“የኢትዮጵያከፍተኛትምህርትተቋማትየራሳቸውንገቢማመንጨትመቻልአለባቸው”

Wednesday, 08 November 2017 18:58

 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት መቻል አለባቸው

ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተስፋዬ ተሾመ


አድማስ ዩኒቨርስቲ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም አስራ አንደኛውን የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በፍሬንድሺፕ ሆቴል አካሂዷል። በዚህ ኮንፍረንስ ላይ በርካታ ምሁራን ተገኝተዋል፤ የተለያዩ የጥናት ወረቀቶችም ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።


የቀረቡት ጥናቶች ዋነኛ መሽከርከሪያ ነጥብ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ጉዳይን በብዙ አቅጣጫ የሚዳስስ ነበር። በዚሁ ዙሪያ ጥናታቸውን ካቀረቡት ምሁራን መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተስፋዬ ተሾመ ይገኙበታል። ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተስፋየ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ስትራቴጂክ ፕላን ኤንድ ዴቨሎፕመንት MBA ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።


ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተሾመ በዕለቱ ያቀረቡት ጥናት Higher Education Quality Assurance in Ethiopia Challenges and Prosepects በሚል ርዕስ የተቃኘ ነበር። ጥናቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራትን በማምጣት ረገድ ሊሰሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ዳሷል።
ያለውን ውስን ሀብትና የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎትንም በአሀዝ አስደግፎ አሳይቷል። በተለይ ከሀገሪቱ የህዝብ እድገት ጋር በተያያዘ የሚኖረው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቁጥር እድገት ከፍተኛ እንደሚሆን በዚሁ ጥናት ተመልክቷል። እንደ ጥናቱ ከሆነ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020 በቅድመ ምረቃና በምርቃ ፕሮግራም የሚኖረው የተማሪ ቁጥር አሁን ካለበት 12 ነጥብ 54 በመቶ ወደ 15 በመቶ ያድጋል።


በዚህ ደረጃ የተማሪዎች ቁጥር መጨመር ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር መልካም መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ ይሁንና ከትምህርት ጥራት አንፃር ሲታይ ግን ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው የተማረ የሰው ኃይል አኳያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማል። እኛም በዚሁ ዙሪያ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተስፋዬ ተሾመ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

  

 

ሰንደቅቀደም ሲል በመድረኩ ላይ ሲያነሷቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንደኛው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጀት የሚመድበው አካል፣ ቀጣይ በጀትን ለመመደብ በትምህርት ተቋሙ ላይ የጥራት ኦዲቲንግ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ቀጣዩ የበጀት ሁኔታም ከዚሁ የኦዲት ውጤት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ አሰራር አሁን ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራር አኳያ እንዴት ይታያል።

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ- እኔ መድረኩ ላይ የገለፅኩት የስኮትላድን አሰራር በምሳሌነት በመውሰድ ነው። የስኮትላንድ ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርስቲዎች በጀት ከመልቀቁ በፊት በየጊዜው የጥራት ኦዲቲንግ እንዲሰራ ያደርጋል። ኦዲት ከተካሄደ በኋላ የሚገኘው ውጤት የበጀቱን ሁኔታ ይወስነዋል። በዚህ ኦዲቲንግ ችግር የተገኘበት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዚው ቅፅበት እርምጃ እንዲወሰድበት አይደረግም። ሆኖም ያለበት ችግር በጥናት ተለይቶ ከችግሮቹ እንዲወጣ የእፎይታ ጊዜ (Grace Period) ይሰጠዋል። በዚህ መልኩ ጥራትንና በጀትን አያይዘው ይሰራሉ፤ እንጂ እንዲሁ ዝም ብሎ በጀት አይለቀቅም።

 

ይሄንን ጉዳይ ወደኛ ሀገር ስታመጣው በእርግጥ ተቋማዊ የጥራት ምርመራ ይካሄዳል። ሆኖም የጥራት ኦዲቲጉን ተከትሎ የሚወሰድ እርምጃ ወይንም የአሰራር ለውጥ የለም። ሁሉም በተለመደው አካሄድ ነው የሚሄደው። ጥራትን ከበጀት ጋር አያይዞ የመስራቱ ጉዳይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ስላለው ሊሰራበት ይገባል እላለሁ።

 

ሰንደቅ- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች  ከሚመደቡ ወይንም ከሚሾሙ ይልቅ በሙያዊና ችሎታ ተገቢነት (Merit) ቢሆን ለትምህርቱ ጥራት የተሻለ እንደሚሆን ሲመለከትም ነበር። ይህ ጉዳይ በምን መልኩ ሊሆን ይችላል?

