የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ውጥንቅጦች

Wednesday, 28 December 2016 13:53

 

በኢትዮጵያ ከዋና ዋናዎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንደኛው የኮንስትራክሽኑ ኢንዱስትሪ ነው። እንደ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ምርት እድገት ውስጥ የ 8 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻን ይዟል። በሰው ኃይል ደረጃም እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆን ሰውን ያቀፈ ሲሆን፤ እንደ መረጃው ከሆነ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሰራተኛ የሰው ኃይል ውስጥ 12 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ አቅፏል።

 ኢንዱስትሪው በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ  በእጥፍ ያደገ መሆኑ ቢመለከትም ዘርፉ አሁንም ድረስ በበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ከሰሞኑ በአዲስ አበባ  የተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተካሄደው ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን የንቅናቄ ኮንፍረንስ ያመለክታል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁን እያሳየ ካለው እድገት አኳያ በበርካታ ችግሮች የታጠረ መሆኑን በብዙ መልኩ ተመልክቷል። ከእነዚህ ችግሮች መካከልም በዋነኝነት የተጠቀሱትን  እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

ያለ አማካሪ ግንባታቸው የሚከናወን ህንፃዎች ጉዳይ

የሀገር ውስጡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚታዩበት ችግሮች አንዱ ተደርጎ በተደጋጋሚ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች የሚታየው የሥነ ምግባር ጉድለትና አቅማቸውን የማይገልፅ የብቃት ማረጋገጫ ጉዳይ ነው። እንደ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ መረጃ ከሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች የሚሰጣቸው የምስክር ወረቀት በብቃት ምዘና ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ የያዙትን ደረጃ የሚገልፅ አይደለም።

የሥራ ተቋራጮችን በተመለከተ አብዛሃኞቹ ከደረጃ 4 እስከ 10 ያሉት ዝቅተኛ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ፣ በዘመናዊ የአስተዳደርና ፋይናስ የማይመሩ፣ብዙም ልምድን ባላከበቱ ባለሙያዎች የሚመሩና የሚሰሩ መሆኑ ተመልክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በብዙ ሀገራት የሚሰራበት ልዩ የሥራ ተቋራጭ       (Special Contractors) አሰራር በሀገሪቱ እየዳበረ ካለመሄዱ ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ሁሉንም ስራ ጠቅልሎ የሚሰራው አንድ ሥራ ተቋራጭ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ይህም በአንድ መልኩ ግንባታውን በሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ ጫናን ከመፍጠር ባሻገር፤ “ልዩ የሥራ ተቋራጮች” በኢንዱስትሪው በብዛት እንዳይፈጠሩ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።

ከዚህ ውጪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሌላኛው ፈተና ተደርጎ የተጠቀሰው የአማካሪ ድርጅቶችና ባለሙያዎች እጥረት ጉዳይ ነው። የዚህን ዘርፍ የባለሙያዎች እጥረትና ችግሩን በተመለከተ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ማዕቀፍ በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል። “በአማካሪ ድርጅቶች የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች በርካታ ቢሆኑም በአካባቢ ስብጥርና ከፍተኛ ልምድን በሚጠይቁት ሥራዎች ዙሪያ እጥረት ይታያል። በቤቶች ልማት ፕሮግራም ላይ ለአብነት በሁሉም ክልል በአርክቴክቸራል፣ በስትራክቸራል፣ በኤሌክትሪካል እና በሳኒተሪ ዲዛይን እንደዚሁም በአፈር ምርመራና በግንባታ ሥራ ቁጥጥር ለማሳተፍ የአማካሪዎች እጥረት ተከስቷል።

