የብርን ምንዛሬ ማውረድ ለኤክስፖርት መሻሻል ወሳኝ መፍትሄ መሆን ይችል ይሆን?

Wednesday, 14 December 2016 13:40

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ለአንድ አስርት ዓመታት የሁለት አሃዝ እድገት ሲያመዘገብ የቆየ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ይህ ለአንድ አስርተ ዓመት የቆየው 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ወደ ነጠላ አሃዝ ከመውረድ ባለፈ በተወሰነ ደረጃ የመውጣትና የመውረድ አዝማሚያዎች እየታዩበት ነው። የኢትዮጵያን 2015/2016 ምጣኔ ሃብት እድገት በተመለከተ አምስተኛውን ግምገማዊ ሪፖርት ይፋ ያደረገው ዓለም ባንክ የተጠቀሰው በጀት ዓመት(2015/2016) የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት 8 በመቶ መሆኑን አመልክቷል።

 

 ቀደም ሲል ለአንድ አስርተ ዓመት የነበረው የ11 በመቶ የእድገት መጠን ወደ 10 ነጥብ 4 መውረዱ የተመለከተው በ2014/2015 በጀት ዓመት ነበር። የባንኩ የትንበያ ሪፖርት የሚያመለክተው የሀገሪቱ ቀጣይ ሁለት ዓመታት እድገትም ከ አንድ አሃዝ ሊወጣ የማይችል መሆኑን ነው።

 

የኢኮኖሚ እድገቱ ለምን አሽቆለቆለ?

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ዋነኛ መሰረት ተደርጎ የሚነሳው የግብርናው ዘርፍ ነው። ኢኮኖሚውም የግብርና መር ነው። ግብርናው በቀጥታ እንደዚሁም የኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆን ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። ይሁንና ባለፈው በጀት ዓመት ከኤሊኖ የአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በግብርና ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ ማሽቆልቆል እንዲታይ ያደረገ መሆኑ በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በራሱ በዓለም ባንክ ይፋዊ የግምገማ ሪፖርት ተመልክቷል።

ይህ የኢኮኖሚ እድገቱ መሰረት የሆነው የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ መውረድ ብሎም መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተረጂዎች  ቀለብ ለመቻል ከካዝነው ሲመድበው የነበረው  ጥሬ ገንዘብ በራሱ ለቀጣይ የልማት ስራ ሊውል ይችል የነበረውን ሀብት ወደ እለት ፍጆታነት እንዲዘዋወር አድርጎታል።

 በእግርግጥ ለአንድ አስርተ ዓመት የባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቡ ሲገለፅ የቆየው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም በፈጣን አዳጊነቱ የሚገለፅ ቢሆንም ይህ የዓመታት የእድገት ድምር ሀገሪቱ ለዘመናት ህልውናዋን ከመሰረተችበት ግብርና በመውጣት የመዋቅር ሽግግር ማድረግ አለመቻሉ አጠያያቂ አድርጎታል።

 ይህ ብቻ ሳይሆን ግብርናው ዛሬም ድረስ በኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴና የአመራረት ስርዓት ውስጥ መገኘቱ፤ ብሎም በአንድና በሁለት የዝናብ ወቅት እጥረት ድርቅ ሲከሰት በሚሊዮን የሚቆጠር አርሶና አርብቶ አደር እጁን ለምፅዋት መዘርጋቱ የኢኮኖሚውን እድገት አስተማማኝነት ፈተና ውስጥ የከተተው  ሆኗል። የዓለም ባንክ ባቀረበው በዚሁ የግምገማ ሪፖርቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና መፍትሔዎችን በስፋት ዳሷል። በዋና ፈተናነት ከዳሰሳቸው ችግሮች መካከል አንደኛው የኤክስፖርት ገቢ እየወረደ መሄድ ነው። ባንኩ በዚሁ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ስለሚታዩት ቀጣይ ተስፋዎችም የራሱ ዳሰሳ አድርጓል።

 

