“ዘቢዳር” የቢራ ገበያውን ተቀላቀለ

Wednesday, 11 January 2017 13:52

 

በቀላሉ በእጅ ሊከፈት የሚችል የቆርኪ ክዳን የደፋው አዲሱ ዘቢዳር ቢራ ባሳለፍነው አርብ ታህሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም የቢራ ገበያውን በይፋ መቀላቀሉን አስታወቀ። የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ ዘቢዳር ቢራ በቅድሚያ ለገበያ የሚቀርበው በደቡብ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ መሆኑ ታውቋል። ዘቢዳር ቢራ ከ1ሺህ 100 በላይ ባለአክሲዮናችን እንዳሉት በመግለጫው ወቅት ተጠቁሟል፡

 

ዘቢዳር በጉራጌ አካባቢ የሚገኝን ተራራ ስያሜ ይዞ የተመሠረተ ሲሆን ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ በኩል በ167 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወልቂጤ ከተማ ጉብሬ ውስጥ በ1500ሺህ ስኩዌር ላይ በሰፈረ ቦታ በዓመት 350 ሺህ ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ኖሮት ስራውን መጀመሩም ተገልጿል። በባለቤትነት የሚመሩት ደግሞ የቤልጂየም ዩኒ ቢራ 60 በመቶ ድርሻ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዥማር 40 በመቶ መሆናቸውም ተነግሯል። ዩኒብራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከከፍተኛ ቢራ አምራቾች መካከል አንዱም ነው። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የኤስ. ኬ. ኦ . ኤል ብራንድ ህጋዊ ባለቤት በመሆን በአስራ አንድ የአፍሪካ አገራት ምርቶችን በማከፋፈል ላይም ይገኛል ተብሏል። የ40 በመቶ አጋር ሆኖ የሚሰራው ዥማር ሁለገብ ኢንዱስትሪ አክስዮን ማኅበር በበኩሉ በአገር ውስጥ የግብርናና ኢንዱስትሪ፤ በትራንስፖርትና ቱሪዝም ዘርፍ በማማከር አገልግሎት እንዲሁም በግንባታና ቤት ሽያጭ ጨምሮ በተለያዩ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለመስራት ያለመ ተቋም ሲሆን ይህ የዘቢዳር ቢራ የመጀመሪያ ፕሮጀክቱም እንደሆነ ታውቋል።

 

በተወዳጅ የቢራ ጣዕም (ላጋር) እና በቀላሉ ለመክፈት በሚመች የቆርኪ ክዳን የቀረበው ዘቢዳር ቢራ፤ በ33 ሴንቲ ሊትር ጠርሙስ በአምስት በመቶ የአልኮል መጠን ለተጠቃሚው ደርሷል። የ1ነጥብ 2 ሚሊዮን የማርኬት ድርሻ በቢራው ገበያ እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን፤ በስሩም 200 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎችና ለበርካታ ባለሙያዎች የስራ እድልን እንደፈጠረ፤ እንዲሁም ማህበራዊ ኃላፊነቱንም ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የሥራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ዘቢዳር ቢራ የጓደኝነትን ስሜት ለመፍጠር የሚያስችል መታወቂያ እንዲኖረው “ስንገናኝ” የሚል  መሪ ቃል እንዳለውም የፋብሪካው ብራንድ ማኔጀር ራዕይ መለስ ተናግረዋል። ዘቢዳር ቢራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የቢራ ገበያ ሁኔታ አጥንቶና ክፍተቱን ለመሙላት የራሱን የተለየ ምርት ይዞ ስለመምጣቱ በመግለጫው ሲነገር ሰምተናል። ዘቢዳር ቢራ በዘመናዊ ቢራ አጠማመቅ የሚዘጋጅና መቶ በመቶ ከንፁህ ገብስ፣ ከጌሾና ከውሃ የተፈጥሮ ግብዓቶች እንደሚጠመቅም ታውቋል።  

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
980 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us