የቻይና መርቸንት ግሩፕ፣ ከባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ጋር በሽርክና ለመስራት እየተደራደረ ነው

Thursday, 01 December 2016 15:12

 

-    አቶ መኩሪያ ኃይሌ እና አቶ አሕመድ ቱሳ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል

 

የቻይናው መርቸንት ግሩፕ አካል የሆነው ሲኖትራንስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ጋር አክሲዮን በመመስረት በሽርክና ለመስራት እየተደራደሩ መሆናቸውን የሰንደቅ ምንጮች ገለፁ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት፣ “የቻይና መርቸንት ግሩፕ አካል ከሆነው ሲኖትራንስ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ድርድሮች ተደርገዋል። ድርድሩን የሚያካሄደው የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ድጋፍ ሰጪ ጽ/ቤት ነው። ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ናቸው። በቅርቡ ሲኖትራንስ የቢዝነስ ፕሮፖዛሉን አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በተያዘው የድርጊት መርሃ ግብር መሰረት አክሲዮን ማሕበሩን ለመመስረት የተጀመሩ ዝግጅቶች በአራት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ። የአክሲዮን ድርሻ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ወደ ሥራ ይገባል። መንግስት ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ ይይዛል” ብለዋል። 

የዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊ አያይዘውም፣ “ድርጅቱ ያለበት ኃላፊነት በጣም ትልቅ ነው። የሀገሪቱ የወጪና የገቢ የሎጅስቲክ ፍላጎት በጣም እያደገ መጥቷል። የአገልግሎቶቹ ባህሪያት ተለውጠዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ናቸው። የገበያ ድርሻ ማስፋት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ይህም በመሆኑ ግልጽ ራዕይ መንግስት አስቀምጦ የስትራቴጂ ሰነዶችን አዘጋጅቶ እየሰራ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ ባለሃብቶች የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ከሎጅስቲክ አቅርቦት ጋር የተሳሰረ ነው። መንግስት ከዚህ የሎጅስቲክ አቅርቦት ችግሮች ሳይላቀቅ ስለአጠቃላይ የትራስፎርሜሽን የለውጥ እቅዶች መሳካት አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም። ስለዚህም ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ደንበኞቹን የሚያረካ ወጪ ቆጣቢ የትራንዚት እና የሎጅስቲክ አደረጃጀት እና የአሰራር ስርዓት ዝርጋታ አስፈላጊ ነው።”

“ሽርክና ማልማት ለምን አስፈለጋችሁ? በዘርፉስ ቁልፍ ችግሮች ምንድን ናቸው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው የሰጡት ምላሽ፣ “ዋናው ቁልፍ ጉዳይ የአመራር እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ነው። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ደግሞ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በአክሲዮን መስራት በዘርፉ ባለሙያዎች የሚመከር ነው። መንግስትም ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው። ምክንያም ሎጅስቲክ ለዓለም ዓቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በሀገራችን ወጪና ገቢ መጠን እያደገ ነው። ይህንን እድገት ያገናዘበ ከፍላጎት ጋር የተጣጣመ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋ የሎጅስቲክ አገልግሎት አስፈላጊ ነው። ማደግ ለሚፈልግ ሀገር የሎጅስቲክ አገልግሎት የማሟላት ፍላጎት፣ የሞት ሽረት ጥያቄ ነው። ምክንያቱም፣ ከሎጅስቲክ ውጪ ስለእድገት ማሰብ አይቻልም። የትኛውም ሀገር በዓለም ላይ የሚጠበቅበትን የሎጅስቲክ አፈፃጸም ሳያሳካ ያደገ ሀገር የለም። መንግስትም ይህንን መሬት የወረደ እውነታ ከግምት አስገብቶ የትራስፎርሜሽኑ አንዱ አካል አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሆኖም ግን የሚፈለጉ ውጤቶች እየመጡ ነው? ለሚልው ጥያቄ፣ መልሱ አይደለም ነው። ለዚህም ነው፣ ከውጭ ኩባያዎች ጋር የቴክኖሎጂና የክህሎት ትራስፎርሜሽን ማድረግ ያስፈለገን” ብለዋል።

