ወደ ኤክስፖርት እየተንደረደረ ያለው በአፍሪካ ግዙፉ ቄራ

Wednesday, 21 December 2016 14:34

 

ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት በአፍሪካ አንደኛ፤ በዓለም አስረኛ ደረጃን የያዘች መሆኗ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ መረጃ ነው። ሀገሪቱ ያላት እምቅ የእንስሳት ሀብት ከፍተኛ ቢሆንም ሀብቱን በመጠቀሙ ረገድ ያለችበት ደረጃ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

 እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ስጋ ኤክስፖርት መዳረሻ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ናቸው። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ኳታር፣የተባበሩት አረብ ኤሜሬትና ሳዑዲ አረቢያ ይገኙበታል። የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ዋነኛ የስጋ ምርት አቅርቦቶቻቸውን የሚያገኙት እንደ ብራዚልና ቺሊ ካሉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ነው።

 

 እነዚህ ሀገራት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በብዙ ርቀት የሚገኙ ሲሆን  ኢትዮጵያ በአንፃሩ ከእነዚህ ሀገራት በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ  ሀገር ናት። ሆኖም በሥጋ ገበያው ከእነዚህ ሀገራት ያላትን ቅርበት ተጠቅማ በመካከለኛው ምስራቅ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አልቻለችም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ሊጠቀሱ የሚችሉ በዘርፉ የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉ። ከችግሮቹ መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት በገበያው ፍላጎት ደረጃ በስፋትና በጥራት የሥጋ ምርትን ማቅረብ አለመቻል ነው። ሆኖም ከሰሞኑ ከሞጆ እስከ አዳሜ ቱሉ በነበረን የስራ ጉብኝት በዚሁ መስመር የሚገኙትንና ወደ ሥጋው ኤክስፖርት ዘርፍ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ የኤክስፖርት ቄራዎችን ተመልክተናል። አንዳንዶቹም ወደ ስራ የገቡ ናቸው። የኢትዮጵያን የሥጋ ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ካሉት ኩባንያዎች መካከል ግዙፍ ሆኖ ያገኘነው አላና ፍሪጎሪፊኮ ቦራንፉድስ የኤክስፖርት ቄራ ፕሮጀክት ነው። ኩባንያው መሰረቱ ህንድ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እየገነባ ያለው በአፍሪካ ግዙፉን የኤክስፖርት ቄራ መሆኑን ከኃላፊዎቹ ገለፃ መረዳት ችለናል። ይህ በአዳሜ ቱሉ የሚገኘው ግዙፍ ኤክስፖርት ቄራ የ75 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ሲሆን ኩባንያው ይህንን የኢንቨስትመንት ስራ ሲያከናውን ምንም አይነት ገንዘብ ከሀገር ውስጥ ባንክ ያልወሰደ መሆኑ ተመልክቷል። ኩባንያው ህንድ ባለው ግዙፍ ቄራው ወደ 75 ሀገራት የሚጠጉ የምርት መዳረሻ ሀገራት አሉት። እ.ኤ.አ በ2013 መሬት የወሰደው ይህ ኩባንያ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ሥራ የሚገባው ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው።

 

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2016 ባሉት አስር ወራት 80 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የስጋ ምርትን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መላኳን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል እሴት  የተጨመረበት የሥጋ ምርት ያለው ድርሻ ከ 2 በመቶ ብዙም የራቀ አይደለም።  አላና የሥጋ ማቀነባበሪያ ግን ይህንን የሥጋ ኤክስፖርት ገቢ ከመሰረቱ የሚቀይር መሆኑን የኤክስፖርት ገቢ እቅዱ ያመለክታል። ሥጋን ጨምሮ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የኤክስፖርት መጠን ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር መብለጥ አልቻለም። ሆኖም አላና የአክስፖርት ቄራ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ኤክስፖርቱ ዘርፍ ገቢ ሙሉ በሙሉ የሚቀየር መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኩባንያው ኢንቨስትመንት የአዳሜ ቱሉ ቄራ ብቻ አይደለም። በሞጆ ከተማም አላና አሸከር የተባለ ሌላ የኤክስፖርት ቄራ እህት ኩባንያ አለው። ይህ ኩባንያ ቀደም ሲል በአንድ ቱርካዊ ባለሀብት የተቋቋመ ሲሆን የከብት አንጀትን ከተለያዩ ቄራዎች ሰብስቦ እያቀነባበረ ወደ ውጭ ይልክ ነበር። ሆኖም ሌላ የቻይና ኩባንያ በተመሳሳይ ስራ በመግባቱ ኩባንያው መወዳደር ባለመቻሉ ከገበያ መውጣት ግድ ሆኖበታል። በሰተመጨረሻ አላና ኤክስፖርት ቄራ ይሄንን የቱርክ ኩባንያ በመግዛት የራሱን ማስፋፊያ ሰርቶ ዘመናዊ ኤክስፖርተር አድርጎታል።

