ናይጄሪያ በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ውስጥ ናት

Wednesday, 11 January 2017 13:54

ናይጄሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብን የያዘችና ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም የሚበዛው ህዝቧ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ችግር ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በኤሌክትሪክ ሀይል ዙሪያ በርካታ ዘገባዎችን የሚያሰራጨው ዋይ ኤልክትሪክሲቲ ማተርስ (Why Electricty Matters) ድረገፅ አመልክቷል። ድረገፁ 80 በመቶ የሚሆነው የናይጄሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ከተፈጥሮ ጋዝ (Natural Gas) የሚገኝ መሆኑን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ “አረንጓዴ ኢኮኖሚ” በሚለው የዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች አንዱ መመዘኛ የናይጄሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም። ይህ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው ሙስና በሀገሪቱ ወሳኝ የተባሉ መሰረተ ልማቶች እንዳይስፋፉ እንቅፋት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

 የድረገፁ ዘገባ ናይጄሪያ ምንም እንኳን ከደቡብ አፍሪካ በሶስት እጥፍ የሚልቅ ህዝብን ብትይዝም በአሁኑ ሰዓት የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ግን የደቡብ አፍሪካ አንድ አስረኛ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል። 98 ሚሊዮን የሚሆኑ ናይጄሪያዊያን ኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። በናይጄሪያ መሰረቱን ያደረገው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከኃይል እጥረት ጋር በተያያዘ ስራውን በድንጋይ ከሰል ለማከናወን እንደተገደደ በዘገባው ተመልክቷል።

 

ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝን በሀይል ምንጭነት ከመጠቀሟ ጋር በተያያዘ ለሀይል መቋረጥ ብሎም መቆራረጥ እየዳረጋት ነው። የጋዝና የነዳጅ ቱቦዎች በተለያዩ ግዛቶች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑና በነዳጅና ጋዝ ስርቆት የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችም በቱቦዎች ላይ የሚያደርሷቸው ተደጋጋሚ ጉዳቶች ለሀይል መቆራረጡ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
495 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us