ኃላፊው አያይዘውም፤ “በርግጥ ይህን አቅጣጫ ማስፈጸም የሚችለው፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ለመስራት በዘርፉ በቂ ልምድ ያለውና መናበብ የሚችል ባለሙያ ነው። ባለሙያ ከዘርፉ ሥራዎች ጋር የተጋባ፤ በዘርፉ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መምረጥ የሚችል ቢያንስ የቀረቡትን የሚረዳ፤ ከዓለም ዓቀፍ የባሕር ንግድና ሕግ ጋር የሚተዋወቅ እና መንግስትን በዘርፉ ላይ ያለውን አቅጣጫ የተረዳ እና የማስፈጸም አቅሙ ከፍተኛ የሆነ መሆን እንዳለበት መገመት አስቸጋሪ አይደለም። በድርጅታችን ውስጥ ውስን ቢሆኑም በዘርፉ የተማሩ ከፍተኛ የሥራ ልምድ ያካበቱ አመራሮች አሉ። እነሱን ይዘን ሌሎችንም እያበቃን እንዲሁም ከውጭ ከሚመጡ የሰው ኃይሎች ጋር አጣምረን በማሰራት የታቀደውን ግብ ማሳካት አይከብደንም” ሲሉ የዘርፉ አስረድተዋል።

የገዢው ፓርቲ አዲሱ የአመራር አሰጣጥ አቅጣጫም እንደሚያሳየው፣ የማዕከላዊ አባል ወይም ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር በመሆን ብቻ ስልጣን እንደማይያዝ ነው። ከዚህ መሰረታዊ አስተሳሰብ አንፃር የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅትን በፖለቲካ ወገንተኝነት ለመምራት መሞከር ለውድቀት ከመጣደፍ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ይህን ወሳኝ መሰረታዊ የእድገት ዘርፍ ለመምራት ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የፖለቲካ አመራሮች ወይም የሲቪል ባለሙያዎች ማግኘት የግድ ይላል። እንደው ዝም ተብሎ የፓርቲ የማዕከላዊ አባል በመሆን ወይም ከፍተኛ ካድሬ በመሆን ብቻ የሚወጡት የሥራ ዘርፍ አይደለም። ከዚህ በፊት በድርጅቱ የነበረው አካሄድ የሚደገም ከሆነ፣ ድርጅቱን ትራንስፎርም ማድረግ ቀርቶ አሁን ባለበት ድንጉዝጉዝ ሁኔታ እንኳን ይዞ መቆየት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

ከዚህ ዘርፍ አገልግሎት ከሚያገኙ የድርጅቱ ደንበኞች መካከል ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ፣ “የባሕር ትራንስፖርት እና የሎጅስቲክ አገልግሎት ዘርፍ የሥራ ቋንቋዎችን ለማወቅ ቢያንስ የአንድ ዓመት ሙሉ ጊዜ ይፈልጋል። የሚሾመው ሰው ከዘርፉ ጋር የማይተዋወቅ ከሆነ የትራንስፎርሜሽን ግቡን ለማሳካት አይቻልም። ከተያዘው የአምስት ዓመት እቅድ ውስጥ፣ አንዱ ዓመት ተሿሚውን ባለስልጣን ሥራ ማላመድ ነው የሚሆነው። በመንግስት እና በተገልጋዮች ጊዜ ላይም የአንድ ዓመት ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው። ስለዚህ ዘርፉ የሚፈልገውን ክህሎት የሚያሟላ መመደብ አስፈላጊ ነው። መንግስት ያስቀመጠውን የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት የትራስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ቁርጠኛ የሆነ እና ደንበኞችን ለማርካት የሚተጋ አመራር ማስቀመጥ ተገቢ ነው። ለእኛም ቢሆን ከመደናቆር ይገላግለናል።” ብለዋል።

