አሳሳቢው የኤክስፖርት ገቢ ማሽቆልቆል ጉዳይ

Wednesday, 24 August 2016 14:01

 

የ2007 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ  አጠቃላይ የኤክስፖርት መጠን 4 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ይህ የኤክስፖርት መጠን ከዓመት ወደ ዓመት የመሻሻልና እድገት ማሳየት ቢጠበቅበትም በሳለፍነው 2008 በጀት አጠቃላይ የኤክስፖርቱ መጠን ወደ 2 ነጥብ 856 አሽቆልቁሏል። በ2008 በጀት ዓመት ከኤክስፖርት ለማግኘት ታቅዶ የነበረው የውጭ ምንዛሪ መጠን 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ሆኖም ከተያዘው እቅድ አንፃር የተገኘው የገቢ መጠን በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሎ ታይቷል።

 ይህም ከቀደመው በጀት ዓመት የ2008 የኤክስፖርት መጠን አንፃር በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማሽቆልቆሉን ያሳያል።  የኢትዮጵያ የኤክስፖርት አፈፃፀም በጀት ዓመት መጨረሻ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ለፓርላማ የቀረበው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያመለክታል። ይህ ገቢ መጠን የዛሬ ስድስት ዓመቱን ሪፖርት ያመለክታል። ከስድስት ዓመታት በኋላ በ2008 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር አንፃር ሲታይ የኤክስፖርት ገቢ  የእድገት ልዩነቱ የዜሮ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሆኖ ይታያል። የሀገሪቱ የኤክስፖርት እድገት በተገቢውና በተፈለገው መጠን ማደግ ይቅርና የመቀነስ ሁኔታን እያሳየ ባለበት ሁኔታ የኢምፖርት ፍላጎቱና እድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ላይ ነው። ይህም የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን ክፍተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋው ይገኛል። ይኸው ለፓርላማ የቀረበው ሪፖርት “ኢኮኖሚያችን በፍጥነት እያደገ ባለበት በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ መድረሱን ግን አሳሳቢ ያደርገዋል” በማለት የገለፀ ሲሆን፤ ሪፖርቱ አያይዞም “የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን እድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል እና ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ያብራራል። ሀገሪቱ የውጭ ሸቀጥን ማስገባት የምትችለው በኤክስፖርት ገበያ በምታገኘው ገቢ ደረጃ ነው።

ከኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ የአንድ ሀገር አለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ የተወዳዳሪነት አቅም የሚለካው በኤክስፖርት የገቢ አፈፃፀም መጠን ነው። በተለያየ መልኩ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም፤ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በ2006 በጀት ዓመት የተገኘው የኤክስፖርት ገቢ መጠን  መሸፈን የቻለው ከ20 በመቶ በታች የሆነ የኢምፖርት ገቢን ነው። ይህም ምን ያህል የሀገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት የሰፋ መሆኑን የሚያመለክት ነው። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ማሽቆልቆሉም ብቻ ሳይሆን እስከዛሬም ድረስ በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ መንጠልጠሉ ሌላኛው ፈተና ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ የሚላኩትም የግብርና ምርቶች እሴት የማይጨመርባቸውና ያላቸው አለም አቀፋዊ የጥራት ተወዳዳሪነታቸውም በሚፈለገው ደረጃ ያልሆኑ ናቸው። በ2008 በጀት ዓመት ለነበረው የኤክስፖርት አፈፃፀም ዝቅተኛነት ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንደኛው የምርቶቹ አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት ነው።

የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ግብርና ላይ ጥገኛ መሆኑ ከደቀኑበት ፈተናዎች መካከል ሌላኛው የምርት አቅርቦቱ መጠን በአየር ንብረት ሁኔታ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው። ለ2008 በጀት ዓመት ኤክስፖርት ገቢ ማሽቆልቆል ምክንያት ተደርገው ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከልም አንዱ በምርት ዘመኑ የተፈጠረው የኢልኒኖ ክስተት ነው።

ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያን የወጭ ንግድ ስብጥር ለመለወጥ የተደረገው ጥረት እስከዛሬም ድረስ ለውጥን ሊያመጣ አልቻለም። ከግብርናው ጥሬ ምርት ባለፈ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለመላክ የተደረገው ጥረት ውጤትን አላመጣም።