 

ይህ ቄራ በአሁኑ ሰዓት እርድ እያከናወነ በመላክ ላይ ሲሆን ተረፈ ምርቶቹን አቀነባብሮ ጥቅም ላይ የሚያውልበትን የማስፋፊያ ሥራንም በመስራት ላይ ይገኛል።   ግዙፉ የአዳሜ ቱሉ አላና የኤክስፖርት ቄራ ደግሞ በርካታ ሀገራትን የምርት መዳረሻው ለማድረግ አስቀድሞ በመስራት ላይ ነው። ኩባንያው ለረዥም ጊዜ በዘርፉ ያሳለፈ በመሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቀባይ ደንበኞች ያሉት በመሆኑም እምብዛም ደንበኞችን የማፈላለጉ ሥራን ማከናወን አይጠበቅበትም። እንደ ኃላፊው ህንድ ከሚገኘው የስጋ ማቀነባበሪያው ቄራው ለሰባ ሀገራት የሥጋ ምርትን የሚልክ መሆኑን ሚስተር ዋይን ገልፀውልናል። በአሁኑ ሰዓትም የኢትዮጵያውን ምርት ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመላክ ለደንበኞቹ በማስተዋወቅ ላይ ነው። ሞጆ በሚገኘው ቄራው የሚቀነባበረውን የሥጋ ምርት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬት፣ ባህሬንና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በመላክ ላይ ሲሆን  ከዚህ ባለፈም ወደ ቻይና፣ቬትናምና መሰል ሀገራት ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኃላፊዎቹ ገልፀውልናል።    

 

 ኩባንያው ያለምንም ችግር ስኬታማ እንደሚሆን ከወዲሁ እርግጠኛ ነው። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች በኃላፊዎቹ በኩል ይጠቀሳሉ። አንደኛው ምክንያት ኩባንያው በዘርፉ የ156 ዓመታት ልምድን እንደዚሁም በሥጋ ኤክስፖርቱ ደግሞ 46 ዓመታትን ያሳለፈ መሆኑ ነው። ይህም ኩባንያው አለም አቀፉን የሥጋ ገበያ በሚገባ እንዲረዳና በርካታ ተቀባይ ደንበኞችንም እንዲያፈራ አድርጎታል። ይህም በመሆኑ በአላና የኤክስፖርት ቄራ በኩል የሚታይ የገበያ መዳረሻ ችግር አይኖርም። ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ የተዘረጋ ሰፊ የገበያ መዳረሻ አድማስ አለው። ይህ ብቻ ሳይሆን የኩባንያው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ቄራ ዓለም አቀፉን ደረጃ አሟልቶ በቀላሉ የኤክስፖርት ገበያውን እንዲቀላቀል የሚያስችለው በቂ አቅም ያለው መሆኑን የቄራው የግንባታ ሂደት በሚገባ ያሳያል። ኩባንያው በኢትዮጵያ የገነባው የኤክስፖርት ቄራ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ መሆኑን ከኃላፊዎቹ ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

በቄራው ባደረግነው ጉብኝት ቄራው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በሚያሟላ መልኩ እጅግ ዘመናዊ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን በዘርፉ ባለሙያዎችም ገለፃ ተደርጎልናል። እርዱ ከተከናወነ በኋላ ሥጋው በተለያዩ የቅዝቃዜ ደረጃ በባለሙያዎች እንዲቀመጥ ይደረጋል። ባለው የቅዝቃዜ ደረጃም ሥጋው እስከ ሁለት ዓመት ሳይበላሽ መቆየት ይችላል። በቄራው በባለሙያዎቹ አጠራር “ብላስት ፍሪዘር ሩምስ” የሚባሉ ስምንት ማቀዝቀዣ ክፍሎች አሉ። እነዚህ ክፍሎች ከዜሮ በታች አርባ ዲግሪ ሴንቲግሬድ የቅዝቃዜ መጠን ያላቸው ናቸው።

 

