በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ ድርጅቶች ጥፋት ተጠያቂው ማነው?

Wednesday, 15 February 2017 13:12

 

 

በአንድ ሀገር የሚካሄዱ የልማት ስራዎች ከሚያስገኟቸው ጥቅሞች በተጨማሪ የሚያደርሷቸው የጎንዮሽ ጉዳቶችም አሉ። የማዕድን ሥራ፣ ግንባታ፣ ኢንዱስትሪም ሆነ ሌሎች የልማት ሥራዎች ከልማቱ በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት ሁኔታ ቢኖርም በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በአካባቢ ብሎም በዙሪያቸው ባለ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ልማቱ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ በዚያው መጠን ጉዳቱም የከፋ መሆኑ ስለሚታወቅ እነዚህን የጎንዮሽ ችግሮች ለመከላከል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በስራ ላይ ናቸው። በአካባቢ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ማህበረሰባዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች የአየር፣የውሃ ብሎም የድምፅና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ።

 

 ልማቱም እንዳይቀር፤ ብሎም አካባቢያዊ ጉዳትም እንዳይከሰት የሚደረግበት እድል ዜሮ ነው። ሆኖም የሚመጣው ልማት አንድም በአካባቢ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት አንፃር የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ወይንም አሉታዊ ተፅዕኖውን ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነስ የሚያስችሉ አለም አቀፋዊ አሰራሮች አሉ። እነዚህ ሥራዎች ልማትንና በአካባቢ ላይ ሊድርስ የሚችል ጉዳትን አጣጥሞ ለማስኬድ በህግ ብሎም በቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚሰሩ ናቸው።

 

 ከዚህ አለፍ ሲልም ስለሚመጣው የእለት ልማትና ገቢ እንጂ ልማቱ በአካባቢ ብሎም በቀጣይ ትውልድ ስለሚያደርሰው ጉዳት ግድ የማይሰጣቸው ወገኖችም አሉ።

 

በዚህ ዙሪያ የላላ አቋም ካላቸው ሀገራት መካከል ቻይና እና ናይጄሪያ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። የናይጀሪያ መንግስት እንደ ቶታል አይነቶቹ ግዙፍ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ሰፊ የሆነ የባህርና የየብስ ብክለት እያደረሱ የነዳጅ ምርትን ለዓለም አቀፍ ገበያ ሲያቀርቡ ችግሩን በቅድሚያ በመከላከሉ ረገድ ብዙም የሰራው ስራ አለመኖሩ በበርካታ አካላት እያስወቀሰው ይገኛል። በተመሳሳይ መልኩ የአካባቢ ጥበቃን ብዙም ታሳቢ ሳታደርግ ቅድሚያ ለምርታማነት ትኩረት የሰጠችው ቻይና የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያላደረገው የቀደመ የልማት ጉዞዋ ዛሬ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል። ሁኔታው ቀድሞ የገባቸው የአደጉ ሀገራት መንግስታት ልማትንና የአካባቢ ጥበቃን በተጣጣመ መልኩ አቆራኝቶ ለማስኬድ ጠበቅ ያሉ ህጎችን ከመተግበር ባለፈ ጥበቅ የሆነ አሰራርን ይከተላሉ። ለውጭ ቀጥተኛ የኢንቬስትመንት ፍሰቱ ልዩ ፍላጎትን ያሳደሩ በርካታ ታዳጊ ሀገራት ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ብዙም ትኩረትን ባለመስጠት በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በላላ የአካባቢ ጥበቃ ሥርዓት መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በማድረግ ላይ ናቸው። ባደጉት ሀገራት ለአካባቢ ጥበቃ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠየቁት እነዚህ ኩባንያዎች የተሻለ የኢንቬስትመንት መዳረሻ አማራጭ ያደረጉት በአካባቢ ጉዳይ ብዙም የማይጨነቁትን ታዳጊ ሀገራት ነው።

 

እነዚህ ታዳጊ ሀገራት አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ በቂ የህግ ማዕቀፍ የሌላቸው፣በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልን ያልያዙና ተቋማዊ አሰራራቸውም በእጅጉ የላላ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በኢንቨስትመንት ስም ወደ እነዚሁ አዳጊ ሀገራት ከገቡት ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ጋር በጥቅም ሳይቀር የተሳሰሩ በመሆናቸው የበርካታ ታዳጊ ሀገራት አካባቢ በማያገግምበት ደረጃ ቀላል የማይባል ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል። አንዳንዶቹ ኩባንያዎች በልማት ስም ደን ጨፍጭፈው  ከወሰዱት የኢንቬስትመንት ፈቃድ ውጪ ጣውላ ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ የሚያሸሹ፣ ከሰል እስከማክሰልና መሸጥ ሥራ ውስጥ ሳይቀር የተሰማሩም አሉ። በአካባቢው ህብረተሰብ ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት ካደረሱም በኋላ የመንግስትን የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ሁሉ ተጠቅመው ሀገር ጥለው የሚወጡም በርካቶች ናቸው።

