ዘርፈ ብዙ መልክን እየያዘ የመጣው የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት

Wednesday, 04 October 2017 12:25

 

የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ወደሆኑ ግንኙነቶች በማደግ ላይ ነው። ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚያዊ ብሎም በፖለቲካዊና ወታደራዊ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር ውስጥ በመግባት ላይ ናቸው። ሀገራቱ በብዙ ዘርፎች በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶችን የተፈራረሙ ሲሆን በዚሁ ዙሪያ የተወከሉ አስፈፃሚዎችም ስራቸውን በመስራት ላይ ናቸው። እንደ ሱዳን ዜና አገልግሎት(SUNA) ዘገባ ከሆነ የኢኮኖሚውን ዘርፍ የሚመለከተው የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ይገናኛሉ።

 

በኢኮኖሚ የጋራ ትብብር ኮሚቴው የሱዳን ልዑካን መሪ የሆኑት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሃሳቦ ሞሀመድ ብደራህማን የኢትዮ ሱዳን  ኢኮኖሚያዊ  ግንኙነትን በተመለከተ ከሰሞኑ በካርቱም  ቤተመንግስት በተካሄደ የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ የሱዳኑ የገንዘብና የኢኮኖሚ ፕላን ሚንስትር የኢትዮ-ሱዳን የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ መሆኑ ታውቋል።

 

በተለይ ሰፊውን የማብራሪያ ክፍል የያዘው ቀደም ባሉት ጊዜያት በሁለቱ ሀገራት መካከል ስለተፈረሙት የመግባቢያ ስምምነቶች መሆኑን የዜና ወኪሉ ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል። እዚህም የመግባቢያ ስምምነቶችን ተንተርሶ የጋራ ትብብሩ የኢኮኖሚ ልማት ወደ መሬት የሚወርድበትን ጉዳይ በተመለከተ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉ ተመልክቷል። ሀገራቱ በመሪዎቻቸው ደረጃ ግንኙነቶቻቸውን ጠንካራ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የሚካሄደው በአዲስ አበባ የሚካሄደው የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ውይይቱ እንደ ባቡር መስመር ግንባታ ብሎም በፖርት ሱዳን ወደብ አጠቃቀም ዙሪያ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

 የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በየሀገራቱ ተከታታይነት  ያላቸው ይፋዊ ጉብኝቶችንም አድርገዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሁለቱን ሀገራት የግንኙነት ለውጥና እድገት የሚያሳዩ የተወሰኑ አንኳር፣ አንኳር ነጥቦችን ተመልክተናል።

 

ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ከመንግስታት ትብብር ባለፈ ወደ ህዝባዊ ትስስርም ጭምር ለማሳደግ ሀገራቱ በጅምርነት እየሄዱባቸው ያሉ ሥራዎች አሉ። በዚህ በኩል የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት፣ የሚዲያ ሰዎች እንደዚሁም የሙዚቃ ቡድን አባላት ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝቶችን ከማካሄድ ባሻገር ሰራዎቻቸውን ሳይቀር ያቀረቡባቸው ሁኔታዎች አሉ። በኢትዮጵያኖችም በኩል ወደ ሱዳን በመሄድ ተመሳሳይ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቷል።

 

የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት አሁን ባለበት ደረጃ እየሰፋ ከሄደ ለምስራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ ትስስር በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ግንኙነት ሊሆን ይችላል የሚሉ ተንታኞች አሉ። የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር መገለጫ ተደርገው ከሚጠቀሱት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የንግድ ልውውጥ ነው።

 