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ- አንድ ነገር ጥራት የሚኖረው በተገቢው ባለሙያ ሲሰራ ነው። በዚህ ጉዳይ የቀደመውን አሰራር ለመለወጥ በትምህርት ሚኒስቴር እየተሰራበት ነው። አንድ ሰው የዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ኃላፊ ሆኖ ሲሾም ታርጌት ተቆጥሮ ሊሰጠው ይገባል። ፕሬዝዳንቱም ቢሆን በዚያ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ያንን ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እሱ ሲረከበው ከነበረበት ሁኔታ የት የት እንዲያደርሰው ነው? ግልፅ የሆነ ኃላፊነት የተሰጠው። ይህ ግልፅ የሆነ በጊዜ ገደብ የተቀመጠ ኃላፊነት ተቀምጦና ለዚህም የሚያስፈልገው በቂ ሀብት ከተመደበ በኋላ በስተመጨረሻ ሂደቱና ውጤቱ ይለካል። ስራው የሚሰራው በዚህ መልኩ ነው።

 

ሰንደቅ- ጥራት ከገንዘብ ጋር እንደሚገናኝ በጥናትዎ ማብራሪያ ላይ ሲያመለክቱ ነበር። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግስት የሚመድበው ገንዘብ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሆኖም ይህ ገንዘብ በትምህርት ጥራቱ ላይ ሳይሆን ትምህርት ማዳረሱ ላይ ትኩረት በመደረጉ በአብዛኛው እየዋለ ያለው ለተቋማቱ መሰረተ ልማት ግንባታ ነው። ከዚህ አንፃር ገንዘቡና ጥራቱ በምን መልኩ ሊገናኝ ይችላል?

ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ- እርግጥ ነው እስከዛሬ ድረስ ትምህርትን ለህዝቡ ለማዳረስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በሰፊው ሲሰራ ቆይቷል። ይህ ተገቢ ነው። የህዝባችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በፍጥነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። የህዝባችንን ቁጥር የሚመጥኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር መኖር የግድ ነው።

 

 ሆኖም ሁልጊዜ መሰረተ ልማት በመገንባትና ህንፃ በመስራት አንቀጥልም። ጥራት ላይ መምጣት አለብን። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ሲናገሩ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመደብላቸውን በጀት ስቴዲየም ሳይቀር እየገነቡበት መሆኑን አመልክተዋል።

 

 እሳቸው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚመደበው በጀት ለምርምርና  ለትምህርት ጥራቱ ማረጋገጫነት መዋል የሚገባው መሆኑን ሲገልፁ ሰምቻለሁ። ይሄንን ሀሳብ እደግፋለሁ። በነገራችን ላይ በውጭ ሀገራት ያሉ በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የገቢ ማገኛ ዘዴዎች የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታም አለ። የእኛ ሀገራት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ ወደዚህ አቅጣጫ ነው ማምራት ያለባቸው።  መንግስት ካለው ውስን ሀብት እነዚህን ተቋማት በጀት እየመደበ ሊቀጥል አይገባውም።

 

ሰንደቅ- ተቋማቱ የራሳቸውን ገቢ ያመንጩ ሲባል በምን መልኩ ነው?

ረዳትፕሮፌሰርተስፋዬ- ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የየራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ይህ አለም አቀፍ አሰራር ነው። የየራሳቸውን ገቢዎች ከሚያመነጩባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ጥናትና ምርምርን ማካሄድ፤ እንደዚሁም የማታ ትምህርትን አስፋፍቶ በመስጠትም ጭምር ነው። በተቋማቱ የሚሰሩትን የቴክኖሎጂ ስራዎችን ለህዝብ በማቅረብም የራስን ገቢ ማመንጨት ይቻላል። አሁን ያለው በጀትን ጠብቆ የማደሩ ሂደት መቀየር መቻል አለበት። በሀገሪቱ በጀት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።

 መንግስት ከዚህ በኋላ መስራት ያለበት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በምን መልኩ የየራሳቸውን ገቢ እያመነጩ መሄድ እንዳለባቸው ነው። ተቋማቱ በተወሰነ ደረጃ የየራሳቸውን ወጪ እየሸፈኑ ሲሄዱ በመንግስት በጀት ላይ የሚያሳድረውን ጫና እየቀነሰ ስለሚሄድ ሀብቱ ለሌላ ልማትም የሚውልበት ብሎም በጥራት ላይ ትኩረት የሚሰጥበት እድል ይኖራል ማለት ነው። ይህ አሜሪካን ጨምሮ በብዙ ሀገራት ያለ አሰራር ነው።¾

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
124 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us