 

በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ክስተቶት እየታዩ ይመስላል። በዝዋይ ሀይቅ ዙሪያ የተኮለኮሉት የአበባና የፍራፍሬ እርሻዎች በዝዋይ ሀይቅ ስነ ምህዳር ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እያደረሱ መሆናቸው እየተነገረ ቢሆንም እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሊገኝ አልቻለም። በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ፋብሪካዎች ወደ ወንዞች በሚለቁት አደገኛ ፍሳሽ የከተማዋ ወንዞች በእጅጉ መበከል ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከተማዋ ያሉት አነስተኛ የግብርና እርሻዎች የሚጠቀሙት ከእነዚሁ የተበከሉ ውሃዎች በመሆኑ እያደረሱ ያሉት ጤንነታዊ ጉዳት በተለያዩ ጥናቶች ሲዳሰስ ቆይቷል።

 

መንግስት “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን እንገነባለን” የሚል መፈክርን እየደጋገመ በሚያሰማባት በዚህች ሀገር ከሰሞኑ የታዩት መረጃዎች በእጅጉ አስደንጋጭ ሆነው ታይተዋል። ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በሀርመኒ ሆቴል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከግል አካባቢ ጥበቃ አማካሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

 

 አንድ ባለሀብት አንድን የኢንቬስትመንት ሥራ ከማከናወኑ በፊት አማካሪ ኩባንያዎች ቀጥሮ የኢንቨስትመንቱን ባህሪ እንደዚሁም በአካባቢ ላይ ሊያደርስ የሚያስችለው ተፅዕኖን ማስጠናት ይጠበቅበታል። ይህም በሰነድ መልኩ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል መቅረብ ይጠበቅበታል።

 

ሰነዱ በጥናቱ ውስጥ ከሚያካትታቸው ሥራዎች መካከል ሊኖር ይችላል ብሎ የተነተነውን የአካባቢ ተፅዕኖ ሊወገድ ወይም ሊቀነስ የሚችልባቸውን መንገዶች ጭምር ማሳየት ነው።

 ይህ ጥናት ከተጠና በኋላ ባለሀብቱ የጥናቱን የመጨረሻ የግምገማ ሰነድ በመያዝ ለፈቃድ ሰጪው አካል ያቀርባል። ፈቃድ ሰጪው አካልም የጥናቱን ሰነድ ከገመገመ በኋላ የኢንቨስትመንቱን መቀጠልና አለመቀጠል የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል። የቀረበው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነድ ፀድቆ ኢንቬስትመንቱ የሚቀጥል ከሆነ ባለሀብቱ የባንክ ብድርን ጨምሮ ለተለያዩ ስራዎች ማቅረብ ከሚገባቸው ሰነዶች መካከል አንደኛው ይሄው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሰነድ ነው።

 

የግል የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ ኩባንያዎቹ ይህንን ኃላፊነት መወጣት ቢገባቸውም በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ  ሚኒስቴር በኩል ተጠንቶ ከሰሞኑ ይፋ የሆኑት ሰነዶች ግን ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን አሳይቷል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከ50 በላይ ለሚሆኑ የግል የአካባቢ ጥበቃ ኩባንያዎች የስራ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ አስር ኩባንያዎችን በናሙናነት በመውሰድ አሰራራቸውን በተመለከተ የራሱን ጥናት አካሂዷል።

 

ጥናቱም ራሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ ኩባንያዎች በተገኙበት ባለፈው አርብ የካቲት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ይፋ ሆኗል። አማካሪ ድርጅቶቹ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊና ታአማኒ የሆነ ስራን መስራት ቢጠበቅባቸውም፤ የተገኘው የጥናት ውጤት ግን ይሄንን አያሳይም። በጥናቱ ከተካተቱት ድርጅቶች መካከል በርካቶቹ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ኃላፊነታቸውን የማይወጡ መሆኑን የቀረበው የዳሰሳ ሪፖርት ያመለክታል።

 

