የተሽከርካሪ ጎማ እድሜ የሚያራዝመው ምርት

Wednesday, 09 August 2017 12:32

 

በሀገራችን አዲስ የሆነና የመኪና ጎማ መፈንዳትንና መተንፈስን የሚከላከል ምርት ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ተዋውቋል። ምርቱ ‘ታየር ፕሮቴክተር’ በሚል ስያሜ የሚጠራ ሲሆን በከለመዳሪ አልባ ጎማዎች ውስጥ በመሞላት ጎማው ሹል ነገር ወይንም በስለትና በሌሎች ባዕድ አካላት ቢወጋ እንኳን እንዳይፈነዳ እንደዚሁም የመተንፈስ ችግር እንዳይገጥመው የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። በተሰጠው ማብራሪያ መሰረት ይሄው ጄል በጎማ ውስጥ ከተሞላ በኋላ በቀላል ተሽከርካሪ ጎማዎች ውስጥ እስከ 6 ሚሊ ሜትር እንደዚሁም ለከባድ ተሸከርካሪዎች እስከ 12 ሚሊሜትር  ስፋት ያላቸው ቀዳዳዎችን በፍጥነት መድፈን ይችላል። አንድ ጎማ የሚያስፈልገው የታየር ፕሮቴክተር መጠን ለማወቅ በጎማው ስፋት መጠን የሚሰራ የራሱ የሆነ ሂሳባዊ ቀመር (Formula) መኖሩንም ከኃላፊዎቹ ገለፃ መረዳት ተችሏል።

 

 ምርቱ በጄል መልክ ፋይበር ፓልምስ እና ከቲክ ጄል ከተባሉ ግብዓቶች የተዘጋጀ ሲሆን በጎማ ውስጥ በተፈለገው ደረጃ ከተሞላ በኋላ የሚሰራ መሆኑ ተመልክቷል። ምርቱ ከብሪታኒያ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የተዋወቀው ታየር ፕሮቴክተር ኢትዮጵያ በተባለ ሀገር በቀል ኩባንያ አማካኝነት ነው። ምርቱን ለአሽከርካሪዎችና ለተሽከርካሪ ባለቤቶች ለማስተዋወቅ ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በተካሄደው ፕሮግራም ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ውጤታማነቱን የሚያሳይ በተግባር የተፈተሸ የማሳያ ሥራም ተከናውኗል።

 

በዕለቱ የተዘጋጀ ተሽከርካሪ በጣውላ ላይ በተመቱ ሹል ሚስማሮች ላይ እንዲሄድ በማድረግ ታየር ፕሮቴክተር ጄልን የተሞላ ጎማ በስለትም ሆነ በሹል ነገር ቢወጋ የማይተነፍስ ብሎም የማይፈነዳ መሆኑን እንዲታይ ተደርጓል። የትራንስፖርት አቅራቢ ባለቤቶችም ለሙከራ ያህል የራሳቸውን ተሽከርካሪ ይሄንኑ ጄል በማስሞላት ሞክረው ውጤቱን እንዲያዩ ተደርጓል።

 

ይሄው ታየር ፕሮቴክተር የተባለው ምርት የአንድ ተሽከርካሪ ጎማ በሙቀትና ቅዝቃዜ ወቅት የሚከሰተውን ለውጥ ተከትሎ የሚፈጠረውን መዋዠቅም ያስቀራል ተብሏል። በዚህም ጎማው በሙቀት ምክንያት ተለጥጦ ጥንካሬውን እንዳያጣ፣እንደዚሁም በቅዝቃዜ ወቅትም እንዳይኮማተር በማድረግ እድሜው እንዲራዘም የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።

 

በዕለቱ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት የድርጅቱ ኃላፊ የቀድሞ ሜጀር ጄነራል ባጫ ደበሌ እና የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጁ አቶ ሳሚ ሚሊዮን፤ ይህ አሁን ወደ ሥራ እየገባ ያለው ምርት አንድ ጎማ ከተመረተ በኋላ በኩባንያው የተቀመጠለትን የዕድሜ መጠን በሚገባ እንዲያገለግል የሚያደርገው መሆኑን አመልክተዋል።

 

