ፔጆት መኪና በኬኒያ ሊገጣጠም ነው

Wednesday, 15 February 2017 13:09

 

የፈረንሳዩ ፔጆት ተሽከርካሪ በኬኒያ ምድር ተገጣጥሞ ለገበያ እንዲቀርብ ሊደረግ ነው። ከሰሞኑ የፔጆት ኩባንያ እና ዬሬዢያ በተባለ የኬኒያ ኩባንያ መካከል በተፈረመው የውል ስምምነት መሰረት ኬኒያዊው ኩባንያ የፔጆት መኪና ደረጃን መስፈርትን ባሟላ መልኩ መኪኖቹን እየገጣጠመ ለገበያ የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል። የሁለቱ ኩባንያዎች የመግባቢያ ስምምነትም ከሰሞኑ በናይሮቢ ተፈርሟል።

 

ዜናውን ያሰራጨው አፍሪካን ኒውስ ድረገፅ እንዳመለከተው ከሆነ በአለም አቀፉ የተሽከርካሪ ገበያ እውቅና ካተረፉ ተሸከርካሪዎች መካከል ፔጆ መኪና በኬኒያ ሲገጣጠም ከጀርመኑ ቮልስ መኪና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ይገኛል። እንደ ስታንደርድ ዲጂታል ዘገባ ከሆነ በስምምነቱ መሰረት የሚገጣጠሙት የፔጆ መኪኖች  ፔጆት 508 እና ፔጆት 3008 በሚል የሞዴል ስያሜ የሚታወቁ ናቸው።

 

 አንድ ሺህ ተሽከርካሪዎችንም በየዓመቱ እየገጣጠሙ ለገበያ ለማቅረብ እቅድ የተያዘ መሆኑን የስታንዳርድ ዘገባ ያመለክታል። የመጀመሪያው የተገጣጠመ ተሽከርካሪም በመጪው ሀምሌ 2009 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለገበያ የሚቀርብ መሆኑን ዘገባውን ካሰራጩት የኬኒያ መገናኛ ብዙኋን መካከል አንዱ የሆነው ደይሊ ኔሽን አመልክቷል።

 

ፔጆት ኩባንያ ከዚህ ቀደም በኬኒያ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ የነበረው ሲሆን ኩባንያው የሀገሪቱ ገበያ ብዙም አዋጪ ሆኖ ስላላገኘው እ.ኤ.አ በ2004 ዘግቶ የወጣ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይሁንና ቀደም ባሉት ጊዜያት በተደረገ የገበያ ጥናት የኬኒያ ገበያና ኢኮኖሚ ለፔጆ ተሽከርካሪ አመቺ ነው ተብሎ በመታመኑ ኩባንያው ከዓመታት በኋላ መልሶ ገበያውን መቀላቀሉ ታውቋል። በሌላ በኩል የኬኒያ መንግስት በሀገሪቱ እየታየ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመፍታት የያዘውን ሰፊ እቅድ ለማሳካት ከዚህ ቀደም ከያዛቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ አዲስ የውሃ ሀይል ማመንጫን ለመገንባት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ተፈራርሟል። ይህም የ19 ቢሊዮን ሽልንግ ፕሮጀክት መሆኑን የደይሊ ኔሽን ዘገባ ያመለክታል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
530 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us