ሁጁዋን ጫማ አምራች ለአንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሥራ እፈጥራለሁ አለ

Thursday, 28 September 2017 14:17

 

በኢትዮጵያ ግዙፉ ጫማ አምራች ኩባንያ የሆነው ሁጁያን ኩባንያ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለአንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ኩባንያውን ጠቅሶ የቻይና የዜና ወኪል ዤንዋ ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል።

 

 በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚሰተር ሻሪ ዛንግ ጋር ቆይታ ያደረገው ይሄው የዜና ወኪል፤ ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ለ 4 ሺህ 2 መቶ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን አመልክቷል።

 

 በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመትም ይህንን የሰራተኛ ቁጥር ወደ 6 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። በሂደት ግን የኩባንያውን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማስፋት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለአንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድልን የሚፈጥርበትን ሁኔታ መኖሩን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ካለባቸው በርካታ ሀገራት መካከል  ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ሀገሪቱ  የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት ኩባንያው የራሱን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል። ሁጁዋን ኩባንያ ሠራተኞችን ከመቅጠር ባለፈተቀጣሪዎች በስልጠና ክህሎትን እንዲያዳብሩ ብሎም ከአሰሪዎቻቸው ጋር መግባባት እንዲችሉ መሰረታዊ የቻይንኛ ቋንቋ እንዲማሩ የሚያደርግ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

 

 ከዚህም በተጨማሪ ሠራተኞች የዘመኑን የጫማ አመራረት ቴክኖሎጂ ልምድን በመቅሰም በራሳቸው የስራ ፈጠራ በግላቸው እንዲሰሩ ጥረት እያደረገም ነው ተብሏል። በቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ ትብብር የፋይናስ እገዛ የሚደረግለት ይህ ግዙፍ ኩባንያ በቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም አማካኝነት እውን እንዲሆን የተደረገ ነው። የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ፎረም ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
117 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ ፀጋው መላኩ

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us