 ካለው ከፍተኛ የቅዝቃዜ መጠን ጋር በተያያዘ ወደ እነዚህ ክፍሎች ሰው መግባት የማይችል መሆኑ ተነግሮናል። ሥጋው ወደዚህ ክፍል የሚላከው በማሽን በሚታዘዝ የብረት ሀዲድ (Conveyer) ነው። ከአንድ ማዕከል የኮምፒዩተር ቁጥጥርም ይደረግበታል። ወደ እዚህ ክፍል እንዲገባ የሚደረገው ሥጋ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ስለሚያገኘው ወዲያውኑ በድንጋይ ደረጃ የሚገለፅ ጠጣር ሥጋ ይሆናል። በዚህ ኤክስፖርት ቄራ ውስጥ ይህንን ሥራ የሚያከናውኑ በአጠቃላይ ስምንት ክፍሎች አሉ። ከዜሮ በታች አርባ ዲግሪ የቅዝቃዜ መጠን ለአስር ሰዓታት ያህል እንዲቆይ ይደረጋል። ከዚያም ወደ ሌላ ክፍል በሀዲድ ተሸጋግሮ በመጠን እየተለየ የማሸግ (Packaging) ሥራው ይከናወናል።

 

እንስሳቱ በቁም የህክምና ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ እና ከታረዱም በኋላ ሆድ እቃቸውን ጨምሮ ጉበታቸውና እያንዳንዱ የሰውነት ክፍላቸው ምርመራ ይደረግበታል። ሁሉም ነገር ያለቀለትና ማቀዝቀዣ ማሽን በተገጠመለት ወደ ኤክስፖርት የሚጓጓዘው የሥጋ ምርት ከፋብሪካው ማቀዝቀዣ ተነስቶ እንዲጫን የሚደረገው ለዚሁ ስራ በተዘጋጀ መጫኛ ተሽከርካሪ አማካኝነት ነው። ይህ የሥጋ መጫኛ ተሽከርካሪ የቀዝቃዛ ክፍሉን ብክለት ለመከላከል ሲባል ለኃይል ምንጭነት ነዳጅን ሳይሆን የባትሪ ኃይልን የሚጠቀም ነው።

   

ምንም የሚጣልና የሚወገድ ተረፈ ምርት የለም

በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያሉ በርካታ ቄራዎች ሥጋን ወደ ውጪ የሚልኩት አርደውና ገፈው የውስጥ ሆድቃን በማስወገድ ብቻ ነው። ከዚሁም ጋር በተያያዘ ሥጋው ብዙም እሴት ሳይጨመርበት ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ከእርድ በኋላ በፈሳሽና በጠጣርነት የሚወገደው ተረፈ ምርት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ  ነው።

 

ከሥጋው እና ከቆዳው ውጪ ቀሪ የሚሆነው የአጥንት፣ ደም፣ ተረፈ ሥጋና የመሳሰለው ውጤት የሚወገደው ተጨማሪ ቦታ ከከተማ ማዘጋጃ ቤቶች እየተጠየቀ ነው። ይህም በአካባቢ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ለባለሀብቶቹም ተጨማሪ ወጪ ነው። አላና ኤክስፖርት ቄራ ግን ይህንን የቀደመ አሰራር ሙሉ በሙሉ በመቀየር ሁሉም ከእርድ የሚገኙ ተረፈ ምርቶች ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ሁኔታ እየሰራ ነው። በእርድ ወቅት የተወገዱ ተረፈ ምርቶች አንድ ላይ ተጠራቅመው በከፍተኛ እምቅ እንፋሎት(Steam) ማጠራቀሚያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል። በዚህ ወቅት የማይፈለገው የስብ ክፍል ከተረፈ ሥጋውና ከአጥንቱ ይለያል። ስቡ ከተለየ በኋላ ለሁለት አይነት አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል።

 

የመጀመሪያው በዚያው በፋብሪካው ውስጥ ተቃጥሎ መልሶ ለኃይል ምንጭነት እንዲያገለግል የሚደረግበት አሰራር ነው። ለሌሎች ሳሙና አምራች ፋብሪካዎች በግብዓትነት እንዲያገለግል ዝግጁ ማድረግ ነው። የስቡ ጉዳይ በዚህ መልኩ ይጠናቀቃል። ሌላኛው ተረፈ ምርት አጥንቱ ሲሆን አጥንቱ ሙሉ በሙሉ ከሥጋው እንዲለይ ከተደረገ በኋላ እንዲፈጭ ተደርጎ ወደ ዶሮ መኖነት እንዲቀየር ይደረጋል።

 