የኢትዮጵያ የገቢ መጠን 13 ሚሊዮን ሲሆን የወጪው 1 ሚሊዮን ቶን አካባቢ ነው። በዓለም ባንክ ደረጃ አሰጣጥ (Logistic performance index) ኢትዮጵያ በ126ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠችው። አሁን በተያዘው የሁለተኛ የትራስፎርሜሽን እቅድ ወደ 57 ደረጃ ከፍ ለማለት ነው። ይህ ማለት ሀገሪቷ በ2017 ወደ መካከለኛ ገቢ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ካስቀመጠችው ግብ አንፃር፣ ተመጣጣኝ የሆነ ቀልጣፋ የሎጅስቲክ እና የትራንዚት አገልግሎት አቅርቧቷ የአሰራር ሥርዓት ላይ መድረስ ይጠበቅባታል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት ሀገር ነች። ሩዋንዳም እንደዚሁ። ሆኖም ማጣቀሻዎች እንደሚያሳዩት ሩዋንዳ ከባሕር በር በጣም ርቃ ብትገኝም በትራንዚት እና በሎጅስቲክ አፈፃፀሟ ከኢትዮጵያ የተሻለ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ከፍተኛ ሥራዎች መስራት አስፈላጊ ነው። በጅቡቲ አንድ እና ሁለት ላይ በግልጽ በአንድ ወደብ እና በአንድ የትራንዚት ኮሪደር ላይ ጥገኛ ሆነ መቀጠል እንደማይቻል ተቀምጧል። በአማራጭ ወደቦች በመጠቀም የሀገሪቷን ወጪ እና ገቢ ማቀላጠፍ ታምኖበታል። በሶማሌላንድ በበርበራ ወደብ ለመጠቀም ስምምነት ተፈርሟል። በርበራ ከጅቡቲ ወደብ ጋር ተቀራራቢ ርቀት ነው ያለው። ሆኖም በአሁን ሰዓት ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ አንዳንድ ፋሲሊቲዎች አለመሟላት፣ በሁለቱ ሀገሮች የሥራ ኃላፊዎች መካከል የመናበብ ችግር እና በጋራ የሚሰሩበት አደረጃጀት አለመፈጠሩ በውስንነት የሚነሳ ቢሆንም በሂደት እንደሚስተካከል አጠራጣሪ አይደለም። በዚህ የበርበራ ወደብ ሰላሳ በመቶ የውጪና የገቢ እቃዎች ለማስተናገድ ታቅዶ እየተሰራ ነው። እንዲሁም በሱዳን አስር በመቶ የገቢና የወጪ እቃዎችን ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው። ስልሳ በመቶ የሚሆነው በጅቡቲ የሚስተናገድ ነው የሚሆነው። ስለዚህም ከመንግስት አንፃር አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የእይታ ችግር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ቀደም ባሉ ጊዚያት የባሕር ትራንዚት የቦርድ ኃላፊ ሆነው በማገልገላቸው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እንዳላቸው ይታወቃል። በዚህ የሥራ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ እንደሚመድቡ ይታመናል።

በተያያዘ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዋና ሥራአስፈፃሚ የነበሩት አቶ አሕመድ ቱሳ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት የቦርዱ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ መኩሪያ ኃይሌ ከኃላፊነታቸው ተነስተው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተክተዋቸዋል።

አቶ መኩሪያ ኃይሌ በደቡብ ኮሪያ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። አቶ አሕመድ ቱሳ የኦሮሚያ ገቢዎች የቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን ምንጮች ለሰንደቅ ገልጸዋል።

የቻይና መርቸን ግሩፕ በዓለማችን 6ኛ ግዙፉ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ አገልግሎት አቅራቢ ነው፡፡

Last modified on Thursday, 01 December 2016 15:15
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
598 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 100 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us