አንድ አማካሪ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ለማካሄድ በመጀመሪያ በጨረታ ተሳትፎ ካሸነፈ በኋላ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ሥራውን ማከናወን ይጠበቅበታል። ይህም ሥራ ፕሮጀክቱ በሚካሄድበት አካባቢ ድረስ በመሄድ በመስክ የሚከናወን ነው። ለዚህም ቢሮን በሰው ኃይል ከማሟላት ጀምሮ ለጥናቱ የሚሆኑ የመስክ መሳሪያዎችን አካቶ መያዝ ይጠበቅበታል።

 

 በጥናቱ ከተካተቱት ድርጅቶች አስር ድርጅቶች መካከል ስምንቱ ድርጅቶች ቢሮ ሲኖራቸው አንደኛው ግን በመኪና መሸጫ ውስጥ አንድ ጥግ ይዞ እየሰራ ተገኝቷል። ሌላኛው ድርጅት ስሙ ብቻ በቢሮው ላይ ከመለጠፍ ውጪ ኃላፊዎቹ በአካል ሊገኙ አለመቻላቸውን በቀረበው ጥናት ተመልክቷል። በስልክም ለማግኘት በተደረገው ሙከራ ፈቃዱን የወሰደው ግለሰብ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኖ ሳይገኝ የቀረ በመሆኑ በቀረበው ጥናት ተመልክቷል።

 

 ሌላው በዚሁ ሪፖርት ከተዳሰሱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው አማካሪ ኩባንያዎቹ ለአስጠኚ ኩባንያዎች የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነው። ጥያቄው የፕሮጀክት ገንዘቡ አነስተኛ የመሆኑ ጉዳይ ሳይሆን ጥናቱ ይጠይቃል ተብሎ ከሚጠበቀው የገንዘብ መጠን አንፃር በእጅጉ አነስተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው። ከዚህ አንፃርም አማካሪ ኩባንያዎቹ ሰነዱን የሚያዘጋጁት በእርግጥም የተባለውን ጥናት በተገቢው መንገድ በማካሄድ ነው? የሚል ጥያቄን ያስነሳል።

 

 የክፍያውንም ሁኔታ ለማረጋገጥ በተደረገው ጥናት ኩባንያዎቹ ጥናቱን ካካሄዱላቸው ድርጅቶች ጋር ያደረጓቸው የክፍያ ስምምነቶች ተፈትሸዋል። በዚህም አጥኚ ኩባንያዎቹ ከ10 ሺህ ብር እስከ 185 ሺህ ብር በሚደርስ ክፍያ ጥናቶችን የሚያካሂዱ መሆኑ ታውቋል።

 

አንድን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ለማከናወን በተለያየ ዘርፍ የተሰባጠረ ትምህርት ያላቸው ባለሙያዎች፣የላብራቶሪ ፍተሻና የመስክ ሥራ መሳሪያዎች የሚያስፈልጉ ሲሆን በሥራው ወቅትም ከሚደረገው የመስክ ጥናት ባለፈ የአካባቢውን ህብረተሰብ በሚገባ አማክሮ የህብረተሰቡን ምላሽ በቃለ ጉባኤ ማስፈር የግድ ይላል። ይሁንና ከተደረገው የዳሰሳ ጥናት መረዳት የተቻለው አጥኚዎቹ ሙያውና ሥራው በሚጠይቀው ኃላፊነት መሰረት በቦታው በመገኘት ተገቢውን የመስክ ሥራ ከመስራት ይልቅ ጋምቤላ ላለው ፕሮጀክት አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው ሰነድ ብቻ የሚያዘጋጁ መሆናቸው ነው። ጥናቱ ይጠይቃል ተብሎ ከሚጠበቀው ገንዘብ በእጅጉ ያነሰ ክፍያ የመጠየቃቸውም ሚስጥር ይኸው የመስክ ጥናትን ካለማካሄድ ጋር የተያያዘ መሆኑ የዳሰሳ ጥናቱ ያመለክታል።

 

 የአካባቢ ተፅዕኖ ሰነድ ዝግጅትን በተመለከተ አንዱ ሰነድ ከሌላው የተቀዳ እስከሚመስል እጅግ የሚመሳሰል መሆኑ፤እንደዚሁም የሚቀርቡትን ሰነዶች ፈትሾ ውሳኔ ለመስጠት በሚያዳግት መልኩ የተንዛዙ ዶክመንቶች የሚቀርቡበት ሁኔታ ያለ መሆኑም በዚሁ ጥናት ተመልክቷል። አንድ የልማት ሥራ ከመከናወኑ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ሲካሄድ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማማከርና ይህንንም ምክክር በቃለ ጉባኤና በሰነድ ማስቀመጥ አንዱ የስራው አካል ነው። ይሁንና ይሄው የቀረበው ጥናት የሚያሳየው የማህበረሰብ ተሳትፎና ቃለ ጉባኤ አያያዝን በተመለከተም ከፍተኛ የሆነ ችግርና ክፍተት የሚታይ መሆኑን ነው። ከአስሩ ኩባንያዎች መካከል አምስቱ የማህበረሰብ ተሳትፎ ቃለ ጉባኤ መያዛቸው ተመልክቷል።