 ይህም በበኩሉ የሥራ መጓተትን እና ሥራዎችም በሚፈለገው ጥራትና ወጪ መሰራታቸውን በየደረጃው ለማረጋገጥ እንቅፋት ሆኖ ይታያል። የምክር አገልግሎት ሽፋንን ስንመለከት ከመንግስት ግንባታ ውጪ ያሉ ግንባታዎችን የሚከታተል ምንም የቁጥጥር ስርዓት ባለመኖሩ የህንፃ ግንባታዎች ደረጃዎችን በማይመጥኑ ባለሙያዎች ወይም አማካሪዎች ወይም ያለ አማካሪ እንዲከናወኑ መደረጉ የተለመደ ክስተት ሆኗል።”

ወደ መሬት መውረድ ያልቻለው የህንፃ አዋጅ

በኢትዮጵያ የህንፃ ኢንዱስትሪውን የሚመራ አንድ የህግ ማዕቀፍ ያልነበረ ሲሆን ይህንን ህግ እውን በማድረግ የግንባታውን ሂደት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ህንፃ አዋጅ በ2001 እንዲወጣ ተደርጓል። አዋጁ የሰራተኛ ደህንነትን፣ ከግንባታ ጋር በተያያዘ መኖር ስለሚገባው የአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ፣ እንደዚሁም ከዲዛይን አውጪ ጀምሮ ግንባታን እስከሚያከናውነው አካላት ድረስ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የህግ ማዕቀፍ ነው። ህጉ ከዚህም በተጨማሪ  ግንባታን በተመለከተ መረጃ ማጣራትን፣ የዲዛይን ምርመራና የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥን እንደዚሁም የክትትል ቁጥጥርን ብሎም ህንፃው ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የመጠቀሚያ ፈቃድን መስጠትን ጭምር አካቶ የያዘ ነው።

  ሆኖም አዋጁ ከወጣ ስምንት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም  ህጉን ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረጉ ረገድ ግን እስከዛሬም ድረስ በርካታ ችግሮች ይታያሉ። በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሬጉላቶሪ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰይፉ ገብረ ሚካኤል አዋጁን ወደ መሬት ወርዶ እንዳይተገበር ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ለአዋጁ መሬት አለመውረድ ምክንያት ተደርገው ከተጠቀሱት መካከል አንደኛው ህጉን  ወደ ትግብራ ከመግባቱ በፊት አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች የማዘጋጀቱ ጉዳይ ጊዜ በመውሰዱ ነው።

እነዚህ አዋጁን ሊያስፈፅሙ የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ሲዘጋጁ  የቆዩ መሆኑን አቶ ሰይፉ ይገልፃሉ። ከዚህም በተጨማሪ  ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ ህጉን በማስፈፀሙ በኩል ሰፊ ኃላፊነትን የሰጠው ለህንፃ ሹም ፅህፈት ቤት ነው። እንደ አቶ ሰይፉ ገለፃ የዚህን ፅህፈት ቤት አደረጃጀት የመፍጠሩ ሂደትም ረዥም ጊዜ መውሰዱ አንዱ ለአዋጁ መተግበር መጓተት ምክንያት ነው። ሌላኛው አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆንባቸውን ከተሞች የመለየቱ ስራም ሌላው ጊዜ የወሰደ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር  ህጉ ሊተገበርባቸው የሚችሉ 248 ከተሞች ሲለዩ የቆዩ መሆኑ ታውቋል እነዚህም ከተሞች አሰር ሺህ እና  ከዚያ በላይ ነዋሪዎችን የያዙ ናቸው ተብሏል። በዚህም መሰረት መመሪያዎችና ደንቦች በየክልሉና ከተሞች እንዲሰራጩ በማድረግ ከተከናወነ በኋላ  እነዚህ ሁሉ ቅድመ ስራዎች ተሰርተው በ2004 መጨረሻ አካባቢ በ248 ከተሞች መሬት ወርዶ እንዲተገበር  ለማድረግ ጥረት የተደረገ መሆኑን አቶ ሰይፉ ይገልፃሉ።

