በአዲስ አበባ ሊተገበር የታሰበው የኮንትራት ታክሲ አገልግሎት አገናኝ አፕልኬሽን

Wednesday, 17 August 2016 12:22

 

አዲስ አበባም ሆነች ሌሎች የአገሪቱ የክልል ከተሞች በታክሲ አገልግሎት በኩል የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ ደካማና፤ አሁን አለም ከደረሰበት የዘመነ የታክሲ አገልግሎት አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይደለም። የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡትን ሚኒባስ ታክሲዎች ይቅርና በአሁኑ ሰዓት በተለምዶ “ላዳ” በመባል የሚጠሩት የኮንትራት ታክሲ አገልግሎቶች አዲስ አበባን የሚመጥኑ አይደሉም።

 

 

ታክሲዎቹ እንደሌሎች አገራት በኩባንያ ሳይሆን በግለሰብ የሚተዳደሩ ናቸው። የሚሰጡት አገልግሎትም በግምት ላይ በተመሰረተ የዋጋ ጥሪ ነው። አብዛኞቹ ተሸከርካሪዎች እጅግ ያረጁና ከባለቤቶቹ የእለት ጉሮሮ መድፈኛነት ባለፈ ለተሻለ አገልግሎት ሊታሰቡ የማይችሉ ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን ታክሲዎቹ በተለይ በምሽት ለወንጀል የተጋለጡ በመሆኑ አሽከርካሪውም ሆነ ተጠቃሚው ላልታሰበ ጉዳትና ህይወት መጥፋት የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ።

 

 

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ እንደዚሁም የበርካታ ዲፕሎማቶችና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የታክሲና የሌሎች ትራንስፖርት አገልግሎቿም ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ መሆን አልቻለም።

 

 በአዲስ አበባ የታክሲ ባለንብረቶችን በአክስዮን በማደራጀት አሁን ያሉትን ተሸከርካሪዎች ቀስ በቀስ በአዲስ ተሽከርካሪዎች ከመለወጥ ጀምሮ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሄደበት ያለው ሙከራ ብዙም ውጤት ሲያመጣ አልታየም።

 

 

ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ የከተማዋን የኮንትራት ታክሲዎች አሰራር ወደ ዘመናዊ አሰራር በመለወጥ አገልግሎት ሰጪንና ተገልጋይን በስልክ አፕልኬሽን የማገናኘት ስራን ለመስራት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ዛይራይድ የተባለ ኩባንያ ገልፆልናል። ኩባንያው በዚህ የስልክ አፕልኬሽን ወይንም ሶፍትዌር አማካኝነት ፈላጊና ተፈላጊ በደቂቃዎች ውስጥ የሚገናኙበትን አሰራር የሚዘረጉ መሆኑን ገልፀውልናል።  አሰራሩ አንዴት ነው? አንድ ሰው የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ምን ምን ናቸው ? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዝ ጥያቄዎችን በማንሳት ከድርጅቱ ማኔጂግ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታደሰ ጋር ቆይታ ያደረግን ሲሆን የሰጡንንም ምላሾች እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- አሁን በኢትዮጵያ ለመስጠት ያሰባችሁት የታክሲ አገልግሎትንና ፈላጊን የማገናኘት ስራ በምን መልኩ የሚከናወን ነው? 

 

 

አቶ ሀብታሙ፡- እኛ ለመስጠት የተዘጋጀነው አገልግሎት የስልክ አፕልኬሽንን በመጠቀም ታክሲ ፈላጊንና የታክሲ አገልግሎትን ሰጪን ማገናኘት ነው።  ሁለቱም፤ ማለትም ፈላጊና ተፈላጊ ይሄንን አፕልኬሽን በስልካቸው ላይ ጭነው እርስ በእርሳቸው የሚገናኙበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። አሽከርካሪውን በተመለከተ በመጀመሪያ መኪናው ታርጋው ይያዛል፣አሽከርካሪው ፎቶግራፍ አብሮ በመረጃነት ይቀመጣል። በዚህ መሰረት ደንበኛው ስለ አሽከርካሪው በቂ መረጃ ይኖረዋል ማለት ነው። ይህም ሆኖ ከተጠፋፉ ደግሞ መደዋወልና አጭር የፅሁፍ መልዕክት መላላክ ይችላሉ።

 

ሰንደቅ፡- ታክሲ አሽከርካሪዎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ማሟላት ያለባቸው ነገር ምንድን ነው?

