የኤክስፖርቱ መውደቅ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የፕሬዝዳን ቱንግግር

Wednesday, 11 October 2017 12:46

 

አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የፌደሬሽን ምክርቤት ሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ የጋራ ስብሰባ ባለፈው ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዷል። በዚሁ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የያዝነውን ዓመት የመንግስት አቅጣጫ የሚያመለክት ንግግር አድርገዋል። የፕሬዝዳንቱ ንግግር ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጭብጦችን የዳሰሰ ነበር። ሆኖም አብዛኛው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ከፖለቲካው ይልቅ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎችን በስፋት የዳሰሰ ነበር። ከእነዚህም የፕሬዝዳንቱ ጭብጦች መካከል አንደኛው የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሽቆልቆልና መፍትሄውን የሚያመላክቱ የዳሰሱት ሀሳብ ይገኝበታል።

 

 የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ አሳሳቢ በሚባል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ በመሄድ በዓመት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከ 3 ቢሊዮን ዶላር በታች ሆኗል። በአንፃሩ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባው ምርትና አገልግሎት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። ይህም ሁኔታ በሀገሪቱ የንግድ ሚዛን ላይ ሰፊ የሆነ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። ፕሬዝዳንቱም በዚሁ ንግግራቸው ቃል በቃል ባለፉት 3 ዓመታት የሀገሪቱ ኤክስፖርት እዛው ባለበት የቆመ መሆኑን በማመልከት፤ ይህም ሁኔታ በሀገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ እጥረት አጋጥሞ የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል። አስመጪዎች ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ለወራት የውጭ ምንዛሪ ወረፋን መጠበቅ መገደዳቸውን ተከትሎ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ለሚቀርቡት ጥያቄዎች ሲሰጥ የነበረው ምላሽ  የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለመኖሩን የሚያመለክት ነበር። ይህ ጉዳይ  በአንዳንድ የብሄራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ሳይቀር ሲገለፅ የቆየ ቢሆንም የፕሬዝዳንቱ ንግግር ግን የኤክስፖርት ገቢው ባለበት መቆሙን፤ይህንንም ተከትሎ የውጭ ምንዛሪው እጥረት መከሰቱን በግልፅ የሚያመለክት ነው።  ፕሬዝዳንቱ መፍትሄ አሰጣጡንም በተመለከተ በያዝነው ዓመት ቁርጥ ያለ መፍትሄ የማያገኝ መሆኑን ቀለል ባለ አገላለፅ ጠቆም በማድረግ አስቀምጠውታል። ይሄንንም ለማመላከት “የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ በከፊልም ቢሆን ለማግኘት” የሚል አገላለፅን መጠቀምን መርጠዋል።

 

 በዚህ ረገድ መንግስት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩትን የተለጠጡ እቅዶች (Ambitious Plans) እያረገበ ለመሄድ የተገደደ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። ዛሬ እጅግ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በታች የወረደው የሀገሪቱ ዓመታዊ የኤክስፖርት ገቢ፤ በ2002ዓ.ም  የሀገሪቱ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይፋ ሲሆን የኤክስፖርት ገቢው በየዓመቱ እያደገ ሄዶ በእቅዱ የመጨረሻ ዘመን ማለትም በ2007 ዓ.ም 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ይደርሳል የሚል ሀሳብ ነበር። ሆኖም ዛሬ ያ እቅድ በዓምስት ዓመት ይቅርና በአስር ዓመቱ ማሳከት የተቻለው ሩቡን ያህሉን ብቻ ነው። ይህ አካሄድ ሀገሪቱ በምን አይነት የኤክስፖርት ገቢ ግኝት ቁልቁለት ውስጥ እንዳለች ከበቂ በላይ ማሳያ ነው። መፍትሄውን በተመለከተ አሁንም ቢሆን የቀደሙት የሀገሪቱ የግብርና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ንግግር በግልፅ ይጠቁማል። እንዲህም በማለት ያስቀምጡታል

 

በመሆኑምየ 2010 እቅድ ዋነኛ ትኩረትም የኤክስፖርት ምርትና ግብይት ጉዳይ የሞት ሸረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድና ለኤክስፖርት ገቢያችን 80 በመቶ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱትን ቡና፣ ሰሊጥ ጥራጥሬ፣ ቅማቅመም አበባና የቁም እንስሳት ላይ በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ሊሆን ይገባል።

 

በኤክስፖርቱ ዘርፍ ዛሬም ቢሆን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጥገኝነት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው የግብርና ምርት ውጤት የተለየ ሆኖ አይታይም። በኤክስፖርቱ ዘርፍ ዛሬም የ80 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ከተባሉት የግብርና የምርት ውጤቶች ባሻገር በፕሬዝዳንቱ ገለፃ መሰረት የማዕዱኑና የማኑፋክቸሪጉ ዘርፍ ኤክስፖርት ገቢን በተመለከተ “ከዚህ በተጓዳኝ” የሚል አገላለፅን በመጠቀም አሁንም ቢሆን ማኑፋክቸሪጉ ዘርፍ በኢትዮጵያ የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ የጎላ ሚና የማይኖረው መሆኑን በግልፅ አመላክተዋል።

