እንጀራ በቺፕስ መልኩ እየቀረበ ነው

Wednesday, 07 December 2016 15:51

 

በብዙዎች ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን  የሚታወቀው የድንች ቺፕስ ነው። ሆኖም በቅርቡ በተካሄደው 4ኛው አዲስ አግሮ ፉድ ዓለምዓቀፍ የግብርናና የግብርና ማምረቻ ቁሳቁሶች፣ የምግብና የምግብ እቃዎች እንደዚሁም የማሸጊያ ቴክኖሎጂ ኤግዚብሽን ላይ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው አንድ የቺፕስ አይነት ነበር። ይህ ቺፕስ የተሰራው ከድርቆሽ እንጀራ ነው። አምራቹ  ኢትዮግሪን ምርትና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለ ኩባንያ ነው።

  ኩባንያው እንጀራንና የተለያዩ የጤፍ ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያ አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ሲሆን ከምርቶቹ መካልም የጤፍ ቺፕስ አንዱ ነው። ይሄው የድርቆሽ እንጀራ ቺፕስ በተለያዩ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ጭምር ተቀምሞ የተሰራ መሆኑን ከተደረገልን ገለፃ መረዳት ችለናል። የጤፍ ቺፕሱ ከማር፣ ከሰሊጥ፣ ከድምብላል፣ ከነጭ ሽርኩት፣ ከቀረፋ ዝንጅብልን ከመሰሉ ሌሎች ተጨማሪ የምግብ አይነቶች ጭምር በተለያየ መልኩ የተዘጋጀ ነው። ተጠቃሚዎችም እንደየፍላጎታቸው እየመረጡ መግዛት የሚችሉት የቺፕሶቹን አይነቶች በመቅመስና የጣዕም ፍላጎታቸውን በሂደት በመለየት ነው።

  በምርቶቹ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጠን ምርቱን ለኤግዚብሽኑ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ላይ የነበረው ወጣት ገመቺሳ ኤጄታ ነው።  ድርጅቱ የጤፍ እንጀራ ምርቶቹን ለታላላቅ ሆቴሎች ከማቅረብ ባሻገር የኤክስፖርት ስራንም በመስራት ምርቱን ለውጭ ገበያ ያቀርባል። በቀንም እስከ አስር ሺህ እንጀራ የማቅረብ አቅም ያለው መሆኑን ወጣት ገመቺሳ ካደረገልን ገለፃ መረዳት ችለናል።

  በቀጣይም ከዚህም በላይ እንጀራ የማቅረብ አቅሙን ለማስፋትና የእንጀራ ቺፕሱንም በሰፊው ለማቅረብ ኩባንያው ሰፋ ያለ የገበያ ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን ወጣት ገመቺሳ ጨምሮ ገልፆልናል። ድርጅቱ ኤክስፖርት ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከኤክስፖርት መዳረሻዎቹ መካከልም አሜሪካ በዋነኝነት የምትጠቀስ መሆኗን ወጣት ገመቺሳ ገልፆልናል። ምርቱ ከሚቀርባቸው ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ሌላኛዋ መዳረሻ ሀገር ናት። የአውሮፓ ገበያንም ሰፋ ባለ ሁኔታ ለመጠቀም እቅድ ተይዟል።

 የቺፕሱን የቆይታ ጊዜ በተመለከተ ጥያቄ ያነሳንለት ወጣት ገመቺሳ በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም የእንጀራ ድርቆሽ እስከ አንድ ዓመት ሊቆይ ይችላል የሚል ግምት ያለ መሆኑን ገልፆልናል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
452 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us