 

አቶ ሀብታሙ፡- ተጠቃሚው አፕልኬሽኑን በማውረድ (Download) እዛው አፕልኬሽኑ ላይ ይመዘገባል። ታክሲ አሽከርካሪውም እንደ ተጠቃሚው አፕልኬሽኑን በማውረድ ፎርሙን መሙላት ይችላሉ። ይሁንና አሽከርካሪዎቹን በተመለከተ እኛ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ስላለብን፤ እኛ ጋር በመምጣት እንዲመዘገቡ ይደረጋል። በዚህ ወቅት ቢሯችን መጥተው ፎቶ ይነሳሉ። መንጃ ፈቃድ በመያዝም ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ፎርም ይሞላሉ። ከዚያም ተፈራርመን እንለያያለን ማለት ነው። ይህ የአምስት ደቂቃ ስራ ነው።

 

ሰንደቅ፡- በዚህ መልኩ ፈላጊና ተፈላጊን በማገናኘታችሁ የእናንተ ገቢና ተጠቃሚነት የቱ ጋር ነው?

 

አቶ ሀብታሙ፡- አገልገሎቱን በማግኘቱ ረገድ ታክሲውን የሚጠቀመው አካል ወይም ደንበኛ ይህንን አገልግሎት በመጠቀሙ የሚከፍለው ምንም አይነት ተጨማሪ ክፍያ አይኖርም። እንደውም እኛ በሰራነው ታሪፍ መሰረት ለተጠቃሚ ደንበኛው ሂሳብ የሚቀንስበት ሁኔታ አለ። አሽከርካሪዎችን በተመለከተ ግን እኛ ከምንሰጣቸው ደንበኞች ክፍያ የተወሰነ ፐርሰነት እንወስዳለን። ይህ የሚሰበሰበው አነስተኛ ክፍያ ለሰራተኛ፣ ለማስታወቂያና ለአንዳንድ ወጪዎች ሊውል የሚችል ነው። ያም ሆኖ በሂደት ይሻሻላል በሚል እሳቤ እንጂ፤ አሁን ሊሰበሰብ የሚችለው ሂሳብ ብዙ ሆኖ አይደለም።

 

ሰንደቅ፡- አሁን ወደ ስራ ለመግባት እያደረጋችሁት ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? በተወሰኑ የታክሲ ደንበኞች ጀምራችሁ ማስፋት ነው? ወይንስ ሌላ ያስባችሁት ነገር አለ?

 

አቶ ሀብታሙ፡- የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን በአሁኑ ሰዓት እኛ ጋር ብዙ የተመዘገቡ የታክሲ አሽከርካሪዎችና ተጠቃሚዎች አሉ። እኛም ያው ያለውን አቅርቦትና ፍላጎት እያየን አገልግሎቱን እያሰፋን የምንሄድበት ሁኔታ ይኖራል።

ሰንደቅ፡- ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ይሄንን አገልግሎት ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋት እቅድ አላችሁ?

 

አቶ ሀብታሙ፡- ይሄንን አገልግሎት በሌሎች አካባቢዎች ለመጀመር ሁለት ከተሞችን ታሳቢ አድርገናል። እነዚህ ከተሞች ሀዋሳና መቀሌ ናቸው። እነዚህን ከተሞች መምረጥ የፈለግነው፤ ከተሞቹ ብዙ እንቅስቃሴና ቱሪስትም ስለሚያዘወትራቸው ነው። በአገልግሎታችን ባጃጅንም ስለምናጠቃልል ከተሞቹ ብዛት ያለው ባጃጅና ታክሲዎች ስለያዙ አይናችንን ጥለንባቸዋል። የአዲስ አበባን ከጨረስን በኋላ ወደ እነዚህ ከተሞች እናመራለን።

 

ሰንደቅ፡- ወደ ስራ በመግባቱ በኩል  የየትኞቹ  መንግስታዊ ተቋማት ድጋፍና ትብብር ነው የሚያስፈልጋችሁ? እስካሁንስ  ምን የፈጠራችሁት ግንኙነት አለ?