የኤክስፖርት መውረድ

የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ገቢ ማሽቆልቆል ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ኤክሰፖርቱ እየቀነሰ ባለበት ሁኔታ የኢምፖርት መጠኑ እየጨመረ በመሄዱ የንግድ ሚዛኑ ልዩነቱ በከፍተኛ ደረጃ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱ ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት ተደርጎ በዓለም ባንክ የግምገማ  ሪፖርት የቀረበውም ይሄው የኤክስፖርት ገቢ እየወረደ መሄድ ነው።

የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ምርቶች በዋጋ ተወዳዳሪ አለመሆን፣በቂ ምርትን ይዞ ወደ አለም አቀፉ ገበያ አለመግባትና እሴት የተጨመሩ ምርቶችን ይዞ ገበያውን መቀላቀል አለመቻል በመሰረታዊነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን የኤክስፖርት ምርት ስብጥሩም ውስንነትም ሌላኛው የኤክስፖርቱ ዘርፍ ችግር ነው።የኤክስፖርት ምርት መዳረሻ ሀገራትንም በተገቢው መንገድ እያሰፉ መሄድ አለመቻለም ሌላኛው ተፈላጊው ውጤት ያልተመዘገበበት የዘርፉ ፈተና ነው።

 

የብር  ምንዛሬን ማውረድ እንደመፍትሄ

የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ገቢ በማሳደጉ ረገድ አለም ባንክ ለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከሚሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች መካካል አንደኛው ሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘቧን ዋጋ ዝቅ ማድረግ ያለባት መሆኑን ነው። ባንኩ የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር ዋጋ ከሌሎች አለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች አንፃር እንዲወርድ መደረጉ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች የዋጋ ተወዳዳሪነታቸው ከፍ እንዲል በማድረግ የኤክስፖርት ገቢዋን የሚያሳድገው መሆኑን ይገልፃል።

 ከሰሞኑ ይህንኑ የአለም ባንክ ምክረ ሀሳብ አስመልክቶ በዘገባው ያሰራጨው ብሉምበርግ ድረገፅ የብርን የመግዛት አቅም በ10 በመቶ እንዲቀንስ ቢደረግ የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ በ5 በመቶ የሚጨምርበት ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን የአለም ባንክን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ አመልክቷል።

 ይህም አሁን የተመዘገበውን 8 በመቶ አጠቃላይ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ወደ አስር በመቶ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ይሄው የብሉምበርግ ዘገባ ያመለክታል። የአለም ባንክ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በሰጠው ምክረ ሀሳብና በፈጠረውም ተፅዕኖ እ.ኤ.አ በ2010 የብር ምንዛሬ መጠን ከዶላር አንፃር በ17 በመቶ እንዲወርድ የተደረገ መሆኑ ይታወሳል። ባንኩ ከዚያ በኋላ የብር ምንዛሪ መጠን እየወረደ መሄድ ሲገባው ይህ እርምጃ ለተከታታይ ዓመታት ሊወሰድ ባለመቻሉ በኢኮኖሚው ላይ አለሉታዊ ተፅዕኖን ያሳደረ መሆኑን ይገልፃል።

 

 በእርግጥ የአንድ ሀገር የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ እንዲወርድ ሲደረግ የዚያን ሀገር የወጪ ምርትን የዋጋ ተወዳዳሪነት ከፍ እንደሚያደርገው ይታወቃል። ሆኖም በዚያው መጠን የሚያስከትላቸውም አሉታዊ የኢኮኖሚ ውጤቶችም እንዳሉም አይዘነጋም። ከአንድ ሀገር መገበያያ ገንዘብ  እንዲወርድ ከማደረግ ጋር በተያያዘ  ይከሰታሉ ተብለው ከሚጠቀሱት አሉታዊ ውጤቶቹ መካከለረም ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት የሚፈጠር መሆኑ ነው።

 

 የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይፋ ሲሆን በ2007 መጨረሻ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ገቢ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ነበር። ሆኖም የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተጠናቆ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ አጋማሹ እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ባለፈው በጀት ዓመት የነበረው የሀገሪቱ ኤክስፖርት አፈፃፀም ከ 3 ቢሊዮን ብር በታች መሆኑን የሚያሳይ ነው። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከአመት አመት እያሽቆለቆለና ከእቅዱም በእጅጉ እየራቀ ባለበት ሁኔታ የሀገሪቱ  የገቢ ምርቶች (Import goods) ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው። ይህም  የንግድ ሚዛኑን እያሰፋው በመሄድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የኢምፖርት ገቢ መጠን በኤክስፖርት ከሚገኘው አንፃር ሲታይ ከአምስት እጥፍ በላይ ነው። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ወደ ሶስት ቢሊዮን የሚጠጋ ሲሆን የኢምፖርት ወጪው ደግሞ ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል። በዚህ ደረጃ ልዩነት የሚታይበት የሀገሪቱ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ልዩነት የብር ዋጋ በአንድ ጊዜ እንዲወርድ ቢደረግ፤ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን የሚችለው በየትኛው አቅጣጫ ነው? የሚለው ነው።

 

የኢትዮጵያ በኤክስፖርቱ ዘርፍ ውጤታማ መሆን ያልቻለችው በበርካታ ምክንያቶች መሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት እንደዚሁም በራሱ በአለም ባንክ ሲገለፅ ቆይቷል። የብር የምንዛሬ ለውጥ የሀገሪቱን የውጪ ምርቶች ርካሽ በማድረግ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገረው የአለም ባንክ፤ ከብር ምንዛሪ ለውጥ ባሻገር ባሉት ሌሎች የኤክስፖርት ገቢ ማሻሻያዎች ፍተሻ እንዲደረግ የሚሰጠው ምክረ ሀሳብ በአንፃራዊነት ላላ ያለ ነው።

ኢትዮጵያ በኤክስፖርቱ የንግድ ዘርፍ ስኬታማ መሆን ያልቻለችባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። እነዚህ ችግሮች በሚገባ ተፈትሸው ወደ ውጤት እንዲሸጋገሩ ባልተደረገበት ሁኔታ የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ በሚችለው የብር የምንዛሬ ለውጥ ላይ ለምን ትኩረት ማድረግ እንደተፈለገ ግልፅ አይደለም።

 

ኢትዮጵያ በቂና ብዙ ስብጥር ያለው ምርትን ለውጭ ማቅረብ ካልቻሉ በርካታ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት።  ለዚህ ችግር ወሳኙ መፍትሄ ምርታማነት ከፍ ማድረግ መሆኑን በመንግስት በተለይም በንግድ ሚኒስቴር በኩል በተደጋጋሚ ሲገለፅ የቆየ እውነታ ነው።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርቱ ዘርፍ ለአለም አቀፉ ገበያ የወጪ ምርቶችን በተገቢው የጥራት ደረጃ የማቅረብ ጉዳይም ሌላኛው ለዓመታት ያልተፈታ መሰረታዊ ኢኮኖሚው ችግር አለበት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የኢትዮጵያ የወጪ  ምርቶች በተቀባይ ሀገራት እገዳ ሲጣልባቸው ቆይቷል። ከጥራት ችግር ጋር በተያያዘ በመካከለኛው ምስራቅ የኢትዮጵያ ስጋ በተደጋጋሚ እገዳ ሲጣልበት መቆየቱ አንዱ የሀገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶች የጥራት ጉድለት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ከጥራት መጓደል ጋር በተያያዘ በቡና ምርት ላይ ሳይቀር በጃፓን ገበያ እገዳ ተጥሎ እንደነበርም የሚታወስ ነው።

 

