የንግድውድድርናሸማቾችጥበቃ አዋጅን ማሻሻልለምንአስፈለገ?

Wednesday, 19 April 2017 12:30

 

 

በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ ያለውን የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ለማሻሻል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። አዋጁን የማሻሻሉ ሥራ የተጀመረው በዚህ ዓመት ነው። በያዝነው ዓመትም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአዋጁ መሻሻል በርካታ ምክንያቶች ተነስተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አዘጋጅቶ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት ላይ ነው። እኛም ከሰሞኑ ባካሄደው አንድ መድረክ ላይ ተገኝተን አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገባቸውን ነጥቦች ተመልክተናል።

 

  ከዚህ ቀደም በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ ሲሰራበት የነበረው የወንጀል ምርመራ ጉዳይ ሁሉም ተጠቃሎ በፌደራል ፖሊስ ሥር እንዲሆን የተደረገ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩም ክስ የመመስረቱም ጉዳይ በፌደራል አቃቤ ህግ ሥር እንዲሆን ተደርጓል። እነዚህም ሁኔታዎች ቀደም ሲል የወንጀል ምርመራና  ክስ የመመስረት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩትን አንዳንድ አስፈፃሚ መሰሪያቤቶች የነበሯቸውን እነዚህን ኃላፊነቶች ለፌደራል ፖሊስና እና ለፌደራል አቃቤ ህግ እንዲያስረክቡ ተደርጓል። የመመርመርና የመክሰስ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲያስረክቡ ከተደረጉት አስፈፃሚ መስሪያቤቶች መካከል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደዚሁም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም የገቢዎና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚጠቀሱ ናቸው።   

 

 የንግድ ውድድርና  ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል አንደኛው የወንጀል ጉዳዮችን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን ነበር። ሆኖም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው እነዚህ ስልጣንና ተግባራት ወደ ፌደራል ፖሊስና ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሸጋገራቸው፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃላፊነት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑ ታውቋል። ይህም በመሆኑ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ስልጣንና ተግባር እንደገና መደንገግ በማስፈለጉ ለህጉ መሻሻል አይነተኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ኃላፊዎቹ ይገልፃሉ።

 

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የወንጀል ጉዳዮችን የመመርመር ብሎም የመክሰስ ስልጣኑ ይወሰድበት እንጂ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶችን በዳኝነት የማየት ስልጣኑ እንደተጠበቀ ነው። በዚሁ የህግ ማሻሻያ ረቂቅ ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የዳኞች ቁጥርን የሚመለከተው ይገኝበታል። አሁን በስራ ላይ ባለው ህግ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ስራውን የሚያከናውነው በሶስት ዳኞች አማካኝነት ነው። ሆኖም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች የሚያሳዩት ከዳኞች አለመሟላት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች የሚጓተቱበት፤ ብሎም ተገልጋዮች ቅሬታ የሚያሰሙበት ሁኔታ እንደነበር ነው። ይህንንም ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በረቂቅ አዋጁ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የጉዳዩ ክብደትና ውስብስብነት እየታየ በአንድ ዳኛ የሚታይበት አሰራር የሚኖርበት ሁኔታ እንዲኖር ተመልክቷል።

 

በዚህ አንቀፅ ላይ በተሳታፊዎች በኩል ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል      “ጉዳዮችን በአንድ ዳኛ መመልከት ነገሮችን ከግራና ከቀኝ አጣርቶና አመዛዝኖ ለማየት እድልን ካለመስጠቱም ባሻገር አሰራሩ ለሙስናም ጭምር የሚያጋልጥ በመሆኑ የቀድሞው አሰራር ቢቀጥል ይሻላል” የሚለው ይገኝበታል።

 

 አሁን በስራ ላይ ያለው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ የንግድ እቃዎችንና አገልግሎቶች ስርጭትን መቆጣጠርን እንደዚሁም የንግድ እቃዎችን መደበቅና ማከማቸትን በተመለከተ ሰፋ ያሉ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። በዚሁ ህግ አንቀፅ 24 መሰረት ማንኛውም ነጋዴ ከመደበኛው የግብይት አሰራር ውጪ የሸቀጥ ምርቶችን ማከማቸት ወይም መደበቅ የማይችል መሆኑ ተደንግጓል።

ነጋዴ ያልሆነ ግለሰብም ቢሆን ለግሉ፤ እንደዚሁም ለቤተሰቡ ፍጆታ ከሚያውለው በላይ እቃዎችን ማከማቸት የማይችል መሆኑ ተመልክቷል። ህጉ አንድ ሸቀጥ ተከማችቷል ለማለትም ከነጋዴው አጠቃላይ ካፒታል አንፃር ያለው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በቁጥር ለይቶ አስቀምጧል። ይህም ከነጋዴው ካፒታል 25 በመቶ የማያንስ ሆኖ ሆኖ ሲገኝ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል።  አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን ጉዳዩን ከዚህም በላይ ጠበቅ በማድረግ ከተቀመጠው የካፒታል መጠን በተጨማሪ መሰረታዊ የንግድ እቃን ያለደረሰኝ ወይንም ያለ ህጋዊ ማስረጃ ከነጋዴ ገዝቶ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር እንደዚሁም ከንግድ ቦታ ውጪ ሸቀጡን በመውሰድ ማከማቸትና መደበቅ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ደንግጓል።

 

