሐፊ “ለምሳሌ የአዲስ አበባ ቆዳ አምራቾች ቆሻሻ ማስወገጃ በማጣታቸው ከአንድ ወር በላይ ከምርት ርቀው ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አብዲሳ የቆዳው ኢንዱስትሪ በታሰበው ፍጥነት እንዲያድግ ከተፈለገ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች መፍትሄ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል። መፍትሄ ያሏቸውን ሲያስቀምጡም “የባንክ አሰራርን ለኢንቨስተሮች አመቺ ማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ሂደትን ማፋጠን፣ ጨውን በዘላቂነት ማልማት የሚቻልበትን አሰራር መፍጠር እና ሲኤዲ (CAD) ወደነበረበት መመለስ” የሚሉት ይገኙበታል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሰ ኃይሌ በበኩላቸው “በዚህ መንግስት ከምንም በላይ እንደቆዳ እና ሌጦ የተደገፈ ዘርፍ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የቆዳ ውጤቶች በሥፋት ይቀበሉ ከነበሩ ጣሊያን፣ ህንድ፣ ሆንግኮንግ እና ቻይና በተጨማሪ ቬትናምን አምስተኛ የገበያ መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ከኢንስቲቲዩቱ የቀረበው ሪፖርት አስታውቋል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
497 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us