ካስትል ወይን አዲስ በካርቶን የታሸገ ወይን ምርት ለገበያ ቀረበ

Wednesday, 21 December 2016 14:32

 

ካስትል ወይን ጠጅ ባለሁለት ነጥብ አምስት ሊትር የካርቶን እሽግ የወይን ጠጅ ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ። የፋብሪካው የማርኬቲንግና ሽያጭ ኃላፊዋ ወ/ት አለምፀሐይ በቀለ ባሳለፍነው ሐሙስ (ታህሳስ 6 ቀን 2009 ዓ.ም) በራማዳ ሆቴል ምርቱን ባስተዋወቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ “እነዚህ የካርቶን የወይን ምርቶች ከውጪ ሀገር ይገቡ  ነበር፡፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ለምርቱ አስፈላጊ የሆነውን አዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በማምረት ለገበያ አቅርበናል” ብለዋል።

ይህ አዲሱ የካርቶን የወይን ጠጅ እስከሚያልቅ ድረስ ምንም አይነት አየር የማስገባትም ሆነ የመበላሸት ስጋት አይኖርበትም የተባለ ሲሆን፤ ለጊዜው መጠናቸው 2 ነጥብ አምስት ነው ያሉት ኃላፊዋ በቀጣይ ግን እንደሚጨምር ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ ያለው የሮዝና የነጭ ወይን ጠጅ ቀለም ያለው እንደሆነም በመግለጫወ ተብራርቷል።

ካስትል ወይን ጠጅ ፋብሪካ በሚያቀርባቸው የአኬሲያ እና በሪፍት ቫሉ የወይን ምርቶቹ የውጪ ምንዛሬን ከማዳኑም ባሻገር፤ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ገበያዎችን የመሳብ አቅም ላይ መድረሱም ተወርቷል። የምርቱን ጥራትና ደረጃ ከመጠበቅ ባሻገርም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የወይን ጠጅ መስተንግዶ ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ወ/ት ዓለምፀሐይ፤ በሆቴል መስተንግዶ ለማሰልጠን ባለሙያዎች አጋዥ ይሆናል የተባለትን የመስተንግዶ ስርዓት በዲቪዲ ማሰራጨት መጀመራቸውንም ተናግረዋል። ይህም ለቱሪዝሙ እንደአንድ መስህብ የሚፈጥር ሲሆን፤ የወይኑን አይነት ማወቅ በራሱ እንግዶችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ያግዛል ተብሏል። ይህንንም ስልጠና ከሬስቶራንቶችና ከሆቴሎች በተጨማሪ ለመስተንግዶ ማሰልጠኛዎች ጋር በመቀራረብ መስራት ስለመጀመራቸው ይፋ አድርገዋል።

ካስትል ወይን ጠጅ ፋብሪካ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም በ520 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት መቋቋሙ የተገለፀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 1ነጥብ 4 ሚሊዮን ጠርሙስ አጠቃላይ የዓመታዊ ምርቱ አቅም ሆኗል። በሀገር አቀፍ ደረጃ 11 በመቶ የገበያ ሽፋን የያዘ ሲሆን፤ 28 ደረጃቸውን የጠበቁና በቴክኖሎጂ የታገዙ የመጥመቂያ ማሽኖች አሉት።

ካስትል ወይን ጠጅ ለ11 አገራት ምርቱን የሚያቀርብ ሲሆን፤ በዝዋይ አካባቢ በ162 ሄክታር ላይ ስራውን የጀመረ ቢሆንም አሁን ላይ የ82 ሄክታር የማስፋፊያ ስራ በመስራት ላይ መሆኑም ተገልጿል። በአጠቃላይ ለ850 ሰዎች የስራ ዕድል ስለመፍጠሩ ሰምተናል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
507 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us