ሌላው ለህጉ መሻሻል መነሻ ተደርጎ የተጠቀሰው ህጉ ወጥቶ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ በአፈፃፀም ሂደት በርካታ ክፍተቶች በማጋጠማቸው መሆኑን ኃላፊዎቹ አመልክተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም እቃዎችን በህገወጥ መንገድ አጓጉዞ መደበቅን ወይንም ማከማቸትን በተመለከተ አሁን በስራ ላይ ያለው ሀግ “በማናቸውም ማጓጓዣ” በሚል ያስቀመጠው ሀሳብ አሻሚ ሆኖ በመገኘቱ ሰዎች ሸቀጦች በሰው አሸከመው ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዙ ለመያዝ  ሰውን እንደ አንድ ማጓጓዣ መቁጠር የሚቻልበት ሁኔታ ሥለነበር ለአሰራ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ተመልክቷል። በዚህም መሰረት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ “በማናቸውም መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘ መሰረታዊ ሸቀጥ” በሚል እንዲስተካከል የተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

 

አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ወደ ስራ በተገባበት ወቅት ተገኝተውበታል ከተባሉት ክፍተቶች መካከል አንደኛው ለሰው ልጅ ጤንነት ጎጂ የሆኑ የንግድ እቃዎችን ማዘጋጀት የሚመለከተው አንቀፅ ይገኝበታል። በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 22 ንዑስ አንቀፅ 10 ላይ “ለሰው ጤና እና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ ዕቃን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል። ሆኖም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህ አንቀፅ በአሰራር ደረጃ ወደ ተግባር ሲገባ ክፍተቶች የታየበት መሆኑን አመልክቷል።

 

አንቀፁ ለሰው ልጅ አደገኛ የሆኑ የንግድ እቃዎችን ከመሸጥ ወይም ለሽያጭ ከማቅረብ ውጪ ይሄንኑ አደገኛ ሸቀጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚያዘጋጁ ሰዎችን ለመከታተልና በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ድንጋጌን ባለማካተቱ መሰል አደገኛ ሸቀጦችን የሚያዘጋጁ ግለሰቦችና አካላት ከተጠያቂነት የሚያመልጡበት ሁኔታ ሲፈጠር የቆየ መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት ተችሏል። ሆኖም ረቂቅ አዋጁ  “ማዘጋጀት” የሚለውን ቃል እንዲያካትት በመደረጉ አሁን በአሰራር እየታየ ያለውን ክፍተት ይሞላል የሚል ተስፋ ያላቸው መሆኑን በረቂቅ ህጉ ላይ ማብራያ የሰጡት ባለሙያዎች አመልክተዋል።

 

ሌላው በህጉ ላይ ታዩ ከተባሉት ክፍተቶች መካከል ሌላኛው በሸማች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን በተመለከተ ህጉ ተጠያቂ የሚያደርገው ነጋዴን ብቻ የመሆኑ ጉዳይ ነው። እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ በአሁኑ ሰዓት በህግ በነጋዴነት የማይታወቁና የንግድ ፈቃድ አውጥተው የማይነግዱ በርካታ የንግዱ ዘርፍ ተዋናዮች በመኖራቸው የሸማቾችን መብት ለመጠበቅ ባለው ህግን የማስከበር ሂደት እነዚህን በህግ የማይታወቁ ነጋዴዎችንም ጭምር አካቶ ተጠያቂ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አሁን በስራ ላይ ባለው ህግ “ማንኛውም ነጋዴ” የሚለው ሀሳብ ወጥቶ በአዲሱ ረቂቅ ማንኛውም ሰው”  በሚለው  ሀሳብ እንዲተካ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።   

 

 አሁን በስራ ላይ ባለው ህግ መሰረት፤ሸማቹ የገዛውን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጉድለት ያለበት ሆኖ በሚያገኝበት ወቅት፤ ሻጩ ነጋዴ የሸጠውን እቃ እንዲለውጥ ወይም ክፍያውን እንዲመልስ፣ ወይም አገልግሎቱን ያለ ክፍያ እንዲሰጠው ወይም ክፍያውን እንዲመልስለት በ15 ቀናት ውስጥ መጠየቅ እንደሚችል ተደንግጓል። ይሁንና  ይህ ድንጋጌ ነጋዴው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንደሚገባው ቀነ ገደብ ያላስቀመጠ በመሆኑ  የሸማቹን ማህበረሰብ መብት በማስከበሩ ረገድ በአሰራር ላይ ችግር ሲፈጥር መቆየቱ ተመልክቷል። ይህንንም ችግር ለመፍታት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ  ነጋዴው የሸጠው እቃ ወይም አገልግሎት ችግር እንዳለበት በሸማቹ አካል ጥያቄ ከቀረበለት በ7 ቀናት ውስጥ ምላሽ የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑ ተደንግጓል።

 

ከዚህ ውጪም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 “ሸማች ማነው?” የሚለውን ትርጓሜ በተመለከተ ሸማች ማለት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃን የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው በሚል ተቀምጦ  የነበረውን ሀሳብ፤ በረቂቅ አዋጁ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው በሚል እንዲተካ ተደርጓል። ይህም አንድ ሰው ከራሱ እንደዚሁም ከቤተሰቦቹ ውጪ ሌላ ሰው ሸቀጦችን ወይንም አገልግልቶችን የሚገዛበት ሁኔታ በመኖሩ ትርጓሜውን ሰፋ ለማድረግ በማሰብ ነው ተብሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
308 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us