ወጋገን ባንክ 805 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረገበትን የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንጻ አስመረቀ

Wednesday, 04 October 2017 12:33

 

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከአራት ዓመታት በላይ የወሰደው የወጋገን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ ባሳለፍነው ቅዳሜ (መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም) የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ተመርቋል። በአዲስ አበባ ስቲዲየም አካባቢ በ1ሺህ 800 ስኩዬር ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ይህ ህንፃ ከመሬት ያለው ከፍታ 107 ሜትር ሲሆን፤ ሶስት የተሽከርካሪ (መኪና) ማቆሚያ ወለሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 33 ወለሎች እንዳሉትም ተሰምቷል። ህንጻው የአካባቢ ብክለትን የሚከላከልና ለአካባቢውም ተጨማሪ ውበት እንደሚሰጥም የህንጻውን ዲዛይንና የማማከር ስራ የሰራው ሀገር በቀሉ ኢቲጂ ዲዛይነርስ ኤንድ ኮንሰልታንትስ ፒ.ኤል.ሲ ስራ አስኪያጅ በምረቃው ወቅት ሲናገሩ ሰምተናል። በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ ፕሮዝዳንት፤ “የወጋገን ባንክ በዋና ከተማችን እምብርት ላይ ያስገነባው ይህ ውብ ህንፃ የዘርፉን አጠቃላይ እምርታ እንዲሁም የባንኩን ከፍተኛ ዕድገት የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ ዕድገቱ ለባንኩ ባለአክሲዮኖች ብቻ ሳይሆን፤ ለብሔራዊ ኢኮኖሚውም ከፍተኛ እሴት የሚጨምር በመሆኑ በአገሪቱ የመልካም ገፅታ ግንባታ አስተዋፅኦው እጅግ የጎላ ነው” ብለዋል።

 

የወጋገን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ መጠናቀቅ ባንኩን ከቢሮ ኪራይ ያዳነው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ አጠቃላይ የግንባታው ወጪም 805 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል። ህንጻውን በመገንባት ረገድ የቻይናው ጃያንግዢ ኮርፖሬሽን ፎር ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኒካል ኮፐሬሽን የተባለ ተቋራጭ መሆኑም ተገልጿል። ህንጻው 8 የመወጣጫ አሳንሱሮች የተገጠሙለት ሲሆን፤ የደህንነት መቆጣጠሪያ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የሙቀትና የቅዝቃዜ መቆጣጠሪያና ዘመናዊ የህንፃ አስተዳደር ስርዓት ያለው መሆኑን ተነግሯል።

 

የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ የተመረቀው ይህ ህንፃ ከቢሮ አገልግሎት በተጨማሪ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ለሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጥ ካፍቴሪያና ለሱቅ የሚሆኑ የሚከራዩ ክፍሎች አካቶ የያዘ መሆኑም በምረቃው ወቅት ተመልክቷል። ከዚህም ባሻገር እስካሁን በአዲስ አበባ ከተገነቡት ህንጻዎች በርዝመቱ አቻ የማይገኝለት እንደሆነም ሰምተናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
214 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us