ከሀገራቱ የግንኙነት እድሜ አኳያ ሲታይ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ብዙም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በድንበር አካባቢ ካለው የአካባቢው ነዋሪዎች ግብይት ባለፈ በመንግስታቱ የጋራ ሥምምነት የታቀፈና በዚያም የሚመራ ጠንካራ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ነበር ብሎ መናገር ያስቸግራል። የንግድ ግንኙነት ሂደቱ እያደገ ሄዶ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ታስገባ የነበረውን የቤንዚን ምርት ሙሉ በሙሉ ከሱዳን እስከማስገባት የደረሰችበት ሁኔታም ነበር። ሆኖም የደቡብ ሱዳን መገንጠልን ተከትሎ 80 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ ምርት በደቡብ ሱዳን ይዞታ ስር ከመቅረቱም ባሻገር የነዳጅን ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተደጋጋሚ ውዝግብ መነሳቱ ኢትዮጵያ ከሱዳን የምታስገባው ነዳጅ ወጥነት ባለው መልኩ እንዳይቀጥል አድርጎታል። ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የንግድ ግንኙነት የታሪፍ ጫናን ለማስወገድ እ.ኤ.አ በ2005 የስምምነት ፊርማቸውን አኑረዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጉምሩክ አሰራራቸውንም የተጣጣመ በማድረግ የንግድ ፍሰቱ እንዲጨምር ተከታታይ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

 

 ይህም ስምምነት በህገወጥ መንገድ ወደ ሁለቱ ሀገራት የሚገቡት የሁለቱ ሀገራት ምርቶችን ጭምር ለመቆጣጠር ያግዛል የሚል ግምት ቢኖርም ወደ ሥራ ሲገባ ግን እስከአሁንም ድረስ በቂ ውጤት አልተመዘገበበትም። በተለይ እንደ ቡና ያሉ ዋና ዋና የሚባሉት የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን እየገቡ ከመሆንም ባሻገር ወደ ሶስተኛ ሀገርም ጭምር የሚሻገሩበት ሁኔታ መኖሩንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

1.የመሰረተ ልማት ትስስር

ሌላኛው ተስፋ የሚጣልበት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሰረተ ልማት ትስስር ነው። ሀገራቱ በዚህ በኩል በሶስት መሰረታዊ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ትስስር ለመፍጠር አጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ቀደም ያሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እነዚህም የመሰረተ ልማት ትስስሮች መንገድ ባቡርና የኤሌክትሪክ ኃይል ናቸው። መንገድን በተመለከተ ሁለቱ ሀገራት በሀለት አቅጣጫ መገናኘት የሚችሉባቸው ዋነኛ የመንገድ አውታሮች አሏቸው። አንደኛው በአዘዞ.መተማ አድርጎ ሰፊ የሱዳንን ግዛት በማቋረጥ እስከ ፖርት ሱዳን የተዘረጋ ሲሆን፤ይህም መንገድ በጋ ከክረምት አገልግሎት የሚሰጥ (all-weather road) ነው። መንገዱ በአሁኑ ሰዓት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ሁለተኛው መንገድ በቤኒሻንጉል ክልል ኩምሩክ ወደ ሱዳን የሚዘልቅ ነው። ይህ መንገድ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን በሱዳን በኩል የሚቀር ግንባታ አለ።ብዙም የተጠናከረ ባይሆንም ከመንገድ ግንባታው ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተጀመረበት ሁኔታ አለ።

 

ሌላኛው የሁለቱ ሀገራት የመሰረተ ልማት ትስስር ማሳያ የሆነው የቴሌኮሙ ዘርፍ ነው። ዋነኛው አለም አቀፉ የቴሌኮም የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል አንደኛው የቀይ ባህር ሜድትራኒያን መስመር ሲሆን ኢትዮጵያም ከዚህ መስመር ጋር ለመገናኘት በአንድ መልኩ በጂቡቲ በኩል መስመሩን የዘረጋች ሲሆን ሁለተኛው መስመር በሰሜን አቅጣጫ ወደ ፖርት ሱዳን የተዘረጋው ነው።