 በማኒፋክቸሪንጉ ዘርፍ በተለይም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንደዚሁም በስኳሩ በኩል ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጀምሮ የተቀመጠው እቅድ በአፈፃፀሙ ሲፈተሸ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ይታይበታል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ ላይ ወደ ኤክስፖርት ገብቶ ሌሎችን የኢኮኖሚ ዘርፎች በገቢ ይደግፋል ተብሎ የታሰበው የስኳር ፕሮጀክት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሳይቀር ወደ ኤክስፖርት መግባት አልቻለም።

እንደ ምሳሌ ያህልም የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲታቀድ በ2007 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት 1 ቢሊዮን ዶላር እንደዚሁም ከስኳር 660 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያው በጀት ዓመት ተጠናቆ በዚህ ባሳለፍነው 2008 በጀት ዓመት ሳይቀር እነዚህ ምርቶች ለኤክስፖርቱ ዘርፍ ያላቸው ድርሻ እጅግ አነስተኛ ነው። የስኳሩ ዘርፍ ጭራሹኑ ወደ ኤክስፖርት መግባት ይቅርና ለዓመታት የተጓተቱት ፕሮጀክቶች ሳይቀሩ ከፍተኛ ገንዘብ በልተው ዛሬም ድረስ መጠናቀቅ አልቻሉም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው በጀት ዓመት የፓርላማ መክፈቻ ላይ የፕሬዝዳንቱን ንግግር መሰረት ባደረገ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ሰፊ ቦታ የተሰጠው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ማሽቆልቆልና የንግድ ሚዛኑን ጉድለቱ እየሰፋ የመሄዱ ጉዳይ ነበር። በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከመግለፅ ባለፈ በቀጣይ መፍትሄ ነው ያሏቸውን ሀሳቦች በሚከተለው መልኩ ገልፀው ነበር።

 “ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ሁኔታ ይህ የገቢና ወጪ ንግድ መዛባት ካልተስተካከለ ኢኮኖሚያችን ውስጥ ከፍተኛ መመሰቃቀልን የሚፈጥር ነው። ስለዚህ የወጪ ንግድ ሚዛን ወይንም የኤክስፖርትና ኢምፖርት መካከል ያለውን ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ ማጥበብ ይጠበቃል። ይህንን የምናደርግበት ዋነኛው ምክንያት ሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ እያደገች ያለች አገር በመሆኗ ከውጭ የምናስገባው የልማት እቃዎች በጣም ከፍተኛ ነው። ይሄንን መሸፈን የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ በወጭ ንግድ አማካኝነት የማናገኝ ከሆነ በሂደት ልማታችን ተንገራግጮ የሚቆምበት ሁኔታ ይኖራል።

 ከዚህ አኳያ የወጪ ንግዳችንን እናሰፋለን ብለን የያዝናቸው እቅዶች አሉ። እነዚህንም እቅዶች ማሳካት የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህም ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን የሚል እቅድ ነው የያዝነው። አሁንም ሰባ በመቶ የሚሆነውን ወጭ ንግዳችንን የሚይዘው የግብርና ምርቶች ናቸው። ይህ ከሆነ የግብርና ምርትን መጨመር በጣም አንገብጋቢ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ምርታማነትን በተመለከተ አብዛኛው አርሶ አደር የሚፈለገው የምርት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ተግተን መስራት ይኖርብናል።

 ይህ ኃላፊነት የመንግስትንም፣የአርሶ አደሩንም ሆነ የሌሎች ድጋፍ ሰጪዎችን ኃላፊነት መወጣት የሚጠይቅ ስራ ነው። ስለዚህ የወጭ ንግዳችንን ማሻሻል ካስፈለገ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር አለብን ማለት ነው። ይህም ለሁለት ጉዳዮች ይጠቅመናል። አንደኛው ከሽያጭ የምናገኘውን ገቢ ያሳድግልናል። ሁለተኛው የግብርና ምርቶች የወጭ ንግድ በየጊዜው የሚዋዥቅ ቁማር መሰል ባህሪ ያለው እንደመሆኑ መጠን ከሽያጭ የምናገኘውን ገቢ በማሳደግ በዋጋ መውድቅና መዋዠቅ የሚመጣውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል።

 ከዚህ አኳያ የግብርና ምርቶችን የኤክስፖርት መጠን መጨመር ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው። ለወጭ ንግድ የሚውሉ የግብርና ምርቶች ይታወቃሉ። ቡና፣ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ አበባ እንደዚሁም አትክልትና ፍራፍሬ መስኮች፣ የቁም እንስሳት፣ስጋ እና የመሳሰሉት ናቸው። በእነዚህ በሚታወቁት የግብርና ምርቶች የጥራትና የብዛት የምርት አቅርቦት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባናል። ይህ የመጀመሪያው መፍትሄ ነው።