 ይሄንኑ ጉዳይ በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ከዚህ በተጓዳኝ በማዕድን ዘርፍ ወርቅና ሌሎች ጌጣጌጥ ማዕድናት እንዲሁም እየተስፋፉ የመጡትን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማዕከል በማድረግ የማኑፋክቸሪግ ምርቶች ኤክስፖርት በፍጥነት እንዲያድግ በማድረግ ላይ ይሆናል።በማለት አስቀምጠውታል። የኤክስፖርቱ መውደቅ የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን እየተዛባ እንዲሄድ ከማድረግ ባሻገር በውጭ እዳ ክፍያ ላይ ብሎም በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰው ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ በሚሰበስቡ ባለሀብቶች ገቢ ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው። ይህም በሀገሪቱ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖም በሌላ አቅጣጫ ሊታይ የሚችል ተግዳሮት ነው። አንድ የውጭ ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ፤ መነሻ ኢንቨስትመንቱን እንዲያካሂድ የሚፈቀድለት በብር ሳይሆን በውጭ ምንዛሬ ነው። ይህም በዶላር፣ በፓውንድ፣ በዩሮና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ አይነቶች ሊሆን ይችላል።

 

ባለሀብቱ ኢንቨስትመንቱን በውጭ ምንዛሪ ካፈሰሰ በኋላ አምርቶ ወደ ገበያ በመግባት የሚያገኘውን ገቢ በውጭ ምንዛሪ መንዝሮ ትርፉን የመውሰድ መብቱ የተጠበቀና ዓለም አቀፋዊ የኢንቬስትመንትና የንግድ አሰራር ነው። ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ያለ የኤክስፖርት ገቢው እጅግ አነስተኛ የሆነ ሀገር ለውጭ ባለሀብቶች የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ የትርፍ ገቢ ድርሻ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ባለሀብቶች ሀገሪቱን ለመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ተመራጭ የማድረጋቸው እድል የእምቅ ሀብታቸውን ያህል አይደለም። በመሆኑም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተመራጭ የሚሆኑት መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰው ምርቶቻቸውን ሀገር ውስጥ በመሸጥ የገቢ ትርፍን ከመንግስት የውጭ ምንዛሪ ካዝና የሚሰበስቡት ባለሀብቶች ሳይሆኑ፤ አምርተው ወደ ውጪ በመላክ ለራሳቸው ብሎም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የውጭ ባለሀብቶች ናቸው።

 ይህ ካልሆነ ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ስራ (Import Substitution) ላይ የተሰማሩ ባለሀበቶች የግድ የሚያስፈልጉ ይሆናል። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ችግር ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው። ኤክስፖርት ለማድረግ የመንግስት ማበረታቻ ከተጠቀሙ በኋላ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች በርካቶች መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

 

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያለተቀናጀ ሥራ በክፍተትነት በመጠቀምና በጥቅም ትስስር ኤክስፖርት ካደረጉም በኋላ ቢሆን ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሀገር ውስጥ የማያስገቡ መኖራቸውንም ቀደም ያለው የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት ያመለክታል። የኤክስፖርት ምርቶች የጥራት ችግርና ምርቶቹን ወደ ውጪ በመላኩ ሂደት ያለው የሎጂስቲክ ችግርም ሌላኛው ፈተና ነው። የኤክስፖርቱን ዘርፍ ይታደጋሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው እንደ ስኳር ያሉ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች እንኳን ዘርፉን መታደግ ይቅርና የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎት እንኳን እንዲሸፈን ማድረግ ባለመቻላቸው ሀገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሪ የስኳር ምርትን ከውጭ ለማስገባት ተገዳለች።

 

የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርተቶች እሴት ሳይጨመርባቸው እንደዚሁ የሚላኩ በመሆናቸው በዓለም አቀፉ ገበያ ያላቸው ዋጋም እጅግ አነስተኛ ነው። ቡናው ከመታጠብ ያለፈ ተጨማሪ እሴት ሳይጨመርበት፣ ሰሊጥ ሳይፈተግ፣ የማዕድን ምርቶች ወደ ተፈላጊው የጌጣጌጥ ምርትነት ሳይለወጡ እንዲሁ ባሉበት ደረጃ ለኤክስፖርት ገበያ ይቀርባሉ። በፕሬዝዳንቱ ንግግር መሰረት በዚህ ዓመት የቁም ከብት የመላኩ ሥራ ሳይቀር ይቀጥላል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት በጥሬ ምርች የገጠመውን ዓለም አቀፍ ዋጋ መውደቅ ለመከላከል ምርጫው ያደረገው እሴትን በመጨመር ምርቶቹን ተወዳዳሪና ተፈላጊ ማድረግ ሳይሆን፤ የኤክስፖርት ምርት መጠንን (Export Volume) ከፍ ማድረጉ ላይ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
250 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 960 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us