የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናስ ፍላጎት ንረትና የወጪ ቁጠባ ፈተና

Wednesday, 13 September 2017 12:08

 

በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ ተስፋፍቶ የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ በመንግስት በኩል ተደርሶባቸዋል ከተባሉት የችግሩ ምንጮች መካከል አንደኛው በሀገሪቱ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች መኖራቸው ነው። ይህንንም ድምዳሜ ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በ2009 የሁለቱ ምክርቤቶች መክፋቻ ስበሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት ወጣቶችን ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚያስችል የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ዝግጁ ያደረገ መሆኑን በመግለፅ ይህም የገንዘብ በየክልሉ በድርሻ የሚከፋፈል መሆኑን አመለከቱ። የፕሬዝዳንቱ የመስከረም ወር መጨረሻ 2009 ንግግርን ተከትሎ ይህንን የወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድን የሚመለከተው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ  በዚያው ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር። በዚህ አዋጅ መሰረትም በሀገሪቱ የሚገኙና እድሚያቸው ከ18 እስከ 34 ያሉ ወጣቶች የፈንዱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።

 

ይህንንም የፈንድ አዋጅ መፅደቁን ተከትሎ በየክልሉ የሚገኙ በአዋጁ የተመለከቱትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ተደርጓል። በዚህም ከሶስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን በየክልሉ በገጠርና በከተሞች የተመዘገቡ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ ይህ ገንዘብ ከፌደራሉ መንግስት የሚለቀቅ መሆኑ ሲገለፅ ከወራት በፊት ለፓርላማው በቀረበቀው በጀት ውስጥ ተካቶ የፀደቀ ግን አልነበረም።

 

 ይህም በመሆኑ በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲገባ ለክልሎች የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን በተመደበላቸው የክፍፍል መጠን ሆኖ አልተገኘም። ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ክልል የተመደበለትና የተለቀቀለት የገንዘብ መጠን ሊመጣጠን ባለመቻሉ ለስራ ፈጠራ የመዘገባቸውን ወጣቶች ለማስተናገድ የተገደደው  ከመደበኛ በጀቱ በመቀነስ ነበር። ለአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የተመደበው የገንዘብ መጠን ወደ 419 ሚሊዮን ብር ሲሆን በዚህም ወጣቶች እንዲጠቀሙ የተደረገው 17 ሚሊዮን ብሩን ብቻ ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ በመንግስት የተገባው ቃልና በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲወረድ የታየው እወነታ ፈፅሞ የሚገናኝ ሆኖ አልታየም።

 

የመንግስት የፋይናስ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ከማደጉ ባሻገር የገቢው መጠን ደግሞ በዚያው መጠን አሽቆልቁሏል። በዚህ በኩል በተለይ በውጭ ምንዛሪ የታየው ማሽቆልቆል ከዓመት ዓመት እየከፋ ሄዷል። ከዚህም በተጨማሪ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ያለፈችብት ህዝባዊ ዓመፅም ኢኮኖሚውን ክፉኛ ጎድቶታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የደመወዝተኛው የደመወዝ ግብር ዝቅ እንዲል መደረጉ ለመንግስት ገቢ መውረድ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። መንግስት የደመወዝ ግብርን ሲቀንስ ይሄንኑ ያጣውን ገቢ የሚያተካኩ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ታሳቢ በማድረግ ነበር። ከእነዚህም ታሳቢ የገቢ ምንጮች መካከል አንዱ ተደርጎ የተወሰደው በአዲስ መልኩ የተሻሻለውን የገቢ ግብር አዋጅ ተከትሎ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረግን ነበር።

 

 መንግስት የቀን ገቢ ግምቶችን ማሻሻያ የሚያደርገው በየስድስት ዓመቱ ሲሆን በተሻሻለው አዋጅ መሰረት የቀን ገቢ ግምት በየሶስት ዓመቱ እንዲሆን ተደንግጓል።  በሳላፍነው ዓመት የመንግስት የቀን ገቢ ግምት ማሻሻያ ወቅት ስለነበር የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ የተካሄደው ግምት የማወጣት ስራ በርካታ የንግዱን ማህበረሰብ አስቆጥቷል። ይህም ጉዳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲያወዛግብ ከመቆየቱም ባሻገር በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል የንግድ ስራን እስከማቆም የዘለቀ አድማ እንዲካሄድ አድርጓል። የመንግስት የገቢ ፍላጎት ንረት ገቢውን ለመሻሻል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የወጪ መጠኑንም ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

 

 በዚህም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቀነስ የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም መመሪያ ተግባራዊ የሚሆን ከሆን የመንግስትን ወጪ በመቀነስ በገቢውና በወጪው መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አይነቱ አካሄድ ከኢህአዴግ መንግስት ቀደም ካለ ታሪክ አንፃር ሲታይ ከወጪ አኳያ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። መንግስት ገቢውን ከፍ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ በርካታ ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት ወጪው በከፍተኛ ደረጃ እየናረ መሄዱን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ገቢውን ለማሳደግና ወጪውን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ነው። ከውጪ አንፃር ባለፉት ጊዜያት ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀላል የማይባል ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የድርቁ ሁኔታ ቀላል የማይባል ገንዘብን መጠየቁም አንዱ ፈተና ነበር። እነዚህና ሌሎች የኢኮኖሚው ተግዳሮቶች መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ያፀደቀውን የ10 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንኳን በተፈለገው መጠን እንዳይለቅ አድርጎታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
153 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us