በቂ ምላሽ ያላገኘው የተሽከርካሪና የወፍጮ ባለንብረቶች የግብር ቅሬታ

Thursday, 28 September 2017 14:20

 

ከግብር አጣጣልና ክፍያ ጋር በተያያዘ በንግዱ ማህበረሰብና በታክስ አስከፋዩ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መካከል አለመግባባቶች ከተፈጠሩ ዋል አደር ብለዋል። የያዝነው ዓመት የግብር ውዝግብ የተነሳው አዲሱን የቀን ገቢ ግምት የተንተራሰ የግብር አጣጣልን ተከትሎ በርካቶች በእጅጉ የተጋነነ ግብር የተጣለባቸው መሆኑን በመግለፃቸው ነው። ያም ሆኖ በርካታ ቅሬታዎች ተሰምተውና ለአቤቱታዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸው የሚበዛው የንግድ ማህበረሰብ የግብር ግዴታውን በአግባቡ የተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይሰማሉ።

 

በግብር አጣጣሉ ዙሪያ ቅሬታ እያሰሙ ካሉት የንግድ ማህበረሰብ አካላት መካከልም የትራንስፖርት አገልግሎት ባለንብረቶች እንደዚሁም የእህል ወፍጮ ሥራ ላይ የተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩት የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች የተጣለባቸው የግብር መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። በዚሁ ዙሪያም ባሳለፍነው ሰኞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለንብረቶችና ከወፍጮ ቤት ባለቤቶች ጋር ሰፋ ያለ ውይይትን አካሂዷል።

 

 በእለቱም በነጋዴዎቹ በርካታ ቅሬታዎች ተነስተዋል። ከተነሱት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መካከልም የግብር ትመናው ግልፅ አይደለም። በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ክልሎች ያለው የግብር አጣጣል ወጥነት የሌለው ነው። የግብር ደንቡ የወጣው ነጋዴው ሳይመክርበት ነው። በርካታ ተሽከርካሪዎች ያላቸው የአገልግሎት አቅም (Performance) የተለያየ ሆኖ ሳለ፤ የግብር አጣጣሉ ግን አንድ አይነት ነው።ተሽከርካሪዎች የሚሰሩበት ቀን ውስን ቢሆንም የሚጣልባቸው ግብር ግን ዓመቱን ሙሉ እንደሰሩ ተደርጎ በ365 ቀናት በማባዛት ነው፣ ካሽ ሬጂስተር ለነጋዴው ቢሰጥም ግብሩ የሚሰራው ግን የካሽ ሬጂስተርን መረጃ መሰረት ያደረገ አይደለም የሚሉትና ሌሎች በርካታ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።

 

ነጋዴዎቹ ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል ሲከፍሉት የነበረውን የግብር መጠን በመግለፅ በዘንድሮው ዓመት እንዲከፍሉ የተጠየቁትን ብሎም የከፈሉትን የግብር መጠንም በንፅፅር አሳይተዋል። በዚሁ ዙሪያ አንድ የወፍጮ ቤት ባለቤት ባቀረቡት ቅሬታ ከዚህ ቀደም 645 ብር ዓመታዊ ቁርጥ ግብር ሲከፍሉ የነበረ መሆኑን ገልፀው ሆኖም በአዲሱ የግብር ተመን የተጣለባቸው የግብር መጠን ግን ወደ 11 ሺህ 834 ብር ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል።

 

አቶ አረቡ አልየ ይባላሉ። የሁለት ደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ባለንብረት ናቸው። ነዋሪነታቸው በአዳማ ከተማ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጡት በዚሁ የገቢዎችና ጉምሩክ ስብሰባ ለመካፈል መሆኑን ገልፀውልናል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባገኘናቸው ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ የመጨረሻው የስብሰባው ውጤት ከተስፋ የዘለለ ሆኖ እንዳላገኙት ገልፀውልናል። በግብር አጣጣሉ በኩል በተለይ ወጥነት የሚታይበት ሆኖ አለመገኘቱ አንዱ የቅሬታቸው ምንጭ ነው። እሳቸው ግብር የሚከፍሉት በሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎቻቸው ነው። ሁለቱም ተሽከርካሪዎቻቸው አንድ አይነት ሞዴል፣ የመጫን አቅምና የስሪት ዘመናቸውም ተመሳሳይ ቢሆንም፤ የሁለቱ ተሽከርካሪዎች ፋይል በተለያየ ክፍለ ከተሞች በመገኘቱ ብቻ የተለያየ ግብርን የሚከፍሉበት ሁኔታ መፈጠሩን በመግለፅ፤ ይህም የግብር አጣጣሉ ምን ያህል ወጥነት የሌለውና በአጣጣሉ ሂደትም ታሳቢ ተደርጎ የሚወሰደው ግብዓት ምን እንደሆነ ያልገባቸው መሆኑን ገልፀውልናል።

 

አንድ ተሳታፊም ባለፈው በጀት ዓመት 18 ሺህ ብር ግብር ከፍለው በያዝነው ዓመት ግን 98 ሺህ ብር የተጠየቁ መሆኑን አመልክተዋል። የግብሩን መብዛት አቤቱታ ባቀረቡበት ወቅትም መጠኑ ብዙም ዝቅ ሳይል 81 ሺህ ብር እንዲከፍሉ የተደረገ መሆኑን ባለንብረቱ አመልክተዋል። ተወያዮቹ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከተው አካል ቀድሞውኑ ጠርቶ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ አለማድረጉንም ጭምር በማንሳት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። የተሽከርካሪዎቹ ግብር አጣጣል በሚጭኑት አቅም መጠን ሲሆን በጭነት ልክ ግብራቸው የማይወሰን እንደዚሁም ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ ሞተር የሌላቸው ተሳቢዎች ጉዳይም ተነስቷል። በዚህ ዙሪያ የታየውን ችግር ለመፍታት በየቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ሰርኩላር የሚተላለፍ መሆኑን ከመድረኩ በኃላፊዎች በተሰጠው ገለፃ ተመልክቷል።

 

በሌላ በኩል ከመድረኩ በተሰጠው ምላሽ በተሽከርካሪዎቹም  አገልግሎት ላይ የተጣለው የግብር ማሻሻያ መነሻ በ1997 ዓ.ም የነበረውን የግሽበት መጠን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ተመልክቷል። በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የታየው ወጥነት የሌለው የግብር አወሳሰን አሰራርም በስህተትነት ተወስዶ በቀጣይ ማስተካከያ የሚደረግበት መሆኑን ከመድረኩ በተሰጠው ማብራሪያ ተገልጿል። ግብሩን ለመወሰን ለጊዜው ስራ ላይ የዋለው የግሽበት ማስተካከያ (Inflation Adjustment) ለአጭር ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚሆን የተመለከተ ሲሆን በቀጣይ የሚለወጥበት አሰራርም ይኖራል ተብሏል። ተወያይ ነጋዴዎቹ በበኩላቸው ግሽበት ታሳቢ ተደርጎ ግብሩ ከተጣለ በዚሁ ግሽበት እንደ ነዳጅ፣ ጎማ፣ ቅባትና የመሳሰሉት የተሽከርካሪዎቻቸው ግብዓቶችም ዋጋ ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ እየናረ በመሄዱ ይህም ጉዳይ አብሮ ሊታይ ይገባው የነበረ መሆኑን አመልክተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
127 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 141 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us