ሱዳን ከከፍተኛ የአየር ንብረት ተጋላጭ ሀገራት መካከል ተመደበች

Wednesday, 04 January 2017 14:18

ሱዳን ለአየር ንብረት ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ ከተመደቡት ሀገራት መካከል አንዷ ሆና መመደቧን የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመልክቷል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን የውሃ ትነቱን መጠን በፍጥነት እንዲጨምር እያደረገው መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። በሰሜን አፍሪካ ሀገራት እየተስፋፋ የሄደው በረሃማነት ሱዳንን ጭምር በማዳረስ ላይ መሆኑን የገለፀው ይሄው ዘገባ በተደረገውም ጥናት እ.ኤ.አ በ2060 አሁን በሱዳን ያለው አማካይ የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሺየስና እስከ 3 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ይላል። ይህንንም የሙቀት መጠን መጨመር ተከትሎም ከመደበኛ ዝናብ ይልቅ መደበኛ ያልሆነ ዝናብ በሀገሪቱ የሚታይ መሆኑ ተመልክቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱም ለድርቅና ለውሃ እጥረት ተጋላጭነት እድሏም የሰፋ ነው ተብሏል።

ዓለም የተፈናቃዮች ክትትል ማዕከል (International Displacement Monitoring Center) እንዳመለከተው ከሆነ በሱዳን ከፍተኛ የዝናብ መጠን ካስከተለው ጐርፍና ድርቅ ጋር በተያያዘ ሰዎች መፈናቀል የጀመሩት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ነው። እስከዛሬም ድረስ እስከ 6 መቶ ሺህ የሚሆኑ ሱዳናውያን መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ መሆኑን ይሄው የሲ ኤን ኤን ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

በሱዳን አነስተኛ የእርሻ መሬት ይዞታ በርካታ ገበሬዎችን ከያዙ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን 70 በመቶ የሚሆነው የገጠር ነዋሪ ሱዳናዊ የዝናብ ጥገኛ አርሶ አደር ነው። ግሎባል ሀንገር ኢንዴከስ እንዳመለከተው ከሆነ የምግብ ዋስትና ፈተና ካለባቸው 113 ሀገራት መካከል ሱዳን የ8ኛ ደረጃን ይዛለች። ይህም ሀገሪቱን በዓለማችን የምግብ እህል ዋስትና ማረጋገጥ ከገቡ 15 ኋላቀር አገራት መካከል አንዷ አድርጓታል ተብሏል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የሱዳን አርሶ አደሮች ምርትም በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ መሆኑን ይሄው ዘገባ ያመለክታል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመቋቋም የሱዳን መንግስት የራሱን የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድን ነድፎ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ተብሏል። ሱዳን ከአየር ለውጡ ጋር በተያያዘ ዜጐቿ የቢጫ ወባ፣ ወባና የኰሌራ ተጠቂ የመሆን እድላቸውም ሰፊ ነው ተብሏል።

ያደጉትና በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት ለአየር ንብረት ብክለት ምክንያት በመሆናቸው በለውጡ ተጠቂ ለሆኑ ታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሰፊ ትግል ሲደረግ ቆይቷል። የዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳንን የሚያካትት መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
456 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us