ሁለተኛው የማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ምርቶች ናቸው። ይህንን በተመለከተ  አሁን ያሉትን አምራች ኩባንያዎች በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ ድጋፍ ተደርጎላቸው ከፍተኛ ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ነው። ከዚህ አኳያ የጀመርናቸው ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ነው። በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት ኩባንያዎቻችን በመጨረሻው የቅልጥፍና የማምረት ደረጃ እንኳን ቢያመርቱ በቂ የኤክስፖርት መጠን ሊያመርቱ ስለማይችሉ በውጭ ባለሀብቶችም ሆነ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አዳዲስ አምራች ባለሀብቶች በተለያየ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው። እነዚህን ሁለቱን በማጣመር የማኒፋክቸሪግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ምርቶችን መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማድረግ ያስፈልጋል ብለው ነበር።

ሆኖም በተፈለገው መጠን ምርታማ ለመሆን በርካታ ማነቆዎች አሉ። ከማነቆዎቹ መካከልም በየዘርፉ የሰለጠነ አምራች የሰው ሀይል አለመኖር፣ መንግስት በሚሰጣቸው አገልግሎቶችም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር አለ። ከዚህም በተጨማሪ የቴሌኮም የውሀና የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተደራጀ ሁኔታ ለባለሀብቱ የሚቀርቡበት ሁኔታ መኖር መቻል አለበት። ሌሎች አገልግሎቶችም ቢሆኑ ለምሳሌ የሎጀስቲክስ አገልግሎቶች የትራንስፖርት ወጪን በሚቀንስ መንገድ ሊሰጡ ይገባል። እነዚህ ማነቆዎች ስላሉ። የማኑፋክቸሪጉን ዘርፍ ምርታማነት እንደዚሁም የኤክስፖርት  አቅም ለማሳደግ እነዚህን ዝርዝሮች ይዘን አንድ በአንድ መፍታት ያስፈልጋል ማለት ነው።

ከማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ውስጥ ፕሬዝዳንቱ ባቀረቡት ንግግር ስለስኳር ጉዳይ አንስተው “የስኳር ምርታችን በተለያዩ ምክንያቶች ለኤክስፖርት ገበያ ሊደርስ አልቻለም። በሚቀጥለው አመት በወሳኝ መልኩ ወደ ኤክስፖርት ገበያ የሚገባበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን። ይህን ብቻ ሳይሆን የኤክስፖርትን ስብጥር ከፍ ማድረግ አለብን ብለን የያዝናቸውንም ዘርፎች ማየት ይገባናል። ለምሳሌ አበባ አትክልትንና ፍራፍሬን ከተመለከትን ነባር ኩባንያዎች መሬት ማስፋፋት ስላቃታቸው ብቻ በዚህ ዘርፍ ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ የኤክስፖርት ገቢ ላይ መድረስ ስንችል ሳንደርስ ቀርተናል። እነዚህ ባለሀብቶች ለማስፋፊያ የሚሆን መሬትን ለማግኘት ጥያቄ አቅርበዋል። ነገር ግን መሬትን  በማቅረብ ባለው መጓተት ማስፋፊያውን ሳያገኙ ቀርተዋል። መሰል ችግሮቻችንን ከፈታን የኤክስፖርት ምርታችንን ማሳደግ እንችላለን። ክልሎችም የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በማደራጀት በከፍተኛ ሁኔታ የጀመሩት ሁኔታ ስላለ፤ በዚህ በኩል ከላይ እስከታች ተቀናጅተን ከሰራን አሁን ያጋጠመንን የወጪ ንግድ ሚዛን ለማጥበብ የበኩሉን ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ።

በማዕድኑም ዘርፍ ቢሆን በተለይ ባህላዊ የወርቅና ሌሎች ጌጣጌጦችን የማምረት ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ከተንቀሳቀስን በዚህም ዘርፍ ቢሆን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያልተናነሰ የኤክስፖርት ገቢን ማግኘት ይቻላል። እነዚህ ያስቀመጥናቸውን መፍትሄዎች ታሳቢ አደርገን በቁርጠኝነት የምንስራ ከሆነ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
778 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us