የንግዱ ዘርፍ የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ጅምር

Wednesday, 20 September 2017 13:52

 

Economyየኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ ለተነሱ ችግሮች የራሱን ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ይህ ድጋፍ ወጥነት በሌለው መልኩና ለጊዜያዊ ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ በዘለቄታዊነትና ቀጣይነት ባለው አሰራር የተደገፈ አልነበረም። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባለፉት ጊዚያት የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበር ለድርቅ ተጎጂዎች እንደዚሁም ከሳዑዲ ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

 

 ይሁንና ለመሰል ችግሮች ቋሚ የሆነ ድጋፍ ለማድረግና ዘለቄታዊነት እንዲኖረው በማሰብ “የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድን” ለማቋቋም ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።  ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ተወካዮችና ኃለፊዎች  በያዝነው ሳምንት አንድ ስብሰባ በማካሄድ በማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ ማቋቋማያ ቻርተር ላይ ገለፃና አጠር ያለ ውይይት ተካሂዷል። በዚሁ ረቂቅ ቻርተር መሰረት የግሉ ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሚኖራቸው ሙሉ በሙሉ ፈቃደኝነቱ ባላቸው  የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ወይንም ተቋማት መሆኑን ተመልክቷል።

 

ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ የሚኖሩት ተግባራትም በዚሁ ረቂቅ ቻርተር ላይ በዝርዝር ተቀምጧል። በዚህም ቻርተር መሰረት የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ፤ በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ከሥራና ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እገዛ ያደርጋል ተብሏል። ለሀገሪቱና ለህዝቡ የሚጠቅሙ የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን መደገፍም አንዱ የዚሁ ፈንድ እገዛ አካል ተደርጎ ተወስዷል። አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንደዚሁም ዘመናዊ የግብርና ሥራዎች በሀገሪቱ እንዲስፋፉም በማህበራዊ ኃላፊነት ልማት ፈንዱ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ዘርፎች ተደርጎ ተወስዷል። ይህ በቀጣይ የሚቋቋመው የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነ የራሱ ቢሮ የሚኖረው መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ተቋሙን የሚመራና የሚያስተዳደር ቦርድ የሚኖረው መሆኑም ተመልክቷል። የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ የበላይ አካል ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚሆን በዚሁ ገለፃ የተመለከተ ሲሆን ጉባኤውም ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱን ዓመታዊ በጀትና የሥራ መርሃ ግብር ማፅደቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሂሳብ መዛግብትንና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችንም የሚመረምር የውጭ ኦዲተርን የመሾም ስልጣንም የተሰጠው ለጠቅላላ ጉባኤው ነው። ጉባኤው እንደ ሁኔታውና አግባቡም ሥልጣኑን በውክልና ለቦርዱ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩም በዚሁ ረቂቅ ቻርተር ላይ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በዚሁ ዙሪያ በሰጡን ማብራሪያ የግሉ የንግድ ማህበረሰብ ይህንን ፈንድ በማገዙ ረገድ በቀጣይ ከሚኖረው ድርሻና ኃላፊነት ባሻገር የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ተሳታፊ የሚሆንበት አሰራርም ይኖራል። እንደሳቸው ገለፃ በቀጣይም ከ2 መቶ ያላነሱ የመስራች ጉባኤ አባል ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 በእርግጥ በኢትዮጵያ በቁጥር በርካታ የንግድ ማህበረሰብ ክፍሎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት የሆኑት ግን ውስን ናቸው። ከዚህ አንፃር ምክር ቤቱ ምን ያህል ሰፊውን የንግድ ማህበረሰብ ሊያንቀሳቅስ ይችላል የሚል ጥያቄም ተነሰቶ ነበር።

 

አቶ ሰለሞን በዚህ በኩል አንድ ዜጋ ወገኑን ለማገዝ ሰብአዊነትንና ቁርጠኝነትን ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ምክርቤቱ ከአባላቱ ውጪ የሆኑትን የንግድ ማህበረሰብ አካላት የማንቀሳቀስ ብሎም የማስተባበር አቅሙ ያለው መሆኑን አመልክተዋል። እያንዳንዱ ነጋዴ ለዚህ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ለሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚሰጠው የገንዘብ መጠን ብዙም በወጪ ደረጃ ሊታይ የማይችል መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ሆኖም ብዙዎች ከተሳተፉበት የሚኖረው ድጋፍ በቀላሉ የማይታይ መሆኑን አመልክተዋል። “አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ቀድሞውኑ የራሳቸው የማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት አሰራር የዘረጉ በመሆኑ፤አሁን በምክር ቤቱ ሊቋቋም የታሰበው የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ከሌሎች ጋር የስራ መደራረብን የሚፈጥርበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም ወይ?”  የሚል ጥያቄም ለአቶ ሰለሞን ተነስቶላቸው ነበር።

 

 እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ ሌሎች ቀደም ሲል በተናጠል የሚሰሯቸውን የማህበራዊ ኃላፊነቶች እንደተጠበቁ ባለበት ሁኔታ በዚህኛው አዲሱ የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት እድሉም ክፍት ነው። አዲሱ የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ የንግዱን ማህበረሰብ ኪስ በማይጎዳና ሀብትን በማቀናጀት የሚሰራ በመሆኑ ከሌሎቹ የቀደሙ አሰራሮች የተለየ ነው። ሌላው ለአቶ ሰለሞን የተነሳላቸው ጥያቄ “የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት የግሉን ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ለማቋቋም አልዘገየም ወይ?” የሚል ነው። እንደሳቸው ገለፃ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የእድሜ ቆይታ ከደርግ መንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞ አጭር በመሆኑና የግሉም ዘርፍ የራሱን አቅም ለመገንባት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲሰራቸው ከነበሩት ሥራዎች አንፃር የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱን የማቋቋሙ ሥራ ዘገየ ሊባል የሚችል አይደለም።

 

 

Last modified on Wednesday, 20 September 2017 17:26
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
134 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 139 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us