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ዶሮ እርባታ ፈታኝ ከሆኑቱ ጉዳዮች ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚይዘው የመኖ አቅርቦት ነው። ባለፉት ዓመታት የመኖ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየናረ መሄድ የዶሮ ዋጋ እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል። ይህም በሌሎች ሀገራት ካለው የዶሮ ዋጋ በላይ የኢትዮጵያ የዶሮ ዋጋ ወድ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም በቀጥታ ከመኖ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ነው። ችግሩን በመፍታቱ ረገድ የአላና  ኤክስፖርት ቄራ  በዘመናዊ መልክ የሚቀነባበረው የመኖ አቅርቦት በቀጣይ የዶሮውን መኖ እጥረት ሙሉ በሙሉ የሚፈታው መሆኑን  ኃላፊዎቹ ይናገራሉ። ከተደረገልን ገለፃ መረዳት እንደቻልነው በኢትዮጵያ የአንድ ኪሎ የዶሮ መኖ ዋጋ አራት ዶላር አካባቢ ሲሆን በፓኪስታን፣ በባንግላዲሽና በመሰል ሀገራት ተመሳሳይ መጠን ያለው መኖ ከ2 ዶላር በታች ነው። በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡን የአላና እህት ኩባንያ የሆነው አላና አክሸከር ኤክስፖርት ቄራ ተብሎ የሚጠራው ኩባንያ የኦፕሬሽን ዳይሬከተር የሆኑት ሚሰተር ዋይን ጋስኮ የቄራ ኢንዱስትሪ ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ ስራ መሆኑን ገልፀውልናል።

 

በተጨማሪ  ሌላኛው የቄራው ተረፈ ምርት ደም ሲሆን ደሙም ከምንም አይነት ሌላ ፈሳሽ ጋር ሳይቀላቀል ራሱን ችሎ እንዲቀነባበር ይደረጋል። በዚህ የማቀነባበር ስራም ደርቆ እንዲታሸግ ይደረጋል። ከዚያም ለአሣ ቀለብነት እንዲውል ይደረጋል። እንደ ሚስተር ዋይን ገለፃ ከተቀነባበረው የደሙ ተረፈ ምርት የሚገኘው ገቢ የኩባንያው ገቢ ሳይሆን በየጊዜው የሚገኘው ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ሥራ የሚውል ነው። አላና ኤክስፖርት ቄራ የራሱን ተረፈ ምርት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቄራዎች የሚያስወግዱትንም ተረፈ ምርት ሙሉ በሙሉ በመሰብሰብ አቀነባብሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ እቅድ ያለው መሆኑም ተመልክቷል።

 

የቆዳው ዘርፍ አስተማማኝ ግብዓት

የኢትዮጵያ የቆዳው ኢንዱስትሪ ዘርፍ በብዙ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ ነው። ከችግሮቹ መካከል አንደኛው የኢንዱስትሪው ዋነኛ ግብዓት የሆነው ቆዳ በጥራትና በስፋት ለፋብሪካዎች መቅረብ አለመቻል። በሀገሪቱ ካሉት ሀይማኖታዊ ባላት ውጪ በሀገሪቱ ብዙም የእርድ ልምዱ የለም። ይህም በመሆኑ በሀገሪቱ ዘመናዊ ቄራዎች ካለመስፋፋታቸው ጋር በተያያዘ ቆዳ ፋብሪካዎች ቀጣይነት ያለውና ጥራት ያለው ቆዳን በቋሚነት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ ብዙዎቹ ቆዳ ፋብሪካዎች የሚሰሩት ከአቅማቸው በታች ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት ባለመቻሉ  በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በቆዳው ኤክስፖርት ዘርፍ የተያዘው እቅድ ስኬትን ያገኘው ከአራት እጥፍ ባነሰ ሁኔታ ነበር።

 

እንደ ሚስተር ዋይን ገለፃ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቄራዎች መስፋፋታቸው በቆዳው ዘርፍ ያለውን የአቅርቦት ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይፈታዋል። በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የቆዳ ፋብሪካዎች ከአላና ኤክስፖርት ቄራ ጋር አብሮ ለመሥራት ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ኃላፈው ገልፀውልናል።

 

የዘርፉ ፈተናዎች

የቄራው ዘርፍ ኢንዱስትሪውንና ግብርናውን ከማስተሳሰር ባለፈ አግሮ ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲተሳሰሩም የማድረግ አቅም አለው። ሀገሪቱ ካላት ሰፊ የእንስሳት ሀብትና በዙሪያዋ ካለው ሰፊ  እምቅ የገበያ  ፍላጎት አንፃር ዘመናዊ የቄራ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

 