 ጥቅሙ ከኩባንያዎችና ከግለሰብ አሽከርካሪዎች ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑም ተመልክቷል። በዕለቱም ከተሰጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው በኢትዮጵያ ካለው ከፍተኛ የጎማ ፍላጎት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው። የተሽከርካሪ ዓመታዊ እድገት መጠንም ከ30 በመቶ በላይ መድረሱን ተከትሎ ይህ ፍላጎት የበለጠ እያደገ የሚሄድ መሆኑም ተመልክቷል። የጎማ ፍላጎቱ እያደገ ቢመጣም ሀገር ውስጥ የሚገቡት ጎማዎች አምራች ኩባንያው ያስቀመጠው የአገልግሎት ዘመን ሳይደርሱ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከጥቅም ውጪ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ መሆናቸውን ሜጀር ጄነራል ባጫ አመልክተዋል።

 

ሆኖም ይህ አዲሱ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ጎማዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው በተገቢው ጊዜ እንዲያጠናቀቁ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገለፃ ከማድረግ ባለፈ በተግባር እንዲታይም አድርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በጎማ ፍንዳታ የሚከሰት አደጋ እንዳይኖርም በማድረግ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የሚኖረው መሆኑም ተመልክቷል። ከጎማ አየር መቀነስ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ብክነት እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ በአሁኑ ሰዓትም ከ80 በላይ በሆኑ ሀገራት ምርቱ ጥቅም እየሰጠ ነው ብለዋል።

 

 ከኃላዎቹና ከባለሙያዎቹ ገለፃ በኋላ በተሰብሳቢዎች በኩል የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም ምርቱ የት ይገኛል? በማንስ በኩል ይሞላል? በዚህ በኩል በተሰጠው ምላሽ  ምርቱን በጎማ ውስጥ በመሙላቱ ረገድ ስልጠና መስጠት ስለሚያስፈልግ ለጊዜው እንዲሁ የሚሰራጭበት ሁኔታ የማይኖር መሆኑን ሜጀር ጄነራል ባጫ አመልክተዋል።

 

 ከዚሁ ጋር በተያያዘም ንዑስ አከፋፋዮችን ጨምሮ በየጎሚስታው የሚሰሩ ባለሙያዎችም ምርቱን እንዴት ጎማ ውስጥ እንደሚሞሉ ሥልጠና የሚሰጣቸው መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል። ሥልጠናውን ሳይወስዱ ምርቱን ግብዓት ውስጥ ለመሙላት መሞከር ከመጠኑ በላይ ወይንም በታች መሙላትን ስለሚያስከትል በዚያው መጠን የሚከተል ጉዳትም ይኖረዋል ተብሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን ምርቱ በተገቢው መልኩ ካለመሞላቱ ጋር በተያያዘ የተባለውን የጎማ ጉዳት መከላከል ባይችል ተገልጋዩ በምርቱ ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬን እንዲያሳድር የሚያደርገው መሆኑንም በገለፃው ተመልክቷል። ይህም በመሆኑ ለጊዜው ኩባንያው ራሱ ባሉት ባለሙያዎች አማካኝነት በሚጠራባቸው ቦታዎች በመሄድ ጎማዎችን የመሙላት ሥራን የሚሰራ መሆኑን በተሰጠው ማብራሪያ ተጠቁሟል።

 

 ይሁንና ኩባንያው ከሚኖረው ሰፊ ፍላጎትና ከሥራ ፈጠራም አንፃር በቀጣይ ሥልጠና በመስጠት ሌሎች ይሄንኑ አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ ባለፈ በቋሚነት የመሙላት ሥራን አይሰራም ተብሏል። ሀገር ውስጥ ያሉትን ከለመዳሪ አልባ ጎማዎችን ለመሙላትም እስከ 30 ሺህ የሚደርስ ሰራተኛ የሚያስፈልግ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም ከሥራ እድል ፈጠራም አኳያ በቀላሉ የማይታይ መሆኑን የቀድሞ ሜጀር ጀኔራል ባጫ አመልክተዋል።

 

ከጎማ ጋር በተያያዘ ከሚሰሩት የጎሚስታ ባለሙያዎችን በማብቃት በጋራ የሚሰራ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። ኩባንያው ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለትልልቁ ኩባንያዎችም ይሄንኑ አገልግሎት በስፋት ያቀርባል ተብለዋል። “ጎማው አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላ በውስጡ ያለው ጄል በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያደርስ አይችልም ወይ?” የሚል ጥያቄም በተሳታፊዎች በኩል የተነሳ ሲሆን ለዚህም በተሰጠው ምላሽ ምርቱ ከተፈጥሮ ግብዓቶች የተሰራ በመሆኑ በመጨረሻ ምንም አይነት የሚያደርሰው አካባቢያዊ ጉዳት የለም ተብሏል። አገልግሎቱም ከለመዳሪ አልባ ለሆኑ የተሸከርካሪ ጎማዎች ብቻ ነው ተብሏል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
248 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us