 

አቶ ሀብታሙ፡- የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ሰጥቶናል። መንገድ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂውን በተመለከተ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ከሁለት ሰዓት ያላነሰ ማብራሪያና ገለፃ አድርገናል። እነሱም ቴክኖሎጂውን ወደውታል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ሄደን ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ቴክኖሎጂው ያለውን ጠቀሜታ አስረድተናል። በተለይ ማታ ማታ በታክሲ አሽከርካሪውም ሆነ በተሳፋሪው ላይ የሚደርሰውን ወንጀል ለመከላከል ቴክኖሎጂው ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በፖሊስ በኩልም ተቀባይነትን አግኝቷል። ከዚህ ውጪ በሂደት አብረን ልንሰራ የምንችለው ከኢትዮቴሌኮም ጋር ነው። ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ከቴሌኮም ጋር የተለየ ግንኙነት ስላላስፈለገን እንደማንኛውም ተገልጋይ ያለውን አገልግሎት የምንጠቀም በመሆኑ ችግር የለውም።ሆኖም አገልግሎቱን በመጠቀሙ በኩል ተገልጋዮችን የበለጠ ለማበረታታት ታሪፉ የዋጋ ቅናሽ እንዲኖረው ከቴሌኮም ኩባንያው ጋር የምንነጋገርበት ሁኔታ ይኖራል።

 

ሰንደቅ፡- አንድ አሽከርካሪ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የግድ ኦንላይን መሆን ይጠበቅበታል?

 

አቶ ሀብታሙ፡- አዎ አገልግሎቱን ለመጠቀም ኦንላይን መሆንን ይጠይቃል። ሆኖም እኛ አፕልኬሽኑን ስንሰራው በዝቅተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት ጭምር እንዲሰራ አድርገን ነው የሰራነው። በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች እስከ ደብረዘይትና ሆለታ ድረስ ሄደን ሞክረነዋል። እንደሚሰራም አረጋግጠናል። እኛም ቢሆን የታክሲውንና የአገልግሎት ፈላጊውን ቁጥር እያየን ስምሪቱን የምናስተካከልበት የአሰራር ስርዓትም አለን።

 

ሰንደቅ፡-ይህ አይነቱ አሰራር በሌሎች አገራት ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

 

አቶ ሀብታሙ፡- በሌሎች አገራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ቴክኖሎጂ ነው። በአሜሪካ የኢትዮጵያን ሁለት ኢኮኖሚ ያህል የሚያንቀሳቅስ “ዩበር” የተባለ ኩባንያ አለ። እነሱ በእርግጥ የሚጠቀሙት የግል መኪናዎችንና ሊሙዚኖችን ሳይቀር ነው። እነሱ በ60 በመቶ ባነሰ ዋጋ የተሻለ መኪና ይዘው ቀረቡ። ይህ ቴክኖሎጂ በኬኒያ ከተተገበረ በኋላ የአንድ ታክሲ ገቢ በሶስት እጥፍ ነው የጨመረው።

 

ሰንደቅ፡-ይህ አፕልኬሽን ጠጥቶ ማሽከርከርን ከመከላከል አንፃር ያለው ጠቀሜታ እንዴት ይገለፃል?

 

አቶ ሀብታሙ፡- እዚህ ጋር ቺካጎ ከተማን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ችካጎ ላይ ብዙ ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ሰዎች ነበሩ። ይህ ቴክኖሎጂ ቺካጎ ላይ ጠጥቶ የማሽከርከር ሁኔታን በ60 በመቶ ቀንሶታል። እነዚህ ሰዎች ለምንድነው ጠጥተው የሚያሽከረክሩት ተብሎ ሲጠየቅ ዋነኛ ምክንያታቸው ከጠጡ በኋላ ታክሲ ሲጠቀሙ በአሽከርካሪዎች አደጋ ይደርስብናል ብለው ስለሚያስቡ ነው። በእርግጥ እውነት  ነው። አንድ ሰው ከጠጣ በኋላ የታክሲውን ታርጋና ማንነት ማስታወስ ስለማይችል ስለደህንነቱ ምንም አይነት ዋስትና የለውም። በታክሲ ውስጥ ደግሞ በተለይ በምሽት ሰዓት መዘረፍ፣መደፈርና ሌሎች ወንጀሎችም ይፈፀማሉ።

 

 ሆኖም ይህ አፕልኬሽን ፈላጊንና ተፈላጊን ሲያገናኝ የአሽከርካሪውንና የተሸከርካሪውን መረጃ በሚገባ ስለሚገልፅ ይህ ለተጠቃሚው ዋስትና ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ስለደህንነቱ ዋስትና ካገኘ ጠጥቶ ከማሽከርከር ይልቅ ታክሲ መጠቀምን ይመርጣል ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡-ይህ ፕሮግራም መቼ ነው ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው?