 ይህም መስመር የሁለቱን ሀገራት የቴሌኮም ግንኙነት ጭምር ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል። የትራንስፖርት ግንኙነቱንም በተመለከተ አሁን ውጤት እያስገኘ ከመጣው የመንገድ መሰረተ ልማት ትስስር በተጨማሪ ሀገራቱን በባቡር መሰረተ ልማት ጭምር ለማስተሳሰር ጥናቶች እንዲካሄዱ የሁለትዮሽ ስምምነት ተደርጓል። የባቡር መስመር ተስስሩ እውን የሚሆን ከሆነ ኢትዮጵያን ከሱዳኑ ፖርት ሱዳን ወደብ ጋር የሚያገናኝ ስለሚሆን ሀገሪቱ በጂቡቲ ወደብ ላይ የሚኖራትን ጥገኝነት የሚቀንሰው ከመሆኑም ባሻገር ከጂቡቲ ወደብ በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ከፖርት ሱዳን በኩል በቀላሉ የገቢ ወጪ ንግድ ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸው ይሆናል።

 

የኤሌክትሪክ ትስስርም ሌላኛው የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል ሊወሰድባት የሚችለውን የንግድ ሚዛን የበላይነት የማረገብ አቅም ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል ኢትዮጵያ ለሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይልን ማቅረብ ከጀመረች ዋል አደር ብትልም አሁንም ቢሆን ሱዳን ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ኃይልን ትፈልጋለች።

 የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ለሱዳን በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንዲቻል የዋናው ባለ 5 መቶ ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር በግንባታ ላይ ነው። ኢትዮጵያንና ሱዳንን የሚያገናኘውና  በጎንደር፣ ሸኸዲ፣ መተማ፣ ገዳሪፍ የተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እ.ኤ.አ በ2013 የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የተመረቀ ሲሆን ይህም መስመር ኢትዮጵያ ለሱዳን 1 መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልን በማቅረብ በዓመት ከአንድ መቶ እስከ አንድ መቶ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንድታገኝ ያደረጋት መሆኑን የኦል አፍሪካ ዶት ኮም ዘገባ ያመለክታል።

 

2.የህዳሴው ግድብና ሱዳን

አሁን በግንባታ ላይ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሱዳን ደንበር በአማካኝ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ እንደመሆኑ መጠን የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ግብፅና ሱዳን የግድቡን ሁኔታ በተመለከተ እንዲረዱት ተደርጓል። በዚህ በኩል ሱዳን የግድቡን ፋይዳ በመረዳት ሥጋቷን ከማስወገድ ባሻገር በግድቡ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መስራቱን የመረጠችው ገና ከጅምሩ ነበር። ከዚያም ባለፈ ለግንባታው የሚሆን የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችንም እስከማቅረብም ደርሳለች። በግድቡ ላይ ተደጋጋሚ ስጋቷን እየገለፀች ያለችው ግብፅ፤ ሱዳንም የዚህ አቋም ተጋሪ እንድትሆን ያደረገቻቸው ጥረቶች በሙሉ ፍሬ ሊያፈሩ አልቻሉም።

 

  የወታደራዊው ዘርፍ ግንኙነት

      ሁለቱ ሀገራት ግንኙነቶቻቸውን በማሳደግ የሁለትዮሽ የጋራ ወታደራዊ ፕሮቶኮል እስከመፈራረም ደርሰዋል። የጋራ ሚሊተሪ ኮሚሽንንም አቋቁመዋል። እ.ኤ.አ በ2009 በተደረገ ስምምነት መሰረትም የሁለቱን ሀገራት የጋራ ድንበር ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ የፕሮቶኮል ስምምነትን አድርገዋል። ከዚያ በኋላም ይህ ስምምነት እንዲታደስ ተደርጓል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሁለቱ ሀገራት የጋራ ሚሊተሪ ኮሚሽን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እየተገናኘ ተከታታይ ውይይቶችን ያካሂዳል። በ2009 የተደረገውን ስምምነት ተከትሎም የጋራ ደንበር ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮችን ክትትል ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
196 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 139 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us