 ዛሬ በዱባይ፣ በኳታር በሳኡዲ አረቢያ በከፍተኛ ደረጃና ጥራት በስፋት ስጋ በማቅረብ ላይ ያሉት ከመካከለኛው ምስራቅ በብዙ ማይልስ ርቀት ላይ የሚገኙት እንደ ብራዚል ያሉት የላቲን አሜሪካ ሀገራት ናቸው። ኢትዮጵያ በአንፃሩ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቅርብ እርቀት ላይ የምትገኝ ብትሆንም በሀገራቱ ያላት የኤክስፖርት አቅርቦትና ተወዳዳሪነት ግን እዚ ግባ የሚባል አይደለም። እነዚህ ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች ችግሮች ባልተፈቱበት ሁኔታ የብርን የምንዛሪ ዋጋ በማውረድ የሀገሪቱን የኤክስፖርት ምርቶች የዋጋ ተወዳዳሪነት ከፍ የማድረጉ ውጤታማነት አጠያያቂ ያደርገዋል። 

 

በግብርና ምርት ላይ የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ምርት፤ አለም አቀፉ ገበያ ውስጥ ገብቶ በዋጋ ተወዳድሮ እድሉን መወሰን ከመቻሉ በፊት የበርካታ ሀገራትን የጥራት ደረጃ ማለፉ ራሱ ሌላው ፈተና ነው። አንድ ሀገር ሁሉንም የሚጠበቁበትን የኤክስፖርት መመዘኛዎች ሁሉ አልፎ በዋጋ ረገድ በተጨማሪ ተወዳዳሪነት መጠቀም ሲፈልግ በመገበያያ ገንዘቡ ላይ የምንዛሪ ለውጥ ቢያደርግ ብዙም ችግር የሚኖረው አይሆንም። ሆኖም ሌሎች ኤክስፖርቱን ያዳከሙ ችግሮች ተፈትሸው መፍትሄ ባልተሰጠበት ሁኔታ ግን የብርን ምንዛሬ በአዋጅ ወይም በመመሪያ በአንድ ጊዜ እንዲወርድ ማድረጉ በተለይ የውጪ ምርት ሸማች ለሆነችው ኢትዮጵያ ህዝቧ የሚያስከትለው የዋጋ ንረት በግሽበት ደረጃ የሚገለፅ ይሆናል። ባንኩ በተደጋጋሚ የብርን የምንዛሪ መጠን እንዲወርድ ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን፤ ይህ ምን ያህል በመንግሥት በኩል ተቀባይነት ኖሮት ሊተገበር እንደሚችል በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም ከነበሩት ልምዶች አንፃር ሲታይ ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ ምክረ ሃሳቡ የሚተገበር ይመስላል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለት ጊዜያት ያህል የብርን የምንዛሪ መጠን በመመሪያ እንዲወርድ ያደረገው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም ባንክ ምክረ ሃሳብ መሆኑ የሚታወስ ነው።  

 

ምን ተስፋዎች አሉ?

የአለም ባንክ በዚህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትንታኔው በቀጣይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሰረት መሆኑን የገለፀው እስከዛሬ ሲካሄድ የነበረውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ነው። እንደ ባንኩ ገለፃ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ስታካሂዳቸው የነበሩት በርካታ መሰረተ ልማቶች ፍሬ የሚሰጡበት ጊዜ ደርሷል። ከእነዚህም ወሳኝ መሰረተ ልማቶች መከካልም የባቡርን እና የኤሌክትሪክ ኃይል በዋነኝነት ለይቶ አስቀምጧል።

 

የባቡር መሰረተ ልማትን በተመለከተ በተለይ የኢትዮ-ጂቡቲ አዲሱ የባቡር መስመር ግንባታ እስከ ዛሬ በጭነት ተሽከርካሪዎች ሲጓጓዝ የነበረውን የወጪ ገቢ ሸቀጥ በመጠን ብሎም በቅልጥፍና በማሻሻል የንግዱ እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲሆን በማድረግ የኢኮኖሚውን እድገት የሚያሳልጠው መሆኑን ባንኩ ያመለክታል።

 ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት በስፋት መዋዕለ ነዋዩዋን እያፈሰሰችበት ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል መሰረተ ግንባታም ወደ ኤክስፖርቱ ዘርፍ በመግባት ኢኮኖሚውን በውጭ ምንዛሪ የሚደግፍ መሆኑን ባንኩ ጨምሮ ገልጿል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
540 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us