አልሲሲ በ364 ሸቀጦች ላይ የገቢ ታሪፍ ጭማሪ ጣሉ

Wednesday, 07 December 2016 15:55

 

የግብፅ ኢኮኖሚ በተፈለገው መጠን ሊያገገም ባለመቻሉ መንግስት አሁንም ተከታታይ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአልሲሲ መንግስት ከሰሞኑ “የቅንጦት ሸቀጦች ናቸው” ባላቸው 364 ገቢ ሸቀጦች ላይ የታሪፍ ጭማሪ አካሂዷል። ይህ ድንገተኛ የታሪፍ ጭማሪ የተካሄደው ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ቢሮ በወጣ ቁጥር 538/2016 መመሪያ ነው።

ይህ የሸቀጦች ታሪፍ ጭማሪ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያው ታሪፍ ጭማሪ የተካሄደው እ.ኤ.አ በ2013 በመመሪያ ቁጥር 184 ነበር። ዝርዝሮቹ በጋዜጣ ለህዝቡ እንዲደርሱ የተደረገ ሲሆን እንደ ኢንዲፔንደት ዘገባ ከሆነ በዚህ የታሪፍ ጭማሪ የሸቀጦች ዋጋ በአማካይ 60 በመቶ እንዲንር ተደርጓል።በዚህ የሸቀጦች ታሪፍ ጭማሪ ከውጭ በሚገቡ እንደ ሽቶ፣ የመዋቢያ ምርቶች (Cosmetic products) ርችት፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ስኒከር መጫሚያዎች፣ የማብሰያ ወጥ ቤት እቃዎች፣ እና በመሳሰሉት ላይ ከፍተኛው ታሪፍ እንዲጣል ተደርጓል። ለኮካ ምርት በሚውሉ ግብዓቶች ላይ እንደዚሁም በማስቲካና በሌሎች መሰል ምርቶች ላይም የታሪፍ ጭማሪ ተካሂዷል።

መንግስት ገቢውን ከፍ ለማድረግ እንደዚሁም ወጪውን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቀደም ሲል በመንግስት እየተደጎመ ለህዝቡ ሲቀርብ የነበረው የነዳጅ ምርት ድጎማው እንዲነሳ መደረጉ ይታወሳል።

ግብፅ በዓረቡ ዓለም የተከሰተውን የዓረብ አብዮት ተከትሎ ከደረሰባት የኢኮኖሚ ድቀት ለመውጣት በርካታ ገንዘብ ነክና ገንዘብ ነክ ያለሆኑ የኢኮኖሚ ማስተካከያዎችን ስትወስድ ብትቆይም አሁንም ድረስ ኢኮኖሚው በተፈለገው ደረጃ መስተካከል አልቻለም። እንደ አህራም ኦንላይን ዘገባ ከሆነ በቀጣይም ሌሎች መሰል እርምጃዎች የሚጠበቁ ይሆናል። የአልሲሲ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ማስተካከያ ለማድረግ እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ግን በበርካታ ግብፃዊያን ላይ ራሱን የቻለ ጫናን በማሳደር ላይ ነው። የግብፅ ፓውንድ ከዶላር አንፃር ያለው ዋጋ እየወረደ መሄድ ደግሞ ሌላኛው ለሀገሪቱ የዋጋ ንረት መባባስ ፈተና ሆኖ የተደቀነ ሲሆን ይህም በተለይ የዶላርን የጥቁር ገበያ የደራ እንዲሆን አድርጎታል።

 የግብፅ ፓውንድ ዋጋ ከዶላር አንፃር መውረድ በራሱ ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረትን ያስከተለ ሲሆን በቅርቡ መንግስት የወሰደው ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የገቢ ታሪፍን ከፍ የማድረግ ስራ ደግሞ ሀገሪቱን ወደ ግሽበት ቀለበት ውስጥ እየከተታት ነው።

 በግብፅ ያሉ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ትርፎቻቸውን በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ለመውሰድ የሚያደርጉት ጥረትም እክል እየገጠመው መሆኑን ተከትሎም ማዕከላዊ ባንኩ አንዳንድ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውስድ ላይ ነው። የአልሲሲ መንግስት በተለይ እየገጠመው ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለመፍታት የሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን እገዛ ሲጠይቅ የቆየ ሲሆን በቅርቡም ፕሬዝዳንት አልሲሲ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬት ተጉዘው ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ዓመታዊ ብሄራዊ በዓል ቀንን ጭምር የሚታደሙ ሲሆን የእገዛ ጥያቄንም ለሀገሪቱ ባለስልጣናት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ግብፅ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንድትወጣ ቀጥተኛ የነዳጅ አቅርቦትን በማድረግና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያም የተረጋጋ እንዲሆን ባለፈው ነሀሴ ወር ለግብፅ ማዕከላዊ ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለቃለች።

የግብፅ መንግስት በከፍተኛ ወጪና ገቢውን ለማስተካከል ከፍተኛ የሆነ በዜጎቹ ላይ የኑሮ ጫናን ሊያስከትሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ የመንግስት ወጪ በተለይም በወታደራዊው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመናር ላይ ነው። መንግስት ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት እንኳን በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ከካዝናው በማውጣት ከውጊያ መርከቦች እስከ ጦር አውሮፕላኖች ሲገዛና የስሩልኝ የቀብድ ክፍያን ሲፈፅም ቆይቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
453 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us