 

 ከዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ “ቃለ ጉባኤውን የምንሰጠው ለባለሀብቱ ነው” ያሉ ድርጅቶች መኖራቸውም ተመልክቷል።  እንደዚሁም “ቃለ ጉባኤው የሚገኘው በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤታችን ነው” በማለት ምላሽ የሰጡ መኖራቸውንም በቀረበው ጥናት ተገልጿል። ከተያዙት ቃለ ጉባኤዎች ግማሹ ከድርጅቱ ማህተም ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካይ ወይንም የቀበሌው ማህተም የሌለበት በመሆኑ ታአማኒነታቸውን ጥያቄ የሚያስገባ መሆኑ ተመልክቷል።

 

 የፍተሻ መሳሪያን በተመለከተ  የዳሰሳ ጥናቱ በሚካሄድበት ወቅት እነዚሁ በናሙናት ጥናት የተካሄደባቸው አማካሪ ድርጅቶች መሳሪያዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ተጠይቀው ነበር።

ከአስሩ ድርጅቶች ውስጥ አምስቱ መሳሪዎችን አሳይተዋል፣ አንደኛው ቢሮ ዝግ ሆኖ በመገኘቱ ለማረጋገጥ አልተቻለም። ሁለቱ ደግሞ መሳሪያዎቻቸው ቅርንጫፍ ቢሯችን ነው ያለው በማለታቸው የመስክ ሥራ መሳሪያዎቻቸውን ማየት ያልተቻለ መሆኑን በጥናት አቅራቢው ተመልክቷል። ከዚህ ውጭም ያሉት ሌሎች አማካሪ ድርጅቶች ባለሙያዎቹ መሳሪያዎቻቸው ከአዲስ አበባ ውጭ ለመስክ ስራ ተልኳል የሚል ምላሽ በመሰጠታቸው የመሳሪያዎቹን መኖር አለመኖር ማረጋገጥ ያልተቻለ መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል።

 

የሰራተኞቻቸውን አቅም ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ ከአንዱ አማካሪ ድርጅት በስተቀር ሌሎቹ ሀሳቡ እንኳን የሌላቸው መሆኑን ነው ጥናቱ ያመለከተው። ህዝብ ማማከርን በተመለከተም ህብረተሰቡን ለማማከር በሚያደርጉት ጥረት በየአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የስብሰባ አበል የሚጠይቁበት ሁኔታ ስላለም፤ ለዚሁ ስራቸው አንዱ እንቅፋት አድርገው መግለፃቸውን ይሄው ጥናት ያመለክታል።

 

 ከዚህ ባለፈም የራሱ የፈቃድ ሰጪው አካል አንዳንድ የስራ ሀላፊዎች በጎን ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጪ  ከአማካሪ ድርጅቶችና ከባለሀብቱ ጋር ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ መልሰው በመንግስት ወንበር የውሳኔ ሰጪነት አሰራር ውስጥም የሚሳተፉበት ሁኔታ መኖሩም ተመልክቷል።

 

 በዚህ ጉዳይ ከመድረኩ በተሰጠው ምላሽ ጉዳዩ ከሥነ ምግባር ጥሰት  ባለፈ የጥቅም ግጭትን የሚፈጥር፣ ፍትሃዊነትን የሚያጓድልና በደረቅ ወንጀልነትም የሚያስጠይቅ ድርጊት ነውም ተብሏል። ከሁሉም በላይ አስገራሚ የሚያደርገው እነዚህ አማካሪ ድርጅቶች ስራቸውን መስራት የሚያስችላቸው ደረጃ ላይ ናቸው ተብሎ ከሚመለከተው የመንግስት አካል የብቃት ማረጋገጫ ያገኙና ይሄንንም በየጊዜው የሚያድሱ መሆናቸው ነው። ከዚህ ባለፈም እነዚህን አካላት ለመቆጣጠር፣ ለመከታተልና አቅም ለመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው መንግስታዊ አካል አሰራረርም በእጅጉ የላላ መሆኑም በእለቱ በተሳታፊዎች በኩል ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል አንዱ ነው። በዚህ በኩል የተወሰደው የናሙና ዳሰሳ ጥናት ይሄንን አሳይቷል። ተጠያቂነትን በተመለከተ ግን ብዙም የተነሳ ጉዳይ አልነበረም። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
774 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us