አድማሱን እያሰፋ የመጣው ኤግዚብሽን

Wednesday, 07 December 2016 15:50

 

የግብርና፣ የግብርና ማምረቻ ማሽነሪዎች እንደዚሁም የምግብና የምግብ ማምረቻ ቴክኖሎጂዎች እና ፓኬጂግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ኤግዚብሽን ባሳለፍነው ሳምንት ከህዳር 23 እስከ 26 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ተካሂዷል።

 ለአራተኛ ጊዜ በተከናወነው በዚሁ ኤግዚብሽን ላይ የተለያዩ የግብርና ምርት ግብዓቶች፣ በፋብሪካ የምርት ሂደት ውስጥ ያለፉ የምግብ አይነቶች እና ማሽነሪዎች ቀርበዋል።

 የውጭ ኩባንያዎቹ ከመጡባቸው ሀገራት መካከልም ቱርክ፣ ቻይና፣ኢንዶኔዥያና ህንድ ተጠቃሽ ናቸው። ሆኖም በርካቶቹ የቱርክ ኩባንያዎች ናቸው። ከሌሎች ሀገራት ኩባንያዎች በተለየ ሁኔታ የቱርክ ኩባንያዎች ተሳታፊነት ለምን በቁጥር ላቅ ብሎ ታየ የሚል ጥያቄን አንስተን ነበር።

 በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የኤግዚብሽኑ አዘጋጅ ኢቴል አድቨርታይዚግና ኮሙኒኬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሪት ሀይማኖት ተስፋዬ ኤግዚብሽኑ በመጀመሪያ ሲታሰብ የቱርክ ታላላቅ ባለሀብቶችን ሀገር ውስጥ በመምጣት ምርቶቻቸውን የሚያስተዋወቁበትና ወደ ገበያው የሚገቡበትን እድልና የገበያ ግንኙነት መፍጠር እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም በጊዜ ሂደት ከቱሩክ ባለሀብቶች ባለፈ የሌሎች ሀገራት ኩባንያዎችም በዚህ ኤግዚብሽን ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እያደረባቸው በመሄዱ ከቱርክ ውጪ ያሉ ሀገራት ኩባንያዎችም እንዲሳተፉ የተደረገ መሆኑን ገልፀውልናል። ባለፈው ዓመት የተሳታፊዎች ቁጥር 42 የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በዚህ ዓመት ወደ 56 ያደገ መሆኑን ወይዘሪት ሀይማኖት አመልክተዋል። የተሳታፊ ሀገራትም ቁጥር ወደ አስር ማደጉ ታውቋል።

 የኤግዚብሽኑ አዘጋጅ ኢቴል አድቨርታይዚግ ኤግዚብሸኑን ከቱርክ መንግስትና በዚያው በቱርክ ከሚገኝ  አለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ሲሆን የኤግዚብሽኑ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ወጪው የሚሸፍነውም የቱርክ መንግስት መሆኑ ታውቋል።  በእለቱ በቦታው ተገኝተው ኤግዚብሽኑን በንግግር የከፈቱት በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ሚስተር ፋቲህ ኦልሳይ የኢትዮጵያና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

 ቱርክ ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪካ ሀገራት ያላት አጠቃላይ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት 6 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ከዚህ አጠቃላይ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ውስጥ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው በኢትዮጵያ ኢንቨስት የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

  በኤግዚቢሽኑ ላይ በርካቶች ምርቶቻቸውን የሚቀበሉ አስመጪ ወኪል የሚፈልጉ ሲሆን እንደ ወይዘሪት ሀይማኖት ገለፃ የሚገቡት ማሽኖች የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች የአመራረትና የአስተሻሸግ ደረጃን ከፍ በማድረግ የተሻለ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲጨምር ስለሚያደርጉ በተዘዋዋሪ የሀገሪቱን የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት እንዲጨምር ማድረግ ይችላሉ። በኤግዚብሽኑ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ። በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩና የንግድ ትስስርን ለመፍጠር ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶችም የራሳቸውን ጉብኝት በማድረግ የሃሳብ ልውውጥንም አድርገዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
415 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us