 በዚህም ሂደት እስከ መጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ ድረስ ህጉን በ177 ከተሞች እንዲተገበር እንቅስቃሴ መደረጉ ተመልክቷል። ሆኖም  አዋጁ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በሙሉ በሙሉ ለመተግበር ያልተቻለ መሆኑን አቶ ሰይፉ ጨምረው ይገልፃሉ። በዚህ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ያመለከቱት ባለሙያው፤ ለዚህ ሰፊ ክፍተት መፈጠር ምክንያት የሆኑ በርካታ ማነቆዎች መኖራቸውን በመግለፅ። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም ታክለው ህጉ እንዳይተገበር እንቅፋት እንደሆኑ ገልፀዋል።

በዚህ በኩል ህጉ በቅድሚያ መንግስት በሚገነባቸው ህንፃዎች ላይ  ተፈፃሚ እንደሆነ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ጥረቱ ሳይሳካ የቀረ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። የህንፃ ሕጉን በመተግበሩ ረገድ ወጥነት የሌለ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው ግለሰብ ገንቢዎች በህጉ መሰረት ፈቃድ እያገኙ ግንባታቸውን እንዲያከናውኑ የሚደረገብት አሰራር የተጀመረ ቢሆንም የመንግስት ህንፃዎች ግን የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ የሚገነቡበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።

የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዳይ

በዚህ ኮንፍረንስ ከተነሱት ወሳኝ ሌሎች ጉዳዮች መካከል አንደኛው የሀገሪቱ ተቋራጭ ኩባንያዎች አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዳይ ነው። የየኩባንያዎቹ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ካነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ የሀገሪቱ ሥራ ተቋራጮች በምን መልኩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ? የሚለው ጉዳይ ነው። የሁለት ቀኑ ውይይትና ጥያቄዎች ተጨምቀው ከተላኩላቸው በኋላ በመጨረሻ በኮንፍረንሱ ላይ በመገኘት ማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ የሀገር ውስጥ ስራ ተቋራጮች አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በመጀመሪያ በሀገር ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ያለባቸው መሆኑን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በግንባታው ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ ሰፊ አቅምን በሚጠይቁ የሀገር ውስጥ ግንባታዎች የአገር በቀል ተቋራጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ችግሩን ፈቶ የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም ወደ አለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመሰረታዊነት ሁለት ስራዎች በራሳቸው በተቋራጮቹ መሰራት የሚገባቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። እነዚህም በአንድ መልኩ በሀገር ውስጥ ግንባታን ከሚያከናውኑ የውጭ ተቋራጮች ጋር በንዑስ ተቋራጭነት በመስራት አለም አቀፍ ልምድንና አሰራርን መቅሰም ሲሆን ሁለተኛው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ ከውጪ ተቋራጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና (Joint Venture) መስራት ነው።

 የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን ከውጭ ሀገር ተቋራጭ ጋር በሽርክና እንዲሰሩ በማድረጉ ረገድ ግን የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኔጅመንት ዘመናዊነት ብዙ ሊፈተሽ የሚገባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያዎች ከባለሙያዎች ውጪ በቤተሰብ ስብስብ የሚመሩበትን አሰራር ማስወገድ ካልቻሉ በስተቀር ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመስራት የማይችሉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከአነስተኛ ፎቆች ባለፈ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች መገንባት የተጀመረ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በመገንባቱ ረገድ የሀገሪቱ የሥራ ተቋራጮች አቅም ያላደገ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በውጭ ኩባንያዎች የተያዙ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ኩባንያዎቹ በሀገር ውስጥ ያለውን ውድድር በብቃት የሚያሸንፉበትን አቅም እየፈጠሩ መሄድ ከቻሉ ወደ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚሸጋገሩበት እድል ያለ መሆኑንም አመልክተዋል። ሆኖም የሀገር ውስጡ ግንባታ በውጪ ኩባንያዎች እየተወረረ ባለበት ሂደት ግን ስለ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሰብ የማይቻል መሆኑ ጨምረው ገልፀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
533 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us