በበርካታ ዘርፎችና ድርጅቶች ዙሪያ መረጃ ይሰጣል የተባለ “8143” የጥሪ ማዕከል ስራ ጀመረ

Wednesday, 16 August 2017 11:51

 

በተለያዩ ዘርፎች አስፈላጊውን መረጃ በአፋጣኝ ለመስጠት የተቋቋመው “8143” የተሰኘ ሀገር በቀል የጥሪ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ። ራሱን በሀገሪቱ ከሚገኙ ቁጥር አንድ የመረጃ አቀባዮች ተርታ በማስቀመጥ እየሰራ ይገኛል የተባለው ይህ ድርጅት፤ በመኪናና ቤት ሽያጭ፣ የስራ ማፈላለግ፣ የሲኒማ ቤት አድራሻና የፊልም አይነቶችን፣ የብሔራዊ ፈተና ውጤቶችንና የዩኒቨርስቲ የጥሪ ቀናትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ለሚቀርብለት ጥያቄዎች ከጥሪ ማዕከሉ መልስ እንደሚሰጥ የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጁ እና ባለቤት አቶ ዮሴፍ ሃይሌ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀርመኒ ሆቴል ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

 

በአሁኑ ወቅት ከመሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት እና ዳኒ ግራናት ቀለም ድርጅት ጋር አጋር በመሆን ስለድርጅቶቹ ለመረጃ ፈላጊዎች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በቀጣይም ማንኛውንም አይነት ድርጅት፤ ኮንሰርትና ኤቨንት የሚያዘጋጁ ተቋማት በተመለከተ በሚፈፀም ህጋዊ ውል መሠረት መረጃ ለመስጠት እየተሰናዱ እንደሚገኙም ሰምተናል። በ2010 የትምህርት ዘመን ለ15 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት መሣሪያዎችን ድጋፍ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የመሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሠረት አዛገ በበኩላቸው ይህን መሰሉ የመረጃ ማዕከል ስለድርጅታችን ያለውን የመረጃ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ የተሻለ ተደራሽ እንደሆኑ እንደሚያግዛቸው ተስፋ አለኝ ብለዋል።

 

በ“8143” ተመዝግበው መረጃዎቻቸው ለፈላጊው ህብረተሰብ እንዲደርስላቸው የሚፈልጉ ተቋማት ህጋዊነታቸው ብቻ አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ ለመመዝገብ ምንም አይነት ክፍያ እንደማይጠይቁም ገልጸዋል። የጥሪ ማዕከሉ በአንድ ጊዜ እስከ አስራ አምስት ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በቀንም 14 ሰዓታት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። መረጃውን ፈልገው ወደጥሪ ማዕከሉ የሚደውሉ ሰዎች በመደበኛ የስልክ አገልግሎት ክፍያ እንደሚቆጥርባቸውም ተነግሯል።

 

ጥሪ ማዕከሉ አሁን ካሉት ደንበኞች በተጨማሪ ሌሎችም ተቋማት አብረውት እንዲሰሩ እንደሚፈልግና በቀላሉም መረጃዎችን ለፈላጊው ማድረስ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፤ በተጓዳኝም ስራና ሰራተኛን ማገናኘት፤ የጠፋ አድራሻዎችን መጠቆም የፍቅር አለፍ ሲልም የትዳር አጋርን እስከማፈላለግ እንደሚያገለግል ተገልጿል። በጥሪ ማዕከሉ አማካኝነት ተገናኝተው ወደተሳካ የፍቅር ግንኙነት የገቡ ሰዎችን በአንድ ላይ የመዳር ሃሳብ እንዳላቸውም በመግለጫው ላይ ሲነገር ሰምተናል።

 

አጠቃላይ ወጪ ከ460 ሺህ ብር በላይ እንደሆነ የተነገረለት ይህ የጥሪ ማዕከል፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል። አጋር ለመሆን ምንም አይነት ክፍያ አለመኖሩን ያስታወሱት አቶ ዮሴፍ፤ በቀጣይም ከበርካታ ድርጅቶች ጋር በመስራት የህብረተሰባችንን የመረጃ ፍላጎት እናሟላለን ብለዋል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
118 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us