ቻይና ያልተመዘገቡ የሞባይል ስልክ ቀፎዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ አደረገች

Wednesday, 04 January 2017 14:14

 

በሀገር ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለመቆጣጠር ላለፉት ዓመታት ስትሰራ የቆየችው ቻይና ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2017 ዕለት ጀምሮ ያልተመዘገቡ ቀፎዎች ከሥራ ውጪ ያደረገች መሆኗን ቻይና ደይሊ ከሰሞኑ ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል። እንደዘገባው ከሆነ መንግስት ይህንን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ማናቸውም በሀገሪቱ ያሉ ተንቀሳቃሽ ስልኰችን ባለቤቶች እንዲያስመዘግቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ጥሪው በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በሕትመት ውጤቶችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር ሲሰራጭ የቆየ መሆኑ ታውቋል።

ጥሪውንም ተከትሎ በርካታ የሀገሪቱ ዜጐችና ነዋሪዎች ስልካቸውን ማስመዝገባቸው የታወቀ ሲሆን፤ ይሁንና ጥሪውን ችላ ብለው ያላስመዘገቡ ግለሰቦች ግን የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በጠባበት ዕለት በእጃቸው ያለው ተንቀሳቃሽ ስልክ ከጨዋታ ውጪ ሆኖ አግኝተውታል።

መንግስት ስልኰቹ ከማዕከል አገልግሎት እንዳይሰጡ ካደረገ በኋላ ግለሰቦቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስልካቸውን በማስመዝገብ ወደ አገልግሎቱ የማይገቡ ከሆነ ቁጥሮቻቸውን ሳይቀር በመዝጋት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን የሚያቋርጥ መሆኑን አስታውቋል። በቻይና ከአንድ ተንቀሳቃሽ መስመር በላይ መያዝ የተለመደ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት 1 ነጥብ 54 ቢሊዮን የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመሮች በስራ ላይ መሆናቸውን የዤኑዋ ዘገባ ያመለክታል።

ዘገባው በቻይና በአሁኑ ሰዓት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 686 ሚሊዮን መድረሱን ገልጿል። በሀገሪቱ እያደገ ከመጣው ከፍተኛ የኢኰኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ የመረጃ ልውውጥ መጠንም በዚያው መጠን ማደጉ የቻይናን መንግስት የቁጥጥር ሥርዓት ክፉኛ ሲያሳስበው ቆይቷል። መንግስት የመረጃ ቁጥጥሩን ለማጠናከር የተንቀሳቃሽ ስልኰችን ለመመዝገብ እንቅስቃሴ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2013 ነበር፤ ሆኖም ከበርካታ ዓመታት ሂደት በኋላ ወደተግባር የተገባው በያዝነው የፈረንጆቹ 2017 አዲስ ዓመት ነው።

ከበርካታ ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያ በኋላ ቀፎዎቻቸውን ያላስመዘገቡ ዜጐች በአዲሱ ዘመን መባቻ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ቀፎዎቻቸው ጥሪን፣ መደወልንም ሆነ አጭር መልዕክትን ማስተናገድ ሳይችሉ ቀርተዋል። አሁንም ቢሆን በተሻለ የኢኰኖሚ እድገት ውስጥ የምትገኘው ቻይና ባለፉት 30 ዓመታት 7 መቶ ሚሊዮን የሚሆን ህዝቧን ከድህነት ማውጣቷን ዘገባዎች ያመለክታሉ። እንደ ሁዋይት ፔፐር መረጃ ከሆነ እ.ኤ.አ. በ1949 የአንድ ቻይናዊ አማካይ እድሜ 49 ዓመት የነበረ ሲሆን፤ ይህ የእድሜ ጣሪያ እ.ኤ.አ. በተወሰደው ወደ መረጃ 76 ዓመት ተመንድጓል። በ1949 ከ80 በመቶ በላይ ቻይናዊ ያልተማረና ለትምህርት ከደረሱት ልጆች መካከልም የትምህርት እድል ማግኘት የቻሉት 20 በመቶ ብቻ ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ2015 ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሜያቸው ከደረሱ ልጆች መካከል የትምህርት እድል ማግኘት የቻሉት ደግሞ 99 ነጥብ 88 በመቶ መሆናቸውን ቻይና ደይሊ ያመለክታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
413 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us