ጥፋተኞችን በህግ ለመጠየቅ ውሳኔ ያስተላላፈው የጃካራንዳ አክስዮን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ

Wednesday, 04 January 2017 14:19

 

በሀገሪቱ ከተመሰረቱት አክስዮን ማህበራት መካከል ጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ በ2 ሺህ ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ ባለአክስዮኖችን ያቀፈ ነው። በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው ይህ አክስዮን ማህበር ከተመሰረተ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም በመሀል በገጠሙት በርካታ ውስብስብ ችግሮች ወደ ፊት መራመድ ሳይችል ቆይቷል።

 

የድርጅቱን ችግር ፈትቶ ስራውን በተፈለገው አቅጣጫ ወደፊት ለማስኬድ በተደረገው ጥረትም ባለፈው እሁድ ታህሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በንግድ ሚኒስቴር አዳራሽ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል። በዕለቱ የተበተነው የስብሰባ ፕሮግራም የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ እንደሚጀመር የሚገልፀው እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ቢሆንም ስብሰባው ግን የተጀመረው በ6 ሰዓት ተኩል ነበር። ለስብሰባው መጀመር መዘግየት ዋነኛ ምክንያትም የነበረው የተሰብሳቢዎች ዘግይተው በቦታው መድረስና እየተንጠባጠቡ መገኘት ነበር።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ምልዓተ ጉባኤውን የተሟላ ለማድረግ ሲባል የስብሰባ መጀመሪያው ጊዜ ሰዓታትን ወስዷል። አንዳንዶችም በጥበቃው በመሰላቸት ትተው ለመሄድ ተገደዋል። ተሰብሳቢዎች ታግሰው እንዲቆዩ ለማድረግም ከመድረኩ ተደጋጋሚ ማሳሳቢያዎች ሲሰጡ ቆይቷል። መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስችለው ምልዓተ ጉባኤው መሟላቱ ተረጋግጦ ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ለጉባኤው ቀርቧል።

 

በምዕራብ ሸዋ ዞን በባኮ ልዩ ወረዳ የጀመረው የእርሻ ልማት ለሁለት ዓመታት ያህል ከተቋረጠ በኋላም ወደ ስራ የገባ መሆኑ በዚሁ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። የአትክልት ምርትን በተመለከተ ለሁለት ጊዜያት ያህል ተመርቶ የተሸጠ መሆኑ ተመልክቷል። ከዚህም በተጫማሪ ከአንድ ቅባት ላኪ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት የቦሎቄ፣ የሰናፍጭና የጥቁር አዝሙድ ዘር እንዲገባ ተደርጓል ተብሏል። ሚያዚያ ላይ ሊሰበሰብ የሚችል የአትክልት ምርት መኖሩም ተመልክቷል። የአዋሽ ቢ ሾላ የእርሻ ስራን በተመለከተም ኩባንያው በአክስዮን ማህበሩ አቅም ሊሰራ የማይችል በመሆኑ የአክስዮን ማህበሩ አባል ከሆኑ ግለሰቦች ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል።

 

አክስዮኑ የርካታ ንብረቶች መጥፋትና መባከን የደረሰበት መሆኑ ተገልጿል። መጥፋታቸው ከተገለፁት ንብረቶች አንዱ የድርጅቱ የሽያጭ መመዘገቢያ ማሽን ሲሆን በተሰናባቹ ቦርድ ለጥገና በሚል ይሄንኑ አገልግሎት በሚሰጥ አንድ ኩባንያ ተልኮ የነበረ መሆኑን በመግለፅ፤ በአሁኑ ሰዓትም በፖሊስ ክትትል ስር መሆኑ ታውቋል። የድርጅቱ ሲንግል ጋቢና ፒክ አፕ መኪናም እንደዚሁ በፖሊስ ክትትል ተፈልጎ ከተገኘ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ እጅ በምርመራ ላይ የሚገኝ መሆኑን ይሄው ሪፖርት አመልክቷል። ለባኮ እርሻ ልማት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የመሬት መከሽከሻ መሳሪያም ተፈታቶ ከተወሰደ በኋላ በተደረገው ክትትል የመከስከሻው አካላትና ሌሎች የአክስዮን ማህበሩ እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል። የድርጅቱን ሰራተኞችን በተመለከተም በአዲስ አበባ፣ በባኮና በአዋሽ ያሉና የተበተኑትን የጥበቃና የንብረት ክፍል ሰራተኞች የስምንት ወራት ያልተከፈለ ደመወዛቸው ተከፍሏቸውና ክሳቸውም በማቋረጥ  ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል።

 

በዚሁ ሪፖርት ከተዳሰሱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የድርጅቱ የቢሮ እቃዎች ሲሆን በተሰናባቹ ቦርድ የተቀጠረው ጠበቃ የሰራበት ገንዘብ ያልተከፈለው መሆኑን ገልፆ ክስ ከመሰረተ በኋላ በፍርድ ቤት አስወስኖ የአክስዮን ማህበሩ መረጃዎች ያለባቸውን ሶስት ኮምፒዩተሮችና ፎቶ ኮፒ ማሽንን የወሰደ መሆኑ ተመልክቷል። የድርጅቱን መረጃ የያዙትን ኮምፒዩተሮች ከሚወስድ ይልቅ ሌሎች ተሸከርካሪዎችን መውሰድ የሚችልበት እድል የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ሳይሆን የቀረ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

 

ጉባኤው በዕለቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካካለም ከዚህ ቀደም በአክስዮን ማህበሩ ላይ የንብረትም ሆነ የጥሬ ገንዘብ ጥፋት ያደረሱ ሰዎች በህግ የሚጠየቁበት ሂደት እንዲኖር ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በንግድ ሚኒስቴር በኩል የኦዲት ስራው ተከናውኖና የማጣራት ስራውም በሚገባ ተከናውኑ በሚገኘው ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛው አካል ተለይቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ይደረጋል ተብሏል። አክስዮን ማህበሩ ከዚህ ቀደም የነበሩት የቦርድ አባላት ብዛት ሶስት የነበሩ ሲሆን በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ግን ወደ ሰባት ከፍ እንዲል ተደርጓል። የቦርዱ አባላት የተመረጡት በአክስዮን ማህበሩ ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ ያላቸው እንደዚሁም በሙያቸው አክስዮን ማህበሩን ሊያገለግሉ ይችላሉ የተባሉ ናቸው። የግብርና ሥራውን የሚያከናውንባቸው የተለያዩ የግብርና ቦታ ይዞታዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ሸዋ  ባኮ ቲፔ ወረዳ 3 መቶ ሄክታር የእርሻ መሬት፣ አዋሽ ቢ ሾላ 15 ሄክታር መሬት ይገኙበታል። ከእነዚህም መሬቶች ላይ የግብርና ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጠቅላላ ጉበኤው ውሳኔ ተሰጥቶበታል። አክስዮን ማህበሩ ቀጣይ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለውን የፋይናስ አቅም  በማጠናከሩ ረገድ ከስራ እንደዚሁም ከባለአክስዮኑ የሚሰበሰቡ ገቢዎችን ለመጠቀም እቅድ ይዟል። ከባለአክስዮኖች ገንዘብን በመሰብሰቡ ረገድ ወደ 13 ሚሊዮን ብር አካባቢ እስከ ጥር 30 ድረስ ለመሰብሰብ ታስቧል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
509 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us