የኢትዮጵያ 60 በመቶ የቆዳ ስፋት በአርብቶ አደሮች የተያዘ ነው። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ የአፋር ክልል፣የአሮሚያ ሰፊው ክፍልና የደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞንን ጨምሮ ሰፊው አካባቢ በአርብቶ አደርነት የሚታወቅ ነው። ሆኖም አርብቶ አደሩ በሀብትነት ተጠቅሞባቸው ህይወቱን ሲለውጥ አልታየም። እንደውም ድርቅ በተደጋጋሚ ሲከሰት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደ አጣ የነጣ ድህነት የሚወርድበት ሁኔታ አለ። በቂ ውሃና ምግብ በሀገር ውስጥ በሚገኝባቸው ወራት ከብቶቹን ወደ ኬኒያና ሶማሊያ ከማሻገር ባለፈ እዚያው ሸጦ የሚመለስበት ሁኔታም አለ።

 

በሶማሊያ የመሸጉ የአረብ ሀገራት የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ከሶማሌያዊያን ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የቁም ከብት እየተረከቡ ባህር የሚያሻግሩበት ሁኔታም አለ። እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አርብቶ አደሩንም እንደ ባለቤት አልጠቀሙትም። መሰል ቄራዎች መስፋፋታቸው ግን አርብቶ አደሩ አስተማማኝ የሀገር ውስጥ ገበያን እንዲፈጠርለት ከማድረግ ባሻገር ለኢንዱስትሪው ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት ወደ ዘመናዊ እርባታ ስራ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ይሆናል።

 

አላና ኤክስፖርት ቄራ ወደ ሙሉ የማምረት ሥራው ሲገባ በቀን ከ2 ሺህ አምስት መቶ እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ የዳልጋ ከብቶችን እንደዚሁም በቀን ከ አምስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ፍየልና በግን አርዶ በማቀነባበር ወደ ውጪ ይልካል። ሞጆ በሚገኘው እህት ኩባንያው አማካኝነት ደግሞ በዓመት አንድሺህ ሁለት መቶ ቶን የሚሆን የበግ፣ የፍየልና የዳልጋ ከብት ሥጋን ለመላክ እየሰራ ነው።

 

ይህም ከወራት በኋላ እውን የሚሆን ነው። ሌሎች አዳዲስ የኤክስፖርት ቄራዎችም ወደ ሥራ ለመግባት በመንደርደር መሆናቸውን ከነበረን ጉብኝት መረዳት ችለናል። የነባር ኤክስፖርት ቄራዎችም እንቅስቃሴ ሳይረሳ ማለት ነው። በዚህ ደረጃ ቄራዎች በቀን ከፍተኛ እርድ እያከናወኑ ወደ ውጭ ሥጋን በሚልኩበት ሁኔታ ከሀገሪቱ የእንስሳት ሀብት አኳያ እርባታውን ዘመናዊ ዘዴን እንዲከተል ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር በሀገር ውስጥ አቅርቦት ብሎም በራሳቸው በቄራዎቹ ላይ እጥረትን መፍጠሩ አይቀርም። ይህ አንዱ ፈተና ነው።

 

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኢንቨስትመንት ቴክኖሎጂ ድጋፍ ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ከሊፋ ሁሴን ሥጋቱ መኖሩን ገልፀው፤ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ እቅዶች መኖራቸውን ገልፀውልናል። በአንድ መልኩ ቄራዎቹ ራሳቸው የእርባታ ጣቢያዎችን እንዲያቋቁሙ ማድረግ ሲሆን ከዚህ ውጪም በአርብቶ አደር አካባቢ ያሉት እንስሳት አርቢና አቅራቢ የህብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከር ነው።

 

ከዚህ ውጪም በባለሀብቶቹ የተነሳው ጥያቄ የኢንቨስትመንት መሬት የሊዝ ዋጋ ውድ መሆን ነው። አቶ ከሊፋ ለዚህ በሰጡን ምላሽ ባለሀብቶቹ ቄራዎቹን ከተማ ውስጥ ሳይሆን የእንስሳቱ ሀብት ወዳለበት የአርብቶ አደሩ ክልል ዘልቀው እንዲገቡ የተፈለገ በመሆኑ የከተማው የሊዝ ዋጋ ኢንቨስትመንቱን በልዩ ሁኔታ የሚያበረታታ አልሆነም። ሆኖም ባለሀብቶቹ የእንስሳቱ ሀብት ወዳለበት አካባቢ ዘልቀው በመግባት መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ከሆነ መሬት በርካሽ የሊዝ ዋጋ ያገኛሉ ተብሏል። ሌላኛው የባለሀብቶቹ ፈተና ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደዚሁም አዳዲስ የተገነቡ ቄራዎች ደግሞ በተፈለገው ጊዜ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማግኘት አለመቻል ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
692 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us