 

አቶ ሀብታሙ፡- ወደ ስራ የምንገባው ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ ነው። ለዚህ የተመረጡ አሽከርካሪዎች ስላሉን ስራ የምንጀምረው በእነዚህ ታክሲዎች ነው።

 

ሰንደቅ፡-አንድ ሰው መጠቀም ቢፈልግ እነዚህን አፕልኬሽኖች ከየት ነው የሚያገኘው?

 

አቶ ሀብታሙ፡- አንድ ሰው የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በመጀመሪያ አፕልኬሽኖቹን ማውረድ (Down load) ማድረግ ይጠይቃል። አይፎን ተጠቃሚ ከሆነ አፕ ስቶር ውስጥ ገብቶ ለዚህ አገልግሎት የተዘጋጀውን ዛይ ራይድ (ZayRide) የተባለውን አፕልኬሽን በማውረድ መጠቀም ይችላል። የአንድሮይድ አፕልኬሽን ስልክ ተጠቃሚ ከሆኑ ደግሞ ፕሌይ ስቶር ውስጥ በመግባት ይሄንኑ አፕልኬሽን መጠቀም ይችላሉ። ሰማያዊው የተጠቃሚው ነው። ጥቁር ቀለም ያለው ደግሞ ያሽከርካሪው ነው።

 

ሰንደቅ፡-ተጠቃሚው እንዲያውቀው በማድረጉ በኩል የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ?

 

አቶ ሀብታሙ፡- አሰራሩም ሆነ ፕሮግራሙ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ጋዜጦችንና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን በመጠቀም በስፋት የምናስተዋውቅበት ሁኔታ ይኖራል።

 

ሰንደቅ፡-ዛይራይድ ማለት ምን ማለት ነው? 

 

 

አቶ ሀብታሙ፡- ዛይራይድ የሚለውን ስያሜ የሰጠነው በዝዋይ አካባቢ ከሚገኘው ዛይ ከተባለ ቋንቋ ነው። በአንድ ወቅት ወንድሞቼ በዚህ አካባቢ ሲያልፉ ስለዚህ ቋንቋ የአካባቢው ህብረተሰብ ነገራቸው። በህብረተሰቡ ገለፃ መሰረት የቋንቋው ተናጋሪዎች  ወደ ከተማ እየገቡና በሌሎች እየተዋጡ ቋንቋ በሂደት እየተረሳ ሄዷል።  ተናጋሪውም ከ 5 ሺህ በታች የሚሆን ህዝብ ነው ይባላል። እኛም ለምን ለዚህ ቋንቋ እውቅና አንሰጠውም በሚል ነው ስያሜው በዚህ እንዲሆን ያደረግነው።

 

ሰንደቅ፡- አፕልኬሽኖቹ የበለጠ ለህብረተሰቡ ቅርብ የሚሆኑት በአገርኛ ቋንቋ አገልግሎት መስጠት ሲችሉ ነውና በእናተ በዚህ በኩል እየሰራችሁት ያለው ስራ ምንድን ነው?

 

አቶ ሀብታሙ፡- አፕልኬሽኑ በአማርኛ ተተርጉሟል። በቀጣይ ደግሞ በኦሮምኛና በትግርኛም እንቀጥላለን። ከዚህም በተጨማሪ እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው ነገር ቢኖር አገልግሎት በተለይ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አገልግሎት መሆኑን ነው። ማየት የተሳናቸው ከሆነ አፕልኬሽኑ የድምፅ አገልግሎት ይሰጣል። አንድ እንደልቡ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችል አካል ጉዳተኛ ለደህንነቱ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ያለበት ቦታ ሆኖ ታክሲ ጠርቶ መጠቀም ይችላል። እንደዚህ አይነት የታክሲ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ሰዎች የግል ሾፌር እንዳላቸው አድርገው ነው የሚቆጥሩት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
800 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us